desa 2006 01

የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ስለቤተክርስቲያን ዘላቂ ልማት ከበጎ አድራጊዎች ጋር ውይይት አደረገ፡፡

የካቲት 28 ቀን 2006 ዓ.ም. 

ወርቁ በላይሁን ደሴ ማእከል

የደሴ ማእከል ቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል “ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት በጋራ እንሥራ” በሚል መርህ ለሁለተኛ ጊዜ ከደሴ ከተማ በጎ አድራጊዎች ጋር የካቲት 23 ቀን 2006 ዓ.ም ውይይት አደረገ፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ desa 2006 01ጥሪ የተደረገላቸው በጎ አድራጊዎች የተገኙ ሲሆን፤ ለዘላቂ የቤተ ክርስቲያን ልማት መሠራት ስለሚገባቸው መሠረታዊ ጉዳዮች ውይይት ተደርጓል፡፡

በውይይቱም በስብከተ ወንጌል፣ በቅዱሳት መካናትና በአብነት ት/ቤቶች ዙሪያ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ወጥነት ባለው መልኩ የልማት ፕሮጀክቶችን መሥራት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት በማእከሉ ተቀርጸው የቀረቡ ፕሮጀክቶችንና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎችንም ለመሥራት የምዕመናንን ተሳትፎ ለማጠናከር ስድስት ኣባላት ያሉት አስተባባሪ ኮሚቴ በዕለቱ ተመርጧል፡፡

ኮሚቴውም ለቀረቡት ፕሮጀክቶች የአካውንት መክፈቻ የሚሆን ገንዘብ ለመሰብሰብ ጥረት ያደረገ ሲሆን፤ አስተዋጽዖን በተመለከተ እያንዳንዱ ተሳታፊ በተሰጠው የቃል ኪዳን ሰነድ ላይ ሞልተዋል፡፡ በየወሩ ድጋፍ ለሚያደርጉ በጎ አድራጊዎችም የተባባሪ አባልነት መታወቂያ እንዲዘጋጅ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የማእከሉ ሰብሳቢ ዶ/ር ዮሐንስ ደምሴ በዕለቱ የተገኙት ተሳታፊዎች በሥራ ቦታና በመኖሪያ አካባቢ የሚያውቋቸውን በውይይቱ ያልተገኙ ምዕመናንን በዚህ በጎ አገልግሎት እንዲሳተፉ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ ለመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ማእከሉ ያዘጋጀውን ዶክመንተሪ ፊልም የቀረበ ሲሆን፤ የወንጌል ትምህርት ተሰጥቷል፡፡