ሚያዚያ 30 ቀን 2006 ዓ.ም.
በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
በጥንተ ጠላት ዲያቢሎስ አሳሳችነት አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላላፋቸው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ ተፈርዶባቸው ነበር፡፡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ አዳምና ሔዋን ከክህደት የደረሱት በዲያቢሎስ አሳሳችነት በመሆኑና ለሰው ልጆች ካለው ፍጹም ፍቅር የተነሳ የተፈረደባቸውን ሞት በሞቱ ሊደመስስ ሰው ሆነ፡፡ ዮሐ1፡1 ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ 30 ዓመት ሲሞላው ተጠመቀ፡፡ እንደተጠመቀም ልዋል ልደር ሳይል ገዳመ ቆሮንቶስ ሄደ፡፡ በዚያም ጾመ ጸለየ በዲያቢሎስም ተፈተነ፡፡ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ካስተማረ በኋላ አስቀድሞ ለአዳምና ለሔዋን ሞታቸውን ሊደመስስ፡፡ ዕዳቸውን ደመስሶ ነጻ ሊያደርጋቸው በገባው ቃል ኪዳን መሠረት መከራ ተቀበለ፤ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ቆመ፣ ምራቅ ተተፋበት፣ ተገረፈ፣ በገመድ ታስሮ ተጎተተ፣ በመስቀል ተሰቅሎ ሞተ የአዳምና የሔዋንን ዕዳ በደል ደመሰሰ፡፡ ሞት ድል ተነሳ፡፡ ማቴ. 27-28
ይህንን የቤዛነት፣ የነጻነትና የድል በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮች በየዓመቱ ጌታ የጾመውን ጾም ከጾሙ በኋዋላ መከራውን ስቃዩን ከሆሳዕና በዓል ጀምሮ በማሰብ፤ በጥንተ ጠላታችን አማካኝነት አይሁድ ክብርህን ዝቅ ቢያደርጉ፣ ቢያዋርደህ፣ ቢገርፉህ፣ እርቃንህን ቢያደርጉህ፣ ቢሰቅሉህና ቢገድለህ እኛ ግን “ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም፡፡ አማኑኤል አምላኪዬ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም፡፡
ኦ እግዚእየ ኢየሱስ ክርስቶስ ለከ ኃይል ክብር ወስብሐት ወእዘዝ ለዓለም ዓለም፡፡ ኃይሌ መከታዬና ረዳቴ ለሆንከው ለአንተ ለአምላኬ አማኑኤል ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና ጽናትም ለዘለዓለሙ የአንተ ናቸው፡፡” የሚለውንና በሌሎች የሰሙነ ህማማት ሥርዓቶች አማካኝነት እስከ ዕለተ ዓርብ ድረስ ቅዱስ ጳውሎስ በፊል. 3፡10 ላይ እንደጠቀሰው “እርሱንና የትነሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራወም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ በሞቱ እንደመስለው እመኛለሁ፡፡” እንዳለው እንደ አቅማቸው እያዘኑ፣ እያለቀሱ፣ ከምግብ እየተከለከሉ፣ ጸጉራቸውን ተላጭተው የአምላካቸውን መከራ ያስባሉ፡፡ “ሞትን ድል አድርጎ ተነስቷል!” የሚለውን የምሥራች ከቤተ ክርስቲያናቸው ለመስማት በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡ ትንሣኤውም ይበሰርላቸዋል፡፡ “ጌታ በእውነት ተነሥቷል፡፡” እያሉ ይመሰክራሉ፡፡
ትንሣኤው የድህነት ብሥራት በመሆኑ ለሃምሳ ቀናት ያህል ብሥራቱ በቤተ ክርስቲያን በቅዳሴው፣ በማኅሌቱ፣ በወንጌሉ ወዘተ. ይዘከራል በማንኛውም ቦታም ክርስቶስ ተንሥአ እሙታን … እየተባለ ሞት መደምሰሱን ነጻነት መታወጁን በሰላምታ ይበሠራል፡፡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ነጻነት በተለያየ ይገልጹታል፡፡ በየጊዜያቱና በየዘመናቱ የተነሡ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ ከዚህ ቀጥሎ የተገለጠውን ትምህርትና ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶ ሲኦልን ረግጦ፣ በሞቱ ሞትን አጠፋው፤ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ አባት ሆይ፤ አመሰግንሃለሁ ብሎ ሥግው ቃል አመሰገነ፡፡ /እልመስጦአግያ ዘሐዋርያት 5፥1/እንደ ሞተ እንዲሁ ተነሣ፣ ሙታንንም አስነሣ፤ እንደተነሣም እንዲሁ ሕያው ነው፤ አዳኝ ነው፡፡ በዚህ ዓለም እንደዘበቱበት፣ እንደሰደቡት፤ እንዲሁ በሰማይ ያሉ ሁሉ ያከብሩታል፤ ያመሰግኑታል፡፡ ለሥጋ በሚስማማ ሕማም ተሰቀለ፤ በእግዚአብሔርነቱ ኃይል ተነሣ፣ ይኸውም መለኮቱ ነው፡፡ ወደ ሲኦል ወርዶ ነፍሳትን ማረከ፡፡ /ቅዱስ ሄሬኔዎስ ሃይ. አበ. 7፥28-31/ እንዲህ ሰው ሆኖም ሰውን ፈጽሞያድን ዘንድ ታመመ፣ ሞተ፣ ተቀበረ፤በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ /ዘሠለስቱ ምዕት 19፥24/
ሞትን ያጠፋው፤ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ የሞት ሥልጣን የነበረው ዲያብሎስን የሻረው እርሱ ነው፤ሰው የሆነ፤ በሰው ባሕርይ የተገለጠአምላክ ነው፤ እግዚአብሔር ያደረበት ዕሩቅ ብእሲ አይደለም፤ ሰው የሆነ አምላክ ነው እንጂ፤ ፈጽሞ ለዘለዓለሙ በእውነት ምስጋና ይገባዋል፡፡ /ቅዱስ አትናቴዎስ ሃይ. አበ. 25፥40/
ሥጋው በመቃብር ያሉ ሙታንን አስነሣ፤ ነፍሱም በሲኦል ተግዘው የነበሩ ነፍሳትን ፈታች፡፡ በዚያም ሰዓት የጌታችን ሥጋው በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ መቃብራት ተከፈቱ፤ ገሃነምን የሚጠብቁ አጋንንትም ባዩት ጊዜ ሸሹ፡፡ የመዳብ ደጆች ተሰበሩ /ሊቃነ አጋንንት፣ ሠራዊተ አጋንንት ድል ተነሡ/የብረት ቁልፎቿም ተቀጠቀጡ /ፍዳመርገም ጠፋ/፤ ቅድስት ነፍሱ በሲኦል ተግዘው የነበሩ የጻድቃን ነፍሳትን ፈታች፡፡ /ዝኒ ከማሁ 26፥20-21/
ሥጋ ከመለኮቱ ሳይለይ በመቃብር አደረ፤ ነፍሱም ከመለኮት ሳትለይ በገሃነም ተግዘው ለነበሩ ነፍሳት ደኅነትን ታበስር ዘንድ፤ ነጻም ታደርጋቸው ዘንድወደ ሲኦል ወረደች፤ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንደተናገረው ቃል ዐፅም ሥጋ ወደ መሆን ፈጽሞ እንደተለወጠ የሚናገሩ የመናፍቃንን የአእምሮአቸውን ጉድለት ፈጽመን በዚህ ዐወቅን፤ ይህስ እውነት ከሆነ ሥጋ በመቃብር ባልተቀበረም ነበር፤ በሲኦል ላሉ ነፍሳት ነጻነትን ያበስር ዘንድ ወደ ሲኦል በወረደ ነበር እንጂ፡፡ ነገር ግን ከነፍስና ከሥጋ ጋር የተዋሐደ ቃል ነው፤ እርሱ የሥጋ ሕይወት በምትሆን በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ ለነፍሳት ነጻነትን ሰበከ፡፡ ሥጋ ግን በበፍታ እየገነዙት በጎልጎታ በዮሴፍ በኒቆዲሞስ ዘንድ ነበረ፤ ቅዱስ ወንጌል እንደተናገረ፡፡ አባቶቻችን ሥጋ በባሕርዩ ቃል አይደለም፤ ቃል የነሣውሥጋ ነው እንጂ ብለው አስተማሩን፤ ይህንን ሥጋም ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ቶማስ ዳሠሠው፤ በሥጋው ሲቸነከር ቃል ታግሦ የተቀበለውን የችንካሩን እትራትም በእርሱ አየ፡፡ /ዝኒ ከማሁ 30፥31-36/
አሁን እግዚአብሔር ሞተ ሲል ብትሰማ አትፍራ፤ የማይሞተውን ሞተሊሉ አይገባም ከሚሉ ዕውቀት ከሌላቸው፤ ሕማሙን፣ ሞቱን ከሚክዱ መናፍቃን የተነሣ አትደንግጥ፡፡ እኛ ግን በመለኮቱ ሞት እንደሌለበት፤ በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ሥልጣን እንደ ተነሣ እናውቃለን፤ ሞት የሌለበት ባይሆንስ ኖሮ በሥጋ በሞተ ጊዜ ሥጋውን ባላስነሣም ነበር፤ ሥጋው እስከ ዓለም ፍጻሜ በመቃብር በኖረ ነበር እንጂ፡፡ /ቅዱስ ባስልዮስ ሃይ. አበ. 34፥17-18/
ከመስቀሉ ወደ ሲኦል በመውረዱ አዳነን፤ በአባታቸው በአዳም በደል በሲኦል ተግዘው የነበሩ ጻድቃንን ፈታ፤ ከሙታን ተለይቶ አስቀድሞ በተነሣ በእውነተኛ ትንሣኤውም አስነሣን፤ የንስሐንም በር ከፈተልን፡፡ /ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ 36፥30/
በአባታችን በአዳም በደል የተዘጋ የገነት ደጅን የከፈተልን፤ ዕፀ ሕይወትን የሚጠብቅ ኪሩብንም ያስወገደው፤ የእሳት ጦርን ከእጁ ያራቀ፤ ወደ ዕፀ ሕይወት ያደረሰን እርሱ ነው፤ ፍሬውንም /ሥጋውን፤ ደሙን/ ተቀበልን፡፡ አባታችን አዳም ሊደርስበት ወደ አልተቻለው፤ በራሱ ስሕተት ተከልክሎበት ወደነበረው መዓርግ ደረስን፤ ክፉውንና በጎውን ከሚያስታውቅ፤ ወደ ጥፋት ከሚወስድ፤ በአዳምና በልጆቹም ላይ ኃጢአት ከመጣበት ከዕፀ በለስ ፊታችንን መለስን፡፡ /ዝኒ ከማሁ 36፥38-39/
የሕይወታችን መገኛ የሚሆን የክርስቶስ ሞት የእኛን ሞት ወደ ትንሣኤ እንደለወጠ እናምናለን፤ ክርስቶስም ሞትን አጥፍቶ የማታልፍ ትንሣኤን ገለጠ፤ እንደተጻፈ፡፡ ከሰው ወገን ማንም ማን ሞትን ያጠፋ ዘንድ፣ ትንሣኤንም ይገልጣት ዘንድ አይችልም፤ ዳዊት በሕያውነት የሚኖር፤ ሞትንም የማያያት ሰው ማነው? ነፍሱን ከሲኦል፤ ሥጋውን ከመቃብር የሚያድን ማን ነው? ብሎ እንደተናገረ፡፡ /ቅዱስ አቡሊዲስ ሃይ. አበ. 42፥6-7/
በመለኮትህ ሕማም ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ በሥጋ መከራ የተቀበልክ አንተ ነህ፤ ከአብ ጋር አንድ እንደ መሆንህ ሞት የሌለብህ አንተ ነህ፤ ከእኛም ጋር አንድ እንደመሆንህ በፈቃድህ የሞትክ አንተ ነህ፡፡ በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በኪሩቤል ላይ ያለህ አንተ ነህ፤ ከሙታን ጋር በመቃብር የነበርህ አንተ ነህ፤ በአንተ ሕማምና ሞትም ድኅነት ተሰጠ፤ ከሙታን ጋር የተቆጠርህ አንተ ነህ፤ ለሙታንም ትንሣኤን የምትሰጥ አንተ ነህ፡፡ ሦስት መዓልት፤ ሦስት ሌሊት በመቃብር ያደርህ አንተ ነህ፤ በዘመኑ ሁሉ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የምትኖር አንተ ነህ፤ በመለኮት ሕማም ሳይኖርብህ በሥጋ የታመምክ አካላዊ እግዚአብሔር ቃል አንተ ነህ፡፡ /ቅዱስ ኤራቅሊስ 48፥12-13/
እኛስ ኃጢአታችንን ለማስተሥረይ በሥጋ እንደታመመ፤ እንደሞተ፤ ከነፍሱም በተለየ ጊዜ ሥጋውን እንደገነዙ፤ ከሙታንም ተለይቶ በእውነት እንደተነሣ፤ ከተነሣም በኋላ በእውነት ወደ ሰማይም እንደ ዐረገ እናምናለን፡፡ ኋላም እርሱ በሚመጣው ዓለም በሕያዋን በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል፤ የሰውን ወገኖች ሁሉ በሞቱበት፤ በተቀበሩበት ሥጋ ከሞት ያስነሣቸዋል፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያለመለወጥ ሁል ጊዜ ይኖራል፤ እርሱ በዚህ በሞተበት፤ በተገነዘበት ሥጋ ከሙታን አስቀድሞ እንደተነሣ፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ ዘኢየሩሳሌም ሃይ. አበ. 52፥11-12/
የሥጋን ሕማም ለመለኮት ገንዘብ በአደረገ ጊዜ የእግዚአብሔር አካል በባሕርዩ በግድ ሕማምን አልተቀበለም፤ ሕማም በሚስማማው ባሕርዩኃይልን እንጂ፤ ሞትም በሥጋ ለእግዚአብሔር ቃል ገንዘብ በሆነ ጊዜ ሞትንአጠፋ፤ ከሞትም በኋላ ፈርሶ በስብሶ መቅረትን አጠፋ፡፡ /ቅዱስ ቴዎዶጦስ ሃይ. አበ. 53፥27/
መለኮት በሥጋ አካል በመቃብር ሳለ መለኮት የሥጋ ሕይወት በምትሆን በነፍስ አካል ወደ ሲኦል ወረደ፤ እንደዚህ ባለ ተዋሕዶ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ከትንሣኤ በኋላ አይያዝም፤ አይዳሰስም፤ በዝግ ቤት ገብቷልና፤ ነገር ግን ምትሐት እንዳይሉት ቶማስ ዳሠሠው፤ የተባለውን ከፈጸመ በኋላ ቶማስ አመነበት፡፡ /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ ሃይ. አበ. 56፥37-38/
ክርስቶስ የሙታን በኲር እንደምንተባለ? እነሆ በናይን ያለች የደሀይቱን ልጅ አስቀድሞ አስነሣው፤ ዳግመኛም አልዐዛርን በሞተ በዐራተኛው ቀን አስነሣው፡፡ ኤልያስም አንድ ምውት አስነሣ፤ ደቀ መዝሙሩ ኤልሣዕም ሁለት ሙታን አስነሣ፤ አንዱን ሳይቀበር፤ ሁለተኛውን ከተቀበረ በኋላ ሥጋውን አስነሣ፡፡ እነዚያ ሙታን ቢነሡ ኋላ እንደ ሞቱ፤ እነርሱ ኋላ አንድ ሆነው የሚነሡበትን ትንሣኤ ዛሬ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የሙታን ትንሣኤያቸው በኲር ነው፤ እንግዲህ ወዲህም ሞት የሌለበትን ትንሣኤ አስቀድሞ የተነሣ እርሱ ነው፤ ዳግመኛም ሞት አያገኘውም ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ /ቅዱስ ኤጲፋንዮስ. 57፥3-6/
ቃል ሥጋውን በመቃብር አልተወም፤ በሲኦልም ካለች ከነፍሱ አልተለየም፤ ከነፍስ ከሥጋ በአንድነት ነበረ እንጂ፤ ለዘለዓለም ክብር ምስጋና ይግባው፡፡ /ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ሃይ. አበ. 60፥29/
ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ በትንሣኤ ከእናንተ ጋር እስከምመጣበት ቀን ድረስ ከዚያ ወይን ጭማቂ አልጠጣም፤ በሐዲስ ግብር በምነሣበት ጊዜ የምታዩኝ እናንት ምስክሮቼ ናችሁ ያለውን የማቴዎስን ወንጌል በተረጎመበት አንቀጽ እንዲህ አለ፡፡ ሐዲስ ያለው ይህ ነገር ምንድነው? ይህ ነገር ድንቅ ነው! መዋቲ ሥጋ እንዳለኝ ታያላችሁ፤ ነገር ግን ከትንሣኤ በኋላ የማይሞትነው፤ አይለወጥም፤ ሥጋዊ መብልንም መሻት የለበትም፤ ከትንሣኤ በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ቢበላም ቢጠጣም መብልን ሽቶ አይደለም፤ እርሱ ከሙታን ተለይቶ እንደተነሣ ያምኑ ዘንድ በላ ጠጣ እንጂ፡፡ ይህ ድንቅ ሥራ ነው! ያለ መለወጥ ሰው የሆነ ቃል የተቸነከረበትን ምልክት /እትራት/ አላጠፋምና፡፡
በሚሞቱ ሰዎች እጅ እንዲዳሠሥ አድርጎታልና፤ አምላክ የሆነ ሥጋ የሚታይበት ጊዜ ነውና አላስፈራም፤ እርሱ በዝግ ደጅ ገባ፤ ግዙፉ ረቂቅ እንደሆነ ሥራውን አስረዳ፤ ነገር ግን በትንሣኤው ያምኑ ዘንድ የተሰቀለው እርሱ እንደሆነ የተነሣውም ሌላ እንዳይደለ ያውቁ ዘንድ ይህን ሠራ፡፡ ስለዚህም ተነሣ፤ በሥጋውም የችንካሩን ምልክት /እትራት/ አላጠፋም፤ ዳግመኛም ከትንሣኤው አስቀድሞ ደቀ መዛሙርቱ ጧት ማታ ከእርሱ ጋር ይበሉ እንደነበረ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በላ፤ ስለዚህም በዐራቱ መዓዝነ ዓለም ትንሣኤውን አስረዱ፤ ከትንሣኤውም በኋላ ያየነው ከእርሱም ጋር የበላን የጠጣንም እርሱ ነው ብለው አስረዱ፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሃይ. አበ. 66፥7-12/
በእርሱ ሞት ከብረናል፤ በመለኮቱ ሞት ሳይኖርበት በሥጋ ሞተ፤ ምንጊዜም ቢሆን እርሱ የሕይወት ልጅ ሕይወት ነው፤ ይኸውም ከእግዚአብሔር አብ የተወለደው ልደት ነው፡፡ ወደ ሕይወት ሥጋ ደፍሮ በመጣ ጊዜ ሞት እንዲህ ድል ተነሣ፤ መፍረስ መበስበስም በእርሱ /በክርስቶስ/ እንዲህ ጠፋ፤ ሞትም ድል ተነሣ፡፡ /ቅዱስ ቄርሎስ ሃይ. አበ. 72፥12/
ሕማምን ሞትን ገንዘብ አደረገ፤በሥጋው የሞተው ሞትም የእኛን ባሕ ርይ በመዋሐዱ ነው፤ ከዚህ በኋላ ተዋሕዶውን አስረዳ፤ ሞት ሰው የመሆን ሥራ ነውና፤ ከሙታን ተለይቶ መነሣትም አምላክ የመሆን ሥራ ነውና፤ እነዚህ ሁለት ሥራዎችን /ሞትን፤ ትንሣኤን/ እናውቃለን፡፡ /ዝኒ ከማሁ 72፥35/
በሥጋ ሞተ እንዳልን ዳግመኛ በሥጋ ተነሣ እንላለን፤ ስለ ትንሣኤም የእርሱ ገንዘብ እንደሆነ፤ ሙስና መቃብርም እንዳላገኘው ይነገራል፤ ይህ ለመለኮት አይነገርም፤ የተነሣው ሥጋው ነው እንጂ፡፡ /ዝኒ ከማሁ 79፥9/
የሞትን ሥልጣን አጠፋ፤ ዲያብሎስንና ኃይሉን /ኃጢአትን/ ሻረ፤ የብረት መዝጊያዎችን ሰበረ /ፍዳ መርገምን አጠፋ/፤ ሲኦልን በዘበዘ፤ የጣዖት ቤቶችን አፈረሰ፤ የምሕረትን በር ከፈተ፤ ይህችውም በደሙ የከበረች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ለሁሉ የዘለዓለም ሕይወት መገኛ የሚሆን ልጅነት የተገኘበት ሥጋውን ደሙን ሰጠን፡፡ /ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ሃይ. አበ. 83፥6/
ለእኛስ እግዚአብሔር ቃል በባሕርየ መለኮቱ እንደታመመ፤ እንደሞተ፤እንደተቀበረ ልንናገር አይገባንም፡፡ ከሙታን ተለይቶ በመነሣቱ ሞት የሌለበት እንደሆነ፣ መድኀኒታችን በሚሆን በሞቱና በሦስተኛው ቀንም በመነሣቱ ትንሣኤን እንደሰጠን እናምናለን፤ የሞተ እርሱ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡ ሁሉን የሚችል እርሱ ካልተነሣ፣ የችሎታ ሁሉ ባለቤት እርሱ የሌለ ከሆነ፣ እንኪያስ ትንሣኤም ሐሰት ነዋ! ትንሣኤም ሐሰት ከሆነ ሃይማኖታችን ከንቱ ነው፤ እንኪያስ አይሁድንም እንመስላቸዋለን፡፡ ሰው እንደመሆኑ በሥጋ ባይሞትስ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው አምላክ እንደመሆኑ ሞትን ባላጠፋ ነበር፡፡ የአዳም የዕዳ ደብዳቤም ከእግዚአብሔርና ከሰው መካ ከል ባልተደመሰሰም ነበር፡፡ /ቅዱስ ሳዊሮስ ሃይ. አበ. 84፥18-20/
ፈጣሪያችን ክርስቶስ ለጌትነቱ እንደሚገባ ሥጋ መለወጥ የሌለበት እስኪሆን ድረስ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤ ሙስና መቃብርን አጥፍቷልና፤ በሥጋ በተቀበላቸው በሚያድኑ በእነዚህ ሕማማት ከጽኑ ሞት፣ ከዲያብሎስም ሥልጣን ያድነን ዘንድ ወደ ቀደመ ቦታችንም ያገባን ዘንድ፡፡ /ቅዱስ ዮሐንስ ዘአንጾኪያ ሃይ. አበ. 90፥34/
ይታመም ዘንድ በተገባው በሥጋው፣ ነውር የሌለበትን ሕማም በፈቃዱ በእውነት ተቀበለ እንጂ፤ በምትሐት እንዳልታመመ እናገራለሁ፤ እንደሕማሙ ሞትንም በመስቀል ላይ ተቀበለ፡፡ ለአምላክነቱ በሚገባ፤ ድንቅ በሚያሰኝ ትንሣኤውም የጌትነቱን ሥልጣንገለጠ፡፡ ሥጋውንም የማይሞት አደረገ፤ ከኃጢአት በራቀ በንጹሕ ማኅፀን በተዋሐደው ጊዜ ለመለኮት ገንዘብ ስለሆነበሥራው ሁሉ አይለወጥም፡፡ /ቅዱስ ቴዎዶስዮስ ሃይ. አበ. 92፥15/
ሕማም የማይስማማው እርሱ በሥጋ ሞትን ታገሠ፤ ብረት ወደ እሳት በገባ ጊዜ ሁለንተናው እሳት እንደሆነ እስኪታሰብ ድረስ በእሳት ዋዕይ እንዲግል፣ በመዶሻ በተመታ ጊዜ በመስፍሕ /መቀጥቀጫ/ ላይ እንዲሳብ /እንዲቀጠቀጥ/፤ እሳትም ከብረት ጋር ተዋሕዶ ሳለ ፈጽሞ እርሱ እንዳይመታ፤ ከብረቱም እንዳይለይ፣ ግን የመዶሻ ኃይል ሳያገኘው እንዲመታ፤ ለመዶሻ እንዲሰጥ፤ የሚያድን የጌታ ሕማም እንዲህ እንደሆነ ዕወቅ፡፡ በዚህ ትንሽ ምሳሌ፤ በእሳትና በብረት ተዋሕዶ ምልክትነት ፍጹም ተዋሕዶን እንወቅ፤ የእግዚአብሔር ቃል ይህ መከራና ሕማምን የሚቀበል ሥጋን ተዋሕዶ በሞተ ጊዜም ከሦስት ቀን በኋላ አምላክነቱ በተገለጠበት ትንሣኤው ሞትን አጠፋው፤ ሥጋው በመቃብር በመቀበሩም በመቃብር ውስጥ የነበረ መፍረስን መበስበስን አጠፋልን፤ ከሥሩም ነቀለው፤ ይህንም የሚያስረዳ ከቅዱሳን ወገን ብዙ ሰዎች ተነሡ፡፡ /ቅዱስ ባስልዮስ ሃይ. አበ. 96፥50-52/
ዳግመኛ እርሱ እንደሞተ በሦስተኛውም ቀን እንደተነሣ፣ ስለተነሣም ሥጋው የማይፈርስ የማይበሰብስ፣ የማይታመም፣ የማይሞት እንደሆነ እናምናለን፡፡ ሥጋውም ከእርሱ ጋር አንድ ሆኖ ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአርያም በልዑል ዙፋኑ ተቀመጠ፤ ዳግመኛም በሙታንና በሕያዋን ይፈርድ ዘንድ ሁሉ አንድ ሆኖ በሚነሣበት ጊዜ እርሱ በጌትነት ይመጣል፤ ለሁሉም እንደሥራው ይከፍለዋል፤ እኛ በእነዚህ ቃላት ሳናወላውል ጸንተን እንኖራለን፡፡ /ቅዱስ ዲዮናስዮስ ሃይ. አበ. 99፥32/
በፈቃዱ በሥጋው የእኛን ሕማም ታመመ፤ በእውነት የእኛን ሞት ሞተ፤ ይኸውም የነፍስ ከሥጋ መለየት ነው፤ በፈቃዱ በተለየ አካሉ ሞትን ገንዘብ አደረገ፡፡ በሦስተኛውም ቀን በሥልጣኑ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአባቱ ዕሪና ተቀመጠ፤ በኋለኛይቱ ቀንም በሙታን በሕያዋን ሊፈርድ ይመጣል፡፡ /ቅዱስ ፊላታዎስ ሃይ. አበ. 105፥14/
በሞቱ ሞትን ያጠፋው እሱ ነው፤ በሦስተኛው ቀን በመነሣቱም ሲኦልን በዘበዘ፣ ለሁሉም ትንሣኤን ገለጠ፡፡ ፈጽሞ አልተለወጠም፤ ለሁሉ አምላክነቱን አስረዳ፤ ሙስና መቃብርን ከእኛ አጠፋ፤ በቀደመ ሰው በአባታችን በአዳም ትእዛዝ ማፍረስ ምክንያት ሠልጥኖብን ለነበረ ኃጢአት ከመገዛት አዳነን፡፡ /ቅዱስ ዲዮናስዮስ 111፥13/
እሑድ በመንፈቀ ሌሊት ነፍሱ ንከሥጋው አዋሕዶ በመለኮታዊ ኃይል ተነሣ፤ እርሱ ራሱ ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ ልሰጥ ሁለተኛም መልሼ ላዋሕዳት ሥልጣን አለኝ፤ ይህን ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ እንዳለ፡፡ በነጋም ጊዜ ለማርያም መግደላዊት ታያት፤ እጅ ልትነሣው በወደደች ጊዜም አትንኪኝ አላት፤ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና፤ ስለዚህም ሥጋዊ አካሉ ከዚያን አስቀድሞ በአብ ቀኝ እንዳልተቀመጠ ዐወቅን፡፡ /አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽሐፈ ምሥጢር ዘትንሣኤ 95/
ሞትን በሥጋ በቀመሰ ጊዜ መለኮቱ በመቃብር ውስጥ ያለነፍሱ ከበድኑ ጋር ነበር፡፡ በሲኦልም ውስጥ ያለ ሥጋው ከነፍሱ ጋር ህልው ነበር፡፡ በአባቱም ቀኝ ያለነፍስና ያለሥጋ ህልው ነበር፡፡ በትንሣኤውም ጊዜ ነፍሱን ከሥጋው ጋር አዋሕዶ አስቀድሞ ለአይሁድ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስተኛው ቀን እሠራዋለሁ ብሎ እንደተናገረ፤ አይሁድም ይህ ቤተ መቅደስ ተሠርቶ ያለቀው በዐርባ ሰባት ዓመት ነው፤ አንተ ግን በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ትላለህ አሉት፤ ይህንንም የተናገረው ስለራሱ ሰውነት ነው፡፡
በተነሣም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ ነገር እንደተናገረ አሰቡ፡፡ በመጽሐፍና ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስም የተናገራቸውን ቃል አመኑ፤ ሁለተኛም ነፍሴን በፈቃዴ አሳልፌ እሰጣለሁ፤ ልለያት መልሼም አዋሕጄ ላስነሣት ሥልጣን አለኝ፤ ይህንንም ትእዛዝ ከአባቴ ተቀበልኩ፡፡ ዳዊትም አቤቱ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ ይላል፡፡ ነቢዩ አቤቱ አንተ የመቅደስህን ታቦት ይዘህ ተነሥ ለምን አለ? የመቅደሱ ታቦት ከሆነችው ከዳዊት ዘር ከነሣው ሥጋ ጋር በመለኮታዊ ኃይሉ ከሞት እንቅልፍ ከመንቃት በስተቀር የእግዚአብሔር መነሣት ምንድነው? /አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ መጽ. ምሥጢር ዘትንሣኤ 77-79/
ዮሴፍ ኒቆዲሞስ ከጲላጦስ ተካሰው ከመስቀል አውርደው፣ በድርብ በፍታ ገንዘው በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ በሦስተኛው ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገብቶ በጽርሐ ጽዮን ታያቸው፡፡ /ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ 1፥29-31/
ሰውን ስለመውደድህ ይህን ሁሉ አደረግህ፤ ከሙታን ተለይተህ መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳትል ተነሣህ፡፡ ከእግረ መስቀል ሙታንን አስነሣህ ነፍሳትን ከሲኦል ማርከህ ለአባትህ አቀረብህ፡፡ /ቅዳሴ ያዕቆብ ዘስሩግ 1፥24/
በታወቀች በተረዳች በሦስተኛይቱ ቀን መቃብር ክፈቱልኝ፤ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ተነሣ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት በዝግ ቤት ገባ፤ የተወጋውን ጎኑን፤ የተቸነከረውን እጁን፣ እግሩን አሳያቸው፡፡ በዓለመ ነፍስ የሆነውን እያስተማራቸው ዐርባ ቀን ኖረ፡፡ /ቅዳሴ ዘሠለስቱ ምዕት 4፥25-27/
ሰማያት /ሰማያውያን መላእክት /የደስታ በዓልን ያደርጋሉ፤ ደመናት /ቅዱሳን/ የደስታን በዓል ያደርጋሉ፣ ምድር /ምድራውያን ሰዎችም/ በክርስቶስ ደም ታጥባ /ታጥበው/ የፋሲካን በዓል ታደርጋለች /ያደርጋሉ/ ያከብራሉ /ታከብራለች/፡፡
ዛሬ በሰማያት /በሰማያውያን መላእክት/ ዘንድ ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ምድርም በክርስቶስ ደም ታጥባ የፋሲካን የነጻነት በዓል ታደርጋለች፡፡ የትንሣኤያችን በኩር ክርስቶስ ከሙታን ሰዎች ሁሉ ተለይቶ ቀድሞ ተነሣ፡፡ /ድጓ ዘፋ ሲካ/