ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለ ሃይማኖት

ግንቦት ፲፪ ቀን፣ ፳፻፰ ዓ.ም

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ ግንቦት ፲፪ ቀን በዚህች ቀን ቅዱስ ሚካኤል ሊቀ መላእክት፣ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ እስክንድር፣ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቅዱስ መስቀል፣ ቅዱስ ሚናስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስ፣ የመላልዔል ልጅ ያሬድ፣ እንደዚሁም ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ይታሰባሉ፡፡ በዚህ ዝግጅት የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ፍልሰተ ዓፅም የሚያስታውስ ጽሑፍ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤

ስምዑ ወለብዉ ኦ ፍቁራንየ መጽሐፈ ዜናሁ ለክቡር ወቅዱስ ወለብፁዕ ፍቁረ እግዚአብሔር ዘይትነበብ በዕለተ ፍልሰተ ሥጋሁ አመ ፲ወ፪ ለግንቦት ዝ ውእቱ ድሙር ምስለ በዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበዓለ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ፍቁሩ ለተክለ ሃይማኖት፤ ወዳጆቼ ሆይ፣ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ የተደነቀ፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሚሆን የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ክብሩን፣ ገናንቱን የሚናገረውን፣ ዐፅሙ የፈለሰበትን ግንቦት ፲፪ ቀን የሚነበበውን መጽሐፍ አስተውላችሁ ስሙ፤ /ገድለ ተክለ ሃይማኖት ምዕ.፷፪፥፭/፡፡

ተክል ማለት ፍሬያማ ዕንጨት፣ ዛፍ፣ ቅመም፣ ቅጠላ ቅጠል፣ የሚበላ፣ የሚሸተት፣ ገነታዊ ዕፅ፣ እንዲሁም ሕግ ሥርዓት ማለት ነው /ማቴ.15፥13/፡፡ ሃይማኖት ማለት ደግሞ በሀልዎተ እግዚአብሔር፣ እግዚአብሔር የሁሉ አስገኚ መሆኑን፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በቅዱሳን ተራዳኢነት ማመን አምኖም መመስከር ማለት ሲሆን ተክለ ሃይማኖት የሚለው ሐረግም የሃይማኖት ተክል፣ ይኸውም የጽድቅ ፍሬን ያፈራና ከኃጢአት ሐሩር ማምለጫ ዛፍ፣ ምእመናንን በቃለ ወንጌል ያጣፈጠ ቅመም፣ መዓዛ ሕይወቱ የሚማርክ፣ ቢመገቡት ረኃበ ነፍስን የሚያስወግድ ቅጠል፣ የጻድቃን መጠለያ ዕፅ የሚል ትርጕም ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ መጽሐፈ ገድላቸውም ተክለ ሃይማኖት ማለት የአብ፣ የወልድ፣ የመንፈስ ቅዱስ ተክል ማለት ነው ሲል ይተረጕመዋል፡፡ አባታችን እርሳቸውም በአሚነ ሥላሴ ጸንተው ሌሎችንም እንዲጸኑና እንዲያምኑ አድርገዋልና፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖት በ፲፫ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ከአገራችን ከኢትዮጵያ ምድር ከሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ከኢቲሳ መንደር ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብ እና ከእናታቸው እግዚእ ኀረያ አብራክ የተገኙ ቅዱስ አባት ናቸው፡፡ አባታችን ሕይወታቸዉን ሙሉ ለእግዚአብሔር በመስጠት፣ እንደ በሬ ተጠምደው፣ እንደገበሬ ታጥቀው ይህንን ዓለም ንቀው በጾም በጸሎት ተወስነው በብሕትውና ከመኖራቸው በተጨማሪ እንደቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ የሰበኩ፣ በጌታችን በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የፈወሱ ሐዋርያ ናቸው፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን ውለታቸውን በማሰብና ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ቅድስና መሠረት በማድረግ በስማቸው ጽላት ቀርፃ ስታከብራቸው ትኖራለች፡፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከሚታወሱባቸው በዓላት መካከልም በዛሬው ዕለት የሚከብረው ፍልሰተ ዐፅማቸው አንደኛው ሲሆን ታሪኩንም በአጭሩ እነሆ፤

ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ የሚያልፉበት ቀን በተቃረበ ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከቅዱሳን ነቢያትና ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ወደእርሳቸው በመምጣት የሚያርፉበት ዕለት መድረሱን ነግሯቸው የተጋድሏቸውን ጽናት አድንቆ በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የዕረፍታቸው ጊዜ መቃረቡን ባወቁ ጊዜ የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ሁሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ ፳፬ ቀን ከዚህ ዓለም ድካም ዐረፉ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም ለአንድ ቅዱስ አባትና ካህን በሚገባ ሥርዓት በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀበሯቸው፡፡ ጌታችንም ከእመቤታችንና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ተገልጾ ታያቸው፤ ነፍሳቸውንም የጠራሽ፣ ንጽሕት ነፍስ ሆይ ወደእኔ ነዪ ብሎ በክብር ተቀበላት፡፡

በመጽሐፈ ገድላቸው እንደተጠቀሰው ቅዱስ አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዚህ ዓለም የኖሩበት ዕድሜ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ከዐሥር ወር ከዐሥር ቀን ነው፡፡ ገድላቸው ዕድሜያቸውን በመከፋፈል፡- በእናት አባታቸው ቤት ፳፪ ዓመት፤ በከተታ ፫ ዓመት፤ በዊፋት ፱ ወር፤ በዳሞት ፲፪ ዓመት፤ በአማራ ፲ ዓመት፤ በሐይቅ ፲ ዓመት፤ በደብረ ዳሞ ፲፪ ዓመት፤ በትግራይ ገዳማት በመዘዋወርና ወደ ኢየሩሳሌም በመመላለስ ፩ ዓመት፤ ዳዳ በሚባል አገር ፩ ወር፤ በአሰቦ ገዳም ፳፱ ዓመት ከ፲ ቀን መቆየታቸውን ይናገራል /ገ.ተ.ሃ.፶፱፥፲፬-፲፭/፡፡

ወደ ፍልሰተ ዐፅማቸው ታሪክ ስንመለስ መጽሐፈ ገድላቸው እንዲህ ሲል ይጀምራል፤ ስምዑ ወለብዉ ኦ ፍቁራንየ መጽሐፈ ዜናሁ ለክቡር ወቅዱስ ወለብፁዕ ፍቁረ እግዚአብሔር ዘይትነበብ በዕለተ ፍልሰተ ሥጋሁ አመ ፲ወ፪ ለግንቦት ዝ ውእቱ ድሙር ምስለ በዓለ ትንሣኤሁ ለእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ወበዓለ ሚካኤል ሊቀ መላእክት ፍቁሩ ለተክለ ሃይማኖት፤ ወዳጆቼ ሆይ፣ የከበረ፣ የተቀደሰ፣ የተደነቀ፣ የእግዚአብሔር ወዳጅ የሚሆን የአባታችን የተክለ ሃይማኖት ክብሩን፣ ገናንቱን የሚናገረውን፣ ዐፅሙ የፈለሰበትን ግንቦት ፲፪ ቀን የሚነበበውን መጽሐፍ አስተውላችሁ ስሙ፤ ይኸውም ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል ጋር የተክለ ሃይማኖት ወዳጅ ከመላእክት አለቃ ከቅዱስ ሚካኤል በዓል ጋር የተባበረ ነው፡፡ ወንድሞቻችን እንነግራችኋለን፤ እናስረዳችኋለን፡፡ እንደ ዮሐንስና እንደ ነቢዩ ኤርምያስ ከእናቱ ማኅፀን እግዚአብሔር የመረጠው የክቡር አባታችን ዐፅሙ የፈለሰበት ቀን ዛሬ ነው፤ /ገ.ተ.ሃ.፷፪፥፭-፰/፡፡

አባታችን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከዚህ ዓለም ከተለዩ በ፶፯ኛው ዓመት የካቲት ፲፱ ቀን ለመንፈስ ልጃቸው ለአባ ሕዝቅያስ ብርሃን ለብሰው በሕልም ተገለጡላቸውና ወዳጄ ሕዝቅያስ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን! ጌታዬ በኋለኛው ዘመን ከዚህ ሥፍራ ልጆችህ ሥጋህን ያፈልሳሉ ያለኝ ዘመን ደርሷልና ሳትዘገይ ልጆቼን ሁሉ ቅጠራቸውና እስከምፈልስበት ቀን ድረስ ግንቦት ፲፪ ቀን ይሰብሰቡ፡፡ እናንተም በምስጋና በጸሎት መንፈሳዊ በዓልን አድርጉ፡፡ አባቴ ተክለ ሃይማኖት የሚለኝ ሁሉ በዚህች በፍልሰተ ዐፅሜ ቀን ይምጣ፤ መንፈሳዊ በዓልንም ያድርግ፡፡ እኔና ቅዱስ ሚካኤል ከወዳጄ አባ ፊልጶስ ጋር ስለኔ ፍቅር የተሰበሰበውን ሕዝብ ልንባርክ እንመጣለን፤ ከአሏቸው በኋላ ተሠወሯቸው፡፡

አባ ሕዝቅያስም እንደታዘዙት የአባታችሁን ዐፅም ከዋሻው ወደ ታላቁ ቤተ ክርስቲያን ታፈልሱ ዘንድ ኑ፤ ተሰብሰቡ ብለው የአባታችን ወዳጆች በያሉበት ሀገር ሁሉ መልእክት ላኩ፡፡ ምእመናንም ጥሪውን ተቀብለው በዓሉን ለማክበር ከአራቱም አቅጣጫ ተሰበሰቡ፡፡ ዐሥራ ሁለቱ መምህራንም መጡ፤ እነዚህም፡- የወረብ አገሩ አባ አኖሬዎስ፣ የፈጠጋሩ አባ ማትያስ፣ የእርናቱ አባ ዮሴፍ፣ የሞረቱ አባ አኖሬዎስ፣ የመርሐ ቤቴው አባ መርቆሬዎስ፣ የጽላልሹ አባ ታዴዎስ፣ የወገጉ አባ ሳሙኤል፣ የወንጁ አባ ገብረ ክርስቶስ፣ የድንቢው አባ መድኃኒነ እግዚእ፣ የዳሞቱ አባ አድኃኒ፣ የክልአቱ አባ ኢዮስያስ እና የመሐግሉ አባ ቀውስጦስ ናቸው፡፡

እነዚህ መምህራን ከአባ ሕዝቅያስ ጋር በመሆን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ዐፅም ከዐረፈበት ዋሻ ባወጡት ጊዜ ዐፅማቸው ዕለት የተገነዘ በድን ይመስል ነበር፤ መዓዛውም ሽቱ፣ ሽቱ ይሸት ነበር፡፡ በአባታችን ዐፅም ቀኝና ግራም መስቀል ተተክሎ ነበር፡፡ በዐፅማቸውም ብዙ ድንቅ ተአምራት ተደርገዋል፡፡ ይህንን የአባታችንን ዐፅም አባ ሕዝቅያስና ዐሥራ ሁለቱ መምህራን በሣጥን አክብረው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወስደው በመንበሩ ፊት ሦስት ጊዜ አዞሩት፡፡

በዚህች ዕለት አስቀድመው የካቲት ፲፱ ቀን ለአባ ሕዝቅያስ በሕልም እንደነገሯቸው ብፁዕ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ከቅዱስ ሚካኤልና ከአባ ፊልጶስ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መጥተው ዐፅማቸው እስኪያረፍ ድረስ ከመንበሩ ተቀምጠው ቆይተው ዐፅማቸው ካረፈ በኋላ የተሰበሰበውን ሕዝብ ባርከው በክብር ወደ ሰማይ ዐረጉ፡፡ መምህራኑና ምእመናኑም በዓሉን በታለቅ ደስታ አክብረው በሰላም ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፍልሰተ ዐፅም ከዋለበት ዕለት ጋር ርክበ ካህናት አብሮ መዋሉ በዓሉን ልዩ ድምቀት ሰጥቶት ነበር /ገ.ተ.ሃ.፷፭፥፩-፳፬/፡፡

ከዚያ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በታላቁ ገዳም በደብረ ሊባኖስ ቅዱሳን ፓትርያሪኮች፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና በርካታ ምእመናን እየተሰበሰቡ በዓሉን በድምቀት ያከብራሉ፡፡ የብፁዕ አባታችን ዐፅማቸው በፈለሰበት ዕለት ዐሥራ ሁለቱ መምህራን እና በርካታ ምእመናንን እንደተሰበሰቡ ሁሉ እኛንም እግዚአብሔር አምላካችን በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስበን፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትና የመንፈስ ልጆቻቸው ጸሎት፣ ረድኤትና በረከት ለዘለዓለሙ ይጠብቀን፡፡

ምንጭ፡-

ገድለ ተክለ ሃይማኖት፣ ፲፱፻፹፱ ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር፣ ግንቦት ፲፪ ቀን፡፡