የአባ ሙሴ ጸሊም ዕረፍት

አባ ሙሴ ጸሊም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ሰኔ ፳፫ ቀን ፳፻፱ .

ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከልዩ ልዩ ዓለማዊ ሥራ ጠርቶ ቃሉን ለመስበክ፣ ስሙን ለመቀደስ እና ክብሩን ለመውረስ ያበቃቸው ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው፡፡ በዛሬው ዝግጅታችን በኃጢአት ሕይወት ከኖሩ በኋላ በንስሓ ተመልሰው ለመንግሥተ ሰማያት ከተጠሩ ጻድቃን መካከል አንዱ የኾኑትን የአባ ሙሴ ጸሊምን የዕረፍት ታሪክ በአጭሩ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፤

የአባ ሙሴ ጸሊም (ጥቁሩ ሙሴ) በዓለ ዕረፍት በየዓመቱ ሰኔ ፳፬ ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ይከበራል፡፡ አባ ሙሴ ቆዳቸው ጥቁር በመኾኑ ‹ጸሊም› (ጥቁር) በሚል ቅጽል ስም ይጠራሉ፡፡ እኒህ ቅዱስ ለሰማዕትነት ክብር ከመብቃታቸው በፊት በቆዳቸው ብቻ ሳይኾን በግብራቸውም የጠቆሩ ማለትም ኀጢአትን የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ያለ መጠን ይበሉ፣ ይጠጡ፣ ይቀሙ፣ ያመነዝሩ እንደዚሁም ሰው ይገድሉ ነበር፡፡ በሥጋቸው ጠንካራ፣ በጕልበታቸውም ኃይለኛ ከመኾናቸው የተነሣም ሊቋቋማቸው የሚችል ማንም እንዳልነበረ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡ እግዚአብሔርን ካለማወቃቸው የተነሣ በባዕድ አምልኮ ተይዘው የኖሩት አባ ሙሴ ጸሊም ፀሐይን ለሚያመልኩ ሰዎች አገልጋይም ነበሩ፡፡

በዚህ ዓይነት ሰይጣናዊ ሥራ ከኖሩ ከዓመታት በኋላ የሰውን ልጅ ጠፍቶ መቅረት የማይወደው አምላከ ቅዱሳን እግዚአብሔር ወደ ቤቱ መልሶ አምላክነቱን ለመመስከር፣ ስሙን ለመቀደስ፣ መንግሥቱንም ለመውረስ መርጧቸዋልና የፀሐይን ፍጡርነት፣ ግዑዝነት ገለጸላቸው፡፡ ስለዚህም ብዙ ጊዜ ወደ ፀሐይ በማንጋጠጥ ‹‹ፀሐይ ሆይ አንተ አምላክ ከሆንኽ አነጋግረኝ … የማላውቅህ ሆይ ራስህን አሳውቀኝ›› እያሉ ይመራመሩ ጀመር፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም፣ የገዳመ አስቄጥስ መነኮሳት እግዚአብሔርን ያውቁታል፤ ያዩታል፤ እንደዚሁም ያነጋግሩታል እየተባለ ሲነገር ይሰሙ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ወደ ገዳሙ ይሔዱ ዘንድ አነሣሣቸው፡፡ ወደ አስቄጥስ ገዳም ሔደዉም ከካህናቱ አንዱ የኾኑትን አባ ኤስድሮስን ‹‹እውነተኛውን አምላክ ታሳውቁኝና ታስረዱኝ ዘንድ ወደ እናንተ መጥቻለሁ›› አሏቸው፡፡ እርሳቸውም እግዚአብሔርን ፍለጋ ወደ ገዳሙ መምጣታቸውን አድንቀው ከአባ መቃርስ ጋር አገናኟቸው፡፡ አባ መቃርስም የክርስትና ሃይማኖትን አስተምረው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቀው ‹‹ታግሠህ የማስተምርህን ትምህርተ ወንጌል ከጠበክ እግዚአብሔርን ታየዋለህ›› እያሉ በተስፋ ቃል እያጽናኗቸው ቆዩ፡፡ ከዓመታት በኋላም በልዩ ልዩ ዓይነት ፈተና ፈትነው አመነኮሷቸው፡፡

አባ ሙሴ ጸሊም ብዙ ገድልን ከሚጋደሉ ቅዱሳን አብልጠው መጋደል በጀመሩ ጊዜም ሰይጣን ለማሰናከልና ከገዳሙ ለማስወጣት በማሰብ ቀድሞ ያሠራቸው በነበረው ግብረ ኃጢአት ሊዋጋቸው ጀመረ፡፡ አባ ኤስድሮስም እያጽናኑ፣ እየመከሩ በተጋድሏቸው ይበልጥ እንዲጸኑ ያተጓቸው ነበር፡፡ የመነኮሳቱ የውኃ መቅጃ ሥፍራ ሩቅ ነበርና አረጋውያን መነኮሳት በመንገድ ብዛት እንዳይደክሙ አባ ሙሴ ዘወትር ውኃ እየቀዱ በየበዓታቸው ደጃፍ ያስቀምጡላቸው ነበር፡፡ እንዲህ እያደረጉ በመጋደልና በማገልገል ላይ ሳሉ ጸላዔ ሠናያት ሰይጣን እግራቸውን በከባድ ደዌ መታቸውና ለብዙ ቀናት የአልጋ ቁራኛ ኾነው ኖሩ፡፡ እርሳቸውም በደዌ የሚፈታተናቸው ጥንተ ጠላት ሰይጣን መኾኑን ተረድተው ሰውነታቸው ደርቆ በእሳት የተቃጠለ እንጨት እስኪመስል ድረስ ተጋድሏቸውን እጅግ አበዙ፡፡ እግዚአብሔርም ትዕግሥታቸውን ዓይቶ ከደዌያቸው ፈወሳቸው፤ የሰይጣንን ውጊያ አርቆ ጸጋውን አሳደረባቸው፡፡

አባ ሙሴ፣ እርሳቸው ወደሚኖሩበት ገዳም የተሰበሰቡ ፭፻ የሚኾኑ ወንድሞች መነኮሳትን በአበ ምኔትነት እያስተዳደሩ ሳሉ ‹‹በመልካም ለሚያገለግሉት ከፍተኛውን ሹመት ይስጧቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን ብዙ ባለሟልነት አለና›› (፩ኛጢሞ.፫፥፲፫) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረው፣ ከተጋድሏቸውና ከትሕትናቸው አኳያ ማኅበረ መነኮሳቱ ለቅስና መዓርግ መረጧቸው፡፡ ሥርዓተ ክህነት ሊፈጽሙላቸው ወደ ቤተ መቅደስ በአቀረቧቸው ጊዜም ሊቀ ጳጳሳቱ ‹‹ይህን ጠቋራ ለምን አመጣችሁት? ከዚህ አውጡት›› ብለው አረጋውያኑን ተቆጧቸው፡፡ አባ ሙሴ ይህን ቃል ከሊቀ ጳጳሳቱ በሰሙ ጊዜም ‹‹መልክህ የከፋ ጠቋራ ሆይ! መልካም አደረጉብህ›› እያሉ ራሳቸውን በመገሠፅ ከቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ጽናታቸውንና ትዕግሥታቸውን የተመለከቱት ሊቀ ጳጳሳቱም በሌላ ቀን አባ ሙሴን አስጠርተው በአንብሮተ እድ በቅስና መዓርግ ሾሟቸው፡፡ ከዚያም ‹‹ሙሴ ሆይ! እነሆ በውስጥም በውጪም ዅለመናህ ነጭ ኾነ›› ብለው በደስታ ቃል አናገሯቸው፡፡ ሙሴም በተቀበሉት መዓርግ እግዚአብሔርን፣ መነኮሳቱንና ገዳሙን በትጋት ሲያገለግሉ ኖሩ፡፡

እግዚአብሔር በአባ ሙሴ ላይ አድሮ ከአደረጋቸው ተአምራት መካከል ያለ ወቅቱ ዝናብ እንዲዘንብ ማድረጋቸው አንደኛው ነው፤ ከዕለታት አንድ ቀን በበዓታቸው ምንም ውኃ በሌለበት ቀን አረጋውያን በእንግድነት መጡባቸው፡፡ ውኃ የሚቀዳበት ቦታ በጣም ሩቅ ነበርና አባ ሙሴ የሚያደርጉትን አጡ፡፡ እንግዶቹን ወደ በዓታቸው ካስገቡ በኋላም ከመነኮሳቱ ተለይተው ‹‹ውኃ ካልሰጠኸኝ ቅዱሳን አገልጋዮችህን ምን አጠጣቸዋለሁ?›› እያሉ እግዚአብሔርን በጸሎት ይጠይቁት ጀመሩ፡፡ እርሱም በስሙ ለሚታመኑ ድንቅ ሥራውን መግለጥ ልማዱ ነውና ጸሎታቸውን ሰምቶ ዝናብ አዝንቦ የውኃ ጉድጓዶችን ሞላላቸው፡፡ እንግዶቹንም እንደ ሥርዓቱ እግራቸውን አጥበው፣ ምግብና ውኃ ሰጥተው አስተናገዷቸው፡፡ አረጋውያኑ በዝናቡ መጣል እየተገረሙ አባ ሙሴን ‹‹ብዙ ጊዜ ትወጣ፣ ትገባ የነበረው ለምንድን ነው?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም ‹‹እግዚአብሔርን ውኃ እንዲሰጠኝ እየተማጸንኹት ነበር፡፡ በቸርነቱም ዝናምን ልኮልን ውኃን አገኘን›› አሏቸው፡፡ በዚህ ጊዜ በቅዱሳኑ ላይ አድሮ ድንቅ ድንቅ ተአምራቱን የሚገልጠውን እግዚአብሔርን አመሰገኑት፤ በአባ ሙሴ ቅድስናም ተደነቁ፡፡

በአንዲት ዕለት አባ ሙሴ ከአረጋውያን ጋር ወደ አባ መቃርስ ገዳም በሔዱ ጊዜ አባ መቃርስ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጾላቸው ‹‹ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ›› በማለት ለአባ ሙሴ ጸሊም ስለ ተዘገጀው የሰማዕትነት ክብር አስቀድመው ትንቢት ተናገሩ፡፡ አባ ሙሴም ይህን ቃል ሲሰሙ ‹‹አባቴ ሆይ እኔ እኾናለሁ፡፡በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው› የሚል ጽሑፍ አለና›› ብለው መለሱ፡፡ በብሉይ ኪዳን ‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይሙት፤ ዓይን ያጠፋ ዓይኑ ይጥፋ›› የሚል አንድ ሰው በሠራው ወንጀል መጠን እንዲቀጣ የሚያስገድድ ሕግ ነበር (ዘፀ. ፳፩፥፳፬-፳፭፤ ማቴ. ፭፥፴፰)፡፡ አባ ሙሴ ጸሊም ለገዳማዊ ሕይወት ከመብቃታቸው በፊት ሰዎችን በሰይፍ ሲያጠፉ እንደ ነበሩት ዅሉ እርሳቸውም በሰይፍ ለመሞት መዘጋጀታቸውን ሲገልጹ ‹‹አባቴ ሆይ እኔ እኾናለሁ፡፡በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደል ዘንድ አለው› የሚል ጽሑፍ አለና›› ብለዋል፡፡ ይህም በንጹሕ ልቡናቸው ወደ እግዚአብሔር መመለሳቸውን የሚያመለክት ንግግር ነው፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ያገኙትን ዅሉ በሰይፍ የሚገድሉ የበርበር ሰዎች ወደ በዓታቸው መጡ፡፡ አባ ሙሴም አብረዋቸው የነበሩትን መነኮሳት ‹‹መሸሽ የሚፈልግ ይሽሽ›› አሏቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አባታችን አንተስ አትሸሽምን?›› ብለው ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም እኔ ‹‹‹በሰይፍ የገደለ በሰይፍ ይገደላልስለሚለው የእግዚአብሔር ቃል እነሆ ይቺን ቀን ለብዙ ዘመናት ስጠባበቃት ኖሬአለሁ›› በማለት ለሰማዕትነት መዘጋጀታቸውን ነገሯቸው፡፡ ይህን ቃል እየተነጋገሩ ሳሉም የበርበር ሰዎች ከበዓታቸው ገብተው በሰይፍ ቈርጠው ገደሏቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋርም ሰባት መነኮሳት በሰማዕትነት ሞቱ፡፡ አንደኛውም ከምንጣፍ ውስጥ ተሠውረው ከቆዩ በኋላ በእጁ አክሊል የያዘ የእግዚአብሔር መልአክ ቆሞ ሲጠባበቅ በተመለከቱ ጊዜ ከተሠወሩበት በመውጣት የሰማዕትነትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አባ መቃርስ ‹‹ከእናንተ ውስጥ የሰማዕትነት ክብር ያለው አንድ ሰው አያለሁ›› በማለት የተናገሩት ትንቢት ደረሰ፡፡ ‹‹አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው›› ሲል ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ኃይለ ቃልም በአባ ሙሴ ተጋድሎ ተፈጸመ  (ሮሜ. ፰፥፴)፡፡ የአባ ሙሴ ጸሊም ሥጋም በአስቄጥስ ገዳም ደርምስ በተባለ ቦታ እንደሚገኝ፤ ከእርሱም ብዙ ድንቆችና ተአምራት እንደሚታዩ በመጽሐፈ ስንክሳር ተገልጿል፡፡

‹‹እስከ ዛሬ ድረስ መንግሥተ ሰማያት ትገፋለች፤ ግፈኞችም ይናጠቋታል›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ማቴ.፲፩፥፲፪/፣ አባ ሙሴ ጸሊም አስቀድሞ መንግሥተ ሰማያትን ገፍተዋታል፤ ማለትም የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያወርሰውን የጽድቅ ሥራ ትተው ወደ ገሃነም በሚያስጥል ኃጢአት ኖረዋል፡፡ በኋላ ግን እግዚአብሔርን ፈልገው ከማግኘታቸው ባሻገር በመንፈሳዊ ተጋድሎ በመበርታት ለክህነት እና ለቅድስና በቅተው ምድራዊ ሕይወታቸውን በሰማዕትነት አጠናቀዋል፡፡ በክህደት፣ በኑፋቄ እንደዚሁም በኀጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር እቅፍ ርቀን የምንኖር ክርስቲያኖችም ከሃዲ፣ ሰውን ገዳይ፣ ቀማኛ፣ ዘማዊ የነበረውን ሰው ወደ አሚነ እግዚአብሔር እና ወደ ገቢረ ጽድቅ በመለወጥ ደግ አባት፣ መምህር፣ የሚያጽና እና ሥርዓትን የሚሠራ ካህን፣ እንደዚሁም ሰማዕት ለመኾን ያበቃችውን፤ በተጨማሪም በዅሉም አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ስሙ ለዘለዓለሙ እንዲጠራ ያደረገችውን የንስሓን ኃይል በማስተዋል ዛሬዉኑ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፡፡ ኀጢአታችንን ይቅር ይለን ዘንድም ዘወትር እንማጸነው፡፡ እግዚአብሔር እስከ ሺሕ ትውልድ ድረስ ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን፣ ኀጢአትንም ይቅር የሚል አምላክ ነውና (ዘፀ. ፴፬፥፯፤ ማቴ. ፮፥፲፪)፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን! እኛንም በአባ ሙሴ ጸሊምና በሰማዕታት ዅሉ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከታቸውም ከእኛ ጋር ትኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ምንጭ፡መጽሐፈ ስንክሳር፣ ሰኔ ፳፬ ቀን፡፡