metshate 01

ሦስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጥናት መጽሔት ለኅትመት በቃ

መጋቢት 8 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

metshate 01የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል በተለያዩ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን በማካሄድ ያሳተመውን ሦስተኛው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምርምር መጽሔት /Journal/ ለኅትመት በቃ፡፡

የምርምር መጽሔቱ ጠቀሜታ ከፍተኛ እንደሆነ የገለጹት የጥናትና ምርምር ማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ስይፈ አበበ “ለፖሊሲ አውጪዎች እና ለውሳኔ ሰጪዎች ግብአት ይሆናል፤ቤተ ክርስቲያን በጥናት እና ምርምር የተደገፈ ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት እንድታበረክት ያግዛታል፤ለተለያዩ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ምላሽ ይሰጣል፤ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት እና በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚገኙ ምሁራን ልጆቿን ለቀጣይ ጥናት ያነሳሳል፣ ያበረታታል” ብለዋል፡፡

የምርምር መጽሔቱ ሰባት ጥናታዊ ጽሑፎችን በማካተት የቀረበ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ፡-

  • የቅዱስ ያሬድ የሕይውት ታሪክና የሥራዎቹ አጭር ዳሰሳ ታሪክ /History/

  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አሻራ በሸካቾ ብሔር ፤ማኅበራዊ እና ቅርስ /Social Heritage /

  • የደንና ብዝኀ ሕይወት ጥበቃ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን /Forestry & Biodiversity/

  • The Ethiopian Religious Community and Its Ancient Monastery, Deires-Sultan, in Jerusalem from Foundation to 1850s ታሪክ /History/ Treasures of the Lake Zway Churches and Monastery, South Central Ethiopia ቅርስ /Heritage/

  • Woody, Species Diversity, Floristic Composition and Structure of DebreLibanose Forests. Biodiversity

  • Oromo Language use in Wellega Dioceses: opportunities and Challenges በአፍ መፍቻ ቋንቋ ማስተማር/Teaching with Mother toungs/ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ተዘጋጅቷል፡፡

የምርምር ማዕከሉ በምርምር ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ አጥኚዎችን ያበረታታል፣ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የማማከር አገልግሎት ይሰጣል፤ የውይይት መድረኮችን እና ዐውደ ጥናቶችን በማዘጋጀት ያወያያል፡፡

ጥንታዊቷ የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተመዘበረች

 መጋቢት 4 ቀን 2006 ዓ.ም.

ሹመት ገ/እግዚአብሔር

በደሴ ማእከል ከወረኢሉ ወረዳ ማእከል

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን በወረኢሉ ወረዳ የምትገኘው የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ማንነታቸው ባልታወቁ ዘራፊዎች ተመዘበረች፡፡

የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከወረኢሉ ከተማ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም በግምት ከጧቱ 4፡00 ሰዓት ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች ንዋየ ቅድሳቷ የመዘረፍና የመውደም አደጋ ደርሶባታል፡፡

ድርጊቱ የተፈጸመው የቤተ ክርስቲያኒቱን በርና መስኮት ሰብሮ በመግባት ሲሆን፤ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የቅዳሴ መጽሐፍ ባለምልክቱ፣ ሰባት የቤተ ክርስቲያን መጋረጃ፣ ሰባት መቋሚያ፣ ሦስት ምንጣፍ እና አምስት መሶበ ወርቅ ተሰርቋል፡፡ ትልቅ የመፆር መስቀል እና የእጅ መስቀሎች የተፈላለጡ ሲሆን መንበሩ ተገነጣጥሏል፡፡ ቤተ ክርስቲያኗንና መንበሩን ሳርና ስዕለ አድህኖ በመሰብሰብ ለማቃጠል የተደረገው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

መጽሐፈ ክርስትና፣ ሥርዓተ ተክሊልና መጽሐፈ ግፃዌ ሙሉ በሙሉ ተቀዳደው፤ ሻኩራ፣ ፃህል፣ እርፈ መስቀል፤ ሻማዎች፣ የተቀጠቀጡ አንድ ሺህ ጧፎች፤ አስር ኪሎ እጣን፤ ጥላዎች ተቀዳደው፤ 15 ባለ መስታወት ፍሬም ስዕለ አድህኖዎች ተሰባብረው፤ ከፍሬም ውጭ የሆኑ 88 ስዕለ አድኅኖዎች ተቀዳደው ጫካ ውስጥ የተጣሉ ሲሆን፤ መቋሚያዎችና አምፖሎች ከነማቀፊያቸው ተሰባብረው ገደል ውስጥ ተጥለዋል፡፡ 6 ትላልቅ ሥዕለ አድኅኖዎችም ተቃጥለዋል፡፡

ይህንን ልብ የሚያደማና የሚያሳዝን ድርጊት የወረዳው ከፍተኛ የሥራ ሓላፊዎች እና የፀጥታ ኃይሎች ቦታው ድረስ በመሄድ የተመለከቱ ሲሆን፤ ድርጊቱን የፈፀሙትን ወንጀለኞች ለመያዝ የወረዳው ፖሊስ አስፈላጊውን ክትትልና ምርመራ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የወይብላ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን በግራኝ አህመድ ከመቃጠሏና ከመውደሟ በፊት “ቀርቀሬ ማርያም” በሚል ስያሜ ትጠራ የነበረ ሲሆን፤ የአካባቢው ተወላጆች ወደ ጦር ሜዳ በሔዱ ጊዜ “ያገሬ ታቦት ወይ በይኝ፣ ከዚህ ጦርነት በሰላም ከመለሺኝ ስመለስ ስዕለቴን አገባለሁ” ብለው በመሳላቸውና ሥዕለታቸውም በመድረሱ ሲመለሱ “ወይብላ ማርያም” በሚል ስያሜ እንደተጠራች ይነገራል፡፡ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኗ እንደገና ታንፆ ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ መልክ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነበረች፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ሥርጭት አንደኛ ዓመት ተከበረ

 

መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ሥርጭት አንደኛ ዓመት በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ አርቲስቶች የማኅበሩ ደጋፊዎችና የማኅበሩ የሥራ አመራር አባላት በተገኙበት ተከበረ፡፡

በዕለቱ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን አንደኛ ዓመት ለማክበር የተገኙትን ባለድርሻ አካላት “እንኳን ደኅና መጣችሁ” ያሉት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ እንደገለጹት “ማኅበረ ቅዱሳን ወንጌለ መንግሥትን ለዓለም ለማዳረስ በሚደረገው መንፈሳዊ አገልግሎት የኅትመት ውጤቶች ሲጠቀም መቆየቱን ገልጸው አሁንም በቴክኖሎጂው በመታገዝ በዓለም ሁሉ ከምንደርስበት መንገዶች አንዱ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩ መጀመር የምሥራች ሲሆን በእውቀት፣ በገንዘብ፣ በጉልበት ድጋፋችሁ ሁል ጊዜ የማይለየን ክቡራን እንግዶቻችን አሁንም ድጋፋችሁ እንዳይለየን በሚል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቃለ እግዚአብሔርን ለመመገብ የተገኙት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ እንዳስተማሩትም “ስብከት የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ነው፡፡ የጠፋው በኃጢአት ምክንያት የኮበለለ የሰው ልጅ ሲሆን የሚጠራው፣ የሚያፈላልገው እግዚአብሔር ነው፡፡ ከማፈላለጊያ መንገዶች አንዱ ደግሞ ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት በመሆኑ አገልግሎቱን ልንረዳ ይገባል፡፡ በማለት አስተምረዋል፡፡

በዕለቱ መርሐ ግብር መሠረት የበገና መዝሙር በመ/ር አቤል ሙሉጌታ፣ መነባንብ በአርቲስት ንብረት ገላው፣ በቴሌቪዥን ክፍል ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ በዶ/ር መርሻ አለኸኝ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ለታዳሚው ቁጭትን የፈጠረና በተለይ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ቃለ እግዚአብሔርን በተለያዩ ቋንቋዎች ማዳረስ ሲቻል አለማዳረሳችን ግንዛቤ አግኝቷል፡፡

ከጥናታዊ ጽሑፉ በመነሣት የአኀት አብያተ ክርስቲያናት (ኮፕት) ጥቂት ምእመናን ይዘው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሲኖራቸው፤ የኛ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ምእመናን እያለን ይበልጥ መሥራት ሲገባን አለመሥራታችን፣ በሀገራችን የሌላ እምነት ተከታዮች የ24 ሰዓት ሬድዮና ቴሌቪዥን ሲኖራቸው እኛ ግን በሳምንት ከሦስት ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ መኖሩ በንጽጽር ቀርቦ የጉባኤው ተሳተፊ ለቀጣዩ ከማኅበሩ ጋር በመተባበር የበኩላቸውን እንደሚያበረከረቱ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የማኅበሩ በሳምንት የአንድ ሰዓት የቴሌቪዥን ሥርጭት ወደ 24 ሰዓት እንዲያድግ በቅርቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተጋባዥ እንግዶች አበክረው አሳስበዋል፡፡ የማኅበሩን የቴሌቪዥን መርሐ ግብር በ EBS TV እሑድ ከ5፡00-600 ሰዓት የሚተላለፍ ሲሆን በድጋሚ ሐሙስ ጠዋት 1፡00-2፡00 ሰዓት ይተላለፋል፡፡ በተጨማሪም www.eotc.tv ይከታተሉ፡፡

 

desa 2006 01

የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ስለቤተክርስቲያን ዘላቂ ልማት ከበጎ አድራጊዎች ጋር ውይይት አደረገ፡፡

የካቲት 28 ቀን 2006 ዓ.ም. 

ወርቁ በላይሁን ደሴ ማእከል

የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል “ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት በጋራ እንሥራ” በሚል መርህ ለሁለተኛ ጊዜ ከደሴ ከተማ በጎ አድራጊዎች ጋር የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም ውይይት አደረገ፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ desa 2006 01ጥሪ የተደረገላቸው በጎ አድራጊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ለዘላቂ የቤተ ክርስቲያን ልማት መሠራት ስለሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱም በስብከተ ወንጌል፣ በቅዱሳት መካናትና በአብነት ት/ቤቶች ዙሪያ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ወጥነት ባለው መልኩ የልማት ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት በማእከሉ ተቀርጸው የቀረቡ ፕሮጀክቶችንና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችንም ለመሥራት የምዕመናንን ተሳትፎ ለማጠናከር ስድስት ኣባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ በዕለቱ ተመርጧል፡፡

ኮሚቴውም ለቀረቡት ፕሮጀክቶች የአካውንት መክፈቻ የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት ያደረገ ሲሆን፤ አስተዋጽዖን በተመለከተ እያንዳንዱ ተሳታፊ በተሰጠው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ሞልተዋል፡፡ በየወሩ ድጋፍ ለሚያደርጉ በጎ አድራጊዎችም የተባባሪ አባልነት መታወቂያ እንዲዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ዮሐንስ ደምሴ በዕለቱ የተገኙት ተሳታፊዎች በሥራ ቦታና በመኖሪያ አካባቢ የሚያውቋቸውን በውይይቱ ያልተገኙ ምዕመናንን በዚህ በጎ አገልግሎት እንዲሳተፉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ለመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ማእከሉ ያዘጋጀውን ዶክመንተሪ ፊልም የቀረበ ሲሆን፤ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

 

ምኲራብ

 የካቲት 27 ቀን 2006 ዓ.ም. 

ታመነ ተ/ዮሐንስ

 

“ዘወትርም በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር” ሉቃ.19፥47

ምኲራብ የአይሁድ የጸሎት ቤት ሲሆን በብሉይ ኪዳን ዘመን የአይሁድ አምልኮ በኢየሩሳሌም በነበረው ቤተ መቅደስና በሥርዓቱ የተመሠረተ ነበር፡፡ ናቡከደነጾር ግን ቤተ መቅደሱን አፈረሰ ሕዝቡንም ወደባቢሎን አፈለሰ፡፡ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ አይሁድ በሚገኙባቸው ሥፍራዎች ሁሉ ለጸሎትና ለማኅበረተኛነት ልዩ ቤት ሊሠሩ እንደጀመሩ ይታሰባል፡፡ /የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት/

አይሁድ በምኲራቦቻቸው የሕግንና የነቢያትን መጻሕፍት /የብራና ጥቅሎች/ በአንድ ሣጥን ውስጥ ያስቀምጣሉ በመሆኑ እኒህን የጸሎት ሥፍራዎቻቸውን ለትምህርትና ለአምልኮ ይጠቀሙባቸዋል፡፡ በሕገ ኦሪት የአይሁዳውያን ወደ ቤተ መቅደስ መሄድ ሕግና ልማዳቸው ነበር፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ ተግባራት ከሚሄዱበትም ይልቅ በዓመት አንዴ የሚቀርበውን መሥዋዕትና መባዕ ለመስጠት ወደ ቤተ መቅደስ ይወጡ ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ከብቻዋ ከኃጢአት በቀር ከሕግ ጸባያዊ /ከተፈጥሮ ሕግ/ እኩል ሕግ መጽሐፋዊንም /የመጽሐፍት ሕግን/ ሲፈጽም ስለኖረ እንደ ሕጉ ወደ ቤተ መቅደስ በመሄድ ሥርዓት ይፈጽም ነበር፡፡

“ዐሥራ ሁለት ዓመትም በሞላው ጊዜ እንደአስለመዱ ወደ ኢየሩሳሌም ለበዓል ወጡ” እንዲል /ሉቃ.2፥42/ አምላካችንና መድኃኒትችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሥርዓት የሐዲስ ኪዳን አስተምህሮውን /ወንጌልን/ መስበክ ከጀመረም በኋላ አጽንቶ ይፈጽም ነበር፡፡ መጽሐፍም ይህን ሲያጸናልን፡- “ዕለት ዕለትም በቤተ መቅደስ /ምኩራብ/ ያስተምር ነበር፡፡” /ሉቃ.19፥47/ ይለናል፡፡

ጌታችን በምኩራብ እየተገኘ ሲያስተምር ትምህርቱን ሕግን አውቆ እንደሚያሳውቅ ሠራዔ ሕግ ስለሆነ በሙሉ ሥልጣንና ኃይል ያስተምር ነበር፡፡ “በሰንበት በምኩራብ ገብቶ ያስተምራቸው ጀመረ፡፡ ትምህርቱንም አደነቁ፤ እንደጻፎቻቸው ያይደለ እንደ ባለሥልጣን ያስተምራቸው ነበርና” እንዲል /ማር.1፥21/፡፡

ይህም ስለምን ነው ቢሉ ባያውቁትም ቅሉ ከርሱ ባገኙት ሥልጣንና ከመምህራኖቻው በተማሩት እውቀት ተመርተው ያስተምሩ ነበር፤ እርሱ ግን ዓለምን በመዳፉ የያዘ ለእነርሱም በሕገ ኦሪት አማካኝነት እውቀት ዘበፀጋን ከፍሎ የሰጠ ነውና ከራሱ አንቅቶ ያስተምር ነበርና ነው፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መሠረትና መንገድ በምኩራብ እየተገኘ በግልጥ ያስተምርና ይፈውስ ነፍሳትንም ወደመንጋው ይጨምር ነበር፡፡ አስተምህሮውን ለምን በግልጥ አደረገ ቢባል አንደኛው ምክንያት አይሁድ ለመማርና ለመለወጥ ያይደል እንከን ያገኙበት ዘንድ ዕለት ዕለት ከትምህርት ገበታው ላይ ይገኙ ለነበሩት ለፈሪሳውያንና ለጸሐፍት ምክንያትን ያሳጣ ዘንድ ነበር፤ ይኸውም በሥውር ፈጽሞት ቢሆን ኖሮ ከገሊላ ጀምሮ እስከዚህ ድረስ በመላው ይሁዳ እያስተማረ ሕዝቡን ያውካል ብለው ለከሰሱት ምክንያት ማሳመኛ አይደለም በሆነ ነበርና ነው፡፡

እንዲሁም ሕዝብን በእርሱ ላይ በማነሳሳት ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩ የካህናት አለቆችና ጸሐፍትን መጽሐፍ እንዲህ ይላል “የካህናት አለቆችና ጻፎችም ቆመው በብዙ ያሳጡት ነበር፡፡” /ሉቃ.23፥5-10/ ስለሆነም አይሁድ እንኳን በምክንያት ተደግፎላቸው ቀርቶ ነቁጥ ከማይገኝበት ከጌታችን በሆነው ባልሆነው ምክንያት ይፈልጉ ነበርና ለዚህ የተመቸ እንዳይሆን /ለእነርሱም የመሰናከያ ምክንያት እንዳይሆን/ ይህን አድርጓል፡፡

ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ “በአባቱ እቅፍ ያለ ልጁ እርሱ ገለጠልን” /ዮሐ.1፥18/ እንዲል ትንቢታትንና ምሳሌያትን እያፍታታ፣ የተሰወረውን እየገለጠ ሊያስተምር ወደዚህ ዓለም መጥቷልና ማስተማሩን በግልጥ አደረገ፡፡ እርሱም ቢሆን አንዳች ነገርን እንዳልሰወረ በሊቀካህናቱ ፊት ባቆሙት ጊዜና ስለትምህርቱ በጠየቁት ጊዜ እንዲህ በማለት መስክሯል፡- “እኔ ለዓለም በግልጥ ተናገርሁ፤ አይሁድ ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብም በቤተ መቅደስም ሁል ጊዜ አስተማርሁ፤ በስውርም የተናገርሁት አንዳች ነገር የለም፡፡” /ዮሐ.18፥20/

በሌላ መልኩ ይህ ቤተ መቅደስ /የጸሎት ሥፍራ/ በኦሪት የሚፈጸሙ ሥርዓቶችን /መሥዋዕትንና መብዓ ማቅረብን የመሳሰሉትን/ የሚያከናውኑበት ሥፍራ የነበረ እንደመሆኑ መጠን በሥፍራው የመሥዋዕት እንስሳት፣ የመሥዋዕት ማቅረቢያና ማሟያ ግብአቶች ለሽያጭ ይቀርቡ ነበር፤ አይሁድ አምልኳቸውን ከመፈጸም ይልቅ ቅሚያ፣ ዝርፊያ፣ ማታለል ይፈጽሙበት ነበር፡፡ ጌታችን “ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል ተብሎ ተጽፏል፤ እናንተ ግን የሌባና የቀማኛ ዋሻ አደረጋችሁት” /ማቴ.21፥13/ በማለት ተቃውሟቸዋል ሻጮችንም ሆነ ገዢዎች የነበሩትን ሁሉ በጅራፍ ገርፎ አባሯል፡፡ ሻጮችንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ…..” /ማቴ.21፥12/ እና “ማንም ዕቃ ተሸክሞ በመቅደስ እንዲያልፍ አልፈቀደም” /ማር.11፥16/ የሚሉት ኃይለ ቃላት ይህንኑ ድርጊቱን የሚያስረዱን ናቸው፡፡

እንዲሁም ቤተ መቅደስን የመንጻት ሥርዓት በፈጸመበት ወቅት ካስተላለፋቸው መልእክታት አንዱ የጥንቱ የመስዋዕት አቀራረብ ሥርዓት ማክተሙን ማወጅ ነበር ስለዚህም ለመሥዋዕት የቀረቡ በጎችንም እንዲያወጡ አዘዘ፡፡ እውነተኛው የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕትም እርሱ መሆኑንና ጊዜው መድረሱን አጠየቀ ከፊቱ መንገዱን ሊያዘጋጅ በኤልያስ መንፈስ ይመጣል የተባለው መጥምቁ ዮሐንስም “እነሆ የዓለሙን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት በተደጋጋሚ ያወሳው ስለዚህ ነበር /ዮሐ.1፥29 እና 36/፡፡

ጌታችንም ቢሆን በመዋዕለ ሥጋዌው ስለ ኦሪት አንዳንድ ሥርዓቶችን ማለፍ ለሐዋርያትና ለሚከተሉት እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር “ኦሪትም ነቢያትም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዮሐንስ ድረስ ነበሩ፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የእግዚአብሔር መንግሥት ይሰበካል፤ ሁሉም ወደ እርስዋ ይጋፋል፡፡” /ሉቃ.16፥16 “ከኦሪት አንዲት ቃል ከምትወድቅ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል” እንዳለ ጌታችን በቃሉ፡፡ ምክንያቱም እርሱ ያስተማረው ወንጌል ጥንት በመጻሕፍተ ነቢያት የተገኘ ስለነበረ ነው፡፡

እንግዲህ ቅዱስ ያሬድ ከደረሳቸው የዜማ ድርሳናት ውስጥ በዐብይ ጾም የሚዜመው ጾመ ድጓ የዓብይ ጾም ሳምንታትን በ9 ከፋፍሎ የሚገኝ ሲሆን በዚህ ጽሑፋችን ምኩራብ ስለተሰኘው ሳምንትና ጌታችን በቤተ መቅደስና በምኩራብ እየተገኘ ስላስተማረባቸው ጊዜያት የምናስብበትን ጾሙን በቃለ እግዚአብሔር አስረጅነትና ሕይወትነት የሥርዐቱን ፍጹም መንፈሳዊነት ተረድተን የምንጾመው ነው፡፡ ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለት ዕለት በቤቱ የሚነገረውን ቃሉን ለመስማትና ለመተግበር ያበቃን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁን፡፡

 

semet 2006 3 2

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በዓለ ሢመት ተከበረ::

የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

semet 2006 3 2
semet 2006 3 1የብፁዕ ወቅደስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ 1ኛ ዓመት በዓለ ሢመት ዛሬ የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የኢትዮጵያ አባት አርበኞች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ምእመናን በተገኙበት ተከበረ፡፡

የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪጅ ብፁዕ አቡነ ማቲዎስ በዓለ ሢመቱን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉ ሲሆን የደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ሊቃውንት ዝማሬ ፣  የአዲስ አበባ ገዳማት፣ አድባራት ሊቃውንት የአጫበር ዝማሜ፣ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን መዝሙር ቀርቦ መጋቤsemet 2006 2 ምስጢር ወልደ ሩፋኤል ፈታሔ ወመድስ አቅርበዋል፡፡

ቅዱስነታቸው ካደረጓቸው ንግግሮች ዋና ዋናዎቹ

  • ይህ በዓል የቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዓል ነው፡፡

  • የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ሳይበረዝ መጠበቅ የኛ ግዴታ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሥራ በእግዚአብሔር ስም የሚሠራ ስለሆነ አድሏዊነት የሌለበት መልካም ሥራ መሆን አለበት፡፡

  • እግዚአብሔር የማይቀበለው ሙስና ካልጠፋ ሕይወት አይኖረውም፡፡ ሙስና ጸያፍ ነው፤ የሚያማስነውና የሚማስነው አብረው ይጠፋሉ፡፡ የሚያማስነው ሰው ነው፡፡ የሚማስነው ደግሞ የድሆች ገንዘብ ነው፡፡ እግዚአብሔርን ማታለል አይቻልም፡፡ በእግዚአብሔር ላይ መቀለድ አይቻልም፡፡ ይህን ቃል የዛሬ ዓመት የተናገርኳቸው ናቸው፡፡ ዛሬ የደገምኩት ለአጽንኦተ ነገር ነው፡፡ የተናገርኳቸው ቃላት ሁሉ እንደጸኑ ናቸው፡፡ አሁን በበለጠ አጠናክራቸዋለሁ ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጋር፡፡

tenat 2006 1

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል” በሚል ርእስ ጥናት አቀረበ

 የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

tenat 2006  1
“የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል” በሚል ርዕስ በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ዋና ክፍል አዘጋጅነት በአቶ አለማ ሐጎስ አቅራቢነትና በአቶ አበባው አያሌው አወያይነት በማኅበሩ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም ቀረበ፡፡

tenat 2006  2ጥናቱ ያተኮረው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ወቅት ያደረገችውን አስተዋጽኦ የዳሰሰ ሲሆን በዋናነት፡-

  • ለአፍሪካና ለጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል በር የከፈተች መሆኗና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በአፍሪካውያን መፈለጓና ቤተ ክርስቲያን መመስረታቸውን፡፡
  • በጦርነት ዘመቻ የሃይማኖቱ መሪዎችና ተከታዮቹ እግዚአብሔርን መከታ አድርገው መዝመታቸው፡፡
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሀገር ለመውረር የመጣን ጠላት በመመከት ግንባር ቀደም ሆና ለአንድነትና ለነጻነት መታገሏ፡፡
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከድል በኋላ በምርኮኞች አያያዝ ላይ ያደረገችው አስተዋጽኦና ሌሎችም ዐብይ ጉዳዮች በጥናት አቅራቢው ከቀረቡ በኋላ ከተሳታፊዎች ጥያቄና አስተያየትtenat 2006  3 ቀርበዋል፡፡በውይይቱ የኢትዮጵያ አባት አርበኞች፣ ምሁራንና የማኅበረ ቅድሳን አባላት ተገኝተዋል፡፡

 

 

ማእከሉ ወደ ሲሌ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ፡፡

 

የካቲት 20 ቀን 2006 ዓ.ም.

ከአርባ ምንጭ ማእከል

በማኅበረ ቅዱሳን አርባ ምንጭ ማእከል መራሔ ፍኖት በሚል መሪ ቃል ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መጋቢት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ ሲሌ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ፡፡

በማእከሉ የግቢ ጉባኤ ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊ የሆኑት አቶ ኃይለ ኢየሱስ እንግዳው እንዳስታወቁት ጉዞው የሚደረገው ተማሪዎች በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው እንዲጠነክሩ፣ አርዓያነት ያለው ሕይወት እንዲኖራቸው፣ ወደ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት በመሄድ በረከት እንዲያገኙ፣ ዘመኑን መዋጀት የሚያስችላቸውን ዕውቀት ገንዘብ እንዲያደርጉ ለማገዝ ታስቦ የተዘጋጀና በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተመርኩዞ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ሲሆን በተጨማሪም ቅኔ፣ መዝሙር የሚቀርብበትም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ማእከሉ ከዚህ በፊት ግቢ ጉባኤያትን ያሳተፈ የእግር ጉዞ በከተማው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሲያካሂድ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ኃይለ ኢየሱስ፤ ይህን ጉዞ ለየት የሚያደርገው ከአርባ ምንጭ ከተማ ውጭ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን የሚከናወን በመሆኑ ነው፣ ሲሉ ገልጸው፤ ተማረዎችም የጉዞው ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ሓላፊው አሳስበዋል፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡

የካቲት 18 ቀን 2006 ዓ.ም.

በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን አሜሪካ ማእከል ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ንዑስ ክፍል ለቤተ ክርስቲያን እና ለማኅበሩ አገልግሎት ጠቃሚ የሆኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና አራሮችን በቀላሉ ለማቅረብ የተቁዋቁዋመ ክፍል ነው። ይህ ክፍል ከ1999 ዓ.ም (2008) ጀምሮ በሰሜን አሜሪካ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ከንዑስ ክፍሉ ባገኘነው መረጃ መሠረት ክፍሉ፡-

  1.  የሰሜን አሜሪካ ዋና ማእከል የሚጠቀምበትን ዋና የትምሕርት ፣የዜና፣ የማስታውቂያ፣ ዌብ ሳይት አዘጋጅቷል (Mkus.org)

  2.  ለገዳማት እና አድባራት መርጃ የሚሆን ገንዘብ ማስገኛ እና ሪፖርት ማድረጊያ (ኢንተራክቲቭ) ዌብ ሳይት አዘጋጅቶ በአገልግሎት ላይ እንዲውል አድርጓል (Gedamat.org)

  3. የአባላትን መመዝገቢያ እና መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ሰርቶ በስራ አውሟል http://us.mahiberekidusan.org/Login.aspx

  4.  የአብያተ ክርስቲያናት አድራሻ ማግኛ ዌብ ሳይት ሰርቶ ለተገልጋዮች ምእመናን አቅርቧል (Eotc.info)

  5. የእቅድ እና ሪፖረት ማቅረቢያ ዌብ ሳይት አዘጋጅቶ ለአገልግሎት አውሏል (plar.mkus.org)

  6. ቤተ ክርስቲያን የሰበካ ጉባኤ አባላት ለማስተዳደር የሚረዳ ዘዴ (ሲሰትም) አዘጋጅቷል

  7.  የዝቋላ ቤተ ክርስቲያን ለጊዚያዊ መርጃ የሚሆን የፔፓል ዌብ ሳይት አዘጋጅቶ ገንዘብ የሚሰበሰብበትን መንገድ አፋጥኗል

  8. የተዋሕዶ ቴሌቪዥን (Eotc.tv) የሚጠቀምበትን ዌብ ሳይት በማዘጋጀት መነፈሳዊ የቴሌቭዥን ዝግጅቶችን ለማስተላለፍ ችሏል

  9. ለጥናትና ምርምር የሚጠቅሙ ዌብ ሳይቶች (Servey websites) በቀላሉ መስራት የሚያስችል አቅም ፈጥሯል

  10. አባላት መወያየት የሚችሉበት ማኅበራዊ ዌብ ሳይት ፈጥሯል፡፡ (http://www.eotcworld.org/)

  11. የቤተ ክርስቲያንን የቀን መቁጠሪያ (ካላንደር) በዌብ ላይ ሰርቶ አቅርቧል http://www.eotc.info/calendar

  12. እነዚህን የተሠሩ ሥራዎች ሁሉ አባላት በአንድ ቦታ ላይ እንዲያገኙዋቸው በሚያስችል መልኩ http://www.mahiberekidusan.org/portal/ አስቀምጧል።

  13. የአይፎን ስልክ አፕሊኬሽኖች (የቤተ ክርስቲያን ማውጫ፣ የቴሌቪዠን እና የዜና፣ የቅዱሳን መጻሕፍት፣ተዋሕዶ ሚድያ፣ ግጻዌ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ ቀን መለወጫ፣ የእልቱን ምንባብ ማውጫ) ሰርቶ አውጥቶአል። 

  14. ለማኅበሩ በአጠቃላይ የሚያገለግል አዲስ እና ተመሳሳይነት ያለው የኢሜል አድራሻ አዘጋጅቶ በሰሜን አሜሪካ በሁሉም ደረጃ ያሉ ክፍሎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ጀምሯል።

  15.  አብያተ ክርስቲያናት የራሳቸውን ዌብ ሳይት እንዲሰሩ የሚያስችል ቴምፕሌት አዘጋጅቶአል። ከአብያተ ክርስቲያናት በተጠየቀ ቁጥር በአግልግሎት ላይ እንዲውል ያደርጋል።

  16. ከአባላት ግንኙነት ክፍል ጋር በመተባበር የአባላትን መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ሊጨምር የሚገባቸውን መረጃዎች መጨመር እና ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ መፈለግ ችሏል፡፡

 

በመሠራት ላይ ያሉ፡-

  1. የሽያጭ አገልግሎት (ሐመር፣ ስምዓ ጽድቅ፣ አልባሳት…)የሚሰጥ ዌብ ሳይት መስራት (ለልማት ክፍል)

  2. ለአንድሮይድ እና ለዊንዶውስ ስልኮች የሚሆን አፕሊኬሽኖች (የቤተ ክርስቲያን ማውጫ፣ የቴሌቪዠን እና የዜና፣ የቅዱሳን መጻሕፍት፣ የአባላት መሰረታዊ መረጃ፣ ተዋሕዶ ሚድያ፣ ግጻዌ፣ ቀን መቁጠሪያ፣ ቀን መለወጫ፣ የእልቱን ምንባብ ማውጫ) መስራት።

  3.  ጉባኤ ቤት ወይም የዜማ ማጥኛ ዌብ ሳይት ማዘጋጀት

  4.  አባላት ስልጠና (Members training) እና የርቀት ትምህርት (Virtual campus) መስጫ ሶፍትዌር ወይም ዌብ ሳይት መሥራት 

  5. ሕፃናትን ማእከል ያደረገ ለትምህርት አገልግሎት የሚሆን ዌብ ሳይት መሥራት

  6. ክፍሉ የሚያስተዳድራቸውን ሰርቨሮች አቅም ማሻሻል፣ የሚያዙ ዳታዎች (data) በትክክል ግልባጭ (backup) እንዲኖራችው ማደረግ እና ችግር ሲኖር ማገገም የሚችሉብት ዘዴ (disaster recovery plan) ቀድሞ ማዝጋጀት

  7.  የቤተ ክርስትያን ትምህርት፣ መዝሙራት፣ ድራማዎች፣ እና ሌሎች ቪድዮዎች በቀላሉ የሚገኙበት (EOTC tube) ዌብ ማዘጋጀት

  8. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የ81ዱ (ሰማንያ አሐዱ) መጸሐፍ ቅዱስን በድምፅ (በንባብ) ማዘጋጀት

    የሚሉት ሥራዎች ይገኙበታል።

 

በአጠቃላይ ክፍሉ ከተቋቋመ ጀምሮ ያበረከታቸው አገልግሎቶች የሚያስመሰግኑ እና በ2004 በሚኒሶታ በተደረገው ጉባኤ ሽልማት ያገኘበት ሲሆን ቤተ ክርስቲያናችን እና ማኅበራችን በዚህ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ማግኘት የሚገባቸውን ስናነጻጽረው የተሰሩት ስራዎች አበረታች ጅምሮች እንጂ በቂ ናቸው ሊባሉ አይችሉም። ይህንን ትልቅ ክፍተት ለመሙላት ደግሞ ከማንም በላይ በዚህ በአሜሪካ የምትኖሩ በዚህ ሙያ የተካናችሁ ወንድሞች እና እህቶች ትልቅ የአገልግሎት እድል የበላይ ተቋዳሾች ናችሁ፣ ስለሆነም ከመቼውም በላይ በትጋት ይህንን አገልሎታችሁን በማጠናከር የታቀዱትን እና ከእቅድም በላይ ለመስራት እንድትበረቱ በእግዚአብሔር ስም እጠይቃለን።

 

እስከ አሁን በቤቱ የጠበቀን ለዚህ ትልቅ አገልግሎትም የጠራን የቅዱሳን አምላክ ብርታቱን ሰጥቶ ከዚህ ትልቅ በረከት እንድንሳተፍ ይርዳን።

 

ይቆየን!

 

ጥናትና ምርምር የጥናት ጉባኤው ሊያካሂድ ነው

 የካቲት 17 ቀን 2006 ዓ.ም.

በታመነ ተ/ዮሐንስ

 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና በፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል” በሚል ርእስ ጥናታዊ ጽሑፍ ሊያዘጋጅ ነው፡፡

እንደማእከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አበበ ገለጻ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቷን ሕልውና ከማስጠበቅ አልፋ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ይወጡ ዘንድ ባደረጉት ትግል የነበራትን ሚና ለማመላከት እንዲሁም ግንዛቤ ለማስጨበጥ ይረዳ ዘንድ ማእከሉ ይህንን የጥናት ጉባኤ አዘጋጅቷል፡፡ አያይዘውም የጥናት ጉባኤው በየዓመቱ የሚከበረውን የዓድዋ ድል ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለድሉ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ለማዘከር እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ የሀገራችንን ሉላዊነት ለማስጠበቅ የተጫወተችውን ሚና በዚህም ዘመን ትውልዱ ማንነቱን በመጠበቅ ዙሪያ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ሊኖረው እንደሚገባ ጥናቱ ያመላክታል ብለዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል ይህን መሰል ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተያያዥነት ባላቸው ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ እና ባሕላዊ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን በሚገኘውም የሥራ ውጤት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያደርጋል፡፡

የጥናት ጉባኤው የካቲት 22 ቀን 2006 ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጽ/ቤት ሕንጻ ላይ የሚከናወን ሲሆን፤ በዕለቱ ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሑራን እና ጥሪ የተደረገላቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡