ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም.
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

ጳጉሜን፡- “ጭማሪ፣ ተወሳክ፣ አምስት ቀን ተሩብ” የሚል ትርጉም አለው፡፡ ጳጉሜን 13ኛ ወር ትባል እንጂ በውስጧ የያዘቻቸው ቀናት ቁጥር በአንድ ሳምንት ካሉ ቀናት ያነሱ ናቸው፡፡ እንደዚያም ሆኖ ኢትዮጵያን ብቸኛዋ የዓለማችን ባለ 13 ወራት ሀገር እንድትሆን ያስቻለች ልዩ ወር ናት፡- ወርኀ ጳጉሜን፡፡
ጳጉሜን ገዝፋና ጎልታ የምትታየው በመንፈሳዊ ዓለም ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋ ትታሰባለች፡፡ በዚህ የተነሣ በርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ወርኀ ጳጉሜን በጾምና በጸሎት /በሱባኤ/ ያሳልፏታል፡፡ በተለይም እንደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በቅዱስ ሩፋኤል ዕለት ሰማያት የሚከፈቱበት /ተርኅዎ ሰማይ/ መሆኑን በማመን ምእመናን ወደ ፈፍላጋት በመሄድ እንዲሁም በጳጉሜን ቀናት በሚዘንበው ዝናብ በመጠመቅና በረከትን ይሻሉ፡፡ ጸሎታቸውንም ከምንገባም በበለጠ ያቀርባሉ፡፡
ወርኀ ጳጉሜን የጌታችን ምጽአት የሚታሰብባት በመሆኗ የሚዘመረው መዝሙር፣ የሚነበቡ ምንባባትና ቅዱስ ወንጌሉ እንዲሁም የሚሰበከው ምስባክ ይህንኑ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ከነዚህም ውስጥ፡-
“ከመ እንተ መብረቅ ዘይወፅእ እምጽባሕ ወያስተርኢ እስከ አረብ ከማሁ ምጽአቱ ለወልደ እግዚአብሔር ምስለ ኀይለ ሰማያት በንጥረ መባርቅት/ከ/ ምስለ አእላፍ መላእክት /ከ/ ወኲሎሙ ሊቃነ መላእክት /ከ/ አክሊለ አክሊላት ዲበ ርእሶሙ” ይህም ማለት፡-
“መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንዲታይ በመባርቅት ፍጥነት፡ – ሰማያውያን ኀይላት ከብዙ መላእክትና የመላእክት አለቆች ጋር በካህናት ራስ ላይ ያሉት አክሊሎች መገኛ የሆነው የሾህ አክሊል ደፍቶ የእግዚአብሔር ልጅ እንዲሁ ይመጣል” ማለት ነው፡፡
በየዓመቱ ጳጉሜን ሦስት ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓልም በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት፣ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ይህም ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከከበሩት ቅዱሳን መላእክት ሦስተኛው ነው፡፡ መጽሐፍ፡- “ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ” እንዲል፡፡ /ጦቢት 12፥15/
መላእክት ሲፈጠሩ የማይሞቱ፣ የማይራቡ፣ ጾታ የሌላቸው ዝንተ ዓለም በቅድስና ጸንተው እንዲያገለግሉና ፈጻምያነ ፈቃድ እንዲሆኑ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት ከአንዱ ዲያብሎስና ከተከታዮቹ አጋንንት በቀር ቅዱሳን መላእክት ሁሉ በተፈጠሩበት ዓላማ ጸንተው ያሉና የሚኖሩ ናቸው፡፡ በዚሁ አገልግሎታቸውም የእግዚአብሔርንና የሰውን በጎ ፈቃድ ሲፈጽሙ ይኖራሉ፡፡ ያለማቋረጥ ፈጣሪያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት አንዱ መልአከ ጥኢና ወሰላም /የሰላምና የጤና መልአክ/ የሚባለው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡
“ሩፋኤል” የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡
በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ሆነ ቁስል ይፈወስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ “በሰው ቁስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው” መጽሐፈ ሄኖክ 6፥3 ይላል፡፡ ለቆሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው ለማሕጸን ችግር ሁሉ ለሴቶች እረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም ሕፃኑ አርባ ቀን ሞልቶት፣ በማሕፀን እያለ “ተስእሎተ መልክዕ” /በሥላሴ አርአያ መልኩ መሳል ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ/ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በወሊዳቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማሕፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡
ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነት ያለን ረቂቅ ርኩስ መንፈስ ያውቃል፡፡ አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ጭን ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል፡፡ /ጦቢት.3፥8-17/
“ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው” /ሄኖክ 3፥5-7/ በዚህ መሠረት ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ /ሄኖክ፤2፥18/ የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ “በበሽታ ሁሉ ላይ በሰው ልጆችም ቁስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡” በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል፡፡ /ሄኖክ.10፥13/
የጦቢትን ልጁ ጦቢያን በሰው አምሳል ተገልጦ ከተራዳው በኋላ ወደ ሰማይ በሚያርግበት ጊዜ ራሱን ሲገልጥ “የቅዱሳንን ጸሎት ከሚያሳርጉ ወደ ከበረ ወደገነነ ወደ እግዚአብሔር ጌትነትም ከሚያገቡ ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ አላቸው” /ጦቢት.12፥15/
የቅዱስ ሩፋኤል በዓሉ የሚከበርባቸው ምክንያቶችም ሁለት ናቸው፡፡ እነርሱም አንደኛው በዓለ ሢመቱን ምክንያት በማድረግ ሲሆን ሁለተኛው የቅዳሴ ቤቱ የተከበረበት ስለሆነ ነው፡፡ ይኸውም በመጽሐፈ ስንክሳር እንዲህ ተመዝግቧል፡፡ ከእስክንድርያ አቅራቢያ በምትገኝ በደሴት የታነጸች ቤተ ክርስቲያኑ በከበረ ሊቀ ጳጳሳት ቴዎፍሎስ ዘመን በውስጧ ተአምር የተገለጸባት የከበረችበት ነው፡፡
ይህም እንዲህ ነው፤ ሀብትም ሴት ወደ ሊቀ ጳጳሳት አባ ቴዎፍሎስ መጥታ ሳለ ከእርሷ ጋርም ብዙ ሰው ነበረ፡፡ ከባሏም የወረሰችው ብዙ ገንዘብ አላት፡፡ በሊቀ ጳጳሳቱ ቤት አንጻር ያለውን ኮረብታ አስቆፈረችው በዚያም የወርቅ መዝገብ ተገለጠ፡፡ በዚያም ወርቅ ብዙዎች አብያተ ክርስቲያናትን አነፀ፤ ከእርሳቸውም አንዲቱ የመላአክት አለቃ በሆነ በከበረ መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል በስሙ የታነፀች ይህች ናት፡፡ ሥራዋንም በፈጸመ ጊዜ እንደዛሬው በዚች ቀን አከበራት፡፡ ብዙ ምእመናንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያሉ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈጽማ ተናወጸች፤ ያቺ ደሴት በታላቅ አንበሪ ጀርባ ላይ የቆመች ናትና፡፡ የሰዎች ብዛትም በከበደው ጊዜ ቤተ ክርስቲያኒቱን ያፈርሳት ዘንድ ሰይጣን አነሣሣው፡፡ ወደ ክብር ባለቤት እግዚአብሔርም በከበረ መልአክ ሩፋኤል ስም ጮሁ፡፡ ያን ጊዜ ይህ የከበረ ሩፋኤል ያንን አንበሪ በጦሩ ወግቶ እንዲህ አለው “እግዚአብሔር አዝዞሃልና ከቦታህ ሳትናወጽ ጸጥ ብለህ ቁም!” አንበሪውም ጸጥ ብሎ ቆመ፡፡ አልታወከም፡፡ በውስጧም ድንቆች ተአምራቶች ተገለጡ ለሕሙማንም ፈውስ ሆነ” ይላል፡፡
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን በወርኀ ጳጉሜን ከሚታሰቡት እና ከሚከበሩት በዓላት መካከል ጳጉሜን 2 ቀን የሐዋርያው ቅዱስ ቲቶ በዓለ ዕረፍቱ፣ እንዲሁም ጳጉሜን 5 ቀን የነቢዩ አሞጽ ዕረፍት ይጠቀሳሉ፡፡
ፈጣሪያችን ከሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል እና ከቅዱሳኑ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡