አስደናቂው የድንግል ማርያም ሞት

%e1%88%9e%e1%89%b3-%e1%88%88%e1%88%9b%e1%88%ad%e1%8b%ab%e1%88%9d

በዲያቆን ታደለ ፋንታው

ጥር ፳ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን ፍጥረቱንና ዓለሙን ለማዳን የመረጠው ጊዜ በደረሰ ጊዜ አስቀድሞ በመልአኩ አፍ እንዳናገረ ከድንግል ማርያም በድንግልና ተወለደ፤ ክብሩም በእርሷ ላይ ተገለጠ /ኢሳ.፷፥፪/፡፡ ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርስዋ አደረ፡፡ ይህም ያነጻቸው፣ ይቀድሳቸው ዘንድ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ በነቢያት በሐዋርያት ላይ እንዳደረው ዓይነት ማደር አይደለም፤ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሥጋዋ ሥጋን፤ ከነፍስዋ ነፍስን ተዋሕዶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ኾነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል፡፡ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፤›› በማለት ገልጾታል /ሉቃ.፩፥፵፭/፡፡

በእግዚአብሔር፣ በመላእክቱና በሰው ፊት የከበረ ሰው መታሰቢያው ለዘለዓለም ነው፡፡ በቤቱ፣ በቅፅሩ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምን ይቀበላልና /ኢሳ.፶፭፥፫/፡፡ ይህንን ታላቅ በረከት እንደሚሰጣቸው የተናገረውም የማይዋሸው እግዚአብሔር አምላክ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ወልድ እናት ከድንግል ማርያም የበለጠ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ማንን ልንጠራ እንችላለን? ከእርሷ ሊከብር የሚችል፣ በቅድስና ሕይወት ያለፈ ማን ይኖራል? እግዚአብሔር አምላክ ዘለዓለማዊ ኃይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸባቸው ሥራዎቹ መካከል በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ላይ የገለጸው ተዋሕዶ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡

ይህንን ኹኔታም ‹‹ብርቱ የኾነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል፤ ስለዚህም ምክንያት ፍጥረት ዅሉ ያመሰግኑኛል፤›› በማለት ድንግል ማርያም ገልጻዋለች /ሉቃ.፩፥፵፱/፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታችንን ‹‹ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ፤›› ብሏታል /ሉቃ.፩፥፳፰/፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹የጌታዬ እናት›› ብላታለች /ሉቃ.፩፥፵፫/፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ልጄ›› ይላታል /መዝ.፵፬፥፱/፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞንም ‹‹እኅቴ›› ይላታል /መኃ.፭፥፩/፡፡ ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም እናት ኾና ተሰጥታዋለች /ዮሐ.፲፱፥፳፮/፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደ ገለጸው የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷ እና የማይሞተው ጌታ ሞት እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ‹‹እነዚህ ድንቅ ምሥጢራት በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች ዅሉ በላይ ኾነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጐናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው፤›› ይላል ቅዱስ አግናጥዮስ፡፡

ምስጋናዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ‹‹አቤቱ መሰንቆ ልቡናዬን አነቃቃ፤ የልቤንም እንዚራ፡፡ ድምፁን ከፍ አድርጎ የዳዊት ልጅ የኾነችውን የጌታውን እናት ድንግል ማርያምን ያመሰግናት ዘንድ፡፡ ለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን የወለደች እናቱ የኾነች እርሷን ከፍ ከፍ ያደርጋት ዘንድ፤›› በማለት ለምስጋናዋ ይዘጋጃል፡፡ በሌላ አንቀጽም ‹‹ከሕሊናት ዅሉ በላይ ለኾነ ለዚህ ነገር አንክሮ ይገባል፤ ምድራዊት ሴት ፈጣሪዋን ወለደችው፡፡ እርሱም እናቱን ፈጠረ፤›› ይላል፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫም በመጽሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ‹‹ከሚያሰጥመው ባሕር ሞገድ የተነሣ የማትነቀነቅ፤ መልኅቆቿም በሦስቱ ሥላሴ ገመድ የተሸረቡ ናቸው፡፡ ይህቺ ደግሞ ከነፋሳት ኃይል የተነሣ የማትናወጥ በጭንጫ ላይ ያለች የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ ናት፡፡ እርሷን የተጠጋ መውደቅ፣ መሰናከል የለበትም፤›› የሚላት እመቤታችን ሞት ሥጋ ለለበሱ ዅሉ አይቀርምና እርሷም እንደ ሰው የምትሞትበት ጊዜ ደረሰ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ ከልጇ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር፤ ከጌታችን ስቅለት በኋላ ደግሞ ዐሥራ አምስት ዓመታት በምድር ኖራለች፡፡ ጌታን የፀነሰችበትን ወራት ስንጨምር በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይኾናል፡፡ ያረፈችውም ጥር ፳፩ ቀን ነው፡፡ እመቤታችን ባረፈች ጊዜ ሐዋርያት ሊቀብሯት ሲሹም ከአይሁድ ክፋት የተነሣ ልጇ ሌላ ክብርን ደረበላት፡፡ ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ፲፮ ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች፡፡

ልጇ ወዳጇ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ ዅሉ እርሷንም በእርሱ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አድርጓታል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም የኃያሉ እግዚአብሔር እናቱ፣ መቅደሱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ኾና እያለ ሞትን መቅመሷ በራሱ የሚያስገርም ምሥጢር ነው፡፡ ከቤተ ክርስትያን ወገን ሞትን እንዳያዩ የተወሰዱ ቅዱሳን ሄኖክ፣ ኤልያስ፣ ሌሎችም አበው እንዳሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ይናገራሉ፡፡

ይህ ከሕሊናት ዅሉ በላይ የኾነው የእመቤታችን ዕረፍት ርቀቱ በመጽሐፈ ዚቅ እንዲህ ተብሏል፤ ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ  ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐፅብ ለኵሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላደላም፤ ሞትስ ለሟች ይገባዋል፡፡ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው፡፡››

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደ ኾነ ያስረዳል፤ የመጀመሪያው ‹‹ለመለኮት ማደርያ ለመኾን የበቃችው ኃይል አርያማዊት ብትኾን ነው እንጂ እንደ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን አምላክ ልትሸከመው ይቻላታል?›› የሚሉ ወገኖች ነበሩና እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያስረዳ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፡፡ በሕይወታቸው ዅሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ዅሉ ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም፤›› አለ /ዕብ.፪፥፲፬-፲፭/፡፡ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መኾኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛውም ቅዱስ ያሬድ እንደ ተናገረው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት አምላክ መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ዅሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነዪ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› /መኃ.፪፥፲-፲፬/ በማለት የተናገረው ትንቢት እመቤታችን የዚህ ዓለም ድካሟ ዅሉ መፈጸሙን ያስረዳል፡፡ ልጇን ይዛ ከአገር ወደ አገር በረሀብና ጥም የተንከራተተችበት ጊዜ አሁን አለፈ፡፡ ታናሽ ብላቴና ሳለች ልጇን አዝላ በግብጽ በረሃ የተቀበለችው መከራ ዅሉ ፍጻሜ አገኘ፡፡

ከእግረ መስቀል ሥር ወድቃ የልጇን የቈሰለ ገላ እየተመለከተች የደረሰባት ልብ የሚሰነጥቅ ኀዘን ወደ ደስታ ተለወጠ፡፡ ልጇ ሲንገላታ፣ ሲሰደድ፣ ሲገረፍ፣ ሲሰቀል፣ ሲቸነከር ያየችበት ዓለም አለፈ፡፡ ‹‹በነፍሷ ሰይፍ ያልፋል›› ተብሎ የተነገረው ልብ የሚሰነጥቅ መከራ የሚቀጥልበት ጊዜ ተፈጸመ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና፤›› ሲል የተነጋረውም ይህንኑ ምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡

እመቤታችን አሁን የልጇን ልዕልና ከሚያደንቁ ጋር ታደንቃለች፤ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት ጋር ታከብረዋለች፡፡ ይኸውም ከገቡ የማይወጡበት፤ ኀዘን፣ መከራ፣ ችግር የሌለበት ሰማያዊ አገር ነው፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ስደት፣ መከራ፣ ኀዘን፣ ሰቆቃ፣ መገፋት፣ መግፋትም የለም፡፡ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው የድል አክሊልን የሚቀዳጁበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚህም ከፍጡራን ኹሉ ከፍ ባለ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘለዓለም እንደምትኖር እናምናለን፡፡ ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ፍቅሯ፣ አማላጅነቷ፣ የልጇም ቸርነት በኹላችን ላይ አድሮ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዘመነ አስተርእዮ

በርእሰ ደብር ብርሃኑ አካል

ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፱ .

አስተርእዮ ቃሉ የግእዝ ቃል ሲኾን መታየት መገለጥ ማለት ነው፡፡ ገሃድ የሚለው ቃልም በጾምነቱ ሌላ ትንታኔ ሲኖረው ትርጕሙ ያው መገለጥ ማለት ነው፡፡ በግሪክ ‹‹ኤጲፋኒ›› ይሉታል፡፡ የእኛም ሊቃውንት ቃሉን በቀጥታ በመውሰድ ‹‹ኤጲፋኒያ›› እያሉ በዜማ መጻሕፍቶቻቸው ይጠሩታል፡፡ ትርጕሙም ከላይ ከጠቀስናቸው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አስተርእዮ የሚለው ቃል ‹‹አስተርአየ›› ከሚለው ግሥ ራሱን ችሎ ሳይለወጥ በአምስቱ አዕማድ የሚፈታ ብቸኛ ግሥ ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አስተርአየ፤ ታየ፤ ተያየ፤ አሳየ፤ አስተያየ፤ አየ ተብሎ ይፈታል ማለት ነው፡፡

ዘመነ አስተርእዮ ሲያጥር ከጥር ፲፩ ቀን እስከ ጥር ፴፤ ሲረዝም ደግሞ ከጥር ፲፩ ቀን እስከ መጋቢት ፫ ቀን ይኾናል፡፡ በዚህም መሠረት ቀናቱ ሲያጥር ፳፤ ሲረዝም ፶፫ ይኾናሉ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ለሐዋርያት ሕጽበተ እግር ካደረገበት ቀን (ከጸሎተ ሐሙስ) እስከ ጰራቅሊጦስ ቢቈጠር ቀናቱ ፶፫ ስለሚኾኑ የእነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስ በጥምቀት ዕለት ለልዕልና (ጌታ ሰውን ምን ያህል እንዳከበረው) ለማሳየት እጁን ከጌታችን ራስ በላይ ከፍ እንዳደረገ ጌታችንም ለትሕትና እጁን ከሐዋርያት እግር በታች ዝቅ አድርጎ እግራቸውን አጥቧቸዋልና ነው፡፡

ጥምቀት የሕጽበት አምሳል ሲኾን፣ ሕጽበት (መታጠብ) ደግሞ በንባብ አንድ ኾኖ ሁለት ምሥጢራት አሉት፡፡ የመጀመሪያው፡- ምእመናን የእንግዳ እግር እንዲያጥቡ ጌታችን ትምህርት ማስተማሩ ሲኾን፣ ሁለተኛውም ለሐዋርያት ጥምቀታቸው መኾኑ ነው፡፡ ሐዋርያት በጸሎተ ሐሙስ ቢጠመቁም መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት የጰራቅሊጦስ ዕለት ነውና፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያን እንደ ጠየቀውና ጥምቀታቸው ሕጽበተ እግር መኾኑን እንደ መለሰለት፡፡

በሌላ በኩል ከዘመነ ልደት እስከ ጥምቀት ተወልደ፤ ተሠገወ (ሰው ኾነ) ይባላል እንጂ አስተርአየ (ተገለጠ) አይባልም፡፡ ከጥምቀት በኋላ ግን አብሮ፣ ተባብሮ ተጠምቀ፤ ተወልደ፤ ተሠገወ፤ አስተርአየ ይባላል፡፡ ከጥምቀት በፊት አስተርእዮ ለመባሉ በሦስት ነገሮች ነው፡፡ የመጀመሪያው፡- የማይታየው ረቂቅ አምላክ በበረት ተወልዶ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎ ቢታይ፤ እንደ ሕፃን ሲያለቅስ ቢሰማም ሰው ዅሉ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ሙሉ ሰው ይኾናል እንደሚባለው፣ አምላክ ነኝ ብሎ በአንድ ቀን ሳያድግ በጥቂቱ ማደጉንና ስደት እንደ ውርደት ኾኖ እንዳይቈጠር ለሰዎች ስደትን ባርኮ (ጀምሮ) ለመስጠት፤ ሄሮድስም ሊገድለው ይፈልገው ስለ ነበር ወቅቱ የሚሰደድበት እንጂ የሚታይበት ስላልነበረ ነው፡፡

ሁለተኛው፡- ሰው በተፈጥሮም ኾነ በትምህርት አዋቂ ቢኾን ለሚመለከተው ሥራና ደረጃ እስከ ተወሰነ ጊዜ ይህ ሕፃን ለእንዲህ ያለ ማዕረግ ይኾናል አይባልም፤ ተንከባክባችሁ አሳድጉት ይባላል እንጂ፡፡ ሕፃኑ አዋቂ ነው አይባልም፤ ያውቃል ተብሎም ለትልቅ ደረጃ አይበቃም፡፡ በየትኛውም ሓላፊነት ላይ አይሰጥም፤ ራሱን በመግዛት ይጠበቃል እንጂ፡፡ ጌታችንም በመንፈስም በሥጋም ባለ ሥልጣን ቢኾንም ፍጹም ሰው ኾኗልና አምላክ ነኝ፤ ዅሉን በዕለቱ ልፈጽም ሳይል በየጥቂቱ ማደጉን እናያለን፡፡

የሰውን ሥርዓት ከኀጢአት በቀር ለመፈጸም በየጥቂቱ አደገ፡፡ ‹‹በበሕቅ ልሕቀ›› እንዲል፡፡ ሰው ዅሉ ፴ ዓመት ሲኾነው ሕግጋትን ለመወከል፣ ለመወሰን እስከ ፴ ዓመት መታገሡም ስለዚሁ ነው፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ሰው ቢመቸው ይወፍራል፤ ቢከፋው ይከሳል እንጂ ቁመት አይጨምርም አይቀንስም፡፡ ጌታችን ሰው ሙሉ፣ አእምሮው የተስተካከለለት ጐልማሳ በሚኾንበት ዕድሜ በ፴ ዓመት በግልጽ በመታየቱ ወቅቱ ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› ተብሏል፡፡

ሦስተኛው፡- በ፴ ዓመት እርሱ ሊጠመቅበት ሳይኾን የመጀመሪያ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት መሠረት የኾኑ ጥምቀትንና ጾምን ሠርቶ በመሳየትና መመሪያ አድርጎ ለምእመናን በመስጠት እሱ ሙሉ ሰው ኾኖ ተገልጾ የቃሉን ትምህርት ለመስማት፤ የእጁን ተአምራት ለማየት ይከተለው ለነበረው አምስት ገበያ ያህል ሕዝብ  ትምህርት፣ ተአምራት ያደረገበት፤ ሥራዬ ብሎ የመጣበት መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት የፈጸመበት ዘመን በመኾኑ ነው፡፡ የታየውም ወልድ ብቻ አይደለም፤ አብ ‹‹ይህ የምወደው ልጄ ነው›› ሲል፤ መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ሲወርድ ረቂቁ አምላክ የታየበት፤ የሥላሴ የአንድነትና ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት ዕለት ስለ ኾነ ይህ ወቅት ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

በአስተርእዮ ሌሎች በዓላትም ይጠሩበታል፡፡ ለምሳሌ ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይቶ በደመና ተነጥቃ ወደ ገነት በመግባት ለጻድቃን እና ለመላእክት በሰማይና በምድር የተሰጣት ጸጋ፣ ክብር የተገለጸበት ዕለት ስለኾነ በዓሉ ‹‹አስተርእዮ ማርያም›› ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ አምላክ በሥጋ ከድንግል መወለዱንና በዚህ አካለ መጠንም ለዓለም መገለጡን አስተርእዮ ብሎ ሲናገር፤ አባ ጽጌ ብርሃን ደግሞ በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ ‹‹እግዚአብሔር ጽጌ ትንቢት ለቢሶ ሥጋኪ ሥጋ ዚአነ፤ አመ አስተርአየ በምድር ወተአምረ ለነ፤ ንዌድሰኪ እንዘ ንብል ምክሐ ዘመድነ፤ ዮም በፍሥሓ ለማርያም እምነ፤ አስተርእዮ በሰማይ ኮነ፡፡ – የትንቢት አበባ እግዚአብሔርእኛ ሥጋ የኾነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ ለእኛ እንዲታወቅ በምድር እንደ ተገለጠ፤ የወገናችን መመኪያ ድንግል ሆይ፣ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ኾነ› እያልን እናመሰግንሻለን፤›› ሲል ገልጾታል፡፡ ነቢዩ ዳዊትም፡- ‹‹በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ፤ በነቢያት ይወለዳል ሲባል የሰማነው በበረት ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው፡፡ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አየነው፤›› በማለት የአምላካችንን መገለጥ ተናግሯል /መዝ.፵፯፥፮/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ዝክረ በዓለ ጥምቀት

timk

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

በዓለ ጥምቀት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንደ በዓለ መስቀል በዐደባባይ የምታከብረው ልዩ በዓል ነው፡፡ በዓሉ ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ባሻገር አገራዊ ቅርስም ነው፡፡ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለው ደማቅ መንፈስ ከተማዋን ታላላቅ እንግዶችን በቤቷ ለመቀበል ሽር ጉድ የምትል አንዲት ወይዘሮን አስመስሏታል፡፡ በየቦታው በተዘጋጁ ድንኳኖች የሚሰሙ ኦርቶዶክሳውያን መዝሙራት፤ ነጭ ልብስ ለብሰው የሚንቀሳቀሱ ምእመናን፤ በየቤቱ የነበረው ባህላዊ ዝግጅት ልዩና ማራኪ ነበር፡፡ ይህ ልዩ በዓል እንደ አሁን በፊቱ ዅሉ በዘንድሮው ዓመትም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በደማቅ መንፈሳዊ ሥርዓት ተከብሮ ውሏል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በጊዜያዊው የጥምቀት ቤተ መቅደስ በጃንሜዳ የበርካታ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት በተሰባሰቡበት በቅዱስ ፓትርያርኩ ቡራኬ የተከበረው የ፳፻፱ ዓ.ም በዓለ ጥምቀት ከዋይዜማው ጀምሮ መንፈሳዊ ቀልብን በሚገዙ፤ ልቡናን በሚመስጡ፣ ሕሊናን በሚማርኩና ነፍስን በሚያስደስቱ ሥርዓታት ተውቦ ነበር፡፡

በትምህርተ ወንጌል፣ በዝማሬ፣ በዕልልታ፣ በጸሎተ ቅዳሴ፤ በቦታው የተገኙ የቤተ ክርስቲያችን አባቶች (ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ መምህራን፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት)፤ እንደዚሁም የአኃት አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፤ ከየአጥቢያው ታቦታቱን በዝማሬ አጅበው የመጡ የሰንበት ት/ቤት እና የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን፤ የበዓሉን ሥርዓት ለመመልከት ከውጪ አገር እና ከአገር ውስጥ የመጡ ጐብኚዎች፤ በበዓሉ ለመታደም በነቂስ ከየቤታቸው ወጥተው በጃን ሜዳ የተሰባሰቡ በመቶ ሺሕ የሚቈጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ እና የአካባቢው ምእመናን ጃን ሜዳን ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ፍርድ የሚሰጥበት ዐውደ ምሕረትን አስመስለውታል፡፡

pp

እኛም በጃን ሜዳ ተገኝተን በዓሉን አክብረናል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ በዋይዜማው (የከተራ ዕለት) በጃንሜዳ ተገኝው ስለ ጌታችን ጥምቀት ካስተማሩት ቃለ እግዚአብሔር በተጨማሪ በዕለቱም ‹‹ወይርአይ ኵሉ ዘነፍስ አድኅኖቶ ለእግዚአብሔር፤ ነፍስ ዅሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ፤›› /ሉቃ.፫፥፮/፣ በሚል ኃይለ ቃል በሰጡት ቃለ ምዕዳናቸው የሰውን ልጅ ለሞት ያበቃው ኀጢአት በጥምቀተ ማይ እና በልደተ መንፈስ ቅዱስ መወገዱን ማስተማራቸውም አንዱ የበዓሉ በረከት ነበር፡፡

ቅዱስነታቸው በቃለ ምዕዳናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየጎዳናው፣ በየመንደሩ፣ በየወንዙ ቅዱስ የኾነውን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ይዛ በመዝሙር፣ በጭብጨባ፣ በሆታ፣ በዕልልታ፣ በውዳሴ፣ በማኅሌት፣ በቅኔ፣ በስብከተ ወንጌል፣ በጸሎት የከበረውን ውኀ ባርኮ በመርጨት ልዩና በኾነ የአምልኮ ጉዞ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ አስተምህሮን አጉልቶ ሊያሳይ በሚያስችል መልኩ በዓለ ጥምቀት እንዲከበር በማድረጓ ለአገራችን ኢትዮጵያ ልዩ የኾነ ግርማ ሞገስን አጐናጽፋ እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡ ከ፶ ሚሊየን በላይ የሚኾን ሕዝበ ክርስቲያን በነጻነት፣ በአንድነት፣ በደስታና በፍቅር ከቤተ ክርስቲያኑ አንሥቶ እስከ ባሕረ ጥምቀቱ፤ ከባሕረ ጥምቀቱ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ ድረስ ምንም መለያየት ሳይኖር፣ ጥላቻ ሳያጋጥም፣ በየቋንቋውና በየባህሉ ፈጣሪውን እያመሰገነ እንደ ዓባይ ወንዝ የእግዚአብሔር ሠራዊት ኾኖ ከዳር እስከ ዳር እየተመመ በዓለ ጥምቀትን ማክበሩ ዅሉን የሚገዛ የእግዚአብሔር ኀይል መገለጫ መኾኑን ቅዱስ ፓትርያኩ አስገንዝበዋል፡፡

img_0513

‹‹ይህ በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ሕይወትና የሥራ ፍሬ ምስክር ነው፡፡ ይህ በዓል የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን አበው የማይፈርስ ጽኑዕ ግንብ ነው፡፡ ይህ በዓል የኢትዮጵያ እና የእግዚአብሔር የኾነ ጽኑዕ የቃል ኪዳን ትስስርን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው፤›› ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ የኢትዮጵያን ሕዝብ እርስበርስ ከማቀራረብና ከማስተሳሰር አኳያ ከበዓለ ጥምቀት የሚበልጥ በዓል እንደሌለ ጠቅሰው ኢትዮጵያውያን ይህንን ጸጋ እግዚአብሔርና ግርማ ሞገስ የተሞላ በዓል እስከ መጨረሻው ሊጠብቁትና ሊንከባከቡት፤ ሊያሳድጉትና ሊያበለጽጉት፤ ለዓለምም ሊያስተዋውቁት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ እና የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ጠባቂ እንደዚሁ በበዓለ ጥምቀት ዋይዜማ ከሰጡት ትምህርተ ወንጌል በተጨማሪ በዕለቱም ‹‹ተሣሃልከ እግዚኦ ምድረከ ወሜጥከ ፄዋሁ ለያዕቆብ ወኀደገ ኀጢአቶሙ ለሕዝብከ፤ አቤቱ ምድርህን ይቅርል አልኽ፡፡ የያዕቆብን ምርኮ መለስህ፡፡ የሕዝብህን ኀጢአት ይቅር አልህ፤›› /መዝ.፹፬፥፩/ በሚል ኃይለ ቃል እግዚአብሔር አምላካችን አዳምን ከዘለዓለማዊ ሞት ማዳኑን እና ለሕዝቡ ያደረገውን ይቅርታ የሚያስገነዝብ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡

img_0506

በበዓሉ ከታደሙ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት መካከል የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ኂሩት ወልደ ማርያም ያስተላለፉት መልእክት ደግሞ ሌላው የጥምቀት ትውስታ ነው፡፡ ሚኒስትሯ በዚህ መንፈሳዊ በዓል ላይ ተገኝተው መልእክት ለማስተላለፍ በመቻላቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸው ኢትዮጵያውያን የብዙ ሀብት ባለቤት የኾነች አገር ስላለችን ዕድለኞች እንደ ኾንን እና አገራችን ካሏት ልዩ ልዩ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሀብታት መካከል በዓለ መስቀል አንዱ መኾኑን ጠቅሰው ይህንን የማይዳሰስ ሃይማኖታዊ ሀብት ጠብቀው ለትልድ ያቆዩ ቀደምት ኢትዮጵያውያንን አመስግነዋል፡፡ ዶ/ር ኂሩት አያይዘውም ከልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ጐብኚዎች በአንክሮ እና በተደሞ ኾነው የበዓሉን ሥርዓት እንዲከታተሉ ያደረጋቸው በዓለ ጥምቀት በሌላው ዓለም የማይገኝ፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ኾነው ደስታቸውን የሚገልጹበት ልዩ በዓል በመኾኑ ነው ብለዋል፡፡

በዓለ ጥምቀት በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት እንዲመዘገብ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሯ ለዚህም ቤተ ክርስቲያንና መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ አብያተ መዝክራትን በማስፋፋት መንፈሳዊ ቅርሶችን የመጠበቅ ጉዳይ በቤተ ክርስቲያኗ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳሰቡት ዶ/ር ኂሩት ወልደ ማርያም በመጨረሻም ‹‹በበዓለ ጥምቀት አከባበር ላይ የሚታየው የኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ ኅብረት በማኅበራዊ ሕይወታችንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አደራ›› በማለት መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሓላፊ አቶ ገብረ ጻድቅ ሀጎስ እንደዚሁ በዓለ ጥምቀት የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ የሚገነባ እና ለዓለም የሚያስተዋውቅ በዓል ከመኾኑ ባሻገር ለአገሪቱ የቱሪዝም ገቢ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳለው መናገራቸውም አይዘነጋም፡፡

img_0514

በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በበዓለ ጥምቀት ወቅት አባቶች ካህናት ከዋይዜማው ጀምሮ ከምግብ ተከልክለው፤ እንቅልፍ አጥተው በቅዳሴ፣ ታቦት በማክበርና በመሳሰሉ ተልእኮዎች መሰማራታቸው፤ የየአድባራቱና ገዳማቱ ሊቃውንት፣ የየሰንበት ት/ቤቶችና የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራን በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመሰንቆ፣ በዋሽንት፣ በበገና ታግዘው የሰሚዎችን ልቡና በሚማርክ ያሬዳዊ ዝማሬ ታቦታን ማጀባቸው፤ ብዙ ምእመናን ሥርዓት ባለው (ክርስቲያናዊ በኾነ) አለባበስ አጊጠው በዕልልታና በጭብጨባ እየዘመሩ በበዓሉ መታደማቸው፤ በተለይ እንደ አዲስ አበበባ ባሉ ሰፋፊ ከተሞች ወጣቶች የክብር ምንጣፍ ለታቦታቱ ለመዘርጋት መፋጠናቸው የብዙዎችን ቀልብ የሚስቡና የሚያስደስቱ የአገልግሎት ክፍሎች ናቸው፡፡

መለዮ ሹራብ ለብሰው ለታቦታቱ የክብር ምንጣፍ ለመዘርጋት ወዝ እስኪወጣቸው ድረስ የሚሽቀዳደሙ ወጣቶች አቤት ሲያስቀኑ! በእውነት በእግዚአብሔር ጥሪ ለመልካም አገልግሎት የተሰማሩ የተዋሕዶ ፍሬዎች ናቸው፡፡ እነዚህን ወንድሞችና እኅቶች ስንመለከት ‹‹በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ፤›› /መክብብ ፲፪፥፩/ የሚለው የጠቢቡ ሰሎሞን ምክር በአእምሯችን ድቅን ይላል፤ የወጣቶቹ ርብርብ ምክሩ በተግባር ላይ እንደ ዋለ የሚያመላክት መንፈሳዊ አገልግሎት ነው፡፡ ወጣቶቹ የሚያገለግሉት ምንጣፍ በመዘርጋት ብቻ አይደለም፤ በየከተሞች በሚገኙ መንገዶችና ዐደባባዮች በረጅሙ የተዘረጉ ሰንደቅ ዓላማዎችና ጌጣጌጦች፤ በሙዚቃና በሐራ ጥቃ ‹‹መዝሙራት›› የተዋጡ አካባቢዎችን ነጻ ያወጡ መንፈሳውያን የሲዲ ዝማሬዎች በየዓመቱ የሚከናወኑ የወጣቶቹ ተጨማሪ ተልእኮዎች ናቸው፡፡

img_0524

ታቦታትን አጅበው ለሚጓዙ፣ በፀሐይ ለደከሙ ምእመናን ጠበል ጸሪቅ እና የሚጠጣ ውኀ በየመንገዱ ማቅረብም ሌላኛው ተግባራቸው ነበር፡፡ ይህ መልካምና አርአያነት ያለው የወጣቶቹ ተልእኮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚመለከትን አካላት ዅሉ ወጣቶቹን በገንዝብ፣ በጕልበት፣ በሐሳብና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ መደገፍና መከባከብ ይገባናል፡፡ እኛም እንደ ዝግጅት ክፍል እነዚህን ወንድሞችና እኅቶችን ‹‹እግዚአብሔር መጨረሻችሁን ያሳምርላችሁ!›› እንላቸዋለን፡፡ ለታቦተ ሕጉ ምንጣፍ በዘረጉ እጆቻችን የሰው ንብረት እንዳንወስድ፤ የሰው ባል ወይም ሚስት እንዳናቅፍ፤ ሰውን እንዳንደበድብ፤ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በተሸቀዳደምንባቸው እግሮቻችን ወደ ኀጢአት መንገድ እንዳንሔድባቸው፤ ደሃ ወገኖቻችንን እንዳንረግጥባቸው እግዚአብሔር የዅላችንንም መጨረሻ ያሳምርልን፡፡

በቃና ዘገሊላ መድኀኒታችን ክርስቶስ ውኀውን ወደ ወይን ጠጅ በቀየረበት ዕለት የሰርግ ቤቱ አጋፋሪ ወይኑን በቀመሰ ጊዜ እንደ ተደነቀ በቅዱስ ወንጌል ተጽፏል /ዮሐ.፪፥፱/፡፡ ቅዱስ ያሬድም በድርሰቱ ‹‹ጥዒሞ አንከረ ሊቀ ምርፋቅ በረከተ ዘአምላክ ገብረ›› በማለት ይህንኑ ምሥጢር ጠቅሶታል፡፡ የቃናው ወይን ጠጅ የቀመሱትን ዅሉ ያስደነቀበት ምክንያት በክርስቶስ ተአምር የተገኘ ንጹሕ መጠጥ በመኾኑ ነው፡፡ እኛም የእግዚአብሔር የእጁ ሥራዎች ከመኾናችን ባሻገር በቅዱስ ሥጋው እና በክቡር ደሙ ቤዛነት ለመንግሥቱ የጠራን ልጆቹ ነን፡፡ ስለዚህ የእኛን መንፈሳዊ ኅበረት፣ ክርስቲያናዊ ፍቅር እና የአምልኮ ሥርዓት የሚመለከቱ ሰዎች ይደነቃሉ፡፡ ይህ መንፈሳዊ ሥርዓት ግን በበዓላት ላይ ብቻ የሚፈጸም ተግባር መኾን የለበትም፡፡ ክርስትናችንን ከዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በየቀኑ መኖር ይጠበቅብናልና፡፡

img_0534

አንድ ጊዜ መንፈሳዊ፤ ሌላ ጊዜ ዓለማዊ በኾነ የተቀላቀለ ሥርዓት ከኖርን ግን እንኳን የውጮቹ ሊደነቁብን የውስጦቹ ወገኖቻችንም በእኛ የማስመሰል ክርስትና ሊደናገሩብን፤ ‹‹እነዚህ እንደዚህ ሲያደርጉ የተመለከትናቸው አይደሉም እንዴ?›› በሚል የጥርጣሬ መንፈስም ሊሰናከሉብን ይችላሉ፡፡ ለሌሎች መሰናክል ከመኾን ይልቅ የወፍጮ ድንጋይ በአንገታችን ታስሮ ወደ ጥልቅ ባሕር መስጠም እንደሚሻለን ደግሞ ጌታችን በወንጌል ተናግሯል /ማቴ.፲፰፥፮/፡፡ ጌታችን እንደ ተነናገረው ምግባራችን ለእኛም ለሌሎችም የማይጠቅም ኢ ክርስቲያናዊ ከኾነ እንደ አጥፍቶ ጠፊ ሞቶ መግደል መገለጫችን ይኾናል ማለት ነው፡፡ እናም ራሳችንን አጥተን ለሰዎችም መጥፋት ምክንያት እንዳንኾን እንጠንቀቅ መልእክታችን ነው፡፡

ከዚህ ላይ ይህን ሐሳብ ያነሣነው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ እንደ በዓለ ጥምቀት ባሉ ልዩ በዓላት ወቅት በየከተማው የሚስተዋሉ ኢ ክርስቲያናዊ ተግባራት እንዲስተካከሉ ለመሳሰብ ነው፡፡ ጥቂቶቹን ለመጠቆም ያህል በዓሉን ተገቢ ላልኾነ የተቃራኒ ጾታ መቀጣጠሪያ ማድረግ፤ በየመጠጥ ቤቱ መተላለፊያ መንገዶችን በመዝጋት፣ በጩኸትና በሁካታ አካባቢን እየረበሹ መጠጥ መጠጣትና መስከር እኛንም ሃይማኖታችንንም የሚያስነቅፍ ድርጊት ነውና እናስብበት፡፡ መጠጥ ቢያምረን እንኳን ከዘመዶቻችን ጋር ኾነን በቤታችን ተሰባስበን፣ ጸሎት አድርገን፣ በሥርዓትና በአግባቡ መጠጣት እንችላለን፡፡ በክርስትናችን መስከር (አብዝቶ መጠጣት) እንጂ አልኮል መቅመስ አልተከለከለምና፡፡ ሲበዛና ከሥርዓት ውጪ ሲኾን ግን እንሰክርና በኀጢአት ላይ ኀጢአት ለመፈጸም እንገፋፋለን፡፡ ይህም በቅጣት ላይ ቅጣትን ያመጣብናል፡፡

ttt

በበዓላት ወቅት ለሥጋዊ ጉዳይ የምንቀሽዳድም ክርስቲያኖች ጥቂቶች አይደለንም፡፡ ይህም ሊስተካከል ይገባዋል፡፡ መንፈሳውያን በዓላትን ከዓለማዊ ግብር ለይተን ልናይ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ በዓሉን ስናከብር ለጥላቻ፣ ለድብድብ፣ ለግብረ ዝሙትና ለመሳሰለው ኀጢአት የምንገዛ ወገኖች ይህ የክርስቲያኖች መገለጫ አይደለምና ከዚህ ልማድ እንቈጠብ፡፡ ይህ ልማድ በበዓላት ወቅት በተለይ በበዓለ ጥምቀት ጎልቶ ስለሚታይ በዚህ ዝግጅት አነሣነው እንጂ በሌላ ጊዜ ኀጢአት መሥራት ይቻላል ለማለት አይደለም፡፡ ቀደም ሲል እንደ ጠቀስነው በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንቶ መኖር የዅልጊዜ ተግባራችን ሊኾን የግድ ነውና፡፡ በእርግጥ ተሳስተን ልንሰናከል እንችላለን፤ በዕቅድና በዓላማ ለስካርና ለሌችም የኀጢአት ዘሮች ተገዢ መኾን ግን ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር አይደለም፡፡

img_0574

ከዚሁ ዅሉ ጋርም በየመንገዱና በየዐደባባዩ የምናስቀምጣቸው ቅዱሳት ሥዕላት ጉዳይ ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አንጻር ሊታይ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ሥዕላቱ ንዋያተ ቅድሳት እንደ መኾናቸው ለአምልኮ እና ለጸሎት በተመረጠ ልዩና ንጹሕ ቦታ መቀመጥ ሲገባቸው ለፀሐይ፣ ለአቧራና ለነፋስ በሚጋለጡባቸውና በሚቀደዱባቸው መንገዶች ላይ፣ ጭራሽ በቆሻሻ መጣያ ሥፍራዎች በዘፈቀደ መቀመጣቸው ተገቢ አይደለም፡፡ በአንዳንድ የአዲስ አበባ መንገዶች ስንዘዋወር ሥዕላቱ ከተቀመጡበት ቦታ የሚያነሣቸው ጠፍቶ በነፋስ ተቀዳደው ሲወድቁ ዅሉ ተመልክተናል፡፡ የተወደዳችሁ ምእመናን በተለይ ወጣት ክርስቲያኖች ሆይ! ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

img_0575

ከዚህ ላይ የወጣቶቹን ተልእኮ እየነቀፍን እንዳልኾነ ግን ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ እርግጥ ነው፤ ወጣቶቹ ይህን የሚያደርጉት ለተንኮል ሳይኾን ለሃይማኖታቸው ካላቸው ቀናዒነትና በዓሉ ድምቀት እንዲኖረው ከማሰባቸው የተነሣ መኾኑ አይካድም፡፡ ዳሩ ግን ጥሩ የሠራን መስሎን የምናከናውናቸው ተግባራት ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተቃርኖ እንዳይኖራቸው፤ እንደዚሁም ‹‹መክፈልት ሲሹ መቅሠፍት›› እንደሚባለው ለበረከት ያልነው ተልእኮ ለጥፋት እንዳይዳርገን የሥዕላቱን ኦርቶዶክሳዊ ይዘት ከማስገምገም ጀምሮ እስከምናስቀምጥበት ቦታ ድረስ ከአባቶች ጋር መመካከርና መመርያ መቀበል ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም በየመንገዱ የምንከፍታቸው ዝማሬያት ያሬዳዊነትም አብሮ ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ በአጭሩ ቅዱሳት ሥዕላቱን በየመንገዱ ከማስቀመጣችን በፊት (አስፈላጊነቱ በአባቶች ከታመነበት) ሥዕላቱን ከምንመርጥበት መሥፈርትና ከምናስቀምጥበት ቦታ ጀምሮ እስከ አቀማመጠጥ ሥርዓቱ ድረስ፤ እንደዚሁም ከምንከፍታቸው መዝሙራት ያሬዳዊነት አኳያ ዅሉም በሥርዓት ይኾን ዘንድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባን አንርሳ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን የሊቃውንት ችግር የለባትም፡፡ የትኞቹን ሥዕላትና መዝሙራትን መጠቀም እንደሚገባን ጠጋ ብለን መምህራንን ብንጠይቅ በቂ ትምህርት ይሰጡናል፡፡

img_0570

እንደሚታወቀው በዓለ ጥምቀት ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ አገራዊ ሀብታችን ስለኾነ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ሊገኝ እንደሚገባው እሙን ነው፡፡ ስለዚህም በዓሉን በዓለም አቀፉ የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት በቅርስነት ለማስዝገብ ቤተ ክርስቲያናችን ከመንግሥት ጋር በመኾን ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ በዓለ ጥምቀት በቅርስነት እንዲመዘገብ የሚያደርገው በዐደባባይ የሚከበር በዓል መኾኑ ብቻ ሳይኾን የአከባበር ሥርዓቱ መንፈሳዊነትና ውበት ነው፡፡ የታቦታቱ ዑደት፣ የሊቃውንቱና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ዝማሬ፣ የምእመናኑ አለባበስና የወጣቶቹ ሱታፌ፣ ከበዓሉ በፊትም ኾነ ከበዓሉ በኋላ የምናደርጋቸው ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዅሉ የበዓሉ አካላት ናቸው፡፡

የእኛ የአከባበር ዅኔታ ነው በዓሉን በዓል የሚያስብለው፡፡ በሥርዓት ካከበርነው በዓለም እንደ ተደነቀ ይቀጥላል፤ መንፈሳዊ ሥርዓቱን ካጎደልን ግን በዓልነቱም ይረሳል፡፡ ስለዚህ በዐቢይነት ከክርስቶስ ጸጋና በረከት እንሳተፍ ዘንድ፤ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በዓሉ በቅርስነት እንዲመዘገብ የሚደረገው ጥረት ይሳካ ዘንድ ለወደፊቱ ዅላችንም ክርስቲያናዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በዓለ ጥምቀትን ለማክበር እንዘጋጅ እያልን ጽፋችንን አጠቃለልን፡፡ በዘንድሮው በዓለ ጥምቀት ያከናወናቸውን መልካም ተግባራት አሳድገን፤ ያጎደልናቸውን ደግሞ አሻሽለን በዓሉን በመንፈሳዊ ሥርዓት እንድናከብር አምላካችን ዕድሜ ለንስሐ ሰጥቶ በሚቀጥለው ዓመት በበዓለ ጥምቀቱ ይሰብስበን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

‹‹ጌትነቱን ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ፤›› /ዮሐ. ፪፥፲፩/፡፡

%e1%8c%88%e1%88%8a%e1%88%8b

በመምህር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

ጥር ፲፫ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዐላት አከባበር ቀመር ከበዓለ ልደት፣ ግዝረት እና ጥምቀት ቀጥሎ ቃና ዘገሊላ ይከበራል፡፡  ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለማዳን ወደዚህ ዓለም በመጣበት ወቅት ልዩ ልዩ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡ ከእነዚህ መካከልም በቃና ዘገሊላ በሰርግ ቤት ተገኝቶ ያደረገው ተአምር ተጠቃሽ ነው፡፡

ይህንንም ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ እንዲህ ጽፎታል፤ ‹‹በሦስተኛው ቀን በገሊላ ቃናርግ ኾነ፡፡›› ምን በተደረገ በሦስተኛው ቀን የሚል ጥያቄ በኹላችንም አእምሮ እንደሚመላለስ አያጠያይቅም፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማየ ዮርዳኖስ በእደ ዮሐንስ ጥር ፲፩ ቀን ተጠምቆ ሳይውል ሳያድር ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ዐርባ መዓልትና ዐርባ ሌሊት ጾሞ፤ ዲያብሎስን ድል ነስቶ፤ መዋዕለ ጾሙን ፈጽሞ፤ ለእኛም ዲያብሎስን ደል የምንነሳበትን መንገድ አሳይቶ ከገዳመ ቆሮንቶስ መልስ ደቀ መዛሙርቱን መረጠ፡፡

ከጥር ፲፩ እስከ የካቲት ፳ ቀን ያለው ጊዜ ፵ ቀን ይኾናል፡፡ ጌታችን መዋዕለ ጾሙን የካቲት ፳ ቀን ፈጽሞ በወጣ በሦስተኛው ቀን በገሊላ አውራጃ ቃና በተባለች መንደር ሰርግ ኾነ፡፡ በዚህ ሰርግ ብዙ ሰዎች መታደማቸውን ወይን ጠጁ ማለቅ ያስረዳናል፡፡ የተጠሩት ሰዎች ብዙ ለመኾናቸው ባሻገር ብዙዎችን መመገብ የሚችል አምላክ በሰርግ ቤት መጠራቱ ልዩ ዕለቱን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ሰርግ ከሰዎች በተጨማሪ ሦስት አካላት ተጠርተዋል፡፡

፩. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ

‹‹ወጸውዕዎ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ ጌታ ኢየሱስንም ጠሩት›› /ዮሐ.፪፥፪/፣ ተብሎ እንደ ተጻፈ እናትን ጠርቶ ልጅን መተው ተገቢ አይደለምና እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ጠርተው ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስንም ጠርተውታል፡፡ ይህም ፍጹም ሰው መኾኑን ያስረዳል፡፡ ጌታችን እንደ ሰውነቱ ወደ ሰርግ ቤት ተጠራ፤ እንደ አምላክነቱ ተአምራቱን በማሳየት ጌትነቱን፣ አምላክነቱን ገለጠ፡፡

ከሚደሰቱት ጋር መደሰት፤ ከሚያዝኑት ጋር ማዘን ተገቢ መኾኑን መድኀኒታችን ክርስቶስ በተግባር አስተማረን፡፡ በቃና ዘገሊላ ከሰርግ ቤት እንደ ሔደው በአልዓዛር ቤት ለለቅሶ መገኘቱን ልብ ይሏል፡፡ ወደ ሰርግ ቤት የሔደው በደስታ ነበር፡፡ ‹‹ሖረ ኢየሱስ በትፍሥሕት ውስተ ከብካብ እንዘ ይገብር ተአምረ ወመንክረ በውስተ አሕዛብ፤ ኢየሱስ በአሕዛብ ፊት ተአምራትንና ድንቆችን እያደረገ በደስታ ወደ ሰርግ ሔደ፤›› በማለት ቅዱስ ያሬድ እንደ ገለጠው፡፡

ጌታችን ወደ አልዓዛር ቤት ሲሔድ ግን በኀዘን ውስጥ ኾኖ ነበር፡፡ ‹‹ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም እርሷ (ማርታ) ስታለቅስ ባየ ጊዜ በልቡ አዘነ፤ በራሱም ታወከ (ራሱን ነቀነቀ – የኀዘን ነው) ዕንባውን አፈሰሰ፡፡ አይሁድምምን ያህል ይወደው እንደ ነበር እዩ› አሉ፤›› እንዳለ ወንጌላዊው /ዮሐ.፲፩፥፴፫-፴፰/፡፡

ጌታችን ‹‹አምላክ ነኝና ከሰርግ ቤት አልሔድም፤ ከልቅሶም ቤትም አልገኝም፤›› አላለም፡፡ ከዚህም ጌታችን ከኀጢአት በቀር የሰውነትን ሥራ እንደ ሠራ፤ የሰውን የተፈጥሮ ሕግ እንዳከበረ እና እንደ ፈጸመ እንረዳለን፡፡ በመደሰት እና በማዘን ፍጹም ሰው መኾኑን፤ በሰርጉ ቤት ውኀውን የወይን ጠጅ በማድረግ፤ እንደዚሁም አልዓዛርን ከአራት ቀናት በኋላ ከሞት በማስነሣት ደግሞ ፍጹም አምላክ መኾኑን አስረዳን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነውና በሰርግ ቤት የጎደለውን መላ፡፡ አምላክ ነውና የሞተውን አልዓዛርን ‹‹መግነዝ ፍቱልኝ? መቃብር ክፈቱልኝ? ሳይል›› ከሞት እንዲነሣ አደረገ፡፡

‹‹ወሶበ ኀልቀ ወይኖሙ ወትቤሎ እሙ ወይንኬ አልቦሙ፤  የወይን ጠጅ ባለቀባቸው ጊዜም እናቱ (እመቤታችን)የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም› አለችው›› /ዮሐ.፫፥፫/፡፡ እርሱም ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም፤›› አላት፡፡ ይኸውም ‹‹ያልሽውን ልፈጽም ነው ሰው የኾንኩት፤ ያልሽኝን እንዳልፈጽም ከአንቺ ጋር ምን ጠብ አለኝ?›› ማለት ነው፡፡ ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› የሚለው ቃልም ጌታችን ሥራውን ያለ ጊዜው እንደማይፈጽመው ያሳያል፡፡ ‹‹ለእግዚአብሔር የሥራ ጊዜ አለው፤›› እንዲል /መዝ.፻፲፰፥፻፳፮/፡፡

በሌላ መልኩ ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› የሚለው ቃል እግዚአብሔር አምላካችን ይህን አድርግ ብሎ በግድ ማንም ሊያዝዘው የማይቻለውና በራሱ ፈቃድ የወደደውን ዂሉ የሚያደርግ፤ ቢፈልግ የሚያዘገይ፣ ሲፈልግ ደግሞ በዐይን ጥቅሻ በፈጠነ መልኩ መፈጸም የሚችል፤ በራሱ ፈቃድ እንጂ በሰምች ፈቃድ የማይመራ አምላክ መኾኑን ያስተምረናል፡፡ ‹‹ፈቃድህ በሰማይ እንደ ኾነች እንዲሁ በምድር ትኹን›› ብላችሁ ለምኑኝ ያለውም ለዚህ ነው፡፡

የወይን ጠጁም ሙሉ ለሙሉ አላላቀም ነበር፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ያለውን ቢያበረክተው ተአምራቱን አናደንቅም የሚሉ ይኖራሉና ፈጽሞ ጭልጥ ብሎ እስከሚያልቅ ድረስ መጠበቅ እንደሚገባ ሲያስረዳ ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› አለ፡፡ ሰው ቢለምን፣ ቢማልድም እግዚአብሔር በእርሱ ፈቃድ ጊዜው ሲደርስ ነው የሚፈጽመው፡፡ ምልጃው አልተሰማም፤ ተቀባይነት አላገኝም ማለት ግን አይደለም፡፡ ተቀባይነት ያገኘ መኾኑ የሚታወቀው በመደረጉ ነውና፡፡ ተማላጅነት የአምላክ፤ አማላጅነት ደግሞ የፍጡራን መኾኑን ጌታችን በዚህ ሰርግ ቤት አስተምሯል፡፡ ጌታችን በሰርግ ቤት ባይገኝላቸው ኖሮ ሰዎቹ ምን ያህል ኀፍረት ይሰማቸው ይኾን? የእርሱ እንደዚሁም የእናቱ በሰርጉ ቤት መገኘት ለባለ ሰርጉና ለታዳሚዎች ሙላት ነበር፡፡ እርሱ ባይኖር የሰርጉ ቤት ከደስታ ይልቅ በኀዘን ሊሞላ ይችል እንደ ነበር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

አማላጅ ያስፈለገውም እርሱ የማያውቀው ምሥጢር ኖሮ፤ ሥራውን የሚሠራውም በስማ በለው ኾኖ አይደለም፡፡  ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ይታወቅ ዘንድ እና የሰው ልጆችን ከችግር የሚያወጣበት መንገዱ ብዙ መኾኑን ለማስረዳት ነው እንጂ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሚዜዎችን ‹‹ኵሎ ዘይቤለክሙ ግበሩ፤ ያዘዛችሁን ዂሉ አድርጉ፤›› ማለቷ ‹‹አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?›› የሚለው የጌታችን መልስ እሺታን (ይኹንታን) የሚገልጽ ቃል መኾኑን ያስረዳል፡፡

ጌታችንም ‹‹ውኀ ቅዱና ጋኖችን ምሏቸው›› ባላቸው ጊዜ በታዘዙት መሠረት ውኃውን ቀድተው ጋኖችን ሞሏቸው፡፡ ውኃውንም ክብር ይግባውና በአምላካዊ ችሎታው ወደ ወይን ጠጅ ለወጠው፤ ለአሳዳሪውም ሰጠው፡፡ አሳዳሪው የወይን ጠጅ የኾነውን ውኀ ቀምሶ አደነቀ፤ ከወዴት እንደ መጣ ግን አላወቀም፡፡ ድንቅ በኾነ አምላካዊ ሥራ እንደ ተለወጠም አልተረዳም፡፡ ያን ምሥጢር የሚያውቀው ባለሰርጉ፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ውኀውን የቀዱ ሰዎች ናቸውና፡፡ ታዳሚዎችም ‹‹ሰው ዂሉ የተሻለውን ወይን አስቀድሞ ያቀርባል፤ በኋላም ተራውን የወይን ጠጅ ያቀርባል፡፡ አንተስ መናኛውን ከፊት አስቀድመህ ያማረውን ከኋላ ታመጣለህን?›› በማለት አደነቁ፡፡

ቀድሞም የአምላክ ሥራ እንደዚህ ነው፤ ብርሃን ከመፍጠሩ አስቀድሞ ጨለማን ፈጥሯል፤ ከጨለማ ቀጥሎ ‹‹ብርሃን ይኹን!›› በማለት ብርሃንን ፈጥሯል፡፡ መጀመሪያ ብርሃን ተፈጥሮ ኋላ ጨለማ ቢፈጠር ይከብድ ነበርና መጀመሪያ ፳፩ ፍጥረታት ፈጥሯል፡፡ በመጨረሻም በአርአያውና በአምሳሉ የሰው ልጅን ፈጥሯል፡፡ ናትናኤልንም፤- ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ከዚህ የሚበልጥ ታያለህ›› ብሎታል፡፡ ይህንን ማለቱም የእግዚብሔር ሥራ እየቆየ ውብ፣ ያማረ መኾኑን ያመለክታል፤ ሰው ግን ‹‹የወደዱትን ቢያጡ ያጡትን ይቀላውጡ›› እንዲሉ ጥሩ ነው የሚለውን ነገር ያስቀድማል፤ ያ ሲያልቅበት ደግሞ የናቀውን መፈለግ ይጀምራል፡፡

ተራውን ከፊት፣ ታላቁን ከኋላ ማድረግ የእግዚአብሔር ልማዱ ነው፡፡ ለሰው ልጅ በመጀመሪያ የተሰጠው የሚያልፈው ዓለም ነው፤ በኋላም የማያልፈው መንግሥተ ሰማያት ይሰጠዋል፡፡ ሰው መጀመሪያ ይሞታል፤ በመጨረሻ ትንሣኤ አለው፡፡ ሰው መጀመሪያ ሲወለድ ርቃኑን ነው፤ በኋላ የጸጋ ልብስ ይለብሳል፤ ሀብታም ይኾናል፡፡ ሰው ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ዓለምን የሚያገኛት፣ የሚተዋወቃት በልቅሶ ነው፤ በኋላ ግን ይደሰታል፡፡ ተመልሶ በኀሣር፣ በልቅሶ ወደ መቃብር ይወርዳል፡፡ በደስታ ‹‹መቃብር ክፈቱልኝ? መግነዝ ፍቱልኝ?›› ሳይል ይነሣል፡፡ ይህን የአምላክ ሥራም አድንቆ መቀበል እንጂ መቃወም አይችልም፡፡

፪. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም

‹‹ወሀለወት ህየ እሙ ለእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስየጌታ እናት ከዚያ ነበረች፤›› እንዲል፡፡ የተገኘችውም እንዲያው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ በደግ ሰው ልማድ ተጠርታ እንጂ፡፡ ይህም እመቤታችን በማኅበራዊ ሕይወት የነበራትን ተሳትፎ እና በሰዎች ዘንድ የነበራትን ክብር ያመለክታል፡፡ በሌላ መልኩ በቤተ ዘመድ ልማድ ማንኛውም ዘመድ እንደ ተጠራው ዂሉ እርሷም በገሊላ በነበሩት ሰዎች ዘንድ ታላቅና ቤተ ዘመድ በመኾኗ በዚህ ሰርግ ተጠርታ ነበር፡፡ የተገኘችበት ሰው ሰውኛው ምክንያት ይህ ቢኾንም በዚያ ሰርግ ቤት ማንም ሊሠራው የማይችል የሥራ ድርሻ ነበራት፡፡

ይህ በሰዎች ዘንድ የማይታወቅ በእግዚአብሔርና በእርሷ መካከል ያለ አማላጅነት ነው፡፡ ይኸውም የጎደለውን መሙላት ለሚችል ውድ ልጇ የጎደለውን እንዲሞላ ማማለድ ነው፡፡ እመቤታችን ከሰው ልጆች የተለየች ክብርት፣ ቅድስት፣ ንጽሕት፣ ልዩ በመኾኗ የምታውቀው ምሥጢርም ከሰው የተለየ ነው፡፡ ‹‹ወእሙሰ ተዐቀብ ዘንተ ኩሎ ነገረ ወትወድዮ ውስተ ልባ፤ ማርያም ግን ይህንን ዂሉ ትጠብቀው፣ በልቧም ታኖረው ነበር፤›› /ሉቃ.፪፥፲፱/ የሚለው ቃልም ድንግል ማርያም አምላክን በመውለዷ ከሰው ልጆች የራቀ ምሥጢር እንደ ተገለጠላት ያስረዳል፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ‹‹ጸጋን የተሞላሽ›› በማለት የገለጠው ለእርሷ የተሰጠው ባለሟልነት ልዩ መኾኑን ለማስረገጥ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ በሰርጉ ቤት የምትሠራውን ሥራ በውል ታውቅ ነበር፡፡

 ፫. ቅዱሳን ሐዋርያት

መምህርን ጠርቶ ደቀ መዝሙርን መተው ተገቢ አይደለምና፤ ደቀ መዛሙርቱ ከመምህራቸው ከክርስቶስ ጋር አብረው በሰርግ ቤት ተገኝተው ተአምራቱን ተመልክተዋል፤ በተደረገው ተአምርም አምላክቱን አምነዋል፡፡ ሐዋርያት ከዋለበት የሚውሉ፤ ከአደረበት የሚያድሩ፤ ተአምራት የማይከፈልባቸው፤ ወንጌሉን ለማስተማር የተመረጡ ናቸውና፡፡  ምክንያቱም አየን ብለው እንጂ ሰማን ብለው ቢያስተምሩ አይታመኑምና፡፡

የሐዋርያት በሰርጉ ቤት መገኘትም ካህናት በተገኙበት ዕለት ሥርዓተ ጋብቻን መፈጸም ተገቢ መኾኑን ያስገነዝባል፡፡ በሰርግ ቤት የካህናት መገኘት እና ቡራኬ መስጠት አስፈላጊ ነውና፡፡ በፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፳፬ የተገለጸውም ይህ ትምህርት ነው፤ ‹‹ወማዕሰረ ተዋሰቦሶ ኢይትፌጸም ወኢይከውን ዘእንበለ በሀልዎተ ካህናት ወጸሎት ዘላዕሌሆሙ፤ የጋብቻ አንድነት ካህናት ቢኖሩ እንጂ ያለ እነርሱ አይጸናም፡፡ እነርሱ ጸሎት ሲያደርጉ እንጂ ያለ ጸሎት አይፈጸምም፤›› እንዲል፡፡ በጥንተ ፍጥረት ‹‹ሰው ብቻውን ይኾን ዘንድ መልካም አይደለም ረዳት እንፍጠርለት፤›› /ዘፍ.፪፥፲፱/ በማለት የተናገረ አምላክ ጋብቻ በካህናት ቡራኬና ጸሎት መከናወን እንደሚገባው ሲያስተምረን በቃና ዘገሊላው ሰርግ ቅዱሳን ሐዋርያትን ይዞ ተገኝቷል፡፡

በአጠቃላይ የቃና ዘገሊላ ሰርግ እና በሰርጉ ላይ የታዩ ተአምራት ምልጃዎች ዂሉ ሌላ ምሥጢርንም ያዘሉ ናቸው፡፡ እመቤታችን ‹‹የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም›› በማለት መናገሯ ሕዝብህን (ምእመናንን) ‹‹ደምህን አፍሰህ፣ ሥጋህንርሰህ አድናቸው›› ማለቷ ሲኾን፣ ይህም ‹‹ወይን›› በተባለው የልጇ የክርስቶስ ደም ቤዛነት ዓለም ይድን ዘንድ እመቤታችን ያላትን የልብ መሻት ያስገነዝባል፡፡ ‹‹ጊዜዬ ገና አልደረሰም›› የሚለው የጌታ ምላሽም ደሙ በዕለተ ዓርብ በመስቀል ላይ የሚፈስበት ጊዜ ገና መኾኑን ያመላክታል፡፡ በሰርግ ቤት የተገኘው በሥጋው መከራ ከመቀበሉ አስቀድሞ ነውና፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሐዋርያት በረከት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ጥምቀተ ክርስቶስ

timket-2

ጥምቀተ ክርስቶስ

በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ

ጥር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም  

በነቢያት የተነገረው ትንቢት በወንጌል የተጻፈው የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት ከዘጠኙ ታላላቅ በዓላት አንዱ ነው፡፡ ጥምቀት የሚለው ቃል ‹‹ተጠምቀተጠመቀ›› ካለው ግሥ የወጣ ነው፤ ትርጕሙም በውሃ መጠመቅ ማለት ሲኾን፣ ይኸውም በወራጅ ወንዝ፣ በሐይቅ ውስጥ ወይም በምንጭ የሚፈጸም ነው፡፡ በካህናት እጅ የሚፈጸመው ጥምቀት ከሌላው ጥምቀት ይለያል፡፡

በዘመነ ብሉይ ይፈጸም የነበረው ጥምቀት የንስሓ ጥምቀት ሲሆን በዘመነ ሐዲስ የሚፈጸመው ግን የልጅነት ጥምቀት ነው፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ከሁለቱም ልዩ ነው፡፡ እርሱ ሰውን ያከብራል እንጅ ከሰው ክብርን የማይፈልግ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ ለእኛ አርአያና አብነት ለመኾን በዮሐንስ እጅ በማየ ዮርዳኖስ ተጠምቆ የባሕርይ ልጅነቱንና አምላክነቱነን ከአብ እና ከመንፈሰ ቅዱስ አስመስክሮ ዕለቱን ገዳመ ቆሮንቶስ ገብቶ ጾምን ጀምሯል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው ሕግና የሠራው ሥርዓት እንደ እንግዳ ደራሽ እንደውሃ ፈሳሽ አይደለም፡፡ ቅድመ ዓለም በልብ የመከረውን ኋላም በነቢያት ያናገረውን ትንቢትና ምሳሌ፣ ያስቈጠረውን የዘመን ሱባዔ፣ ለአዳም የሰጠውን የመዳን ተስፋ ለመፈጸም ነው እንጂ፡፡ የተነገረውን ትንቢት፣ የተመሰለውን ምሳሌም እንደሚከተለው መጻሕፍት ይነግሩናል፤

‹‹ወአሜሃ መጽአ እግዚእ ኢየሱስ እምገሊላ ውስተ ዮርዳኖስ ከመ ይጠመቅ እምኀበ ዮሐንስ፤ ያን ጊዜ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ይጠመቅ ዘንድ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ›› /ማቴ.፫፥፲፫፤ ማር.፩፥፱፤ ሉቃ.፫፥፳፩፤ ዮሐ.፩፥፴፪/፡፡ ዮሐንስ ግን አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን? አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን ብሎ አይኾንም አለው፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከናዝሬት ወደ ዓይነ ከርም ኤልሳቤጥን ለመጠየቅ በመጣች ጊዜ የዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ ‹‹የጌታየ እናቱ እኔ ወደ አንቺ እመጣለሁ እንጂ አንቺ ወደኔ ትመጭ ዘንድ ይገባኛልን?›› ብላ ነበርና ከዚያ አያይዞ ተናግሮታል፡፡ ጌታም መልሶ ‹‹ይህ ለኛ ተድላ ደስታችን ነው፤ አንተመጥምቀ መለኮት› ተብለህ ክብርህ ሲነገር፤ እኔምበአገልጋዩ እጅ ተጠመቀ› ተብዬ ትሕትናየ ሲነገር ይኖራል፡፡ ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናልና አንድ ጊዜስ ተው›› አለው፡፡ አንድ ጊዜ ቢጠመቅ ሁለተኛ፤ በፈቃድ ቢጠመቅ በግድ፤ በሰውነቱ ቢጠመቅ በአምላክነቱ መጠመቅ አያሻውምና፡፡

ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ጌታም በዮሐንስ እጅ እንዲጠመቅ በነቢያት ትንቢት ተነግሯልና ጌታችን ‹‹ትንቢተ ነቢያትንም ልንፈጽም ይገባናል›› አለ፡፡ ዳግመኛም ይህ ለምእመናን ተድላ ነውና እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፤ እንደዚሁም ይህ ለባሕርይ አባቴ ለአብ፣ ለባሕርይ ልጁ ለእኔ፣ ለባሕርይ ሕይወቴ ለመንፈስ ቅዱስ ተድላ ደስታችን ነውና ማለቱ ነው፡፡ አንዱ አካል ወልድ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ በደመና ኾኖ ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር፤ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤›› ብሎ ሲመሠክር፤ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ተገልጧልና፡፡ ጌታችን ዮሐንስን ‹‹የጀመርነውንም የቸርነት ሥራ ልንፈጽም ይገባናል … አንድ ጊዜስ ተው›› ካለው በኋላም ተወው (ለማጥመቅ ፈቃደኛ ኾነ)፡፡

ዮሐንስም ‹‹አብ በአንተ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነው፡፡ አንተም በአብ በመንፈስ ቅዱስ ህልው ነህ፡፡ መንፈስ ቅዱስም በአንተና በአብ ህልው ነው፡፡ ሌላውን በአንተ ስም አጠምቃለው አንተን በማን ስም ላጥምቅህ?›› ቢለው ‹‹ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሃለነ አንተ ካህኑ ለዓለም በከመ ሢመቱ ለመልከ ጼዴቅ›› ብለህ አጥምቀኝ አለው፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ባሕር ወርደዋል፡፡ ‹‹ወተጠሚቆ እግዚእ ኢየሱስ ሶቤሃ ወፅአ እማይ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ከውኀው ወጣ፤›› /ዮሐ.፫፥፲፮/፡፡ ቃለ ወንጌል ‹‹ወናሁ ተርኅወ ሎቱ ሰማይ፤ ሰማይ ተከፈተለት›› ይላል፡፡ ይህን ሲልም በሰማይ መከፈት መዘጋት ኑሮበት አይደለም፡፡ የተዘጋ በር በተከፈተ ጊዜ በውስጡ ያለው ዕቃ በግልጽ እንዲታይ ጌታን ሲጠመቅ ከዚህ በፊት ያልተገለጸ ምሥጢር ታየ ሲል ነው፤ ይኸውም የሥላሴ አንድነት ሦስትነት ነው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹ጌታ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሔዶ መጠመቁ ለምንድን ነው? ምነው አገልጋይ ወደ ጌታው ይሔዳል እንጂ ጌታ ወደ አገልጋዩ ይሔዳልን? አገልጋይ በጌታው እጅ ይጠመቃል እንጂ ጌታ በአገልጋዩ እጅ ይጠመቃልን?›› የሚልጥያቄ ከተነሣ ጌታችን መምጣቱ ለትሕትና እንጂ ለልዕልና አይደለምና ነው፡፡ ዳግመኛም ለአብነት ነው፤ ጌታችን ዮሐንስን ‹‹መጥተህ አጥምቀኝ›› ብሎት ቢኾን ኖሮ ዛሬ ነገሥታት፣ መኳንንት ካህናትን ‹‹ከቤታችን መጥታችሁ አጥምቁን›› ባሉ ነበርና፡፡ ካህናት ካሉበት ከቤተ ክርስቲያን ሒዳችሁ ተጠመቁ ለማለት አብነት ለመኾን ራሱ ጌታችን ወደ ዮሐንስ ሔዶ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን መጠመቁም ለእርሱ ክብር የሚጨመርለት ኾኖ አይደለም፤ ዮርዳኖስን ብርህት ማኅፀን እንድትኾን ለማድረግ፤ እኛ ምእመናንም ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፣ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ዳግም ተወልደን መንግሥተ ሰማያት እንድንገባ ለማድረግ፤ እንደዚሁም ሥርዓተ ጥምቀትን ለማስተማርና አብነት ለመኾን ነው፡፡ ‹‹ዘኢተወልደ ዳግመ እማይ ወእመንፈስ ቅዱስ ኢይሬእያ ለመንግሥተ እግዚአብሔር፤ ዳግመኛ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ያልተወለደ ማለትም ያልተጠመቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም፡፡ … ዘአምነ ወዘተጠምቀ ይድኅን ወዘሰ ኢአምነ ወኢተጠምቀ ይደየን፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፡፡ ያላመነ ያልተጠመቀ ግን ይፈረድበታል፤›› ተብሎ ተጽፏልና /ዮሐ. ፫፥፫፤ ማር.፲፮፥፲፮/፡፡

ያውስ ቢኾን ጥምቀቱን በዮርዳኖስ ያደረገው ስለምን ነው? ቢሉ ትንቢቱን፣ ምሳሌውን ለመፈጸም ነው፤ ትንቢቱ፡- ‹‹ባሕርኒ ርእየት ወጐየት ወዮርዳኖስኒ ገብአ ድኅሬሁ፤ ባሕር አይታ ሸሸች፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ፡፡ … ርእዩከ ማያት እግዚኦ ርእዩከ ማያት ወፈርኁ፤ አቤቱ ውኆች አንተን አይተው ሸሹ፤›› ተብሎ ተነግሯል /መዝ. ፸፮፥፲፮፤ ፻፲፫፥፫/፡፡

ምሳሌው፡- ዮርዳኖስ ከላይ ነቁ (ምንጩ) አንድ ነው፤ ዝቅ ብሎ በደሴት ይከፈላል፤ ከታች ወርዶ ይገናኛል፡፡ ዮርዳኖስ ከላይ (ነቁ) ምንጩ አንድ መኾኑ የሰውም መገኛው (ምንጩ) አንድ አዳም ለመኾኑ፤ ዮርዳኖስ ዝቅ ብሎ በደሴት መከፈሉ እስራኤል በግዝረት፣ አሕዛብ በቍልፈት ለመለያየታቸው፤ ዮርዳኖስ ከታች በወደብ መገናኘቱ በክርስቶስ ጥምቀት ሕዝብና አሕዛብ አንድ ወግን ለመኾናቸው ምሳሌ ነው፡፡

ዳግመኛም አብርሃም ለአምስቱ ነገሥተ ሰዶም ረድቶ አራቱን ነገሥተ ኮሎዶጎሞር ድል ነሥቶ በተመለሰ ጊዜ ደስ ቢለው ‹‹በመዋዕልየኑ ትፌኑ ቃለከ ወሚመ ታርዕየኒሁ ኪያሃ ዕለተ፤ በዘመኔ ቃልህን (እግዚአብሔር ወልድን) ትልከዋለህን? ወይስ ያቺን የማዳንህን ቀን በዓይኔ ታሳየኝ ይኾን፤›› ብሎ በጠየቀው ጊዜ ‹‹ምሳሌውን ታያለህና ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድ፤›› ብሎታል፡፡ አብርሃምም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ቢሔድ መልከ ጼዴቅ ኅብስተ አኮቴት፣ ጽዋዓ በረከት ይዞ ተቀብሎታል፡፡ ይኸውም አብርሃም የምእመን፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት፤ መልከ ጼዴቅ የካህናት፤ ኅብስተ አኰቴት፣ ጽዋዓ በረከት የሥጋው የደሙ ምሳሌ ነው /ዘፍ. ፲፬፥፲፫-፳፬/፡፡

ኢዮብና ንዕማን በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠምቀው ከደዌያቸው ድነዋል /፪ኛነገ.፭፥፰-፲፱/፡፡ ኢዮብና ንዕማን የአዳምና የልጆቹ፤ ደዌ የመርገመ ሥጋ፣ የመርገመ ነፍስ፤ ዮርዳኖስ የጥምቀት ምሳሌ ነው፡፡ ኢዮብ፣ ንዕማን፣ ጌታ የተጠመቁበት ዮርዳኖስ ወደቡ አንድ ነው፡፡ እንደዚሁም እስራኤል ከግብጽ ከወጡ በኋላ በኢያሱ ጊዜ ወደ ምድረ ርስት ሲሔዱ ከዮርዳኖስ ወንዝ ደረሱ፡፡ ታቦቱን የተሸከሙና ልብሰ ተክህኖ የለበሱት ሌዋውያን ካህናት በፊት በፊት ሲጓዙ ታቦቱን የሚያጅቡ ሕዝበ እስራኤል ከታቦቱና ከሌዋውያን ካህናት ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው ዮርዳኖስ ከላይና ከታች ተከፍሎላቸው በየብስ ተሻግረው ኢየሩሳሌም ገብተዋል፡፡ ምእመናንም በማየ ገቦ ተጠምቀው ገነት መንግሥተ ሰማያት ለመግባታቸው ምሳሌ ነው፡፡

ኤልያስም ዮርዳኖስን ተሻግሮ ብሔረ ሕያዋን ገብቷል፡፡ የኤልያስ ደቀ መዝሙር ኤልሳዕ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በዮርዳኖስ ዳር እንጨት ሲቈርጡ መጥረቢያው ከውኀው ውስጥ ወደቀ፡፡ ኤልሳዕ የእንጨት ቅርፊት በትእምርተ መስቀል አዘጋጅቶ ምሳሩ ከወደቀበት ላይ ቢጥልበት የማይዘግጠው ቅርፊት ዘግጦ የዘገጠውን ብረት አንሳፎ አውጥቶታል፡፡ እንደዚሁም ዅሉ በባሕርዩ ሕማም ሞት የሌለበት አምላክ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ፣ በቀራንዮ በዕፀ መስቀል ተሰቀሎ፣ ከጎኑ ጥሩ ውኀና ትኩስ ደም አፍስሶ በሲኦል የወደቀው አዳምን ለማዳኑ ምሳሌ ነው /፪ኛነገ. ፮፥፩–፯/፡፡ ይህንን ዅሉ ምሳሌ ለመፈጸም ጌታችን በዮርዳኖስ ተጠምቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት ምሥጢር ምንድን ነው? ቢሉ ዲያብሎስ በአዳምና በሔዋን የጨለማ መጋረጃ ጋርዶ አገዛዝ ስቃይ አጸናባቸው፡፡ ከዚያም ‹‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስአዳም የዲያብሎስ ተገዥ፤ ሔዋንም የዲያብሎስ ተገዥ አገልጋዮች ነን› ብላችሁ ስመ ግብርናታችሁን (የተገዥነታችሁን ስም) ጽፋችሁ ብትሰጡኝ መከራውን አቀልላችሁ ነበር›› አላቸው፡፡ እነሱም መከራው የሚቀልላቸው መስሏቸው ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን ዓመቱ ለዲያብሎስ›› ብሎ በማይጠፋ በሁለት ዕብነ ሩካም (ዕብነ በረድ) ጽፎ አንዱን በዮርዳኖስ፤ አንዱን በሲኦል ጥሎት ይኖር ነበር፡፡ በዮርዳኖስ የጣለውን ጌታችን ሲጠመቅ እንደ አምላክነቱ አቅልጦ እንደ ሰውነቱ ተረግጦ አጥፍቶልናል፡፡ በሲኦል የጣለውንም በዕለተ ዓርብ በአካለ ነፍስ ወርዶ ነፍሳትን ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ ሲያወጣ አጥፍቶልናል፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ የተጠመቀበት አንደኛው ምሥጢርም ይህ ነው፡፡

ጌታችን ጥምቀቱን በውኀ ያደረገው በሌላ ያላደረገው ስለምንድን ነው ቢሉ ትንቢቱ፣ ምሳሌው ሊፈጸም፤ ትንቢት፡- ‹‹ወእነዝኃክሙ በማይ ወትነጽሑ፤ ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ፤ እናንተም ትጠራላችሁ፤›› ተብሎ ተነግሯል /ሕዝ.፳፮፥፳፭/፡፡ ምሳሌ፡- ውኀ ለዅሉ አስፈላጊ ነው፡፡ ያለ ውኀ መኖር የሚችል የለም፡፡ ጥምቀትም ለዅሉም የሚገባ ሥርዓት ነው፡፡ ያለ ጥምቀት ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት አይቻልምና፡፡ ውኀ መልክ ያሳያል፤ መልክ ያለመልማል (ያጠራል)፡፡ ጥምቀትም መልክዐ ነፍስን ያሳያል፤ መልክዐ ነፍስን ያለመልማልና (ያጠራልና)፡፡

መንፈስ ቅዱስ በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥበት አየ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል መውረዱም ምሥጢር አለው፡፡ ርግብ ኃዳጊተ በቀል ናት፤ መንፈስ ቅዱስም ኃዳጌ በቀል ነውና፡፡ ርግብ በኖኅ ጊዜ ‹‹ሐጸ ማየ አይኅ ነትገ ማየ አይኅ፤ የጥፋት ውኀ ጎደለ›› ስትል ቆጽለ ዕፀ ዘይት ይዛ ተገኝታለች፡፡ መንፈስ ቅዱስም ተስፋ መስቀልን ያበሥራልና፡፡ ጥምቀቱን በቀን ያላደረገው በሌሊት ያደረገው ስለ ምን ነው ቢሉ በቀን አድርጎት ቢኾን መንፈስ ቅዱስ በቁሙ ርግብ ነው በተባለ ነበርና፤ አሁንስ ርግብ አለመኾኑ መንፈስ ቅዱስ መኾኑ በምን ይታወቃል ቢሉ ጌታ የተጠመቀው ከሌሊቱ በዐሥረኛው ሰዓት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ተሐዋስያን ወፎች (ርግቦች) ከየቦታቸው አይወጡምና መንፈስ ቅዱስ መኾኑ በዚህ ይታወቃል፡፡

መንፈስ ቅዱስም መውረዱ ከውኀው ከወጣ፣ ከዮሐንስ ከተለየ በኋላ ነው፡፡ ከውኀው ውስጥ ሳለ ወርዶ ቢኾን ለቀድሶተ ማያት ነው የወረደው ባሉት ነበርና፡፡ ከዮሐንስ ጋርም ሳለ ወርዶ ቢኾን ለክብረ ዮሐንስ ወረደ ባሉት ነበርና፡፡ ረቦ ወርዷል ያሉ እንደ ኾነ አብ ምሉዕ ነው፤ አንተም ምሉዕ ነህ፤ እኔም ምሉዕ ነኝ ሲል፡፡ አሰይፎ ወርዷል ያሉ እንደ ኾነ የብሉየ መዋዕል የአብ ሕይወት ነኝ፤ የአንተም ሕይወት ነኝ፤ እኔም ብሉየ መዋዕል ነኝ ሲል፡፡ ወርዶ ራሱን ቆንጠጥ አድርጎ ይዞታል ቢሉ አብ አኃዜ ዓለም ነው፤ አንተም አኃዜ ዓለም ነህ፤ እኔም አኃዜ ዓለም ነኝ ሲል፡፡ ምሥጢሩም እናንተም ብትጠመቁ መንፈስ ቅዱስ ይወርድላችኋል ለማለት፣ አብነት ለመኾን ነው፡፡

‹‹ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ ለተዋሕዶ የመረጥኩት በእርሱ ህልው ኾኜ ልገለጥበት የወደድኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው፤›› የሚል ቃል ከወደ ሰማይ ተሰማ፡፡ ይህም አብ የተናገረበት ቃል ያው የሚጠመቀው አካላዊ ቃል ነው እንጂ ሌላ ቃል አይደለም፡፡ የሥላሴ ልብ፣ ቃል፣ እስትንፋስ አንድ ነውና፡፡ አብ ልብ፤ ወልድ ቃል፤ መንፈስ ቅዱስ እስትንፋስ በመኾን አንድ አምላክ ነውና፡፡ ‹‹አብኒ ልቡናሆሙ ለወልድ ወለመንፈስ ቅዱስ ወልድኒ ቃሎሙ ለአብ ወለመንፈስ ቅዱስ ወመንፈስ ቅዱስኒ እስትንፋሶሙ ለአብ ወለወልድ፤ አብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ልቡናቸው ነው፡፡ ወልድም ለአብ ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስም ለአብ ለወልድ ሕይወታቸው ነው፤›› በማለት ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት እንደ ተናገረው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀውም በሠላሳ ዓመቱ ነው /ሉቃ. ፫፥፳፫/፡፡ በሠላሳ ዓመቱ የተጠመቀበት ምሥጢርም አዳም የሠላሳ ዓመት፤ ሔዋን የዐሥራ አምስት ዓመት ሰው ኾነው ተፈጥረው አዳም በዐርባ ቀን፣ ሔዋን በሰማንያ ቀን ከሥላሴ የተቀበሉትን ልጅነት በምክረ ከይሲ ዕፀ በለስን በልተው አስወስደው ነበረና በሠላሳ ዓመቱ ተጠምቆ መልሶላቸዋል፡፡ በሠላሳ ዓመት የመጠመቁ ምሥጢር ይህ ሲኾን እኛ ዛሬ ወንዶች በዐርባ ቀን፣ ሴቶች በሰማንያ ቀን በዕለተ ዓርብ ከቀኝ ጎኑ በፈሰሰው ማየ ገቦ ተጠምቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ሁለተኛ የምንወለድበት ምክንያትም አዳም በዐርባ ቀኑ፣ ሔዋን በሰማንያ ቀኗ ከሥላሴ ያገኙትን ልጅነት መሠረት በማድረግ ነው /ኩፋ. ፬፥፱/፡፡ የምንጠመቀውም በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ነው፡፡ ‹‹ወእንዘ ታጠምቅዎሙ በሉ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤ ስታጠምቋቸውም በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፤›› እንዲል /ማቴ. ፳፰፥፲፱/፡፡

ዛሬም ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድ በዓለ ጥምቀቱን ለሚያከብሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከታቦታቱ ሁለት ሺሕ ክንድ ርቀው መከተል እንዲገባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፤ ‹‹ሕዝቡን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ሌዋውያን ካህናት ተሸክመውት ባያችሁ ጊዜ ከሰፈራችሁ ተነሥታችሁ ተከተሉት፡፡ በእናንተና በታቦቱ መካከል ያለው ርቀት በስፍር ሁለት ሺሕ ክንድ ይኹን፡፡ በዚህ መንገድ በፊት አልሔዳችሁበትምና፤ የምትሔዱበትን መንገድ እንድታውቁ ወደ ታቦቱ አትቅረቡ፤›› /ኢያ.፫፥፩–፲፯/፡፡

ይህ ኃይለ ቃል ዛሬ ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው ለማደራቸው መነሻ ትምህርት ነው፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀትም ጌታችን ከተጠመቀበት ከ፴ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ሲከበር ይኖራል፡፡

ከበዓለ ጥምቀቱ ረድኤት፣ በረከት ይክፈለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

አስተርእዮ

በመምህር  ለማ በእርሱፈቃድ

ጥር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ  የመሳሰሉትን ፍች ይይዛል፡፡ ቃሉ አስተርአየ ታየ፤ ተገለጠ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የጥር ወር በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት (የታየበት) ወቅት በመኾኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ያለው ጊዜ ዘመነ አስተርእዮ ይባላል፡፡ ይህ ብቻም ሳይኾን የእግዚአብሔር አንድነት፣ ሦስትነት የተገለጠው በዚሁ ወር ነውና ወቅቱ ዘመነ አስተርእዮ ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ የመታየቱ (የመገለጡ) ዋና ዋና ምክንያቶችን ምንድን ናቸው የሚሉ ነጥቦችን በአጭሩ እንመለከታለን፤

፩. የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ

እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን በምሳሌው ፈጥሮ የሚያስፈልገውን ዅሉ አዘጋጅቶ በክብር ይኖር ዘንድ ገነትን አወረሰው፡፡ በማየት የሚደሰትበትና የሚማርበትንም ሥነ ፍጥረትን ፈጠረለት፤ የሚበላውንና የማይበላውንም ለይቶ ሰጠው፡፡ ነገር ግን አትብላ የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ሳይጠብቅ የተከለከለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ ምክንያት ከገነት ተባረረ /ዘፍ.፪፥፲፮/፡፡ በዚያን ጊዜ ነው ርኅራኄ የባሕርዩ የኾነ አምላካችን ‹‹ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው›› የሚለውን የተስፋ ቃል ኪዳን ለአዳም የሰጠው /ሲራ.፳፬፥፮/፡፡

ነቢያቱም ‹‹ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፡፡ ስሙንምአማኑኤል› ብላ ትጠራዋለች፤›› እያሉ ትንቢት ሲናገሩ ቆይተዋል /ኢሳ.፯፥፲፬/፡፡ አዳምም ከነልጆቹ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመናት ይህንን ቃል ኪዳን ሲጠባበቅ ኖሯል፡፡ ‹‹ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ኢሳ.፳፮፥፳/፣ ይህችን ቃል ኪዳን ይፈጽማት ዘንድ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ በሥጋ ተገለጠ ማለት ሥጋን ተዋሐደ፡፡

፪. የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ

‹‹ወዘሰ ይገብራ ለኀጢአት እምነ ጋኔን ውእቱ እስመ ቀዳሚሁ ለሰይጣን አበሰ ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለጋኔን፤ ኀጢአትን የሚሠራትም ከዲያብሎስ ወገን ነው፡፡ ጥንቱንም ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ፡፡ የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ፤›› በማለት ሐዋርያው እንደ ገለጸው /፩ኛዮሐ.፫፥፰/፣ ሰይጣን የሰውን ልጅ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን የመሰለ ቦታ እንዲያጣ፤ ከደስታ ወደ ዘለዓለም ኀዘን፣ ከነጻነት ወደ ግዞት፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ እንዲገባ ረቂቅ ሥራ ሠርቶ ነበርና ይህንን የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ እግዚአብሔር በሥጋ ተገለጠ፡፡

ዲያብሎስ በሥጋ ከይሲ (በእባብ ሥጋ) ተሰውሮ ነገት ገብቶ አዳምና ሔዋንን እንዳሳተ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሥጋ ተዋሕዶ የዲያብሎስን ሥራ አፍርሶበታል፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን አስቶ የግብር ልጆቹ ይኾኑ ዘንድ ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለደያብሎስ›› ብለው የፈረሙትን ደብዳቤ፣ በዮርዳኖስና በሲዖል የቀበረውን የጥፋት የተንኮል ሥራውን ያፈርስ ዘንድ አምላክ ሰው ኾኖ ተገለጠ፡፡

ይህንን የዲያብሎስ ሥራም በዮርዳኖስ ባሕር የተቀበረውን በጥምቀቱ፤ በሲዖል የተቀበረውን በስቅለቱ፣ በሞቱ ደምስሶበታልና ‹‹ወነሰተ ዐረፍተ ማእከል እንተ ጽልዕ በሥጋሁ፤ በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በለበሰው ሥጋ አፈረሰው፤›› በማለት ሐዋርያው እንደ ተናገረው /ኤፌ.፪፥፲፬/፣ የዲያብሎስን ክፉ ሥራ የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡

፫. አንድነቱን፣ ሦስትነቱን ይገልጥ ዘንድ

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጥ አይታወቅም ነበር፡፡ የተገለጠ፣ የታወቀ፣ የተረዳ የአንድነቱን፣ የሦስትነቱን ትምህርት በሚገባ ለማስተማር የተቻለው ጌታችን ሥጋ ለብሶ ከተጠመቀ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ‹‹ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ በአምሳለ ርግብ ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እግዚአብሔር አብ በደመናየምወደው፣ ለመሥዋዕትነት የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው› አለ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፫፥፲፯፤ ሉቃ.፫፥፳፩/፣ ጌታችን የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ለመሻር በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነት እና ሦስትነት ምሥጢር ተገልጿል፡፡ ይህ ምሥጢር ከጥንተ ዓለም ጀምሮ በግልጽ ሳይታወቅ፣ ሳይገለጥ ተሰውሮ ይኖር ነበር፡፡ ‹‹በእንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅቡእ ኅርመቱ እምቅድመ ዓለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር ተሰውሮ ነበር፡፡ ከነቢያት ቃል የተነሣ በዚህ ዘመን ተገለጠ፤›› እንዲል /ሮሜ.፲፮፥፳፬/፡፡

፬. ፈጽሞ እንደ ወደደን ለመግለጽ

እግዚብሔር ሰውን ምን ያህል እንደ ወደደው ለመረዳት እግዚብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነውና፡፡ ማንም ሳያስገድደው፤ ሰው ኹን ብሎ ሳይጠይቀው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ዘመኑን ጠብቆ እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ከኀጢአት በስተቀር ዅሉን ፈጽሞ፣ በገዛ ፈቃዱ መከራ ሥጋን ተቀብሎቈ ሥጋውን ቈርሶ፣ ደሙን አፍሶ የዘለዓለም ሕይወትን ለሰው ልጅ በመስጠቱ ምን ያህል ፍጹም ፍቅሩን እንደ ገለጸልን እንረዳለን፡፡ ‹‹አልቦ ዘየዐቢ እምዝ ፍቅር ከመ ዘቦ ዘይሜጡ ነፍሶ ህየንተ አእርክቲሁ፤ ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ያለ እንደ ኾነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም፤›› እንዳለ ወንጌላዊው /ዮሐ.፲፭፥፲፪/፡፡

በደል የሠራው የሰው ልጅ ይሰቀል ይሙት ሳይል እኔ ልሙት ማለቱ የእግዚአብሔር የፍጹም ፍቅሩ መገለጫ ነው፡፡ ሰው ሰውን የሚወደው ገንዘቡንና የመሳሰሉትን እስከ መስጠት ሊኾን ይችላል፡፡ ሕይወቱን እስከ መስጠት የሚወድ ማንም የለም፤ አልነበረም፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደውን የሰውን ሥጋ ለብሶ መኪራ ሥጋን ተቀብሎ ሰውን በሞቱ ያድን ዘንድ ሞትን የሞተው ፈጽሞ እንደ ወደደን ለመግለጥ ነው /፩ኛዮሐ.፬፥፱/፡፡ ይህም ፍቅሩ ይቃወቅ ዘንድም በሥጋ ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ሊቃውንቱ ይህንን ወቅት ‹‹አስተርእዮ›› በማለት ሰይመውታል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ፡- ይህ ትምህርት ጥርቀን ፳፻፭ .ም በድረ ገጻችን ቀርቦ ነበር፡፡

አስተርእዮተ እግዚአብሔር በፈለገ ዮርዳኖስ

bb

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲጠመቅ

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ቀን ፳፻፱ .

የተወደዳችሁ የድረ ገጻችን ተከታታዮች! እንደሚታወቀው በየዓመቱ ጥር ፲፩ ቀን በዓለ ጥምቀትን እናከብራለን፡፡ በቅድሚያ ለብርሃነ ጥምቀቱ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያልን በዛሬው ዝግጅታችን እግዚአብሔር አምላካችን በሐዲስ ኪዳን ካደረጋቸው መገለጦች ወይም ከታየባቸው መንገዶች መካከል በዮርዳኖስ ወንዝ ያደረገው መገለጥ (አስተርእዮ) አንደኛው መኾኑን የሚያስገነዝብ ትምህርት በአጭሩ ይዘን ቀርበናል፤

‹‹አስተርእዮ›› የሚለው ቃል ‹‹አስተርአየ (አርአየ) = አሳየ፣ ገለጠ፣ ታየ፣ ተገለጠ›› ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ሲኾን፣ ትርጕሙም ‹‹መታየት፣ መገለጥ፣ ማሳየት፣ መግለጥ›› ማለት ነው /የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት/፡፡ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር በፈለገ ዮርዳኖስ›› የሚለው ሐረግም ‹‹የእግዚአብሔር በዮርዳኖስ ወንዝ መገለጥ፣ መታየት›› የሚል ትርጕም አለው፡፡

ከዚህ ላይ ‹‹አስተርእዮተ እግዚአብሔር›› ስንል የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ መገለጥ ማለታችን መኾኑን ለማስታዎስ እንወዳለን፡፡ ‹‹እግዚአብሔር›› የሚለው ቃል ሦስቱም አካላት (ቅድስት ሥላሴ) በጋራ የሚጠሩበት መለኮታዊ ስያሜ ነውና፡፡ ‹‹አንሰ ሶበ እቤእግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ በአሐዱ ስም ሥሉሰ ያምልኩ፤ እኔ እግዚአብሔር በአልሁ ጊዜ ስለ አብም፣ ስለ ወልድም፣ ስለ መንፈስ ቅዱስም እናገራለሁ፤ (ምእመናን) በአንዱ ስም (በእግዚአብሔር) ሦስቱ አካላትን ያመልኩ ዘንድ፤›› እንዳለ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ነባቤ መለኮት /ሃይማኖተ አበው/፡፡

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እግዚአብሔር አምላክ በብሉይም ኾነ በሐዲስ ኪዳን በአንድነቱ በሦስትነቱ በግብር (በሥራ)፣ በራእይና በገቢረ ተአምራት በልዩ ልዩ መንገድ ለቅዱሳኑ ተገልጧል፡፡

በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ምልክት በማሳየት፤ በቅዱሳን ነቢያትና በመሳፍንት፣ በነገሥታት፣ በካህናትና በነቢያት ላይ በማደር ወይም በራእይ በማነጋገር፤ በተጨማሪም በጻድቃኑ ላይ ቸርነቱን በማሳየት፣ በክፉ አድራጊዎች ላይ ደግሞ ኀይሉን በማሳየት ሲያደርጋቸው በነበሩ ተአምራቱና ሥራዎቹ ይገለጥ ነበር፡፡

በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ለአዳምና ለልጆቹ በገባው ቃል መሠረት የሰውን ሥጋ ለብሶ፣ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በአካለ ሥጋ ተገልጦ በገቢረ ተአምራቱ፣ በትንሣኤውና በዕርገቱ አምላክነቱን አሳይቷል፡፡

የብሉይ ኪዳኑ መገለጥ በምልክት፣ በራእይ፣ በድምፅና በመሳሰሉት መንገዶች የተደረገ መገለጥ ነበር፤ የሐዲስ ኪዳኑ መገለጥ ግን ወንጌላዊው ዮሐንስ ‹‹መቼም ቢኾን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው›› /ዮሐ.፩፥፲፰/ በማለት እንደ ገለጸው አምላካችንን በዓይነ ሥጋ ያየንበት አስተርእዮ ስለ ኾነ ከመገለጦች ኹሉ የተለየ ጥልቅ ምሥጢር አለው፡፡

ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር በሥጋ ያደረገውን አስተርእዮ (መገለጥ) ከምሥጢረ ሥላሴ ጋር በተያያዘ መልኩ በሦስት መንገድ ይገልጹታል፤ ይኸውም በእመቤታችን ማኅፀን፤ በዮርዳኖስ ወንዝ እና በደብረ ታቦር ተራራ ላይ እንደ ኾነ ያስረዳሉ፡፡

ይህንንም ‹‹በላዕሌኪ ወበዮርዳኖስ ወበታቦር ሥልሰ ጊዜያተ፤ ዘአልቦ ተውሳከ ወአልቦ ሕጸተ፤ ለውሉደ ሰብእ ያርኢ ዘሥላሴሁ ገጻተ፤ ጽጌኪ ድንግል ተአምሪሁ ከሠተ፤ ወበፀዳሉ አብርሀ ጽልመተ፡፡›› በማለት ይገልጹታል /ማኅሌተ ጽጌ/፡፡

ትርጕሙም ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ጭማሬም ጉድለትም የሌለበትን ሦስትነቱን ለሰው ልጆች ያሳይ ዘንድ በአንቺ (በእመቤታችን በድንግል ማርያም) በዮርዳኖስ እና በደብረ ታቦር ሦስት ጊዜ በመገለጥ አበባሽ (ልጅሽ) ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምራቱን (አምላክነቱን፣ ብርሃነ መለኮቱን፣ አንድነቱን፣ ሦስትነቱን) አሳየ፡፡ በብርሃነ መለኮቱም ጨለማውን አስወገደ (ብርሃን አደረገ)›› ማለት ነው፡፡

ይህም ጌታችን በለበሰው ሥጋ በእመቤታችን ማኅፀን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን መወሰኑን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀበት ዕለት ምሥጢረ ሥላሴን መግለጡን (እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነው፤ እርሱን ስሙት›› ብሎ  ሲመሰክር፣ መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ ራሱ ላይ ሲያርፍ ማለት ነው)፤ እንደዚሁም በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጥ መለኮታዊ አንድነቱና አካላዊ ሦስትነቱ መታወቁን ያመለክታል፡፡

በአጭሩ ይህ ድርሰት እግዚአብሔር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ላይ ያደረገውን አስተርእዮ የሚገልጽ ነው፡፡ ይህ ትምህርትም ጥር ፲፩ ቀን በሚነበበው መጽሐፈ ስንክሳር በተመሳሳይ መልኩ ተጠቅሷል፡፡

ክብር ይግባውና በአካለ ሥጋ የተገለጠው እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) እከብር አይል አምላከ ክቡራን፣ አክባሬ ፍጥረታት፤ እቀደስ አይል አምላከ ቅዱሳን፣ ቀዳሴ ፍጥረታት ኾኖ ሳለ ለኛ የጥምቀትን ሥርዓት ሊሠራልን ሥጋ ከለበሰ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው በመጥምቀ መለኮት በቅዱስ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተጠምቆ ከወንዙ ሲወጣም እነሆ ሰማያት ተከፈቱ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ፡፡ በዚህ ጊዜ የሚሰሙትን ዅሉ ያስደነገጠ፣ ምድራዊ ፍጥረት ሊሸከመው የማይቻል ‹‹ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘሎቱ ሠመርኩ፤ በእርሱ ደስ የሚለኝ፣ ልመለክበት የወደድሁት፣ ለተዋሕዶ የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው!›› የሚል ግሩም ቃል ከሰማይ መጣ /ማቴ.፫፥፲፯/፡፡

ይህ እግዚአብሔር አብ የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አባት መኾኑን የመሰከረበት ቃልም ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር በገለጠበት ዕለት በተመሳሳይ መንገድ ተነግሯል /ማቴ.፲፯፥፭፤ ሉቃ. ፱፥፴፮፤ ፪ኛ ጴጥ.፩፥፲፯/፡፡ ከዚህ በፊት በልዩ ልዩ ምሳሌና ኅብር ሲገለጥ የነበረ ምሥጢረ ሥላሴ በዮርዳኖስ ወንዝ በግልጥ ታየ፤ እግዚአብሔር ወልድ በለበሰው ሥጋ በዮርዳኖስ ወንዝ ሲጠመቅ፤ እግዚአብሔር አብ ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ አባትነቱን ሲመሰከር፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ከሰማይ ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ ፍጡራን በዓይናቸው አዩ፡፡

ይህንን ድንቅ ምሥጢር የተመለከቱ ዅሉ የእግዚአብሔርን ሥራ አደነቁ፤ በአምላክነቱም አመኑ፡፡ ሰይጣን ልቡናቸውን ያሸፈተባቸው መናፍቃን ግን በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ባለማመናቸው የተነሣ ለክብሩ በማይመጥን የአማላጅነት ቦታ ያስቀምጡታል፡፡ እኛ ግን ቅዱሳን ሐዋርያት እንዳስተማሩን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም እንዳስረዱን አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ መለኮት፣ አንድ ሥልጣን፣ አንድ አገዛዝ አላቸው፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል እግዚአብሔር፣ በሦስትነት በአንድነት የሚመለክ፣ አምላክ ወልደ አምላክ ነው ብለን እናምናለን፤ አምነንም እንመሰክራለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ታላቅ የምሥራች ለኦርቶዶክሳውያን ምእመናን!

app-01

በማኅበረ ቅዱሳን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል የተሠራው ‹‹ተዋሕዶ›› የተሰኘው የስልክ አፕሊኬሽን አንድሮይድ (Android) የተባለውን የቴክኖሎጂ ውጤት ለሚጠቀሙ ዘመናዊ ስልኮች እና የኪስ ኮምፒውተሮች አመቺ በኾነ መልኩ እንደገና ተሻሽሎ ቀረበ፡፡

ይህ አፕሊኬሽን በ፳፻፮ ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲኾን፣ ክፍሉ ከተጠቃሚዎቹ የደረሱትን አስተያየቶች በማካተት ልዩ ልዩ ማሻሻያዎችን አድርጎ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲቀርብ አድርጓል፡፡

አፕሊኬሽኑ በውስጡም የጸሎት መጻሕፍትን፣ ወቅታዊ የኾኑ መንፈሳዊ ትምህርቶችን፣ ዜናዎችን እና ልዩ ልዩ መረጃዎችን፤ ያሬዳውያን መዝሙሮችን፣ መንፈሳዊ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶችን፤ እንደዚሁም የየዕለቱ ምንባባትን እና የሬዲዮ ሥርጭቶችን፤ የቀን መቍጠሪያዎችን፣ የበዓላትና አጽዋማት ማውጫዎችን፤ በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ፣ በካናዳ እና በአውሮፓ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የሚከናወኑ መርሐ ግብራትንና ሌሎችንም አርእስተ ጉዳዮች አካቷል፡፡

በልዩ ልዩ የመገናኛ መንገዶችና ገጾች ላይ በሃይማኖት ስም የሚጻፉ የኑፋቄ ትምህርቶች በስፋት በሚለቀቁበት በዚህ ዘመን ይህ የቴክኖሎጂ ውጤት መዘጋጀቱ ለምእመናን ታላቅ የምሥራች ነው፡፡

ስለዚህም አንድሮይድ (Android) የተሰኘውን የቴክኖሎጂ ውጤት መጠቀም የሚችል ዘመናዊ ስልክ ወይም የኪስ ኮምፒዩተር ያላችሁ ምእመናን ዅሉ ከጎግል ፕለይ (Google Play) ውስጥ ተዋሕዶ (Tewahedo) የሚለውን ቃል በመፈለግ በዚህ አፕሊኬሽን እንድትጠቀሙና ኦርቶዶክሳዊ ይዘት ባለው ቃለ እግዚአብሔር ነፍሳችሁን እንድታጠግቡ፣ አእምሯችሁንም በመንፈሳዊ ዕውቀት እንድታጎለብቱ ስንል መንፈሳዊ ግብዣችንን እናቀርባለን፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት ክፍል ይኼንኑ አፕሊኬሽን አይ ኦ ኤስ (IOS)ን ለሚጠቀሙ የእጅ ስልኮች እና የኪስ ኮምፒውተሮች ከአሁን በፊት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡

ታላቁ የቅኔ ጉባኤ ቤት በእሳት ወደመ

chegodie

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ፰ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት በቋሪት ወረዳ ቤተ ክህነት ልዩ ስሙ ፈንገጣ በሚባል ቀበሌ በጨጎዴ ሐና የተቋቋመው፤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን ሲያፈራ የኖረውና እስከ አሁን ድረስም ሊቃውንትን የመተካት ተልእኮውን በመወጣት ላይ የሚገኘው የሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው የቅኔ ምስክር ጉባኤ ቤት ጥር ፯ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ረፋድ ላይ ድንገት በደረሰ የእሳት ቃጠሎ ወደመ፡፡

100_0718

የጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው ከከፊል ደቀ መዛሙርታቸው ጋር (ጉባኤ ቤቱ በእሳት ከመቃጠሉ በፊት)

በቦታው የተገኙ የዓይን እማኞች እንደሚያስረዱት በአካባቢው ያለው የአየር ጠባይዕ ነፋሻ ከመኾኑ፣ ጉባኤ ቤቱ ከእንጨትና ከሣር ከመሠራቱ ባሻገር ደቀ መዛሙርቱ ለክብረ በዓል በወጡበትና የአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን በሔዱበት ሰዓት ቃጠሎው መከሠቱ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል፡፡

ድንገት በደረሰው በዚህ የእሳት ቃጠሎ ሁለት መቶ ሃያ አምስት የደቀ መዛሙርት መኖሪያ ጎጆዎች፣ ልዩ ልዩ መጻሕፍት፣ ምግብ እና አልባሳት በአጠቃላይ ከሰባት መቶ ስልሳ ሦስት ሺሕ አምስት መቶ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የፍኖተ ሰላም ማእከል የላከልን ዘገባ ያመላክታል፡፡

ከማእከሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ጉባኤ ቤቱ ከአምስት መቶ እስከ ስድስት መቶ የሚደርሱ ደቀ መዛሙርት ይማሩበት የነበረ ሲኾን በአሁኑ ሰዓትም በከፊል ከቃጠሎው በተረፈው የጉባኤ ቤቱ ማኅበር ቤት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡

chegodie

የእሳት ቃጠሎው ያደረሰው ጉዳት በከፊል

የቋሪት ወረዳ ማእከል ከቦታው ያገኘውን መረጃ መሠረት አድርጎ ለዝግጅት ክፍላችን እንደ ገለጸው እሳቱ የተነሣው ከጉባኤ ቤቱ አጥር አካባቢ ሲኾን፣ እሳቱ በምን ምክንያትና በማን አማካይነት እንደ ተለኮሰ ለማረጋገጥ መንሥኤው በፖሊስ በመጣራት ላይ ይገኛል፡፡

ለደቀ መዛሙርቱ ምግብ፣ መጠለያና አልባሳት ድጋፍ ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚገባም የምዕራብ ጐጃም ሀገረ ስብከት ከፍኖተ ሰላም ማእከልና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመኾን ውይይት በማካሔድ ላይ እንደሚገኝ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ሥዩማን ቀሲስ አያና በላቸው ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

በመጨረሻም ጉባኤ ቤቱን ወደ ነበረበት ህልውና ለመመለስ፤ ደቀ መዛሙርቱን ከመበተንና የጉባኤውን ወንበርም ከመታጠፍ ለመታደግ እንችል ዘንድ ‹‹መላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፋችሁ አይለየን?›› ሲሉ ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው በጉባኤ ቤቱ ስም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ቤት ላይ በደረሰው ጉዳት ለጉባኤ ቤቱ መምህር ሊቀ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው፣ ለደቀ መዛሙርቱና ለአካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን መጽናናትን ይመኛል፡፡

ዕርገተ ኤልያስ ነቢይ

elias

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ጥር ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ ታኅሣሥ ፩ ቀን የነቢዩ ኤልያስን በዓለ ልደት፤ ጥር ፮ ቀን ደግሞ ዕለተ ዕርገቱን በመንፈሳዊ ሥርዓት ታከብራለች፡፡ የነቢዩን ታሪክ በአጭሩ ለማስታወስ ያህልም የሚከተለውን ዝግጅት አቅርበናል፤

ነቢዩ ኤልያስ በገለአድ አውራጃ በቴስብያ፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝና ሕግ ጸንተው ይኖሩ ከነበሩ ጻድቃን ወላጆቹ ከሌዊ ወገን ከሚኾን አባቱ ከኢያሴንዩ እና ከእናቱ ቶና ታኅሣሥ ፩ ቀን ተወለደ፡፡ በተወለደ ጊዜም እግዚአብሔር ከእናቱ ማኅፀን ጀምሮ መርጦታልና መላእክተ ብርሃን ሰገዱለት፤ በጨርቅ ፈንታም በእሳት ጠቀለሉት፡፡ እናትና አባቱም በኹኔታው ከመፍራታቸው የተነሣ ወደ እርሱ መቅረብን ፈሩ፡፡ በስምንተኛው ቀን ሥርዓተ ግዝረት ሲፈጽሙለትም ስሙን ‹ኤልያስ› አሉት፡፡

ነቢዩ ኤልያስ ሕገ ኦሪትን እየተማረ ካደገ በኋላ እናቱንና አባቱን፣ ዘመዶቹንም፣ ገንዘቡንም ዅሉ ትቶ በበረሃ ተቀመጠ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን መልእክቱ ፲፩፥፴፯-፴፰ ‹‹… ማቅ፣ ምንጣፍና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ተጨነቁ፤ ተቸገሩ፤ መከራ ተቀበሉ፤ ተራቡ፤ ተጠሙም፡፡ ዓለም የማይገባቸው እነዚህ ናቸው፤ ዱር ለዱርና ተራራ ለተራራ፣ ዋሻ ለዋሻና ፍርኩታ ለፍርኩታም ዞሩ፤›› በማለት እንደ ተገናረው ነቢዩም ከዓለማዊ ኑሮ ተለይቶ ማቅ ለብሶ በየተራራው፣ በየፍርኵታውና በየዋሻው መኖር ጀመረ /ገድለ ኤልያስ ነቢይ ዘታኅሣሥ፣ ቍ.፩-፱/፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደሚያስረዳው ‹‹ኤልያስ›› የሚለው ስም ‹‹እግዚአብሔር አምላክ ነው›› የሚል ትርጕም አለው፡፡ በመጽሐፈ ገድሉ እንደ ተጠቀሰው ደግሞ የስሙ ትርጓሜ ‹‹የወይራ ዘይት፣ የወይራ ተክል›› ማለት ነው፡፡ የወይራ ዘይት በጨለማ ላሉት ዅሉ እንዲያበራ ኤልያስም ለእግዚአብሔር ቤት መብራት ነውና፡፡ እስራኤላውያን ሕገ እግዚአብሔርን በመጣስ፣ ጣዖታትን በማምለክ ጨለማ በተዋጡ ጊዜ ነቢዩ ኤልያስ ደርሶ ሰማይን በመለጎም፣ የምንጮችን ውኃ በማድረቅና ሌሎችንም ድንቅ ድንቅ ተአምራት በማሳየት ልቡናቸውን ብሩህ አድርጎ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር መልሷቸዋልና፡፡ ዳግመኛም ኤልያስ ማለት ‹‹ዘይት (ቅባት)፣ መፈቃቀር›› ማለት ነው፡፡ ዘይት (ቅባት) የተባለውም የሰው ፍቅር ሲኾን ይኸውም ነቢዩ ኤልያስ በገቢረ ተአምራቱ በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል ሰላምንና ፍቅርን ማስፈኑን ያመላክታል /የገድለ ኤልያስ መቅድም፣ ቍ.፱-፲፱/፡፡

ነቢዩ በእግዚአብሔር ኀይል ካደረጋቸው ታላላቅ ተአምራት መካከልም ዝናም ማቆሙና ዳግመኛ እንዲዘንም ማድረጉ (፩ኛ ነገ.፲፯፥፩-፪፤ ፲፰፥፵፮-፵፰)፤ የደሃዋን ቤት በበረከት መሙላቱ (፩ኛ ነገ.፲፯፥፲፮-፳፬)፤ የሞተውን ልጅ ማስነሣቱ (፩ኛ ነገ.፲፯፥፳-፳፫)፤ በካህናተ ጣዖት ፊት መሥዋዕቱን ወደ እግዚአብሔር ማሳረጉና የጣዖቱ ካህናትን ማሳፈሩ (፩ኛ ነገ.፲፰፥፳-፵)፤ እና ጠላቶቹን በእሳት ማቃጠሉ (፪ኛ ነገ.፩፥፱-፲፫) ተጠቃሾች ናቸው፡፡

አንድ ቀን ነቢዩ ኤልያስ ጸሎት እያደረገ ሳለ መልአኩ ቅዱስ ራጉኤል ተገልጾ፡- ‹‹ኃላፊ፣ ጠፊ የኾኑ ሕሊናትን ያሸነፍህ፤ ሞትንም ድል ያደረግህ ተጋዳይ ሆይ ፈጽሞ ደስ ይበልህ፡፡ ወደ ሰማይ የምታርግበት ዘመን ደርሷልና፡፡ ፍጹም ደስታ፣ ፈገግታ፣ ተድላ ከሰፈነበት አገር ትኖራለህ፡፡ ደዌ፣ በሽታ፣ ሞት፣ ኀዘን ከሌለበት፤ በረከት፣ ከሞላበት ቤትም ትገባለህ፡፡ በዚያም የልዑል እግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጽፍ እንደ አንተ ያለ ሄኖክ አለ፡፡ አሁንም ተነሥና ዮርዳኖስን ተሻግረህ ሒድ›› አለው፡፡

እግዚአብሔር ኤልያስን ወደ ሰማይ የሚያሳርግበት ጊዜ ሲደርስም ነቢዩ ከጌልጌላ ተነሥቶ ወደ ኢያሪኮ ሲሔድ ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕ ‹‹በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አንተን አልለቅህም፤›› በማለት ተከትሎት ሔደ፡፡ ኢያሪኮ በደረሱ ጊዜም በኢያሪኮ ያሉ ደቂቀ ነቢያት መጡ፡፡ የኤልያስ ዕርገት በመንፈስ ቅዱስ ጥበብ ተገልጾላቸው ኤልሳዕን፡- ‹‹ዛሬ እግዚአብሔር ጌታህን ከአንተ እንደሚወስደው ታውቃለህን?›› አሉት፡፡ እርሱም፡- ‹‹አውቃለሁ፤ ዝም በሉ፤›› አላቸው፡፡ ከዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን ‹‹እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና ከዚህ ተቀመጥ›› ባለው ጊዜ አሁንም ‹‹በሕያው ነፍስህ እምላለሁ፤ አንተን አልለቅህም፤›› በማለት አብሮት ሔደ፡፡

ከነቢያት ወገንም አምሳ ወንዶች ከእነርሱ ጋር በአንድነት ሔደው ከፊት ለፊታቸው ቆሙ፡፡ ኤልያስም በመጠምጠሚያው የዮርዳኖስን ውኀ ቢመታው ውኀው ከሁለት ተከፈለ፡፡ ኤልያስና ኤልሳዕም ወንዙን በደረቅ ተሻገሩ፡፡ ወጥተውም ከምድረ በዳ ቆሙ፡፡ ወንዙን ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ደቀ መዝሙሩ ኤልሳዕን ‹‹ከአንተ ሳልወሰድ ላደርግልህ የምትፈልገውን ለምነኝ፤›› አለው፡፡ ኤልሳዕም ‹‹በአንተ ላይ ያደረው መንፈስ ቅዱስ እጥፍ ኾኖ በእኔ ላይ እንዲያድር ይኹን፤›› ብሎ መለሰ፡፡ ኤልያስም ‹‹ዕፁብ ነገርን ለመንኸኝ፡፡ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ በማርግበት ጊዜ ካየኸኝ እንዳልኸው ይደረግልሃል፡፡ በማርግበት ሰዓት ካላየኸኝ ግን አይደረግልህም፤›› አለው፡፡

ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሔዱ የእሳት ሠረገላ፣ የእሳት ፈረስ በመካከላቸው ገባና ለያያቸው፡፡ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ፣ በንውጽውጽታ፣ በእሳት ሠረገላ ዐረገ፡፡ ኤልሳዕም የኤልያስን ወደ ሰማይ መወሰድ አይቶ ጮኸ፤ ‹‹የእስራኤል ኀይላቸው፣ ጽንዓታቸው አባ፣ አባት ሆይ›› አለ፡፡ ከዚያ በኋላ ዳግመኛ አላየውም፡፡ ኤልያስም ልብሱን ከሁለት ከፈለው፡፡ መጠምጠሚያውንም ለኤልሳዕ ጣለለት፡፡ የኤልያስ ጸጋና በረከትም በኤልሳዕ ላይ አደረ፡፡

ይህም ምሳሌ ነው፤ ኤልያስ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ብሔረ ሕያዋን እንደ ገባ ዅሉ፣ ከውኀና ከመንፈስ ቅዱስ የሚወለዱ ምእመናንም የእግዚአብሔርን መንግሥት ይወርሳሉ፡፡ ‹‹ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ለማየት አይችልም፤›› እንዳለ ጌታችን በወንጌል /ዮሐ.፫፥፫/፡፡

በአጠቃላይ ነቢዩ ኤልያስ በዘመነ ኦሪት ከነበሩት ዐሥራ አምስቱ ነቢያት (ሙሴ፣ ኢያሱ፣ ሳሙኤል፣ ዮናታን፣ ጋድ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞን፣ ኤልሳዕ፣ ዕዝራ፣ ኢሳይያስ፣ ዳንኤል፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል እና መጥምቁ ዮሐንስ) መካከል አንደኛው ነቢይ ነው፡፡ ይህ ቅዱስ በአካለ ሥጋ ከጌታችን ጋር በደብረ ታቦር የተነጋገረ ነቢይ፤ የጣዖታትን መሥዋዕት አፈራርሶ ለልዑል እግዚአብሔር እውነተኛ መሥዋዕትን ያሳረገ ካህን፤ ሥርዓተ ምንኵስናን የጀመረ ባሕታዊ፤ ስለ እግዚአብሔር ለፍርድ መምጣት አስቀድሞ የሚሰብክ ሐዋርያ ነው /የገድለ ኤልያስ ነቢይ መቅድም፣ ቍ.፩-፮/፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ታላቅነት ሲመሰክር ዮሐንስን ‹ኤልያስ› ብሎታል፡፡ ዮሐንስ ልብሱ የግመል ፀጉር እንደ ኾነ ዅሉ፣ ኤልያስም ፀጕራም መኾኑ፤ ሁለቱም መናንያን፣ ጸዋምያን፣ ተሐራምያን /ፈቃደ ሥጋን የተዉ/፣ ዝጉሐውያን /የሥጋን ስሜት የዘጉ/፣ ባሕታውያን መኾናቸው፤ በተጨማሪም ዮሐንስ ሄሮድስና ሄሮድያዳን እንደ ገሠፃቸው ዅሉ፣ ኤልያስም አክአብና ኤልዛቤልን መገሠፁ፤ ዮሐንስ ከክርስቶስ ቀዳሚ ምጽአት /በአካለ በሥጋ መገለጥ/ አስቀድሞ እንዳስተማረ ዅሉ፣ ኤልያስም ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት አስቀድሞ የሚያስተምር መኾኑ ያመሳስላቸዋልና ጌታችን ዮሐንስን ‹ኤልያስ› ብሎ ጠርቶታል /ትርጓሜ ወንጌል፣ ማቴ.፲፩፥፲፬፤ ፲፯፥፲-፲፫/፡፡

መምህራነ ቤተ ክርስቲያን እንዳስተማሩን ነቢዩ ኤልያስ ከጌታችን ዳግም ምጽአት አስቀድሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለዓለም በመስበክ በሰማዕትነት ይሞታል፡፡ አንዳንዶቹ ይህንን ትምህርት ይዘው ‹‹ኤልያስ መጥቷል›› እያሉ ምእመናንን ያሰናክላሉ፤ ነቢዩ እነርሱ እንደሚሉት በስውር ሳይኾን ዓለም እያየው በግልጽ እንደሚመጣ ስለምናምን ኤልያስ ወደዚህ ምድር የሚመጣው የምጽአት ቀን ሲቃረብ መኾኑን አስረግጠን እንናገራለን፡፡

በመጨረሻም ዅላችንም እንደ ነቢዩ ኤልያስ በአካለ ሥጋ ሳይኾን በክብር ከፍ ከፍ እንል ዘንድ በሕሊና ልናርግ ማለትም በመልካም ምግባር ልንጐለምስ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ እንደ ነቢዩ ኤልሳዕ የአባቶቻችን ጸጋ በላያችን ላይ ያድርብን ዘንድ ከቅዱሳን እግር ሥር እና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅፅር፤ እንደዚሁም ከተዋሕዶ ሃይማኖታችን አስተምህሮ መውጣት የለብንም፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም የእግዚአብሔርን መንግሥት እንወርስ ዘንድ ሕገ እግዚአብሔርን ጠብቀን፣ በክርስቲያናዊ ምግባር ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ‹‹… ጌታውን የሚጠብቅ ይከብራል፤›› ተብሎ ተጽፏልና /መጽሐፈ ተግሣፅ ፫፥፲፰ (ምሳሌ ፳፯፥፲፰)/፡፡ የነቢዩ ረድኤትና በረከት አይለየን፡፡

ምንጭ፡-

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ታኅሣሥ ፩ እና ጥር ፮ ቀን የሚነበብ፡፡

የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ኢ.መ.ቅ.ማ፤ 2002 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ ገጽ 173፡፡

ገድለ ኤልያስ ነቢይ፣ መ/ር ተስፋ ሚካኤል ታከለ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡