የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ጥቅምት 21 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

 

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ለአሥር ቀናት ያህል በ17 አጀንዳዎች ላይ ሲነጋገር የሰነበተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ውሳኔዎችን በማስተላለፍ ዛሬ ከቀትር በፊት ተጠናቀቀ፡፡

 

ባለፈው ዓመት የተከናወነውን ሥራ ለመገምገምና የወደፊቱንም እቅድ ለመንደፍ እንዲችል ከየአህጉረ ስብከቱ ጽ/ቤቶች የቀረቡለትን ሪፓርቶች አዳምጦ አስፈላጊውን መመሪያ የሰጠው ቅዱስ ሲኖዶስ በሰሜን አሜሪካ ከሚገኙት አባቶች ጋር የተጀመረው የእርቀ ሰላም ድርድር ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

 

ስድስተኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ አስመልክቶ እስከ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ እንዲዘጋጅ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፤ ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በሚደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ሕጉ ተመርምሮ እንዲጸድቅና የምርጫ ሂደቱ እንዲቀጥል ከስምምነት ተደርሷል፡፡

 

የአዲስ አበባን ሀገረ ስብከትን አስመልክቶ ለመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት አፈጻጸም ያመች ዘንድ በምሥራቅ፣ በምዕራብ፣ በሰሜንና በደቡብ በአራት አህጉረ ስብከት እንዲዋቀር፤ ለእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጀምሮ ሥራ አስኪያጆችና ሠራተኞች እንዲመደቡ ተወስኗል፡፡

 

በብፁዕ አቡነ ናትናኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አማካኝነት የተነበበው የቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ፤ የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በሌሎችም አህጉር አገናኝ ዴስክ እንዲቋቋም የቤተ ክርስቲያኒቱ እንቅስቃሴ የሚዳስስ በእንግዚዝኛና በአማርኛ ቋንቋ የሚዘጋጅ ወርኅዊ መጽሔት እንዲኖር፤ መምሪያውንም የበለጠ ለማጠናከር ይቻል ዘንድ በሰው ኀይልና በበጀት እንዲደገፍ ውሳኔ ተላልፏል፤ በሌላ በኩል የአብነት ትምህርት ቤቶችን ገዳማትንና የካህናት ማሠልጠኛዎችን በበጀት አጠናክሮ በበለጠ እንዲሠሩ ለማድረግ የ10 ሚሊየን ብር በጀት እንዳጸደቀ አመልክቷል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ “የስም መነኮሳት ነን” ባዮች የቤተ ክርስቲያኒቱን የምንኩስና ልብስ እየለበሱ ሕዝቡን በማትለልና ሃይማኖታችንን በማስነቀፍ ተግባር ተሰማርተው እንደሚገኙ ይታወቃል፤ ስለሆነም ሕዝበ ክርስቲያኑ ከእነዚህ ምግባረ ብልሹ ወገኖች ራሱን ነቅቶ እንዲከላከልና መንግሥትም የሕግ ከለላ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦተ ይጠይቃል፡፡” ብሏል፡፡

 

ከመግለጫው በኋላ ከጋዜጠኞች ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ ዞን አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሕዝቅኤል የጳጳሳትን ንብረት አስመልክቶ፡- “በመሠረቱ ጳጳስ የእኔ፣ የግሌ የሚለው ሀብት ንብረት የለውም፡፡ ሊኖረውም አይገባም፡፡ ንብረቶቹ ሁሉ ምእመናን ናቸው፡፡ ምእመናን ሲባል ቤተ ክርስቲያኒቱን ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ጎመን የሚዘራበት፣ ሽንኩርት የሚተክልበት የእርሻ ቦታ እንኳ የለውም” በማለት ተናግረዋል፡፡

 

የቅዱስ ሲኖዶስን መግለጫ ዝርዝር ዘገባ በቅርቡ እናቀርባለን፡፡

aa 001

ሊቀ ጉባኤ ኀይለ ማርያም ዐረፉ

ጥቅምት 20 ቀን 2005 ዓ.ም.

በቀሲስ ለማ በሱፍቃድ


aa 001ሊቀ ጉባዔ ኀይለ ማርያም ንጋቱ ከአባታቸው ከአቶ ንጋቱ ወልደ ሐዋርያትና ከእናታቸው ከወ/ሮ ደመዎዝ ወንድም አየሁ ጥር 12 ቀን 1969 ዓ.ም በሰሜን ሸዋ በሞረትና ጅሩ ወረዳ ልዩ ስሟ ሽነት ቁስቋም በምትባል መንደር ተወለዱ፡፡ ገና በሕፃን ዕድሜያቸው ወደ ታላቁ ገዳም ወደ ደብረ ጽጌ ማርያም በመሄድ ለአጎታቸው ለአባ ፀጋ ወልደ ሐዋርያ በአደራነት ተስጥተው የቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸውን ትምህርት ሀ ብለው ንባብ ከአባ ሀብተ ማርያም በሚገባ ካጠናቀቁ በኋላ እዛው ገዳሙ ውስጥ ከሚገኙት ከመምህር አፈወርቅ የቃል ትምህርትና ጾም ምዕራፍ በሚገባ ተማሩ እንዲሁም ከታላቁ ሊቅ ከየኔታ ጽጌ ጾመ ድጓና ድጓ ተምርው በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ ቀጥሎም አቋቋምና ዝማሬ መዋሲእት ከየኔታ መስፍን አበበ በሚገባ ተምርው ተመርቀዋል፡፡ ይህን ሁሉ ትምህርት ተምሬያለሁ በቃኝ ሳይሉ ተጨማሪ ቃለ እግዚአብሔር ፍለጋ በ1984 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ በመግባት የእውቀት አድማሳቸውን በማስፋት የተክሌ አቋቋምን በመማር በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡

 

ሊቀ ጉባዔ ኀይለ ማርይም ንጋቱ በ1986ዓ.ም በገዳሙ ውስጥ በዲቁና እንዲያገለግሉ ተቀጥረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በነበራቸው መንፈሳዊ ትጋት የተነሣ በመሪ ጌትነት፣ በሊቀ አርድእትነት፣ በሊቀ ጉባኤነት፣ የትምህርት ቤቱ ተቆጣጣሪና ዋና ጸሐፊ በመሆን ከሃያ ዓመታት ላላነሱ ጊዜያት በልዩ ልዩ የሓላፊነት ቦታዎች በቅንንትና በታማኝነት አገልግለዋል፡፡ ሊቀ ጉባኤ ኀይለ ማርያም  በአስኳላው ትምህርታቸው እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል ድረስ ተከታትለዋል፡፡

 

ሊቀ ጉባኤ ኀይለ ማርያም ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምናና በጠበል ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ36 ዓመታቸው ጥቅምት 6 ቀን 2005 ዓ.ም ከዚህች ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተዋል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸውም ጥቅምት 7 ቀን 2005 ዓ.ም በደብረ ሊባኖስ ገዳም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡ ሊቀ ጉባኤ ኀይለ ማርያም ባለ ትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

ስርጭቱን ለማስቀጠል ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑ ተገለጠ፡፡

ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን አማካኝነት ከጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ይሠራጫል በሚል በምእመናን ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የማኅበሩ የቴሌቭዥን መርሐ ግብር የኢ.ቢ.ኤስ ጣቢያ ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ሙሉ ሥርጭቱ በመቋረጡ የተነሣ በታሰበው ጊዜ ለመጀመር አልተቻለም፡፡ ሆኖም የኢ.ቢ.ኤስ ሓላፊዎች በገለጹት መሠረት ጣቢያው እንደገና ሥርጨቱን ለማስጀመር ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ሲሆን ችግሩ እንደተቀረፈም የማኅበሩ ቴሌቪዥን  የሚጀምር መሆኑን አስተባባሪው ዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል፡፡

Aratu 2 (2)

፬ቱ ሆሄያት

ጥቅምት 19 ቀን 2005 ዓ.ም/

በዲ/ን ኅሩይ ባየ

Aratu 2 (2)የመስቀል ደመራ በናፍቆት የምንጠብቀው በዓል ነው፡፡ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በበዓሉ ይታደማል፤ በመዝሙር አምላኩን ያመሰግናል፡፡ ዛሬም እንደጥንቱ በያዝነው ዓመት በደመቀ መልኩ ተከብሯል፡፡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችም የተለያዩ መንፈሳዊ ተውኔቶችን በማቅረብ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

 

የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አራቱ ሆሄያት ተከብረውና ተጠብቀው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ የሆሄያቱ ጉዳይ ለበርካታ ጊዜያት ሲያከራክር የኖረ በመሆኑ ትኩረታችንን በዚሁ አድርገናል፡፡

 

አንድ ሀገር የራሱ የሆነ ቋንቋ፣ ባህል፣ እምነት፣ ታሪክ፣ ትውፊት፣ ሥነ ጽሑፍና ሥነ ቃል ይኖረዋል፡፡ ማኅበረሰቡም አኗኗሩን፣ የሚኖርበትንም አካባቢ የሚገልጥበት የአፍና የጽሑፍ ጥበቦችን እንደሚጠቅም ይታወቃል፡፡ ቃላዊና ቁሳዊ ተብሎ የሚከፈለው የሥነ ባህል ኀልዮት ራሱን ችሎ የሚተገበር ርዕዮተ ዓለም (ፍልስፍና) አለው፡፡

 

ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ዐበይት ሀብቶቿ ውስጥ አንዱ የራሷ የሆነ ፊደልና ቋንቋ እየተጠቀመች ለትውልድ ስታስተምር መኖሯ ነው፡፡ ለዚህም የፊደል፣ የቋንቋ ዕድገትና ሥልጣኔ ከፍተኛውን ድርሻ የምትይዘውና በር ከፋቿ የኢትዮጵያ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እንደ ጥንቱ የሆሄያቱ ታሪክ እንዳይረሳ መልክአቸው እንዳይጠፉ ለትውልዱ ታስተምራለች፡፡ ስለሆነም በዘንድሮው የመስቀል በዓል በመስቀል ዐደባባይ አራቱ ሆሄያት እንዳይረሱ ትኩረት እንደሚያሻቸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

ሆሄ የሚለውን ቃል ፊደል ተብሎ ሲነገር እንሰማለን፤ በጽሑፍም እናነባለን፡፡ ፊደልን ፈደለ ጻፈ ካለው የግእዝ ግስ አውጥተን ጽሑፍ የሚለውን ትርጉም እናገኛለን፡፡ በሌላ አተረጓጐም ፊደል የሚለው ግስ ጠብቆ ሲነበብ ፈጠረ የሚለውን ትርጉም ያስገኛል፡፡ ፊደል ፈጣሪ /መፍጠሪያ/ መባሉም ቃላትን ስለሚያስገኝ ነው፡፡ አባቶቻችን “ዘእንበለ ፊደል ኢይትነገር ወንጌል.. ያለፊደል ወንጌል አትተረጐምም” ማለታቸው ለመጻፍም ሆነ ለማንበብ፤ ለመተርጐምም ሆነ ለማመስጠር ፊደላት ጉልሕ ድርሻ እንዳላቸው ሲያመለክቱ ነው፡፡

 

ፊደል መጽሔተ /መስተዋት/ አእምሮ ነው፤ በመስተዋት የፊትን ጉድፍ ማየትና ራስን መመልከት እንደሚቻለው ሁሉ፤ ልብ ማድረግን፥ ዕውቀትንና ጥበብን የሚገልጡ ፊደላት ስለሆኑ መጽሔተ አእምሮ ተብለዋል፡፡ ፊደል ነቅዐ ጥበብ ሊባልም ይችላል፡፡ የጥበብ መገኛ፣ መፍለቂያ፣ መመንጪያ ናቸውና፡፡ ፊደል መራሔ ዕውራን ማለት ነው፡፡ ዐይነ ስውር በበትር እንዲመራ ዕውቀት ለጠፋበት ልቡናው ለደነዘዘበት የዕውቀት ድካም ላለበት ሰው ፊደልን ቢቆጥር ቢያጠናና ቢያውቅ ካለማወቅ ዕውርነት ወደ ዕውቀት ብርሃንነት ስለሚመለስ ፊደላትን መራሔ ዕውራን እንላቸዋለን፡፡ ፊደል ጸያሔ ፍኖት ወይም መንገድ ጠራጊ ነው፡፡ ንባብን ተገንዝቦ ምስጢርን ለማደላደል ፊደል ጥቅም አለው፡፡

 

ሆሄ /ፊደል/ በቁሙ ከምናየው መልክዐ ገጽ አልፎ በውስጡ የያዘው ታሪካዊ፣ አመክንዮአዊና ምስጢራዊ መልእክቶች አሉት፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የሁሉንም ሆሄያት ስያሜያቸውንና ምስጢራቸውን ማየት አንችልም፡፡

 

የግእዝን ቋንቋ ፊደል በተመለከተ ብዙ አስተያየቶች ቢኖሩም በአንድ ነገር መስማማት ይቻላል፡፡ ሆሄ ወይም ፊደል በቁሙ ከምናየው መልክዐ ገጽ አልፎ በውስጡ የያዘው ታሪካዊ፣ አመክንዮአዊና ምስጢራዊ መልእክቶች አሉት፡፡ የፊደልን ጠቀሜታ የትመጣና ሚና አስረስ የኔሰው ‹‹የካም መታሰቢያ የኢትዮጵያ ፊደል መሠረትነት መታወቂያ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው እንዳመለከቱት “ፊደል ሐውልት ነው፤ ሐውልትም ፊደል ነው፤ ፊደል መልክ ነው፤ መልክም ፊደል ነው፤ ፊደል አባት ነው፤ አባትም ፊደል ነው፤ ፊደል ልጅ ነው፣ ልጅም ፊደል ነው፤ ፊደል ወሰን ነው፡፡ ወሰንም ፊደል ነው፣ ፊደል ዓላማ ነው፣ ዓላማም ፊደል ነው፡፡

 

በወትሯዊ የጽሑፍ ተግባራችን የምንጠቀምባቸው ወደ አራት የሚደርሱ ሆሄያት አሉ፡፡ እነዚህ ፊደላት እነማን እንደሆኑ በቦታው እንገልጠዋለን፡፡ አራቱ ፊደላት በሥነ ድምፅ ትምህርት መካነ ፍጥረታቸው ተመሳሳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ልዩነታቸው በጽሑፍ ላይ ቢሆንም የመገኛቸው ቦታና የድምፃቸው ጠባይ ሊመሳሰል ይችላል፡፡ እነዚህ ሆሄያት በቃላት ውስጥ ሲገቡ የተለያየ የትርጉም ለውጥ የማምጣት ኀይል አላቸው፡፡ አራቱን ሆሄያት ጠንቅቀው የሚጽፉ ጸሐፍት ቢኖሩም ዕያወቁ በቸልተኝነት ሳያውቁ በስሕተት እጃቸው እንዳመጣ የሚጽፉ ደግሞ አያሌ ናቸው፡፡

 

ዶ/ር አምሳሉ አክሊሉ “የሆሄያት አጠቃቀም ችግር” በተባለው መጽሐፋቸው ሆሄያትን በአግባቡ መጠቀም የሚፈልጉና የማይፈልጉ ሰዎች ሦስት ምክንያቶችን እንደሚያቀርቡ አብራርተዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ለፊደላችን ሥርዐትና ወግ ሊበጅላቸው ያስፈልጋል፡፡ በዘፈቀደ መጻፍ እንደግዴለሽነትና ሥርዓት አልበኝነት ያስቆጥራል፤ ያለሥርዐት የሚተገበር ማንኛውም የሰዎች ሕግ ጠቀሜታ የለውም የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ በኹለተኛው በኩል ያሉ ወገኖች ደግሞ እንደተለመደው ለእጃችን የቀረበውን ሆሄ ብንጠቀምበት ምን ችግር አለው ይላሉ፡፡ በሦስተኛው ወገን ያሉ ሰዎች ደግሞ ለጽሕፈታችን ሥርዐት ተሠርቶለት ከኹለት አንዱን ፊደል መርጦ መጠቀም ይበጃል ይላሉ፡፡ ከሦስቱም ምሁራዊ አመክንዮዎች መካከል የፊደላቱን የትመጣና ብያኔ ምሥጢራዊ ፍቺ ጠንቅቀው የሚተረጉሙ ሊቃውንት የመጀመሪያውን ሐሳብ ይደግፋሉ፤ ተገቢና ምክንያታዊ በመሆኑም ቤተ ክርሰቲያናችን ትቀበለዋለች፡፡

 

በግእዝ  ሆሄያት ከሀ-ፐ ድረስ ያሉት ፊደሎች ቁጥር26 ናቸው፡፡ ከእነዚህም አራቱ ሆሄያት ይገኙባቸዋል፡፡ እነዚህ ሆሄያት ከላይ እንደገለጥነው የራሳቸው የሆነ መጠሪያ ስም አላቸው፡፡ ስም ያለው አካል የተለያየ ጠባይና ማንነት ቢኖረው እንጂ ፍጹም አንድነት ሊኖረው አይችልም፡፡ አራቱ ሆሄያት ናቸው የምንላቸው፡-

  1. ሀ፣ ሐ፣ ኀ /ሃሌታው “ሀ”፣ ሐመሩ “ሐ”ና ብዙኀኑ “ኀ”

  2. ሠ፣ ሰ፣ /ንጉሡ “ሠ” ና እሳቱ “ሰ”

  3. አ፣ ዐ አልፋው “አ” ና “ዐይኑ “ዐ”

  4. ጸ፣ ፀ /ጸሎቱ “ጸ” ና ፀሐዩ “ፀ” ናቸው፡፡.

 

እነዚህን ሆሄያት እየቀላቀሉ መጻፍ የትርጉም ለውጥ የሚያመጡ ቃላትን እንደመፍጠር ነው፡፡ አንዱን ከሌላው እያቀላቀሉ መጻፍ ምን ያህል አሳፋሪ እንደሆነ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ሲገልጡ፡-

“እንዳገኙ መጣፍ በድፍረት በመላ

የቋንቋ ደረመን የመጽሐፍ ቢስገላ

ንባብ የሚያሳክክ ምስጢር የሚቆምጥ

መልክዐ ትርጓሜ የሚለውጥ” ብለዋል

 

በዘመናዊ መንገድ በጽሑፍ ማሽን መጻፍ ከመጀመሩ በፊት ከሸምበቆ /መቃ/ ብዕር ተቀርጾ ከዕፀዋት ቀለም ተዘጋጅቶ ከእንስሳት ቆዳ ብራና ተዳምጦ በእጅ ጽሑፍ ይጻፍ ነበር፡፡ ጸሐፊውም ቁም ጸሐፊ ተብሎ ሲጠራ ጽሑፉም ቁም ጽሑፍ ይባላል፡፡ በዚህም መሠረት ቁም ጸሐፊ መሆን የሚፈልግ ሰው ጽሕፈት ሲማር የፊደሎችን አገባብ ጨምሮ ትክክለኛ ቅርፃቸውን ጠብቆ እንዲያውቅ ይደረጋል፡፡

 

በዐፄ በካፋ ዘመነ መንግሥት ሃሌታውን “ሀ” ከሐመሩ “ሐ” ንጉሡን “ሠ” ከእሳቱ “ሰ” ፥ ጻድቁን “ጸ” ከፀሐዩ “ፀ” ለይቶ በሥፍራቸው ያልጻፈ፤ ፊደል አዛውሮ የተገኘ ጸሐፊ እጁን ይቆረጥ እንደ ነበረ የጽሑፍ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

በኋላ ግን በቀን ብዛት የመጻሕፍትን ምስጢር ሳያውቁ የፊደሎችን አገባብ ሳይጠነቅቁ የብዕሩን አጣጣል በማሳመር ብቻ የሚራቀቁና በድፍረት የሚጽፉ ጸሐፍት እየበዙ ስለመጡ ሆሄያቱ ተዘበራርቀው የተቀመጡባቸው መጻሕፍት እየበዙ መጡ፤ ይህም አሠራር የመጻሕፍትን መልክ የምስጢራትን አሰካክ እያበላሸው ይገኛል፡፡

“ባንድ የሚጻፈው በሌላው ሲጻፍ

ቋንቋው ተበላሽቶ ይሆናል ጸያፍ

የጸሐፊ ደዌ ያታሚ መከራ

ጠንቅቆ አለማወቅ የፊደልን ሥራ”

 

እንዳሉት  አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ሆሄ ያለቦታው ሲቀመጥ አንባቢን ግራ ያጋባል፤ ምስጢር ያፋልሳል፤ መልእክት ያጓድላል፤ ንባብ ያጣርሳል፡፡

 

በእነዚህ ሆሄያት ዙሪያ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ክርክር ሲነሣበት እንደነበረ ፕሮፌሰር ባየ ይማም ለሐመር መጽሔት ሲገልጡ እንዲህ ነበር ያሉት፤ ‹‹ከቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ ጀምሮ የፈደል ማሻሻያ ተብሎ ሲነሣ ከቆየ በኋላ በመንግሥቱ ኃይለማርያም ጊዜ የቋንቋ አካዳሚ ጉባኤ ትርፍ የሚባሉ ፊደሎች ይወገዱ ብሎ ወስኗል፡፡ የሆሄው ትምህርት አሁን ቀርቷል ሁሉም እንደፈለገ ነው የሚጽፈው›› ብለዋል፡፡ ይኸን ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ የቋንቋዎች አካዳሚ ክብረ ነገሥት የተባለውን መጽሐፍ በአንድ ፊደል ብቻ አሳትሟል፡፡ ሐዲስ ዓለማየሁም አራቱን ሆሄያት  እንደገደፏቸው አስታውቀዋል፡፡

 

Aratu 2 (1)ሆሄያቱ እንዲቀነሱ ከ1950ዎቹ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ ውዝግብ እንደነበረ በመንግሥቱ ለማ ግለታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ፊደላቱ መቀነስ የለባቸውም ከሚሉ ሊቃውንት መካከል መርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ በአንድ ወገን፣ ፊደላቱ መቀነስ አለባቸው የሚለውን ሐሳብ በመደገፍ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት አቶ አበበ ረታ በሌላ ወገን ሆነው በአራት ኪሎ ቅድስት ሥላሴ ግቢ እንደተከራከሩ ይታወሳል፡፡ መንግሥቱ ለማን ጨምሮ ጥንታዊው ሆሄ ሳይቀነስ ሳይበረዝና ሳይከለስ ባለበት እንዲቀመጥ መሟገታቸውንም እንረዳለን፡፡ በቤተ ክህነት በኩል ፊደላችን ይቀነስ ወይስ አይቀነስ የሚል መንታ ሐሳብ ቀርቦ ሊቃውንቱ ተወያይተውበት ፊደላቱ ባሉበት እንዲቀመጡ የሚለው ወገን መርታቱን አለቃ ለማ  አብራርተዋል፡፡ /ደማሙ ብዕረኛ 1988፥115-128/

 

የሥነ ልሳን ተመራማሪና ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ባየ ይማም ሆሄያቱ ባሉበት ተከብረው በቦታቸው እየገቡ አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው ይገልጣሉ፡፡ “የእነዚህ ፊደላት ምንጩ የግእዝ ግስ እንደሆነ ዐውቃለሁ፡፡ የግእዝን ቋንቋ ከእንግሊዝኛ “የስፔሊንግ” ችግር ጋር ስናነጻጽረው እዚህ ግባ የሚባል ችግር የለውም፡፡ ስለዚህ እንደ ዜግነቴ ሥርዐተ ጽሕፈቱ ከታሪካችንና ከማንነታችን አኳያ እያየን ይዘነው ልንሔድ ይገባል” /ሐመር 8/18-19/፡፡

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር ኀይሉ ሀብቱ በሆሄያቱ ጠቀሜታ በሰጡት አሳብ ፊደሎቻችን ከፊደልነታቸው በላይ አኀዝንም እንደሚወክሉ ጠቁመው የአውሮፓው ሳይንቲስት ጋሊሊዮ ጋሊሊ እግዚአብሔር ዓለምን ሲፈጥር ከቁጥር ጋር በተያያዘ ቀመር እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ በዚህም መሠረት ባላወቅነው ምስጢር ገብተን፤ ባልተረዳነውና መንገድ ፊደላቱን በትክክል አለመጠቀማችን የስንፍና ምልክት ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ቻይናዎች 200 ፊደላት አሏቸው፡፡ የፊደሎቻቸው መብዛት በሳይንሱና በፍልስፍናው ያላቸውን ጉዞ አላቆመውም” ሲሉ ዶ/ር ኀይሉ ተናግረዋል፡፡ የሆሄያቱን አኀዛዊ ምስጢር ጠለቅ ባለ መንገድ አስረስ የኔሰው “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” በተባለው መጽሐፋቸው አብራርተዋል፡፡  /ስምዐ ጽድቅ ነሐሴ 1/15፣ 1999/12/

 

ታሪካዊ ልብወለድ በመድረስ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ የተወጣው አቤ ጉበኛ ለምን ፊደሎቻችንን እንዳልቀነሰ አብራርቷል፡፡

 

“ፊደሎቻችንን መቀነስ ጠቃሚነቱ ስላልታየኝ በራሴ በኩል አልተከተልሁትም፡፡ ሥራ ለማሳጠር ይጠቅማል፡፡ ስለተባለውም ሥራ ጨምሮ ከማየቴ በቀር ቀንሶ አላገኘሁትም፡፡ በራሴ አስተያየት እንዲያውም ሥራ የሚያበዛ ሆኖ ታይቶኛል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትና በዓለም የታወቁበት ልዩ ሙያቸው የዚሁ ቋንቋ ጥናት የሆነው አሜሪካዊ ዶ/ር ዊልፍሬድ ፊንክ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውስጥ ያለውን አስቂኝ የሆነ የፊደል አቀማመጥ አስቂኝነቱን በሚገልጽ ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

 

ከሁሉ በፊት የፊደሎች አገባብ ሕግና ወሰን የለውም፡፡ ስለዚህ ከዶ/ር ፊንክ ጽሑፍ ጥቂት ብጠቅስ መልካም መስሎ ይታየኛል፡፡ . . . ‹ፊደላችን እንኳ የራሱ የሆኑ ያልተሻሻሉ አስቸጋሪ መንገዶች አሉት፡፡ ዊልያም ፍሬማን ግልጽ እንግዝኛ በተባለ መጽሐፉ ላይ ስለ አስገራሚው ፊደላችን ብዙ ያዋየናል፡፡ እሱ እንደሚለው ከፊደሎቻችን ዐሥሩን አንድ ብቻ ያልሆነ ድምፅ ያላቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ‹a› የምንለው ፊደላችን ሰድስት ድምፅ አለው፡፡ ይኸውም fat, fate, father, swallow, water, any በሚሉት ቃሎች እንደምንጠቀምበት ነው፡፡ በአሜሪካዊ እንግሊዝኛ ‹e› የተባለው ፊደል አራት ድምፆች ይሰጣል፡፡ እነዚህም me, men, clerk, pretty በሚሉት ቃሎች እንደምንጠቀምበት ነው፡፡ ‹i› የሚባለው ፊደልም fin, fine, machine  በሚባሉ ቃሎች እንጠቀምበታለን፡፡ ‹o› እንዲያውም ከቅጥና መጠን ወጥቶ እንደ not, note, bosom, women, also, who ባሉ ቃላት ገብቶ እናገኘዋለን፡፡

 

ድምፅ ተቀባዮቹም (consonants) የራሳቸው ድርሻ የሆነ ልክስክስነት አላቸው ለምሳሌ C እና X ለማንም ጎልቶ እንደሚታየው ዋጋ ቢሶች ስለሆኑ ሊተው የሚገቡ ናቸው፡፡ እንዲሁም ሌሎች b comb በሚለው p receipt በሚል ቃል ላይ እየተደነቀሩ ምንም አገልግሎት ሳይሰጡ ይዘለላሉ፡፡ በመሆኑም ቋንቋችን በብዙ መንገዶች የተዘበራረቀ አስደሳችና ሥነ ሥርዓት የሌለው ነው፡፡

 

ለምሳሌ Ough የሚሉት ፊደሎች ሰባት የተለየዩ ድምፆች አሏቸው፡፡ እነሱም though, bough, rough, through, hough, (hock) hiccough (hiccup) በሚሉት ቃሎች እንደምንጠቀምባቸው ነው፡፡›

 

የቋንቋው ሊቅ ከዚህ ጋር ብዙ መረጃዎችን በመስጠት በራሳቸው ቋንቋ ላይ የሚታዩትን ከፍተኛ ችግሮች ገልጸዋል፡፡ ከታላላቆቹ የእንግሊዝ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች አንዱ ጆርጅ በርናርድ ሾውም፤ ኢጣሊያንኛንና እስፓኝኛን የመሳሰሉት ቋንቋዎች ለሌሎች ሕዝብ በቀላሉ ሊገቡና ሊታወቁ ሲችሉ እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ በአስቸጋሪነታቸው ምክንያት የቋንቋው ባለቤቶች በሆኑት ሕዝብ ዘንድ እንኳ በሚገባ የማይታወቁ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡

 

ይህን ስናይ የኛ ፊደሎች ብዛት ጎጂነቱ የጎላ አይደለም፡፡ ‹ደ› ለማለት (dough) ይህን ሁሉ ፊደል ከማስፈር ‹ደ› ብሎ መሔድ እንዴት ቀልጠፉ ነው) የኛ ፊደሎች ሁሉም ራሳቸውን ችለው ድምፅ የሚሰጡ በመሆናቸው ቁጥራቸው በርከት ስላለ ‹እንደሰማይ ከዋክብት የበዙ› የሚባል የማገናኛ አስተያየት ሲሰጣቸው እንሰማለን፡፡ የሰማይ ከዋክብት እንደዚህ ጥቂቶች ቢሆኑ የከዋክብት አጥኚዎች /አስትሮኖመሮች/ ሥራ ይህን ያህል ከባድ ባለሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን ለማጋነን ነፃ ዕድል ከተሰጠ ዘንድ የኛ ፊደሎች ይሁን እንደሰማይ ከዋክብት የበዙ ናቸው ይባሉ፡፡ ነገር ግን በሌሎች ቋንቋዎች ያሉት ያለሕግ፣ ያለወሰን፣ ያለ ሥራ እንደክፉ ሌባ ስማቸውን እየለዋወጡ የሚያወናብዱት ፊደሎች ደግሞ ከምድር አሸዋና ከሰማይ ከዋክብት በብዛት ይወዳደራሉ ብንል ለኛ አጋናኝነት ይቅርታ ሊደረግለት አይገባምን) . . .የኛዎቹ አራቱ ሆሄያት የምንጠቀምባቸው የግእዝ ቋንቋ ለቃሉ ትርጓሜ መለያ በአማርኛ እንደጌጥ እንደውበት አድርገን ድምፃቸውን ሳይለውጡ እንጂ ‹‹መምህር›› ለማለት እንደሌሎች “መኘምህሕርኅ” እያልን ማለት ኘን፣ ሕን፣ ኅን ያለ ዋጋ ደንጉረን ግራ እያጋባን ስላልሆነ የፊደሎችን መልክ ጠንቅቆ ያጠና ሁሉ እንደልቡ ሊያነብባቸው የሚችሉት ከሚያቀልሉት ከፍተኛ ችግር ጋር ሲመዛዘኑ እንኳን እንደሰማይ ከዋክብት እንደጭብጥ ጥሬ ብዙ ሊባሉ የማይገባቸው ፊደሎቻችን በዚህ መጠነኛ ምክንያት ለመቀነስ ከሌላው ተግባር ቀድሞ የሚያስገድደን ችግር ያለ አይመስለኝም፡፡ . . .ስለዚህ የፊደሎችን ቁጥር ለመቀነስ ያልሞከርኩት ከፍ ብሎ በገለጸኩት ምክንያት ብቻ መሆኑን በትኅትና እገልጻለሁ፡፡ /አንድ ለእናቱ 1985 ዓ.ም/

 

ማጠቃለያ

አራቱ ሆሄያት ትርፎች ሳይሆኑ ቀዋምያን ቅንጣቶች ናቸው፡፡ ራሳቸውን ችለው ትርጉም የሚያስተላልፉ የቃላት መቆሚያ ውኃ ልኮችም ናቸው፡፡

 

በምስጢርም በኩል ያየነው እንደሆነ ንጉሡን “ሠ” ተጠቅመን “ሠረቀ” ብለን ብንጽፍ ወጣ የሚለውን ቃል ያስገኝልናል፡፡ “ሰረቀ” ብለን በእሳቱ “ሰ” ብንጠቀም ሌባ /ሽፍታ/ አንድን ነገር ሰረቀ /ያለፈቃድ ወሰደ/ የሚለውን ትርጉም ያስገኛል፡፡ እነዚህ ኹለት ፊደላት ያለቦታቸው ከገቡ ቋንቋውን ብላሽ ምስጢሩን ፈራሽ ያደርጉታል፡፡

 

አራቱ ሆሄያት ቦታቸውን ጠብቀው ቢቀመጡ የሚፈለገውን መልእክት ማስተላለፍ እንደሚቻል ተመልክተናል፡፡ ተግባራዊነቱን ለማከናወን ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያሉ ጽ/ቤቶች የሚጽፉትን ደብዳቤ አርመውና ትኩረት ሰጥተው ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

የፊደላቱ ጉዳይ ሃይማኖታዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊና ታሪካዊ ምስጢር ያላቸው ናቸው፡፡ ትውልዱ ከሃይማኖቱና ከታሪኩ ጋር ለመተዋወቅ እነዚህ ፊደሎች ያስፈልጉታል፡፡ ተከራካሪዎች እንደሚሉት ፊደሎቹ ተቀንሰው በአንዱ ብቻ ብንጠቀም፤ ሳናውቀው የምናስቀረው ትልቅ ዕውቀት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፊደል ሲቀነስ ዕውቀት ይቀንሳል፡፡ ዕውቀት ሲቀነስ ታሪክ ይጓደላል፤ ታሪክ ሲጓደል ማንነት ይጠፋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ታሪክ ፣ ብሉያቱ፣ ሐዲሳቱ፣ ድርሳናቱ፣ ተኣምራቱ፣ ገድላቱ፣ ቅዳሴያቱ፣ ውዳሴያቱ፣ ዜና መዋዕሉ፣ ቅኔያቱና ሌሎች መጻሕፍት የተጻፉበት የግእዝ ቋንቋ አማርኛን ወልዶ ለዚህ ዘመን በመድረሱ የማንነታችን መገለጪያ የታሪካችን ቅርስ ነውና መልኩን ሳይቀር መቀጠል አለበት፡፡

 

ሆሄያቱ ተቀንሰው በአንድ ሆነው እንጠቀም ብንልና ሆሄያቱ ከተረሱ ብሎም ከጠፉ ቀጣዩ ትውልድ ወደ ኋላ ተመልሶ የሀገሩን ታሪክ ሥነ ጽሑፍና ሌሎች የኪነ ጥበብ ውጤቶችን አንብቦ ለመረዳት እክል /እንቅፋት/ ያጋጥመዋል፡፡ የማያውቀውን ፊደል እንዴት ያነበዋል፤ ያላነበበውን እንዴት ይረዳዋል፤ ያልተረዳውንስ እንዴት ይመረምረዋል?

 

ፊደል ይቀነስ ተብሎ የሆነ ስምምነት ላይ ቢደረስ ከአንድ ትውልድ በኋላ የኢትዮጵያን ታሪክ የያዙ ሃይማኖታዊና ፍልስፍናዊ መጻሕፍትን አንብቦ ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት አስቸጋሪ መሆኑንም ማሰብ ይጠይቃል፡፡

 

ሥርዐተ ጽሕፈትን አስተካክሎ ወጥ የሆነ ሕግ አውጥቶ በማስተማርና በማለማመድ የስካንድኒቪያን ሀገሮች የፈጸሙት ተግባር ጥሩ መፍትሔ አስገኝቶላቸዋል፡፡ ወደ ራሳችን ስንመለስ ችግሩን ለመቅረፍ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ድረስ ሥርዐተ ትምህርት ተዘጋጅቶ ቢቀርብ መልካም ነው፡፡ ሥርዐተ ጽሕፈትን ሳያስተምሩ ለምን ይኸን ሆሄ አልጻፍ<ም ብሎ መኰነኑ አግባብ አይደለም፡፡ ሥርዓተ ጽሕፈቱ በወጉና በሕጉ እንዲሆን ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትን፣ የባህልና ቱሪዝም፣ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች፣ ደራስያንንና ታዋቂ ግለሰቦችን ያቀፈ ውይይት ማካሔድና አንድ ስምምነት ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያናችን በ2005ቱ የመስቀል ደመራ በዓል ያስተጋባችው ድምፅ ቢቀጥል፡፡ በዚህ ዙርያ የተሠሩ ጥናቶች እንደአስፈላጊነቱ እየታዩ ሥራ ላይ ቢውሉ ወደ ተግባርም ቢለወጡ ተጨማሪ ዐውደ ጥናቶች ቢቀርቡ ውይይቶች ቢካሔዱ ለተፈጻሚነቱም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ቢወጡ፡፡ የሆሄያቱ መብት መከበር የታሪክ፣ የባህል የእምነትና የማንነት መብት መከበር ነውና ህልውናቸውን እንጠብቅ፡፡ መልካም ነው፡፡ የተላለፈው መልእክት ጋዜጣ ለሚያዘጋጁ መጽሔት ለሚያሳትሙ እጃቸውን ከወረቀት ላይ ለሚያሳርፉ ሁሉ ነው፡፡ በመሆኑም በቀና ልቡና መልእክቱን ተቀብለን ስንፍናን አስወግደን ወደ ዕውቀት ማእድ ልንሳተፍ ያስፈልጋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ የአራት ቀናት ውሎና ውሳኔዎች

ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስና

በዲ/ን ዩሴፍ ይኲኖ አምላክ


  • አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለአስተዳደር እንዲመች በአራት አህጉረ ስብከት ተከፈለ፡፡

 

ጥቅምት 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተካሔደው ሥርዓተ ጸሎት የተከፈተው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ባሳለፍናቸው አራት ቀናት በስድስት ጠቃሚና ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡

 

በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሕዝብ ግኑኝነት ሓላፊ የሆኑት አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኖች በሰጡት መግለጫ ቅዱስ ሲኖዶስ፡-

  • በሕገ ቤተ ክርስቲያን

  • በቤቶችና ሕንጻ አስተዳደር

  • በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጉዳይ

  • በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደራዊ ጉዳዮች

  • በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ስለሚወከሉ አባቶች

  • የቤተ ክርስቲያንን የውጭ ግኑኝነት

 

በተመለከተ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መወያየቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት፡-

  1. ቤተ ክርስቲያን የምትመራበት ቃለ ዓዋዲ ወቅቱን ባገናዘበ ሁኔታ ለአስተዳደርና ለአሠራር አመቺ ይሆን ዘንድ ማሻሻያ እንዲደረግበት፡፡

  2. በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የሚገኙ ሕንፃዎች በአግባቡ እንዲያዙ፣ ልዩ ልዩ ጉዳት የደረሰባቸው እድሳት እንዲደረግላቸው፣ ባሉት ባዶ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ቤቶች እንዲሠሩና በመንግሥት ተወርሰው ያልተመለሱትን የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕንፃዎች የማስመለሱ ጥረት እንዲቀጥል፡፡

  3. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚታየውን ነባራዊ ሁኔታ ለአስተዳደርና ለአሠራር ምቹ ባለመሆኑ ምክንያት አዲስ አበባ ሰሜን፣ ደቡብ፣ ምእራብ፣ ምስራቅ ተብሎ ለአራት አህጉረ ስብከቶች እንድትከፈል ውሳኔ ተላልፏል፡፡

  4. የጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ምቹና ቀልጣፋ እንዲሆን በባለሙያ ጥናት ተካሂዶ ለግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ፡፡

  5. የግብጽ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 117ኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ ሳልሳዊ ሞት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ 118ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ በተዘጋጀችበት በአሁኑ ጊዜ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉ ጳጳሳት እንዲገኙ በተላለፈው ጥሪ መሠረት አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው እንዲገኙ ተወስኗል፡፡

  6. በቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ሰፊ ሥራ ለመሥራትና ስብከተ ወንጌልን አጠናክራ ለመቀጠል ይቻላት ዘንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመላው ዓለም ለማዳረስ እንዲቻል ወርኀዊ መጽሔት እንዲዘጋጅ ተወስኗል በማለት የሕዝብ ግንኙነት ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ገልጸዋል፡፡

 

የህዝብ ግንኙነት ሓላፊው ከዚሁ ጋር በማያያዝ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በቀጣይነት ስለሚወያይባቸው አጀንዳዎች ሲገልጹ፤

  • ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ዓመታዊ በጀት

  • የሦስት ዓመት ሥልታዊ እቅድ

  • ስለ ሙስናና ተያያዥ ችግሮች

  • ስለ ሀብትና ንብረት አጠባበቅ

  • ስለ አብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማት

  • ስለ ፓትርያርክ ምርጫና የምርጫውን ሕግ ስለመወሰን  እንደሚነጋገር አስታውቀዋል፡፡

 

የህዝብ ግንኙነት ሓላፊው አቶ እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ይህንን መግለጫ ለመስጠት ያስፈለገበት ምክንያት ሲገልጹም አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጠላቶች የተለያዩ አሉባልታዎችን በመንዛት ምእመናንን በማደነጋገር ላይ ስለሚገኙ ምእመናን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚተላለፈውን ውሳኔና መልእክት ብቻ እንዲከታተሉና እውነታውን እንዲረዱ ለማድረግ ታስቦ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  በቀጣይነትም ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎች ተከታትለው ለምእመናን ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል፡፡

 

አራተኛ ቀኑን የያዘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡

Kaleawadi

ቃለ ዓዋዲ

ጥቅምት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ኅሩይ ባ


Kaleawadiቃለ ዓዋዲ ቀጥተኛ ትርጉሙ “የአዋጅ ነጋሪ ቃል” ማለት ነው፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ የአዋጅ ነጋሪ ቃል ብሎ የተነበየለት መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስን ነበር፡፡ /ኢሳ.40፥1፵፥፩/ ከጌታችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዊ ልደት ስድስት ወራትን ቀድሞ የተወለደው ቅዱስ ዮሐንስ ጥርጊያውን እያስተካከለ ሰዎችን ለንስሐ እየጠራ ለአማናዊው በግዕ ለኢየሱስ ክርስቶስ አዘጋጅቷቸዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብም /ቃለ ዓዋዲ/ ሦስቱ ጾታ ምእመናንን/ ካህናት፣ ወንዶች እና ሴቶች/ በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን እየተመሩ ሕይወታቸውን እንዲጠብቁ ስለሚያውጅ ቃለ ዓዋዲ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ ቃለ ዓዋዲ የተባለው መጽሐፍ ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅር ያካተተ የሕግ መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰን ከምእመናን ጀምሮ እስከ ካህናት ድረስ ያሉትን የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች መብትና ግዴታ በውሉ የሚያስገነዝብ መመሪያም ነው፡፡

 

ቃለ ዓዋዲ ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበት የሕግ መጽሐፍ ነው ሲባል፤ ቃለ ዓዋዲ ከመኖሩ በፊት ቤተ ክርስቲያን በምን ትተዳደር ነበር? የሚል ጥያቄ ያስነሣ ይሆናል፡፡ ይህንን ጥያቄ የምንመልሰው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ለረዥም ዘመን በሓላፊነት አገልግለው በሞተ ሥጋ የተለዩንን የአባ አበራ በቀለን የአንድ ወቅት ቃለ ምልልስ መሠረት በማድረግ ነው፡፡ አባ አበራ በቀለ እንዳሉት “ቃለ ዓዋዲ ከመፈጠሩ በፊት ቤተ ክርስቲያናችን ትመራበት የነበረ አስተዳደራዊ መዋቅር አላት ከኒቂያ ጉባኤ በፊትም ቢሆን የአስተዳደር ሥርዓት ነበራት፡፡ ከሁሉ በፊት ግን እንደ ሕግ ሆኖ የሚመራት ዋናው የሕግጋት ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ እርሱም የሃይማኖትና የሥነ ምግባርን ሕግ የያዘ ነው፡፡ በብሉይም ሆነ በሐዲስ ኪዳን ዘመን አባቶቻችን በዚህ ሲገለገሉ እንደ ነበር የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይመሰክራል ወደ ሀገራችንም ስንመጣ ፍትሐ ነገሥቱ ከፍተኛውን ቦታ ይይዛል፡፡

 

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ከአብርሃ ወአጽብሃ ዘመነ ንግሥ ጀምሮ እስከ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ድረስ አንድነት ነበራቸው፡፡ ቤተ መንግሥት ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ይገባ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ወደ መንግሥት አስተዳደር ትገባ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ፍትሐ ነገሥቱ በሁለቱም ወገኖች ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በዓፄ ኀይለ ሥላሴ ጊዜ አዳዲስ ሕጎች ሲወጡ ፍትሐ ብሔሩና ወንጀለኛ መቅጫው ሲወጣ የፍትሐ ነገሥቱ አሠራር እየቀዘቀዘ በአዲስ እየተተካ ሄደ፡፡ እንደሚታወቀው ፍትሐ ነገሥት ሁለት ክፍል አለው እርሱም፡-

 

  • ፍትሕ መንፈሳዊና
  • ፍትሕ ሥጋዊ በመባል ይታወቃል፡፡

 

ፍትሕ መንፈሳዊ አሁንም በቤተ ክርስቲያን ተጠብቆ እየተሠራበት ነው፡፡ የሥጋዊ አስተዳደሩ ደግሞ በቤተ መንግሥት በኩል በሌላ አዋጅ ተተክቷል፡፡”

 

በዓለመ መላእክት፣ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪት፣ መላእክትና ሰዎች እግዚአብሔርን ያመልኩበት የነበረ ሥርዓት አለ፡፡ በዘመነ አበው፣ በዘመነ መሳፍንት፣ በዘመነ ነገሥት፣ በዘመነ ነቢያትና በዘመነ ሐዲስም ይህ ሥርዓት የጸና ነው፡፡ የሥርዓት አስፈላጊነት በመጽሐፍ ቅዱስ ተደጋግሞ የተቀመጠ በመሆኑ አሁንም ለሕንፃ ቤተ ክርስቲያንና ለማኅበረ ምእመናን ሥርዓት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያለ ሥርዓት፣ ያለ ሕግ፣ ያለ ደንብ፣ ያለ መዋቅር የምትሠራው ምንም ዓይነት አገልግሎትና ድርጊት የለም፡፡ ሊቀ ጉባኤ እንዳሉት የሕግ ሁሉ ምንጩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ ፍትሐ ነገሥቱም መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርጎ በፍትሕ መንፈሳዊና በፍትሕ ሥጋዊ ተጣምሮ አገልግሎቱን ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ፍትሕ ሥጋዊ ወደ መንግሥት አስተዳደር ተጠቃልሏል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን ራሷን ችላ የምትመራበት ሕግ እንዲጸድቅላት በጠየቀችው መሠረት ከምእመናን ምጣኔ ሀብታዊ ጋር በተገናዘበ መልኩ ሁሉንም የሚያሳትፍ መዋቅር በሁለተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና የመጀመሪያው ቃለ ዓዋዲ ጥቅምት 14/፲፬ ቀን 1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ታተመ፡፡ ቃለ ዓዋዲው ከመውጣቱ በፊት ረቂቁ  ለፓርላማ ቀርቦ ውይይት ከተካሄደበት በኋላ ለምእመናን እንዲደርስ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ በነጋሪት ጋዜጣ መልክ ወጣ፡፡ ይህ ቃለ ዓዋዲ ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም እስከ 1970/፲፱፻፸ ዓ.ም ለአምስት ዓመታት ያህል እንዳገለገለ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ አያይዘው ገልጠዋል፡፡

 

የቃለ ዓዋዲው ተቀዳሚ ዓላማ

ሀ. ቅድስት፣ ከሁሉ በላይ ሐዋርያዊትና አንዲት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን መጠበቅና አገልግሎቷም የተሟላ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህን ሓላፊነት የሚወጡት ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ድረስ የሚገኙት የሥራ ሓላፊዎች ናቸው፡፡

ለ. የካህናት የኑሮ ደረጃ የተሻለ ሆኖ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸውን በትጋት እንዲወጡ ማድረግ፡፡

ሐ. የምእመናን ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እንዲጨምር እና ያሉትንም በምግባር በሃይማኖት ማጽናት፤ በመንፈሳዊ ዕውቀት እንዲበለጽጉ ማገዝ፤ ሁኔታዎችንም ማመቻቸት፡፡

መ. የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር እንዲሻሻል የገቢ ምንጮችና ልማቶች ተበራክተው በገንዘብ አቅም የጎለበተች ቤተ ክርስቲያን ሆና ከተረጂነት እንድትላቀቅ ማድረግ ነው፡፡

 

እነዚህን ዓላማዎች ግቡ አድርጎ የተመሠረተው ቃለ ዓዋዲ አፈጻጸሙ እንዲሳካ ከምእመናን ጀምሮ ሥልጣነ ክህነት እስካላቸው አገልጋዮች ድረስ የሠመረ ግንኙነት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ በዚህ ዘመን ምእመናን ስለ ቃለ ዓዋዲ ያላቸው ግንዛቤ በጣም አነስተኛ ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ጉዞ ምቹ መሆን የካህናት ድርሻ ብቻ የተሟላ አያደርገውም፡፡ የምእመናንም ድርሻ ከፍተኛውን ድርሻ መያዝ አለበት፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለተወሰኑ አካላት ብቻ የማንተወው በመሆኑ የእነሱና የእነሱ ሓላፊነት ብቻ እንደሆነ ማሰብ የለብንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሦስቱም ጾታ ምእመናን ናትና ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፡፡

 

ቃለ ዓዋዲ ተደንግጎ ጸድቆ ሰበካ ጉባኤ ተቋቁሞ በሥራ ላይ ውሎ አሁን ካለበት ደረጃ ለመድረስ በርካታ ፈተናዎችን አልፏል፡፡ በ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራን ጨምሮ የተለያዩ እንግዶችን በመጥራት የመጀመሪያውን የቃለ ዓዋዲ ረቂቅ ለውይይት አቅርበዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በሸዋ ሀገረ ስብከት በዐሥራ አንድ አውራጃዎች እየተዘዋወሩ ስለ ቃለ ዓዋዲ ለካህናትና ለምእመናን ማብራሪያ በመስጠት አዲሱን እቅድ አስተዋውቀዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ልኡካንን መድበው በየአህጉረ ስብከት እየተዘዋወሩ እንዲያስተምሩ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

 

ሆኖም ካህናቱና ምእመናኑ ተወካዮችን መርጠው ሰበካ ጉባኤና ቃለ ዓዋዲ የሚባል በባህላችን የማይታወቅ አዲስ አሠራር መጣብን ብለው ለንጉሠ ነገሥቱ /ኀይለ ሥላሴ/ አቤቱታ እስከማቅረብ ደርሰው ነበር፡፡

 

ይህንና የመሳሰሉትን ችግሮች ተሻግሮ በአገልግሎት ላይ የሚገኘው ቃለ ዓዋዲ ለመጀመሪያ ጊዜ ታትሞ ከወጣበት ከ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ጀምሮ ለ5/፭ ዓመታት አገልግሎ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም የተለያዩ ማሻሻያዎች ታክለውበት ለሁለተኛ ጊዜ ታትሟል ከ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም እስከ 1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም መግቢያ ድረስ ለሃያ አንድ ዓመታት ያገለገለው ቃለ ዓዋዲ ዳግመኛ ተሻሽሎ ለሦስተኛ ጊዜ በ1991/፲፱፻፺፩ ዓ.ም ታትሟል፡፡

 

ጥቅምት 7-11/፯‐፲፩ ቀን 2004/፳፻፬ ዓ.ም 30/፴ኛው መደበኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ የመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ የኢሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ አሳሳቢነት ቃለ ዓዋዲው ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል አሳብ አቅርበዋል፡፡ ምልዓተ ጉባኤውም ቃለ ዓዋዲው ተሻሽሎ እንዲወጣ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል፡፡ የጉባኤው የውሳኔ አሳብ የሚፈጸመው በቅዱስ ሲኖዶስ ይሁንታ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ የጉባኤውን የውሳኔ አሳብ እንዲመለከተው ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡

 

በ1965/፲፱፻፷፭ ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የወጣው ቃለ ዓዋዲ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም ተሻሽሎ የወጣበት ምክንያት በተለይ በ1966/፲፱፻፷፮ ዓ.ም በሀገራችን የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረቷን መንግሥት በውርስ ሲወስደው የገቢ ምንጮች ደረቁ፡፡ የኮሚኒስቱ ፓሊሲ ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የማይመችም ነበር፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች በመንግሥት ተወረሱ፡፡ በመጀመሪያው ቃለ ዓዋዲ ስለ መሬት ርስትና ስለ ቤት ኪራይ የሚናገር አንቀጽ ነበረው፡፡ ይህ ድንጋጌ ለደርግ መንግሥት ጥቅም አላስገኘለትም፡፡ ስለዚህ ተስፋፍቶና ተሻሸሎ እንዲታተም ግድ በመሆኑ በ1970/፲፱፻፸ ዓ.ም በሚያዝያ ወር ተሻሽሎ ወጣ፡፡

 

ለሦስተኛ ጊዜ በ1991/፲፱፻፺፩ ተሻሽሎ እንዲታተም ያስፈለገበት ምክንያት ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡ ካህናትና ዲያቆናት ለመሆን የበቁ አገልጋዮች በዘፈቀደ ሳይሆን በደብሩ አስተዳዳሪ ተመስክሮላቸው የትምህርት ደረጃቸው ታይቶ ክህነቱን እንዲቀበሉ፣  ወጣት ዲያቆናት ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት እየገቡ እንዲማሩና ካህናቱም የሰንበት ትምህርት ቤቶች መርሐ ግብርን ከሚያስተምሯቸው በተጨማሪ በጸሎት ጀምረው በጸሎት እንዲዘጉ፣ የቤተ ክህነት አገልጋዮች ዕድሜ ጣራ 60/፷ ዓመት እንዲሆን፣ ከደመወዛቸውም ከመቶ እጅ የተወሰነ እንዲከፍሉ፣ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ፣ ሥራ አስኪያጅ ሥልጣንና ተግባር የወረዳው ቤተ ክህነት ሊቀ ካህናት ሥልጣንና ተግባር እያለ በመጠኑ የተገለጸውን ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ከቅዱስ ፓትርያርኩ የሚጠበቀውን ሥልጣንና ተግባር በስፋት አብራርቶ ለማስቀመጥ ታስቦ ነው፡፡

 

በ2004/፳፻፬ ዓ.ም 30/፴ኛው መደበኛ አጠቃላይ ዓመታዊ ጉባኤ ሲካሄድ ለአራተኛ ጊዜ እንዲሻሻል ያስፈለገው በቃለ ዓዋዲው እየታየ ያለው የሕገ ቤተ ክርስቲያን ክፍተት ነው፡፡ ለምሳሌ ቤተ ክርስቲያን በቋሚ ሠራተኛነት ቀጥራ ከምታሠራቸው ሠራተኞች መካከል ጥቂቶቹ ገንዘብ ሲያጎድሉ በቤተ ክህነት ሒሳብ መርማሪዎች ኦዲት ተደርገው ባለዕዳ መሆናቸው ሊረጋገጥ ይችላል፡፡ ዕዳቸውን መክፈል ያልቻሉትን ሕገ ወጥ ሠራተኞች በፍርድ ቤት ለመክሰስ አግባብ ባለው የሕግ አካል ቢጠየቁም የቤተ ክህነት ሒሳብ መርማሪዎች የሒሳቡን ሥራ ለማከናወን ሕጋዊ ዕውቅና የላቸውም? የሚል መከራከሪያ በማንሣት ጉዳያቸው በፍጥነት እንዳይታይና እልባት እንዳይሰጠው ይከራከራሉ፡፡ በቃለ ዓዋዲው ሕገ ደንብ ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ባሉት መዋቅሮች የሒሳብ በጀት ክፍል ስላለ በዚህ ክፍል ሒሳቡ እንዲመረመር ያዛል፡፡

 

በመሆኑም ቃለ ዓዋዲ የሒሳብ ጉዳዮችንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተነተነበት አንቀጹ ለፍትሕ መንፈሳዊና ለፍትህ ሥጋዊ በማያሻማ ሐተታ ቢብራራ አግባብ ባለው የሕግ አካል ለመክሰስም ሆነ ለመጠየቅ ያስችላል፡፡

 

የቃለ ዓዋዲ ሕገ ደንብ ለምእመናን ለካህናትና ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ያለው ጠቀሚታ የጎላ ነው፡፡ በሥርዓተ ተክሊል በቅዱስ ቁርባን የተጋቡ ባለትዳሮች ቢጋጩ ወደ ፍርድ ቤት ከሚሔዱ ይልቅ በፍትሕ መንፈሳዊ ቢዳኙ ምንኛ ደስ ይላል፡፡ ካህናትም የቃለ ዓዋዲውን ሕገ ደንብ ጠብቀውና አስጠብቀው ዐሥራት በኩራቱን ሰብስበው ራሳቸውንና ቤተ ክርስቲያንን ወደ ተሻለ እድገት ቢያሸጋግሩበት መልካም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተቃና እንዲሆን እንደ ቃለ ዓዋዲው ድንጋጌ ሓላፊነትን መወጣት ከተቻለ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን ካለባት አስተዳደራዊ ችግር መላቀቅ ትችላለች፡፡

 

ባለፈው ዓመት ቃለ ዐዋዲው እንዲሻሻል የቀረበው አሳብ መክኖ እንዳይቀር ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሕገ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ከተሻሻለ መዋቅሮቻችን ከተጠናከሩ አገልጋዮችም በሞያቸው በሓላፊነትና በተጠያቂነት መሥራት የሚችሉት የደንባችን አጥር ሲጠብቅ ነው፡፡

 

ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፡፡ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም ለሁሉም ናት፡፡ ማንም ቢመጣ ማንም ቢሄድ ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ታሳልፋለች፤ እሷ ግን አታልፍም፡፡ እኛ ብናልፍ ሥራችን ሕያው ምስክር ሆኖ እንዲኖር በሕጋችን መሻሻል ላይ በደንብ እንምከርበት፣ በሚገባ እናስብበት፣ በብስለት እንወያይበት፡፡ በምክክራችን ጊዜ ባለሞያዎችን እናሳትፍ፤ ለነገዋ ቤተ ክርስቲያን አዲስና ብሩህ ተስፋ ዛሬን እንሥራበት፡፡

 

“በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመበት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” /ሐዋ.20፥28/፳፥፳፰

 

እግዚአብሔር አምላካችን ቤተ ክርስቲያናችንን ከጥፋት ይጠብቅልን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል

ማእከሉ ጠቅላላ ጉባኤውን ሊያካሂድ ነው

ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤውን የፊታችን ቅዳሜና እሑድ እንደሚያካሂድ የማእከሉ ዋና ጸሐፊ አቶ ካሳሁን ኀይሌ አስታወቁ፡፡ ቅዳሜ ጥቅምት 17 ቀን 2005 ዓ.ም ከሰዓት በፊት በሚኖረው የመክፈቻ  መርሐ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስን ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ፣ የሀገረ ስብከቱ የመምሪያ ሓላፊዎች፣ የአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የዋናው ማእከል ተወካይ፣ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሊቃነ መናብርት ከየግቢ ጉባኤያትና ከሠራተኛ ጉባኤያት የሚወከሉ ተወካዮች እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ ካሣሁን፡- “የ2004 ዓ.ም የሥራ አፈጻጻምን መገምገም፣ በጸደቀው የማኅበሩ መሪ ዕቅድ ላይ ተመሥርቶ የተዘጋጀውንና ከጥር 1 እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2005 ዓ.ም የሚያገለግለውን ዕቅድ ተወያይቶ ማጽደቅ በዋነኝነት በዚህ ጉባኤ የሚፈጸሙ ተግባራት ናቸው” ብለዋል፡፡

 

ጉባኤው  በሁለት የመወያያ ርዕሶች ላይ እንደሚመክር የታወቀ ሲሆን፤ ከ800 እስከ 1200 የሚደርሱ የማእከሉ አባላት እንደሚታደሙበት ከማእከሉ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

700 ምእመናን ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ተመለሱ

ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በቄለም ወለጋ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ አማካኝነት፥ ለ31ኛው ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አጠቃላይ መንፈሳዊ የሰበካ ጉባኤ የቀረበው ሪፖርት፤ ለ28 ዓመታት ያህል በሰዩ ወረዳ ሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንና በአጥቢያው የሚገኙ ምእመናን ከእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናቸው በመለየት የቆዩትን ሁለት ቀንደኛ የተሐድሶ መናፍቃን መሪዎች ተውግዘው  መለየታቸውን አመለከተ፡፡

 

በተሐድሶ መናፍቃን ሴራ በየዋህነት የተወሰዱ ምእመናንን በንስሐ  ለመቀበልና መናፍቃኑ “የሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ምክር ቤት ” በሚል ስያሜ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የተነጠሉትን በብፁዕ አቡነ ሄኖክ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ትዕግሥት የተሞላበት በሳል አመራር የሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንን ለማስመለስ ስድስት ወራት መውሰዱን ሥራ አስኪያጁ መጋቤ ሐዲስ ለማ በየነ  አስረድተው፤ ምእመናኑ ባለማወቅና በመናፍቃኑ ስውር ሴራ ተታለው ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው መቆየታቸው እንዳሳዘናቸውና በመጨረሻ ግን የተለዩአትን እናት ቤተ ክርስቲያንን ለመቀላለቀል መቻላቸው እንዳስደሰታቸው በመግለጽ፡- “የሰባክያነ ወንጌልና የአገልጋይ ካህናትን ችግር ለመቅረፍ በመላው ዓለም የሚገኙ የቅድሰት ቤተ ክርስቲያን የቁርጥ ቀን ልጆች ከሀገረ ስብከቱ ጎን በመቆም የተቻላቸውን ድጋፍ እንዲያበረክቱልን በታላቅ ትሕትና እጠይቃለሁ” ብለዋል፡፡

 

በመናፍቃኑ ተታለው የቆዩት ምእመናን መጋቢት 19 ቀን 2004 ዓ.ም በሹሻ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን መጽሐፈ ቄደር በተደረሰበት ማየ ንስሐ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት ተቀላቅለዋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ቢያደርገው የምንላቸው ነጥቦች

ጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

 

ቅዱስ ሲኖዶስ ኤጲስ ቆጶሳት የያዘውን፣ የታወቀ ሕጋዊ መንበር፣ ታሪካዊና ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ሆኖ የተደራጀውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምልዐተ ጉባኤ ነው፡፡ ይህ ምልዐተ ጉባኤ ለአንዲቷ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ልዕልና እጅግ አስፈላጊና አንድ ነው፡፡

 

አስፈላጊነቱም የሚመነጨውና የሚረጋገጠው በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ በመሆኑና ውሳኔዎች ሁሉ ይግባኝ የሌለባቸው ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ ሐዋርያት ከክርስቶስ፤ ሐዋርያነ አበውና ሊቃውንት ከሐዋርያት፣ እኛም ከእነዚህ ሁሉ የወረስናቸውን መሠረተ እምነት፣ ሥርዐተ አምልኮና ትውፊት የሚጠብቅና የሚያስጠብቅ ዐቃቤ ሃይማኖት ነው፡፡

 

በዚህ መነሻነት የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት በዓመት ሁለት ጊዜ ይሰበሰባል፡፡ በጥቅምትና በግንቦት ርክበ ካህናት፡፡ በሁለቱም ጉባኤያት በመንፈስ ቅዱስ መመራቱንና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ መሆኑን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንዲያሳልፍ ይጠበቃል፡፡ የሚወሰነውም ውሳኔ እንከን እንዳይኖርበት በፍጹም መንፈሳዊነት ተገቢ ጥንቃቄም እንዲያደርግ ይጠበቃል፡፡

 

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ እንዲሁም እንደ አስፈላጊነቱ ልዩ ስብሰባ በማካሄድ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና፣ አመራር፣ አስተዳደር፣ እርምጃና ፖሊሲ ሁሉ የሚወሰን የመጨረሻው አካል እንደመሆኑ ምልዐተ ጉባኤው ፍሬያማና ውጤታማ ተግባራት የሚከናወኑበት ሊሆን እንደሚገባም ይታመናል፡፡

 

በዚሁ መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን በምልዐተ ጉባኤው ውሳኔና የውሳኔ አፈጻጸም ተጠቃሚ መሆኗ እንዲረጋገጥ አጥብቀን እንሻለን፡፡ በተነጻጻሪም ከጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሔድ የሚጠበቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ይህን እውን ሆኖ እንዲያሳየን ይጠበቃል፡፡ አጀንዳውም ከዚህ አንጻር ቢቃኝ ተገቢ ነው፡፡

 

በዚህ የአጀንዳ ቅኝት ተገቢነትና ወቅታዊነት አግባብ በአጀንዳነት ተወያይቶበት ውሳኔ እንዲያሳልፍባቸው እንደ ልጅነት የምንሻቸው አጀንዳዊ ውሳኔዎች ውስጥ ዐበይቶቹ በአምስት ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ እርቀ ሰላምና የስድስተኛው ፓትርያርክ ሹመት አጠቃላይ አፈጻጸም፣ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የሚሻሻልበትንና ቤተ ክርስቲያናችን ቋሚ የምርጫ ሕግ ባለቤት የምትሆነበትን አገባብ መወሰን፤ ተግባሩና ሓላፊነቱ በግልጽ የተቀመጠለት የቴክኒክ አካል መሰየምና በአምስተኛ ዘመነ ፕትርክና በይደር በተያዙ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ እንዲወሰን የቤተ ክርስቲያን ልጅነት አሳባችንን እናቀርባለን፡፡

 

ከእነዚህም በተጨማሪ ከአምስተኛው ፓትርያርክ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ዕረፍት በኋላ በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክነት የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ናትናኤልም ሆኑ የቋሚ ሲኖዶሱን አፈጻጸም መገምገምና ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገቡ ክስተቶች ላይም ውሳኔ ከመስጠትም በላይ ቀጣዩን የአተገባበር ፍኖተ ካርታ /Roadmap/ ተጠያቂነት በሚያጎናጽፍ አግባብ ቢያስቀምጥ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት ገንቢ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን፡፡

 

ምእመኑም ትናንት የቅዱስ ሲኖዶስን የምሕላ ዓዋጅ ተቀበሎ እንደመፈጸሙ ቀጣዩንም ውሳኔዎቹን መፈጸም ይገባዋል፡፡ ከአባቶቻችን ጎን በመሆን የልጅነት ድርሻውን ቢወጣ እንላለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያናችን በኲለንታዋ ወደቀደመ ክብሯና ልዕልናዋ እንድትመለስ የምልዐተ ጉባኤው ድርሻ በሙቀተ መንፈስ ቅዱስ ዘመኑን የዋጀ ውሳኔ መወሰንና አተገባበሩን መከታተል፤ የቤተ ክህነቱ መዋቅር ድርሻ ውሳኔዎቹን ማስፈጸምና ምቹ መደላድል መፍጠር ሲሆን የምእመኑ ድርሻ ደግሞ ለውሳኔው ተፈጻሚነት ምልዐተ ጉባኤውንም ሆነ የቤተ ክህነቱን መዋቅር በሁሉም መደገፍ ያስፈልጋል፡፡

 

ስለዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔን መቀበል የቤተ ክርስቲያናችን የአንዲትነት፣ ሐዋርያነት፣ ቅድስትነትና ኲላዊነት መገለጫ ነውና ውሳኔዎቹን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት ዝግጁ እንድንሆን ያስፈልጋል፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


  • ምንጭ፡- ጽምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 3 ከጥቅምት 16-30 2005 ዓ.ም.