የሐዋሳ ማእከል በአፍ መፍቻ ቋንቋ ያሠለጠናቸውን ሰባኪያነ ወንጌል አስመረቀ

ጳጉሜን 5 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዳዊት ደስታ


የማኅበረ ቅዱሳን ሐዋሳ ማእከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት የገጠር ስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ንዑስ ክፍል በአፍ መፍቻ ቋንቋ ለአንድ ወር ያሠለጠናቸውን ሠልጣኞች ነሐሴ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡

 

የሲዳማና ቦረና ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “በሕዝቡ ቋንቋ ባለማስተማራችን በማኅሌት ብቻ በመወሰናችን ቤተ ክርስቲያን የተሰወረች ሆና በዚህ በደቡብ ክፍለ ሀገር ትታያለች፡፡ ይህ ትልቅ ጉድለት ነው፡፡ ለቤተ ክርስቲያናችን የቆመ ማኅበር ማኅበረ ቅዱሳን በየትኛው በኩል ጉድለት እንዳለብን የተገነዘቡ ልጆቻችን ይህንን የሥልጠና መርሐ ግብር መጀመራቸው ያለብንን ጉድለት ይሞላል” በማለት በምረቃው ዕለት መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሥልጠናውን ዓላማ አስመልክቶ የሐዋሳ ማእከል የደቡብ ማእከላት ማስተባበሪያ ዋና ሓላፊ አቶ ዘሪሁን ከበደ እንደገለጹት ሥልጠናው በሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ሥር ለሚገኙ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት በአፍ መፍቻ ቋንቋ የሚሰብኩ ሰባኪያነ ወንጌልን በማሠልጠን በገጠር የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማጠናከር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

 

አያይዘውም ከዚህ ሥልጠና በኋላ ሠልጣኞች የአካባቢውን ቋንቋ በመጠቀም የስብከተ ወንጌል አገልግሎትን ለማጠናከር፣ የቤተ ክርስቲያን ዶግማ፣ ሥርዓትና ትውፊትን እንዲያስተምሩ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በመመሥረት በመምራት በማስተማርና በማጠናከር በአጠቃላይ የጠፉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን አስተምርው የመመለስ ሥራ መሥራት እንዲቻል ለማድረግ እንደሆነ ሓላፊው ገልጸዋል፡፡

 

ሠልጣኞቹ ከሲዳማ፣ ጌዲኦ፣ አማሮና ቡርጂ፣ ጉጂና ቦረና ሀገረ ስብከት የመጡ ሲሆን በስድስት ቋንቋ በተለያዩ ርዕሶች ዙሪያ የሰለጠኑና ቁጥራቸውም 26 እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህ ዓመት ሠልጥነው የተመረቁትን ጨምሮ ማእከሉ ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ ያሠለጠናቸው 201 ሠልጣኖች መድረሳቸውንም ለማወቅ ተችሏል፡፡