ነቢዩ ዮናስ (ክፍል አንድ) /ለሕፃናት/

የካቲት 8 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቤካ ፋንታ /ወልደ ኢየሱስ/

 

ልጆችዬ እንደምን ሰነበታችሁልኝ? እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁኝ? ጎበዞች፡፡ ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት በጣም ደስ የሚል ታሪክ ነው፡፡ ስለዚህ በደንብ ተከታተሉኝ እሺ፡፡

 

በድሮ ጊዜ ነው፣ በጣም በጣም በድሮ ጊዜ አንድ እግዚአብሔርን በጣም የሚወድ ልጅ ነበረ፡፡ ስሙ ዮናስ ይባላል፡፡ ታዲያ ዮናስ ደግ፣ የዋህ፣ ለሰዎች ሁሉ ታዛዥ እና ክፉ ነገርን የማያደርግ ነው፡፡ በዚህ ጥሩ ጸባዩ የተነሣ እግዚአብሔር ዮናስን በጣም ይወደዋል፣ ስሙንም ጠርቶ ያናግረዋል፡፡

 

አንድ ቀን እግዚአብሔር ዮናስን እንዲህ ብሎ አዘዘው፡- “ወዳጄ ዮናስ ሆይ ወደ ታላቂቱ ከተማ ወደ ነነዌ ተነሥና ሂድ፡፡ ለነነዌ ሕዝብም እንዲህ በላቸው፡- ክፉ ሥራ መሥራት ትታችሁ ጥሩ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካም ሥራ ካልሠራችሁ እግዚአብሔር ይቆጣችኋል፣ ከክፉ ሥራችሁ ካልተመሳችሁ ከተማችሁን ያጠፋባችኋል፡፡” ብለህ ተናገር ብሎ አዘዘው፡፡ ዮናስ ግን እግዚአብሔር ወደ ላከው ወደ ነነዌ መሄድ ትቶ ወደ ሌላ ሀገር ተርሴስ ወደምትባል ሀገር ሊሄድ ወደ ባሕር ዳርቻ ሄደና በመርከብ ላይ ተሳፈረ /ወጣ/፡፡ ከዚያም መርከብ ውስጥ ሆኖ በባሕሩ ላይ መጓዝ ጀመረ፡፡ ግን የሚሄደው እግዚአብሔር ወደ ላከው ሀገር ሳይሆን ወደ ሌላ ሀገር ነበረ፡፡

 

እግዚአብሔርም ዮናስ እንዳልታዘዘው ባየ ጊዜ ነፋሱን አዘዘው፡፡ ነፋሱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ባሕሩን በጣም ያነቃንቀው ያወዛውዘው ጀመረ ከዚያ ከባድ ማዕበል ሆነ፡፡ የባሕሩም ውኃ መርከቧን ሊያሰጥማት አወዛወዛት፡፡ አንዴ ወደ ቀኝ አንዴ ወደ ግራ ልትወድቅ፣ ልትገለበጥ መርከቧ ተወዛወዘች፡፡ ያን ጊዜ በውስጧ ያሉ የመርከቧ ሠራተኞች መርከቧ እንዳትገለበጥና እንዳይሞቱ በጣም ቢደክሙም ነፋሱ ግን ውኃውን እያነሳ መርከቧ ላይ ይጥልባቸዋል፡፡

 

ልጆችዬ በጣም የሚገርማችሁ ነገር ግን ይህ ሁሉ ነፋስ ሲነፍስ መርከቧም ወዲህና ወዲያ ስትወዛወዝ ዮናስ በመርከቧ ውስጥ ሆኖ አልሰማም ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ? በመርከቧ ውስጠኛ ክፍል ገብቶ ኀይለኛ እንቅልፍ ተኝቶ ስለነበረ ነው፡፡ የመርከቧ ሠራተኞ ወደ ዮናስ መጣና ኧረ መርከባችን በባሕር ውስጥ ልትሰጥምብን ነው፣ ኧረ ልንገለበጥ ነው፤ ከተኛህበት ንቃ ብሎ ከእንቅልፉ ቀሰቀሰው፡፡ ዮናስ ተነሥቶ ሲያይ ነፋሱ በጣም ይጮኻል፣ የባሕሩም ውኃ መርከቧን ሊገለብጣት ወደ ላይ እየተነሣ መርከቧን ይመታታል፡፡ የመርከቡ ሠራተኞችም ሁሉም በጣም ተደናግጠውና ፈርተዋል፡፡ ነፋሱን እንዲያቆምላቸውና በሰላም እንዲሄዱ ሁሉም እግዚአብሔርን “አድነን፣ ነፋሱን አቁምልን፣ በሰላም አገራችን አድርሰን፡፡” እያሉ መጸለይ ጀመሩ፡፡

 

ዮናስም ይሄ ሁሉ ችግር የመጣው እርሱ ለእግዚአብሔር ባለመታዘዙና ሂድ ወደ ተባለበት አገር ባለመሄዱ ምክንያት የመጣ እንደሆነ አወቀ፡፡ እግዚአብሔርም በዮናስ ተቆጥቶ እንዲህ ማድረጉን በተረዳ ጊዜ የመርከቧን ሠራተኞች “ይሄ ሁሉ ችግር የደረሰባችሁ በእኔ ጥፋት ስለሆነ ወደ ባሕሩ ውስጥ ጣሉኝ፡፡ ከዚያ ነፋሱ ይቆምላችሁና በባሕር ውስጥ ከመገልበጥ እና ከመሞት ትድናላችሁ፡፡ ስለዚህ ወደ ባሕሩ ውስጥ እኔን ጣሉኝ፡፡” አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የመርከቧ ሠራተኞች ዮናስን ወደ ባሕር ውስጥ ወረወሩት፡፡ ወዲያውኑ የሚነፍሰው ኀይለኛ ነፋስ ቆመ፡፡ መርከቧም በሰላም ተጓዘች፡፡

 

ደጉና የዋሁ ዮናስ ወደ ሰፊው ባሕር ውስጥ ተጣለ፡፡ ወደ ባሕሩ ጥልቅ ውስጥም ገባ፡፡ በዙሪያውም በውኃ ተከበበ፡፡ ልጆችዬ ውኃ ውስጥ ደግሞ የሰው ልጆች መተንፈስ አንችልም፣ ማንም ሰው ደግሞ መተንፈስ ካልቻለ ይሞታል፡፡ ዮናስ ግን ጥልቁ ባሕር ውስጥ ተጥሎም አልሞተም፡፡ ዮናስ ለምን እንዳልሞተ፣ በባሕር ውስጥ ሲገባ ምን እንዳገኘው በሚቀጥለው ክፍል ይዤላችሁ እመጣለሁ፡፡

 

አሁን ከመሰናበቴ በፊት ሦስት ጥያቄ እጠይቃችኂለሁ፡-

  1. እግዚአብሔር ዮናስን በጣም የሚወደውና የሚያነጋግረው ዮናስ ምን ዓይነት ጸባይ ስላለው ነው?

  2. ዮናስ የተሳፈረባት መርከብ በነፋስ ብዙ ችግር የደረሰባት በማን ስህተት ነው?

  3. እግዚአብሔር ዮናስን የላከው ምን ወደ ተባለ ሀገር ነው?

ይቀጥላል