gubaye 2

የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተጀመረ

ጳጉሜ 1 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

gubaye 2የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ የመምሪያ ሓላፊዎች፤ ቀሳውስትና ካህናት፤ በሬዴራል ጉዳዮች የሃይማኖት ተወካዮች ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ተጀምሯል፡፡

 

በዋዜማው ነሐሴ 29 ቀን 2004 ዓ.ም. ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመጡ የማኅበሩ አባላት ከምሽቱ 12፤00 ስዓት ጀምሮ የጠቅላላ ጉባኤው አስተባባሪ ኮሚቴ ባዘጋጀው ትራንስፖርት ከማኅበሩ ዋናው ማእከል አቧሬ ወደሚገኘው አቡነ ጎርጎርዮስ የትምህርትና ሥልጠና ማእከል በመጓዝ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት፤ የመርሐ ግብር ትውውቅ፤  ሕጽበተ እግርና የእራት መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡

 

gubaye 6ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ጠዋት የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ በመመራት በመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በተጋበዙ ቀሳውስትና ካህናት ጸሎተ ወንጌል የተካሄደ ሲሆን በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ተከፍቷል፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳን የሁለት ዓመት የአገልግሎት ክንውን ሪፖርት በማኅበሩ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶ/ር ሙሉጌታ ስዩምgubaye 7 አማካይነት የቀረበ ሲሆን ሪፖርቱም በሚዲያ አገልግሎት በግቢ ጉባኤያት፤ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት፤ በቅዱሳት መካናትና የአብነት ትምህርት ቤቶች ላይ የተሠሩ ከፍተኛና አነስተኛ ፕሮጀክቶች፤ ስለ ቤተ ክርስቲያናችን የተደረጉ የጥናትና ምርምር ሥራዎች፤ የቤተ ክርስቲያንና የምእመናን ማኅበራዊ አገልግሎት፤ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚያደርሱትን ጥቃትና የተወሰዱ እርምጃዎች፤ ወዘተ የተከናወኑ ተግባራት በዝርዝር ቀርቧል፡፡

 

በተያዘው መርሐ ግብር የኦዲት ሪፖርት ቀርበዋል፡፡ የማኅበሩ ሒሳብ የ2003 ሪፓርት የውጪ ኦዲተር ሀብተ ወልድ መንክርና ጓደኞቹ በቻርተር የተመሰከረላቸው የሂሳብ አዋቂዎች የኦዲት ሪፖርቶች ቀርበዋል፡፡ በዚህም ሂሳቡ ትክክለኛ እና የማኅበሩን ገጽታ የሚያሳይ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

 

በቀረበው የማኅበሩ የሁለት ዓመታት ክንውን እንዲሁም አጠቃላይ አስተያየት እንዲሰጡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል መልካም ፈቃድ ከብፁዐን ሊቃ ነጳጳሳት ተጋብዘዋል፡፡ በተጨማሪም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም ከበጎ አድራጊ ምእመናን፤ ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር፤ ከፀረ ተሐድሶ ጥምረት የተወከሉ እንግዶች በማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ዙሪያ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

 

አስተያየታቸውን ከሰጡ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሣልሳዊ የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “በገሊላ አውራጃ ጌታ አሥራሁለት ሐዋርያትን እንደ መረጠ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስም በምሳሌነት ይህች ቤተ ክርስቲያን የተማረ የሰው ኀይል ያስፈልጋታል በማለት 12 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ይዘው ነው በዝዋይ ሥራ የጀመሩት፡፡ ማኅበሩ ማኅበራችን ነው” በማለት የማኅበረ ቅዱሳንን አመሠራረት አስታውሰዋል፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት አስተያት “ማኅበረ ቅዱሳን ብዙ ምሁራንና አዋቂዎች የተሰባሰቡበት ነው፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የቅዱስ ሲኖዶስ ቋሚ ተጠሪ ነው” በማለት ነበር የገለጹት፡፡

 

ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ “ማኅበረ ቅዱሳን በ20 ዓመት ውስጥ ያከናወነው አገልግሎት እኛ የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊዎች ብቻ ሳንሆን ተቃራኒዎችም የሚመሰክሩት ነው” በማለት ተናግረዋል፡፡

 

ሊቀ ካህናት ኃ/ሥላሴ ዓለማየሁ የዴንቨር ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም አስተዳዳሪና የካሊፎርኒያ  አካባቢ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ በሰጡትgubaye 11 አስተያየት ”ከማኅበሩ ጋር በግጭትም፤ በፍቅርም ተገናኝተናል፡፡ ማኅበሩን ከማወቄ በፊት የተቀበልኩት በበጎ መንፈስ አልነበረም፡፡ ነገር ግን በሚያስደንቅ ሁኔታ እኔን የሚያሳምኑ ነገሮች የተፈጠሩት ውስጣችን ገብተህ አገልግሎታችንን ተመልክተህ ፍረድ የሚል ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ አላቅማማሁም ገባሁ፡፡ የማኅበሩን ማንነት ውስጡን ሕይወቱን ለማየት በምሞክርበት ጊዜ በትክክል የቤተ ክርስቲያኒቱ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ለማወቅ እድል አገኘሁ” በማለት ከማኅበሩ ጋር ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል፡፡

 

የጠዋቱ መርሐ ግብር በዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክና በአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ ተጠናቋል፡፡

 

ከስዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር የማኅበሩ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ሓላፊ ዲ/ን ንጋቱ ባልቻ ሪፖርት የቀረበ ሲሆን በሪፖርቱም የማኅበሩ ስልታዊ ዕቅድ አፈጻጸም፤ የማኅበሩ ሥራ አመራር አፈጻጸም፤ የጠቅላላ ጉባኤያት ውሳኔ በተመለከተ ያልተተገበሩ፤ የሂሳብ ሪፖርት ላይ ታይተዋል ያሏቸውን ክፍተቶች አቅርበዋል፡፡በተጨማሪም የጠቅላላ ጉበኤ ውሳኔ ወይም አቅጣጫ የሚሹ ጉዳዮች ተለይተው ጠቅላላ ጉባኤው ቀጣዩን ስልታዊ እቅድ እና የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ ሲከለስ እንዲካተቱ ትኩረት እንዲሰጣቸው አሳስበዋል፡፡ በኦዲትና ኢንስፔክሽን በቀረበው ሪፖርት ላይና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እንዲሁም ከአባላት በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ማኅበሩን ወደ ፊት ሊጠቅሙ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

 

በመጨረሻም የሚቀጥሉትን አራት ዓመታት ማኅበሩን የሚመሩ የሥራ አመራር አባላትን የሚያስመርጥ 5 አባላትን ያቀፈ አስመራጭ ኮሚቴ ለመምረጥ አስተያየት ከተሰጠባቸው በኋላ በብፁዕ አቡነ ዮናስ የአፋር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት ጸሎተ እግዝእትነ ማርያምና አቡነ ዘበሰማያትን በማድረስ አምስቱን አስመራጭ ኮሚቴ አባላትን በእጣ እንዲለዩ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት የዕለቱ መርሐ ግብር በብፁዕ አቡነ ዮናስ ቡራኬ ተጠናቋል፡፡

 

የጠቅላላ ጉባኤው እስከ አርብ ጳጉሜ 2 ቀን የሚቀጥል ሲሆን የተለያዩ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበትና ለቀጣዩ አራት ዓመት ማኅበሩን የሚመለከት ስልታዊ ዕቅድ ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡