PIC_0322

የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የንባብና የቅዳሴ ትምህርት ቤት ተመረቀ

ነሐሴ 28 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

PIC_0322የከምባታ፣ ሀዲያ፣ ስልጤና ጉራጌ አህጉረ ስብከት በሆሳዕና ከተማ በደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው የንባብና የቅዳሴ የአብነት ትምህርት ቤት የጥገና እና የግንባታ እንዲሁም የውስጥ ቁሳቁስ የማሟላት ሥራ ተጠናቆ እሑድ ነሐሴ 20 ቀን 2004 ዓ.ም ተመረቀ፡፡

 

የአብነት ትምህርት ቤቱን በማጠናከር በሀገረ ስብከቱ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ካህናትና ዲያቆናት ማፍራት የሚቻልበት ሁኔታ ለማመቻቸት በማኅበረ ቅዱሳን ሆሳዕና ማእከል ፕሮጀክቱ ተቀርጾ በማኅበረ ቅዱሳን ከአሜሪካ ማእከል በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ፣ በዋናው ማእከል በቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል አስተባባሪነት ተሠርቶ ለመመረቅ በቅቷል፡፡

 

“በተደረገው ጥገናና ግንባታ የሰባት ክፍሎች የውኃ ልክ፤ የወለል ሊሾ፤ የግድግዳ ግርፍ ሥራ፤ የኮርኒስና ቀለም ቅብ የተሠራ ሲሆን ከእነዚህPIC_0314 ክፍሎች ውስጥ  አምስቱ ለተማሪዎች ማደሪያ፣ አንድ ክፍል ለመምህራን፣ አንድ ክፍል ለተማሪዎች መማሪያ፣ አንድ መመገቢያ አዳራሽ ታድሰዋል፡፡ አንድ ክፍል ሙሉ ለሙሉ በመፍረሱ በአዲስ መልክ ተገንብቷል፡፡ በተጨማሪም አንድ መቀጸያ ክፍል፣ አራት መጸዳጃ ቤቶች፣ ሁለት ገላ መታጠቢያ ቤቶች፣ አንድ ምግብ ማብሰያ ክፍል አዲስ ግንባታ መከናወኑንና ሙሉ የውስጥ መገልገያ ቁሳቁስ አልጋ፣ ፍራሽ፣ የመማሪያ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ የምግብ ማብሰያና መመገቢያ ቁሳቁስ ተሟልቶለታል፡፡” በማለት ዲ/ን አእምሮ ይሔይስ የቅዱሳት መካናት የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር በምረቃው ላይ ባሰሙት ሪፖርት ገልጸዋል፡፡

 

በማኅበሩ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው መርሐ ግብር ለተማሪዎችና ለመምህራን በያሉበት ሀገረ ስብከት የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመጸሐፍት ድጋፍ በማቅረብ ጉባኤ ቤት፣ የተማሪዎች ማደሪያ ቤቶችን በመሥራት፣ በመጠገን፣ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን በማካተት ለዘመናት የሚገባ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ማድረግ ነው ያሉት ዲ/ን አእምሮ ይሔይስ “የሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን የአብነት ትምህርት ቤት 40 ተማሪዎችን በአዳሪነት በመቀበል ሙሉ የማደሪና የመመገቢያ አገልግሎት ለመስጠት እንዲችል ተደርጎ ተገንብቷል፡፡ ፕሮጀክቱም የአስተዳደርን ወጪ ጨምሮ በአጠቃላይ ብር 553,779.20 (አምስት መቶ ሃምሳ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሰባ ዘጠኝ ብር ከሃያ ሣንቲም) ፈጅቷል” ብለዋል፡፡ ሥራውንም በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመሥራት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስና ሥራ አስኪያጅ ላደረጉት ከፍተኛ ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

ከሀገረ ስብከቱ በተገኘው  መረጃ መሠረት በጉራጌ፤ ሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ውስጥ ካሉት 121 አብያተ ክርስቲያናት መካከል ከ60 የማያንሱት መንፈሳዊ አገልግሎት በአግባቡ ለመስጠት የማይችሉ ናቸው፡፡ የአብነት ትምህርት ቤቱ ጥገናና እድሳት በማግኘቱ በቀጣይ ካህናትንና ዲያቆናትን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችለው ሲሆን በሀገረ ስብከቱ የተዘጉ አብያተ ክርስቲናት ተከፍተው ምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚገኙበትንና ስብከተ ወንጌል የሚጠናከርበት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

 

በምረቃው መርሐ ግብር ላይ የሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፤ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደርና አገልጋዮች፤ የማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አመራር አባላትና አገልጋዮች፤ እንዲሁም ተማሪዎችና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

PIC_0039በተያያዘም ከማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ባገኘነው መረጃ መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከፍተኛ ችግር ላጋጠማቸው ገዳማትና አድባራት እንዲሁም የአብነት ትምህርት ቤቶች ድጋፍ እያደረገ ሲሆን ግንባታቸው የተጠናቀቁና በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ፕሮጀክቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ፡

 

  • የጎንደር የደብረ ኀይል ወደብረ ጥበባት በኣታ ለማርያም ደብር የአቋቋም ምስክር ጉባኤ ቤት በብር 5,981,321.30 (አምስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አንድ ሺህ ሦስት መቶ ሃያ አንድ ብር ከሠላሳ ሳንቲም) ባለ ሁለት ፎቅ የተማሪዎች መኖሪያ የመጀመሪያው ምዕራፍ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

  • የደብረ ባሕሪይ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እና አባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ባለ 3 ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ  በብር 2,300,057.00 (ሁለት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሺህ ሃምሳ ሰባት ብር) እየተሠራ ይገኛል፡፡

  • ሞጣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተማሪዎች መማሪያ፣ ማደሪያና ቤተ መጸሐፍት ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ በብር 1,344,144.15 (አንድ ሚሊዮን ሦስት መቶ አርባ አራት ሺህ አንድ መቶ አርባ አራት ብር ከአሥራ አምስት ሳንቲም) እየተከናወነ ይገኛል፡፡

  • የጎንደር ቅድሰት ቤተልሔም ጉባኤ ቤትና የቤተ መጸሐፍት ግንባታ በ787,318.26 (ሰባት መቶ ሰማንያ ሰባት ሺህ ሦስት መቶ አሥራ ስምንት ብር ከሃያ ስድስት ሳንቲም) በመሥራት ተጠናቋል፡፡

  • ደብረ ጽጌ ቅድስት ማርያም ገዳም የአብነት ትምህርት ቤት የሁለተኛው ምእራፍ የመጸዳጃ ቤት፣ ምግብ ማብሰያና መማሪያ ክፍሎች በመገንባት ላይ ሲሆኑ ብር 717,368.98 (ሰባት መቶ አሥራ ሰባት ሺህ ሦስት ስልሳ ስምንት ብር ከዘጠና ስምንት ሳንቲም) ተመድቦለታል፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ የተማሪዎች ማደሪያ፣ አልጋ፣ ጠጴዛና ወንበሮች አንዲሁም የተለያዩ መገልገያ ቁሳቁስ ተሟልቶለታል፡፡

  • የምድረ ከብድ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ሊትር ውኃ የሚይዝ በኮንክሪት የተገነባ ማጠራቀሚያ ታንከር በ329,606.19 (ሦስት መቶ ሃያ ዘጠኝ ሺህ ስድስት መቶ ስድስት ብር ከአሥራ ዘጠኝ ሳንቲም) ተገንብቶ ርክክቡ ተፈጽሟል፡፡ በተጨማሪም የአብነት ትምህርት ቤቱን ጣሪያ ቆርቆሮ እንዲለብስ ተደርጓል፡፡

  • የአምባ ማርያም የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት በብር 157,600.00 ( አንድ መቶ ሃምሳ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ ብር) ተሠርቶ ተጠናቋል፡፡

  • የበልበሊት ኢየሱስ ገዳም የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በብር 72,472.58 (ሰባ ሁለት ሺህ አራት መቶ ሰባ ሁለት ብር ከሃምሳ ስምንት ሳንቲም) ለመሥራት በጅምር ላይ ይገኛል፡፡

 

ማኅበሩ በቀጣይነት የሚያከናውናቸው ሥራዎች እንዳሉና በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ከቅዱሳት መካናት የልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡