ዘመነ አስተርእዮ

በርእሰ ደብር ብርሃኑ አካል

ጥር ፲፱ ቀን ፳፻፱ .

አስተርእዮ ቃሉ የግእዝ ቃል ሲኾን መታየት መገለጥ ማለት ነው፡፡ ገሃድ የሚለው ቃልም በጾምነቱ ሌላ ትንታኔ ሲኖረው ትርጕሙ ያው መገለጥ ማለት ነው፡፡ በግሪክ ‹‹ኤጲፋኒ›› ይሉታል፡፡ የእኛም ሊቃውንት ቃሉን በቀጥታ በመውሰድ ‹‹ኤጲፋኒያ›› እያሉ በዜማ መጻሕፍቶቻቸው ይጠሩታል፡፡ ትርጕሙም ከላይ ከጠቀስናቸው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አስተርእዮ የሚለው ቃል ‹‹አስተርአየ›› ከሚለው ግሥ ራሱን ችሎ ሳይለወጥ በአምስቱ አዕማድ የሚፈታ ብቸኛ ግሥ ነው፡፡ ይህም ማለት፡- አስተርአየ፤ ታየ፤ ተያየ፤ አሳየ፤ አስተያየ፤ አየ ተብሎ ይፈታል ማለት ነው፡፡

ዘመነ አስተርእዮ ሲያጥር ከጥር ፲፩ ቀን እስከ ጥር ፴፤ ሲረዝም ደግሞ ከጥር ፲፩ ቀን እስከ መጋቢት ፫ ቀን ይኾናል፡፡ በዚህም መሠረት ቀናቱ ሲያጥር ፳፤ ሲረዝም ፶፫ ይኾናሉ ማለት ነው፡፡ ጌታችን ለሐዋርያት ሕጽበተ እግር ካደረገበት ቀን (ከጸሎተ ሐሙስ) እስከ ጰራቅሊጦስ ቢቈጠር ቀናቱ ፶፫ ስለሚኾኑ የእነዚህ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ዮሐንስ በጥምቀት ዕለት ለልዕልና (ጌታ ሰውን ምን ያህል እንዳከበረው) ለማሳየት እጁን ከጌታችን ራስ በላይ ከፍ እንዳደረገ ጌታችንም ለትሕትና እጁን ከሐዋርያት እግር በታች ዝቅ አድርጎ እግራቸውን አጥቧቸዋልና ነው፡፡

ጥምቀት የሕጽበት አምሳል ሲኾን፣ ሕጽበት (መታጠብ) ደግሞ በንባብ አንድ ኾኖ ሁለት ምሥጢራት አሉት፡፡ የመጀመሪያው፡- ምእመናን የእንግዳ እግር እንዲያጥቡ ጌታችን ትምህርት ማስተማሩ ሲኾን፣ ሁለተኛውም ለሐዋርያት ጥምቀታቸው መኾኑ ነው፡፡ ሐዋርያት በጸሎተ ሐሙስ ቢጠመቁም መንፈስ ቅዱስ የተቀበሉት የጰራቅሊጦስ ዕለት ነውና፡፡ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ስለ ቅዱሳን ሐዋርያት ጥምቀት ቅዱስ ባስልዮስ ዘቂሣርያን እንደ ጠየቀውና ጥምቀታቸው ሕጽበተ እግር መኾኑን እንደ መለሰለት፡፡

በሌላ በኩል ከዘመነ ልደት እስከ ጥምቀት ተወልደ፤ ተሠገወ (ሰው ኾነ) ይባላል እንጂ አስተርአየ (ተገለጠ) አይባልም፡፡ ከጥምቀት በኋላ ግን አብሮ፣ ተባብሮ ተጠምቀ፤ ተወልደ፤ ተሠገወ፤ አስተርአየ ይባላል፡፡ ከጥምቀት በፊት አስተርእዮ ለመባሉ በሦስት ነገሮች ነው፡፡ የመጀመሪያው፡- የማይታየው ረቂቅ አምላክ በበረት ተወልዶ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎ ቢታይ፤ እንደ ሕፃን ሲያለቅስ ቢሰማም ሰው ዅሉ ሠላሳ ዓመት ሲሞላው ሙሉ ሰው ይኾናል እንደሚባለው፣ አምላክ ነኝ ብሎ በአንድ ቀን ሳያድግ በጥቂቱ ማደጉንና ስደት እንደ ውርደት ኾኖ እንዳይቈጠር ለሰዎች ስደትን ባርኮ (ጀምሮ) ለመስጠት፤ ሄሮድስም ሊገድለው ይፈልገው ስለ ነበር ወቅቱ የሚሰደድበት እንጂ የሚታይበት ስላልነበረ ነው፡፡

ሁለተኛው፡- ሰው በተፈጥሮም ኾነ በትምህርት አዋቂ ቢኾን ለሚመለከተው ሥራና ደረጃ እስከ ተወሰነ ጊዜ ይህ ሕፃን ለእንዲህ ያለ ማዕረግ ይኾናል አይባልም፤ ተንከባክባችሁ አሳድጉት ይባላል እንጂ፡፡ ሕፃኑ አዋቂ ነው አይባልም፤ ያውቃል ተብሎም ለትልቅ ደረጃ አይበቃም፡፡ በየትኛውም ሓላፊነት ላይ አይሰጥም፤ ራሱን በመግዛት ይጠበቃል እንጂ፡፡ ጌታችንም በመንፈስም በሥጋም ባለ ሥልጣን ቢኾንም ፍጹም ሰው ኾኗልና አምላክ ነኝ፤ ዅሉን በዕለቱ ልፈጽም ሳይል በየጥቂቱ ማደጉን እናያለን፡፡

የሰውን ሥርዓት ከኀጢአት በቀር ለመፈጸም በየጥቂቱ አደገ፡፡ ‹‹በበሕቅ ልሕቀ›› እንዲል፡፡ ሰው ዅሉ ፴ ዓመት ሲኾነው ሕግጋትን ለመወከል፣ ለመወሰን እስከ ፴ ዓመት መታገሡም ስለዚሁ ነው፡፡ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ሰው ቢመቸው ይወፍራል፤ ቢከፋው ይከሳል እንጂ ቁመት አይጨምርም አይቀንስም፡፡ ጌታችን ሰው ሙሉ፣ አእምሮው የተስተካከለለት ጐልማሳ በሚኾንበት ዕድሜ በ፴ ዓመት በግልጽ በመታየቱ ወቅቱ ‹‹ዘመነ አስተርእዮ›› ተብሏል፡፡

ሦስተኛው፡- በ፴ ዓመት እርሱ ሊጠመቅበት ሳይኾን የመጀመሪያ መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት መሠረት የኾኑ ጥምቀትንና ጾምን ሠርቶ በመሳየትና መመሪያ አድርጎ ለምእመናን በመስጠት እሱ ሙሉ ሰው ኾኖ ተገልጾ የቃሉን ትምህርት ለመስማት፤ የእጁን ተአምራት ለማየት ይከተለው ለነበረው አምስት ገበያ ያህል ሕዝብ  ትምህርት፣ ተአምራት ያደረገበት፤ ሥራዬ ብሎ የመጣበት መንፈሳዊ ሕግና ሥርዓት የፈጸመበት ዘመን በመኾኑ ነው፡፡ የታየውም ወልድ ብቻ አይደለም፤ አብ ‹‹ይህ የምወደው ልጄ ነው›› ሲል፤ መንፈስ ቅዱስም በእርግብ አምሳል ሲወርድ ረቂቁ አምላክ የታየበት፤ የሥላሴ የአንድነትና ሦስትነት ምሥጢር የተገለጠበት ዕለት ስለ ኾነ ይህ ወቅት ዘመነ አስተርእዮ ተብሏል፡፡

በአስተርእዮ ሌሎች በዓላትም ይጠሩበታል፡፡ ለምሳሌ ድንግል ማርያም ጥር ፳፩ ቀን ነፍሷ ከሥጋዋ ተለይቶ በደመና ተነጥቃ ወደ ገነት በመግባት ለጻድቃን እና ለመላእክት በሰማይና በምድር የተሰጣት ጸጋ፣ ክብር የተገለጸበት ዕለት ስለኾነ በዓሉ ‹‹አስተርእዮ ማርያም›› ይባላል፡፡ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ፡፡ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ አምላክ በሥጋ ከድንግል መወለዱንና በዚህ አካለ መጠንም ለዓለም መገለጡን አስተርእዮ ብሎ ሲናገር፤ አባ ጽጌ ብርሃን ደግሞ በማኅሌተ ጽጌ ድርሰቱ ‹‹እግዚአብሔር ጽጌ ትንቢት ለቢሶ ሥጋኪ ሥጋ ዚአነ፤ አመ አስተርአየ በምድር ወተአምረ ለነ፤ ንዌድሰኪ እንዘ ንብል ምክሐ ዘመድነ፤ ዮም በፍሥሓ ለማርያም እምነ፤ አስተርእዮ በሰማይ ኮነ፡፡ – የትንቢት አበባ እግዚአብሔርእኛ ሥጋ የኾነውን የአንቺን ሥጋ ለብሶ ለእኛ እንዲታወቅ በምድር እንደ ተገለጠ፤ የወገናችን መመኪያ ድንግል ሆይ፣ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ ፍጹም በደስታ መገለጥ ኾነ› እያልን እናመሰግንሻለን፤›› ሲል ገልጾታል፡፡ ነቢዩ ዳዊትም፡- ‹‹በከመ ሰማዕነ ከማሁ ርኢነ፤ በነቢያት ይወለዳል ሲባል የሰማነው በበረት ተጥሎ፤ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግዕዘ ሕፃናት ሲያለቅስ ሰማነው፡፡ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ አየነው፤›› በማለት የአምላካችንን መገለጥ ተናግሯል /መዝ.፵፯፥፮/፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡