ነቢዩ ዮናስ ክፍል አንድ

እንደምን አላችሁ ልጆች? ከአሁን በፊት ለእናንተ የሚኾኑ ትምህርታዊ ጽሑፎችን በድረ ገጻችን ስናቀርብላችሁ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በልዩ ልዩ ምክንያት ዝግጅቱን አቋርጠን ቆይተናል፡፡ ለዚህም እናንተን ይቅርታ እየጠቅን ከዛሬ ጀምሮ ወቅታዊ ይዘት ያሏቸውን ትምህርታዊ ጽሑፎች በየጊዜው እንደምናቀርብላችሁ ቃል እንገባለን፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም የነቢዩ ዮናስንና የነነዌ ሰዎችን ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም የንባብ ጊዜ ይኹንላችሁ!

ነቢዩ ዮናስ ክፍል አንድ

በልደት አስፋው

የካቲት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ልጆች! እግዚአብሔር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ ሲፈልግ ወደ ሕዝቡ ከሚልካቸው ነቢያት መከካል አንዱ ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምን ኾነ መሰላችሁ ልጆች፣ ወደ አንዲት ታላቅ ከተማ ሔዶ እንዲሰብክ የእግዚአብሔር ቃል ለነቢዩ ዮናስ መጣለት፡፡ ልጆች ይህች ታላቅ ከተማ ነነዌ ትባላለች፡፡ በዚህች በነነዌ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአታቸው እጅግ በዝቶ ነበር፡፡ ርኅሩኁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰውን መዳን እንጂ ጥፋቱን ስለማይፈልግ ንስሐ ግቡ ብሎ እንዲያስተምራቸው ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ግን የፈጣሪውን ትእዛዝ ላለመፈጸም ሊኮበልል አሰበ፡፡ ከዚያም ተርሴስ ወደምትባል አገር የምታልፍ መርከብ አግኝቶ በእርሷ ተሳፈረ፡፡ ልጆች ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለል ወይም መሸሽ ይቻላል? አይቻልም አይደል? እስቲ ነቢዩ ዮናስ የተሳፈረባት መርከብ ምን እንደ ገጠማት እንመልከት፤

ነቢዩ ዮናስ በመርከብ ተሳፍሮ ሲሔድም እግዚአብሔር ታላቅ ነፋስን አምጥቶ በባሕሩ ላይ ታላቅ ማዕበልን አስነሣ፡፡ በዚህ ጊዜ መርከቢቱ ልትሰበር ደረሰች፡፡ ለምን እንደዚህ እንደኾነ አወቃችሁ ልጆች? ነቢዩ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ በማሰቡ ነው፡፡ መርከቢቷ ውስጥ ያሉ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ መርከቧ ክብደት ስለበዛባት ነው ብለው አስበው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ዅሉ ወደ ባሕር ቢጥሉትም መርከቢቱ ግን ልትረጋጋ አልቻለችም ነበር፡፡ ማዕበሉም አልቆም አለ፡፡ ልጆች ይህ ዅሉ ሲኾን ግን ነቢዩ ዮናስ ተኝቶ ነበር፡፡ ከዚያም የመርከቡ አለቃ ወደ እርሱ ቀረበና ‹‹ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደኾነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ›› አለው፡፡ በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሰዎችም ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ ዕጣ እንጣጣል›› ተባብለው ዕጣ ሲጣጣሉ ዕጣው በነቢዩ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን?›› አሉት፡፡

ነቢዩ ዮናስም ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለሉን በነገራቸው ጊዜ ሰዎቹ በፍርኀት ኾነው ‹‹ይህ ያደረግኸው ምንድን ነው?›› አሉት፡፡ ባሕሩንም ሞገዱ እጅግ ያናውጠው ነበርና ‹‹ባሕሩ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁ፡፡ አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፡፡ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፤›› አላቸው (ትንቢተ ዮናስ ፩፥፩-፲፫)፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ባሕሩ ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡ ልጆች! ባሕሩ ሲናወጥ የነበረው ለምን እንደኾነ ተረዳችሁ? ዮናስ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትቶ ለመሸሽ በመርከቡ በመሳፈሩ ነው! እግዚአብሔርን ሳንታዘዝ ያሰብንበት ቦታ መድረስ የምንችል ይመስላችኋል ልጆች? አንችልም አይደል? አዎ፤ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ዓለሙን ዅሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነውና በባሕርም ኾነ በየብስ (በደረቅ መሬት) ብንጓዝ ከእርሱ መሰወር ፈጽሞ አይቻለንም፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ቦታና ከእርሱ እይታ የተሰወረ ምንም ነገር የለምና፡፡

ልጆች! ቀጣዩን ክፍል ነገ ይዘንላችሁ እንቀርባለን እሺ? ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡

ጾመ ሰብአ ነነዌ

በርእሰ ደብር ብርሃኑ አካል

ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጾመ ነነዌ ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዷ ስትኾን የምትጾመውም ለሦስት ቀናት ነው፡፡ ይህቺ ጾም የምትጀመርበት ዕለትም ልክ እንደ ዐቢይ ጾም ሰኞን አይለቅም፡፡ ጾሟ የምትጀመርበት ቀን ሲወርድ ወይም ወደ ኋላ ሲመጣ እስከ ጥር ፲፯ ቀን ድረስ ነው፡፡ ቀኑ ሲወጣ ወይም ወደ ፊት ሲገፋ ደግሞ እስከ የካቲት ፳፩ ቀን ይረዝማል፡፡ ጾመ ነነዌ በእነዚህ ፴፭ ቀናት ውስጥ ስትመላለስ (ከፍ እና ዝቅ ስትል) ትኖራለች፤ ከተጠቀሱት ዕለታት አትወርድም፤ አትወጣም፡፡ በዚህ ዓመትም (፳፻፱ ዓ.ም) ጥር ፳፱ ቀን ትጀመራለች፡፡

‹‹ጾመ ሰብአ ነነዌ፤ የነነዌ ሰዎች ጾም›› የሚለው የጽሑፋችን ርእስ እንደሚያስረዳው ይህቺን የሦስት ቀን ጾም የጾሟት በነነዌ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ከተማዋም (ነነዌ) በጤግሮስ ወንዝ ዳርቻ የምትገኝ ስትኾን መሥራቿም ናምሩድ ነው /ዘፍ.፲፥፲፩-፲፪/፡፡ ጥንታዊቷ የነነዌ ከተማ ለአሦር መነሻ የኾነች፤ እጅግ ሰፊና ያማረች፤ የቅጥሯ ርዝመትም ፲፪ ኪሎ ሜትር የሚሸፈን ነበር፡፡ በከተማዋ ንጉሡ ሰናክሬም ብዙ ሕንጻዎችን ገንብቶባት ነበር /ዮናስ ፬፥፲፩/፡፡ በዚያ ዘመን የነበሩ የነነዌ ሰዎች ኀጢአታቸው በዝቶ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ሲል ቸርነትና ምሕረቱ የማያልቅበት እግዚአብሔር መክሮ፣ ዘክሮ እንዲመልሳቸውና ንስሐ እንዲገቡ ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ሕዝብ ላከው /ሉቃ.፲፩፥፴/፡፡

ዮናስ የስሙ ትርጕም ‹ርግብ› ማለት ነው፡፡ በዳግማዊ ኢዮርብዓም ዘመነ መንግሥት የነበረ ነቢይ ነው፡፡ ይህ ነቢይ መኖሪያው በገሊላ በጋትሔፌር ድንበር ከተማ ነበረ፡፡ አባቱም አማቴ ይባላል፡፡ ኢዮርብዓም ሶርያውያንን አባሮ የእስራኤልን ድንበር እንዲመልስ ነቢዩ ዮናስ ትንቢትን ተናግሯል /፪ኛነገ.፲፬፥፳፭፤ ዮናስ ፩፥፩/፡፡ ነቢዩ ኤልያስ ያስነሣው የሰራጵታዋ መበለት ሕፃን ነቢዩ ዮናስ እንደ ኾነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያስረዳል /፩ኛነገ.፲፯፥፲፱/፡፡ መድኀኒታችን ክርስቶስም የዮናስን ከዓሣ ኾድ መውጣት የራሱ ትንሣኤ ምሳሌ አድርጎ ነግሮናል /ማቴ.፲፪፥፲፱-፵፪፤ ሉቃ.፲፩፥፴-፴፪/፡፡

እግዚአብሔር ‹‹ሔደህ በነነዌ ላይ ስበክ›› ባለው ጊዜ ነቢዩ ዮናስ ‹‹አንተ መሐሪ ነህ፤ ልትጠፉ ነው ብዬ ተናግሬ ብትምራቸው ሐሰተኛ ነቢይ እባላለሁ›› ብሎ ላለመታዘዝ እስራኤልን ለቆ በመርከብ ወደ ተርሴስ ሸሸ፡፡ እግዚአብሔርም ታላቅ ነፋስን አስነሥቶ መርከቧ በማዕበል እንድትመታ አደረገ፡፡ ከዮናስ ጋር በመርከቧ ተሳፍረው የነበሩ ነጋድያንም ያላቸውን ሀብት ወደ ባሕሩ መጣል ሲጀምሩ ነቢዩ ዮናስ ጥፋቱን ተገንዝቦ ‹‹ማዕበሉ በእኔ ምክንያት የመጣ ስለ ኾነ ንብረታችሁን ሳይኾን እኔን ወደ ባሕር ጣሉኝ›› ብሎ ተማጸናቸው፡፡ እነርሱም ‹‹ስለዚህ ሰው ነፍስ እንዳንጠፋ፣ ንጹሕም ደም በእኛ ላይ እንዳይደረግብን አይኾንም›› አሉ፡፡

ወደ ባሕሩ ለመጣል ዕጣ በተጣጣሉ ጊዜም ዕጣው በዮናስ ላይ ስለ ወጣ ነጋድያኑ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ታላቅ ዓሣ አንበሪ ዮናስን በአፉ ተቀብሎ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት አሳድሮ ወደ ነነዌ አደረሰው፡፡ እግዚአብሔር የቅል ተክልን ምሳሌ በማድረግ ቅጠሉ በመድረቁ ዮናስ ባዘነ ጊዜ ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ኾኑ ያሳዝኑኛል›› በማለት ነቢዩ ዮናስም ውሸታም ላለመባል መኮብለሉ ስሕተት መኾኑን አስረድቶታል፡፡

ዮናስም ነነዌ መሬት ላይ መድረሱን ባወቀ ጊዜ ከእግዚአብሔር መሸሽ አለመቻሉን ተረዳ፤ የነነዌ ሰዎችንም ‹‹ንስሐ ግቡ›› እያለ መስበክ ጀመረ፡፡ የነነዌ ሰዎችም ንስሐ በገቡ ጊዜ እግዚአብሔር ይቅር ብሎ ከጥፋት አድኗቸዋል፡፡ ሐሰት እንዳይባልም እሳቱ እንደ ደመና ኾኖ ከላይ ታይቶአል፡፡ የታላላቁ ዛፍ ቅጠል እስኪጠወልግ ድረስ አድርቆ ለሕዝቡ አሳይቷቸዋል፡፡ ንስሐቸው በከንቱ እንዳልቀረ አስረድቷቸዋል /ትንቢተ ዮናስን በሙሉ ይመልከቱ/፡፡ ታኅሣሥ ፭ ቀን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ‹‹ወበልዐ አሐደ ኀምለ›› በማለት ንስሐ ያልገቡ አንድ አገር ያህል ሰዎች በእሳቱ እንደ ጠፉ ይነግረናል፡፡

ጾመ ነነዌ የሦስት ቀን ሱባኤ ናት፤ በሦስት ቀናት ጾምና ጸሎት ንስሐ የገቡ የነነዌ ሰዎች ከጥፋት እንደ ዳኑ ዅሉ፣ በብሉይ ኪዳን አስቴር ሦስት ቀን ጾማ፣ ጸልያ በእስራኤል ላይ የመጣውን መቅሠፍት እንዲመለስ አድርጋለች /አስ.፬፥፲፭-፲፮/፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከበዓል ስትመለስ ሕፃኑ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ ላይ ጠፍቶአት ከሦስት ቀን ፍለጋ በኋላ በቤተ መቅደስ አግኝታዋለች /ሉቃ.፪፥፵፮/፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለሄሮድስ በሰጠው ምላሽ መልስ ሦስት ቀን የሱባኤ ፍጻሜ መኾኑን ገልጿል /ሉቃ.፲፫፥፴፪/፡፡

ጾመ ነነዌ የእግዚአብሔርን ቸርነትና መሐሪነት የምናስታውስበት ጾም ነው፡፡ ይኸውም እኛ ፍጡራኑ በበደልን ጊዜ ፈጽሞ ከማጥፋት ይልቅ ምክንያት ፈልጎ እንድንድን ያደርገናል፡፡ ዮናስ ለስብከት ፈቃደኛ ባይኾን እንኳን እግዚአብሔር በተለየ ጥበቡ እንዲሔድ አድርጎታል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ሌላ የሚልከው ነቢይ አጥቶም አይደለም፤ እርሱንም ጭምር ሊያስተምረው ስለ ፈለገ እንጂ፡፡ የነነዌ ሰዎች የተነሳሕያን ምሳሌ ናቸው፡፡ ይህም ማለት ሰው ጥፋቱን አምኖ ንስሐ ከገባ እግዚአብሔር ይቅር ማለቱን አይተውም፡፡ ለዚህም ነው ዮናስን ‹‹አንተ ላልደከምክበት እና በአንድ ቀን በቅሎ ላደገ ቅል ስታዝን እነሆ በታላቂቱ ነነዌ ከተማ ያሉ ከአንድ መቶ ሃያ ሺሕ በላይ ሕዝብና እንስሳቱ የእጄ ፍጥረቶች ስለ ኾኑ ያሳዝኑኛል›› ያለው፡፡

ቀደምት የቤተ ክርስቲያን አባቶቻችን ይህን እና ሌሎች አጽዋማትን እንድንጾም የወሰኑልን ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሕጉ የተዘጋጀልን እንደ ነነዌ ሰዎች እኛም ጾመን፣ ጸልየን ከኀጢአታችን እንነጻ ዘንድ ነው፡፡ ዛሬ ዓለማችን በኀጢአት ማዕበል እየተናወጠች ባለችበት ወቅት እኛም እንደ ነነዌ ሰዎች ከበደላችን ብንመለስ እና ንስሐ ብንገባ ቸሩ ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይቅርታና ምሕረት የባሕርይ ገንዘቡ ስለ ኾነ ‹‹ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ይቅር እላችኋለሁ፤›› ይለናል፡፡

ስለኾነም በነቢዩ ዮናስ ላይ የተደረጉ ተአምራትንና ካለመታዘዝ የሚመጣ ቅጣት ቀላል አለመኾኑን በማስተዋል፣ ለነነዌ ሰዎች የወረደውን ምሕረት በመገንዘብ ለእግዚአብሔርም ኾነ ለሃይማኖት አባቶች እና ለወላጆቻችን መታዘዝ ይገባናል፡፡ ስንጾምም እግዚአብሔር አምላካችን መዓቱን በምሕረት፣ ቍጣውን በትዕግሥት መልሶ በኀጢአት ለጠፋው ዓለም ይቅርታውን ይልካል፡፡ በመጾማችን ራሳችን ከመዓትና ከመቅሠፍት ከመዳናችን ባሻገር በእኛ በደል ምክንያት አገራችን፣ ዕፀዋቱና እንስሳቱም ሳይቀር ከድርቅና ከቸነፈር ይተርፋሉና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ኢትዮ አሜሪካውያን ሕፃናት መዓርገ ዲቁና ተቀበሉ

usa

ጥር ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በማኅበረ ቅዱሳን ሰሜን አሜሪካ ማእከል ዋሺንግተን ስቴት በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል ለመዓርገ ዲቁና የሚያበቃ የአብነት ትምህርታቸውን ለሁለት ዓመታት ሲከታተሉ የቆዩ ኢትዮ አሜሪካውያን ሕፃናት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዋሺንግተን እና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መዓርገ ዲቁና ተቀበሉ፡፡

ሕፃናቱ መዓርገ ዲቁና የተቀበሉት በዓለ ጥምቀት በሲያትል ከተማ በተከበረበት ጥር ፲፬ ቀን እና የእመቤታችን በዓለ ዕረፍት በሲያትል ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በተዘከረበት ጥር ፳፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ነው፡፡

ዲያቆናት

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል ከዲያቆናቱ ጋር

በተያያዘ ዜና ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በማኅበረ ቅዱሳን አሜሪካ ማእከል ከሲያትል ንዑስ ማእከል በቀረበላቸው ጥሪ መሠረት የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ማሠልጠኛ ማእከል ባትል ከተማ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤትን ጐብኝተዋል፡፡ ለተመራቂ ተማሪዎችም የአንገት መስቀል አበርክተውላቸዋል፡፡

በዕለቱ የአካባቢው ማኅበረ ካህናትና የተማሪዎቹ ወላጆች ለብፁዕነታቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲኾን የትምህርት ቤቱ የአብነት መምህር በግእዝ እና አማርኛ ቋንቋዎች መወድስ ቅኔ፤ ተማሪዎቹም የቃል ትምህርትና ምስባክ አቅርበዋል፡፡

uu

በመርሐ ግብሩ ላይ የትምህርትና ሥልጠና ማእከሉ በሲያትል ንዑስ ማእከል ውስጥ በሲያትል፣ በቤልቪዉ እና በባትል፤ እንደዚሁም በሰሜን አሜሪካ ግዛቶች ባሉ ሦስት ከተማዎች በድምሩ በስድስት ትምህርት ቤቶች ከ፪፻ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ፤ በዚሁ ትልቅ ድካምና ጥረት በሚጠይቀው አገልግሎት ውስጥ ከማኅበሩ አባላት በተጨማሪ በአካባቢው የሚገኙ መምህራን፣ ካህናትና ዲያቆናት እንደዚሁም ሰባክያነ ወንጌል እና ወላጆች የሚያደርጉት አስተዋጽዖ የጎላ መኾኑ ለብፁዕነታቸው ሪፖርት ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም በአሜሪካ ማእከል የአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል አማካይነት በውጭው ዓለም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ተተኪ አገልጋይና ምእመናንን ለማፍራት ማኅበረ ቅዱሳን እያበረከተ ስለሚገኘው አተዋጽዖ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

u

ብፁዕነታቸውም ‹‹በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ›› በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል ሲሰጡ ማኅበረ ቅዱሳን ከመነሻው ጀምሮ ዓላማውና ተልእኮው ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተተኪዎችን ማፍራትና ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት መኾኑን እንደሚያውቁ ገልጸው አሁንም ማኅበሩ በማከናወን ላይ የሚገኘውን መንፈሳዊ አገልግሎት አድንቀዋል፡፡

በማእከሉ በተመለከቱት መልካም ተግባር በከፍተኛ ኹኔታ መደሰታቸውንና ይህ ሥራም ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዘመን እየገጠማት ባለው ፈርጀ ብዙ ፈተና የተወሰነውን አገልግሎት ሊቀርፍ የሚችል ተግባር መኾኑን ጠቅሰው ማኅበረ ቅዱሳንን፣ የማእከሉ መምህራንን፣ ወላጆችን እና ተማሪዎችን በአጠቃላይ ዅሉንም ባለ ድርሻ አካላት ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል አመስግነዋል፡፡

በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ቃለ ምዕዳን እና ጸሎተ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ኾኗል፡፡

ምንጭ፡- በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል