የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ሥርጭት አንደኛ ዓመት ተከበረ

 

መጋቢት 2 ቀን 2006 ዓ.ም.

መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ

የማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ሥርጭት አንደኛ ዓመት በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ አርቲስቶች የማኅበሩ ደጋፊዎችና የማኅበሩ የሥራ አመራር አባላት በተገኙበት ተከበረ፡፡

በዕለቱ የቴሌቭዥን ሥርጭቱን አንደኛ ዓመት ለማክበር የተገኙትን ባለድርሻ አካላት “እንኳን ደኅና መጣችሁ” ያሉት የማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ እንደገለጹት “ማኅበረ ቅዱሳን ወንጌለ መንግሥትን ለዓለም ለማዳረስ በሚደረገው መንፈሳዊ አገልግሎት የኅትመት ውጤቶች ሲጠቀም መቆየቱን ገልጸው አሁንም በቴክኖሎጂው በመታገዝ በዓለም ሁሉ ከምንደርስበት መንገዶች አንዱ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩ መጀመር የምሥራች ሲሆን በእውቀት፣ በገንዘብ፣ በጉልበት ድጋፋችሁ ሁል ጊዜ የማይለየን ክቡራን እንግዶቻችን አሁንም ድጋፋችሁ እንዳይለየን በሚል ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ቃለ እግዚአብሔርን ለመመገብ የተገኙት መጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ እንዳስተማሩትም “ስብከት የአፋልጉኝ ማስታወቂያ ነው፡፡ የጠፋው በኃጢአት ምክንያት የኮበለለ የሰው ልጅ ሲሆን የሚጠራው፣ የሚያፈላልገው እግዚአብሔር ነው፡፡ ከማፈላለጊያ መንገዶች አንዱ ደግሞ ይህ የቴሌቪዥን አገልግሎት በመሆኑ አገልግሎቱን ልንረዳ ይገባል፡፡ በማለት አስተምረዋል፡፡

በዕለቱ መርሐ ግብር መሠረት የበገና መዝሙር በመ/ር አቤል ሙሉጌታ፣ መነባንብ በአርቲስት ንብረት ገላው፣ በቴሌቪዥን ክፍል ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ በዶ/ር መርሻ አለኸኝ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ለታዳሚው ቁጭትን የፈጠረና በተለይ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ቃለ እግዚአብሔርን በተለያዩ ቋንቋዎች ማዳረስ ሲቻል አለማዳረሳችን ግንዛቤ አግኝቷል፡፡

ከጥናታዊ ጽሑፉ በመነሣት የአኀት አብያተ ክርስቲያናት (ኮፕት) ጥቂት ምእመናን ይዘው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ሲኖራቸው፤ የኛ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ምእመናን እያለን ይበልጥ መሥራት ሲገባን አለመሥራታችን፣ በሀገራችን የሌላ እምነት ተከታዮች የ24 ሰዓት ሬድዮና ቴሌቪዥን ሲኖራቸው እኛ ግን በሳምንት ከሦስት ሰዓት ላልበለጠ ጊዜ መኖሩ በንጽጽር ቀርቦ የጉባኤው ተሳተፊ ለቀጣዩ ከማኅበሩ ጋር በመተባበር የበኩላቸውን እንደሚያበረከረቱ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም የማኅበሩ በሳምንት የአንድ ሰዓት የቴሌቪዥን ሥርጭት ወደ 24 ሰዓት እንዲያድግ በቅርቡ የገቢ ማሰባሰቢያ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተጋባዥ እንግዶች አበክረው አሳስበዋል፡፡ የማኅበሩን የቴሌቪዥን መርሐ ግብር በ EBS TV እሑድ ከ5፡00-600 ሰዓት የሚተላለፍ ሲሆን በድጋሚ ሐሙስ ጠዋት 1፡00-2፡00 ሰዓት ይተላለፋል፡፡ በተጨማሪም www.eotc.tv ይከታተሉ፡፡