መጪውን ጊዜ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” መዋጀት

መስከረም 18 ቀን 2005 ዓ.ም.


ጊዜ ይመጣል ጊዜ ይሄዳል፡፡ ጊዜ መጥቶ ሲሄድ ግን እንደው ዝም ብሎ አይደለም፡፡ የጊዜውን አሻራ አሳርፎ ነው፡፡ አሻራው ግን አዎንታዊም አሉታዊም ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ምርጫው በጊዜ መጠነ ክበብ ውስጥ ያለው የሰው ልጅ ነው፡፡

 

የሰው ልጅ ደግሞ በጊዜያት ውስጥ የረቀቀና የገዘፈ ዓለም ባለቤት ሆኖ የተፈጠረና ጊዜ የማይቆጠሩላቸው የሥሉስ ቅዱስ ፍጡር ነው፡፡ በሕያውነቱ ረቂቁን ዓለም- ዓለመ ነፍስን መስሎና ሆኖ ሲኖር፤ በምድራዊነቱ ግዙፉን ዓለም- ዓለመ ሥጋን በተዋሕዶ ነፍስ መስሎና ሆኖ ይኖራል፡፡ በዚህም የሁለት ዓለም ባለቤት ነው፡፡ የሰማያዊና ምድራዊ ወይም የመንፈሳዊና ዓለማዊ፡፡

 

እንዲህ ሆኖ ሲፈጠር በነጻ ምርጫው እንዲኖር የሚያስችለው ነጻ አእምሮ የተቸረው ብቻ ሳይሆን የምርጫውን ተገቢነትና ትክክለኛነት የሚያረጋግጥበት አእምሮ የተሰጠውም ባለጸጋ ፍጡር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

በረጅሙ የጊዜ ሂደት ውስጥ ከግዙፉ ዓለም- ዓለመ – ሥጋ፤ ግፊት አንጻር መውደቅ መነሣቱ አይቀሬም ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገርም መውደቁ ሳይሆን ወድቆ አለመቅረቱ – መነሣቱ ነው፡፡ ሃይማኖተኛ የሚያሰኘውም ይኼው የመነሣት ጉዞ አካል የሆነው መንፈሳዊነቱ ነው፡፡

 

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምትገለገለውም የምትጎዳውም በዚሁ ፍጡር ነው፡፡ የመውደቅ መነሣቱም ሰንኮፍ አሐቲ፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊት፣ ኲላዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጥላውን ማሳረፉ አይቀሬ ነው፡፡

 

በዚህ ወቅት በምድር ያለችው ሰማያዊ ቤታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በልዩ ልዩ ሰብዓዊ ግፊት በወለዳቸው እኲያት እየተፈተነች ነው፡፡ ከውጪ ከሥጋ በሆኑ በሉላዊነትና የዚህ ውጤት በሆኑት በዘመናዊነት፣ ዓለማዊነት፣ ለዘብተኝነት እየተፈተነች መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

 

በተለይ ከሰሞኑ ከፓትርያርክ አሰያየም ጋር ተያይዞ ለአስቀመጡት የጥፋት ግብ አባቶችን፣ ሊቃውንቱንና ምእመኑን ለመከፋፈል ዓላማ እንዲረዳቸው አጽራረ ቤተ ክርስቲያን ወንዛዊነትን – ጎጣዊነትንና – ዘውገኝነት የቤተ ክህነነቱ ባሕርያዊ ቁመና ለማድረግ ሲውተረተሩ መገንዘብ ችለናል፡፡

 

እነዚህ የክፍፍልና የልዩነት ዐውድማዎች የከፋ ጥፋት ከማድረሳቸው በፊት የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” በወለደው ጥብዓት በቃችሁ ሊባሉ ይገባል፡፡ የሃይማኖት ብሔርተኝነት መነሻው አገራችን በሰማይ፤ ኑሮአችን በዓለመ ነፍስ ከመሆኑ ላይ ነው፡፡ የሃይማኖት ብሔርተኝነት ሲባልም ሃይማኖትን በሃይማኖት እናት፣ አባትና ብሔር አድርጎ መውሰድ ወይም በአጭሩ የሃይማኖት ወገንተኛ ማለት ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ወንዝ- ጎጥና- ዘውግ ዘለል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” በቤተ ክርስቲያናችን የነበረና የቆየ ማእከለ አንድነት እንጂ አዲስ ክስተት አይደለም፡፡ ለዚህም ትንታኔያችን ማሳያው ሁለት ነው፡፡

 

የመጀመሪያው ምድረ ሙላዱ /መካነ ሙላዱ/ ከኢትዮጵያ ያልሆነው እና ከኢትዮጵያ ተልኮ ሄዶ ከእስክንድርያው ፓትርያርክ በቅዱስ አትናቴዎስ ዘንድ ኤጲስ ቆጶስ ሆኖ ተሾሞ የመጣው ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ነው፡፡ በአራተኛው መቶ ዓመት “ቅዱስና ያለ ተንኮል የሚኖር ነውርም የሌለበት ከኀጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ያለ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባናል” /ዕብ.7፥26/ ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ ሊቀ ካህንነት እንደተናገረው፤ ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ከሾማቸው ከሐዋርያት ሐረገ ክህነት ተያይዞ የመጣ የሐዋርያት ተከታይ የሆነ ሊቀ ካህናት ማግኘት ይገባል ብላ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳስ እንዲያስመጣላት ቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማን ወደ እስክንድርያ ስትልክ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እንጂ በወንዛዊ- በጎጣዊ- በዘውጋዊ ብሔርተኝነት አይደለም፡፡ ቅዱስ አትናቴዎስ የእስክንድርያው ፓትርያርክም ራሱኑ /ቅዱስ ፍሬምናጦስን/ ሾሞ የላከው በጎጠኝነት- በዘውገኝነት- በወንዘኝነት ሳይሆን በሃይማኖት ብሔርተኝነት መሆኑን ማስታወስ እንወዳለን፡፡

 

ሁለተኛው ምድረ ሙላዳቸው ከኢትዮጵያ ያልሆኑ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን /479 ዓ.ም. አካባቢ/ የሮማ ግዛት ከነበሩ ልዩ ልዩ አገሮች ዘጠኝ ቅዱሳን ወደ አገራችን መምጣት ነው፡፡ ተሰዐቱ ቅዱሳን በእምነት መሰሎቻቸው የሆኑ ክርስቲያኖች ወደሚኖሩባት ሀገር ወደ ኢትዮጵያ ተሰደው ሲመጡ ከነትምህርታቸው ቅድስናቸውን የተቀበልነው፤ እነርሱም በስደት በሚኖሩበት አገር ሥርዐተ ምንኩስናን ያስፋፉት፤ ገዳማዊ ሕይወትንና ምናኔን ያስተማሩት፣ ገዳማትን በየቦታው ያቋቋሙትና ያልተተረጎሙትን መጻሕፍት ወደ ግእዝ የተረጎሙት በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እንጂ በወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት አለመሆኑን ማስታወስ እንፈልጋለን፡፡

 

በዚህ መልኩ የመጣውን ሥርዐተ ሢመት በሥጋዊና በደማዊ ፍላጎት ማጉደፍ ሥርየት የሌለው በደል ነው፡፡ ትናንት አባቶቻችን በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ቤተ ክርስቲያናችን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ጥገኝነት ተላቃ ራሷን እንድትችልና ከራሷ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እንድትሾም ብርቱ ተጋድሎ ያደረጉት በወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት እንድንራኮትበት ሳይሆን በሃይማኖት ብሔርተኝነት ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንድናሸጋግራት ነበር፡፡

 

ትናንት አባቶቻችን በወንዝ- በጎጥ- በዘውግና ቋንቋ ሳይቧደኑና ሳይደራጁ በሃይማኖት ብሔርተኝነት ጳጳሳትን ሾመዋል፤ ሞያና ሞያተኛን አገናኝተው የአገልግሎት ምደባ አድርገዋል፡፡ ከብሔርና ነገድ በላይ ለሃይማኖት ብሔርተኝነት ተገቢውን ዋጋና ክብር ሰጥተው ቤተ ክርስቲያናቸውንና መንጋቸውን በጥብዓት በመንኖ ጥሪትና በትግሃ ሌሊት አገልግለው ላያልፉ አልፈዋል፡፡

 

አስቀድመን ለመግለጽ እንደሞከርነው ዛሬ ከሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ይልቅ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ብሔርተኝነቱ ገንኖ ወጥቷል፡፡ ብርቱ የተባሉትን ሁሉ እየቆረጠ ሲጥል እያስተዋልንም ነው፡፡ በዚህም የተነሣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሢመት የሚታጩ አበው መንፈሳዊ ሕይወታቸው፣ ሞያዊ ብቃታቸው፣ የአመራር ክሂሎታቸው፣ ዐቃቤ ሃይማኖተኝነታቸው ሳይሆን ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ተክለ ቁመናቸው መስፈርት እስኪመስል አባቶችን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ምእመናን አቧድኖ ለማፋጀት የተዘጋጁ ወገኖች ብቅ ብቅ ማለት መጀመራቸውንም እንገነዘባለን፡፡

 

የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ደፍቀው ወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት የሚያቀነቅኑ እነዚህ ወገኖች ለቤተ ክርስቲያናችን ልዕልና፣ ዕድገትና ልማት እንዲሁም ለምእመናን መብዛትና መጽናናት የሚያስቡ አለመሆናቸውን ከዚሁ ድርጊታቸው መረዳት ችለናል፡፡ ይልቁንስ ለእነርሱ ቀኝ እጅ ሆኖ፤ የእነርሱን ፍላጎት የሚያስፈጽም “የተረኞች” አባት ፍለግ ውስጥ የገቡ ሰዎች ቁመናን ገንዘብ ያደረጉ መሆናቸውንም ተረድተናል፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኒቱ በቀኖናዋ የ”ተረኞች ፓትርያርክ” ሥርዐተ ሢመት የላትም፤ እንዲኖራትም አልተፈቀደም፡፡ ፕትርክና በወንዛዊ- ጎጣዊና- ዘውጋዊ ተረኝነት የሚገኝ ሳይሆን እግዚአብሔር ባወቀው በግብረ መንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ሢመት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “አንዱ እኔ የጳውሎስ ነኝ፤ ሁለተኛውም እኔ የአጵሎስ ነኝ ቢል ሰዎች ብቻ መሆናችሁ አይደለምን? አጵሎስ እንግዲህ ምንድር ነው? ጳውሎስስ ምንድር ነው? በእነርሱ እጅ ያመናችሁ አገልጋዮች ናችሁ፤ ለእያንዳንዳቸውም ጌታ እንደሰጣቸው ያገለግላሉ፡፡ እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፡፡ እንግዲያስ የሚያሳድግ እግዚአብሔር እንጂ የሚተክል ቢሆን ወይም የሚያጠጣ ቢሆን አንዳች አይደለም፡፡ የሚተክልና የሚያጠጣ አንድ ናቸው፤ ነገር ግን እያንዳንዱ እንደራሱ ድካም መጠን የራሱን ደመወዝ ይቀበላል” 1ኛ ቆሮ.3፥4-81 ያለውን በዕዝነ ልቡና መያዝናም ተገቢ ነው፡፡

 

ከዚህ አኳያ የ”ተረኝነት ሥርዐተ ፕትርክና” አስተሳሰብ ፍጹም ሥጋዊ ከመሆኑም በላይ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ አዋራጅና ጎጂ ነው፡፡ የዚህ ፍጹም ሥጋዊ አስተሳሰብ አቀንቃኞች ከወዲሁ ራሳቸውን ተረኛ ጥቅመኛ አድርገው የሰየሙ ናቸው፡፡ መቼ ነው እኛ ደግሞ አስወጪ አስገቢ የምንሆነው? ተረኛ አሿሚ፣ አሻሪ ሆነን ቤት የምንሠራው፤ መኪና የምንገዛው ባዮች መሆናቸውንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 

እንዲህ ዐይነቱ ፍጹም ሥጋዊ ቅኝት የሚያመለክተው አንድ ነገር ነው፡፡ የሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እያጸጸ መምጣቱንና ውስጡ ጥቅመኝነት ሆኖ ሽፋኑ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ የሆነ ብሔርተኝነት መሠረት እየያዘ መሆኑን ነው፡፡

 

እናም መጪውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን የተሻለና በጎ ከማድረግ አኳያ የጊዜውን አበው፣ ሊቃውንትና ምእመን በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ዋጅቶ ከወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ብሔርተኝነት ደዌ መፈወስ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው፡፡

 

የመጪውን ጊዜ ፓትርያርክ አሰያየምም በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” መዋጀት በመንፈሳዊነታቸው እና በአመራር ክሂሎታቸው እንጂ በጎጣዊ- ወንዛዊ- ዘውጋዊ ማንነታቸው መሆን የለበትም እንላለን፡፡ አባቶቻችን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሢመት መብቃት ያለባቸው በአባትነታቸው እንጂ መልክዐ ምድራዊ ብሔርተኝነት በወለደው ወንዛዊነት- ጎጣዊነት- ዘውገኝነት አይደለም፡፡

 

ለተግባራዊነቱ ደግሞ በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽና የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል የሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የአንበሳውን ድርሻ መውሰድ አለባቸው እንላለን፡፡

 

“አባ እገሌ “እገሌ ፓትርያርክ ይሁን” ሲል ሌላኛው ደግሞ ሞቼ እገኛለሁ አለ” እያሉ የሚያናፍሱትን ክፉ ወሬ አሉባልታ የሚያደርግ ቁርጠኝነት ከአባቶቻችን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከራስ ይልቅ ለቤተ ክርስቲያን ቅድሚያ እየሰጡ በሥልጣን የሚጣሉ አባቶች ሳይሆኑ ለአንዲት፣ ቅድስት፣ ሐዋርያዊትና ኲላዊት ቤተ ክርስቲያን ዓላማ በጋራ የሚሠሩ አባቶች እንደአሉን እንደሚያረጋግጡ ጽኑ እምነታችን ነው፡፡

 

ብፁዓን አበው ለሢመተ ፕትርክና ዕጩ ሆነው የሚቀርቡት አባቶቻችን መንፈሳዊ፣ ለመምራት ብቃት ያላቸውና ዐቃቤ ሃይማኖት እስከ አሁኑ ድረስ ወንዛዊ- ጎጣዊ- ዘውጋዊ ማንነታቸው ከየትም ሊሆን ይችላል የሚል ተጨባጭ መልእክት እንደሚያስተላልፉም ባለሙሉ ተስፋ ነን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን በቀጣይ ከባድ ግን ልትወጣው የምትችለው ፈተና አለባት፡፡ በቃላት የሚፈታና የሚነገር ሳይሆን በተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚፈተነው፡፡ ከዚህ አኳያ ቀጣዩ ጉዞ በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” እጅ ለእጅ መያያዝንና ጠንካራ አንድነትን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለምን አልተጣሉም? ለምን አልተከፋፈሉም? የሚሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን አርፈው የሚቀመጡበትም ሁኔታ እንደሌለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

 

ይህን የጥፋት ሕልማቸውን እውን ለማድረግ አባቶችን ለመከፋፈል፣ በምእመናን መካከል ልዩነትን ለመፍጠር፣ ሊቃውንቱን ለማጥላላትና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማዳከም ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉም ይታመናል፡፡ ብፁዓን አበውም፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንም ምእመናንም ይህን አውቀው በሃይማኖት “ብሔርተኝነት” ጠንክሮ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል እንላለን፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 20ኛ ዓመት ቁጥር 1 2005 ዓ.ም.

የማኅበሩ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሰዓት ወደፊት የሚሻሻል መሆኑ ተገለጠ

መስከረም 16 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


ማኅበረ ቅዱሳን ባሳለፍነው ሳምንት ማጠናቀቂያ የቴሌቪዥን መርሐ ግብርን በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ሰርቪስ ቴሌቪዥን (EBS TV) ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁንና ይህንኑ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው  የማኅበሩ አባላት፣ ካህናትና ምእመናን፡- ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመጣው የማኅበሩ አገልግሎት ከልብ መደሰታቸውን አስታውቀው፤ ነገር ግን የተመረጠው ጊዜ ሕዝበ ክርስቲያኑ ከቤተ ክርስቲያን ከሚወጣበት ሰዓት ጋር በጣም መቀራረቡ ፣ በተጨማሪም አጠቃላይ የመርሐ ግብሩ ጊዜ በ30 ደቂቃ መገደቡ እንዳሳሰባቸው ገልጠውልናል፡፡

 

በጉዳዩ ላይ  ያነጋገርናቸው በማኅበሩ ኅትመትና ኤሌክትኒክስ ሚዲያ የሬድዮና ቴሌቪዥን አስተባባሪ ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ “የማኅበሩ የቴሌቪዥን  የአየር ሰዓት ልናገኛቸው ከቻልናቸውና ካልተያዙት አማራጭ ጊዜያት ውስጥ የተሻለው ነው፤ ከካህናቱና ከምእመናኑ የተሰጠውን አስተያየት ሙሉ ለሙሉ የምንቀበለው ሲሆን ወደፊት ከጣቢያው ጋር ተነገግረን የሥርጭት ሰዓቱን ለመቀየር ጥረት እናደርጋለን፡፡ ለጊዜው ግን እሑድ ጧት ከ3፡30 እስከ 4፡00 የሚተላለፈውን መርሐ ግብር መከታተል ላልቻሉ በድጋሚ ሐሙስ ጧት 1፡00 እስከ 1፡30 በድጋሚ ስለሚቀርብ ዝግጅቱን መከታተል ይችላሉ ” ብለዋል፡፡

ADSC00232

ማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዠን መርሐ ግብር ሊጀምር ነው

መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር በየሳምንቱ እሑድ ጧት ከ3፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት የሚቆይ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ሰርቪስ ቴሌቪዠን (EBS TV) ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጠ፡፡

 

ADSC00232በማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ፥ የሬድዮና ቴሌቪዠን ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ ለመካነ ድራችን በሰጡት መግለጫ፡- ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ላለፉት ሃያ ዓመታት በልዩ ልዩ የኅትመት ውጤቶች እንዲሁም በመካነ ድር (website) እና በሬድዮ አማካኝነት በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ በሳምንት አንድ ጊዜ የ30 ደቂቃ መርሐ ግብር ለመጀመር ትናንት መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም  ከኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን የሥራ ሓላፊዎች ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ ስምምነት ማኅበሩ መፈራረሙን  ገልጸዋል፡፡

 

ዲያቆን ሄኖክ በዚሁ ገለጻቸው፥ በአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በ17515 ኪሎ ኸርዝ፣ በ16 ሜትር ባንድ አጭር ሞገድ ዘወትር አርብ ከምሽቱ 3፡30 እስከ 4፡30 ድረስ የሚተላለፈውን የሬድዮ ዝግጅት በመከታተልና ገንቢ አሰተያየት በመስጠት ምእመናን ላደረጉት ተሳትፎ በማመስገን በአዲሱ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ላይም ተመሳሳይ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

 

ማኅበሩ ከጥቅምት 2003 ዓ.ም አንሥቶ በአጭር ሞገድ  የሬድዮ መርሐ ግብር መጀመሩ ይታወሳል፡፡

megelecha

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጠ

መስከረም 12 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መስከረም 11 ቀን 2004 ዓ. ም. መግለጫ ሰጠ፡፡ መግለጫውን የሰጡት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ሓላፊ የሆኑት እስክንድር ገብረ ክርስቶስ ሲሆኑ በመግለጫቸውም “በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥና ዙሪያ ተሸሽገው የተዛባ መረጃን በማቀበል የሽግግር ወቅት ሂደቱን ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዳይራመድ የሚጥሩ ወገኖች ሁሉ ከዚህ አፍራሽ እንቅስቃሴያቸው እንዲታቀቡ እያሳሰብን ይህ ባይሆን ግን የሽግግር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግ ሲባል ቤተ ክርስቲያኒቱ ሕጋዊ እርምጃዎቸን ለመውስድ የምትገደድ መሆኑን አጥብቃ ለማሳሰብ ትወዳለች፡፡” ብለዋል፡፡

 

6ኛውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫን በሚመለከት ጥቅምት በሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሚወሰን መሆኑንና ሕዘበ ክርስቲያኑ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔና የቤተ ክርስቲኒቱን ድምጽ ብቻ መከታታል እንደሚገባው በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡

 

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ክቡር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጠቅላይ ሚኒስትርነት፤ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት  መመረጣቸውን በማስመልከት ለኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት መልእክት ማስተላለፏን ከሕዝብ ግንኙነት መምሪያው የወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

megelecha

enkutatash

የተቀጸል ጽጌ በዓል ተከበረ

መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የሚከበረው የተቀጸል ጽጌ በዓል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም. በድምቀት ተከበረ፡፡

 

ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ  ብፁዕ አቡነ ናትናኤል፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ አረጋውያን አርበኞች፤ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላትና ምእመናን በተገኙበት የተከበረው ይኸው በዓል  ከቅዳሴ በኋላ በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን የዕለቱ ተረኛ በሆነው በርዕሰ አድባራት ወገዳማት አዲስ ዓለም ደብረ ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ያሬዳዊ ዜማ ቀርቧል፡፡ በተጨማሪም የአጫብር ወቆሜ ወረብ፤አንዲሁም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት መዘምራን ያሬዳዊ ዜማ ያቀረቡ ሲሆን በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

 

በመጨረሻም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል በሰጡት ቃለ ምዕዳን ‹‹ያሳለፍነው ወርኀ ነሐሴ የሰው ልቦና በሃዘን የተሰበረበት  ጊዜ ነበር፡፡  መስከረም ሲጠባ በዚህ በዐውደ ምሕረት ተሰብስበን ታላቁን የመስቀል በዓል ተቀጸል ጽጌን እያከበርን እንገኛለን፡፡ ይህ በዓል የሚታወቀው በቤተ መንግሥት ነበር፡፡ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ የራሱ ጊዜ ሰላለው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በቤተ መንግሥት አደባባይ ይከበር የነበረው በዓል በዐውደ ምሕረት እንዲከበር አድርገውታል፡፡ አውደ ምሕረት የእግዚአብሔር ቃል የሚነገርበት ነውና፡፡›› በማለት  የበዓሉን አከባበር ገልጸውታል፡፡

 

ወቅቱንም ለማመልከትና የደስታ ዘመን እንዲሆን በመመኘት ከዐቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አበባ ለምእመናን በማበርከት  መርሐ ግብሩ በጸሎት  ተጠናቋል፡፡

 

ተቀጸል ጽጌ ማለት የአበባ በዓል ማለት ነው፡፡ ክረምቱ፤ ድጡ፤ ማጡ፤ ችግሩና ጨለማው ተወግዶ ምድር በልምላሜ የምታሸበርቅበት፤ በአበባ የምትደምቅበት ወቅት በመሆኑ፡፡ አንድም የዐፄ መስቀል በመባል ይታወቃል፡፡ ጌታችን የመድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትና ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ በዐፄ ዳዊትና በዐፄ  ዘርዐ ያዕቆብ አማካይነት የገባበት ቀን በመሆኑ፡፡ ይህ ግማደ መስቀል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች  ለማሳረፍ ቢሞከርም ከሦስት ዓመታት ጉዞ በኋላ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል” ተብሎ በታዘዘው መሠረት ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ  በግሸን ደብረ ከርቤ ለማኖር ችሏል፡፡

 

enkutatashየተቀጸል ጽጌ በዓል የተጀመረው በ6ኛው ምዕተ ዓመት በዐፄ ገብረ መስቀል አማካይነት ሲሆን በዓሉ የሚከበረው የክረምቱ ማብቃት የሚያበስሩ አበቦች በሚፈኩበት ወር በመስከረም 25 ቀን ለንጉሡ የአበባ ጉንጉን /አክሊል/ በማበርከት ነበር፡፡ መስከረም 10 ቀን እንዲከበር የተወሰነው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ወደ ኢትዮጵያ ካመጡበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ነገስታቱ ልብሰ መንግስታቸውን በመልበስ፤ ካህናቱ ጥንግ ድርብ ለብሰው ዝማሬ በማቅረብ፤ ምዕመናን ፀአዳ ለብሰውና አሸብርቀው በዓሉ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ እስከ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት  ማብቂያ ድረስ ሲከበር ቆይቷል፡፡ ደርግ ስልጣነ መንግሥቱን ሲቆናጠጥ ከሥልጣን እሰከተወገደበት እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ  በዓሉ እንዲቋረጥ አድርጎታል፡፡ በ1984 ዓ.ም.  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው እንደተሾሙ ቀድሞ የነበረውን ሥርዓት በመመለስ በየዓመቱ መስከረም 10 ቀን በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

ውጤታማ ለመሆን በውይይት ማመን

መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ወልደ ማርያም


የአምስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሥርዓተ ቀብር ከተፈጸመ ሳምንታት ተቆጠሩ፡፡ ፓትርያርኩ ዐርፈው መንበረ ፕትርክናው ባዶ መኾኑ ከተረጋገጠበት ዕለት ጀምሮ መንበሩን ለመጠበቅና ለማስጠበቅ ይበቃል ያለውን አካል የመሾም፤ የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት የማስቀጠል ሓላፊነት የተጣለበት ቅዱስ ሲኖዶስ አምስት ዋና ዋና ተግባራትን ፈጽሟል፡፡

 

የመጀመሪያው ፓትርያርኩ ማረፋቸው እንደተሰማና እንደተረጋገጠ በፓትርያርኩ በኩል ቤተ ክርስቲያኗ የሰበሰበቻቸውን ሀብታት በአግባቡ እንዲጠብቁ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ፓትርያርኩ ረቡዕ ለሐሙስ አጥቢያ ከንጋቱ 11 ሰዓት አካባቢ ዐርፈው በዕለቱ ወደ 7፡30 አካባቢ ይኖሩበትና በቢሮነት ይገለገሉባቸው የነበሩትን ቤቶች አሽጓል፡፡ ሁለተኛው ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በሚያዘው መሠረት መንበረ ፕትርክናውን የሚጠብቅ፤ ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ እስኪመረጥ ድረስ ሲኖዶሱን በበላይነት የሚመራ፣ /ህየንተ ፓትርያርክ/ ኾኖ የቤተ ክርስቲያኗን መንፈሳዊ አስተዳደር የሚመራ ዐቃቤ መንበር መምረጥነው፡፡ በዚሁም ነሐሴ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን ከያዙት የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጵጵስና በተጨማሪ ዐቃቤ መንበር ኾነው እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል፡፡

 

ሦስተኛው /በይፋ የተገለጠ ነገር ባይኖርም/ ከወቅቱ ቋሚ ሲኖዶስ ጋር ቀጣዩ ፓትርያርክ ከመመረጡ በፊት ሊሠሩ የሚገባቸውን ተግባራት የቤተ ክርስቲያኗን ሁሉን ዐቀፍ አስተዳደራዊ ፈርጆች አጥንቶ የሚታረመውን አርሞ የሌለውን አዘጋጅቶ ለምልዐተ ጉባኤ የሚያቀርብ ሰባት አባላት ያሉት የሊቃነ ጳጳሳት ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ መምረጡ ነው፡፡ ዐራተኛው የቅዱስ ፓትርያርኩ ሥርዓተ ቀብር ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት ለክብራቸውም በሚገባ መልኩ እንዲፈጸም ማድረጉ ነው፡፡ አምስተኛው እግዚአብሔር ለቤተክርስቲያኗ መልካም መሪ ይሰጥ ዘንድ የጸሎት ዐዋጅ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማወጅ ነው፡፡

 

ከላይ ያየናቸው የቅዱስ ሲኖዶሱ ተግባራት አፈጻጸማቸው በይፋ የታየ መግለጫም የተሰጠባቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶሱ ምን እየሠራ እንዳለ እየተሰጠ ያለ መግለጫ የለም፡፡ ይህ ጽሑፍ ቀጣዩን የቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አመራረጥ አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶሱ ሊሔድበት የሚገባውን መስመር በአጭሩና በመጠኑ ይጠቁማል፡፡

 

1. መቅደም ያለበትን ማስቀደም፡- ቤተ ክርስቲያናችን ባለፉት ሁለት ዐሠርት ዓመታት ጥሩ ተጓዘች፣ በአንጻሩም ቢኾን ኢኮኖሚዋ አደገ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን ዕለት ዕለት የሚገሠግሠው ምእመን ቁጥር ጨመረ ቢባልም ሒደቱን በከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተተ፣ ቤተ ክርስቲያኗን ለዘመናት አስከብረው ለአገርና ለሕዝብ ጠቃሚ አድርገው ያቆዩዋት ዕሴቶቿን ክፉኛ ሲገዳደር የቆየ አንድ መሠረታዊ ችግር አለ፡፡ ይኸውም የቤተ ክርስቲያኗን አስተዳደር በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ እንዲከፋፈል ያደረገና በአባቶች መካከል የተከሠተ የመለያየት ችግር ነው፡፡ ይህ ልዩነት ለሃያ ዓመታት ምእመኑን ሲያደናግር የኖረ፣ በሁለቱ ጎራ ያሉ አባቶችም እርስ በርስ ተወጋግዘው ቤተክርስቲያኗ ሲኖዶስ አልባ እንድትመስል አድርጎ ያቆየ፣ ለብዙ ሥጋውያን ሰዎች ዓላማ ማስፈጸሚያነትም ሲያገለግል የኖረ መሠረታዊ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኗ አሁን በዚያ መጠላለፍና አልሸነፍ ባይነት – ስትናጥበት ከቆየችበት ችግር የምትላቀቅበት መልካም አጋጣሚ ላይ ትገኛለች፡፡ በመኾኑም ቤተ ክርስቲያኒቱን ይመራ ዘንድ የተሰየመው ቅዱስ ሲኖዶስ ይህንን ለሃያ ዓመት የዘለቀ ልዩነት አጥብቦ ቤተ ክርስቲያኗን ወደ ቀደመ የአንድነት ጉዞዋ መመለስ አለበት፡፡ ይህን ሲያደርግም የሚከተሉትን ጉዳዮች በጥንቃቄ ሊያጤን ይገባል፡፡

 

ሀ. የችግሩን መንሥኤ ከመሠረቱ ማጥናት፡- ከላይ የገለጽነው የመከፋፈል ችግር የብዙ ትንንሽ ችግሮች ውጤት ነው፡፡ ዝርዝራቸውን ትተን መገለጫቸውን ብናይ ፖለቲካዊ ዓላማ፣ ሀብት የማካበት ዓላማ፣ የግል ክብርና ምቾት ፍለጋ ዓላማና ቤተ ክርስቲያኗን በኑፋቄ የማወክል ዓላማ ናቸው፡፡ እነዚህን ዓላማዎች በየግላቸው ይዘው የሚንቀሳቀሱ አካላት መጠናቸው ቢለያይም በሁለቱም ጎራዎች አሉ፡፡ እነዚህ አካላት ልዩነቱን በመጠቀም ዓላማዎቻቸውን ሲያሳኩና ለማሳካት ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡ በመኾኑም በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች ቤተ ክርስቲያኗ የምትናፍቀውን ሰላም አስፍነው በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር ደገኛ ተግባር ለመፈጸም፤ የችግሩን ምንጮች አጥንተው በመለየት እነዚህን አካላት በምክርም በተግሣጽም ማረም ወይም መለየት ይገባቸዋል፡፡

 

ለ. የዕርቁን አስፈጻሚዎች በጥንቃቄ መምረጥ፡- በአባቶች መለያየት ምክንያት ቤተ ክርስቲያኗ ከተከፈለችበት ጊዜ አንሥቶ በኦፊሴል ያልተገለጹትን ጨምሮ ሁለቱንም አካላት በመወከል በሚቀመጡ አባቶች አማካኝነት በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ድካሞቹ ሁሉ ውጤት አላመጡም፡፡ ለዚህ ከሚሰጡት ምክንያቶች አንዱ የሚወከሉት አባቶች ችግሩ እንዲፈታ በማድረግ በኩል የማስፈጸም ብቃት ማነስ ወይም ለማስፈጸም ጠንክሮ አለመሥራት ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን መካከል የሚከሠትን ችግር ለመፍታት ምድራዊ ጥበብና ቀመር ቦታ የላቸውም፡፡ «እንዲህ ቢባል እንዲህ በሉ» የሚለው ቅደመ ውትወታም አያስፈልግም፡፡ «እንዲህ ብል እከሌ ምን ይላል?» ወይም «የምናገረውን እከሌን ልጠይቅ» የሚሉት ደካማ አስተሳሰቦችም ሊኖሩ አይገባም፡፡በመኾኑም በቀጣይ ይህንን ሁሉም የሚናፍቀውን አንድነት እውን ለማድረግ ከሁለቱም ወገን የሚመረጡት አባቶች እውነትንና አንድነትን በማስቀደም ራሳቸውን ኾነው የሚወያዩ መኾን ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህም በሁለቱም በኩል ያሉት አባቶች ይወክሏቸው ዘንድ በሚመርጧቸው ሰዎች  ብቃት ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

 

ሐ.  የዕርቅ ውይይቱ በሁሉም አካላት በኩል እንዲጀመር ማድረግ፡- ይህ ችግር እንዲፈታ በማድረግ ሥልጣንና ሓላፊነት ያላቸው በሁለቱም በኩል ያሉ አባቶች እንደ ኾኑ ይታመናል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሃያ ዓመታት መሠረታዊው የአባቶች ልዩነት ያቆሰላቸው በርካታ አካላት በሁለቱም በኩል በየደረጃው አሉ፡፡ እነሱም በሁለቱም በኩል ያሉ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ማኅበራት ናቸው፡፡ ምንም እንኳን አባቶች በዕርቅ ከተዋሐዱ እነዚህ አካላት አሻፈረኝ ብለው እንደተለያዩ ይቀራሉ ባይባልም የእነሱም መወያየት ዕርቁን የተሟላ ያደርገዋል፡፡ የአባቶችን መዋሐድ የማይፈልጉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችንም ለመለየት ያግዛል፡፡

 

2.    በቀጣዩ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ላይ በጥብዓትና በግልጽ መወያየት መጀመር፡- ባለፉት ሃያ ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ችግር ገዝፎ ይታይ የነበረው በኢትዮጵያና በአሜሪካ አብያተ ክህነት መካከል ብቻ አልነበረም፡፡ እዚህ አዲስ አበባም በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክህነቱ አስተዳደርና በቅዱስ ሲኖዶሱ አመራር ላይም ችግሮች ታይተዋል፡፡ ችግሮቹ ገዝፈው የቤተ ክርስቲያኗን ምልዐት እስከ ማወክና ምእመኑን ወደ ቀቢጸ ተስፋ እስከ መክተትም ደርሰው ነበር፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ቅድስና የማይስማሟት ዘረኝነት፣ ሙስናና አድሎአዊነት በይፋ ታይተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና አገልግሎት የሚጠበቀውን ያህል ዘመናዊ አልሆነም፡፡ አህጉረ ስብከት በልማት አገልግሎት መጓዝ ያለባቸውን ያህል አልተጓዙም፡፡ ለዚህ ሁሉ በብዙዎች እንደ ምክንያት ይጠቀስ የነበረው የቅዱስ ፓትርያርኩ የአስተዳደርና የአመራር ችግር ነው፡፡ አከራካሪ ነው፡፡ የኾነው ኾኖ አሁን ይህ ምክንያት በዜማነት የሚነሣበት ጊዜ አልፏል፡፡ ለሃያ ዓመታት በምክንያትነት ሲነሡ የነበሩት ቅዱስ ፓትርያርክ የሉም፡፡ እንደ ሥራቸው ወደሚከፍላቸው አምላክ ሔደዋል፡፡ ስለዚህ የሲኖዶሱ አባላት ሌላ ምክንያት ፈጥሮ የሚቀጥሉትን ሃያ ዓመታትም ተመሳሳይ ዜማ ሲያዜሙ ላለመኖር በመንበረ ፕትርክናው ስለሚያስቀምጡት አባትና ስለሚቀመጥበት አግባብ እንዲሁም ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ቀጣይ አስተዳደራዊ መልክእ መወያየትና ቀጥተኛ መስመር ማስቀመጥ አለባቸው፡፡

 

3.    ችግሮችን አጥንተው ለውሳኔ የሚያቀርቡ ልዩ ልዩ ጉባኤያትን ማቋቋም፡- ሲኖዶስ የቤተክርስቲያኗን መንፈሳዊ አስተዳደር በበላይነት የሚመራ፣ በባለሞያዎች ተጠንቶ በሚቀርብለት መሠረታዊ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል ነው፡፡ ይህ እንዲኾን ደግሞ አስፈላጊውን አቅጣጫ ለአስፈጻሚው አካል መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ በአሁኑ ሰዓት ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪ ማድረግ ያለበት የቤቱን መሠረታዊ ችግሮች ሙያዊ በኾነ መንገድ አጥንተው ከነመፍትሔ ሐሳባቸው  የሚያቀርቡ የባለሞያዎች ቡድኖችን ማቋቋም ነው፡፡ ቡድኖቹም በተወሰነላቸው ጊዜ የቤተ ክርስቲያኗን መሠረታዊ ችግሮች ከመፍትሔ ሐሳቦች ጋር እንዲያቀርቡለት መመሪያና ትእዛዝ መስጠት፣ ለሥራቸው ቅልጥፍናም አስፈላጊው ሎጂስቲክስ እንዲሟላላቸው ማድረግ  ይጠበቅበታል፡፡ የቀደመ አገልግሎቷን ለማስቀጠል 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ የደረሰች ቤተ ክርስቲያን ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት ሙያዊና አስተዳደርንና አሠራርን መከተል ይጠበቅባታል፡፡ ለዚያ ደግሞ አሁን በመስቀለኛ መንገድ ላይ ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ሓላፊነቱን መወጣት ኖርበታል፡፡ አሁን በሚታየው ሁኔታ ሦስት የባለሙያዎች ቡድኖች እንዲቋቋሙ ግድ ይላል፡፡ እነዚህም የገንዘብና የንብረት አስተዳደር ጥናት ቡድን፣ የሰው ኃይል ጥናት ቡድንና የቤተ ክርስቲያን መዋቅርና አሠራር ጥናት ቡድን ናቸው፡፡ እነዚህ ቡድኖች በየተሰጧቸው አርእስት ያሉትን ጉዳዮች ፈትሸው ችግሮችን ነቅሰው በማውጣት የመፍትሔ ሐሳቦችንና የአሠራር መንገዶችን አጥንተው ያቀርባሉ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስም በሚቀርቡለት ሰነዶች ዙሪያ ተወያይቶ ይወስናል፡፡

4.    ጣልቃ ገብነትን በጥንቃቄ መከታተል፡- የቤተ ክርስቲያን ፈተናዎች የሚመነጩት ከውስጥም ከውጭም ነው፡፡ በተደጋጋሚ ሲነሡ የቆዩትና በመነሣት ላይ ያሉ የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ሙሉ በሙሉ በውስጧ ባሉ አካላት /ምእመናን፣ ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክህነቱ ሠራተኞች፣/ ድካም ብቻ የመጡ አይደሉም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ ዐውቃም ይሁን ሳታውቅ በገቡባት ባዕዳን እጆች የተነሣ  ችግር ላይ ስትወድቅ ቆይታለች፡፡ እነዚህ የባዕዳን እጆች አሁንም በቤተ ክህነታችን አሠራር ድርሻ እንዲኖራቸው መፈቀድ የለበትም፡፡ ስለዚህ አሁን ሁሉም ዐይኑን አፍጥጦ እንዲኾን የሚጠብቀው ሒደት ከየትኛውም ውጫዊ አካል ተፅዕኖ በጸዳ መልኩ እንዲኾን ሓላፊነት ያለበት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ምልዐት መትጋት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ረገድ ቤተ ክርስቲያኗ በመስቀለኛ መንገድ ላይ በቆመችበት ሰዓት ወደደጉ የመምራት ሓላፊነት ያለባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከፍተኛ ድርሻ አለባቸው፡፡ እነሱ ከየትኛውም ጫና ነጻ በኾነ መልኩ እንዲመሩ ደግሞ የሚመለከተን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁላችን በምንችለው ሁሉ ልናግዛቸው ያስፈልጋል፡፡

 

5. በቤተ ክርስቲያኗ ቀጣይ ጉዞ ላይ ሁሉም የቤተ ክርስቲያኗ ምልዐት በየደረጃው እንዲወያዩ ቢደረግ፡- ወቅቱ ሁሉም የቤተ ክርሰቲያኗ አካላት ስለ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ቀጣይ ጉዞ ስለ መሪዎቿና አመራር ሥልታቸው፣ ስለ አገልግሎቷና አገልጋዮቿ ብቃት በስፋት መወያየት ያለባቸው ጊዜ ነው፡፡ በዘርፉ ምሁራን በቃልም በመጻፍም እንደሚገለጠው ዘመናዊ አመራር የጋርዮሽ ተግባር ነው፡፡ ይህ አባባል ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲመጣ ተግባራዊነቱ ወሳኝ በኾኑ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉም አካላት እየተወያዩ ለቤተ ክርስቲያኗ ይበጃሉ የሚባሉ ሐሳቦችን ወደ ዋናው ወሳኝ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲልኩ ሲኾን ነው፡፡ በመኾኑም ቅዱስ ሲኖዶሱ ለውይይቱና ለሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች መቃናትና ቀጥተኛነት እሱ የሚመራቸው አካላት /የቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ ሰበካ ጉባኤያት፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሁራን የቤተ ክርስቲያን ልጆች ወዘተ/ በየመልኩ እንዲወያዩ አቅጣጫ መስጠት አለበት፡፡ እነዚህ አካላትም የቅዱስ ሲኖዶስን አባላት ግብዣ በመቀበል ለተግባራዊነቱ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡

 

ስናጠቃልል፡- በአሁኑ ሰዓት ቤተ ክርስቲያናችን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች፡፡ የምዕራፉ ወሳኝነትም ቤተ ክርስቲያኗ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድታ ወደ ፊት የምትራመድበትን አቅጣጫ ለማስቀመጥ በጥንቃቄ መራመድ ያለባት ጊዜ ላይ በመኾኗ ነው፡፡ ጥንቃቄው ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን ለመምራት እግዚአብሔር መርጦ ያስቀመጣቸው አባቶች ድርሻ ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ በጥምቀት ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ የወለደቻቸው ልጆቿ ሁሉ ለእናት ቤተ ክርስቲያናቸው ቀጣይ መልካም ጉዞ በሚችሉት ሁሉ መወያየት ይበጃል ያሉትን ሐሳብ ሁሉ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ይሰምር ዘንድ ደግሞ የእኔ ሐሳብ ብቻ ተቀባይ ይሁን ከሚል መገዳደር ርቆ ሁሉንም በፍቅር ማድረግና የፍቅር አምላክ የመሠረተልንን ቤተ ክርስቲያን በፍቅር ልንኖርባት ያስፈልጋል፡፡ ለሁሉም ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረተ መሥርቶም ያጸና አምላክ ደጉን ሁሉ ያድርግልን፡፡

 

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን

የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የፖትርያርክ ምርጫ የሚመለከት ረቂቅ ሕግ

መስከረም 10 ቀን 2005 ዓ.ም.

ወልደ ማርያም

ምዕራፍ 1

የዐቃቤ መንበሩን ምርጫ በተመለከተ

 

አንቀጽ 1

  • መንበረ ፓትርያርኩ በሞት ወይም በሌላ ምክንያት በመንበሩ ላይ ባይኖር ቅዱስ ሲኖዶስና ሚሊ ካውንስሉ /የምዕመናን ጉባኤ/ በዕድሜ አንጋፋ በሆነው ጳጳስ በሚጠራው ጉባኤ ሰብሳቢነት ቅዱስ ሲኖዶሱ ተሰይሞ ከ7 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ዐቃቤ መንበር ይሰይማል፡፡ የተመረጠውም አባት ዐቃቤ መንበር በመሆን ያገለግላል፡፡ ብሔራዊ ዐዋጅ /republican decree/ ታውጆ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ፣ ትውፊትና ሥርዓት መሠረት ሕጋዊ የሆነው ፓትርያርክ ሹመት ይፈጸማል፡፡

 

ምዕራፍ 2

ለመንበሩ የሚመጥን ሰው ምርጫ

 

አንቀጽ 2

ለፓትርያርክነት ሹመት የሚወዳደር ሰው የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡

  1. በትውልድ ግብጻዊ በሃይማኖቱም የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት አባል የሆነ፡፡

  2. የቤተ ክርስቲያንን ሕግ፣ ሥርዓትና ትውፊት የሚያዘውን የሚያሟላ፣ መነኩሴ የሆነ በጋብቻ ሕይወት ያልተወሰነ /ሜትሮፓሊታንም ሆነ ጳጳስ/ ይህ ቅድመ ሁኔታ ይጠበቅበታል፡፡

  3. ዕድሜው ከአርባ ዓመት ያላነሠ በገዳም ከ15 ዓመት ላላነሠ ጊዜ የኖረ፡፡

አንቀጽ 3

  • ዐቃቤ መንበሩ የሚመራው 18 አባላት ያሉት ቅዱስ ሲኖዶስ የመረጠው የሜትሮፓሊታን የጳጳስነትና ከሚሊ ካውንስሉ /ከምእመናን ጉባኤ/ የተውጣጣ 18 አባላት ያሉት ጉባኤ ለመንበረ ጵጵስናው የሚወደደሩ እጩዎችን ዝርዝር ይይዛል፡፡

  • ኮሚቴው በመንበሩ ላይ ተቀምጦ የነበረው ፓትርያርክ ሥፍራው በሞት ወይም በሌላ ሁኔታ በለቀቀ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ መሰየም ይኖርበታል፡፡ የዚህን ኮሚቴ ስብሰባ የሚጠራው ሊቀ መንበሩ ነው፡፡ ሊቀ መንበሩ ከሌለ ወይም ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ከተፈጠረበት አስቀድሞ የተመረጠው ሜትሮ ፓሊተን የሊቀ መንበሩን ሥፍራ ተክቶ ይሠራል፡፡ ጉባውንም ይጠራል፡፡

  • ጉባኤው የሚካሄደው የሁለቱም ጥምር ጉባኤ አባላት 2/3ኛው ያህል ሲገኙ ነው፤ ምልዓተ ጉባኤው ካልተሟላ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ ይቀጠራል፡፡ ሁለተኛው ምልአተ ጉባኤ ስብሰባውን የሚካፈሉት አባላት ቢሟሉም ባይሟሉም የተገኙት አባላት በአብላጫ ድምጽ የሚወስኑት ውሳኔ ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡

 

አንቀጽ 4

  • ለፓትርያርክነት የሚወዳደረው እጩ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ በስድስት ሜትሮ ፓሊታን ጳጳሳትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች ወይም በሚሊ ካውንስሉ /የምእመናን ጉባኤ/ አስቀድመው ተመርጠው ያገለገሉ ወይም አሁን እያገለገሉ ያሉ አባላትን ይሁንታ የያዘ የጽሑፍ ድጋፍ ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

  • ይሁንታ ያገኙበትን ድጋፍ ሲያቀርቡ የድጋፍ ደብዳቤ የተሰጠበት ቀንና ሰዓት ተመዝግቦ ደረሰኝ ይሰጣቸዋል፡፡

 

አንቀጽ 5

  • የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአንቀጽ 4 ላይ በተቀመጠው መሠረት በ15 ቀን ውስጥ ተሰብስቦ የድጋፍ ደብዳቤዎችን ይመረምራል፤ ሕጉን የተላለፈውን ያስወግዳል፡፡ በሕጉ መሠረት የመጡለትን ድጋፎች ይቀበላል፡፡

  • ኮሚቴው በተቀመጠው የማስረከቢያ ቀን የእጩዎችን ዝርዝር ካይሮ ለሚገኘው የፓትርያርክ ጽ/ቤትና በሌሎችም ሥፍራዎች ላሉ ጽ/ቤቶች ያስረክባል፡፡ የደረሰበትንም ውሳኔ በአረብኛ ቋንቋ ካይሮ ውስጥ በጋዜጣ እንዲታተም ያደርጋል፡፡

 

አንቀጽ 6

  • ለፓትርያርክነት መንበር የሚወዳደር ማንኛውንም እጩ የነጋሪት ጋዜጣ በወጣ በ15 ቀን ውስጥ ለመንበረ ጵጵስናው የማይመጥን ተወዳዳሪ አለ ብሎ ካመነ ለኮሚቴው ሊቀ መንበር /ሰብሳቢ/ ማስታወሻ ሊጽፍ ይችላል፡፡ አሳማኝ የሆነ ነጥብም ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ ለአመልካቹ ደረሰኝ ይሰጠዋል፡፡

  • የቀረበውን ቅሬታ ኮሚቴው ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ ኮሚቴው ውሳኔውን ያሳውቃል ኮሚቴው በአንቀጽ 2 ላይ የተቀመጡትን ነጥቦች ያላሟላ እጩ ካገኘ የማንንም ውሳኔ ሳይጠብቅ እጩውን የመሰረዝ ሥልጣን አለው፡፡ ለፓትርያርክነት እጩ ለመሆን ሁኔታዎችን ያሟሉ የመጨረሻዎቹን እጩዎች ያሳውቃል፡፡ የመጨረሻዎች ተወዳዳሪዎች የድጋፍ ደብዳቤ ያላቸው ሁነው ቁጥራቸው ቢያንስ አምስት ቢበዛ ሰባት መሆን ይኖርበታል፡፡ ስማቸውም በፊደል ተራ ቁጥር ይቀመጣል፡፡

 

አንቀጽ 7

  • ኮሚቴው የመጨረሻውን የፓትርያርክ ምርጫ ቀን ያሳውቃል፡፡ የመጨረሻውን ዝርዝር በፓትርያርኩ መኖሪያ በር ካይሮና በሌሎች አካባቢዎች ባሉ ጽ/ቤቶች ይለጥፋል፡፡ በዝርዝሩ ግርጌ ኮሚቴው ዕጩው የተመረጠበትን ቀን በማሳወቅ መራጮች ድምጽ እንዲሰጡ ይጋብዛል በተቀመጠው ቀንና ሥፍራ በየቀኑ ታትመው በሚወጡ ሦስት ጋዜጦች ካይሮ ውስጥ የምርጫውን ቀንና ሥፍራ ያሳውቃል፡፡ የምርጫ ቀኑ የእጩዎች ዝርዝር ከተገለጠበት ጀምሮ ከ30 ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይከናወናል፡፡

 

ምዕራፍ ሦስት

የፓትርያርኩ ምርጫ ድምጽ ሰጪዎች

 

አንቀጽ 8

  • በፓትርያርኩ ጽ/ቤት መራጮች ድምጽ የሚሰጡበት ሳጥን ይዘጋጃል፤ መራጮች በትውልድ ግብጻውያንና የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ባላቸው ግንኙነት በሃይማኖታቸውና በመልካም ግብራቸው የተመሰከረላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

 

ድምጽ ከሚሰጥበበት ጠረጴዛ የሚቀመጡ አስመራጮች

  1. የፓትርያርኩ መንበር ባዶ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በጎርጎራውያን ቀመር መሠረት ዕድሜው 35 ዓመት የሞላው፡፡
  2. የዩኒቨርሲቲ ዲግሪ ምሩቅ ወይም በግብጽ መንግሥታዊ ተቋም ተቀጥሮ ያገለገለ ወርሃዊ ገቢው 480 የግብጽ ፓውንድ ያላነሰ ወይም በባንክ፣ በካምፓኒ ተቀጥሮ የሚሠራ፣ ወይም በተመሳሳይ የሥራ ገበታ የተሰማራ፣ ገቢው ከ600 የግብጽ ፓውንድ ያላነሰ፣ ወይም ታክስ የሚከፍል ግብጻዊ ሆኖ ገቢው ከ100 የግብጽ ፓውንድ ያላነሰ መሆን ይኖርበታል፡፡
  3. በአንቀጽ 2 በተቀመጠው መሠረት በአስመራጭ ኮሚቴው ተቀባይነትን ያገኘ፡፡

አንቀጽ 9

  • ሦስት ካህናት፣ ሁለት የጠቅላላ ሚሊ ካውንስሉ/ የምእመናን ጉባኤ/ አባላት ወይም አሁን ወይም አስቀድሞ አባል የነበሩ ተመራጮች ያሉበት ኮሚቴ ድምጽ ሰጪዎች የሰጡትን ድምጽ ለመቁጠር ይሰየማል፡፡ ዐቃቤ መንበሩ የኮሚቴውን አባላት ይመርጣል ከካህናት መካከል በዕድሜ፣ ወይም በሌላ ቅድመ ሁኔታ ከፍ ካለው ጀምሮ ወደታች ያሉትን ሁሉ ሊመለከት ይችላል፡፡

 

ይህ ኮሚቴ በጽሑፍ በቀረበው ዳታ መሠረት የድምጽ ሰጪዎችን ድምጽ ከሚከተሉት ክፍሎች ይወስዳል፡፡

  1. ሜትሮ ፓሊታን፣ ጳጳሳት፣ የገዳማት አስተዳዳሪዎች ተመራጮችና ፍላጎት ያላቸው መራጮች፡፡

  2. ካይሮ ከሚገኙ መንፈሳውያት ማኅበራት ጉባኤ አባላትን፣ የአህጉረ ስብከት ተመራጮችን፣ በከተማዎች ያሉ የክርስቲያናዊ ሕግ አስፈጻሚዎች፣ በከተማ ያሉ ታዋቂ መራጮችን፡፡

  3. ከመላው ካይሮ 24 ቀሳውስት 7ቱ ከአሌክሳንድርያ የሆኑ፡፡

  4. የቀድሞ ጊዜና የአሁን የመጅሊስ አልሚሊስ የኮፕቲክ ፓርላማ አባላት፡፡

  5. የጠቅላላ ሚሊ ጉባኤ የቀድሞና የአሁን አባላት፡፡

  6. የጠቅላላ ሚሊ ጉባኤ የቀድሞና የአሁን አባላት፡፡

  7. በአስመራጭ ኮሚቴው የተመረጡ  ከካይሮ 72 አስመራጮች ከእነርሱም መካከል 24ቱ ከአሌክሳንድርያ የሆኑ፡፡

  8. ከእያንዳንዱ ሀገረ ስብከት የተመረጡ 12 ድምጽ ሰጪዎች ሜትሮፓሊቲኑ ወይም ጳጳሱ በሚመራው ኮሚቴ የተመረጡ፡፡

  9. ወይም የአህጉረ ስብከት ጳጳሳት 5 መራጮች የተካተቱበት አካል፡፡

  10. ዕለታዊ ጋዜጣ አዟሪዎችና ዋና አዘጋጆችም እነርሱም የጋዘጠኞች ማኅበር አባላት የሆኑ፡፡

 

የመጀመሪያወቹ አምስቱ ድምጽ ሰጪዎች /መራጮች/ ዝርዝር ዐቃቤ መንበሩ በሚልከው ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

በ6ኛው ተራ ቁጥር የተቀመጡ ድምጽ ሰጪዎች ዝርዝር በአስመራጭ ኮሚቴው ይላካል፡፡

በ7ኛ ተራ ቁጥር የተላኩ ድምጽ ሰጪዎች በሜትሮ ፓሊታን አማካኝነት ይላካሉ፡፡

በ8ኛው ምድብ ላይ ያሉ ድምጽ ሰጪዎች በጋዜጠኞች ጉባኤ አማካኝነት ይላካል፡፡

የፓትርያክነት ምርጫ ቅስቀሳው ከተጀመረ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የመራጮች ዝርዝር ያለምንም ክፍያ ይከናወናል፡፡

 

አንቀጽ 10

  • የመጨረሻውን የመራጮችን ዝርዝር እንደተጠቃለለ በአረብኛ ቋንቋ በሚታተሙ ሦስት ጋዜጦች ካይሮ ውስጥ ይገለጣል፡፡

  • ስማቸው በስህተት በመጨረሻው ዝርዝር ውስጥ ያልተካተተ መራጮች ዝርዝሩ እንዲስተካከል ማመልከት ይችላሉ፡፡ ጉዳዩም ዐቃቤ መንበሩ በሚመራው ኮሚቴ ይታያል፡፡ ከምርጫ አስፈጻሚ መካከል የተመረጡ ሁለት አባላት አብረው ይሆናሉ፡፡ ከሁለቱ አንዱ ካህን ይሆናል፡፡ ይህ ኮሚቴ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻው ይሆናል፡፡ ነገር ግን በስድስተኛውና በሰባተኛው ተራ ቁጥር በአንቀጽ 9 የገለጥነውን መራጭ ኮሚቴው አለመቀበሉ አስፈላጊ መስሎ ከታየው የምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴው ተቀባይነት ያላገኙ መራጮችን ተክተው የሚመዘገቡ ሌሎች መራጮችን መውሰድ መብት አለው፡፡

አንቀጽ 11

  • ስማቸው በምርጫው ጠረንጴዛ ላይ የተካተተ መራጮች ስማቸው ሓላፊነታቸው ሥራቸው ዕድሜአቸው ወደ ምርጫ የገቡበት ጊዜ የምርጫ ቁጥራቸውን የሚያሳይ መታወቂያ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህንን መታወቂያ የመስጠቱ ሓላፊነት የምዝገባ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይም የአጥቢያ ሜትሮፓሊን ወይም ጳጳስ ይሆናል ይህም መራጩ በሚኖርበት አካባቢ ነው፡፡

  • መራጮች መታወቂያቸውን ለመውሰዳቸው መፈረም ይኖርባቸዋል፡፡ መታወቂያውን የሰጠው ወገን ፊርማውን ያስቀምጣል፡፡ ከምርጫው አስቀድሞ ባሉት 15 ቀናት የሚከናወን ይሆናል፡፡

 

2. የምርጫ ሂደት

አንቀጽ 12

  • አስመራጭ ኮሚቴው ዐቃቤ መንበሩን ሰብሳቢ ሦስት ካህናት በቅዱስ ሲኖዶስ የተመረጡ ሦስት አካላት በሰያሚ ኮሚቴው /nomination committee/ የተመረጡ ከምርጫው ከሦስት ቀን አስቀድሞ ይሠየማሉ፡፡ የቃለ ጉባኤውን ሥራ ሰብሳቢው ደስ ያለውን ሰው በመሰየም ያስይዛል፡፡

  • በኮሚቴው ሰብሳቢ ጥያቄ የምርጫ ሂደቱን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲከታተለው ይደረጋል፡፡ ሰብሳቢው ከአቅም በላይ በሆነ ችግር ለመገኘት ባይቻለው ከሜትሮ ፓሊታን መካከል  የሰብሳቢውን ሥራ ተክቶ ይሠራል፡፡ ከኮሚቴው አባላት የጎደለ ቢኖር ከአጠቃላይ ምርጫ ጉባኤው መካከል የሚተካ ሰውን ሰብሳቢው ይመርጣል፡፡

 

አንቀጽ 13

  • ምርጫው በሚካሄድበት ቀን አስቀድመን የገለጥነው ኮሚቴ በፓትርያርኩ ቤት መገኘት ይኖርበታል፡፡ ምርጫው ከ 3፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 11፡00 ሰዓት ድረስ ይከናወናል በቀኑ በ11ኛው ሰዓት ድምጽ መስጠት ያልቻለ መራጭ ቢኖር ኮሚቴው ዝርዝራቸውን ተናግሮ ሁሉንም ድምጽ ይሁንታ እስከሚያገኝ ሥራውን ይቀጥላል፡፡

 

አንቀጽ 14

  • ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከሚመጡ ድምጽ ሰጪዎች በስተቀር /እነርሱ በራሳቸው ወይም ሕጋዊ በሆኑ ወኪሎቻቸው አማካኝነት የሚፈጽሙት ሆኖ ስም ዝርዝርራቸው በምርጫ ጠረጴዛው ላይ ከሰፈረ ውጪ በሕጉ ላይ እንደተቀመጠው

  1. ሜትሮፓሊቲንና ጳጳሳት፡፡
  2. የንጉሡ ተወካይ፡፡
  3. በመላው ግብጽ የታወቁ 24 ሰዎች ይህም በንጉሡ በፕሬዝዳንቱ የሚሰየሙ ይካተታሉ፡፡

 

አንቀጽ 15

  • በምርጫ ጠረጴዛው ላይ አስቀድሞ የስም ዝርዝርራቸው ባለ መራጮች ቁጥር ልክ ካርዶች ይዘጋጃሉ፤ ካርዶቹ በሊቀ መንበሩ /በምርጫ ኮሚቴ ስብሰባው ማኅተም መታተም  ይኖርባቸዋል፤ ለእያንዳንዱ መራጭም ይሰጣል፤ ወደ ምርጫው አደባባይ ሲመጡ ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ካርዱ የመራጩ ስም የምርጫ ቁጥር ይኖረዋል፡፡ ድምጽ ሰጪው ካርዱን ለመውሰዱ ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀው መዝገብ ላይ በፊርማው ያረጋግጣል፡፡

  • ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት ውስጥ ካርድ ያልወሰዱ ካሉ፣ ካርዱ የሌሉ ሰዎች ካርድ በሚቀመጥበት ኤንቨሎፕ ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ለምርጫ ኮሚቴው ሊቀመንበርም ይሰጣል፡፡ ኤንቨሎፑን ካሸገ በኋላ ቀዶ ማኅተም ያደርግበታል፡፡

  • በአስመራጭ ኮሚቴው የተመረጡ 6 ድምጽ ሰጪዎች ያሉበት ኮሚቴ ከምርጫው 3 ቀን አስቀድሞ ካርዶቹን ያስረክባል ምርጫውንም ይቆጣጠራል፡፡

 

አንቀጽ 16

  • ድምጽ ሰጪዎች በአስመራጭ ኮሚቴ ፊት ሲቀርቡ ለጸሐፊው የምርጫ ካርዶቸውን መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ጸሐፊው ካርዱን አትሞ ለዚህ ዓላማ በተዘጋጀው ሳጥን ውስጥ ይከታል፡፡ መራጮች የምርጫ ወረቀት ይጧቸዋል የመረጡትን ሰው ስም ይይዛል፡፡

  • የዕጣ መጣሉ ሁኔታ በተወሰነ አግባብ ውስጥ የሚካሄድ ነው፡፡ ድምጽ የሚሰጠው ሰው ለድምጽ መስጫ በተከለለ ምስጢራዊ ቦታ ሊመርጥ ያሰበውን ዕጩ ያስቀምጣል፡፡ ድምጽ ሰጪዎች በምርጫ ወረቀቱ ላይ ምልክት ባያስቀምጡ ማንነታቸውን የሚገልጽ ነገር ባይኖረው ወረቀቱ ዋጋ አይኖረውም፡፡

 

አንቀጽ 17

  • የምርጫ ሂደቱ ከተጠቃለለ በኋላ ኮሚቴው የመራጭ ሰዎችን ካርድ ይቆጥራል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ቁጥር ከመራጮች ካርድ እና ከቀሪዎች ካርድ ጋር ተደምሮ የተመዝጋቢዎችን አጠቃላይ ቁጥር መስጠቱ ይመሳከራል ይህም የኢትዩጵያ ተወካዮች ቁጥር ጨምሮ ነው፡፡

  • ጸሐፊው ይህንን ሁኔታ በቃለ ጉባኤው ላይ ካሰፈረ በኋላ ኮሚቴው ድምጹን ይለያል ከምርጫው ጋር በተያያዘ ጉዳዮች ላይ ውሳኔውን ያሳልፋል፡፡ እያንዳንዱ መራጭ በሰጠው ድምጽ ላይ ያሰፈረውን አስተያየት ተአማኒነት ይመረመራል፡፡

  • ኮሚቴው የሚሰጠው ይሁንታ አስተያየት ምስጢራዊ ነው፡፡ ውሳኔውንም የሚተላለፈው በሚቆጠረው ድምጽ ይሆናል፡፡ የተሰጠው ድምጽ እኩል ሲሆን ዐቃቤ መንበሩ የሚሰጠው ውሳኔ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

  • የድምጽ ቆጠራው ከተጠናቀቀ በኋላ ሊቀ መንበሩ የመጨረሻዎቹን ሦስት እጩዎች ስም ዝርዝር ያሳውቃል፡፡ እነርሱም የብልጫውን ድምጽ ያገኙ ናቸው፡፡ የኮሚቴው ጸሐፊ ሁለት ኮፒ ቃለ ጉባኤውን ያረቅቃል ዐቃቤ መንበሩ ይፈርምበታል፡፡ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካዮችም ይፈርማሉ፡፡

  • ምርጫው በተካሄደበት እሑድ ምዝገባው ይካሄዳል፡፡ ይሄውም ከላይ ለተገለጸው ሚኒስትር መ/ቤት 1 ኮፒ ቃለ ጉባኤ ይላካል/ቀሪው ካይሮ በሚገኘው የመንበረ ፓትርያርክ ጽ/ቤት ይቀመጣል፡፡ የምርጫ ሂደት ወረቀቶች በኤንቨሎፕ ቀይ ማኅተም ታትሞባቸው በፓትርያርኩ ጽ/ቤት ይቀመጣሉ፡፡

 

አንቀጽ 18

  • በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት ዐቃቤ መንበር ዕጣው የሚጣልበትን ሁኔታ ያመቻቻል፡፡ በዕጣ መጣሉ ሂደት ያሸነፈውን ዕጩ ስም ዐቃቤ መንበሩ ፈርሞበት ሁለት ኮፒ ቃለ ጉባኤ ይጻፋል፡፡ በምርጫ ኮሚቴው ስምና ፊርማ ይጸድቃል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ፊርማቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ የዕጩ ጥቆማ አስተባባሪ ኮሚቴም እንዲሁ ፊርማቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ አንዲ ኮፒ ለሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ይላካል፡፡

  • በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት መሠረት የተሾመው ፓትርያርክ በመላ ሀገሪቱ ይገለጣል፡፡

 

ምዕራፍ 4

ጠቅላላ ደንብና ከጊዜ ጋር የተያያዙ ደንቦች

 

አንቀጽ 19

አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የዕጩ አፈላላጊ ኮሚቴው /nomination committee/ በዚህ ሕግ ውስጥ የተቀመጠውን ጊዜ የማሳጠር ሥልጣኑ አለው፡፡ ይህም በጋራ በሚደረግ ውሳኔ ነው፡፡

ሃይማኖታውያን መስለው ከሚመጡ መናፍቃን ተጠንቀቁ ማቴ 7፥15

መስከረም 8 ቀን 2005 ዓ.ም.


አባ ዘሚካኤል

  • የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት፣ ቋንቋና ዜማ  የመቀራመቱ  ዘመቻ ይቁም!

ትላንት ተዋሕዶን በማናናቅ ምእመናኑን ለማስኮብለል ያልተሳካላቸው መናፍቃን፣ ዛሬ ደግሞ ስልት ቀይሰው የተዋሕዶን ታሪክ፣ ግዕዝ ጠቀሳና ያሬዳዊ ዜማን ያደነቁ በመምሰልየመፈታተናቸው አንድምታው ምን ይሆን? የተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት የመቀራመቱ ድፍረትሳ ተመሳስሎ ተጠግቶ ማንነትዋን ለመጋራት ይሆን?ዓላማው መጀመሪያ ምእመኑን የማዘናጋት ቀጥሎ አንድነን ለማለትና ወደመናፍቅነት ለመሳብ ከዚያም እንደ ሰለጠነው ዓለም ፍጹም ዓለማዊ ለማድረግ ይሆንን?

 

መጽሐፍ ተዓቀቡኬ እምሐሳውያን ነቢያት እለይመጽኡ ሀቤክሙ በአልባሰ አባግዕ፣ የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡ ሐሰተኞች፣ መናፍቃን፣ መምህራን ተጠንቀቁ፣ ወእንተ ውስጦሙሰ ተኩላት መሰጥ እሙንቱ፡፡በውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላ ናቸው፣ ቢመረምሩዋቸው ግን ሰውን እየነጠቁ ወደ ገኀነም የሚያወርዱ የሰይጣን ሰራዊት ናቸው፡፡ (ወንጌል አንድምታማቴ 7፥15)

 

ይህን የወንጌል አሳብ እንደሚያስረዳን መናፍቃን ዓለማውያን የሚጠነስሱት ሴራና ፈጠራ ጌታችን መድኀኒታችንኢየሱስ ክርስቶስ ካስተማረው የማስጠንቀቂያ ትንቢት ቃል ውጭ የሆነ ያልታወቀ፣ ያልተረዳአዲስ ነገር ሊሆን አይችልም፡፡አስቀድሞ”በስሜ ይመጣሉ” ብሎ ተናግሯልና፡፡ ለዚህምቀጥሎ የተመለከተውን የበግ ለምድ ምሳሌ ዝርዘር እንመልከት፣

 

  1. የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡ ተኩላ ያላቸውእውነተኛ መስለው የሚመጡ ሐሰተኞች መምህራንን ነው፣ ነገር ግን በእውነተኛ ሃይማኖት ጸንተው ያሉትን ክርስቲያኖች ተመሳስለው ገብተው በተለያየ ዘዴ ምእመኑን በመቀሰጥናከእምነቱ በማናጋት ወደገሃነም ለማውረድ የሚሠሩትን የዲያብሎስንሠራተኞች ነው፡፡

  2. የበግ ለምድ መልበስምሳሌ የሚያሳየውማስመሰያአሠራራቸውን፣ ድራማ መሰል ጥረታቸውን ነው፡፡ተኩላ ለምድ የሚለብስሆኖ አይደለም፣ ተኩላ ለምድን ከሚለበስ ቢበላው ይመርጣልና፡፡ መናፍቃንም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ባትኖር ይመርጣሉ፣ ነገር ግን ሊውጡት ያሰቡትን ምእመን እንደ ተኩላ ለመንጠቅ ያመቻቸው ዘንድ የቤተ ክርስቲያኗን ግእዝና ዜማ የወደዱ መስለው መታየት የጀመሩትምእመኑን ለማዘናጋት የፈጠሩት አዲሱ ዘዴ ነው፡፡ ነገር ግን ግብራቸው የተኩላ ግብርእንዲመስል፣ ለነዚህ ቀሳጥያን ጌታችንአስቀድሞ ሲመስልባቸው የበግ ለምድ ለብሰው የሚመጡ ተኩላ ነጣቂ አላቸው፡፡ ይህም ተኩላ በግን ለመምሰል የበግን ቆዳ ቢለብስ እንዳይዋሐደውና በግን እንዳይመስል እነሱም እንደ ድራማ ትምህርቱን ልስበከው፣ ዜማውን ላዚመው፣ ቅዳሴውን ልቀድሰው፣መዝሙሩን ልዘምረው ወዘተ ብለው ቢጥሩ እውነተኛውን የተዋሕዶ አገልጋይ፣ አማኝእና ክርስቲያን መሆን አይቻላቸውም፡፡

  3. የበግ ለምድ የተባለው ምሳሌ፣ለምድ የበግ አካል የነበረ እንጂ የተኩላ አካል አይደለም፣ተኩላው ከላይ ለምዱን ቢደርበው አካል ሆኖት ደመ ነፍስ እንዳይዘራና ተኩላ በግ እንዳይሆን ሁሉ መናፍቃንም የተዋሕዶን አሠራር ሳያምኑበት በማስመሰልና ማቅረብ ቢሞክሩም እንኳን ውጤቱ ሕይወት አልባ ዳንኪራ፣ በቀቢጸ ተስፋ ያቀረቡት ሙሾ አስመስሎባቸዋል፡፡ በእሁኑ ወቅት የጀመሩት የተዋሕዶ ምእመናን የሚወዱትን ግዕዝ መጥቀስ፣ ያሬዳዊ ዜማን አስመስሎ ለማቅረብ የተሞከረው ሕይወት አልባ እንቅስቃሴየዚህ ማሳያ ነው፡፡የተዋሕዶ ሕዝብ ማስተዋል ያለበትይህን ሕይወት አልባ ሩጫ፣ ክርስቲያን ሳይሆኑ ክርስቲያንን ለማታለል ያደረጉት  የቅስጥ ድራማ መሆኑን ነው፡፡

 

በወንጌል ትርጓሜ እነዚህን ቀሳጥያን በሁለት ዓይነት ይገልጻቸዋል፣

  1. ሃይማኖተኛ የሚመስሉ መናፍቃን መምህራን

  2. መንፈሳውያን የሚመሰሉ ሥጋውያን መምህራን ይላቸዋል፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት ሁለቱ በተገቢው ሃይማኖት ላልተረዱ ሰዎች አደገኛ ናቸው፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ይገልጻቸዋል ስለመናፍቅነታቸው፣ የዋጃቸውን ጌታ ክደው … የሚያጠፋ ኑፋቄ አሾልከው ያገባሉ፡፡ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሏቸዋል፡፡ ስለ ሥጋዊነታቸው ደግሞ … ይልቁንም በርኲሰት ምኞት የሥጋን ፍትወት እየተከተሉ የሚመላለሱ … ነውረኞችና ርኲሳን … ምንዝር የሞላባቸው ኀጢአትንም የማይተው ዓይኖች አሏቸው የማይጸኑትን ነፍሳት ያታልላሉ፣ መመኘትን የለመደ ልብ አላቸው የተረገሙ ናቸው (1ጴጥ 2፥1-16)ይላል፡፡

 

እነዚህ ሃይማኖተኛና መንፈሳውያን የሚመሰሉ የቤተ ክርሰቲያን ጠላቶችን ከላይ ከቅዱስ መጽሐፍ እንደተገለጸው፣ ምእመናን ማንነታቸውንና ዓላማቸውን መረዳት አለብን፡፡ ማንነታቸው መጽሐፍ እንደጠቀሰው ተኩላነት ነው፣ ማለትም ምንም ግእዝ ቢጠቅሱ ወይም ላላዋቂ ያሬዳዊ ዜማ ያዜምኩ ቢመስሉ እነሱ በልባቸው ከሃዲያን ናቸው፡፡ዓላማቸውም በመመሳሰልአቀራረብ ተቀባይነትን አግኝተው፣ ይህን እግዚአብሔርን የሚያከብር ሕዝብ ከእምነቱ ለማናጋት ነው፡፡

 

በመመሳሰል ”የማይጸኑ ነፍሳትን ያታልላሉ” እንዲል፣ ክርሰቲያን ልብ ሊለው የሚገባው ዋናው ነገር፣ የተዋሕዶ ተጻራሪዎች ሁሉ ሁል ጊዜ የመመሳሰል ስልታቸውን በመቀያየር ያልጸኑትን ምእመንዋን መሻማት የዘመናት አሠራራቸው እንደሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ የፖርቱጋል ካቶሊክ ሚሲዮናውያን የካቶሊክ እምነትን ወደ አገራችን ለማስገባት በተለይ ቤርሙዴዝ፣ አንድሬ አብያዶ፣ ጴጥሮስ ፖኤዝና አልፎኑስ ሜንደዝ ወዘተ ተልከው ነበር፡፡ ከእነዚህ አብዛኞቹ ወደ አገራችን ሲመጡ ሆን ብለው አጥንተው ግእዝን መናገርናየያሬዳዊን ዜማ እስከማዜም የደረሱ ነበሩ፡፡ እንዲያውም በሮም ቫቲካን የኢትዮጵያ ኮሌጅ በማቋቋም የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያንን ቋንቋግእዝን የሚናገሩና ያሬዳዊን ዜማ የሚያዜሙ ነጮችን በመላክ የጎንደርን ቤተ መንግሥት እንዴት ሲያተራምሱት እንደ ነበሩ ታሪክያስረዳናል፡፡ ዛሬም የመመሳሰል ዓላማቸውን እውን ለማድረግ በአገር ውስጥ እንቅስቃሴአቸው የተለያየ ገጽታዎች ሲያሳዩ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ይህንኑ ክብር ታቦትና ማኅሌት የሚወድ ህዝብን ለማታለልና ወደራሳቸው ለማስገባት አንድ ነን የሚል ስብከት፣ በዋና ዋና ከተሞች ባላቸው የጸሎት ቤት ታቦት አለን፣ ማኅሌት ይቆማል ሲሉ፣ ፕሮቴስታንት በበዙበት በሚመሰላቸው አካባቢ ደግሞ ፕሮቴስታንትንመመሳሰልይስተዋልባቸዋል፡፡ ሌሎችምየመመሳሰል አባዜ የተጠናወታቸው መናፍቃን እና ሥጋውያን እንደተለመደው ውጫውያንም ሆኑ የአገራችን በተለይ ከተዋሕዶ የወጡ ማለትም በቀሳጢዎች የተበሉ ካፈርኩ አይመልሰኝ እንዲል በቁጭት ሁል ጊዜ ይህንን ሕዝብ በመጎምዠት ለአጋንንት አሳልፈው ለመሰጠት ሲቋምጡና ለመንጠቅ ሲተጉይገኛሉ፡፡

 

ከላይ በግልጽ ለይተን አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ማንነት ባጭሩ ማብራራት እንደሞከርነው ሁሉ፣ ለምን ስልታቸውን መቀያየር አስፈለጋቸው የሚለውን ማየት ግድ ይለናል፡፡ ስልታቸውን መቀያየር ያስፈለገበት ምክንያት የተዋሕዶ እምነትና ሥርዓት አንዳች የማመን ፍላጎት አድሮባቸው አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ሲወቅሱና ሲከሱ ነበርና፡፡

 

ለዚህ ምክንያት የደረሰባቸውን ክስረት መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ይህም፡-

  1. የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባደረገችው ጸረ ተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ ህዝቡን በማስተማሯ ህዝቡ እኲይ ተግባራቸውን ስለተረዳ

  2. ህዝቡ ራሱ መልስ በመስጠት ራሱን መከላከል ስለጀመረ

  3. በስህተት መንገዳቸው ተጉዞ የነበረው ሕዝብ ወደ ቤቱ መመለስ ስለጀመረ

  4. ቤተ ክርስቲያኗን በማጥላላት ያደረጉት ዘመቻ በመክሸፉ እንደማያዋጣቸው ስለተረዱ

  5. ከቤተ ክርሰቲያኗ ህዘቡን እየደለሉ በማስኮብለል የሚያገኙት ይሁዳዊ ምንደኝነት ስለቀረባቸው

  6. የካሴት ሽያጭ፣ የህዝቡ መዋጮ ወዘተ ገቢ ስለቀረባቸው ፤ ወዘተ ነው፡፡

 

ከላይ የተዘረዘረውና ሌላም የኪሳራ ምክንያቶቻቸውሳይወዱ በግድ ልባቸውን ጸፍቶ አፋቸውን ከፍቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ክርስቲያኑ ሁሉ ይህን ሁኔታ በቀላሉ ማየትናበዝምታ ማለፉ ተገቢ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ክስረት ያናጋው መናፍቅ ከዚህ የበለጠ ሌላ የድፍረት ዘዴ ለመፍጠር መሞከሩ አይቀሬ ነው፡፡ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይበግእዝና በያሬዳዊ ዜማ ያዘጋጁት ዝግጅት ገበያ ተኮርያውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናንን ማእከል ያደረገ መሆኑን ነው፡፡ልንረዳው የሚገባን አንዳንድ ምእመናን የማስመሰል ተንኮላቸውን ባለመረዳት ካሴታቸውን መግዛትና ማዳመጥ ሁለት አደጋ ያመጣባቸዋል፣ አንደኛው በመናፍቅ መንፈስ የተዘጋጀው ዜማ ማዳመጥ ራሱ ቆይቶ መናፍቅ ሚያደርግ መሆኑን፣ ሁለተኛው የመናፍቃን ከኪሳራቸው አንዱ ገንዘብ በመሆኑ አማኙን ህዝብ የሚያስቱበትን ገንዘብ ለነሱ መገበር ራሱ ከመናፍቅነት አይለይም፡፡

 

የአሁኑየለየላቸው መናፍቃን ወዳጅ የመምስል ስልታቸው ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ተኩላ በግን ለመምሰል ቆዳ ብትደርት ተኩላነቷን እንዳይቀይር ሁሉ ምእመናንን ያታልላሉ መስሎአቸው አንዴ ግእዙን አንዴ ዜማውን ያልኩ ቢመስላቸውም ”ዪህቺ ጠጋጠጋ … ” እንዲሉ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ይህ መሰሪነታቸው ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም ዓላማቸው የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ፣ ታሪኳን ተናጋሪ፣ ዜማዋን ወዳጅ፣ ጥንታዊነቷን አክባሪ ወዘተ በመምሰል የህዝቡን ልብ ለማግኘት የተዘየደ ዘዴ ለማንም አይጠፋውም፡፡ ነገር ግን ዘዴው ጊዜ ያለፈበት ድሮ በነ ዐጼ ሱሱንዮስ ዘመን እነ አልፎኑስ ሜንደዝ የሞከሩት ነገር ግን እነ ዐጼ ፋሲል አውቀውት ምላሽ የሰጡበት፣ የማይረሳ ጠባሳ ጥሎ ያለፈ መሆኑ ወገኔ ትዝ ሊለው ግድ ይለዋል፣ የብዙ ክርስቲያን ደም ተከፍሎበታልና፡፡ አሁንም ይህች መመሳሰልና ቀይ መስመር መጣስ የነ አልፎኑስ ሜንደዝ ድፍረት ጋር አንድ ናትና ከወዲሁ ካልታሰበባት በኋላ ከባድ ዋጋ እንዳታስከፍል ስጋታችን ነው፡፡

 

ዋናው ጉዳይ ባለፈው በተካሄደው የጸረ ተሐድሶ ዘመቻ መናፍቃን የፈራረሰባቸውን ሁለንተናዊ ክስረት ማለት በቤተ ክርሰቲያኗ ውስጥ ምእመኑን መናፍቅ የማድረግ ቅሰጣ ሲመታባቸውና ሴራው ሲከሽፍባቸው፣ ውድቀታቸውን መልሶ ለመገንባት ስፖንሰራቸው የሰጣቸው አዲሱ አሰራር  በግልጽ ውዳሴ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንቋንቋ ግእዝ፣ ዜማዋ፣ ታሪኳ ወዘተ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ የለየላቸው መናፍቃን ደርሶ የቤተ ክርስቲያኗወዳጅ መምሰል ለኛ አዲስ ነገር አይደለም፤ ተሐድሶቹም ሲጠቀሙበት የነበረ ስልት ነው፡፡ የተሐድሶ መናፍቃን ዘመቻ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላይ በሚለው መጽሐፍ (በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያየማኅበረ ቅዱሳን ዶክሜንቴሽን ክፍል፣ ቁጥር 1፣ ሚያዝያ 2003 ዓም ገጽ 58)  እንደተጠቀሰው ተሐድሶዎች ያቀዱት ዋና ጉዳይ ተሐድሶ እንኳን እንደሆነ የማያውቅ ግን ተሐድሶ የሆነ ትውልድ መፍጠር እና ሳያውቀው የሚደግፍ ቲፎዞ ማፍራት ነበር፡፡ ማለትም በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ሆኖ የመናፍቅን ዶግማ የተቀበለ የእነሱን ዜማ የሚያዜም ወዘተ ቡድን ማመቻቸት ነበረ፡፡ ስልቶቹን መጽሐፉ እንዲህ ይጠቅሳቸዋል፣

 

  • ተቆርቋሪ መምሰል፣ ገንዘብና እርዳታ በመስጠት፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ተቋማትና ሕዝቡን መያዝ እና ቲፎዞ እንዲሆን ማድረግ፣

  • ኦርቶዶክስን የማያውቅ፣ ፕሮቴስታንት የሆነ፣ ነገር ግን ተሐድሶ (ፕሮቴስታንት) መሆኑን እንኳ የማያውቅ ምእመን ማፍራት፡፡ ማተብ ያሰረ፣ ነጠላ የሚያጣፋ፣ እምነቱና መንፈሱ ግንፕሮቴሰታንት የሆነ፣ ሆኖም ፕሮቴስታንት ነኝ የማይል (ፕሮቴስታንት መሆኑን ሳያውቅ ስለተለወጠ)፣ ”እኔ ኦርቶዶክስ ነኝ” እያለ የሚናገር(ሀርድ ዌሩ ሳይቀየር ሶፍት ዌሩ የተቀየረ)ትውልድ ማፍራት ነው፡፡

 

እንዲሁም በዚህ ወቅት ፕሮቴስታንቱ በግልጽ መሰደቡንና መወገዙን በውስጥ አድርገው በውጪ ውዳሴ የጀመሩት፣ የኦርቶዶክስ ምእመናንን በመመሳሰል ለመሳብና ቢቻላቸው ፕሮቴስታንት ለማድረግ ባይሆንም ቲፎዞ ለማድረግ፣ እንዲሁም ቲፎዞ በመሆን መካከል  በሚፈጠረው ያለመግባባት ክፍተት ያልጸኑትን ለማግኘት ነው፡፡

 

ባጠቃላይምከላይ እንደገለጽነው መናፍቃን ምን ጊዜም የተወሰነ ሃይማኖታዊ የትውፊት፣ የዶግማ፣ የሥርዓት ወዘተ ገደብ የሌላቸው በመሆኑ የሌላውን መንጋ ለመቀሰጥ ቢቻላቸው በማጥላላት ባይቻላቸው በመመሳሰል ራሳቸውን እየለዋወጡ የተለያየ ስልት እንሚጠቀሙ መረዳት ተገቢ ነው፡፡ ለመመሳሰል በሚያደርጉት ቅሰጣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዘመናት ያቆየችውን ትውፊት፣ ቅርስና ሀብት እንዲሁም ግእዝ ቋንቋና ያሬዳዊ ዜማን ማንም እንደፈለገ አስመስሎ ባልተገባ መንገድ የመቀራመቱ ድፍረት ቤተ ክርስቲያን እንዴት ታየዋለች? ያውም ቤተ ክርስቲያን የማትፈቅደው የመናፍቅ ድርጅት በሀብቷ ላይ ሲፈነጭ፣ ይህስ ጉዳይ ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል? አንድ ተቋም ያላትን ሀብት ያለፈቃዷ ማንም መጠቀም ይችላልን? ምእመናን በሙሉ በተለይ የሕግ ባለሙያ ልጆቿ እንዲነጋገሩበት የሚስፈልግ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ምእመናን መገንዘብ የሚገባን መናፍቅ ያወጣውን የቅስጥ ዜማ ያሬዳዊ መስሎን በመጠቀም የዓላማቸው ሰለባ እንዳንሆን አንዱ ለሌላው ማሳሰብና ማስረዳት ተገቢ ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የበግ ለምድ ለብሰው ማለት እውነተኞች መስለው ከሚመጡ ሐሰተኞች፣ ሃይማኖታውያን መስለው ከሚመጡ መናፍቃን፣ መንፈሳውያን መስለው ከሚመጡ ሥጋውያን መምህራን ተጠንቀቁ ብሎ አስተምሮናልና እንጠንቀቅ፣ እርስ በርሳችንም እንጠባበቅ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፡፡


ከምርጫው ይልቅ ለቅድመ ምርጫው!!

መስከረም 8 ቀን 2005 ዓ.ም.


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

 

የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ይህን ያህል ዘመን ተጉዛ ከዚህ የደረሰችው በተአምር ብቻ አይደለም፡፡ ሁል ጊዜ በጽኑ እምነትና ምግባር እግዚአብሔርን በማመስገንና ሰውን በማገልገል የታወቁ እልፍ አእላፍ ቅዱሳን ካህናትና ምእመናን በውስጧ በመኖራቸው ነው፡፡ በእነዚህ ቅዱሳን አበው በየቦታው ትምህርት ቤቶች እንዲስፋፉና መጻሕፍትም እንዲበዙ የተደረገውም ጥረት ለዚህ ታሪካዊ ዕድገት ያበረከተው አስተዋፅኦ የታሪክ ትዝታ ብቻ ሳይሆን አሁንም በተግባር የሚታይ ሐቅ ነው፡፡

 

በዚህ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ሢመተ ጵጵስና በኢትዮጵያ የክርስትና ሕይወት መንፈሳዊና ማኅበራዊ የታሪክ ጉዞ ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ አለው፡፡ በአራተኛው ምዕት ዓመት ሀገራችን የሙሉ ምሥጢረ ቤተ ክርስቲያን ባለቤት በመሆን ፍጹም በረከተ መንፈስ ቅዱስን ተቀበለች፡፡ በዚህም ወቅት ዛሬ ያለችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በመንበረ ጵጵስና ደረጃ ተቋቋመች፡፡

 

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደ ቀለምና ብራና እንደ ቃልና አንደበትም ተዋሕደው “ከኀይል ወደ ኀይል” ከክብር ወደ ክብር፣ ከበረከትም ወደ በረከት ሲጓዙም ኖረዋል፡፡ እንደገናም “በጸጋ ላይ ጸጋን ተቀበልን” እንደተባለው ከ1951 ዓ.ም. አንሥቶ ላለፉት 53 ዓመታት በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት የምናከብረውን ፓትርያርካዊ ክብር ተጎናጸፈች፡፡ አክሊለ በረከትን ተቀዳጀች፤ ፓትርያርካዊ በትረ ክህነትን ጨበጠች፤ መንበረ ፓትርያርክንም ዘረጋች፡፡ ይህን የረጅም ጊዜ ጉዞ ስንመለከት የቤተ ክርስቲያናችን ዕድገትና ልዕልና በከፍተኛ ጥረትና መሥዋዕትነት የተገኙ መሆናቸውን እንረዳለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያናችን ምን ጊዜም አገልግሎቷን ሳታቋርጥ ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን ስታበረክት ኖራለች፡፡ ይሁን እንጂ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ያለች እንደመሆንዋ በዚህ ጉዞ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ከተፅዕኖ ነጻ አልነበረችም፡፡ በእግዚአብሔር ኀይል ያጋጠሟትን ፈተናዎች እየተቋቋመች እዚህ ደርሳለች፡፡

 

ከዚህ ተጨባጭ ሐቅ ስንነሣ ያካሄድናቸው ሢመተ ፕትርክናዎች ሁሉ በተቀመጠው ቀኖናዊ አግባብና በሚፈለገው አቋምና ብቃት ሥሉጣን /የተፋጠኑ/ ሆነው የተጓዙ ነበሩ ብለን በሙሉ ድፍረት መናገር አንችልም፡፡ በርግጥ በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ዓለም የሰው ልጆች ከመካከላቸው ብልጫ ያለውን ሰው ለከፍተኛ ሓላፊነት ይመርጣሉ፡፡ አንዱን ሰው ከሌላው የበለጠ የሚያደርገው ለመንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ያለው ቅንና ቆራጥ አስተሳሰብ፣ አቅም ያለው የሥራ አፈጻጸምና የመሳሰለው መልካም ሥራ ሚዛን ሲደፋ እንደሆነም እንገነዘባለን፡፡

 

በዕለታዊ የሥራ አፈጻጸምና በማኅበራዊ አገልግሎት ከሁሉ የበለጠ አስተዋፅኦ በማድረግ የተመሰከረለትን ሰው ለከፍተኛ ሓላፊነት መምረጥ ተመራጩን ለመጥቀም ሳይሆን ሥራውን በማክበር ተገልጋዩን ወገን በበለጠ ለማገልገል ነው፡፡ ይህም የመራጮችን አስተዋይነትና ለትክክለኛ ዓላማ የቆሙ መሆናቸውን ይገልጣል፡፡ የተጓዝንበትም መንገድ መመዘን ያለበት አንዱ ከዚህ መሆን እንደአለበትም እናምናለን፡፡

 

ከዚህ አኳያ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ የሚያስፈልጋት ፓትርያርክ ምን ዓይነት አባት ነው የሚለው ጥያቄ የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ቢሆንም ይህን ጥያቄ ሊመልስ የሚችለው ምርጫው በራሱ ሳይሆን የምርጫው መደላደል መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ከምርጫው ይልቅ ለቅድመ ምርጫው ቅድሚያ መስጠት የወቅቱ ግዴታ ሊሆን ይገባል፡፡

 

በቅዱስ ሲሄዶስ መሪነት፣ ሊቃውንት ካህናትና ምእመናን በነጻ አሳብና በመንፈሳዊ ትብብር እየተመካከሩ ያለምንም አድልዎና ተፅዕኖ መንፈሳዊ አባታቸውን መምረጥ እንዲችሉና ተመራጩም የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ሳይነሣበት ቤተ ክርስቲያኒቱን በሰላምና በአንድነት እንዲመራ ከምርጫው ይልቅ አሁንም ለምርጫው የሚያስፈልጉ መደላድሎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል እንላለን፡፡

 

ከእነዚህም መደላድሎች ውስጥ ዋናዎቹ ሦስት ናቸው፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛው የአራተኛውን ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን መሰደድና የአምስተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስን ሢመተ ፕትርክና ተከትሎ የተከሰተው የቤተ ክርስቲያን ለሁለት መከፈል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተጀመረው ቤተ ክርስቲያንን አንድ የማድረግ ጥረት በእርቀ ሰላም እንዲቋጭ ተገቢውን ርብርብ ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በሁለቱ አባቶች መካከል ተፈጥሯል የተባለው የቀኖና ቤተ ክርስቲያን ችግር በቤተ ክርስቲያኒቱ በራስዋ ሕጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሠረት በመዋቅራዊ አካላቷ ተቋማዊ አሠራር እንዲፈታ መደረግ አለበት፡፡

 

ሁለተኛው የቅድመ ምርጫ መደላድል፤ ሕጎችን፣ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማውጣት ወይም ማሻሻል የሚያስፈልግ ከሆነ ተገቢነታቸው በሊቃውንቱ ተሳትፎ እየተጠና ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው በቅዱስ ሲኖዶስ እየተወሰነ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ሦስተኛው መደላድል ደግሞ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ድርጅታዊ አወቃቀር ለማሻሻል የቀረቡና የሚቀርቡ ጥናቶችን በማዳበር የለውጥ ሂደቱን ለመምራት የሚችልና መንፈሳዊነት ሞያዊነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ፍትሐዊነት የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የአሠራር መርሕ መሆኑን በተጨባጭ ሊያረጋግጥ የሚችል የቴክኒክ ኮሚቴ በይፋ ማቋቋም ነው፡፡

 

የእነዚህ ሦስት መደላድሎች መቅደም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ነጻነት ከማጎናጸፍና የተለያዩ ሕገ ወጥ ቡድኖችን በዘለቄታዊነት ከአስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲታቀቡ ከማድረጋቸውም በላይ የተከፈለችውን አሐቲ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ወደ አንድነት ይመራል የሚል ጽኑ እምነት አለን፡፡

 

ስለሆነም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምእመናን የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳይ ያገባናል የምትሉ ምሁራን፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የመንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ደቀ መዛሙርትና ልዩ ልዩ ማኅበራት ለቤተ ክርስቲያኒቱ እግዚአብሔር ጥሩ መሪ እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጀውን የሁለት ሱባኤ ጸሎተ ምኅላ ከመፈጸም ጎን ለጎን ለመደላድሎቹ ስኬት ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻርም የግል ጥቅማቸውን የሚያሳድዱ አንዳንድ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በንቃት መከታተል ያስፈልጋል፡፡

 

ከዚሁ ጋር ለእነዚህ ሕገ ወጥ አካሄዶች ሽፋን የሚሆኑና በመሠረቱም ተገቢም ትክክለኛም ያልሆኑ መግለጫዎች፣ ቃለ ምልልሶችና ጽሑፎች እንዲታረሙና በቀጣይም እንዲቆጠቡ መደረግ ይኖርበታል እንላለን፡፡

 

በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽና የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ሁሉ የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ለምርጫው ሳይቸኩል ለቅድመ ምርጫው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ጽኑ እምነታችን ነው፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር


ስምዐ ጽድቅ 19ኛ ዓመት ቁጥር 24 2005 ዓ.ም.


የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ

መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ሪፖርታዥ

TAKLL2004 534የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ የመምሪያ ሓላፊዎች፤ ቀሳውስትና ካህናት፤ የፌደራል ጉዳዮች የሃይማኖት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም.በድምቀት ተጀመረ፡፡

ነሐሴ 29 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዋዜማው ነሐሴ 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ ስድስት ስዓት ጀምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የማኅበሩ አባላት ማኅበሩ እያስገነባው በሚገኘው ሕንጻ ውስጥ በመገኘት የሕንጻው ግንባታና በማኅበሩ የአንዳንድ አገልግሎት ክፍሎችን እንቅስቃሴ በመጎብኘት ማብራሪያ እየተሰጣቸው ቆይተዋል፡፡ ከምሽቱ 12፤00 ስዓት ጀምሮ የጠቅላላ ጉባኤው አስተባባሪ ኮሚቴ ባዘጋጀው ትራንስፖርት ከማኅበሩ ዋናው ማእከል አቧሬ ወደሚገኘው አቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በመጓዝ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት፤ የመርሐ ግብር ትውውቅ፤ ሕጽበተ እግርና የእራት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡

ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም.

ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ጠዋት የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዐቃቤ መንበረTAKLL2004 533 ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመመራት በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን በተጋበዙ ቀሳውስትና ካህናት ጸሎተ ወንጌል የተካሄደ ሲሆን በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቷል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የሁለት ዓመት የአገልግሎት ክንውን ሪፖርት በማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩም አማካይነት የቀረበ ሲሆን ሪፖርቱም በማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የአገልግሎት ክፍሎች እየተከናወኑ የሚገኙትን ተግባራት የዳሰሰ ነበር፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በሚዲያ አገልግሎት፤ በግቢ ጉባኤያት፤ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት፤ በቅዱሳት መካናትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ የተሠሩ ከፍተኛና አነስተኛ ፕሮጀክቶች፤ ስለቤተ ክርስቲያናችን የተደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች፤ የልማት ተቋማት አስተዳደር፤ የቤተክርስቲያንና የምእመናን ማኅበራዊ አገልግሎት፤ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን ጥቃትና የተወሰዱ እርምጃዎች፤ ወዘተ በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት በቀጣይነት የቀረበው የ2003 ዓ.ም. የማኅበሩ የሒሳብ ሪፖርት ሲሆን በውስጥ ኦዲተርና በውጪ የሂሳብ ኦዲተሮች ሀብተ ወልድ መንክርና ጓደኞቹ በቻርተር የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች በተሰኘና እውቅና ባለው ድርጅት አማካይነት ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ በዚህም ሂሳቡ ትክክለኛ እና የማኅበሩን ገጽታ የሚያሳይ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በቀረበው የማኅበሩ የሁለት ዓመታት አገልግሎት፤ እንዲሁም አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ተጋብዘዋል፡፡ በተጨማሪም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ከበጎ አድራጊ ምእመናን፤ ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር፤ ከፀረ ተሐድሶ የሰባኪያን ጥምረት የተወከሉ እንግዶች በማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

TAKLL2004 350አስተያየታቸውን ከሰጡ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “በገሊላ አውራጃ ጌታ አሥራ ሁለት ሐዋርያትን እንደመረጠ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም በምሳሌነት ይህች ቤተ ክርስቲያን የተማረ የሰው ኀይል ያስፈልጋታል በማለት 12 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ይዘው ነው በዝዋይ ሥራ የጀመሩት፡፡ ማኅበሩ ማኅበራችን ነው” በማለት የማኅበረ ቅዱሳንን አመሠራረት አስታውሰዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት አስተያት “ማኅበረ ቅዱሳን ብዙ ምሁራንና አዋቂዎች የተሰባሰቡበት ነው፡፡TAKLL2004 307 ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ ተጠሪ ነው” በማለት ነበር የገለጹት፡፡

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ማኅበረ ቅዱሳን በ20 ዓመት ውስጥ ያከናወነው አገልግሎት እኛ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎች ብቻ ሳንሆን ተቃራኒዎችም የሚመሰክሩት ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡

ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም አስተዳዳሪና የካሊፎርኒያ  አካባቢ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በሰጡት አስተያየት ”ከማኅበሩ ጋር TAKLL2004 347በግጭትም፤ በፍቅርም ተገናኝተናል፡፡ ማኅበሩን ከማወቄ በፊት የተቀበልኩት በበጎ መንፈስ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በሚያስደንቅ ሁኔታ እኔን የሚያሳምኑ ነገሮች የተፈጠሩት ውስጣችን ገብተህ አገልግሎታችንን ተመልክተህ ፍረድ የሚል ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ አላቅማማሁም ገባሁ፡፡ የማኅበሩን ማንነት ውስጡን ሕይወቱን ለማየት በምሞክርበት ጊዜ በትክክል የቤተ ክርስቲያኒቱ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ለማወቅ እድል አገኘሁ” በማለት ከማኅበሩ ጋር ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል፡፡

የጠዋቱ መርሐ ግብር የማኅበሩ የመዝሙር ክፍል አባላት በኅብረት ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና በአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተጠናቋል፡፡

ከስዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር የማኅበሩ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ሓላፊ ዲ/ን ንጋቱ ባልቻ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱም የማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ አፈጻጸም፤ የማኅበሩ ሥራ አመራር አፈጻጸም፤ የጠቅላላ ጉባኤያት ውሳኔ በተመለከተ ያልተተገበሩ፤ የሂሳብ ሪፖርት ላይ ታይተዋል ያሏቸውን ክፍተቶች አቅርበዋል፡፡በተጨማሪም የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ ወይም አቅጣጫ የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው ጠቅላላ ጉባኤው ቀጣዩን ስልታዊ እቅድ እና የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ሲከለስ እንዲካተቱ ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡ በኦዲትና ኢንስፔክሽን በቀረበው ሪፖርት ላይና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም ከአባላት በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማኅበሩን ወደፊት ሊጠቅሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

TAKLL2004 436በመጨረሻም የሚቀጥሉትን አራት ዓመታት ማኅበሩን የሚመሩ የሥራ አመራር አባላትን የሚያስመርጥ 5 አባላትን ያቀፈ አስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ 7 አባላት አስተያየት ከተሰጠባቸው በኋላ በእጩነት እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ በብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምና አቡነ ዘበሰማያትን በማድረስ አምስቱን አስመራጭ ኮሚቴ አባላትን በእጣ እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት የዕለቱ መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ዮናስ ቡራኬተጠናቋል፡፡

ጳጉሜን 1 ቀን 2004 ዓ.ም.

ጳጉሜን 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጠዋት በተካሄደው የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ “በማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ጉዞ የአባላት ተሳትፎና የወደፊት ሁኔታ” በተመለከተ ጥናት የቀረበ ሲሆን በአባላት ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ስብሰባም “ስልታዊ ለውጥ ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት ከማኅበረ ቅዱሳን ተልእኮና አቅም አንጻር” በሚል በዲ/ን ያረጋል አበጋዝና ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ በአባላት ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመጨረሻም የጽ/ቤት ግንባታ ሪፓርት ቀርቦ የመርሐ ግብሩ ፍጸሜ ሆኗል፡፡

ምሽት ላይ ጠቅላላ ጉባኤው በዋነኛነት ሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተወያየ ሲሆን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል እያከናወነ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት ገለጻ ተደርጓል፡፡ ክፍሉም በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ማእከላት የማበረታቻ ሽልማት ከ19.500.00 ብር በላይ አበርክቷል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፤

  • የደብረ ታቦር ማእከል ብር 5000.00
  • የሆሳእና ማእከል ብር 3000.00
  • የመቱ ማእከል ብር 2000.00
  • የደብረ ማርቆስ ማእከል ብር 3000.00
  • የሽሬ ማእከል ብር 2500.00
  • የአሰበ ተፈሪ ማእከል ብር 2000.00
  • የአርባ ምንጭ ማእከል ብር 2000.00 ተበርክቶላቸዋል፡፡

ይህ ስጦታ ሌሎችንም ማእከላት የሚያበረታታ በመሆኑ አገልግሎታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ክፍሉ አሳስቧል፡፡

በቀጣይነት በጠቅላላ ጉባኤው የተሰየመውና ማኅበሩን ለአራት ዓመታት ሊመሩ የሚችሉ የሥራ አመራር አባላትን እንዲያቀርብ የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ ማኅበሩን ሊመሩ ይችላሉ ያላቸውን አባላት ከጠቅላላ ጉባኤው አባላት የተጠቆሙትን ስም ዝርዝር በማሰባሰብ ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቦ በአባላቱ ሰፊ ውይይትና ግምገማ በማድረግ ከ39 እጩዎች መካከል 20 እጩዎችን ለጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ምርጫ እንዲቀርቡ አጽድቋል፡፡ ከ20ዎቹ አጩዎች መካከል የማኅበረ ቅዱሳን የጠቅላላ ጉባኤ የምርጫ ሥነ ሥርዓት ደንብ  አንቀጽ 8 ቁጥር 2 ንዑስ ፊደል ለ በሚያዘው መሠረት ከ20ዎቹ እጩዎች ጸሎት ተደርጎ በእጣ በመለየት 17ቱ እንደሚመረጡ በመግለጽ መርሐ ግብሩ ተጠናቀቀ፡፡

ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም.

ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ጠዋት የማኅበረ ቅዱሳን የአራት ዓመት ስልታዊ እቅድ ረቂቅ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ ኮሚቴው በዋነኛነት የማኅበሩ ርዕይ፣ ተልእኮና የማኅበሩ እሴቶች ፤የማኅበሩ ጥንካሬና ድክመቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶች እንዲሁም የማኅበሩ የውስጥ ጉዳዮችና ስትራቴጂያዊ ግቦችን በማካተት አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም የማኅበሩ ቀጣይ አራት ዓመታት ወሳኝ ጉዳዮችና ግቦች ያሏቸውን የማኅበሩ ተቋማዊ አቅም ማሳደግ፣ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያድግ ማድረግ፣ የግቢ ጉባኤያት ተደራሽነትና ብቃት ማሳደግ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዝግጁ ማድረግ፣ የአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት ድጋፍ ቀጣይ የቤተ ክርስቲያን ችግር በሚፈታ መልኩ ማድረግ፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ በሚሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያሉ ነጥቦች ቀርበዋል፡፡ በእያንዳንዳቸው ዋና ዋና ጉዳዮችም የአፈጻጸም ስልቶችን አስቀምጧል፡፡

ኮሚቴው የአራት ዓመት ስልታዊ እቅዱን ካቀረበ በኋላ ለአባላት በስልታዊ እቅድ ረቂቅ ላይ መካተት ነበረባቸው ያሏቸውን እንዲያቀርቡ በተጠየቀው መሠረት ማየትና መስማት የተሳናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስልታዊ ረቂቅ አቅዱ ውስጥ እንዲካተት ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በመቀጠልም አባላት በቡድን በመከፋፈል ውይይት አድርገዋል፡፡

ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብርም የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ ኮሚቴው ባቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ መሠረት በመተዳደሪያ ደንቡ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ያላቸውን በማሻሻል፣ መውጣት ያለባቸውን በማስወጣትና አዲስ መግባት አለባቸው ብሎ ያመነባቸውን በማካተት ያቀረበ ሲሆን መተዳደሪያ ደንቡን በማስመልክት የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ያላቸውን አስተያየትና ማሻሻያ    በጽሑፍ ለኮሚቴው እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

በመጨረሻም ማኅበሩን ለቀጣይ አራት ዓመታት  የሚመሩ የሥራ አመራር ጉባኤ ምርጫ ማካሔድ ሲሆን አስመራጭ ኮሚቴው መድረኩን ተረክቧል፡፡ በአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ቀሲስ እሸቱ ታደሰ አማካይነት ኮሚቴው በተሰጠው ኀላፊነት መሠረት እጩዎችን ለማቅረብ የተጓዘበትን ሒደት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በቀረበው ማብራሪያም መሠረት  ከጠቅላላ ጉባኤው ተጨማሪ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ ከውይይቱ በኋላም ኮሚቴው   የ20 እጩዎችን ስም ዝርዝር አቅርቧል፡፡

ከምርጫው ቀደም ብሎም በእለቱ በጉባኤው ላይ ከብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት መካካል ብፁዕ አቡነ ዲሜጥሮስ የተባበሩት አረብ ኤምሬት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ እንጦንስ የሰሜን ምሥራቅ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፤ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ የደቡብና መካካለኛው አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተገኝተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በእጩነት ከቀረቡት 20 እጩዎች መካከል በብፁዐን አበው ሊቃነ ጳጳሳት  ፀሎት ከተደረገ በኋላ በእጣ 17ቱ ተመርጠዋል፡፡ 3ቱ ደግሞ በተጠባባቂነት ተሰይመዋል፡፡

በዚህም መሠረት ፡

TAKLL2004 528

  • ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ ሰብሳቢ
  • ወ/ሪት ዳግማዊት ኃይሌ ምክትል ሰብሳቢ
  • ዲ/ን ሙሉዓለም ካሳ ጸሓፊ ሆነው ሲመረጡ በአባልነት ደግሞ፤
  • አቶ ውብሸት ኦቶሮ
  • አቶ ፋንታሁን ዋቄ
  • አቶ አዱኛ ማእምር
  • አቶ ካሳሁን ኃ/ማርያም
  • አቶ ባያብል ሙላቴ
  • አቶ ዳንኤል ገ/መድኅን
  • ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ
  • ዶ/ር ዳኝነት ይመኑ
  • አቶ አንተነህ ሰብስቤ
  • ዲ/ን ዋሲሁን በላይ
  • ዶ/ር ሳሙኤል ኃ/ማርያም
  • ወ/ሪት ገነት ከበደ
  • አቶ ታደሰ አሰፋ
  • አቶ ይላቅ አድማሱ

ለአራት ዓመታት ማኅበሩን ለማገልገል በሥራ አመራርነት ተመርጠዋል፡፡

ተጠባበቂ ሆነው የተመረጡት 3ቱ እጩዎች ደግሞ፤

  • ወ/ሪት ሂሩት በቀለ
  • ዲ/ን ዘመንፈስ ገ/እግዚእ
  • አቶ ዳንኤል ተስፋ ሆነዋል፡፡

የኤዲቶሪያል ቦርድ፡፡

  • ቀሲስ ዶ/ር አሸናፊ በየነ ሰብሳቢ
  • ዲ/ን አባይነህ ካሴ ም/ሰብሳቢ

ኦዲትና ኢንስፔክሽን፡፡

  • አቶ የሺዋስ ማሞ ሰብሳቢ
  • አቶ የትናየት ም/ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ

አዲሱ የሥራ አመራር ኮሚቴም የማኅበሩን የሥራ አስፈጻሚ አባላትን በመሰየም ለጠቅላላ ጉባኤ አቅርበው አጸድቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት

  • ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ዋና ጸሓፊ
  • ዲ/ን አንዱ አምላክ ይበልጣል ም/ዋና ጸሓፊና የሀገር ውስጥ ማእከላት ማስተባበሪያ ክፍል ሓላፊ
  • አቶ ግርማ ተሾመ ም/ዋና ጸሓፊ
  • ቀሲስ ዶ/ር ደረጀ ሺፈራው ትምህርትና ክፍል
  • ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ የኅትመትና አሌክትሮኒክስ ሚዲያ ክፍል ኃላፊ
  • አቶ ግዛቸው ሲሳይ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ቦርድ ሰብሳቢ
  • አቶ መስፍን ጥላሁን የሙያ አገልግሎት ክፍል ኃላፊ
  • ዲ/ን ዘመንፈስ ገ/እግዚእ የልማት ተቋማት አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ
  • አቶ ዘላለም አያሌው የሰው ኃይል አስተዳደር ኃላፊ
  • ሲ/ር ጽዮን ደሳለኝ የውጭ ማእከላት ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ
  • አቶ ከፍያለው መርጊያ እቅድ ዝግጅት ክፍል ኃላፊ
  • ዲ/ን ስንታሁ ደምሴ የፋናንስ ክፍል ኃላፊ
  • አቶ አክሊሉ ለገሰ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ
  • ዲ/ን ዮሐንስ አድገህ የጥናትና ምርምር ማእክል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሰይመዋል፡፡

አዲሱ ሥራ አመራር ኮሚቴ ወደ መድረክ እንዲወጣ በማድረግ ከጠቅላላ ጉባኤው ጋር የተዋወቁ ሲሆን ከቀድሞው የስራ አመራር ኮሚቴ ጋር በሕብረት ፎቶ ግራፍ በመነሳት መልካም የአገልግሎት ጊዜ እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡ መርሐ ግብሩም በብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ጸሎትና ቡራኬ ተጠናቋል፡፡

ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም.  ሌሊት በተካሔደው  የጠቅላላ ጉባኤው ቀጣይ ውይይት በቀኑ መርሐ ግብር የአራት ዓመት ስልታዊ እቅድ ረቂቅ ላይ የተካሔደውን የቡድን ውይይት ውጤት በየቡድኖቹ ሰብሳቢዎችና ጸሐፊዎች አማካይነት እንዲቀርቡ በማድረግ በጠቅላላ ጉባኤው ውይይት ተካሂዶበት ጸድቋል፡፡ በቀጣይነትም የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ዋና የአገልግሎት ክፍሎች ስለክፍሎቻቸው እንቅስቃሴ ለጠቅላላ ጉባኤው ግንዛቤ የማስጨበጥና አሁን ያሉበትን ደረጃ አቅርበዋል፡፡

የ10ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ አቢይ ኮሚቴ የተሠጣቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ያደረጉት ጥረት፤ ያጋጠሟቸው ችግሮችና ችግሮቹን ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ያቀረቡ ሲሆን ዝግጅቱን ለማሳካት የገንዘብ፤ የቁሳቁስና የሃሳብ ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

በመጨረሻም በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ጣልቃ የማይገባና የማኅበሩ የሥራ አመራር፤ የሥራ አስፈጻሚ፤ የየማእከላት ሰብሳቢዎች፤ የኤዲቶርያል ቦርድ ጽ/ቤት፤ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት፤  መምህራን፤ የማኅበሩ ጋዜጠኞች የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል እንዳይሆኑ የሚያግደውን መመሪያ በማብራራት ውይይት ተደርጓል፡፡ በአሉባልታ ላይ የተመሰረተውን ውዥንብር ለማጥራት ይመለከታቸዋል የተባሉ የማኅበሩ አባላት ሃሳባቸውንና አቋማቸውን እንዲገልጹ በማድረግ የተፈጠረውን ውዥንብር ለማጥራት ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ያጸደቀውን ከፖለቲካና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተያያዘ ያለውን አቋም ቀድሞ እንደነበረው እንዲቀጥል አጽንቷል፡፡ በመጨረሻም መርሐ ግብሩ እንደዛሬው ለከርሞው ያድርሰን በሚል ዝማሬ ታጅቦ 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በድምቀት እንደተጀመረ በድምቀት ከሌሊቱ 9፡00 ስዓት ተጠናቋል፡፡