ged te 2006

ለአብነት መምህራኑ የህክምና ምርመራ ተደረገ፡፡ ክብካቤና ክትትል ካልተደረገ ለዐይነ ስውርነት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡

 የካቲት 13 ቀን 2006 ዓ.ም.

 
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

በቅርቡ ለሦስተኛ ጊዜ በማኅበረ ቅዱሳን አዘጋጅነት ሊካሄድ የነበረውን የአብነት መምህራን ሀገር አቀፍ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ  ከመጡት 202 ሊቃውንት ከ70 በላይ የአብነት መምህራን ካታራክት እና ትራኮማ ችግር እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡ክብካቤና ክትትል ካልተደረገ ለዐይነ ስውርነት ሊዳረጉ እንደሚችሉ  የማኅበሩ የሞያ አገልግሎት ዋና ክፍል የሕክምና  ቡድን ገለጸ፡፡

ged te 2006

ማኅበሩ ባቋቋመው ጊዜያዊ ክሊኒክ ለ170ዎቹ ለምስክር መምህራኑ የውስጥ ደዌ፣ የዐይን፣ የነርቭ፣ የአጥንትና ሌሎችም የበሽታ ዐይነቶች ላይ በስፔሻሊስቶች ባካሔደው ምርመራ ከ70 በላይ የአብነት መምህራን ካታራክት እና ትራኮማ ችግር እንዳለባቸው ተረጋግጧል፡፡

ምርመራውን ከምኒልክ ሆስፒታልና ሌሎች የግል የሕክምና ማእከላት ጋራ በመተባበር ማከናወኑን የገለጸው የማኅበሩ የሞያ አገልግሎት ዋና ክፍል የሕክምና  ቡድኑ አባላት ፤የሊቃውንቱ ዐይን ህመም ሊከሰት የቻለው የአብነት መምህራኑ የሚጠቀሙባቸው ጧፎች ቀለም ተቀላቅሎባቸው የሚመረቱ በመሆናቸው ጢሱ እየጎዳቸው በመሆኑ፣ በድንግዝግዝ ብርሃን ማንበባቸው፣ የግል ንጽሕና አጠባበቅና ዕድሜ ከዐይን ጋራ ተያይዞ እንደሆነ ተገለጾ ፤ክብካቤና ክትትል ካልተደረገ ለዐይነ ስውርነት ሊዳረጉ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡

የህክምና ቡድኑ ለ50ዎቹ የንባብና የፀሐይ መነጽሮች የታደለ ሲሆን፤ ከዐሥር ሺሕ ብር በላይ ግምት ያላቸው መድኃኒቶች እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን መነጽር ላላገኙትም ድጋፍ እየጠየቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቡድኑ መምህራኑና ተማሪዎቻቸው ከሚጠቀሙባቸው ያልታከመ የወንዝና የምንጭ ውኃ ጋራ የተያያዙ ውኃ ወለድ የሆድ ሕመሞች፣ የቆዳ በሽታዎች በዚሁ አጋጣሚ በተደረገ የጤና ምርመራ ታውቀው ጊዜያዊ መድኃኒት መሰጠቱን ተነግሯል፡፡ በመጪው ዐብይ ጾምም በየአህጉረ ስብከቱ በግል ጤና አጠባበቅና በመከላከል ላይ ያተኮረ የጤና አጠባበቅ ሥልጠና ለመስጠት ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አመልክቷል፡፡