1-2004

ማኅበረ ቅዱሳን የሥራ አመራር ጉባኤ ምርጫ አካሄደ

ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

ከነሐሴ 30 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን 10ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በመጠናቀቅ ላይ ነው፡፡

1-2004

ጳጉሜን 1 ቀን 2004 ዓ.ም. ጠዋት በተካሄደው የጠቅላላ ጉባኤው ስብሰባ “በማኅበረ ቅዱሳን የአገልግሎት ጉዞ የአባላት ተሳትፎና የወደፊት ሁኔታ” በተመለከተ ጥናት የቀረበ ሲሆን በአባላት ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ከሰዓት በኋላ በቀጠለው ስብሰባም “ስልታዊ ለውጥ ለሁለንተናዊ የቤተ ክርስቲያን እድገት ከማኅበረ ቅዱሳን ተልእኮና አቅም አንጻር” በሚል በዲ/ን ያረጋል አበጋዝና ዲ/ን ብርሃኑ አድማስ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ በአባላት ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመጨረሻም የጽ/ቤት ግንባታ ሪፓርት ቀርቦ የመርሐ ግብሩ ፍጸሜ ሆኗል፡፡

 

ምሽት ላይ ጠቅላላ ጉባኤው በዋነኛነት ሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተወያየ ሲሆን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል እያከናወነ ያለውን ዘርፈ ብዙ ተግባራት የተገለጸ ሲሆን ክፍሉም በገዳማትና አብነት ትምህርት ቤቶች ጋር በተያያዘ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ማእከላት የማበረታቻ ሽልማት ከ19500 ብር በላይ አበርክቷል፡፡

3-2004

በቀጣይነት በጠቅላላ ጉባኤው የተሰየመውና ማኅበሩን ለአራት ዓመታት ሊመሩ የሚችሉ የሥራ አመራር አባላትን እንዲያቀርብ የተሰየመው አስመራጭ ኮሚቴ ማኅበሩን ሊመሩ ይችላሉ ያላቸውን አባላት ለጠቅላላ ጉባኤው አቅርቦ በአባላቱ ሰፊ ውይይትና ግምገማ በማድረግ ከ39 እጩዎች መካከል 20 እጩዎችን ለጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ምርጫ እንዲቀርቡ አጽድቋል፡፡ ከ20ዎቹ አጩዎች መካከል የማኅበረ ቅዱሳን የጠቅላላ ጉባኤ የምርጫ ሥነ ሥርዓት ደንብ  አንቀጽ 8 ቁጥር 3 ንዑስ ፊደል ለ በሚያዘው መሠረት ከ20ዎቹ እጩዎች ጸሎት ተደርጎ በእጣ በመለየት 17ቱ የሚመረጡ ይሆናሉ፡፡

 

ጳጉሜን 2 ቀን 2004 ዓ.ም. ጠዋት በተያዘው መርሐ ግብር መሠረት “የማኅበረ ቅዱሳን የአራት ዓመት ስልታዊ እቅድ ረቂቅ ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ ኮሚቴው በዋነኛነት የማኅበሩ ርዕይ፣ ተልእኮና የማኅበሩ እሴቶች ፤የማኅበሩ ጥንካሬና ድክመቶች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶች እንዲሁም የማኅበሩ የውስጥ ጉዳዮችና ስትራቴጂያዊ ግቦችን በማካተት አቅርቧል፡፡

 

በተጨማሪም የማኅበሩ ቀጣይ አራት ዓመታት ወሳኝ ጉዳዮችና ግቦች ያሏቸውን የማኅበሩ ተቋማዊ አቅም ማሳደግ፣ የቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ አገልግሎት እንዲያድግ ማድረግ፣ የግቢ ጉባኤያት ተደራሽነትና ብቃት ማሳደግ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዝግጁ ማድረግ፣ የአብነት ት/ቤቶችና ገዳማት ድጋፍ ቀጣይ የቤተ ክርስቲያን ችግር በሚፈታ መልኩ ማድረግ፣ የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ዘላቂነቱን ማረጋገጥ በሚሉ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያሉ ነጥቦች ቀርበዋል፡፡ በእያንዳንዳቸው ዋና ዋና ጉዳዮችም የአፈጻጸም ስልቶችን አስቀምጧል፡፡

 

ኮሚቴው የአራት ዓመት ስልታዊ እቅዱን ካቀረበ በኋላ ለአባላት በስልታዊ እቅድ ረቂቅ ላይ መካተት ነበረባቸው ያሏቸውን እንዲያቀርቡ በተጠየቀው መሠረት ማየትና መስማት የተሳናቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስልታዊ ረቂቅ አቅዱ ውስጥ እንዲካተት ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በመቀጠልም አባላት በቡድን በመከፋፈል ውይይት አድርገዋል፡፡

 

ከሰዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብርም የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያው ለጠቅላላ ጉባኤው ቀርቧል፡፡ ኮሚቴው ባቀረበው የማሻሻያ ረቂቅ መሠረት በመተዳደሪያ ደንቡ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ያላቸውን በማሻሻል፣ መውጣት ያለባቸውን በማስወጣትና አዲስ መግባት አለባቸው ብሎ ያመነባቸውን በማካተት ያቀረበ ሲሆን የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ያላቸውን አስተያየትና ማሻሻያ    በጽሑፍ ለኮሚቴው እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

2-2004

በመጨረሻም ማኅበሩን ለቀጣይ አራት ዓመታት  የሚመሩ የሥራ አመራር ጉባኤ ምርጫ ተካሒዷል፡፡ በዚህም መሠረት በእጩነት ከቀረቡት 20 እጩዎች መካከል በብፁዐን አባቶች ፀሎት ከተደረገ በኋላ በእጣ 17ቱ ተመርጠዋል፡፡ 3ቱ ደግሞ በተጠባባቂነት ተሰይመዋል፡፡

በዚህም መሠረት ፡

ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ ሰብሳቢ

ወ/ሪት ዳግማዊት ኃይሌ ምክትል ሰብሳቢ

ዲ/ን ሙሉዓለም ካሳ ፀሐፊ ሆነው ተመርጠዋል፡፡

 

በተጨማሪም የኤዲቶሪያል ቦርድ፤ ኦዲትና ኢንስፔክሽን በኀላፊነት የሚመሩ አባላት የተመረጡ ሲሆን አዲሱ የሥራ አመራር ኮሚቴ የሥራ አስፈጻሚ አባላትን ለጠቅላላ ጉባኤ አቅርበው አጸድቀዋል፡፡

 

ጉባኤው ምሽቱን እንደሚቀጥልና ሌሎች ማኅበሩን የሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሳለፍ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡