የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠናቀቀ

ጳጉሜን 5 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

ነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. የተጀመረው የማኅበረ ቅዱሳን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በታቀደለትና በወጣለት መርሐ ግብር መሰረት በማካሔድ ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ከለሊቱ 9፡00 ስዓት በድምቀት ተጠናቀቀ፡፡

 

ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም.  ለሊት በተካሔደው  የጠቅላላ ጉባኤው ቀጣይ ውይይት በቀኑ መርሐ ግብር የአራት ዓመት ስልታዊ እቅድ ረቂቅ ላይ የተካሔደውን የቡድን ውይይት ውጤት በየቡድኖቹ ሰብሳቢዎችና ጸሐፊዎች አማካይነት እንዲቀርቡ በማድረግ በጠቅላላ ጉባኤው ውይይት ተካሒዶበት ጸድቋል፡፡ በቀጣይነትም የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ዋና የአገልግሎት ክፍሎች ስለክፍሎቻቸው እንቅስቃሴ ለጠቅላላ ጉባኤው ግንዛቤ የማስጨበጥና አሁን ያሉበትን ደረጃ አቅርበዋል፡፡

 

የ10ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ የተሠጣቸውን ኀላፊነት ለመወጣት ያደረጉት ጥረት፤ ያጋጠሟቸው ችግሮችና ችግሮቹን ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ያቀረቡ ሲሆን ዝግጅቱን ለማሳካት የገንዘብ ፤ የቁሳቁስና የሃሳብ ድጋፍ ላደረጉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከፍተኛ ምስጋና በማቅረብ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል፡፡

 

በመጨረሻም በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ማኅበሩ በማንኛውም የፖለቲካ  እንቅስቃሴ ጣልቃ የማይገባና የማኅበሩ የሥራ አመራር፤ የሥራ አስፈጻሚ፤ የየማእከላት ሰብሳቢዎች፤ የኤዲቶርያል ቦርድ ጽ/ቤት፤ የኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ጽ/ቤት፤  መምህራን የማኅበሩ ጋዜጠኖችና የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል እንዳይሆኑ የሚያግደውን መመሪያ በማብራራት ውይይት ተደርጓል፡፡ በአሉባልታ ላይ የተመሰረተውን ውዥንብር ለማጥራት ይመለከታቸዋል የተባሉ የማኅበሩ አባላት ሃሳባቸውንና አቋማቸውን እንዲገልጹ በማድረግ የተፈጠረውን ውዥንብር ለማጥራት ተችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ያጸደቀውን ከፖለቲካና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተያያዘ ያለውን አቋም ቀድሞ እንደነበረው እንዲቀጥል አጽንቷል፡፡ በመጨረሻም መርሐ ግብሩ እንደዛሬው ለከርሞው ያድርሰን በሚል ዝማሬ ታጅቦ 10ኛው ጠቅላላ ጉባኤ በድምቀት እንደ ተጀመረ በድምቀት ከለሊቱ 9፡00 ስዓት ተጠናቋል፡፡