አስተርእዮ

በመምህር  ለማ በእርሱፈቃድ

ጥር ፲ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

አስተርእዮ ማለት መታየት፣ መገለጥ  የመሳሰሉትን ፍች ይይዛል፡፡ ቃሉ አስተርአየ ታየ፤ ተገለጠ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ የጥር ወር በሙሉ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት በሥጋ የተገለጠበት (የታየበት) ወቅት በመኾኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ያለው ጊዜ ዘመነ አስተርእዮ ይባላል፡፡ ይህ ብቻም ሳይኾን የእግዚአብሔር አንድነት፣ ሦስትነት የተገለጠው በዚሁ ወር ነውና ወቅቱ ዘመነ አስተርእዮ ተብሎ ይጠራል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ሥጋ ለብሶ የመታየቱ (የመገለጡ) ዋና ዋና ምክንያቶችን ምንድን ናቸው የሚሉ ነጥቦችን በአጭሩ እንመለከታለን፤

፩. የገባውን ቃል ኪዳን ይፈጽም ዘንድ

እግዚአብሔር አምላካችን ሰውን በምሳሌው ፈጥሮ የሚያስፈልገውን ዅሉ አዘጋጅቶ በክብር ይኖር ዘንድ ገነትን አወረሰው፡፡ በማየት የሚደሰትበትና የሚማርበትንም ሥነ ፍጥረትን ፈጠረለት፤ የሚበላውንና የማይበላውንም ለይቶ ሰጠው፡፡ ነገር ግን አትብላ የሚለውን አምላካዊ ትእዛዝ ሳይጠብቅ የተከለከለውን ዕፀ በለስ በመብላቱ ምክንያት ከገነት ተባረረ /ዘፍ.፪፥፲፮/፡፡ በዚያን ጊዜ ነው ርኅራኄ የባሕርዩ የኾነ አምላካችን ‹‹ከአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለው›› የሚለውን የተስፋ ቃል ኪዳን ለአዳም የሰጠው /ሲራ.፳፬፥፮/፡፡

ነቢያቱም ‹‹ጌታ ራሱ ምልክትን ይሰጣችኋል፤ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፡፡ ስሙንምአማኑኤል› ብላ ትጠራዋለች፤›› እያሉ ትንቢት ሲናገሩ ቆይተዋል /ኢሳ.፯፥፲፬/፡፡ አዳምም ከነልጆቹ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመናት ይህንን ቃል ኪዳን ሲጠባበቅ ኖሯል፡፡ ‹‹ቁጣው እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈው /ኢሳ.፳፮፥፳/፣ ይህችን ቃል ኪዳን ይፈጽማት ዘንድ ወልደ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ አካሉ በሥጋ ተገለጠ ማለት ሥጋን ተዋሐደ፡፡

፪. የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ

‹‹ወዘሰ ይገብራ ለኀጢአት እምነ ጋኔን ውእቱ እስመ ቀዳሚሁ ለሰይጣን አበሰ ወበእንተ ዝንቱ አስተርአየ ወልደ እግዚአብሔር ከመ ይስዐር ግብሮ ለጋኔን፤ ኀጢአትን የሚሠራትም ከዲያብሎስ ወገን ነው፡፡ ጥንቱንም ሰይጣን በድሎአልና ስለዚህ የእግዚአብሔር ልጅ በሥጋ ተገለጠ፡፡ የዲያብሎስን ሥራ ይሽር ዘንድ፤›› በማለት ሐዋርያው እንደ ገለጸው /፩ኛዮሐ.፫፥፰/፣ ሰይጣን የሰውን ልጅ እግዚአብሔርን ያህል ጌታ፣ ገነትን የመሰለ ቦታ እንዲያጣ፤ ከደስታ ወደ ዘለዓለም ኀዘን፣ ከነጻነት ወደ ግዞት፣ ከብርሃን ወደ ጨለማ እንዲገባ ረቂቅ ሥራ ሠርቶ ነበርና ይህንን የዲያብሎስን ሥራ ያፈርስ ዘንድ እግዚአብሔር በሥጋ ተገለጠ፡፡

ዲያብሎስ በሥጋ ከይሲ (በእባብ ሥጋ) ተሰውሮ ነገት ገብቶ አዳምና ሔዋንን እንዳሳተ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም የሰውን ልጅ ሥጋ ተዋሕዶ የዲያብሎስን ሥራ አፍርሶበታል፡፡ ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን አስቶ የግብር ልጆቹ ይኾኑ ዘንድ ‹‹አዳም ገብሩ ለዲያብሎስ ሔዋን አመቱ ለደያብሎስ›› ብለው የፈረሙትን ደብዳቤ፣ በዮርዳኖስና በሲዖል የቀበረውን የጥፋት የተንኮል ሥራውን ያፈርስ ዘንድ አምላክ ሰው ኾኖ ተገለጠ፡፡

ይህንን የዲያብሎስ ሥራም በዮርዳኖስ ባሕር የተቀበረውን በጥምቀቱ፤ በሲዖል የተቀበረውን በስቅለቱ፣ በሞቱ ደምስሶበታልና ‹‹ወነሰተ ዐረፍተ ማእከል እንተ ጽልዕ በሥጋሁ፤ በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በለበሰው ሥጋ አፈረሰው፤›› በማለት ሐዋርያው እንደ ተናገረው /ኤፌ.፪፥፲፬/፣ የዲያብሎስን ክፉ ሥራ የጥል ግድግዳ ያፈርስ ዘንድ ክርስቶስ በሥጋ ተገለጠ፡፡

፫. አንድነቱን፣ ሦስትነቱን ይገልጥ ዘንድ

የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጥ አይታወቅም ነበር፡፡ የተገለጠ፣ የታወቀ፣ የተረዳ የአንድነቱን፣ የሦስትነቱን ትምህርት በሚገባ ለማስተማር የተቻለው ጌታችን ሥጋ ለብሶ ከተጠመቀ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ‹‹ወርእየ መንፈሰ እግዚአብሔር እንዘ ይወርድ በአምሳለ ርግብ ወናሁ መጽአ ቃል እምሰማይ ዘይብል ዝንቱ ውእቱ ወልድየ ዘአፈቅር ዘቦቱ ሠመርኩ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እግዚአብሔር አብ በደመናየምወደው፣ ለመሥዋዕትነት የመረጥኩት ልጄ ይህ ነው› አለ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ /ማቴ.፫፥፲፯፤ ሉቃ.፫፥፳፩/፣ ጌታችን የአዳምና የሔዋንን የዕዳ ደብዳቤ ለመሻር በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነት እና ሦስትነት ምሥጢር ተገልጿል፡፡ ይህ ምሥጢር ከጥንተ ዓለም ጀምሮ በግልጽ ሳይታወቅ፣ ሳይገለጥ ተሰውሮ ይኖር ነበር፡፡ ‹‹በእንተ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘኅቡእ ኅርመቱ እምቅድመ ዓለም፤ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለም ሳይፈጠር ተሰውሮ ነበር፡፡ ከነቢያት ቃል የተነሣ በዚህ ዘመን ተገለጠ፤›› እንዲል /ሮሜ.፲፮፥፳፬/፡፡

፬. ፈጽሞ እንደ ወደደን ለመግለጽ

እግዚብሔር ሰውን ምን ያህል እንደ ወደደው ለመረዳት እግዚብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ያዳነበት ጥበቡ እጅግ ዕፁብ ድንቅ ነውና፡፡ ማንም ሳያስገድደው፤ ሰው ኹን ብሎ ሳይጠይቀው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ዘመኑን ጠብቆ እግዚአብሔር ሰው ኾኖ ከኀጢአት በስተቀር ዅሉን ፈጽሞ፣ በገዛ ፈቃዱ መከራ ሥጋን ተቀብሎቈ ሥጋውን ቈርሶ፣ ደሙን አፍሶ የዘለዓለም ሕይወትን ለሰው ልጅ በመስጠቱ ምን ያህል ፍጹም ፍቅሩን እንደ ገለጸልን እንረዳለን፡፡ ‹‹አልቦ ዘየዐቢ እምዝ ፍቅር ከመ ዘቦ ዘይሜጡ ነፍሶ ህየንተ አእርክቲሁ፤ ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ያለ እንደ ኾነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም፤›› እንዳለ ወንጌላዊው /ዮሐ.፲፭፥፲፪/፡፡

በደል የሠራው የሰው ልጅ ይሰቀል ይሙት ሳይል እኔ ልሙት ማለቱ የእግዚአብሔር የፍጹም ፍቅሩ መገለጫ ነው፡፡ ሰው ሰውን የሚወደው ገንዘቡንና የመሳሰሉትን እስከ መስጠት ሊኾን ይችላል፡፡ ሕይወቱን እስከ መስጠት የሚወድ ማንም የለም፤ አልነበረም፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የወደደውን የሰውን ሥጋ ለብሶ መኪራ ሥጋን ተቀብሎ ሰውን በሞቱ ያድን ዘንድ ሞትን የሞተው ፈጽሞ እንደ ወደደን ለመግለጥ ነው /፩ኛዮሐ.፬፥፱/፡፡ ይህም ፍቅሩ ይቃወቅ ዘንድም በሥጋ ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ሊቃውንቱ ይህንን ወቅት ‹‹አስተርእዮ›› በማለት ሰይመውታል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ማስገንዘቢያ፡- ይህ ትምህርት ጥርቀን ፳፻፭ .ም በድረ ገጻችን ቀርቦ ነበር፡፡