ማእከሉ ወደ ሲሌ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ፡፡

 

የካቲት 20 ቀን 2006 ዓ.ም.

ከአርባ ምንጭ ማእከል

በማኅበረ ቅዱሳን አርባ ምንጭ ማእከል መራሔ ፍኖት በሚል መሪ ቃል ለአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መጋቢት 21 ቀን 2006 ዓ.ም ወደ ሲሌ ደብረ ገነት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ጉዞ ያዘጋጀ መሆኑን ገለጸ፡፡

በማእከሉ የግቢ ጉባኤ ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊ የሆኑት አቶ ኃይለ ኢየሱስ እንግዳው እንዳስታወቁት ጉዞው የሚደረገው ተማሪዎች በክርስቲያናዊ ሕይወታቸው እንዲጠነክሩ፣ አርዓያነት ያለው ሕይወት እንዲኖራቸው፣ ወደ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት በመሄድ በረከት እንዲያገኙ፣ ዘመኑን መዋጀት የሚያስችላቸውን ዕውቀት ገንዘብ እንዲያደርጉ ለማገዝ ታስቦ የተዘጋጀና በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተመርኩዞ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ሲሆን በተጨማሪም ቅኔ፣ መዝሙር የሚቀርብበትም እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ማእከሉ ከዚህ በፊት ግቢ ጉባኤያትን ያሳተፈ የእግር ጉዞ በከተማው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሲያካሂድ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ኃይለ ኢየሱስ፤ ይህን ጉዞ ለየት የሚያደርገው ከአርባ ምንጭ ከተማ ውጭ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን የሚከናወን በመሆኑ ነው፣ ሲሉ ገልጸው፤ ተማረዎችም የጉዞው ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ ሓላፊው አሳስበዋል፡፡