የማኅበረ ቅዱሳን አምስተኛው ዙር ዐውደ ርእይ ተጀመረ፡፡

ዐውደ ርእዩ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ከጠዋቱ 2፡00 እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ ለተመልካቾች ክፍት ኾኖ ይቆያል፡፡

ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀውና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው አምስተኛው ዙር መንፈሳዊ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ የማኅበሩ ሥራ አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ እንደዚሁም የዐውደ ርእዩ ተመልካቾች በተገኙበት በዐዲስ አበባ ኤግዚብሽን ማእከል ግንቦት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በአባቶች ጸሎት ተጀምሯል፡፡

በጸሎተ ወንጌሉ የተሰበከው ምስባክ፡- ጥቀ ዐቢይ ግብርከ እግዚኦ ወኵሎ በጥበብ ገበርከ መልዐ ምድረ ዘፈጠርከ፤ አቤቱ ሥራህ እጅግ ታላቅ ነው፡፡ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፡፡ የፈጠርኸውም ፍጥረት ምድርን ሞላ፤ /መዝ.፻፫፥፳፬/ የሚለው ትምህርት ሲኾን፣ የተነበበው የወንጌል ክፍልም ሉቃ. ፲፥፳፩-፳፬ ያለው ኃይለ ቃል ነው፡፡

ጸሎተ ወንጌሉና ኪዳኑ እንደ ተፈጸመ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ በኋላ ዐውደ ርእዩ በይፋ ለተመልካች ክፍት ኾኗል፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው በዚህ ዐውደ ርእይ የቤተ ክርስቲያን ማንነትና ሐዋርያዊ ተልዕኮ በዓለም፣ በአፍሪካና በኢትዮጵያ፣ ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎችና ከምእመናን የሚጠበቁ ጉዳዮች የትእይንቱ አርእስት ኾነው ይቀርቡበታል፡፡

ዐውደ ርእዩ ከግንቦት ፲፯-፳፪ ቀን ፳፻፰ (17-22 ቀን 2008) ዓ.ም፣ ከጠዋቱ 2፡00 እስከ ምሽቱ 1፡30 ድረስ ለስድስት ተከታታይ ቀናት ለተመልካቾች ክፍት ኾኖ ይቆያል፡፡

ከመጋቢት ፲፭-፳፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ለተመልካች ሊቀርብ የነበረው ይህ ዐውደ ርእይ ለጊዜው ግልጽ ባልነበረ ምክንያት ታግዶ ቢቆይም፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ውይይት እገዳው ተነሥቶ ለእይታ በቅቷል፡፡

Tewahedoapp

ተዋሕዶ የአይፎን አፕሊኬሽን ተሻሽሎ አገልገሎት መስጠት ጀመረ::

አፕሊኬሽኑ ለሁሉም የአፕል ስልኮችና አይፓዶች በሚኾን መልኩ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡

ትምህርቶችን፣ ጸሎታትን፣ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶችን፣ የየዕለቱን ምንባባትና የአብያተ ክርስቲያናት መረጃዎችን ይዟል፡፡

ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

Tewahedoappበሰሜን አሜሪካ ማእከል

በእጅ ስልክ አማካይነት ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ትምህርቶችን፣ ስብከቶችን፣ መዝሙራትንና ጸሎታትን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችለው ተዋሕዶ የአይፎን አፕሊኬሽን ተሻሽሎ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጠ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል ሙያ አገልግሎትና ዐቅም ግንባታ ክፍል ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ እንደገለጠው፤ በማእከሉ ታቅፈው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በሞያቸው በሚያገለግሉ አባላት ቀደም ሲል የተዘጋጀው አፕሊኬሽኑ ለምእመናን ሰፊ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ከተጠቃሚዎች በተሰጡ አስተያየቶችና በባለሞያዎቹ ምክርና ጥረት ለሁሉም የዓፕል ስልኮችና አይፓዶች በሚኾን መልኩ ተሻሽሎ ቀርቧል፡፡ በአዲስ መልክ የተሸሻለው ይህ አፕሊኬሽን ከበርካታ ትምህርቶች፣ ጸሎታት፣ መዝሙራት፣ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች በተጨማሪ የኢትዮጵያን ካላንደር (በዓላትና አጽዋማት ማውጫ)፣ በየዕለቱ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ምንባባትን እንዲሁም በአሜሪካ፣ በካናዳና አውሮፓ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን አድራሻና መሠረታዊ መረጃዎችን ያካተተ ነው፡፡

በተጨማሪም አፕሊኬሽኑ ልዩ ልዩ ዓመታዊ በዓላት እና አጽዋማት ሲደርሱ ለተጠቃሚዎቹ ማስታወሻ እንዲልክ ኾኖ ተዘጋጅቷል፡፡ የማእከሉ ሙያና ዐቅም ማጎልበቻ ክፍል ምእመናን ይህንን አፕሊኬሽን እዚህ ላይ በመጫን እንዲገለገሉ፣ ላልሰሙትም እንዲያሰሙ ሲል ያበስራል፡፡

ርክበ ካህናት

ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ረክብ የሚለው ቃል ተራከበ ተገናኘ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጕሙም ማግኛ፣ መገኛ፣ መገናኛ ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፰፴፩/፡፡ ርክበ ካህናትም የካህናት መገኛ፣ መገናኛ፣ ጉባኤ (መሰባሰቢያ)፣ መወያያ፣ ወዘተ የሚል ትርጕም ይኖረዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ቋንቋ ክህነት የሚለው ቃል ከጵጵስና ጀምሮ እስከ ዲቁና ድረስ ያሉትን መዓርጋት የሚያጠቃልል ስያሜ ሲሆን ካህን (ነጠላ ቍጥር)፣ ካህናት (ብዙ ቍጥር) በአንድ በኩል ቀሳውስትን የሚወክል ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሳውስት፣ የዲያቆናት የጋራ መጠሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ርክበ ካህናት የቃሉ ትርጕም እንደሚያስረዳው የአባቶች ካህናት ማለትም የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት (የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት) ጉባኤ ማለት ነው፡፡

በዓሉ በየዓመቱ የትንሣኤ በዓል በዋለ በ፳፭ኛው ቀን ሁልጊዜ በዕለተ ረቡዕ ይዋል እንጂ ወሩና የሚውልበት ቀን ግን የበዓላትንና የአጽዋማትን ቀመር ተከትሎ ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ የአጽዋማትና የበዓላት ቀመር ከመዘጋጀቱ በፊት ማለትም በቅዱስ ድሜጥሮስ አማካኝነት ዐቢይ ጾም ሰኞ፣ ስቅለት ዓርብ፣ ትንሣኤ እሑድ፣ ርክበ ካህናት ረቡዕ፣ ዕርገት ሐሙስ፣ ጰራቅሊጦስ እሑድ እንዲሆን ከመደረጉ በፊት ርክበ ካህናት ግንቦት ፳፩ ቀን ይውል ነበር /መጽሐፈ ግጻዌ ግንቦት ፳፩/፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ርክበ ካህናት በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ኛው ቀን፣ በበዓለ ሃምሳ እኩሌታ በዕለተ ረቡዕ ይዘከራል፡፡ በያዝነው ዓመት በ፳፻፰ ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ከተከበረበት ዕለት (ሚያዝያ ፳፫ ቀን) ጀምሮ ብንቈጥር ፳፭ኛው ቀን ግንቦት ፲፯ ቀን ይሆናል፡፡ በመሆኑም የዘንድሮው ርክበ ካህናት ግንቦት ፲፯ ቀን (በነገው ዕለት) ይውላል ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተዳድሩ የቆዩ አባቶቻችን በጋራ በመሰባሰብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደዚሁም ለምእመናን አንድነትና መንፈሳዊ ዕድገት የሚበጁ መንፈሳውያን መመሪያዎችን የሚያስተላልፉበት ዕለት ነው፡፡

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደተገለጸው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ተገልጦ ከዐሥራ አንዱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ በልቷል፡፡ ከምሳ በኋላም ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ትወደኛለህን? እያለ ከጠየቀው በኋላ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በቅደም ተከተል በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ በማለት የአለቅነት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ቅዱስ ጴጥሮስን ማስጠንቀቁን፤ ፍጻሜው ግን የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንንና መላው ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳ ትርጕም አለው /ዮሐ.፳፩፥፩-፲፯ (አንድምታ ትርጓሜ)/፡፡

ይህንን የጌታችን ትእዛዝና የሐዋርያትን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባኤ ያደርጋል፤ የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (የቅዱስ ማቴዎስ በዓል) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ይህ ርክበ ካህናት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርገው ጉባኤ የሚተላለፉ መመሪያዎችና የሚጸድቁ ውሳኔዎች ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምእመናን አንድነት፣ ለአገር ሰላምና ደኅንነት የሚጠቅሙ ይሆኑ ዘንድ ሁላችንም በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንንና አባቶቻችንን ይጠብቅልን፤ እኛንም ለአባቶች የሚታዘዝ ልቡና፣ ሓላፊነታችንን የምንወጣበትን ጥበብና ማስተዋሉን ያድለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

የሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ሰባተኛ ዓመት የዕረፍት ቀናቸው ተዘከረ

በዕለቱ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት በሚል ርእስ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ላይ የዳሰሳ ጥናት ቀርቧል፡፡

ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ በስእለት መልክ ለእግዚአብሔር መሰጠታቸውን እኅታቸው ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ከቻለ አባ አበራ ሕያው ናቸው እንጂ አልሞቱም ተብሏል፡፡

ግንቦት ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

የሊቀ ገባኤ አባ አበራ በቀለ (ስመ ጥምቀታቸው ኃይለ መስቀል) ሰባተኛ ዓመት የዕረፍት ቀናቸው መታሰቢያ ቤተሰቦቻቸው፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራሮችና አባላት በተገኙበት ግንቦት ፲፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ ሕንፃ ተዘክሯል፡፡

በዕለቱ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት በሚል ርእስ በ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ባዘጋጁት መጽሐፋቸው ላይ የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት ዲያቆን አሻግሬ አምጤ እንደገለጹት አባ አበራ ባለ ፬፹፬ ገጽ በሆነው በዚህ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ ክርስትና የፍቅር ሃይማኖት መሆኑንና የሃይማኖታችን ታሪክ በፍቅር ተጀምሮ በፍቅር መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡ እንደዚሁም የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ ሦስት ዐበይት ነጥቦች እንደሚያስፈልጉና እነዚህም ማመን፣ መጠመቅና ትእዛዛትን መጠበቅ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በትምህርተ ሃይማኖት መቅድማቸውም ሃይማኖት ከእግዚአብሔር ለሰው የተሰጠ መሆኑን አስረድተው እምነት የሁሉ ነገር መሠረት እንደሆነ በማብራራት መሠረት ሕንፃዎችን ሁሉ እንደሚሸከም እምነትም ምግባራትን ሁሉ እንደምትይዝ፣ ሕንፃ ያለመሠረት እንደማይቆም ምግባርም ያለ ሃይማኖት እንደማይጸና የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን ትምህርት ጠቅሰው አስተምረዋል፡፡

በዳሰሳ አቅራቢው እንደተብራራው መጽሐፉ በክፍል አንድ አንቀጹ ሠለስቱ ምእት በኒቅያው ጉባኤ የደነገጉትን ጸሎተ ሃይማኖት እና በጉባኤ ቍስጥንጥንያ የተሰበሰቡ ፻፶ ሊቃውንትን ውሳኔ መጽሐፍ ቅዱስንና ሊቃውንትን መሠረት በማድረግ ያብራራል፡፡ ባጠቃላይም ስለ ሃይማኖት በመመስከር ላይ እንደሚያተኩር እና ሰይጣንን ክዶ የክርስቶስ ተከታይ ስለመሆን እንደሚያትት የጥናቱ አቅራቢ ዲያቆን አሻግሬ አስረድተዋል፡፡ ክፍለ ሁለት የክርስቶስ የማዳን ሥራና ጸጋ እውን የሚሆነው ቃሉን በመስማትና ምሥጢራትን በመፈጸም መሆኑን እንደሚያስረዳ፣ ክፍል ሦስት ደግሞ ክርስቲያናዊ ሕይወትና ምግባር በእምነት፣ በተስፋና በፍቅር መገለጡ ተብራርቶበታል፡፡

ምእመናን የመዳን ተስፋችን እውን እንዲሆን በሥስቱ አርእስተ ሃይማኖት ማለትም በእግዚአብሔር ፍቅር፣ በክርስቶስ ጸጋ እና በመንፈስ ቅዱስ ኅብረትና ረድኤት መመሥረት እንደሚገባን ይናገራል፡፡ በተጨማሪም አባ አበራ ፍቅርን አንደኛ እግዚአብሔር ለሰው ያለው ፍቅር፣ ሁለተኛ ሰው ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅር እና ሦስተኛ ትእዛዛቱን መጠበቅ (አምላክህንና ባልንጀራህን ውደድ የሚሉትን) በማለት በሦስት ክፍል አቅርበውበታል፡፡ ይህም የአባ አበራ መጽሐፍ በዚህ ዓመት በማኅበረ ቅዱሳን እንደገና ታትሞ ገበያ ላይ ውሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሕይወት በነበሩበት ወቅት ያስተማሩት ትምህርትና ያደረጉት ንግግር በቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ሥዩምና በዲያቆን ሙሉዓለም ካሣ አስተባባሪነት በድምፅና ምስል ተቀናብሮ ለመርሐ ግብሩ ታዳሚዎች የቀረበ ሲሆን ቀጥሎም ቤተሰቦቻቸውና በቅርብ የሚያውቋቸው ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የመንፈስ ልጆቻቸው አባ አበራ ፍቅርን፣ መንፈሳዊነትን፣ ደግነትን፣ ቅንነትን እና ትሕትናን የተላበሱ፣ ከስስትና ከፍቅረ ንዋይ የራቁ አባት እንደነበሩ መስክረውላቸዋል፡፡

ታናሽ እኅታቸው ወ/ሮ ጸዳለ በቀለ አባ አበራ ሕፃን እያሉ ጥቅምት ፳፰ ቀን ወላጅ እናታቸው አዝለዋቸው በመንገድ ሲጓዙ በዘመኑ ታዳጊ ወንዶች ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሽፍቶች ባገኗቸው ጊዜ እናታቸው አባቴ አማኑኤል ሆይ ልጄን ከነዚህ ሽፍቶች ብታድንልኝ የአንተ አገልጋይ ይሁን ብለው በስእለት መልክ ለእግዚአብሔር ሰጥተዋቸው ነበር፤ ይህም ሕይወታቸውን በሙሉ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል ብለዋል፡፡

መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁንም ከሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ጋር በመሆን በስብከተ ወንጌልም በአስተዳደርም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲያገለግሉ መኖራቸውን አውስተው በተለይ ለወላጅ እናታቸው ልዩ ፍቅርና አክብሮት እንደነበራቸው ተናግረዋል፡፡ አክለውም የጻድቅ ሰው መታሰቢያ ለዘለዓለም ይኖራል የሚለውን ኃይለ ቃል መነሻ በማድረግ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ራሳቸውን መሥዋዕት አድርገውና ልዩ ልዩ ፈተናዎችን ተቋቁመው ያሰቡትን መንፈሳዊ ዕቅድ ሁሉ አሳክተው ያለፉ አባት መሆናቸውን ጠቅሰው ወጣቱ ትውልድ የእርሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅ ከቻለ አባ አበራ ሕያው ናቸው እንጂ ሞቱ አይባልም ሲሉ መልእክታቸውን አጠቃለዋል፡፡

ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ በበኩላቸው አባ አበራ በአገር ውስጥም፣ ከአገር ውጪም በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተዘዋወሩ ብዙ ዕውቀት መቅሰማቸውን ገልጸው፣ አክለውም ለሚሰማቸው ብቻ ሳይሆን ለሚመለከተቻውም አስተማሪ ሕይወት እንደነበራቸው፣ በሕይወት ከኖሩበት ጊዜ በላይ ካረፉ በኋላ ለብዙ ሰዎች ምሳሌ እንደሚሆኑና ሁሉም ሊማርባቸውና ሊያስታውሳቸው እንደሚገባ ገልጸው እኒህን አባት ለመዘከር ያመች ዘንድ በስማቸው የሚሰየም አንድ ስኮላርሺፕ ቢኖረን መልካም ነውና ሁላችንም ብናስብበት ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በተጨማሪም ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ፣ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ፣ አቶ ኤርምያስ ዓለሙ እና አቶ ሙሉጌታ ምትኩ ስለ አባ አበራ መንፈሳዊ ሕይወት ተመሳሳይ አሳብና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

ከጽርሐ ጽዮን ማኅበር አባላት አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉእመቤት በላቸውም፡- ክርስትና ማለት ራስን መካድ መሆኑን የተማርሁት ከአባ አበራ ነው፡፡ ሁላችንም አንረሳቸውም፡፡ እኛ ጊዜያችን እያለቀ ነው፡፡ እናንተ ወጣቶች ትግሉን እንደእርሳቸው ታገሉት፤ ትጥቁን እንደእርሳቸው ታጠቁት፡፡ የአባ አበራን ፈለግ ተከትላችሁ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ የሚመጣባችሁን ሁሉ ፈተና በጸጋ ተቀብላችሁ ወንጌልን ስበኩ ሲሉ እናታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በአባቶች ምክርና ጸሎተ ቡራኬ በስማቸው የተዘጋጀው ጸበል ጸሪቅ ከቀረበ በኋላ ከምሽቱ 2፡30 ገደማ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

ክቡር ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ ከአባታቸው ከግራ አዝማች በቀለ መኩሪያ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በሸዋምየለሽ ድፋባቸው ከዐዲስ አበባ በስተምሥራቅ አቅጣጫ የረር አካባቢ በሚገኘው ልዩ ስሙ ቡኢ በተባለ ሥፍራ በዕለተ ስቅለት ሚያዝያ ፪ ቀን ፲፱፻፳፰ ዓ.ም ተወልደው በ፸፫ ዓመታቸው ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል፡፡

ለአርባ አምስት ዓመታት ያህል ቅድስት ቤተ ክርስቲያንንና ሀገራቸውን በፍጹም ፍቅር ሲያገለግሉ የቆዩት ሊቀ ጉባኤ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ካበረከቱት ከፍተኛ አተዋጽዖ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን በውኃ እንፋሎት የሚንቀሳቀስ መኪና የሠሩ ጥበበኛም ነበሩ፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንም እኒህ ታላቅ አባት ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ግምት ውስጥ በማስገባት የሰባተኛ ዓመት የዕረፍት ቀናቸው እንዲዘከር አድርጓል፡፡

ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፲፪ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ ግንቦት ፲፪ ቀን በዚህች ቀን ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት፣ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ እስክንድር፣ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ መስቀል፣ ቅዱስ ሚናስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ የመላልዔል ልጅ ያሬድ፣ እንደዚሁም ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይታሰባሉ፡፡ በዚህ ዝግጅት የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ፍልሰተ ዓፅም የሚያስታውስ ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ስምዑ ወለብዉ ኦ ፍቁራንየ መጽሐፈ ዜናሁ ለክቡር ወቅዱስ ወለብፁዕ ፍቁረ እግዚአብሔር ዘይትነበብ በዕለተ ፍልሰተ ሥጋሁ አመ ፲ወ፪ ለግንቦት ዝ ውእቱ ድሙር ምስለ በዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበዓለ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ፍቁሩ ለተክለ ሃይማኖት፤ ወዳጆቼ ሆይ፣ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ የተደነቀ፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሚሆን የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ክብሩን፣ ገናንቱን የሚናገረውን፣ ዐፅሙ የፈለሰበትን ግንቦት ፲፪ ቀን የሚነበበውን መጽሐፍ አስተውላችሁ ስሙ፤ /ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ.፷፪፥፭/፡፡

ተክል ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው /ማቴ.15፥13/፡፡ ሃይማኖት ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የሁሉ አስገኚ መሆኑን፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን አምኖም መመስከር ማለት ሲሆን ተክለ ሃይማኖት የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራና ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል ትርጕም ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ ገድላቸውም ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው ሲል ይተረጕመዋል፡፡ አባታችን እርሳቸውም በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ አድርገዋልና፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ከአገራችን ከኢትዮጵያ ምድር ከሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከኢቲሳ መንደር ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው እግዚእ ኀረያ አብራክ የተገኙ ቅዱስ አባት ናቸው፡፡ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን ውለታቸውን በማሰብና ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ቅድስና መሠረት በማድረግ በስማቸው ጽላት ቀርፃ ስታከብራቸው ትኖራለች፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወሱባቸው በዓላት መካከልም በዛሬው ዕለት የሚከብረው ፍልሰተ ዐፅማቸው አንደኛው ሲሆን ታሪኩንም በአጭሩ እነሆ፤

ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደእርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነግሯቸው የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ሁሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾ ታያቸው፤ ነፍሳቸውንም የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደእኔ ነዪ ብሎ በክብር ተቀበላት፡፡

በመጽሐፈ ገድላቸው እንደተጠቀሰው ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ ገድላቸው ዕድሜያቸውን በመከፋፈል፡- በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በዊፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይ ገዳማት በመዘዋወርና ወደ ኢየሩሳሌም በመመላለስ ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በአሰቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን ይናገራል /ገ.ተ.ሃ.፶፱፥፲፬-፲፭/፡፡

ወደ ፍልሰተ ዐፅማቸው ታሪክ ስንመለስ መጽሐፈ ገድላቸው እንዲህ ሲል ይጀምራል፤ ስምዑ ወለብዉ ኦ ፍቁራንየ መጽሐፈ ዜናሁ ለክቡር ወቅዱስ ወለብፁዕ ፍቁረ እግዚአብሔር ዘይትነበብ በዕለተ ፍልሰተ ሥጋሁ አመ ፲ወ፪ ለግንቦት ዝ ውእቱ ድሙር ምስለ በዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበዓለ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ፍቁሩ ለተክለ ሃይማኖት፤ ወዳጆቼ ሆይ፣ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ የተደነቀ፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሚሆን የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ክብሩን፣ ገናንቱን የሚናገረውን፣ ዐፅሙ የፈለሰበትን ግንቦት ፲፪ ቀን የሚነበበውን መጽሐፍ አስተውላችሁ ስሙ፤ ይኸውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል ጋር የተክለ ሃይማኖት ወዳጅ ከመላእክት አለቃ ከቅዱስ ሚካኤል በዓል ጋር የተባበረ ነው፡፡ ወንድሞቻችን እንነግራችኋለን፤ እናስረዳችኋለን፡፡ እንደ ዮሐንስና እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ከእናቱ ማኅፀን እግዚአብሔር የመረጠው የክቡር አባታችን ዐፅሙ የፈለሰበት ቀን ዛሬ ነው፤ /ገ.ተ.ሃ.፷፪፥፭-፰/፡፡

አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ዓለም ከተለዩ በ፶፯ኛው ዓመት የካቲት ፲፱ ቀን ለመንፈስ ልጃቸው ለአባ ሕዝቅያስ ብርሃን ለብሰው በሕልም ተገለጡላቸውና ወዳጄ ሕዝቅያስ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን! ጌታዬ በኋለኛው ዘመን ከዚህ ሥፍራ ልጆችህ ሥጋህን ያፈልሳሉ ያለኝ ዘመን ደርሷልና ሳትዘገይ ልጆቼን ሁሉ ቅጠራቸውና እስከምፈልስበት ቀን ድረስ ግንቦት ፲፪ ቀን ይሰብሰቡ፡፡ እናንተም በምስጋና በጸሎት መንፈሳዊ በዓልን አድርጉ፡፡ አባቴ ተክለ ሃይማኖት የሚለኝ ሁሉ በዚህች በፍልሰተ ዐፅሜ ቀን ይምጣ፤ መንፈሳዊ በዓልንም ያድርግ፡፡ እኔና ቅዱስ ሚካኤል ከወዳጄ አባ ፊልጶስ ጋር ስለኔ ፍቅር የተሰበሰበውን ሕዝብ ልንባርክ እንመጣለን፤ ከአሏቸው በኋላ ተሠወሯቸው፡፡

አባ ሕዝቅያስም እንደታዘዙት የአባታችሁን ዐፅም ከዋሻው ወደ ታላቁ ቤተ ክርስቲያን ታፈልሱ ዘንድ ኑ፤ ተሰብሰቡ ብለው የአባታችን ወዳጆች በያሉበት ሀገር ሁሉ መልእክት ላኩ፡፡ ምእመናንም ጥሪውን ተቀብለው በዓሉን ለማክበር ከአራቱም አቅጣጫ ተሰበሰቡ፡፡ ዐሥራ ሁለቱ መምህራንም መጡ፤ እነዚህም፡- የወረብ አገሩ አባ አኖሬዎስ፣ የፈጠጋሩ አባ ማትያስ፣ የእርናቱ አባ ዮሴፍ፣ የሞረቱ አባ አኖሬዎስ፣ የመርሐ ቤቴው አባ መርቆሬዎስ፣ የጽላልሹ አባ ታዴዎስ፣ የወገጉ አባ ሳሙኤል፣ የወንጁ አባ ገብረ ክርስቶስ፣ የድንቢው አባ መድኃኒነ እግዚእ፣ የዳሞቱ አባ አድኃኒ፣ የክልአቱ አባ ኢዮስያስ እና የመሐግሉ አባ ቀውስጦስ ናቸው፡፡

እነዚህ መምህራን ከአባ ሕዝቅያስ ጋር በመሆን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ዐፅም ከዐረፈበት ዋሻ ባወጡት ጊዜ ዐፅማቸው ዕለት የተገነዘ በድን ይመስል ነበር፤ መዓዛውም ሽቱ፣ ሽቱ ይሸት ነበር፡፡ በአባታችን ዐፅም ቀኝና ግራም መስቀል ተተክሎ ነበር፡፡ በዐፅማቸውም ብዙ ድንቅ ተአምራት ተደርገዋል፡፡ ይህንን የአባታችንን ዐፅም አባ ሕዝቅያስና ዐሥራ ሁለቱ መምህራን በሣጥን አክብረው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወስደው በመንበሩ ፊት ሦስት ጊዜ አዞሩት፡፡

በዚህች ዕለት አስቀድመው የካቲት ፲፱ ቀን ለአባ ሕዝቅያስ በሕልም እንደነገሯቸው ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከቅዱስ ሚካኤልና ከአባ ፊልጶስ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጥተው ዐፅማቸው እስኪያረፍ ድረስ ከመንበሩ ተቀምጠው ቆይተው ዐፅማቸው ካረፈ በኋላ የተሰበሰበውን ሕዝብ ባርከው በክብር ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ መምህራኑና ምእመናኑም በዓሉን በታለቅ ደስታ አክብረው በሰላም ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐፅም ከዋለበት ዕለት ጋር ርክበ ካህናት አብሮ መዋሉ በዓሉን ልዩ ድምቀት ሰጥቶት ነበር /ገ.ተ.ሃ.፷፭፥፩-፳፬/፡፡

ከዚያ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምእመናን እየተሰበሰቡ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ፡፡ የብፁዕ አባታችን ዐፅማቸው በፈለሰበት ዕለት ዐሥራ ሁለቱ መምህራን እና በርካታ ምእመናንን እንደተሰበሰቡ ሁሉ እኛንም እግዚአብሔር አምላካችን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስበን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የመንፈስ ልጆቻቸው ጸሎት፣ ረድኤትና በረከት ለዘለዓለሙ ይጠብቀን፡፡

ምንጭ፡-

ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፪ ቀን፡፡

ቅዱስ ያሬድ ኢትዮጵያዊ

ግንቦት ፲፩ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም

ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ በየዓመቱ ግንቦት ፲፩ ቀን ከሚታወሱ ቅዱሳን መካከል የእመቤታችን እናት ቅድስት ሐና፣ ቅድስት ታውክልያ፣ ቅዱስ በፍኑትዩስ፣ አባ አሴር፣ ቅዱስ ያሬድ፣ ብፅዕት አርሴማ፣ ቅድስት ኤፎምያ፣ ቅድስት አናሲማ፣ ቅድስት ሶፍያ፣ አባ በኪሞስ፣ አባ አብላዲስ እና አባ ዮልዮስ ተጠቃሾች ሲሆኑ፣ በዛሬው ዝግጅታችን የቤተ ክርስቲያን እንዚራ፣ የኢትዮጵያ ብርሃን እየተባለ የሚጠራውን የቤተ ክርስቲያናችን ድምቀት፣ የአገራችን ኩራት የሆነውን የጥዑመ ልሳን፣ ኢትዮጵያዊ ማኅሌታይ የቅዱስ ያሬድን ታሪክ በአጭሩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

በ፭፻፭ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ በአክሱም ከተማ ከአባቱ ከአብዩድ (ይስሐቅ) እና ከእናቱ ታውክልያ (ክርስቲና) አንድ ቅዱስ ተገኘ፤ ይኸውም ቅዱስ ያሬድ ነው /ገድለ ቅዱስ ያሬድ/፡፡ ቅዱስ ያሬድ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ ከአጎቱ ከአባ ጌዴዎን ዘንድ ትምህርት ሊማር ቢሔድም ለበርካታ ዓመታት ትምህርት ሊገባው አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም የተነሣ መምህሩ ይገርፉት፣ ይገሥፁት ነበር፡፡ እርሱም ከትምህርቱ ክብደት ባለፈ የመምህሩ ተግሣፅ ሲበረታበት ጊዜ ከአባ ጌዴዎን ቤት ወጥቶ በመሸሽ ላይ ሳለ ደክሞት ከአንድ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፡፡

ከዛፉ ሥር ተጠልሎ ሳለ አንድ ትል ፍሬውን ለመመገብ ወደ ዛፉ ሲወጣ፣ ነገር ግን መውጣት ስለተሳነው በተደጋጋሚ ሲወድቅ ቆይቶ ከብዙ ሙከራ በኋላ ከዛፉ ላይ ሲወጣ፣ ፍሬውንም ሲመገብ ይመለከታል፡፡ ቅዱስ ያሬድ የትሉን ትጋት ከአየ በኋላ እርሱም በተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግ የከበደው ምሥጢር እንደሚገለጽለት በማመን ወደ መምህሩ ተመልሶ ይቅርታ ከጠየቀ በኋላ ትምህርቱን እንደገና መቀጠል ጀመረ፡፡ እግዚአብሔርን በጸሎት እየተማጸነ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ልቡናው ብሩህ ሆኖለት የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ትርጓሜን አጠናቆ መዓርገ ዲቁና ተቀበለ፡፡

እግዚአብሔርም የክብር መታሰቢያ ሊያቆምለት ወዷልና ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ልኮ በሰው አንደበት እንዲያናግሩት አደረጋቸው፡፡ እነርሱም ካናገሩት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሰማያዊት አወጡትና በዚያም የሃያ አራቱን ካህናተ ሰማይ (ሱራፌል) ማኅሌት ተማረ፡፡ ወደ ምድርም ተመልሶ በአክሱም ጽዮን በሦስት ሰዓት ገብቶ በታላቅ ቃል፡- ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ ቀዳሚሃ ለጽዮን ሰማየ ሣረረ ወበዳግም አርአዮ ለሙሴ ዘከመ ይገብር ግብራ ለደብተራ፤ ለአብ ምስጋና ይገባል፤ ለወልድ ምስጋና ይገባል፤ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይገባል፡፡ የጽዮን ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ፡፡ ዳግመኛም እንዴት መሥራት እንዳለበት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው፤ አስተማረው እያለ በዜማ እግዚአብሔርን አመሰገነ፡፡ የቅዱስ ያሬድን ድምፅ የሰሙ ሁሉ ጳጳሳቱና ነገሥታቱ ሳይቀሩ ካህናቱም ምእመናኑም ወደርሱ ተሰብስበው ሲሰሙት ዋሉ፡፡ ይህንንም ምስጋና አርያም ብሎ ጠራው፤ ይኸውም በዜማ ትምህርት ቤት ከቃል ትምህርቶች አንደኛው ሆኖ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር ይህንን ሊቅ፡- አምሳሊሆሙ ለሱራፌል፤ የሱራፌል አምሳላቸው ይለዋል፡፡ ከመላእክት ወገን የሆኑት ሱራፌል እግዚአብሔርን ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያሉ በመንበሩ ፊት ቆመው እንደሚያመሰግኑ ሁሉ ቅዱስ ያሬድም ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እያለ በመላእክት ቋንቋ እግዚአብሔርን አመስገኗልና፤ ደግሞም የተማረው ከእነርሱ ነውና የሱራፌል አምሳላቸው ተባለ፡፡ እርሱም፡- ሃሌ ሉያ ዋይ ዜማ ዘሰማዕኩ በሰማይ እመላእክት ግናይ እንዘ ይብሉ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር መልዐ ሰማያተ ወምድረ ቅድሳተ ስብሓቲከ፤ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን! ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ እግዚአብሔር፤ የምስጋናህ ስፋት ሰማይና ምድርን መላ፤ /ኢሳ.፮፥፫/እያሉ ሲያመሰግኑ ከመላእክት የሰማሁት ምስጋና ምንኛ ድንቅ ነው? በማለት ዜማውን የተማረው ከመላእክት መሆኑን በድርሰቱ መስክሯል፡፡

ከዚያ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝቶ ከዓመት እስከ ዓመት ድረስ በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ፣ በአጽዋማትና በሰንበታት፣ እንዲሁም በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በሰማዕታት፣ በደናግል በዓላት የሚደረስ ቃለ እግዚአብሔር በሦስት ዜማዎች ማለትም በግእዝ፣ በዕዝልና በአራራይ ደረሰ፡፡ የሰው ንግግር፣ የአዕዋፍ፣ የእንስሳትና የአራዊት ጩኸት ሁሉ ከነዚህ ከሦስቱ ዜማዎች እንደማይወጡ መጽሐፈ ስንክሳር ይናገራል፡፡

በአንዲት ዕለት ቅዱስ ያሬድ ከብሉይና ከሐዲስ፣ እንደዚሁም ከሊቃውንትና ከመነኮሳት የተውጣጣውን መንፈሳዊ ድርሰቱን በዘመኑ ከነበረው ከንጉሥ ገብረ መስቀል ፊት ቆሞ ሲዘምር ንጉሡ በድምፁ በመማረኩ የተነሣ ልቡናው በተመስጦ ተሠውሮበት (የሚያደርገዉን ባለማወቁ) የቅዱስ ያሬድን እግር በጦር ወጋው፡፡ ከቅዱስ ያሬድ እግር ደምና ውኃ ቢፈስስም ነገር ግን ማኅሌቱን እስኪፈጽም ድረስ ሕመሙ አልተሰማውም ነበር፡፡

ንጉሡም ያደረገዉን ሁሉ ባወቀ ጊዜ ደነገጠ፤ ጦሩንም ከእግሩ ነቅሎ ስለፈሰሰው ደምህ ዋጋ የምትፈልገዉን ሁል ለምነኝ እያለ ተማጸነው፡፡ ቅዱስ ያሬድም ላትከለክለኝ ማልልኝ ብሎ ቃል ካስገባው በኋላ ወደ ገዳም ሔዶ ይመነኩስ ዘንድ እንዲፈቅድለትና እንዲያሰናብተው ለመነው፡፡ ንጉሡም ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ፤ ተከዘ፡፡ ከእርሱ እንዲለይ ባይፈልግም ነገር ግን መሐላዉን ማፍረስ ስለከበደው እያዘነ አሰናበተው፡፡

ከዚያም ቅዱስ ያሬድ በአክሱም ጽዮን ቤተ መቅደስ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ፡- ቅድስት ወብፅዕት ስብሕት ወቡርክት ክብርት ወልዕልት አንቀጸ ብርሃን መዐርገ ሕይወት፤ ፈጽሞ የከበርሽና የተመሰገንሽ፣ ከፍ ከፍም ያልሽ፣ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽƒ‚ƒƒ‚ እያለ አንቀጸ ብርሃን የተባለውን የእመቤታችን ምስጋና እስከ መጨረሻው ድረስ ደረሰ፡፡ ይህንን ጸሎት ሲያደርስም አንድ ክንድ ያህል ከመሬት ከፍ ብሎ ይታይ ነበር፡፡ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሔዶ (ሰሜን ተራሮች አካባቢ) በጾም በጸሎት ተወስኖ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያው ፈጸመ፡፡ እግዚአብሔርም ስሙን ለሚጠራ፣ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው፤ ከዚያም በሰላም ዐረፈ፡፡ /ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፩/

የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት በገድለ ቅዱስ ያሬድ ላይና በመጽሐፈ ስንክሳር እንደመዘገቡልን ግንቦት ፲፩ ቀን ቅዱስ ያሬድ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ያረፈበት ቀን ነው፤ እዚህ ላይ ግን አከራካሪ ጉዳይ አለ፤ ይኸውም አንደኛው ቅዱስ ያሬድ ሞቶ ተቀብሯል የሚል ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ ቅዱስ ያሬድ እስከነ ነፍሱ ተሠወረ እንጂ አልሞተም የሚል ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ሞተ የሚሉ ወገኖች ከሚጠቅሷቸው ማስረጃዎች ውስጥ በመጽሐፈ ስንክሳር፡- ወበዛቲ ዕለት አዕረፈ ያሬድ ማኅሌታይ፤ በዚህች ዕለት ማኅሌታይ ያሬድ ዐረፈ፤ እና ወእምዝ አዕረፈ በሰላም፤ ከዚህ በኋላ በሰላም ዐረፈ የሚሉት ሐረጋት የሚገኙ ሲሆን፣ ተሠወረ የሚሉት ደግሞ እዚያው ስንክሳሩ ላይ፡- ወእምዝ ሖረ ሀገረ ሰሜን ወነበረ ህየ ወፈጸመ ገድሎ፤ ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን አገር ሒዶ ገድሉን በዚያ ፈጸመ፤ ተብሎ የተገለጸውን እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡

በእርግጥ ቃሉን በትኩረት ለተመለከው ሰው ዐረፈ ማለት ሞትን ብቻ ሳይሆን እንደነ ሄኖክ ከዚህ ዓለም ጣጣና እንግልት ተለይቶ በሕይወት እያሉ (ሳይሞቱ) ተሠውሮ መኖርንም ያመለክታል፡፡ ገድሉን በሰሜን አገር ፈጸመ የሚለውም መሠወሩን ብቻ ሳይሆን መሞቱንም ሊያመለክት ይችላል የሚሉም አሉ፡፡ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን መምህራን እንደሚያስተምሩን እነእገሌ ቀበሩት የሚል ቃል ስለማይገኝ ቅዱስ ያሬድ ተሠወረ እንጂ ሞተ ተብሎ አይነገርለትም፡፡ ለዚህም ማስረጃ እርሱ በተሠወረበት ተራራ እስከ አሁን ድረስ የከበሮ (የማኅሌት) ድምፅ ይሰማል፤ የዕጣን መዓዛ ይሸታል፡፡ ይህም ቅዱሱ ከሰው ዓይን ተሠውሮ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንደሚገኝ አመላካች ነው፡፡

የቅዱስ ያሬድ ድርሰቶችም ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለአገርም ድንቅና ወደር የሌላቸው ሀብቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የዜማ ድርሰቶቹ (ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ፣ መዋሥዕት) እንደሌሎቹ ቅርሶች ሁሉ በዩኔስኮ እንዲመዘገቡ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከፍተኛ ርብርብ በያደርጉ መልካም ነው፡፡ በቅዱስ ያሬድ ዜማ የሚደምቀው በዓለ ጥምቀት በዩኔስኮ ሲመዘገብ ዜማውን ከበዓሉ ለይቶ ማስቀረት የታሪክ ተወቃሾች ያደርገናልና ሁላችንም እናስብበት እንላለን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በአባታችን በቅዱስ ያሬድ ጸሎት ይማረን፡፡ በረከቱም ከእኛ ጋር ለዘለዓለም ትኑር፤ አሜን፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን አዘጋጅነት ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀረቡ

ግንቦት ፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

ዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በጸሎተ ሃይማኖት *ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ* የሚለው ንባብ *በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ* ተብሎ መስተካከል አለበት ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕቃ ቤትና በቅዱሳት መካናት አማካኝነት የቅርስ ቤተ መዛግብት እንደሆነች ተገልጿል፡፡

ወጣቱ ትውልድ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት ተነግሯል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማዕከል አዘጋጅነት *የአርዮስና መንፈቀ አርዮሳውያን ተጽዕኖ በቤተ ክርስቲያን ላይ* እና *የቤተ ክርስቲያን ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የመጠበቅ ሒደት በአድባራትና ገዳማት* በሚሉ ዐበይት አርእስት የሚመለከታቸው ምሁራንና ተሳታፊ ምእመናን በተገኙበት ቅዳሜ ግንቦት ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በማኅበሩ አዳራሽ ሁለት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡

*የአርዮስና መንፈቀ አርዮሳውያን ተጽዕኖ በቤተ ክርስቲያን ላይ* በሚለው ርእሰ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ቀሲስ ዶክተር ምክረ ሥላሴ ገብረ አማኑኤል ሲሆኑ በጥናታቸውም የአርዮስ የኑፋቄ ትምህርት የእግዚአብሔር ወልድን የባሕርይ አምላክነት የሚቃወም መሆኑን ጠቅሰው አርዮስና ኑፋቄዉ በ፫፻፲፰ ኦርቶዶክሳውያን ሊቃውንት በ፫፳፭ ዓ.ም በኒቅያ በተደረገው ጉባኤ ቢወገዝም ትምህርቱ ግን እስከ ዛሬ ድረስ ቤተ ክርስቲያንን እየተፈታተናት እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

አያይዘውም በጉባኤ ኒቅያ በተወሰነው የሃይማኖት መሠረት (ጸሎተ ሃይማኖት) ውስጥ *ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ* የሚለው የግእዝ ንባብ *በመለኮቱ ከአብ ጋር የሚተካከል* ተብሎ መተርጐሙ ትክክል አለመሆኑን መረጃ በማስደገፍ ገልጸው ይህ ሐረግ *በመለኮቱ ከአብ ጋር አንድ የሆነ* ተብሎ መስተካከል እንዳለበትና የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትም ይህንን ምሥጢር ለምእመናን ማስረዳት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡

*የቤተ ክርስቲያን ተንቀሳቃሽ ቅርሶችን የመጠበቅ ሒደት በአድባራትና ገዳማት* በሚለው ርእስ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዲያቆን አለባቸው በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕቃ ቤትና በቅዱሳት መካናት አማካኝነት በቅርስ ቤተ መዛግብትነት የምትገኝ መሆኗን ጠቅሰው ወጥ የሆነ መመሪያና ዕቅድ አለመኖር፣ የቅርስ አጠባበቅና ክብካቤ ችግር፣ ወዘተ የመሰሉ ተግዳሮቶች እንዳሉባት በጥናታቸው ጠቁመዋል፡፡

በጥናታቸው ማጠቃለያም ቤተ ክርስቲያናችን የእምቅ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ገልጸው የዕቅድና ወጥ መመሪያ ዝግጅት፣ የአስተዳደርና የዓቅም ግንባታ ሥራ፣ ለምእመናን ስለቅርሶች ግንዛቤ መስጠትና የባለቤትነት ስሜት እንዲያድርባቸው ማድረግ፣ ወዘተ የመሰሉ ተግባራት ለቅርስ አጠባበቅ ችግር መፍትሔ ሊሆኑ እንደሚችሉ በዝርዝር አስረድተው *ሁላችንም ይህንን በመረዳትና የተጀመሩ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለወደፊት የተሻለ መሥራት ይጠበቅብናል* ብለዋል፡፡

በዐውደ ጥናቱ ላይ ከተገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መካከል አንዱ የሆኑት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘርይሁን አስተያየት በሰጡበት ወቅት፣ *ትልቁ ነገር የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች መመለስ ነው፤ ማኅበረ ቅዱሳን መምህራንን በመጋበዝ እንደዚህ ዓይነት ጥናታዊ ውይይት ማካሔዱ ለአባቶች ተገዢ መሆኑን አመላካች ተግባር ነው* ብለዋል፡፡ በተጨማሪም *ቤተ ክርስቲያናችን፣ Living Church of Living Faith and Ever Growing Church – ዘለዓለማዊት፣ የዘለዓለማዊው ሃይማኖት መሪ የሆነች እና ዘለዓለም የምታድግ ናት፤ ስለሆነም ወጣቱ ትውልድ የዚህችን ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነት አለበት* ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በመጨረሻም በሁለቱም ጥናቶች ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሡ ጥያቄዎች በአቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቶ ሲያበቃ የውይይቱ መሪ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ የማጠቃለያ ንግግር ካደረጉ በኋላ በአባቶች ቃለ ምዕዳንና ጸሎተ ቡራኬ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል መታሰቢያ ሐውልት ቆመላቸው

ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም በድምቀት ይመረቃል፡፡

ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

ለሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በጎሬ ከተማ ላይ የተሠራላቸው መታሰቢያ ሐውልት ግንቦት 14 ቀን 2008 ዓ.ም በድምቀት እንደሚመረቅ መታሰቢያ ሐውልቱን በማስገንባት ላይ የሚገኘው ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የሐውልቱ ምርቃት ቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያ ሓላፊዎችና የጎሬ ሕዝብ በተገኙበትይመረቃል፡፡

ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ጎንደር ጠቅላይ ግዛት በደብረ ታቦር አውራጃ እስቴ ወረዳ ልጫ መስቀለ ክርስቶስ በሚባል ቦታ ከአባታቸው ከቄስ ገብረ ክርስቶስና ከእናታቸው ወ/ሮ ትኩዬ በ1874 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ከፊደል ጀምሮ ጸዋትወ ዜማ፣ ዝማሬና መዋስዕት፣ ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ መዝገበ ቅዳሴ ከነትርጓሜው፣ አቋቋምና ቅኔ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ከታላላቅ መምህራን ተምረዋል፡፡

ግንቦት 25 ቀን 1921 ዓ.ም ከዐራት አባቶች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ በማቅናት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ተብለው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ ከብፁዕነታቸው ጋር ጵጵስናን የተቀበሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡

ከግብፅ እንደተመለሱም ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የምዕራብ ኢትዮጵያ /የጎሬና የወለጋ ጠቅላይ ግዛት/፣ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የምሥራቅ ኢትዮጵያ፣ ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ የትግራይና የሰሜን ኢትዮጵያ፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጎንደርና የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ሊቃነ ጳጳሳት ሆነው ተሹመው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን አገልግለዋል፡፡

በ1928 ዓ.ም ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ከፍተኛ ተጋድሎ ከፈፀሙ አባቶች መካከል ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል አንዱ ናቸው፡፡ ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ አዲስ አበባ ላይ በፋሺስት ኢጣሊያ ከተገደሉ ከዐራት ወራት በኋላ ጎሬ ላይ ፋሺስትን አውግዘው ሰማዕትነት ተቀብለዋል፡፡

በመተከል ሀገረ ስብከት ግልገል በለስ 8620 አዳዲስ አማንያን ተጠመቁ

ሚያዝያ 17 ቀን 2008 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

እስከዚህ ዕድሜያችን ድረስ ስንጠብቃችሁ ነበር ተጠማቂያኑ፡፡

02gilgel 2በመተከል ሀገረ ስብከት በግልገል በለስ ማእከል ሥር በሚገኙ 3 ወረዳዎች 8620 አዳዲስ አማንያንን ሚያዝያ 15 እና 16 ቀን 2008 ዓ.ም መጠመቃቸውን የማኅበረ ቅዱሳን ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ገለጸ፡፡

በማንዱራ፣ ድባጤ እና ዳንጉ ወረዳዎች የሚገኙት እነዚህ አዳዲስ አማንያን በማኅበረ ቅዱሳን አስተባባሪነት ከሀገረ ስብከቱ፣ ከወረዳ ቤተ ክህነቶች እና ከግልገል በለስ ማእከል ጋር በመተባበር የቅድሰት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ሲማሩ መቆየታቸውን ከማኅበሩ የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ መርሐ ግብር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ፍቅር እንዳላቸው የገለጹት ተጠማቂያኑ እስከዚህ ዕድሜያችን ድረስ ስንጠብቃችሁ ነበር በማለት ሲናፍቁት የነበረው ጊዜ በመድረሱና ፍላጎታቸው በመሳካቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

የመረጃው ዝርዝር እንደደረሰን እናቀርባለን፡፡

ሆሳዕና

ሚያዝያ 14 ቀን 2008 ዓ.ም

በመምህር ኃለ ማርያም ላቀው

ሆሳዕና የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ሆሼዕናህ የሚል ሲሆን ትርጉሙም እባክህ አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ይህ ቃል በዘመነ ብሉይ በቀደምት ነቢያት ዘንድ የተለመደ ቃል ነው፡፡ አቤቱ እባክህ አሁን አድን፣ አቤቱ እባክህ አሁን አቅና፣ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፡፡ መዝ.117፡25-26 የሆሳዕና በዓል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የሚቀድሙትና የሚከተሉት ሕዝብ በተለይም አእሩግና ሕፃናት ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፣ ሆሳዕና በአርያም በማለት ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል ነው፡፡ በዓሉም ሆሳዕና የሚለውን ስያሜ ያገኘው በዕለቱ ከተዘመረው መዝሙር ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ይህ ዕለት የጸበርት እሑድ /Palm Sunday/ ይባላል፡፡ ታሪካዊ አመጣጡ የመልካም ምኞትና የድል አድራጊነት መገለጫ ሆኖ ከደገኛው አባታችን ይስሐቅ ልደት ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ይኸውም ሣራ የወላድነት ዕድሜዋን ጨርሳ ልማደ እንስት ከተቋረጠባት በኋላ ሁሉን ቻይ የሆነ አምላክ ይስሐቅን በሰጣት ጊዜ ዘመዶችዋ የተሰማቸውን ደስታ ለመግለጽ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ የጎበኟትን አምላክ አመስግነዋል፡፡ እስራኤል ከአስከፊው የግብፃውያን አገዛዝ ተላቀው ባሕረ ኤርትራን በደረቅ ሲሻገሩ የተሰማቸውን እጥፍ ድርብ ደስታ በገለጡ ጊዜ፣ እንዲሁም ዮዲት የተባለች ንግሥተ እስራኤል ሆሎፎርኒስ የተባለ አላዊ ንጉሥን ድል ባደረገች ጊዜ ቤተ እስራኤል እንደ ሰንደቅ ዓለማ የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ አደባባይ ወጥተው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፡፡

በዘመነ ሐዲስም መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ዘር ከዲያብሎስ ቁራኝነት ከሲኦል ባርነት ነጻ ለማውጣት ወደ ዙፋን መስቀሉ /ሉቃ.22፤18/ በተጓዘ ጊዜ ሕፃናት እና አእሩግ ነጻ የሚወጡበት ቀን መድረሱን እነርሱ ሳያውቁ እግዚአብሔር ባወቀ ዘንባባ በመያዝ ዘምረዋል፡፡ እስራኤል ዘንባባ በመያዝ እንዳመሰገኑት እኛም አስራኤል ዘነፍስ ዕለቱን ዘንባባ /ጸበርት/ በግንባራችን በማሰር በዓሉን በየዓመቱ እያስታወስን እናከብራለን፡፡ በዚህ ዕለት ዘንባባ እየተባረከ ለሕዝቡ ይታደላል፡፡

ሕፃናትና አእሩግ ለዳዊት ልጅ መድኃኒት መባል ይገባዋል፡፡ እያሉ ዘምረዋል፡፡ ይህ ሁሉ በአንድ ወገን የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሲሆን በሌላ በኩል የነበረው አቀባበል ደግሞ እጅግ የሚያሳዝን ነበር፡፡ ሥርዓተ ኦሪትን፣ ትንቢተ ነቢያትን በሚገባ እንከተላለን ይሉ የነበሩ ጸሐፍት ፈሪሳውያን መምህር ሆይ ደቀ መዛሙርትህን ገሥጻቸው አሉት፡፡ ጌታችንም መልሶ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ ሲል መልሶላቸዋል፡፡ ቅናት አቅላቸውን ያሳታቸው ፈሪሳውያንም የዋህ የሆነው ሕዝብ ምስጋና ወደ ጥላቻ እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡ ከሁሉ የሚያሳዝነው በዕለተ ሆሳዕና እሑድ ዘንባባ ይዘው የዘመሩለትን ጌታ ዓርብ ይሰቀል ዘንድ ይገባል ብለዋል፡፡

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ጀርባ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚህም በነቢዩ ዘካርያስ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ትንቢት ተፈጸመ፡፡እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው፤ ትሑትም ሆኖ በአህያም፣ በአህያዪቱ ግልገል በውርንጫዪቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡ ዘካ.9፡9፤ ማቴ.21፡4፤ ማር.11፡1-10፤ሉቃ.19፡28-40፤ ዮሐ.12፤15፡፡ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መሆኑን ያመለክታል፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲሆንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ ነበር፡፡ ጌታም እውነተኛ የኅሊና ሰላም ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ጀርባ ወደ ቤተ መቅደስ ሕይወታችን ተጉዟል፡፡

መላእክት በዕለተ ልደቱ በሰማይ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል በምድር ሰላም ለሰው ሁሉ ይሁን /ሉቃ.2፡13/ እያሉ የዘመሩለት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ በመዋዕለ ትምህርቱም ሰላሜን እሰጣችኋለሁ /ዮሐ.14፡27/ ብሎ እንዳስተማረ ያን ሰላም የሚሰጥበትን ዕለት መቅረቡን ለማመልከት ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአህያ ጀርባ መቀመጡ ኅቡዕ ምሥጢር አለው፡፡ በአህያ ጀርባ የተቀመጠ ሰው ሌላውን አሳድዶ አይዝም፣ እርሱም ሮጦ አያመልጥም፡፡ በዚህም ጌታችን በእምነት ለሚፈልጉት የሚገኝ ቅርብ ሲሆን በእምነት ለማይፈልጉት ግን የማይገኝ መሆኑን አስተምሯል፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ፀሐይ ዕድሜያችን ሳትጠልቅ በእምነት እንፈልገው፡፡ አሞጽ4፡፡ የአህያን ጀርባ ያልናቀ ጌታችን ትሑት ሰብእና እና የተሰበረ ልቡና ወዳለው ሰው ዘወትር ይጓዛል፣ የተዋረደውንና የተሰበረውን ልብ አይንቅም፡፡ ኢሳ.66፡2፤ መዝ.50፡17፡፡

ለታሰሩት መፈታትን ሊሰብክ ሰው የሆነ ጌታችን ከማሰሪያዋ በተፈታች አህያ እንደተቀመጠ ሁሉ ከኃጢአት እስራት በተፈታ ሕይወት ዛሬም ያድራል፤ የኅሊና ሰላምን ይሰጣል፡፡ ስለዚህ ንስሐ ገብተን ጌታችንን ሆሳዕና በአርያም እያልን ልናመሰግነው ይገባል፡፡

ምንጭ፡ ሐመር ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ መጋቢት/ሚያዝያ 1996 ዓ.ም