ርክበ ካህናት

ግንቦት ፲፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ረክብ የሚለው ቃል ተራከበ ተገናኘ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ሲሆን ትርጕሙም ማግኛ፣ መገኛ፣ መገናኛ ማለት ነው /ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ገጽ ፰፴፩/፡፡ ርክበ ካህናትም የካህናት መገኛ፣ መገናኛ፣ ጉባኤ (መሰባሰቢያ)፣ መወያያ፣ ወዘተ የሚል ትርጕም ይኖረዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ቋንቋ ክህነት የሚለው ቃል ከጵጵስና ጀምሮ እስከ ዲቁና ድረስ ያሉትን መዓርጋት የሚያጠቃልል ስያሜ ሲሆን ካህን (ነጠላ ቍጥር)፣ ካህናት (ብዙ ቍጥር) በአንድ በኩል ቀሳውስትን የሚወክል ሆኖ በሌላ በኩል ደግሞ የጳጳሳት፣ የኤጲስ ቆጶሳት፣ የቀሳውስት፣ የዲያቆናት የጋራ መጠሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ርክበ ካህናት የቃሉ ትርጕም እንደሚያስረዳው የአባቶች ካህናት ማለትም የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት (የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት) ጉባኤ ማለት ነው፡፡

በዓሉ በየዓመቱ የትንሣኤ በዓል በዋለ በ፳፭ኛው ቀን ሁልጊዜ በዕለተ ረቡዕ ይዋል እንጂ ወሩና የሚውልበት ቀን ግን የበዓላትንና የአጽዋማትን ቀመር ተከትሎ ከፍና ዝቅ ሊል ይችላል፡፡ የአጽዋማትና የበዓላት ቀመር ከመዘጋጀቱ በፊት ማለትም በቅዱስ ድሜጥሮስ አማካኝነት ዐቢይ ጾም ሰኞ፣ ስቅለት ዓርብ፣ ትንሣኤ እሑድ፣ ርክበ ካህናት ረቡዕ፣ ዕርገት ሐሙስ፣ ጰራቅሊጦስ እሑድ እንዲሆን ከመደረጉ በፊት ርክበ ካህናት ግንቦት ፳፩ ቀን ይውል ነበር /መጽሐፈ ግጻዌ ግንቦት ፳፩/፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ርክበ ካህናት በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ኛው ቀን፣ በበዓለ ሃምሳ እኩሌታ በዕለተ ረቡዕ ይዘከራል፡፡ በያዝነው ዓመት በ፳፻፰ ዓ.ም የትንሣኤ በዓል ከተከበረበት ዕለት (ሚያዝያ ፳፫ ቀን) ጀምሮ ብንቈጥር ፳፭ኛው ቀን ግንቦት ፲፯ ቀን ይሆናል፡፡ በመሆኑም የዘንድሮው ርክበ ካህናት ግንቦት ፲፯ ቀን (በነገው ዕለት) ይውላል ማለት ነው፡፡ ይህ በዓል ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሲያስተዳድሩ የቆዩ አባቶቻችን በጋራ በመሰባሰብ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን የተቀላጠፈ አገልግሎት እንደዚሁም ለምእመናን አንድነትና መንፈሳዊ ዕድገት የሚበጁ መንፈሳውያን መመሪያዎችን የሚያስተላልፉበት ዕለት ነው፡፡

በቅዱስ ዮሐንስ ወንጌል እንደተገለጸው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ተገልጦ ከዐሥራ አንዱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ በልቷል፡፡ ከምሳ በኋላም ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ትወደኛለህን? እያለ ከጠየቀው በኋላ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በቅደም ተከተል በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ በማለት የአለቅነት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ቅዱስ ጴጥሮስን ማስጠንቀቁን፤ ፍጻሜው ግን የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንንና መላው ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳ ትርጕም አለው /ዮሐ.፳፩፥፩-፲፯ (አንድምታ ትርጓሜ)/፡፡

ይህንን የጌታችን ትእዛዝና የሐዋርያትን ሥልጣነ ክህነት መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜ ጉባኤ ያደርጋል፤ የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (የቅዱስ ማቴዎስ በዓል) ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ይህ ርክበ ካህናት ነው፡፡ በዚህ ዕለት ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያደርገው ጉባኤ የሚተላለፉ መመሪያዎችና የሚጸድቁ ውሳኔዎች ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት፣ ለምእመናን አንድነት፣ ለአገር ሰላምና ደኅንነት የሚጠቅሙ ይሆኑ ዘንድ ሁላችንም በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንንና አባቶቻችንን ይጠብቅልን፤ እኛንም ለአባቶች የሚታዘዝ ልቡና፣ ሓላፊነታችንን የምንወጣበትን ጥበብና ማስተዋሉን ያድለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡