KidaneMihret

ኪዳነ ምሕረት

የካቲት 15 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኀይለ ኢየሱስ ቢያ

KidaneMihret

“ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ” 88፥3 በማለት በነቢዩ ቅዱስ ዳዊት አድሮ ራሱ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አበው ነቢያት ጻድቃን ቅዱሳንና ሰማዕታት ጋር ቃል ኪዳን እንደ ገባና እንደሚገባ ተናግሯል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እግዝአብሔር እንደሚጠራ እንደሚያከብር እንደሚቀድስ ቃል ኪዳን እንደሚሰጥ ነግሮናል፡፡ /እንግዲህ እርሱ ራሱ ከጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎት የሚቃወማቸው ማን ነው? ብሏል፡፡ ሮሜ.8፥33

 

ቅዱስ ዳዊትም “ነኪር ነገሩ በእንቲአኪ ሀገረ እግዚአብሔር የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ ስለ አንቺ የተነገረው ነገር ድንቅ ነውብሏል፡፡ መዝ.86፥3 ስለዚህ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የገባው ቃል ኪዳን ከቅዱሳን ቃል ኪዳን ሁሉ ልዩ ነው፡፡

 

ቃል ኪዳን መሐላ የሚለው መዝገበ ቃላዊ ፍች እንደሚከተለው ተገልጿል፡-

ኪዳነ ምሕረት የካቲት 16 ቀን እመቤታችን ከልጇ የምሕረት ቃል ኪዳን /ውል / ስምምነት፣ የተቀበለችበት ዕለት የበዓል ስም ነው፡፡ ኪዳን ማለት ኪዳን፡- ውል፣ መሐላ፣ ቃል ኪዳን፣ የውል ቃል ማለት ነው፡፡ ተካየደ፡- ተዋዋለ፣ ቃል ኪዳን ተጋባ፣ ተማማለ ማለት ነው፡፡ ዘዳ.29፥1፣ ኤር.31፥31-33፣ መዝ.88፥3 በሌላ በኩል ኪዳን፡- የጸሎት ስም ነው፡፡ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ከማረጉ በፊት ለሐዋርያት ያስተማራቸው ጸሎት “ኪዳን” ይባላል፡፡

 

በየዓመቱ የካቲት 16 ቀን የምናከብረው በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በጎልጎታ በልጇ በመቃብር ላይ ሁና ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ “ኦ ወልድየ ወፍቁርየ እስእለከ በእንተ ዘተሰባእከ እምኔየ ወበማሕፀንየ ዘጸረተከ፤ ልጄ ወዳጃ ሆይ ከሥጋዩ ሥጋ ከነፍሴ ነፍስ ነሥተህ ሰው በመሆንህ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በቻለችህ ማኅፀኔ ከአንተ ጋር ሀገር ለሀገር ስለመሰደዴ መጥተህ ልመናዬን ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” እያለች ስትጸልይ÷ ጌታ እልፍ አእላፍ መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “ሰላም ለኪ ማርያም እምየ፤ እናቴ ማርያም ሰላም ላንቺ ይሁን እንዳደረግልሽ የምትለምኚኝ ምንድን ነው?” አላት፡፡

 

  • ኩሉ ዘጸውአ ስምዬ፤ በስሜ የተማጸነውን

  • ወዘገብረ ተዝካርየ፤ መታሰቢያዬን ያደረገውን

  • ስለስሜ ለችግረኛ የሚራራውን

  • በስሜ ቤተ ክርስቲያን ያነጸውን

  • በስሜ ለቤተ ክርስቲያን ዕጣንና ዘይት መብአ የሰጠውን

  • ከሃይማኖት ፍቅር ጽናት፣ ልጁን በስሜ የጠራውን ሁሉ ማርልኝ ከሞተ ነፍስ አድንልኝ” አለችው፡፡

 

ጌታም “ይህን ሁሉ እንዳደርግልሽ መሐልኩ ለኪ በርእስየ ወበአቡየ ወበመንፈስ ቅዱስ ሕያው” ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላት ዐርጓል፡፡

 

ከዚህ የተነሣ ነው ያዕቆብ ዘሥሩግ በቅዳሴው “ዳግመኛም በእናትህ በማርያም ተማፅነናል÷ ይህችውም አንተን በመውለድ እመቤታችንና የባሕርያችን መመኪያ ናት÷ አንተ መታሰቢያሽን ያደረገ÷ ስምሽንም የጠራ ÷የዘላለም ድኅነትን ይድናል ብለሃታልና፡፡” ያለው (ገጽ 242)

 

በዚህ ዕለት የሚታሰብ በተአምረ ማርያም መጽሐፍ….. የተገለጸ ሁለት ተአምር አለ፡፡

  1. ስምዖን የሚባል እንግዳ ተቀባይ ደግ ሰው ነበር፡፡ ሰይጣን ለምቀኝነት አያፍርምና ከዕለታት አንድ ቀን በእንግድነት እቤቱ ገብቶ “ልጅህን አርደህ ካላበላኸኝ÷ ሌላ ምግብ አልበላም” አለው፡፡ በዚህ ጊዜ ስምዖን ወደ እርሱ የመጣውን “የእግዚአብሔር እንግዳ” ላለማሳዘን አወጣ አወረደ፤ በዚያውም ላይ “አብርሃም ልጁን ሰውቶ ነው፡ የእግዚአብሔር ሰው የተባለው፣” በማለት÷ ልጁን አርዶ ሰጠው፡፡ “በግድ ቅመስልኝ” አለው፡፡ ስምዖን አርዶ የቀቀለውን የልጁን ሥጋ በቀምሰ ጊዜ ተዋሕዶት፤ ቤተሰቦቹን ጎረቤቶቹን መንገደኛውን ሁሉ ይበላ ጀመር፡፡ በዚህም 78 ሰው በልቶ አንድ በቁስል የተመታ ሰው ሊበላው ሲል፡- “በሥላሴ ስም፣ በቅዱስ ሚካኤል ስም፣ በቅዱስ ገብርኤል ስም ውኃ አጠጣኝ” ብሎ ለመነው፤ ዝም አለው፡፡ በመጨረሻም “በድንግል ማርያም ስም” አለው፡፡የእመቤታችንን ስም በሰማ ጊዜ በላኤሰብእ ወደ ልቡናው ተመልሶ “እስኪ ድገመው” አለው፤ “ስለ ድንግል ማርያም ውኃ አጠጣኝ” ብሎ ለመነው፡፡ ያን ጊዜ “ይህችስ እንደምታስምር በልጅነቴ ሰምቻለሁ” ብሎ ጥቂት ውኃ ሰጠው፣ ጉሮሮ እንኳን ሳይርስለት ጨረስህብኝ ብሎ ነጥቆት ሄደ፡፡ “ገበሬው በላኤ ሰብ የምትባል አንተነህ?” አለው፡፡ ያን ጊዜ “ለካስ ሰው ሁሉ አውቆብኛል” ብሎ ዋሻ ገብቶ በመጸጸት በዚያው ሞተ፡፡ ነፍሱን መላእክተ ጽልመት መጥተው ሲወስዷት እመቤታችን “መሐር ሊተ ዛተ ነፍሰ ኦ ወልድየ ዘይትሔሰው ቃልከ፤ ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ ቃልህ ይትበላልን” አለችው፡፡ “ሰባ ስምንት ነፍስ ያጠፋ÷ ፈጣሪውን የካደ ይማራልን?” አላት፤ እመቤታችንም “በስሜ የተጠማውን ውኃ አጥጥቶ የለምን?” ብላ አስምራዋለች፡፡ ነፍሱንም መላእክተ ብርሃን መጥተው ወደ ገነት አስገብተዋታል፡፡

  2. ከክርስቲያን ወገን የሆነ ሀብት አግኝቶ ያጣ አንድ ሰው ነበር፡፡ “ከብሬ በኖርሁበት ሀገር÷ተዋርጄ አልኖርም” ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ሲሄድ፣ ሰይጣን ያዘነ መስሎ÷ ደንጊያውን፡- በምትሐት ወርቅ አስመስሎ÷ “አብን ወልድን መንፈስ ቅዱስን፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታትን፣ መላእክትን ካድልኝና ይህን እሰጥሃለሁ” አለው፡፡ ካደለትና ተቀብሎ ዞር ሲል፤ “ምእመናን የሚመኩባት ድንግል ማርያም `የአምላክ እናት አይደለችም` ብለህ ካድልኝ” አለው፡፡ “እሷንስ አልክድም” አለው፡፡ በደንጊያ ቀጥቅጦ ገደለው፡፡ መላእክተ ጽልመት ነፍሱን እጅ አደረጉ፤ መላእክተ ብርሃንም አብረው ቀረቡ እመቤታችንም ቀርባ፤ “ልጄ ይህችን ነፍስ ማርልኝ” አለችው፡፡ “ከልብኑ ይታመሐር እምየ፤ እናቴ ውሻ ይማራልን” አላት፡፡ “ስምሽን የጠራውን መታሰቢያሽን ያደረገውን እምርልሻለሁ ያልኸው ቃል ይታበላልን” አለችው “ምሬልሻለሁ” አላት፡፡

 

እግዚአብሔር ከመረጥኳቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ ባለው መሠረት ከቅዱሳን ጋር ያደረጋቸው ቃል ኪዳኖች ብዙዎች ናቸው (መዝ.88፥3)፡፡ ከእነዚህም መካከል አንዱ የእመቤታችን ኪዳን/አማላጅነት/ ነው፡፡

 

አማላጅነትዋ

እንደሚታወቀው ማማለድ ማለት ስለሌላው መጸለይ፣ መለመን፣ የደረሰውን ችግር እንዲወገድ ማስደረግ፣ ማስማር ማለት ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከእግዚአብሔር በታች ከቅዱሳን ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያለችና የከበረች ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት የማማለድ ሥልጣን “ሰአሊ ለነ ቅድስት፤ ቅድስት ሆይ ለምኚልን” እያሉ ለሚለምኑአት ሁሉ ከእግዚአብሔር እያማለደችና እየለመነች ምሕረትን እንደምታሰጥ ቀናውንና የተመሰገነውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሁሉ ያምናሉ፡፡ ምክንያቱም ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር እናትና አገልጋይ በመሆንዋ ከሁሉም ቅዱሳን በበለጠ ለእግዚአብሔር ቅርብ ናትና፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድም ሆነ በሰው ዘንድ ባለሟልነት ወይም ቅርብ መሆን ጉዳይን ያስፈጽማል፡፡

 

ለምሳሌ

  • መልአኩ ቅዱስ ገብርአል በእግዚአብሔር ፊት የሚቆም ባለሟል በመሆኑ የድኅነትን ምሥጢር አብሣሪ ሆኗል፡፡ ሉቃ.1፥19፣ 1፥26

  • አስቴር የንጉሡ አርጤክስስ ሚስት በመሆኗ በወገኖቿ አይሁድ የታወጀውን የሞት አዋጅ አስለውጣለች፡፡ መጽሐፈ አስቴር.3፥10

  • ነቢዩ ሙሴ በእግዚአብሔር ፊት ባለሟል በመሆኑ ለእስራኤላውያን ምሕረት አሰጠ፡፡ ዘጸ.32፥14 “ይህንን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው ያለዚያ ግን እኔን ከጻፈከው መጽሐፍህ እባክህ ደምስሰኝ አለው እግዚአብሔርም ራራላቸው፡፡”

  • የቅድስት ድንግል ማርያምም አማላጅነት እንደ ፀሐይ የበራ ሐቅ ነው፡፡ ይህንን እውነት ቅዱስ ያሬድ ሲመሰክር “ወታስተሠርዪ ኀጢአተ ሕዝብኪ ተበውሀ ለኪ እም አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ወከመ ትኩኒ ተንከተመ ለውሉደ ሰብእ ለሕይወት ዘለዓለም” ማለት “ለሕዝብሽ ለወገኖችሽ የኃጢአት ይቅርታን ታሰጪ ዘንድ ዘለዓለማዊ ሕይወትንም ለሚወርሱ ሁሉ መሸጋገሪያ ድልድይ ትሆኚ ዘንድ ከአብ ከወልድ ከመንፈስ ቅዱስ÷ከአንድ አምላክ ሥልጣን አግኝተሻል በማለት አመስግኗታል፡፡” /አንቀጸ ብርሃን ተመልከት/

 

በአባ ጽጌ ድንግልም በማኅሌተ ጽጌው “ሶበሰ ኪዳንኪ ምክንያተ ድኂን ኢሀሎ ፈለገ እሳት ወደይን እም አሰጠመ ኩሎ፤የድኅነት ምክንያት ቃል ኪዳንሽ ባይኖር ኖሮ የጥፋት እሳት ፤መርገም /ኀጢአት/ ባጠፋን ነበር” ብሏል፡፡

 

በሥርዓተ ቅደሴአችንም

  • ድኅነትን የምንለምንሽ ክብርን የተመላሽ ቅድስት ሆይ ደስ ይበልሽ

  • ሁል ጊዜ ድንግል የምትሆኚ አምላክን የወለድነሽ የክርስቶስ እናት ሆይ ኀጢአታችንን ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ልጅሽ ወደ ወዳጅሽ ወደ ላይ ጸሎታችንን አሰርጊ፣

  • በእውነት የጽድቅ ብርሃን የሚሆን አምላካችንን ክርስቶስን የወለድሽልን ንጽሕት ሆይ ደስ ይበልሽ፣

  • ንጽሕት ድንግል ሆይ ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግ ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሠርይልን ዘንድ ወደ ጌታችን ለምኚልን፡፡

  • በእውነት ለሰው ወገን አማላጅ የምትሆኝ አምላክን የወለድሽ ንጽሕት ቅድስት ድንግል ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ፡፡

  • የኀጢአታችንን ሥርየት ይሰጠን በልጅሽ በክርስቶስ ፊት ለምኝልን፣

  • በእውነት ንግሥት የምትሆኝ ንጽሕት ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ

  • የባሕርያችን መመኪያ ሆይ ደስ ይበልሽ

  • አምላካችን አማኑኤልን የወለድሽልን ሆይ ደስ ይበልሽ

  • በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት እውነተኛ አስታራቂ ሆነሽ ታስቢን ዘንድ እንለምንሻለን፡፡

  • ለነፍሳችን ይቅርታን ያደርግልን ዘንድ ኀጢአታችንንም ያስተሰርይልን ዘንድ” በማለት እንማጸናታለን፡፡

አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው

  • ጥፋትን ያይደለ ይቅርታን አሳስቢ

  • ማዓትን ያይደለ ምሕረትን አሳስቢ

  • ለጻድቃን ያይደለ ለኀጥአን አሳስቢ

  • ለንጹሐን ያይደለ ለተዳደፉት አሶስቢ ብሏል፡፡ ቁ.165-171

 

የእመቤታችን ክብር ከቅዱሳን ክብር ሁሉ የተለየ ነው፤ ይህም እንደምን ነው ቢሉ

  • ለአምላክ እናትነት የተመረጠች ልዩ እናት በመሆኗ ሉቃ.1፥26

  • አምላክ ከሥጋዬ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ ከእርሷ በመወለድ

  • ከመለለዷ በፊት በወለደች ጊዜ ከወለደች በኋላ ምን ጊዜም ድንግል በመሆኗ ኢሳ.7፥14

  • በሁለቱም ወገን /በአሳብም በገቢርም/ ድንግል በክልኤ በመሆኗ

  • አማላጅነቷ የወዳጅነት ሳይነሆን የእናትነት በመሆኑ ዮሐ.2፥5

  • ዓለም ይድን ዘንድ የድኅነት ምክንያት አድርጎ አምላክ የመረጣት ስለሆነ የእመቤታችን ክብር /ቃል ኪዳን/ ከቅዱሳን ክብር ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊትም በመዝሙሩ

“እግዚአብሔር ጽዮንን መርጧታልና ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወዷታልና ይህች ለዘለዓለም ማረሪያዬ ናት መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ፡፡” በማለት ነግሮናል፡፡ እግዚአብሔር የመረጠውንና የከበረውን መቃወም እንደሣይቻ ሐዋርያውቅ ቅዱስ ጳውሎስም “እንግዲህ እርሱ ራሱ ከጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወመቸው ማን ነው” ብሏል፡፡ ስለዚህ ብዙ ከንቱ አሳቦችን ትተን እንደበላኤሰብ በቃል ኪዳኗ ተጠቅመን ንስሐ ገብተን ቅዲስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ተቀበልን የስሙ ቀዳሽ የመንግሥቱ ወራሽ ለመሆን ያብቃን፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ተራደኢነት አይለየን፡፡

ዋቢ መጻሕፍት

  • ተአምረ ማርያም

  • ስንክሳር

  • መዝገበ ታሪክ

  • ክብረ ቅዱሳን

  • አማርኛ መዝገበ ቃላት

መመለስ /ክፍል ሁለት/

የካቲት  15 ቀን  2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ዝምታቸው አስፈራኝ፡፡ “እባክዎ አባቴ ይርዱኝ” አልኩ የሰፈነውን ጸጥታ ሰብሬ፡፡

ዐይኖቻቸውን ከመስቀላቸው ላይ ሳይነቅሉ ‹‹ልጄ ነገ ከእኔ ስላለመኮብለልህ ምን ማረጋገጫ አለኝ?” ስጋታቸውን ገለጹ፡፡

“አመጣጤ የመጨረሻዬ ይሆን ዘንድ ነው፡፡ ውስጤ ተሰብሯል፡፡ ታከተኝ አባቴ!” የተቋረጠው የዕንባ ጎተራዬን ነካካሁት፡፡ ይፈልቅ ጀመር፡፡

ለመወሰን ተቸግረው በትካዜ ከያዙት የእጅ መስቀላቸው ጋር የሚሟገቱ ይመስል እያገላበጡት ዝምታን መረጡ፡፡

እኔ ደግሞ ውሳኔያቸው ናፈቀኝ፡፡ መልስ እሰኪሰጡኝ ድረስ እኔም በለቅሶና በዝምታ አገዝኳቸው፡፡

“አንድ ነገር ታደርጋለህ፡፡” ቀና ብለው እንኳን አላዩኝም፡፡ ዐይኖቻቸውን መስቀላቸው ላይ ተክለዋል፡፡

“ከቃልዎ አልወጣም – የፈለጉትን ይዘዙኝ፡፡”

 

“በጥሞና እንድታደምጠኝ እፈልጋለሁ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዶግማዋንና ቀኖናዋን አገልጋዮች ካህናትም ሆንን ምዕመናን የመጠበቅ ግዴታ አለብን፡፡ አበ ነፍስን በሚመለከት ቤተክርስቲያናችን ስርዓት ሰርታለች፡፡ በዚህም መሰረት አንድ ምእመን በቅድሚያ ንስሐ ለመግባት ሲወስን በጾም ፤ በጸሎት ፤ በስግደትና በጎ ምግባራትን በመስራት ራሱን ማረቅ አለበት፡፡ ስለኃጢአቱ የሚጸጸት፤ ዳግም ያንን ኃጢአት እንደማይሰራ የቆረጠ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ንስሐ አባት ሲመርጥም በጸሎት በመታገዝ እግዚአብሔር መልካም አባት እንዲሰጠው መለመን አለበት፡፡ የንስሐ አባት ከያዘ በኋላ ሌላ ለመቀየር መነሳሳት አይቻልም፡፡ መቀየር ካለበትም በቂ ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ አበ ነፍሱ በሞት የተለዩ ከሆነ ፤   የሐይማኖት ህጸጽ ካለባቸው ፤  የአካባቢ ርቀት በየጊዜው እንዳይገኛኑ ከገደባቸው፤ የሥነ ምግባር ችግር ካለባቸው፤ እንዲሁም ሌሎች መግባባት የማያስችሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ አበ ነፍስ መቀየር ይቻላል፡፡ ለመቀየር ሲታሰብም ከአበ ነፍሱ ጋር ተነጋግሮና ተሰነባብቶ ሊሆን ይገባል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች ውጪ አበ ነፍስን መቀየር አይቻልም፡፡ አሁንም የተጓዝክበት መንገድ ትክክል ባለመሆኑ ሁሉንም አባቶች ይቅርታ ጠይቀህ፤ ቀኖና ተቀብለህ ስታጠናቅቅ ሊያሰናብቱህ ይገባል፡፡ በመካከላችሁ ያለውን አለመግባባት በመፍታት ከተግባባችሁ ግን ከአንዳቸው ጋር ትቀጥላለህ፡፡ አበ ነፍስ መቀያየር መፍትሔ አይሆንህም፡፡  ካልተሳካልህ ብቻ ነው አሰናብተውህ ወደ እኔ የምትመጣው፡፡” አሉኝ በተረጋጋና  አነጋገር፡፡

 

በድንጋጤ ደነዘዝኩኝ፡፡ ፍጹም ያልጠበቅሁት ውሳኔ፡፡ “እንዴት እችላለሁ አባቴ?” አልኩኝ  እየተርበተበትኩ፡፡

“በትክክል የቤተክርስቲያን ልጅ ነኝ ብለህ የምታምን ከሆነ ሥርአቷንም የመጠበቅ ግዴታ አለብህ፡፡” አሉኝ ኮስተር ብለው፡፡

 

አቋማቸው የሚወላውል አልነበረም፡፡ ትክክል እንደሆኑ ውስጤ አምኖበታል፡፡ ነገር ግን አሻፈረኝ ብዬ ከኮበለልኩባቸው አባቶች እግር ስር ወድቄ ይቅርታ መጠየቁ ተራራ የመውጣት ያህል ከብዶ ታየኝ፡፡

 

ጭንቅላቴን እያሻሹ “አይዞህ፡፡ ክርስትና የሚኖሩት እንጂ በአቋራጭ ለክብር የሚበቁበት መድረክ አይደለም፡፡ በማስተዋል መጓዝ ይገባሃል፡፡” ብለው አቡነ ዘበሰማያት ደግመው፤ በእግዚአብሔር ይፍታህ ደምድመው ተሰናብተውኝ ከአጠገቤ ሔዱ፡፡

 

ተንበርክከኬ የቻልኩትን ያህል አነባሁ፡፡ ትኩስ የሚያቃጥል ዕንባ ፈሰሰኝ፡፡ መረጋጋት ተሳነኝ፡፡፡ለረጅም ደቂቃዎች እንደተንበረከክሁ ቆየሁ፡፡

 

ጉዞ ወደ መጀመሪያው አበ ነፍሴ . . . ፡፡

 

ለሦስት ቀናት ያህል ከራሴ ጋር ስሟገት ቆይቼ በሌሊት አዲስ አበባ ወደሚገኘው ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አመራሁ፡፡ ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብቼ የኪዳን ጸሎት እስከሚጀመር ድረስ የግል ጸሎቴን አደረስኩ፡፡

 

የኪዳን ጸሎት እየደረሰ ሳለ እግረ መንገዴን የንስሐ አባቴን ፍለጋ ዐይኖቼን አንከራተትኩ፡፡ አልነበሩም፡፡ ከኪዳን ጸሎት በኋላ በየመጠለያው ፈለግኋቸው፡፡ የሉም፡፡

 

ወደ አንድ አባት ጠጋ ብዬ “ይቅርታ አባቴ መምሬ ወልደ ገብርኤልን ፈልጌ ነበር፡፡ የት አገኛቸው ይሆን?” አልኳቸው፡፡

በደንብ ካስተዋሉኝ በኋላ “መምሬ ወልደ ገብርኤል የሚባሉ እዚህ የሉም፡፡” አሉኝ፡:

“ተቀይረው ይሆን?” ጥርጣሬዬን ገለጽኩላቸው፡፡

“አልሰማህም እንዴ? እሳቸው እኮ ካረፉ አንድ ዓመት ሆኗቸዋል፡፡”

አፌ ተሳሰረ፡፡ ድንጋጤ ወረረኝ እኔ የገደልኳቸው ያህል ተሰማኝ፡፡

“እሰከ ዛሬ እንዴት አላወቅህም?”

“አላወቅሁም አባቴ፡፡ በጣም ያሳዝናል፡፡” አልኩኝ ባደረግሁት አሳፋሪ ተግባር በመጸጸት፡፡ ራሴን እየወቀስኩ ካህኑን አመስግኜ ከግቢው ወጣሁ፡፡

 

ሁለተኛውን አበ ነፍሴን ለማግኘት ጥረት አደረግሁ፡፡ የንስሐ ልጆቻቸውን ለሚቀርቧቸውና ለሚያምኗቸው አባቶች ሰጥተው ወደ አውሮፓ መጓዛቸውን አረጋገጥኩ፡፡

 

ሦስተኛው አበ ነፍሴን ፍለጋ ቀጠልኩ . . .፡፡

 

ተሳካልኝ፡፡ የፈጸምኩትን ድርጊት በመጸጸት ነገርኳቸው፡፡ በተፈጥሮ ቁጡና በክርስትና ሕይወት ወለም ዘለም ማለት አያስፈልግም የሚል አቋም ስላላቸው ለመጥፋቴ ምክንያት እንደሆኑኝ ከመንገር ወደ ኋላ አላልኩም፡፡

 

“ልጄ ፈተና ሆንኩብህ? በመጥፋትህ በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ተመልሰህ በመምጣትህ ደስ ብሎኛል፡፡” በማለት በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ ቀጥለውም ”መቆጣቴ ለክፋት ሳይሆን ክርስትና በዋዛ ፈዛዛ የሚኖሩት ባለመሆኑና መንፈሳዊ ጥንካሬን የሚጠይቅ፤ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚያስፈልግ ስለማምን ልጆቼን ለማጠንከር ነው፡፡ ክርስትና እንደ ወርቅ ተፈትኖ ነጥሮ መውጣትን ይፈልጋልና፡፡ ስለዚህ ልጄ አትቀየመኝ፡፡” በማለት እንድረጋጋ መንገዶችን አመቻቹልኝ፡፡ ቁጡነታቸው ስለሚያስፈራ እንዴት አድርጌ እፊታቸው እቆማለሁ? እያልኩ ነበር ሳስብ የነበረው፡፡ ራሳቸውን መውቀስ ሲጀምሩ ተረጋገሁ፡፡

 

አጠገባቸው አስቀምጠው ጭንቅላቴን እያሻሹ “አየህ ልጄ! – የክርስትና ጉዞ እስከ ቀራንዮ ድረስ መሆኑን አትዘንጋ፡፡ጉዞው ከባድና እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ ተሸክመኸው የምትጓዘው መስቀሉን ነው፡፡ መውደቅ ፤መነሳት፤ መገረፍ ፤በችንካር መቸንከር ሕይወትንም ለእግዚአብሔር አሳልፎ እሰከ መስጠት ይደርሳል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአዳምንና የእኛን ልጆቹን በደል ይሽር ዘንድ፤ ከዲያቢሎስ ቁራኝነት ነጻ ያወጣን ዘንድ አምላክ ሲሆን እንደኛ ስጋን ለበሰ፡፡ በቀራንዮ መስቀል ላይ የነገሠውን አምላካችንን አስብ፡፡ የጀመርከውን የቀራንዮ ጉዞ እንደ ሎጥ ሚስት ወይም እንደ ዴማስ ያለፈውን የኃጢአት ጉዞህን ለመመልከት ወደ ኋላ የምትዞርበት ሳይሆን ፊት ለፊት የተሰቀለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማየት ፤ በመስቀሉ ስር የተገኙትን እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያምንና ቅዱስ ዮሐንስን ትመለከት ዘንድ ነው፡፡ በርታ፡፡” አሉኝ በፍቅር እየተመለከቱኝ፡፡

 

የሚናገሩት ቃለ እግዚአብሔር ማር ማር እስኪለኝ ጣፈጠኝ፡፡

 

የእግዚአብሔር ቃል ምን ይላል መሰለህ? “የቀድሞውንስ ያለ ማወቅ ዘመን እግዚአብሔር አሳልፎታል፡፡ ዛሬ ግን በመላው ዓለም ንስሐ እንዲገቡ ሰውን ሁሉ አዝዟል፡፡” በማለት በሐዋ. ሥራ. ምዕ.17፡30 ተጽፏል፡፡ ያለፈውን የኃጢአት ሥራዎችህን ተጠይፈህና ጥለህ በእግዚአብሔር እቅፍ ስር ትሆን ዘንድ መምረጥህ መልካም አደረግህ፡፡ ወደፊት ደግሞ ብዙ ይጠብቅሃል፡፡” አሉኝ በጥልቅ ትኩረት እየተመለከቱኝ፡፡

 

“አንድን የኃጢአት ግብር ከመፈጸሜ በፊት ላለመስራት እታገላለሁ፡፡ ነገር ግን ሰርቼው እገኛለሁ፡፡ ለራሴ ውሳኔዎች ውስጤን ማሰልጠን ፤ ማስጨከን ተሳነኝ፡፡” አልኳቸው በተሰበረ ልብ፡፡

 

“እግዚአብሔር የተናገረውን ቃል አያስቀርም፤ ይቀራል ብለው የሚናገሩ አሉና፤ ነገር ግን ስለ እነርሱ ይታገሳል፡፡ ማንም ይጠፋ ዘንድ አይሻምና ንስሐ ይገቡ ዘንድ ለሰው ሁሉ ዕድሜን ይሰጣል እንጂ፡፡ በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በ2ኛ ጴጥ.3፡9 ላይ ገልጾታል፡፡ እግዚአብሔር ይመጣል በፊቱም እንቆማለን፡፡ መልሳችን ምን ይሆን? ማሰብ ያለብን ይህንን ነው፡፡ ንስሐ ለመግባት መወሰንህ መንፈሳዊ ጀግንነትህን ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ያለውን አያስቀርምና፡፡ በኋላ ከመጠየቅ ለመዳን ዛሬ ራስን ከኃጢአት በማራቅ ንስሐ መግባት ትክክለኛ መፍትሔ ነው፡፡” በማለት ሕሊናን ሰርስረው የሚገቡ የተመረጡ ቃላት በልቦናዬ ውስጥ አፈሰሱት፡፡ መልስ አልነበረኝም፡፡ ዝምታን መረጥኩ፡፡

 

“አሁን ውሳኔህን አሳውቀኝ፡፡ እግዚአብሔር ወደ እኔ መልሶ ያመጣህ ምክንያት ቢኖረው ነው፡፡ ይህንን ሃላፊነቴን እወጣ ዘንድ ግድ ይለኛል፡፡ አባት እሆንሀለሁ አንተም ልጄ ትሆናለህ” አሉኝ፡፡

 

“አመጣጤ እንዲያሰናብቱኝ ለመማጸን ነበር፡፡ ምን ያህል ስህተት ውስጥ እንደነበርኩ ተረድቻለሁ፡፡ ለዚህም የረዱኝን አባት ማመስገን አለብኝ፡፡ እግዚአብሔር ሰብሮኛል፡፡ ይጠግነኛልም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መኖርን እናፍቃለሁ፡፡ ይህ ባይሆን ተመልሼ እርስዎ ዘንድ አልመጣም ነበር፡፡ እንደወጣሁም እቀር ነበር፡፡ የመጣሁት ወስኜ ነው፡፡  እግዚአብሔር እርስዎን ሰጥቶኛልና እዳ እንዳልሆንብዎ እርዱኝ፡፡” አልኩ፡፡

 

“ቆም ብለህ ራስህን እንድታይ ያስፈልጋል፡፡ የሰራኸውን ኃጢአት እግዚአብሔርን በመፍራት ፤ በተሰበረ መንፈስ ውስጥ ሆነህ ልትናዘዝ ይገባሃል፡፡” አሉኝ ለመስማት ራሳቸውን እያዘጋጁ፡፡

 

ውስጤ የታጨቁትን የኃጢአት ኮተቶች ሁሉ አራገፍኩ፡፡

 

“ወደ ልቦናህ ተመልሰህ ከውስጥህ ያለውን ሁሉ አውጥተህ ዳግም ላትመለስበት ወስነሃልና የሚገባህን ቀኖና እሰጥሃለሁ፡፡ የሚሰጥህን ቀኖና በአግባበቡ በማስተዋልና በፍቅር ልትፈጽመው ይገባል፡፡ በጾም ፤ በጸሎት ፤በስግደትና በትሩፋት ከበረታህ የሚፈታተንህን ክፉ መንፈስ ማሸነፍ ትችላለህ፡፡” በማለት አባታዊ ምክራቸውን ከለገሱኝ በኋላ አስፈላጊ ነው ያሉትን ቀኖና ሰጡኝ፡፡ በአቡነ ዘበሰማያትና በእግዚአብሔር ይፍታህ ተደመደመ፡፡

 

“በየሳምንቱ ቅዳሜ ማታ እዚሁ እየተገናኘን በመንፈሳዊ ሕይወትህ ዙሪያ የሚገጥምህ ችግር ካለ ፤ እንዲሁም አስፈላጊ ያልካቸውን ጉዳዮች ልታማክረኝ ትችላለህ፡፡” በማለት ካበረታቱኝ በኋላ አሰናበቱኝ፡፡

 

ከንስሐ አባቴ እንደተለያየሁ ያመራሁት ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ነው፡፡ ባለውለታዬ የሆኑትን አባት ለማመስገን፡፡

 

ክርስቲያናዊ ሕይወቴን ለማስተካከልና ራሴን ለመግዛት እግዚአብሔርን እየለመንኩ፤ የንስሐ አባቴ ምክርና ድጋፍ ሳይለየኝ በተረጋጋ መንፈስ ለመኖር ጥረት በማድረግ ላይ ነኝ፡፡ ከምንም ነገር በላይ መንፈሳዊ ሕይወቴን ለሚያንጹ ተግባሮች ቅድሚያ ሰጠሁ፡፡ የአቅሜን ያህል በጾም፤ በስግደትና በጸሎት እየበረታሁ ነው፡፡ የንስሐ አባቴ በጥሩ ሁኔታ ቃለ እግዚአብሔር እየመገቡኝ ፤ ስደክም እያበረቱኝ መፈርጠጤን ትቼ ለሌሎች መካሪ ሆኛለሁ፡፡ ራስን መግዛት ተማርኩኝ፡፡ ያለፈው በኃጢአት የኖርኩበት ዘመን ዳግም ላይመለስ መንፈሳዊ ጋሻና ጦሬን አጥብቄ ይዣለሁ፡፡ ነገን ደግሞ እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ እኖራለሁ. . . ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ነቢዩ ዮናስ (ክፍል ሁለት) /ለሕፃናት/

የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም.

በወልደ ኢየሱስ /ቤካ ፋንታ/


እግዚአብሔር በጣም የሚወዳችሁ እናንተም እግዚአብሔርን በጣም የምትወዱት ሕፃናት እንደምን ሰነበታችሁልን?

 

ልጆችዬ ባለፈው በክፍል አንድ ጽሑፍ ስለ ደጉ ልጅ ስለ ዮናስ የተማርነውን ታስታውሳላችሁ? ዮናስ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙ ምክንያት በባሕር ላይ የሚሄድባት መርከብ ከባድ ችግር ደርሶባት ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ዮናስን ወደ ባሕር ውስጥ ሲጥሉት ንፋሱ ቆመ፡፡ መርከቧም በሰላም መሄድ ቻለች፡፡ ዮናስ ግን ወደ ስምጡ ባሕር እንደገባ አይተን ነበረ ያቆምነው፡፡ ዛሬ ካቆምንበት እንቀጥላለን፡፡

 

በመጀመሪያ ግን አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ፡-

  • ትልቁ በጣም ትልቁ በባሕር ውስጥ ከሚኖሩት ዓሣዎች ሁሉ የሚበልጠው ትልቁ ዓሣ ስሙ ምን ይባላል?

 

ደጉ ዮናስ የመርከቧ ሠራተኞች ከመርከቧ ላይ ወርውረው ወደ ሰፊው ባሕር ሲጥሉት ውኃው ውስጥ ሰመጠ፡፡ ከዚያ ወደ ስምጡ ባሕር ሲገባ በውኃ ስለተከበበ ዮናስ መተንፈስ አቃተው እግዚአብሔርም ለዮናስ አዘነለት እንዳይሞትም አስቦለት በባሕር ውስጥ ካሉት ዓሣዎች ሁሉ በጣም ትልቁን ዓሣ ላከለት፡፡ ትልቁ ዓሣ ስሙ ዓሣ አንበሪ ይባላል፡፡ እግዚአብሔርም ዓሣውን እንዲህ ብሎ አዘዘው “የምወደው ደጉ ዮናስ ውኃው እንዳያፍነውና እንዳይሞት ሂድና ዋጠው፡፡ በሆድህ ውስጥም ለሦስት ቀን እና ለሦስት ሌሊት ይኖራል፡፡” ሲለው ዓሣ አንብሪው ካለበት ቦታ ፈጥኖ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ወዶ ዮናስ ደረሰና ዋጠው፡፡ ከዚያ ወደ ስምጡ ባሕር ውስጥ እየዋኘ ሄደ፡፡

 

ልጆችዬ የሚገርማችሁ ነገር ትልቁ ዓሣ ዮናስን ሲውጠው ዮናስ አልሞተም፡፡ በዓሣው አፍ ገብቶ፣ በጉሮሮው አልፎ መጨረሻ ላይ ሆዱ ውስጥ ሲደርስ ዮናስ ደነገጠ፡፡ ወዲያውም ቆሞ ሲመለከት ያለው ትልቁ ዓሣ ሆድ ውስጥ ነው፡፡ በሆድ ውስጥ ሆኖ መተንፈስ ይችላል፣ ማየት ይችላል፣ መቆም ይችላል፣ መናገርም ይችላል፡፡

 

ዮናስ እግዚአብሔር ዓሣ አንበሪውን ልኮት ከሞት እንዳዳነው ሲያውቅ በዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሆኖ በጉልበቱ ተንበረከከና አንገቱን ቀና አድርጎ ወደ ላይ ወደ ሰማይ እያየ “እግዚአብሔር ሆይ ስለምንህ ጸሎቴን ሰምተህ ከሞት ስላዳንከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ በዚህ በዓሣ ውስጥም የዓሣው ጨጓራ እንዳይፈጨኝ ስለጠበቅኸኝ አመሰግንሃለሁ….” እያለ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ሙሉ ሳያቋርጥ ደስ ብሎት እግዚአብሔርን ሲያመሰግነው፣ እያጨበጨበ መዝሙር ሲዘምር እግዚአብሔር የዮናስን ጸሎት ሰማ፡፡ እግዚአብሔርም ዓሣውን “ልጄ ዮናስን ወደ ደረቅ መሬት ሄደህ ትፋው” ብሎ አዘዘው፡፡ ዓሣውም ዮናስን በባሕርl ዳር አጠገብ ወዳለች ነነዌ ወደምትባል ሀገር ተፋው፡፡

 

ዮናስ ከዓሣ አንበሪው ሆድ ውስጥ ሲወጣ ቶሎ ብሎ የሄደው እግዚአብሔር ወደ ላከው ሀገር ወደ ነነዌ ነው፡፡ ዮናስ ከባሕሩ ሲወጣ አንድ ነገርን ተምሮዋል፤ ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ብዚ ችግር እንደሚያመጣ አውቆዋል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር ወደ ላከው ነነዌ ወደምትባል ሀገር ሄደ፡፡ የነነዌ ሕዝብ ሆይ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎዋችኋል፡- ክፉ ሥራ መሥራት ትታችሁ ጥሩ ሥራ እኔ እግዚአብሔር የምወደውን መልካም ሥራ ካልሠራችሁ እቆጣችኋለሁ፡፡ ክፉ ሥራ መሥራት ካልተዋችሁ የምትኖሩበትን ከተማ እሳት ከሰማይ አውርጄ አቃጥላታለሁ፡፡” እያለ እየዞረ ለሕዝቡ ሁሉ ነገራቸው፡፡

 

የነነዌ ሕዝቦች የነቢዩ ዮናስን ቃል ሲሰሙ በጣም ደነገጡ፡፡ እግዚአብሔርም ከተማቸውን እንዳያጠፋባቸው እነርሱንም ይቅር እንዲላቸው ሁሉም ተሰበሰቡና ተማከሩ “እግዚአብሔር በክፉ ሥራችን ምክንያት ተቆጥቶ ሀገራችንን እንዳያጠፋ እንጹም፤ እግዚአብሔር እኮ እየጾምን ከለመንነው ይቅር ይለናል፡፡ ስለዚህ ከአሁን ሰዓት ጀምረን ሁላችንም ምግብ ሳንበላ ውኃ ሳንጠጣ ክፉ ሥራ መሥራት ትተን በጾም ለሦስት ቀን እግዚአብሔርን እንለምነው፡፡” ተባባሉና ሕፃናትም፣ ወጣቶችም፣ እናቶችም፣ አባቶችም፣ እንስሳቶችም ሁሉም “እግዚአብሔር ሆይ ይቅር በለን፣ ከአሁን በኋላ ክፉ ሥራ አንሠራም፣ ጥሩ ሥራ እየሠራን አንተ ያዘዝከንን እንፈጽማለን፡፡” እያሉ ለሦስት ቀን ውኃ ሳይጠጡ፣ ምግብ ሳይበሉ በጾም እግዚአብሔርን ለመኑት፡፡

 

እግዚአብሔርም ወደ ነነዌ ሕዝብ ሲመለከት ሁሉም እየጾሙ አየ፡፡ ሁሉም “ይቅር በለን” ይላሉ፡ የነነዌ ሕዝቦች ክፉ ሥራ መሥራት ትተው እየጾሙ እየጸለዩ ሲለምኑት እግዚአብሔር ከሰማይ ከተማዋን ሊያጠፋ እየፈጠነ የሚወርደውን እሳት እሳት እንዳይወርድባቸው ከለከለው እየወረደ የነበረውም እሳት ጠፋ፡፡

 

ልጆችዬ እግዚአብሔር የሚጾም ልጅን በጣም ነው የሚወደው፡፡ እግዚአብሔርን እየጾምን እየጸለይን ከለመነው በእኛ ላይ ክፉ ነገር አይመጣብንም፣ ቤተሰቦቻችንንም እግዚአብሔር ይጠብቅልናል፡፡ ጾመ ነነዌ የሚባለውን ለሦስት ቀን የሚጾመውን ጾም በሚመጣው ሰኞ ጀምረን እስከ ዕረቡ ለሦስት ቀን እንጾመዋለን፡፡ ታዲያ ልጆች ስንጾም ሳንዋሽ፣ ሳንሳደብ ክፉ ሥራ ሳንሠራ፣ ለእግዚአብሔርም ለቤተሰቦቻችንም እየታዘዝን መጾም ይኖርብናል፡፡ መልካም የጾም ቀናት ይሁንላችሁ፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ከነቢዩ ዮናስ በረከትን ያድለን፡፡ አሜን፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እሁድ ይጀምራል

የካቲት  13 ቀን 2005 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስ

በማኅበረ ቅዱሳን ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል እየተዘጋጀ የሚቀርበው የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እሑድ የካቲት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡30 – 4፡00 ሰዓት ድረስ በናይል ሳት ኢቢኤስ ላይስርጭቱን እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡

ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ የቴሌቪዥን ስርጭቱ እንደሚጀመር ብንዘግብም በኢቢኤስ የስርጭት መቋረጥ ምክንያት ሳይተላለፍ መቆየቱ ያታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት  በኢቢኤስ ላይ የተከሰቱት ችግሮች የተቀረፉ በመሆናቸው በየሳምንቱ እሁድ ከጠዋቱ 3፡30 – 4፡00 ሰዓት ፤ እንዲሁም በድጋሚ በየሳምንቱ ሐሙስ ከጠዋቱ 1፡00 – 1፡30 ሰዓት የሚተላለፍ መሆኑን የቴሌቪዥን ክፍሉ አስተባባሪ የሆኑት ዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡

በምእመናን በጉጉት ይጠበቅ የነበረው ይህ መርሐ ግብር በተደጋጋሚ በተከሰተው ችግር ምክንያት በመቋረጡ ዝግጅት ክፍሉ ይቅርታ እየጠየቀ ከእሑድ የካቲት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ መከታተል እንደሚችሉ አስታውቋል፡፡

DSC09260

የምርጫው ሂደት በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ሁሉም በጸሎት እንዲያስብ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ6ኛ ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለፓትርያርክነት እጩ ሆነው የሚቀርቡ ጳጳሳትን ለመምረጥ ካህናትና ምእመናን ጥቆማ እንዲያደርጉ ከየካቲት 1 – 8 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰጠው የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

አስመራጭ ኮሚቴው በአንድ ሳምንት ውስጥ አከናወንኳቸው ያላቸውን ሥራዎች ባቀረበበት በዚሁ መግለጫ በርካታ ምእመናን ለቤተ ክርስቲያኒቱ 6ኛ ፓትርያርክ ሊሆኑ ይገባቸዋል ያሉትን አባት በአካል በመቅረብ እንዲሁም በፋክስ መልእክት በመላክ ጥቆማ መስጠታቸውን ገልጧል፡፡ ከካህናትና ምእመናን የተገኘው ጥቆማም ለአስመራጭ ኮሚቴው በግብአትነት የሚያገለግል ሲሆን ከየካቲት 9 -14 ቀን 2005 ዓ.ም. በወጣው የፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ መሠረት አስመራጭ ኮሚቴው ለይቶ ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ እጩ ፓትርያርኮችን የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያቀርብ መግለጫው አመልክቷል፡፡ የምርጫው ሂደት በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ፤ ካህናትና ምእመናን እግዚአብሔርን በጸሎት እንዲጠይቁ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስመራጭ ኮሚቴው ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሾችንም ሰጥተዋል፡፡

ከጋዜጠኞች ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ምርጫው ከሌሎች ተጽእኖ ምን ያህል የፀዳ ነው? የሚለውን ለቀ ማዕምራን ፋንታሁን ሙጬ የአስመራጭ ኮሚቴው ጸሐፊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን አስመራጭ ኮሚቴው ከሌሎች አካላት ተጽእኖ የጸዳና ራሱን ችሎ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡  የአኀት ቤተ ክርስቲያንና የሲቪክ ማኅበራት ምርጫውን ለመታዘብ ይገኛሉ? የሚለውን ሲመልሱም ከአኀት ቤተ ክርስቲናት፤ ከአለም አብተ ክርስቲናት ምክር ቤት፤ ከአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ ከታዋቂ አገር ሽማግሌዎችና ከመንግስት አካላት በታዛቢነት እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

በስፋት ጥቆማ እየሰጡ የሚገኙት የአዲስ አበባ ካህናትና ምእመናን ናቸው፡፡ ሌሎቹ አህጉረ ስብከቶችስ? በሚል ለቀረበው ጥያቄም ሲመልሱ “በርቀት ምክንያት በአካል መቅረብ ያልቻሉ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. አስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ላይ ሁለት ፋክስ ቁጥሮችን ይፋ አድርጓል፡፡ ፋክሶቹም 24 ሰዓት በመስራት ከአውሮፓና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጥቆማዎችን እንደተቀበሉና በአካል ቀርበው ጥቆማቸውን የሚሰጡትንም በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ሞልተው በታሸገው የጥቆማ መስጫ ሳጥን ውስጥ እያስገቡ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡

በፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ ላይ እጩ የሚሆኑትን አባቶች ከተለዩ በኋላ ከምእመናን የሚቀርቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ለመቀበል የ15 ቀናት የጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን አስመራጭ ኮሚቴው የገለጸው በሦስት ቀናት ልዩነት ፓትርያርክ ሆነው የሚመረጡት አባት እንደሚታወቁ ነው፡፡ ይህ አካሔድ ከሕገ ደንቡ ጋር አይጋጭም? የሚለውንም ሲመልሱ “ከምርጫ ሕገ ደንቡ ጋር ተያዞ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጸድቆ ለአስመራጭ ኮሚቴው የተሰጠ ተጨማሪ ሕግ አለ፡፡ አስመራጭ ኮሚቴውን በሚያስመርጥበት ወቅት ኮሚቴው ሊሰሯቸው የሚገባውን ተግባራት ቋሚ ሲኖዶስ እየተከታተለ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንደሚችል የተገለጸበት ሕግ ነው፡፡ ይህንን ሕግ ተከትሎ የድርጊት መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ነው አስመራጭ ኮሚቴው ለቋሚ ሲኖዶስ ያቀረበው፡፡  ቋሚ ሲኖዶስ የቅዱስ ሲኖዶስም ምልዓተ ጉባኤ በሰጠው ሥልጣንና ውክልና መሠረት አስመራጭ ኮሚቴው ያቀረበውን የጊዜ ሰሌዳ ትክክል ነው ብሎ አጽድቆ ሰጥቶታል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ሕግ የማውጣትም ሆነ ሕግ የመለወጥ ስልጣን የለውም” በማለት የመለሱ ሲሆን ስለቀኑ ማጠር ሲያብራሩም ወደ አብይ ጾም የተቃረበ በመሆኑ ከዚያ በፊት ማጠናቀቅ እንደሚገባ ግንዛቤ ተወስዶ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም ከ53ቱም አህጉረ ስብከቶች ለመራጭነት ይገኛሉ ተብሎ ይፋ የተደረገው 800 መራጮች ብቻ ናቸው ፡፡ ነገር ግን ሲሰላ ከዚያ በላይ ስለሚሆኑ እንዴት ይታያል? በማለት ለቀረበው ጥያቄም በፓትርያርክ ምርጫው ላይ በመራጭነት የሚሳተፉ ሰዎች 800 ይሆናል የሚለውም እንደ መነሻ የተያዘ እንጂ የመጨረሻ ቁጥር ያለመሆኑን ያብራሩ ሲሆን የአስመራጭ ኮሚቴው አባላትም ከጋዜጠኞች ለቀረቡት ጥያቄዎች ተጨማሪ ምላሽ በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክን ጨምሮ 13ቱም አስመራጭ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል፡፡

ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. አስመራጭ ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የካቲት 18 ቀን አምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ለምእመናን በይፋ እንደሚገለጹ፤ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ የተመረጡት ፓትርያርክ በመገናኛ ብዙሃን እንደሚገለጽና የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. በዓለ ሲመት እንደሚከናወን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

የካቲት 9 ቀን 2005 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስሰ


DSC09260

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ6ኛ ፓትርያርክ አስመራጭ ኮሚቴ የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለፓትርያርክነትእጩ ሆነው የሚቀርቡ ጳጳሳትን ለመምረጥ ካህናትና ምእመናን ጥቆማ እንዲያደርጉ ከየካቲት 1 – 8 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰጠው የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

 

አስመራጭ ኮሚቴው በአንድ ሳምንት ውስጥ አከናወንኳቸው ያላቸውን ሥራዎች ባቀረበበት በዚሁ መግለጫ በርካታ ምእመናን ለቤተ ክርስቲያኒቱ 6ኛ ፓትርያርክ ሊሆኑ ይገባቸዋል ያሉትን አባት በአካል በመቅረብ እንዲሁም በፋክስ መልእክት በመላክ ጥቆማ መስጠታቸውን ገልጧል፡፡ ከካህናትና ምእመናን የተገኘው ጥቆማም ለአስመራጭ ኮሚቴው በግብአትነት የሚያገለግል ሲሆን ከየካቲት 9 -14 ቀን 2005 ዓ.ም. በወጣው የፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ መሠረት አስመራጭ ኮሚቴው ለይቶ ከሦስት ያላነሱ ከአምስት ያልበለጡ እጩ ፓትርያርኮችን የካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያቀርብ መግለጫው አመልክቷል፡፡ የምርጫው ሂደት በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ፤ ካህናትና ምእመናን እግዚአብሔርን በጸሎት እንዲጠይቁ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡  እጩ ሆነው የሚቀርቡ ጳጳሳትን ለመምረጥ ካህናትና ምእመናን ጥቆማ እንዲያደርጉ ከየካቲት 1 – 8 ቀን 2005 ዓ.ም. የሰጠው የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን አስታወቀ፡፡

 

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ አስመራጭ ኮሚቴው ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሾችንም ሰጥተዋል፡፡

 

ከጋዜጠኞች ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ምርጫው ከሌሎች ተጽእኖ ምን ያህል የፀዳ ነው? የሚለውን ለቀ ማዕምራን ፋንታሁን ሙጬ የአስመራጭ ኮሚቴው ጸሐፊ ምላሽ የሰጡ ሲሆን አስመራጭ ኮሚቴው ከሌሎች አካላት ተጽእኖ የጸዳና ራሱን ችሎ የተሰጡትን ኃላፊነቶች በመወጣት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡  የአኀት ቤተ ክርስቲያንና የሲቪክ ማኅበራት ምርጫውን ለመታዘብ ይገኛሉ? የሚለውን ሲመልሱም ከአኀት ቤተ ክርስቲናት፤ ከአለም አብተ ክርስቲናት ምክር ቤት፤ ከአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት፤ ከታዋቂ አገር ሽማግሌዎችና ከመንግስት አካላት በታዛቢነት እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡

 

በስፋት ጥቆማ እየሰጡ የሚገኙት የአዲስ አበባ ካህናትና ምእመናን ናቸው፡፡ ሌሎቹ አህጉረ ስብከቶችስ? በሚል ለቀረበው ጥያቄም ሲመልሱ “በርቀት ምክንያት በአካል መቅረብ ያልቻሉ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. አስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ላይ ሁለት ፋክስ ቁጥሮችን ይፋ አድርጓል፡፡ ፋክሶቹም 24 ሰዓት በመስራት ከአውሮፓና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጥቆማዎችን እንደተቀበሉና በአካል ቀርበው ጥቆማቸውን የሚሰጡትንም በተዘጋጀው ቅጽ ላይ ሞልተው በታሸገው የጥቆማ መስጫ ሳጥን ውስጥ እያስገቡ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡

 

በፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ ላይ እጩ የሚሆኑትን አባቶች ከተለዩ በኋላ ከምእመናን የሚቀርቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ለመቀበል የ15 ቀናት የጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን አስመራጭ ኮሚቴው የገለጸው በሦስት ቀናት ልዩነት ፓትርያርክ ሆነው የሚመረጡት አባት እንደሚታወቁ ነው፡፡ ይህ አካሔድ ከሕገ ደንቡ ጋር አይጋጭም? የሚለውንም ሲመልሱ “ከምርጫ ሕገ ደንቡ ጋር ተያዞ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ጸድቆ ለአስመራጭ ኮሚቴው የተሰጠ ተጨማሪ ሕግ አለ፡፡ አስመራጭ ኮሚቴውን በሚያስመርጥበት ወቅት ኮሚቴው ሊሰሯቸው የሚገባውን ተግባራት ቋሚ ሲኖዶስ እየተከታተለ አስፈላጊውን ለውጥ ማድረግ እንደሚችል የተገለጸበት ሕግ ነው፡፡ ይህንን ሕግ ተከትሎ የድርጊት መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ነው አስመራጭ ኮሚቴው ለቋሚ ሲኖዶስ ያቀረበው፡፡  ቋሚ ሲኖዶስ የቅዱስ ሲኖዶስም ምልዓተ ጉባኤ በሰጠው ሥልጣንና ውክልና መሠረት አስመራጭ ኮሚቴው ያቀረበውን የጊዜ ሰሌዳ ትክክል ነው ብሎ አጽድቆ ሰጥቶታል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው ሕግ የማውጣትም ሆነ ሕግ የመለወጥ ስልጣን የለውም” በማለት የመለሱ ሲሆን ስለቀኑ ማጠር ሲያብራሩም ወደ አብይ ጾም የተቃረበ በመሆኑ ከዚያ በፊት ማጠናቀቅ እንደሚገባ ግንዛቤ ተወስዶ እንደተከናወነ ገልጸዋል፡፡

 

በመጨረሻም ከ53ቱም አህጉረ ስብከቶች ለመራጭነት ይገኛሉ ተብሎ ይፋ የተደረገው 800 መራጮች ብቻ ናቸው ፡፡ ነገር ግን ሲሰላ ከዚያ በላይ ስለሚሆኑ እንዴት ይታያል? በማለት ለቀረበው ጥያቄም በፓትርያርክ ምርጫው ላይ በመራጭነት የሚሳተፉ ሰዎች 800 ይሆናል የሚለውም እንደ መነሻ የተያዘ እንጂ የመጨረሻ ቁጥር ያለመሆኑን ያብራሩ ሲሆን የአስመራጭ ኮሚቴው አባላትም ከጋዜጠኞች ለቀረቡት ጥያቄዎች ተጨማሪ ምላሽ በመስጠት ተሳትፈዋል፡፡

 

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አቃቤ መንበረ ፓትርያርክን ጨምሮ 13ቱም አስመራጭ ኮሚቴዎች ተገኝተዋል፡፡

 

ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. አስመራጭ ኮሚቴው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የካቲት 18 ቀን አምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ለምእመናን በይፋ እንደሚገለጹ፤ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ የተመረጡት ፓትርያርክ በመገናኛ ብዙሃን እንደሚገለጽና የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም. በዓለ ሲመት እንደሚከናወን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

ነቢዩ ዮናስ (ክፍል አንድ) /ለሕፃናት/

የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ /ወልደ ኢየሱስ/

 

ልጆችዬ እንደምን ሰነበታችሁልኝ? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁኝ? ጎበዞች፡፡ ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት በጣም ደስ የሚል ታሪክ ነው፡፡ ስለዚህ በደንብ ተከታተሉኝ እሺ፡፡

 

በድሮ ጊዜ ነው፣ በጣም በጣም በድሮ ጊዜ አንድ እግዚአብሔርን በጣም የሚወድ ልጅ ነበረ፡፡ ስሙ ዮናስ ይባላል፡፡ ታዲያ ዮናስ ደግ፣ የዋህ፣ ለሰዎች ሁሉ ታዛዥ እና ክፉ ነገርን የማያደርግ ነው፡፡ በዚህ ጥሩ ጸባዩ የተነሣ እግዚአብሔር ዮናስን በጣም ይወደዋል፣ ስሙንም ጠርቶ ያናግረዋል፡፡

 

አንድ ቀን እግዚአብሔር ዮናስን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- “ወዳጄ ዮናስ ሆይ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ተነሥና ሂድ፡፡ ለነነዌ ሕዝብም እንዲህ በላቸው፡- ክፉ ሥራ መሥራት ትታችሁ ጥሩ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ሥራ ካልሠራችሁ እግዚአብሔር ይቆጣችኋል፣ ከክፉ ሥራችሁ ካልተመሳችሁ ከተማችሁን ያጠፋባችኋል፡፡” ብለህ ተናገር ብሎ አዘዘው፡፡ ዮናስ ግን እግዚአብሔር ወደ ላከው ወደ ነነዌ መሄድ ትቶ ወደ ሌላ ሀገር ተርሴስ ወደምትባል ሀገር ሊሄድ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደና በመርከብ ላይ ተሳፈረ /ወጣ/፡፡ ከዚያም መርከብ ውስጥ ሆኖ በባሕሩ ላይ መጓዝ ጀመረ፡፡ ግን የሚሄደው እግዚአብሔር ወደ ላከው ሀገር ሳይሆን ወደ ሌላ ሀገር ነበረ፡፡

 

እግዚአብሔርም ዮናስ እንዳልታዘዘው ባየ ጊዜ ነፋሱን አዘዘው፡፡ ነፋሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ባሕሩን በጣም ያነቃንቀው ያወዛውዘው ጀመረ ከዚያ ከባድ ማዕበል ሆነ፡፡ የባሕሩም ውኃ መርከቧን ሊያሰጥማት አወዛወዛት፡፡ አንዴ ወደ ቀኝ አንዴ ወደ ግራ ልትወድቅ፣ ልትገለበጥ መርከቧ ተወዛወዘች፡፡ ያን ጊዜ በውስጧ ያሉ የመርከቧ ሠራተኞች መርከቧ እንዳትገለበጥና እንዳይሞቱ በጣም ቢደክሙም ነፋሱ ግን ውኃውን እያነሳ መርከቧ ላይ ይጥልባቸዋል፡፡

 

ልጆችዬ በጣም የሚገርማችሁ ነገር ግን ይህ ሁሉ ነፋስ ሲነፍስ መርከቧም ወዲህና ወዲያ ስትወዛወዝ ዮናስ በመርከቧ ውስጥ ሆኖ አልሰማም ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? በመርከቧ ውስጠኛ ክፍል ገብቶ ኀይለኛ እንቅልፍ ተኝቶ ስለነበረ ነው፡፡ የመርከቧ ሠራተኞ ወደ ዮናስ መጣና ኧረ መርከባችን በባሕር ውስጥ ልትሰጥምብን ነው፣ ኧረ ልንገለበጥ ነው፤ ከተኛህበት ንቃ ብሎ ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው፡፡ ዮናስ ተነሥቶ ሲያይ ነፋሱ በጣም ይጮኻል፣ የባሕሩም ውኃ መርከቧን ሊገለብጣት ወደ ላይ እየተነሣ መርከቧን ይመታታል፡፡ የመርከቡ ሠራተኞችም ሁሉም በጣም ተደናግጠውና ፈርተዋል፡፡ ነፋሱን እንዲያቆምላቸውና በሰላም እንዲሄዱ ሁሉም እግዚአብሔርን “አድነን፣ ነፋሱን አቁምልን፣ በሰላም አገራችን አድርሰን፡፡” እያሉ መጸለይ ጀመሩ፡፡

 

ዮናስም ይሄ ሁሉ ችግር የመጣው እርሱ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙና ሂድ ወደ ተባለበት አገር ባለመሄዱ ምክንያት የመጣ እንደሆነ አወቀ፡፡ እግዚአብሔርም በዮናስ ተቆጥቶ እንዲህ ማድረጉን በተረዳ ጊዜ የመርከቧን ሠራተኞች “ይሄ ሁሉ ችግር የደረሰባችሁ በእኔ ጥፋት ስለሆነ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣሉኝ፡፡ ከዚያ ነፋሱ ይቆምላችሁና በባሕር ውስጥ ከመገልበጥ እና ከመሞት ትድናላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባሕሩ ውስጥ እኔን ጣሉኝ፡፡” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የመርከቧ ሠራተኞች ዮናስን ወደ ባሕር ውስጥ ወረወሩት፡፡ ወዲያውኑ የሚነፍሰው ኀይለኛ ነፋስ ቆመ፡፡ መርከቧም በሰላም ተጓዘች፡፡

 

ደጉና የዋሁ ዮናስ ወደ ሰፊው ባሕር ውስጥ ተጣለ፡፡ ወደ ባሕሩ ጥልቅ ውስጥም ገባ፡፡ በዙሪያውም በውኃ ተከበበ፡፡ ልጆችዬ ውኃ ውስጥ ደግሞ የሰው ልጆች መተንፈስ አንችልም፣ ማንም ሰው ደግሞ መተንፈስ ካልቻለ ይሞታል፡፡ ዮናስ ግን ጥልቁ ባሕር ውስጥ ተጥሎም አልሞተም፡፡ ዮናስ ለምን እንዳልሞተ፣ በባሕር ውስጥ ሲገባ ምን እንዳገኘው በሚቀጥለው ክፍል ይዤላችሁ እመጣለሁ፡፡

 

አሁን ከመሰናበቴ በፊት ሦስት ጥያቄ እጠይቃችኂለሁ፡-

  1. እግዚአብሔር ዮናስን በጣም የሚወደውና የሚያነጋግረው ዮናስ ምን ዓይነት ጸባይ ስላለው ነው?

  2. ዮናስ የተሳፈረባት መርከብ በነፋስ ብዙ ችግር የደረሰባት በማን ስህተት ነው?

  3. እግዚአብሔር ዮናስን የላከው ምን ወደ ተባለ ሀገር ነው?

ይቀጥላል

መመለስ /ክፍል አንድ/

የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

ከእንዳለ ደምስሰ

ከቀኑ አሥራ ሁለት ስዓት ፡፡

 

ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ስደርስ ልቦናዬን እየተፈታተነኝ ያለውን የዐሳብ ድሪቶ አውልቄ ለመጣል ትንፋሼን ሰብስቤ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡

 

ከተሳለምኩ በኋላ ከዋናው በር በስተግራ በኩል ካለው ዋርካ ሥር አመራሁ፡፡ የሰርክ ስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር እየተካሄደ ነው፡፡ አካባቢዬን ቃኘሁ፡፡ ምእመናን አመቺ ነው ባሉት ቦታ ላይ ተቀምጠው የዕለቱን ትምህርት ይከታተላሉ፡፡ መምህሩ በሉቃስ ወንጌል ምዕ.15፥7 -10 ያለውን ኀይለ ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ እያነበቡ ነው፡፡

 

“. . . ንስሐ ከማያስፈልጋቸው ዘጠና ዘጠኙ ጻድቃን ይልቅ ንስሐ ስለሚገባ ስለ አንድ ኀጢአተኛ በሰማያት ፍጹም ደስታ ይሆናል . . . ፡፡” ሰባኪው ስብከታቸውን ቀጥለዋል . . . .፡፡

 

የሸሸግሁት ቁስል ስለተነካብኝ ውስጤ በፍርሃት ተወረረ፡፡

 

— “ማን ነገራቸው? ለዘመናት ስሸሸው የኖርኩትን የንስሐ ትምህርት ዛሬም ተከትሎኝ መጣ?” አጉረመረምኩ፡፡

 

ቀስ በቀስ ስብከቱን እያደመጥኩ ራሴን በመውቀስ ጸጸት ያንገበግበኝ ጀመር፡፡– “ለምን ስሜታዊነት ያጠቃኛል? ለምን ወደ ትክክለኛው የክርስትና ሕይወቴ አልመለስም? ዛሬ የመጨረሻዬ ይሆናል፡፡” ውሳኔዬ ቢያስደስተኝም መሸርሸሩ አይቀርም በሚል ደግሞ ሰጋሁ፡፡ ስንት ጊዜ ወስኜ ተመልሼ ታጥቦ ጭቃ ሆኛለሁ?! አንድ መቶ ጊዜ – አንድ ሺህ ጊዜ – ከዚህም በላይ . . . ፡፡ ቃለ እግዚአብሔር በሰማሁ ቁጥር ልቤ ይሰበራል፡፡ እጸጸታለሁ፡፡ ነገር ግን ከቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር እንደወጣሁ በልቦናዬ የተተከለው ቃለ እግዚአብሔር ንፋስ እንደ ጎበኘው ገለባ ይበተናል፡፡ ውሳኔዬም ይሻራል፤ ልቦናዬ ይደነድናል፡፡ ወደ ቀድሞ እሪያነቴ እመለሳለሁ፡፡ ሁልጊዜ — “የተጠናወተኝ አጋንንት ነው እንዲህ የሚሰራኝ!” እያልኩ አሳብባለሁ፡፡

 

ሰባኪው ቀጥለዋል፡፡ “. . . አሁንም ከክፋትህ ተመለስና ንስሐ ግባ፡፡ የልቦናህንም ዐሳብ ይተውልህ እንደሆነ እግዚአብሔርን ለምን ፡፡ /የሐዋ. ሥራ ምዕ.8፥22/ ” የበለጠ ተሸበርኩ፡፡

 

አመጣጤ መምህረ ንሰሐዬ ይሆኑ ዘንድ ካሰብኳቸውና ቀጠሮ ከሰጡኝ አባት ጋር ለመገናኘት ነበር፡፡ ለመምህረ ንስሐነት በራሴ ፍላጎት ያጨኋቸው አባትም ዘገዩ፡፡ ከሶስት ቀናት በፊት ሳገኛቸው አብረን ተቀምጠን የተነጋገርንበት ቦታ ላይ ሆኜ እየጠበቅኋቸው ነው፡፡ ያገኘሁዋቸው ከሰንበት ትምህርት ቤቱ የቅርብ ጓደኛዬ ነው፡፡ ቀድሞ ከነበሩኝ የንስሐ አባቴ ጋር ስላልተግባባን፤ በተለይም ቁጣቸውን መቋቋም ስላቃተኝ ለመቀየር ወስኜ ነው የመጣሁት፡፡

 

— “ይገርማል! ስንተኛዬ ናቸው ማለት ነው? 1 – 2 – 3 . . . 4ኛ!” በአንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ሦስት መምህረ ንስሐ ይዤ ፈርጥጫለሁ፡፡ — “ምን አይነት አባት ይሆኑ? የማይቆጡ፤ የማያደናብሩ፤ ጥቂት ብቻ ቀኖና የሚሰጡ ከሆነ ነው አብሬ የምቆየው፡፡” እንደተለመደው ለማፈግፈግ ምክንያት አዘጋጀሁ፡፡

 

መልሼ ደግሞ — “ምን አይነት ሰው ነኝ?! ዳግም ወደ ኀጢአት ላልመለስ ከራሴ ጋር እየተነጋገርኩ መልሼ እዚሁ አፈርሰዋለሁ እንዴ?! መጨከን አለብኝ፡፡ የሆነውን ሁሉ እናዘዛለሁ፡፡” ሙግቴ ቀጥሏል . . . ፡፡

 

ሰባኪው “. . . እንግዲህ ኀጢአታችሁ ይሠረይላችሁ ዘንድ ንስሐ ግቡ፤ ተመለሱም፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የይቅርታ ዘመን ይመጣል፡፡” የሐዋ.ሥራ ምዕ.3፥19 እያሉ በመስበክ ላይ ናቸው፡፡

 

— “ይቺ ጥይት ለእኔ የተተኮሰች ናት!” አልኩ በልቤ ሰባኪው ርዕስ እንዲቀይሩ  እየተመኘሁ ፡፡  — “እውነት ግን የይቅርታ ዘመን የሚመጣልኝ ከሆነ ለምን ከልቤ ንስሐ አልገባም? እስከ መቼ በኀጢአት ጭቃ እየተለወስኩ እዘልቀዋለሁ? መርሐ ግብሩ ይጠናቀቅ እንጂ ዝክዝክ አድርጌ ነው የምነግራቸው፡፡” ቅዱስ ጊዮርጊስን በተሰበረ ልብ ኀጢአቴን እናዘዝ ዘንድ እንዲረዳኝ ተማጸንኩት፡፡

 

ሰባኪው በቀላሉ የሚለቁኝ አይመስልም፡፡ “. . . ከእግዚአብሔር ፍርድ እንደምታመልጥ ታስባለህን? ወይስ በቸርነቱ ብዛት በመታገሱ ለአንተም እሺ በማለቱ እግዚአብሔርን አላዋቂ ልታደርገው ታስባለህን? የእግዚአብሔርንስ ቸርነቱ አንተን ወደ ንስሐ እንዲመልስ አታውቅምን? ነገር ግን ልቡናህን እንደማጽናትህ ንስሐም እንዳለመግባትህ መጠን የእግዚአብሔርን እውነተኛ ፍርዱ በሚገለጥበት ቀን ቁጣን ለራስህ ታዘጋጃለህ፡፡” ሮሜ. 2፡3-5 እያሉ በሚሰብኩት ስብከት ልቡናዬን አሸበሩት፡፡

 

— “የአሁኑ ይባስ! ዛሬ ስለ እኔ ተነግሯቸው ነው የመጡት፡፡ ወረዱብኝ እኮ!” እላለሁ፡፡ መልሼ ደግሞ  — “እውነታቸውን ነው ይበሉኝ!!” ትምህርትም ሆነ እውቀት ሳያንሰኝ ከልቤ ልመለስ አለመቻሌ አሳፈረኝ፡፡

 

በሰ/ት/ቤት ውስጥ እንደ ማደጌና ለአገልግሎት እንደ መትጋቴ ለንስሐ  ጀርባ መስጠቴ ምን የሚሉት ክርስትና ነው? ሌሎች በአርአያነት የሚመለከቱኝ፤ ‹ክርስትናን ከኖሩት አይቀር ልክ እንደ እሱ ነው!› የተባለልኝ – ነገር ግን በኃጢአት ጥቀርሻ የተሞላሁ አሳፋሪ ሰው ነኝ፡፡ ነጠላ መስቀለኛ ለብሶ፤ መድረኩን ተቆጣጥሮ መርሐ ግብር መምራት፤ ለመስበክ መንጠራራት ፤ለመዘመር መጣደፍ ፤. . . ምኑ ቀረኝ?

 

ጊዜው የጉርምስና ወቅት በመሆኑ ለኀጢአት ስራዎችም የበረታሁበት ወቅት ነው ፡፡ ሰ/ት/ቤት ውስጥ የማያቸው እኅቶቼን ሁሉ የእኔ እንዲሆኑ እመኛለሁ፡፡ ምኞት ኀጢአት መሆኑን ሳስብ ደግሞ መለስ እላለሁ፡፡ ግን ብዙም ሳልቆይ  እቀጥላለሁ፡፡ በሥራ ቦታዬ ደግሞ ማታለልን ፤ በጉልበት የሌሎችን ላብ መቀማትን ፤ ማጭበርበር የዘወትር ተግባሬ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት ስሔድ ደግሞ ሁሉን እርግፍ አድርጌ ለበጎ ስራ እተጋለሁ፡፡ — “መርዛማ ዛፍ መልካም ፍሬን ማፍራት ትችላለችን?” ራሴን እየሸነገልኩ ለጽድቅም ሆነ ለኩነኔ በረታሁ፡፡

 

አንድ ቀን በሰ/ት/ቤታችን ውስጥ በሥነ ምግባሩ የታወቀ፤ ለሌሎች አርአያ የሆነ እንደ እኔ አጭበርባሪ ነው ብዬ የማልገምተውና የማከብርው ጓደኛዬ የንስሐ አባት መያዙን ነገረኝ፡፡ እኔስ ከማን አንሳለሁ? ይመቹኛል የምላቸውን አባት መርጬ ያዝኩ፡፡ ተደሰትኩ፡፡ ቀስ በቀስ በሚኖረን ግንኙነት ኀጢአቴን ሳልደብቅ መናዘዝ ጀመርኩ፡፡ ዛሬ ቀኖና ተቀብዬ፤ ጸሎት አድርሰውልኝ በእግዚአብሔር ይፍታህ የተደመደመ ኃጢአቴን ገና ከአባቴ እንደተለየሁ እደግመዋለሁ፡፡ እንደውም አብልጬ እሰራለሁ፡፡ እናዘዛለሁ፡፡ ተመልሼ እጨቀያለሁ፡፡ የንስሐ አባቴን ትዕግስት ተፈታተንኩ፡፡ እሳቸውም አምርረው ይገሥጹኛል፡፡ ድርጊቴ ተደጋገመ፡፡ ሁኔታቸው ስላላማረኝ ሳልሰናበታቸው ጠፋሁ፡፡

 

ለሁለተኛ ጊዜ ሌላ የንስሐ አባት ያዝኩ፡፡

 

እኚህ ደግሞ በጣም እርጋታን የተላበሱ ሲሆኑ ሲመክሩኝ ደግሞ የሌሎችን ታሪክ በምሳሌነት በማንሳት ያስተምሩኛል፡፡ ቀኖና ሲሰጡኝም በትንሹ ነው፡፡ የሰራሁት ኀጢአትና የሰጡኝን ቀኖና ሳመዛዝን ኀጢአቴ ይገዝፍብኛል፡፡ የሚሸነግሉኝ ይመስለኛል፡፡

 

— “ጸሎት አታቋርጥ፤ መጻሕፍትን መድገም ትደርስበታለህ፤ በቀን ለሶስት ጊዜያት አንድ አንድ አቡነ ዘበሰማያትን ድገም፡፡ ለሕፃን ልጅ ወተት እንጂ ጥሬ አይሰጡትም፡፡ ስትጠነክር ደግሞ ከፍ እናደርገዋለን፡፡” ይሉኛል፡፡

 

የናቁኝ መሰለኝ፡፡ — “እንኳን አባታችን ሆይ እኔ ጀግናው የዘወትር ጸሎት ፤ ውዳሴ ማርያም፤ አንቀጸ ብርሃን ፤ የሰኔ ጎልጎታ፤ መዝሙረ ዳዊት፤ ሰይፈ መለኮት፤ሰይፈ ሥላሴ ጠዋትና ማታ መጸለዬን አያውቁም እንዴ?! እንዴት በአባታችን ሆይ ይገምቱኛል?” አኮረፍኩ፡፡ ጠፋሁ፡፡

 

ደግሞ ሌላ ፍለጋ፡፡

 

ሦስተኛው የንስሐ አባቴ በትንሹም በትልቁም ቁጣ ይቀናቸዋል፡፡ እንደመቆጣታቸው ሁሉ አረጋግተው ሲመክሩ ደግሞ ይመቻሉ፡፡ ነገር ግን ቁጣቸውን መቋቋም ስለተሳነኝ ከእሳቸውም ኮበለልኩ፡፡

 

ዛሬ ውሳኔዬን ማክበር አለብኝ፡፡ ወደ ልቦናዬ መመለስ፡፡ በሉቃስ ወንጌል ምዕ. 15 ላይ እንደተጠቀሰው የጠፋው ልጅ፡፡ ወደ አባቴ ቤት በቁርጠኝነት መመለስ፡፡ ልጅ ተብዬ ሳይሆን ከባሪያዎች እንደ አንዱ እቆጠር ዘንድ፡፡

 

ከምሽቱ 12፡30 ሆኗል፡፡

 

ሰባኪው አሰቀድሞ ይሰጡት የነበረውን የንስሐ ትምህርት ቀጥለዋል፡፡  “. . . በተመረጠችው ቀን ሰማሁህ፤ በማዳንም ቀን ረዳሁህ፤ እነሆ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት፡፡” 2ኛ ቆሮ. ምዕ› 6፡2 እያሉ ቃለ እግዚአብሔርን በምዕመናን ልቦና ላይ ይዘራሉ፡፡

 

— “እውነትም ለእኔ የተመረጠችው ቀን ዛሬ ናት፡፡ አምላኬ ሆይ ኃይልና ብርታትን ስጠኝ፡፡ ወደ ትክክለኛው አእምሮዬ እመለስ ዘንድ፤ በኀጢአት የኖርኩበት ያለፈው ዘመን ይበቃ ዘንድ እርዳኝ!!” አልኩ የተፍረከረከውን ልቦናዬ ያጸናልኝ ዘንድ እየተመኘሁ፡፡

 

— “አሁን ምንድነው ማድረግ ያለብኝ? እ – በመጀመሪያ ራሴን ማረጋጋት፡፡ ከዚያም እሰከ ዛሬ የፈጸምኩትን የኃጢአት ኮተት ማሰብ ፤ በመጨረሻም አንኳር የሆኑትን መናዘዝ፡፡” አልኩ ህሊናዬን ለመሰብሰብ እየጣርኩኝ፡፡

 

— “ግን እኮ የኀጢአት ትንሽ እንደሌለው ተምሬያለሁ፡፡ስለዚህ ሸክሜን ሁሉ ለመምህረ ንስሐዬ መናዘዝ አለብኝ፡፡” ውሳኔ ላይ ደረስኩ፡፡

 

ኀጢአት ናቸው ብዬ በራሴ አእምሮ የመዘንኳቸውን አስቦ መጨረስ አቃተኝ፡፡ በድርጊቴ ተገርሜ — “በቃ የኀጢአት ጎተራ ሆኛለሁ ማለት ነው? መቼ ይሆን ሰንኮፉ የሚነቀለው? እባክህ አምላኬ በቃህ በለኝ!”  ኃጢአቴን ማሰብ አደከመኝ፡፡

 

የዕለቱ የሰርክ ጉባኤ እንደተጠናቀቀ አበ ንስሐ ይሆኑኝ ዘንድ ቀጠሮ ያስያዝኳቸው አባት በመጠባበቅ አይኖቼ ተንከራተቱ፡፡

 

— “ረስተውኝ ይሆን እንዴ? – እውነታቸውን ነው – እኔ መረሳት ያለብኝ ሰው ነኝ፡፡ ለምንም – ለማንም የማልጠቅም ከንቱ ሆኛለሁ፡፡ ኀጢአት ያጎበጠኝ ምናምንቴ ነኝ!! የኀጢአት ሸክሜን የማራግፍበት ፍለጋ በመባዘን እሰከ መቼ እዘልቀዋለሁ? እውነተኛ ንስሐ መግባት ተስኖኝ እስከ መቼ እቅበዘበዛለሁ?” የዕንባ ጎተራዬ ተከፈተ፡፡ ከዓይኔ ሳይሆን ከልቤ ይመነጫል፡፡ መጨረሻዬ ናፈቀኝ፡፡

 

“እንደምን አመሸህ ልጄ?” አሉኝ የቀጠርኳቸው አባት ጭንቅላቴን በመስቀላቸው እየዳበሱኝ፡፡

 

ዕንባዬ ያለማቋረጥ እየወረደ ቀና ብዬ ተመለከትኳቸው፡፡ ከተቀመጥኩበት ተነስቼ መስቀል ተሳለምኩኝ፡፡ በሃምሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አባት ናቸው፡፡ ገብስማ ሪዛቸው ግርማ ሞገስ አላብሷቸዋል፡፡

 

“ምነው አለቀስክ?” አሉኝ አጠገቤ ካለው ጠፍጣፋ ድንጋይ ላይ እየተቀመጡ፡፡

 

ሳግ እየተናነቀኝ “ሸ- ሸ – ክሜ ከ- ከ-ብ-ብዶ-ብብ-ኝ ነው አባቴ! ም- ምንም  የማ- ማልጠቅም ሆኛለሁ!!” አልኳቸው ሆድ ብሶኝ፡፡

 

“መጸጸት መልካም ነው፡፡ ጸጸት ጥንካሬን ይወልዳል ልጄ! አይዞህ፡፡” አሉኝ በጥልቀት እየተመለከቱኝ፡፡

 

— “እግዚአብሔር ረድቶኝ የመጨረሻዬ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡” አባባላቸውን ተመኘሁት፡፡

 

— ‹‹አምላኬ ሆይ ብርታትን ስጠኝ፡፡ ውስጤ የታመቀውን የኃጢአት ጥቀርሻ ይታጠብ ዘንድ፤ የሆነውን ሁሉ በተሰበረ መንፈስ እናዘዝ ዘንደ እርዳኝ፡፡›› አልኩኝ ለራሴ፡፡ ቀና ብዬ አያቸው ዘንድ ብርታት አጣሁ፡፡

 

“ስመ ክርስትናህ ወልደ ሚካኤል ነው ያልከኝ?”

 

“አዎ አባቴ!”

 

“ሰሞኑን ስንገናኝ ከንስሐ ልጆቼ ጋር ጉዳይ ይዘን ስለነበር ጉዳይህን አልነገርከኝም፡፡ ለምን ይሆን የፈለግኸኝ?”

 

“አባቴ በቀጠሯችን መሠረት መጥቻለሁ፡፡ በኀጢአት ምክንያት የተቅበዘበዝኩኝ፤ ኀጢአቴ ያሳደደኝ፤ ለዓለም እጄን የሰጠሁ ምስኪን ነኝ፡፡ ህሊናዬ ሰላም አጥቷል፡፡ ያሳርፉኝ ዘንድ አባትነትዎን ሽቼ ነው የመጣሁት፡፡” አልኳቸው በተሰበረ ልሳን፡፡

 

ለጥቂት ሰከንዶች ከራሳቸው ጋር የሚመክሩ በሚመስል ስሜት ቆይተው “ልጄ የንስሐ ልጆች በብዛት አሉኝ፡፡ ሁሉንም ለማዳረስ አልቻልኩም እኔም በፈተና ውስጥ ነኝ፡፡ አንተ ደግሞ ተጨምረህ ባለ እዳ ሆኜ እንዳልቀር ሰጋሁ፡፡ ይቅርታ አድርግልኝና ሌላ አባት ብትፈልግ ይሻላል፡፡” አሉኝ ትህትና በተላበሰ አነጋገር፡፡

 

“እግዚአብሔር እርስዎን አገናኝቶኛልና ወደ ሌላ ወዴትም አልሔድም፡፡ ያለፈው ይበቃኛል፡፡” አነጋገሬ ውሳኔዬን እንደማልቀይር ይገልጽ ነበር፡፡

 

“ያመረርክ ትመስላለህ፡፡” አሉኝ ውሳኔዬ አስገርሟቸው፡፡

 

“አባቴ ታከተኝ፡፡ ቆሜ ስሔድ ሰው እመስላለሁ ፤ ነገር ግን ኀጢአት በባርነት የገዛኝ ርኩስ ነኝ፡፡ የመጣሁት ከባርነት ይታደጉኝ ዘንድ ነው፡፡ እባክዎ አባቴ እሺ ይበሉኝ!” ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡

 

ለቅሶዬን እስክገታና አስክረጋጋ ድረስ ጠብቀው “እንዲህ በተሰበረ መንፈስ ውሰጥ ሆነህ ጥዬህ ብሄድ ሸክሙ ለራሴው ነው፡፡ አንድ ጊዜ መጥተሃልና አላሰናክልህም፡፡” አሉኝ በፍቅር እያስተዋሉኝ፡፡

 

“እግዚአብሔር ይስጥልኝ አባቴ!” እግራቸው ላይ ተደፋሁ፡፡

 

“ተው – ተው አይገባም ልጄ – ቀና በል፡፡” ብለው ከተደፋሁበት በሁለት እጃቸው አነሱኝ፡፡

 

“ከዚህ በፊት አበ ነፍስ ነበረህ?” አሉኝ አረጋግተው ካስቀመጡኝ በኋላ፡፡

 

በአዎንታ ጭንቅላቴን ከፍና ዝቅ በማድረግ ገለጽኩላቸው፡፡

 

“በምን ምክንያት ተለያያችሁ?”

 

ራሴን ለማረጋገት እየሞከርኩ ዕንባዬን ጠርጌ በረጅሙ ተነፈስኩ፡፡

 

“አባቴ ታሪኩ ብዙ ነው፡፡ ከአንድም ሦስት ጊዜ የንስሐ አባት ቀያይሬያለሁ፡፡”

 

“ለምን?” በመገረም ነበር የጠየቁኝ፡፡

 

“ለእኔም እንቆቅልሽ ነው፡፡ ከአንዱ እየፈረረጠጥኩ ወደ አንዱ እየሔድኩ ነፍሴን አሳሯን አበላኋት፡፡”

 

“ከሦስቱም እየተሰናበትክ ነው እዚህ የደርስከው?” የበለጠ ለመስማት በመጓጓት ጠየቁኝ፡፡

 

“ከአንዳቸውም ጋር በስንብት አልተለያየሁም፡፡ በራሴ ፈቃድ ኮበለልኩ፡፡”

 

ለውሳኔ የተቸገሩ በሚመስል ስሜት የእጅ መስቀላቸውን እያገላበጡ ተከዙ፡፡ በመካካላችን ጸጥታ ሰፈነ. . . ፡፡

ይቀጥላል

te 2

ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያናዊ መረጃዎችን የመስጠት አቅሟን ማሳደግ እንደሚገባ ተጠቆመ

የካቲት 5 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

te 2በማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ማእከል አስተባበሪነት “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስስቲያን ተልዕኮ በሉላዊቷ ዓለም እና በዘመናዊው ማኅበረሰብ” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀረበ፡፡

 

በማኅበሩ ሕንፃ ውስጥ የካቲት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጥናታዊ ጽሑፉን ያቀረቡት አቶ ፋንታሁን ዋቄ ሲሆኑ ቀሲስ ዶክተር ደረጀ ሺፈራው መርሐ ግብሩን መርተውታል፡፡ አቶ ፋንታሁን ዋቄ በጥናታቸው ላይ ዘመናዊነትና መዘመን ምንድነው? ዘመናዊነትና መዘመን ለዓለማውያንና ለኦርቶዶክሳዊያን ክርስቲያኖችምን የተለየ ትርጉም ይኖረዋል? የዓለም ተለዋዋጭነት /Dynamizm/ ፍጥነት መገንዘብ፤ ለኦርቶዶክሳዊው ክርስትና ሉላዊነት ምን ይጠቅማል? የቤተ ክርስቲያን መዘመን እንዴት፤ ለምን? በሚሉ ርዕሶች ዙሪያ ሰፊ ትንታኔ ሰጥተዋል፡፡

 

ጥናት አቅራቢው ዘመናዊነትን “ስፋትና ጥልቀት ያላቸው ኢኮኖሚያዊ፤ ማኅበራዊ፤ ፖለቲካዊና ባሕላዊ የለውጥ ሂደቶች ድምር ውጤት የሆነ የኅብረተሰብ ለውጥ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ ስለዚህ ዘመናዊነት አዲስነት፤ ያለፈውን መተው፤ መለወጥ፤ አሁን የተሻለ የሚሰኘውን ማድረግና መሆን”ተብሎ ሊተረጎም ይችላል በማለት የጠቀሱ ሲሆን በመንፈሳዊው እይታ ኅብረተሰብ በፈጣሪ ፈቃድ መኖር የሚገባውና በምድር ላይ የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጫ ምሳሌ የሆነ አኗኗር ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ኅብረተሰብ ዘመነ ሲባልም ከዚህ አንጻር ሊታይ እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ዘመናዊነት ሦስት መልክ አለው ይላሉ፡፡ ማለትም በአስተሳሰብ /አዕምሯዊና መንፈሳዊ/ ፤ በአኗኗር እና በአዕምራዊ ጥበብ በሚገኝ ቁሳዊ ውጤት መራቀቅ ተብሎ ሊለካ ፤ሊተነተን እንደሚችል ያብራሩ ሲሆን አያይዘውም የቤተ ክርስቲያን መዘመንን መለኪያ ሲተነትኑ “በየትውልዱና በየዘመኑ የሰው ልጅ ሕገ እግዚአብሔርን የሚጻረር አስተሳሰብ ፤እምነትና አኗኗርን በመተው ክርስቶስን ወደ መምሰል ሕይወት እንዲመጣ በቴክኖሎጂ፤ በተቋም አቅም በአስተዳደር ወዘተ ይህንን ተልዕኮ ለማስፈጸም በሚያስችል ደረጃ መዘጋጀት የአፈጻጸም ዘመናዊነት ሊባል ይችላል፡፡” በማለት በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡

 

ሴኩላር ሂዩማኒዝም/ዓለማዊነት/ በተመለከተም  ሲያብራሩ “በእግዚአብሔር መኖር ከማያምን ሳይንሳዊ ማዕቀፈ እሳቤ የሚመነጭ የኑሮ ፍልስፍና አኗኗር ነው፡፡መሠረቱም የዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ሳይንስና በኒውተን የተፈጥሮ ሳይንስ መንጭቶ የመንፈሳዊው ዓለም መኖርን የማይቀበል ትምህርት ሲሆን፤ ዘመናዊው ማኅበራዊ ሳይንስ የዚህ ማእቀፈ እሳቤ ሰለባ ነው፡፡ በዛሬው ዓለም መዘመን እጅጉን የተቆራኘው ከሴኩላር ሂውማኒዝም/ዓለማዊነት/ ጋር ነው፡፡ ሥልጣኔ ፤እድገት፤ መሻሻል፤ ማወቅ፤ ሰው መሆን ሁሉ በሴኩላር ሂውማኒዝም ማዕቀፈ አሳቤ የሚመራ በመሆኑ መደበኛ ትምህርት ፤ ዘመናዊው ሥርዓተ መንግሥት ፤ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት፤ የአስተዳደር መመሪያ ሁሉ በሴኩላር ሂዩማኒዝም መሥፈርት የሚመዘን ነው” በማለት ይገልጹታል፡፡

 

የሉላዊነት አጀማመርን በተመለከተም እንደየ ማዕቀፈ እሳቤው ወይም መሠረተ ፍልስፍናው ዘመን መነሻ እንደሚለያይና የሕገ እግዚአብሔር ሉላዊነት ለአዳም በኤደን የተሰጠችው ብቸኛዋ ሉላዊሕግ እንደነበረችየገለጹት የጥናቱ አቅራቢ አቶ ፋንታሁን ክርስትናም በዚህች በተከፋፈለች ዓለም ውስጥ ሉላዊ ሕግ ትሆን ዘንድ በጌታችን ዓለምን ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ አድርጉ ብሎ ባዘዘ ጊዜ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 

አቶ ፋንታሁን በጥናታቸው መዘመንን በክርስቲያናዊ ትምህርትና መዘመን በሴኩላር ሂዩማኒዝም እይታ ያላቸውን ልዩነቶችን በማነጻጸርና በመተንተን ያቀረቡ ሲሆን በተለይም ሃይማኖት የሰዎችን ራስን የመግለጽ ዝንባሌ በማገድ ልማትና እድገት ላይ እንቅፋት ይሆናል፤ መንፈሳዊነት ሲጸና ድህነት ይሰፍናል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ ሴኩላር ሂዩማኒዝም /ዓለማዊነት/ መንፈሳዊነትን እንደሚዋጋ አብራርተዋል፡፡

 

የዘመነው ሴኩላር ሂዩማኒዝም ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ቴክኖሎጂን፤ ኢኮኖሚን፤ ትምህርትን፤ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ፤ የመንግሥታትte 1 ሕጎችን፤ መገናኛ ብዙኀንን በትጋት በመጠቀም ላይ እንደሚገኝና ፤በአንጻሩ ቤተ ክርስቲያን ከእነዚህ ተቋማትና ቴክኖሎጂዎች ራሷን በማግለል ትጠቃለች፡፡ይህንን ጥቃት ለመቀልበስ ቤተ ክርስቲያን ተገዳዳሪ ሉላዊ ኃይል ለማድረግ በተለያዩ አውዶች በተሰሚነትና በከፍተኛ አቅም ለማሳተፍ ዝግጅት ማድረግ እንደሚገባ በመግለጽ የጥናታቸውን ማጠቃለያ ያሉትን  አቅርበዋል፡፡ ባቀረቡት ማጠቃለያም ክርስትና ሉላዊ ሆኖየሚቀጥለው የቤተ ክርስቲያን ተከታዮች ማዕቀፈ እሳቤ ክርስቶሳዊ ማድረግና ማእቀፈ አሳቤውን የሚገልጽ አኗኗር ተግባራዊ ማድረግ፤ በማንኛውም የዘመናዊ ትምህርት የሚያድጉ የቤተ ክርስቲያን ልጆቿ በቂ የሆነ ክርስቲያናዊ ትምህርት እንዲያገኙ ማድረግ፤ ራሷን በመሠረታዊ ፍላጎቶች በመቻልና ከጥገኝነት የማላቀቅ ዕድሎችን ማስፋት፤በሴኩላር ሂዩማኒዝም ማዕቀፈ እሳቤ አመንጪነት የሚፈሰውን የመረጃ ጎርፍ የሚመጥን ክርስቲያናዊ መረጃ የመስጠት ዝግጅት ማጎልበት፤ ለምግባር እንቅፋት የሆኑ የዕለት ተዕለት ኑሮ ጥያቄዎችን በግልጽ በመመለስ ክርስቲያኖች የተበታተነ የግል ውሳኔእንዳይከተሉ መርዳት፤ የተቀደሰ ቤተሰብ አስተዳደርን በሚመለከት የሴኩላር ፍትሕ ዳኝነትን ከቤተ ክርስቲያን አንጻር እንዲያውቁ ማድረግና የመሳሰሉትን ጠቅሰዋል፡፡

 

ጥናታዊ ጽሑፉ እንደተጠናቀቀ ሰፋ ያለ ውይይት የተካሔደ ሲሆን ከሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ከተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡

hege 1

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የፓትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ

የካቲት 4 ቀን 2005 ዓ.ም.


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የፖትርያርክ ምርጫ ሕገ ደንብ ዝርዝር እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

 

 

hege 1hege  2hege 3hege 4hege 5hege 6hege 7hege 8hege 9

asmerach com

ስድስተኛው ፓትርያርክ የሚመረጡበት ጊዜ ይፋ ተደረገ

ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላ

 

asmerach comስድስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ለማስመረጥ የተቋቋመው አስመራጭ ኮሚቴ ከምርጫው ሂደት ጋርና  በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ጥር 30 ቀን 2005 ዓ.ም ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ምርጫው ተከናውኖ፣ በዚሁ ዕለት ምሽት 12 ሰዓት ላይ፤ ውጤቱ ለሕዝቡ ይፋ እንደሚደረግ አስታውቋል፡፡

 

መራጮች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ ከጥንታውያን ገዳማትና አድባራት፤ ከካህናት፤ ከምእመናን፤ ከሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት የተወከሉ ሲሆኑ ጠቅላላ ቁጥራቸው 800 መሆኑን ያስታወቀው መግለጫው፡- በመጨረሻ እጩ ሆነው የሚቀርቡ አምስት እጩ ፓትርያርኮች የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ አመልክቷል፡፡ የምርጫውን ሂደት ለማስፈጸም የወጣው መግለጫ “ምእመናን ካህናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ማንነታቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ በመያዝ ለእጩነት የሚያስቡትን አባት አስመራጭ ኮሚቴው ጽ/ቤት ድረስ በአካል በመቅረብ እንዲሁም ከሀገር ውጪ የሚገኙ በፋክስ ቁጥር 0111567711 እና 0111580540 ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን 2005 ዓ.ም እንዲጠቁሙ”  ጥሪውን አቅርቧል፡፡

 

ስድስተኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በመሆን የሚመረጡት አባት እሑድ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓ.ም በዓለ ሢመቱ በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም መግለጫው አመልክቷል፡፡

 

ከየሀገረ ስብከቱ በመራጭነት የተወከሉ ሰዎች የካቲት 19 ቀን 2005 ዓ.ም አዲስ አበባ እንዲገቡ ያዘዘው የአስመራጭ ኮሚቴው መግለጫ እግዚአብሔር አምላካችን የወደደውንና የፈቀደውን በመንበሩ ያስቀምጥ ዘንድ ካህናትና ምእመናን ከየካቲት 1 እስከ 8 ቀን ድረስ አምላካቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ ለአንድ ሱባኤ የሚቆይ የጸሎት ጊዜ መታወጁን አስታውቋል፡፡

 

p1p2p3p4p5