የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም.
ሊቀ ጉባኤ ቀለመ ወርቅ ውብነህ
ጾም ማለት መተው መከልከል ማለት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ሠርታ ጾመን ከአምላካችን ጋር ህብረት እንዲኖረን ፤መንፈሳዊ ኃይል እንድናገኝ አድርጋለች፡፡ ጾም በእግዚአብሐር የተቀደሰ ስለሆነ ወደ ቅድስና ጎዳና የሚመራ ነው፡፡
በጾም ወራት ከመባልዕት መከልከል ብቻ ሳይሆን ዐይን ክፉ ከማየት አንደበት ክፉ ከመናገር ጆሮ ክፉ ከመስማት መቆጠብ እንደሚገባ ተጽፎአል፡፡ “ይጹም ዐይን፣ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም እምሰሚዓ ኀሡም በተፋቆሮ” /ቅዱስ ያሬድ ጾመ ድጓ/፡፡ በጾም ወራት፣ ላምሮት፣ ለቅንጦት፣ የሚበሉ ወይም ለመንፈሳዊ ኃይል ተቃራኒ የሆኑ ሥጋዊ ፍትወትን የሚያበረታቱ፣ ሥጋንና የሚያሰክሩ መጠጦችን /ዳን.10፥2-3/ ቅቤና ወተትን ማራቅ ታዟል፡፡ /መዝ.108፥24፣ 1ቆሮ.7፥5፣ 2ቆሮ.6፥6/
በብሉይ ኪዳን ጾም ከፍተኛ ቦታ አለው፡፡ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ከእግዚአብሔር በሚገናኙበት ወራት እህልና ውኃ በአፋቸው አይገባም ነበር፡፡ /ዘፀ.34፥28/አስቴር አስቀድማ ሦስት ቀን ጾማ ጸልያ በእስራኤል ላይ የመጣውን መቅሰፍት እንዲመለስ አድርጋለች፡፡አስ4፡15-16 በኃጢአት ብዛት የታዘዘው የእግዚአብሔር መዓት የሚመለሰው ሕዝቡ በጾም ሲለምኑትና ሲማልዱት ነበር፡፡ /ዮና.2፥7-10/
በሐዲስ ኪዳንም ጾም ሰው ሠራሽ ሕግ ሳይሆን እራሱ ክርስቶስ የሥራ መጀመሪያ አድርጎ የሠራው ሕግ ነው፡፡ /ማቴ.4፥2፣ ሉቃ.4፥2/ ይህም ብቻ ሳይሆን በቁራኝነት ተቆራኝቶ አብሮ የሚኖር መንፈሰ ርኩስ ሰይጣን እንኳን በጾም የሚወገድ መሆኑን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተናግሮአል፡፡ ማቴ.17፥21፣ ማር.9፥2
ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የታዘዙ ሐዋርያትም በየጊዜው ከመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ የሚቀበሉት በጾም በጸሎት ላይ እንዳሉ ነበር፡፡ /የሐዋ.ሥራ.13፥2/ ለስብከተ ወንጌል የሚያገለግሉ ዲያቆናትና ቀሳውስትም የሚሾሙት በጾምና በጸሎት ነበር፡፡ /የሐ. ሥራ.13፥3፣ 14፥23/ እነቆርኔሌዎስ ያላሰቡትን ያዩና ያገኙ የነበረው በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን ማልደው ነው፡፡ /የሐ. ሥራ.10፥30/
ዐቢይ ጾምም ቤተክርስቲያናችን እንድንጾም ካወጀችልን ጾም አንዱ ነው፡፡ዐቢይ ጾምየተለያዩ ስሞች አሉት፡፡ አንደኛ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም በመሆኑ እንዲሁም ዐቢይ እግዚአብሔር ወዓቢይ ኀይሉ ዓቢይ እግዚአብሔር ወብዙኃ አኰቴቱ የተባለ ጌታ የጾመው ስለሆነ፣ /መዝ.47፥1፣ መዝ.146፥5/፡፡ ሁለተኛ ሁዳዴ ጾም ይባላል፡፡ ይህም የመንግሥት እርሻ ወይም ማንኛውም የሕዝብ ብዛት ያለበት ሥራ ሁዳድ ስለሚባል ሲሆን ከአጽዋማት ሁሉ ብዙ ቀናት ስለሚጾምና ኃያሉ አምላካችን ስለጾመው ነው፡፡፣ /አሞ.7፥1/፡፡ ሦስተኛ በዓተ ጾም ይባላል፡፡የጾም መግቢያ፣ መባቻ ወይም ጾሙ የሚሰፍርበት በዓት ማለት ነው፡፡ አራተኛ ጾመ አርባ ይባላል፡፡ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው 40 /ዓርባ/ ቀን ስለሆነ፣ /ማቴ.4፥1/ አምስተኛ ጾመ ኢየሱስይባላል፡፡ ጾሞ፣ ጹሙ ብሎ ስላዘዘን፣ ስድስተኛ ጾመ ሙሴ ይባላል፡፡ ቅዱስ ያሬድ በዘወረደ ሰኞ ዕዝል ከመዝ ይቤ ሙሴ እስመ ለዓለም፣ ሙሴኒ ይቤ በውስተ ኦሪት እያለ በጾመ ድጓ ስለ ዘመረ ነው፡፡
ዐቢይ ጾምጌታ ከተጠመቀ በኋላ የጾመው የአርባ ቀን ጾም ነው፡፡ ማቴ.4፥1 ምእመናን ጌታቸው ያደረገውን ምሳሌ ተከትለው ይጾሙታል፡፡ ዐቢይ ጾም ስምንት ሳምንታት /55 ቀኖች/ አሉት፡፡ ሰባት ቅዳሜ ስምንት እሑድ ይገኛሉ፡፡ አሥራ አምስት ቀን ማለት ነው፡፡ ከጥሉላት እንጂ ከእህል ውኃ ስለማይጦሙ የጦሙ ወራት አርባ ቀን ብቻ ይሆናል፡፡
ዘወረደ /ዘመነ አዳም/
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያ ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡ ዘወረደ ማለት፣ ከላይ የመጣ፣ የወረደ ማለት ነው፡፡ ይህም የአምላካችን ሰው መሆን ያመለክታል፡፡ ከሰማይ ከወረደው በቀር ወደሰማይ የወጣ የለም ካለው ከጌታችን ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በመነሳት ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በዚህ ዕለት ምስባክ “ዘወረደ እምላዕሉ አይሁድ ሰቀሉ ወሚመ ኢያእመሩ እግዚአ ኩሉ ዘየሐዩ በቃሉ” በማለት በጾመ ድጓው መጀመሪያ ላይ ገልጾት ይገኛል፡፡
አዳምን ለማዳን ከሰማይ የወረደውን አይሁድ ሰቀሉት፣ የሰማይን ሥልጣን ያለው የሁሉ ጌታ እንደሆነም ምንም አላወቁም ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ ይህም ድርሰት በቤተ ክርስቲያናችን የጾም መጀመሪያ የሆነው ዕለተ ሰንበት ዋዜማ፣ መግቢያ፣ /መሐትው/ ሆኖ ከዋዜማ በፊት ምንጊዜም በየዓመቱ ይቆማል፡፡ ይዘመራል፡፡ ይመሰገናል ማለት ነው፡፡
ስለዚህ የሳምንቱ ስያሜ ከዚህ የተወሰደ ነው፡፡ እንዲሁም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ሥራውን የጀመረው፤ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ሰው በመሆን ፣ በዮርዳኖስ ተጠምቆ በማስተማር እንደሆነ ሁሉ የመጀሪያው ሳምንት ዘወረደ ይባላል፡፡
በዚህ ሳምንት በተለይም እሑድና ሰኞ የሚነገሩት ውዳሴያት ከመጻሕፍተ ኦሪትና ነቢያት የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሁለተኛም ሙሴኒ በመባል ይታወቃል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ለማዳን ከሰማይ መውረዱንና በመስቀል መሰቀሉን ስለሚያወሳ ነው፡፡
በተጨማሪም ይህ የመጀመሪያው ሳምንት ጾመ ሕርቃል ይባላል፡፡ በ714 ዓ.ም.ሕርቃል /ኤራቅሊየስ/ የቤዛንታይን ንጉሥ ነበረ፡፡ይህ ሳምንት በስሙ የተጠራበት ምክንያት በዘመኑ ፋርሶች ኢየሩሳሌምን ወርረው የጌታችን መስቀል ማርከው ወስደው ነበር፡፡ እርሱ ወደፋርስ ዘመቶ መስቀሉን ከእነርሱ ነጥቆ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሷል፡፡
ሕርቃል ከፋርሶች ጋር ከመዋጋቱ በፊት ሐዋርያት በሲኖዶሳቸው ነፍስ የገደለ ሰው እስከ እድሜ ልኩ ይጹም ብለው ሥርዓት ሠርተዋልና ጾሙን ፈርቶ ስለነበር በኢየሩሳሌም የነበሩ ምእመናን አሳቡን ደግፈው “አንተ ጠላታችንን አጥፋልን ፣መስቀሉን አስመልስልን እንጂ የአንድ ሰው እድሜ ቢበዛ ሰባ ሰማንያ ነው ፡፡ጾሙንአምስት አምስት ቀን ተከፋፍለን እኛ ተከፋፍለን እንጾምልሃለን፡፡”ብለው ጾመውለታል፡፡
ይህንን መሠረት በማድረግ ያላወቁት አንድ ጊዜ ጾመው ትተውታል፡፡ ያወቁት ግን ቀድሞም ሐዋርያት ጾመውታል ብለው ሥርዓት አድርገው በዓመት በዐቢይ ጾም መጀመሪያ ላይ ጾመ ሕርቃል እያሉ የሚጾሙት ሆነዋል፡፡ስለዚህ ቤተክርስቲያናችን ይህንን መሠረት በማድረግ በጌታችን ከመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም የመጀመሪያውን ሳምንት ጾመ ሕርቃል በሚል ስያሜ ሰማይ እንዲጾም አድርጋለች፡፡ /መጋቢት 10 ስንክሳር ይመልከቱ፡፡/
የቤተ ክርስቲያናችን ታሉቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፣ በዘወረደ ጾመ ድጓው ሰንበት ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን፣ ሕይወት ላለው ነገር ሁሉ ጸጥታና ሰላም የሰፈነባት የዕረፍት ቀን ስለመሆኗ “አዘዞ እግዚአብሔር ለሙሴ ወይቤሎ ሰብዕከ ወላህምከ ወኲሉ ቤትከ ያዕርፍ በሰንበት” ዘፀ.20፥10፣23፣12፣ ጾመ ድጓ፣ እግዚአብሔር ሙሴን ሕዝብህ የከብትህ መንጋህ ቤተሰብህ ሀሉ በሰንበት ቀን ከድካማቸው ይረፉ በማለት አዘዘው ይላል፡፡ በዚህም ዘመነ ጾም፣ ወይም ጾመ ሙሴ ይባላል፡፡
በጾመ ድጓው ዘወረደ እየተባለ የሚታወቀው፣ በጾመ አርባው ወቅት በተለይም በመጀመሪያው ሳምንት የሚገኘው ያሬዳዊ ድርሰት በነግህ በሠለስት፣ በቀትርና በሠርክ እንዲሁም ቅዳሜና እዡድ በሌሊት የሚዘመር ነው፡፡ በውስጡም የያዘው ፍሬ አሳብ፣ የጾምን፣ የጸሎትን፣ የምጽዋትንና የፍቅርን ጠቃሚነት አጉልቶ የሚያስተምር ነው፡፡
በዚህ በጾም ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት በአብዛኛው ከቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች ውስጥ የሚዘመረው ምዕራፍ የተባለው ነው፡፡ ምዕራፍ የተባለበት ምክንያትም በየመዝሙራቱ መሀል ሃሌታና ድጓ እያስገባ ለመዝሙሩ ማረፊያ ስላበጀለት በዚህ ምክንያት ምዕራፍ የሚል ስያሜ ሊያገኝ ችሏል፡፡ ይህ የዜማ መጽሐፍ በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላል፡፡ ይኸውም የዘወትር ምዕራፍና የጾም ምዕራፍ በመባል ይታወቃል፡፡የዘውትር ምዕራፍ የሚባለው በዓመቱ ውስጥ ባሉት ቀናት ውስጥ ሳምንታትና በዓላት ሁልጊዜ በአገልግሎት ላይ የሚውል ሲሆን፣ የጾም ምዕራፍ የሚባለው ደግሞ በጾመ አርባ ብቻ ለአገልግሎት የሚውል ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በዐሥሩ ምህላት አርዕስተ ምህላ በዚሁ ክፍል ይካተታል፡፡ የምዕራፍ ቅንብር ከመዝሙረ ዳዊት፣ ከድጓና ከጾመ ድጓ ጋር የተቀናጀ ነው፡፡ የትምህርት አሰጣጡም እንደ ድጓው ወይም እንደ ዝማሬ መዋሥዕቱ መጽሐፍ ተዘርግቶ ሳይሆን በቃል የሚጠናና የሚወሰን ነው፡፡ ስለሆነም ምዕራፍን ለመማር 150 መዝሙረ ዳዊትን፣ ከነቢያት 15 ምዕራፎችንና 5 መኃልያተ ሰሎሞንን በቃል ሸምድዶ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ወይም ግድ ነው፡፡
ጾምን መጾም የፈቃድ ብቻ ሳይሆን የትእዛዝም ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ ነቢዩ ኢዩኤል “ቀድሱ ጾመ ወስብኩ ምህላ” ጾምን ያዙ አጽኑ ምሕላንም ዐውጁ ሸማግሌዎቹን ከፈጣሪያችን ቤት ሰብስባችሁ በአንድነት ሁናችሁ ወደ እግዚአብሔር ጩሁ /ለምኑ/ ብሏል፡፡ ኢዮ.ምዕ.1፥11፣ 2፣12፣15-16 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ወኲኑ ላዕካነ፣ ለእግዚአብሔር በጾም ወበንጽሕ፡፡ በጾም፣ በንጽሐና ተወስናችሁ እግዚአብሔርን አገልግሉ ብሏል 2ቆሮ.6፥4-6፡፡
ጾም ከሌለ ወይም ተገቢ ካልሆነ ጌታችን በምትጾሙበት ጊዜ እንደ ግብዞች አትሁኑ ስለ ጽድቅ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን ክብራን ናቸው ለምን አለ? ማቴ.5፥፣6፣16፡፡ ነቢዩ ዳዊትም ሰውነቴን በጾም አሳመምኳት በቀጠና፣ በሰልት አደከምኳት ለምን አለ መዝ.34፥68፣ ት.ዳን. 9፥3-4፣ 14፥5
ነብዩ ሚኪያስ ሐዋርያት ሙሸራውን ከነሱ ለይተው የሚወስዱበት ጊዜ ይመጣል ያን ጊዜ ይጾማሉ ያለውን የጌታን ቃል መሠረት በማድረግ ክርስቶስ በሞት ከተለያቸው በኋላ ጾመዋል፡፡ ጾምንም ሠርተዋል የሐዋ.ሥራ 13፥3፡፡ ሠለስቱ ምዕትም ሐዋርያት የጾሙትንና እንዲጾም የወሰኑትን መጾም ይገባል ብለው ቤተ ክርስቲያን የተቀበለቻቸውን አጽዋማት እንዲጾሙ መወሰናቸው ይህን የጌታ ቃል መሠረት በማድረግ ስለሆነ፣ የትእዛዝ መሆኑን ተገንዝበን መጾም አለብን፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሠራዔ ሕግ እንደመሆኑ አርባ ቀን አርቦ ሌሊት ጾመ እንጂ እርሱ ሳይጾም ጾሙ አላለንም ማቴ.4፥2፡፡ ጾመን ለማበርከት ያብቃን፡፡
ይቆየን