ነቢዩ ዮናስ ክፍል አንድ

እንደምን አላችሁ ልጆች? ከአሁን በፊት ለእናንተ የሚኾኑ ትምህርታዊ ጽሑፎችን በድረ ገጻችን ስናቀርብላችሁ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በልዩ ልዩ ምክንያት ዝግጅቱን አቋርጠን ቆይተናል፡፡ ለዚህም እናንተን ይቅርታ እየጠቅን ከዛሬ ጀምሮ ወቅታዊ ይዘት ያሏቸውን ትምህርታዊ ጽሑፎች በየጊዜው እንደምናቀርብላችሁ ቃል እንገባለን፡፡ በዛሬው ዝግጅታችንም የነቢዩ ዮናስንና የነነዌ ሰዎችን ታሪክ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም የንባብ ጊዜ ይኹንላችሁ!

ነቢዩ ዮናስ ክፍል አንድ

በልደት አስፋው

የካቲት ፪ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ልጆች! እግዚአብሔር ለሕዝቡ መልእክት ለማስተላለፍ ሲፈልግ ወደ ሕዝቡ ከሚልካቸው ነቢያት መከካል አንዱ ነቢዩ ዮናስ ነው፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምን ኾነ መሰላችሁ ልጆች፣ ወደ አንዲት ታላቅ ከተማ ሔዶ እንዲሰብክ የእግዚአብሔር ቃል ለነቢዩ ዮናስ መጣለት፡፡ ልጆች ይህች ታላቅ ከተማ ነነዌ ትባላለች፡፡ በዚህች በነነዌ ከተማ የሚኖሩ ሰዎች ኀጢአታቸው እጅግ በዝቶ ነበር፡፡ ርኅሩኁ አምላካችን እግዚአብሔር የሰውን መዳን እንጂ ጥፋቱን ስለማይፈልግ ንስሐ ግቡ ብሎ እንዲያስተምራቸው ነቢዩ ዮናስን ወደ ነነዌ ላከው፡፡ ነቢዩ ዮናስ ግን የፈጣሪውን ትእዛዝ ላለመፈጸም ሊኮበልል አሰበ፡፡ ከዚያም ተርሴስ ወደምትባል አገር የምታልፍ መርከብ አግኝቶ በእርሷ ተሳፈረ፡፡ ልጆች ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለል ወይም መሸሽ ይቻላል? አይቻልም አይደል? እስቲ ነቢዩ ዮናስ የተሳፈረባት መርከብ ምን እንደ ገጠማት እንመልከት፤

ነቢዩ ዮናስ በመርከብ ተሳፍሮ ሲሔድም እግዚአብሔር ታላቅ ነፋስን አምጥቶ በባሕሩ ላይ ታላቅ ማዕበልን አስነሣ፡፡ በዚህ ጊዜ መርከቢቱ ልትሰበር ደረሰች፡፡ ለምን እንደዚህ እንደኾነ አወቃችሁ ልጆች? ነቢዩ ዮናስ ከእግዚአብሔር ፊት ለመሸሽ በማሰቡ ነው፡፡ መርከቢቷ ውስጥ ያሉ ሰዎችም እጅግ ፈሩ፡፡ መርከቧ ክብደት ስለበዛባት ነው ብለው አስበው በውስጧ የነበረውን ዕቃ ዅሉ ወደ ባሕር ቢጥሉትም መርከቢቱ ግን ልትረጋጋ አልቻለችም ነበር፡፡ ማዕበሉም አልቆም አለ፡፡ ልጆች ይህ ዅሉ ሲኾን ግን ነቢዩ ዮናስ ተኝቶ ነበር፡፡ ከዚያም የመርከቡ አለቃ ወደ እርሱ ቀረበና ‹‹ምነው ተኝተሃል? እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደኾነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ›› አለው፡፡ በመርከቡ ውስጥ ያሉት ሰዎችም ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እናውቅ ዘንድ ኑ ዕጣ እንጣጣል›› ተባብለው ዕጣ ሲጣጣሉ ዕጣው በነቢዩ ዮናስ ላይ ወጣ፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ‹‹ይህ ክፉ ነገር በማን ምክንያት እንዳገኘን እባክህ ንገረን?›› አሉት፡፡

ነቢዩ ዮናስም ከእግዚአብሔር ፊት መኮብለሉን በነገራቸው ጊዜ ሰዎቹ በፍርኀት ኾነው ‹‹ይህ ያደረግኸው ምንድን ነው?›› አሉት፡፡ ባሕሩንም ሞገዱ እጅግ ያናውጠው ነበርና ‹‹ባሕሩ ጸጥ እንዲል ምን እናድርግብህ?›› ሲሉ ጠየቁት፡፡ እርሱም ‹‹ይህ ታላቅ ማዕበል በእኔ ምክንያት እንዳገኛችሁ አውቃለሁ፡፡ አንሥታችሁ ወደ ባሕር ጣሉኝ፡፡ ባሕሩም ጸጥ ይልላችኋል፤›› አላቸው (ትንቢተ ዮናስ ፩፥፩-፲፫)፡፡ ሰዎቹም ነቢዩ ዮናስን ወደ ባሕሩ ጣሉት፡፡ በዚህ ጊዜ ባሕሩ ከመናወጥ ጸጥ አለ፡፡ ልጆች! ባሕሩ ሲናወጥ የነበረው ለምን እንደኾነ ተረዳችሁ? ዮናስ እግዚአብሔር ያዘዘውን ትቶ ለመሸሽ በመርከቡ በመሳፈሩ ነው! እግዚአብሔርን ሳንታዘዝ ያሰብንበት ቦታ መድረስ የምንችል ይመስላችኋል ልጆች? አንችልም አይደል? አዎ፤ አንችልም፡፡ ምክንያቱም ዓለሙን ዅሉ የፈጠረ እግዚአብሔር ነውና በባሕርም ኾነ በየብስ (በደረቅ መሬት) ብንጓዝ ከእርሱ መሰወር ፈጽሞ አይቻለንም፡፡ እግዚአብሔር የሌለበት ቦታና ከእርሱ እይታ የተሰወረ ምንም ነገር የለምና፡፡

ልጆች! ቀጣዩን ክፍል ነገ ይዘንላችሁ እንቀርባለን እሺ? ለዛሬው ከዚህ ላይ ይቆየን፡፡