ግስ

ዲያቆን ዐቢይ ሙሉቀን

የግስ ምንነት

ግስ ከቃል ክፍሎች አንዱ ሲሆን በብዙ መንገድ ሊፈታ ይችላል። በዋናነት ግን ድርጊት አመልካች የሆነ በዐረፍተ ነገር ውስጥ የሐሳብ መደምደሚያ፣ ወይም የዐረፍተ ነገር ማሠሪያ ተብሎ ይተረጎማል። በርካታ ምሁራን በተለያየ መልኩ ስላብራሩት የምሁራኑን አገላለጽ እንደሚከተለው እንመልከት።

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተባለ መጽሐፋቸው እንዲህ ያስረዳሉ።

ግስ ፡- መግሰስ፣ አንዱን ቃል ማርባት፣ ማብዛት፣  የሩቁን  ለቅርብ፣  የወንዱን ለሴት፣ ያንዱን ለብዙ መስጠት፣  ማወራረስ፣  የቅኔ፣ የዚቅ፣ የወረብ፣ የለዘብ።

ግስ፡- ጓዝ፣ እክት፣ ግስንግስ ፣ ዕቃ፣ ግሴት የሚያዝና፣ የሚዳሰስ ኹሉ፣

ግስ፡- በቁሜሙ፣ የቋንቋ መጣፍ፣ የዘርና የነባር መድበል፣ መዝገበ ቃል፣ ንባቡ በፊደል ተራ የታከተ፣ የተከተተ። ምሥጢሩ ግን ተወራራሽ ቃል ማለት ነው። አንዱ አንቀጽ እስከ ሰማንያ ነባሩና ጥሬው እስከዐሥር መርባቱ በመወራረስ ነውና። (ኪዳነ ወልድ፣ ገጽ ፫፻፴፫-፫፻፴፬)

አለቃ ኪዳነ ወልድ በተለያየ አገላለጽ ቢገልጹትም በዋናነት ግን ግስ አንቀጽን ማርባት፣ መግሰስ፣ ጓዙን ማሳየት ወዘተ ማለት እንደሆነ እንረዳለን። በሌላ በኩል የአማርኛ ሰዋስውን በስፋት ያጠኑት ፕሮፌሰር ባየ ይማም ደግሞ የአማርኛ ሰዋስው በሚል መጽሐፋቸው እንደሚከተለው ያስረዳሉ።

ግስ፡- ማንኛውም በዐረፍተ ነገር መድረሻ ላይ ሊገባ የሚችልና እንደ /-ሁ/፣/-ህ/ ፣/-ሽ/ ወዘተ ያሉ መደብ አመልካች ምዕላዶችን ሊያስከትል የሚችል ቃል ሁሉ ግስ ተብሎ በዚህ ክፍል ውስጥ ሊመደብ ይችላል። (ባየ.ገጽ ፹፬) ይሉንና በሌላኛው ገጽ ደግሞ

ግሶች ለመደብ፣ ለጾታ ፣ለቍጥር፣ ለአንቀጽ፣ ለስልት፣ እንዲሁም ለጊዜ የተለያዩ ቅጣይ ምዕላዶችን፣ በማስቀደም ወይም በማስከተል ቅድመ መድረሻ ተናባቢያቸውን በማጥበቅ ወይም ባለማጥበቅ እንዲሁ ከተለያዩ ረዳት ግሶች ጋር በመጣመር ቅርጻቸውን ሊለዋውጡ ይችላሉ። (ባየ.ገጽ.፻፴፫) በማለት ያስረዳሉ።

ፕሮፌሰር ባየ ይማም ከመዋቅር አንጻር በአማርኛ ስለተመለከቱት እንጂ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ከግእዝ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ምክንያቱም በአማርኛ መዋቅር ግስ ወይም ማሰሪያ አንቀጽ ከዐረፍተ ነገር መጨረሻ ስለሚገባ ነው። በግእዝ ቋንቋ ግን በመጀመሪያም በመጨረሻም ሊገባ ይችላል። ሌላው መስፈርት ግን በመደብ፣ በጾታ በቁጥር ወዘተ መብዛቱና መደብ፣ ጾታ እና ቍጥር አመልካች ምዕላድ ማስከተሉ በሁለቱም ቋንቋ ተመሳሳይነት አለው። ምን አልባት አመልካች ምዕላዶች ይለያዩ ካልሆነ በቀር። ከላይ በኪዳነ ወልድ አገላለጽ የተመለከትነውም ማርባት፣ ማብዛት፣ መግሰስ ወዘተ የተባለው ይህን የሚያስረዳ ነው።

መምህር አስበ ድንግል ግእዝ ልሳነ ኢትዮጵያ በሚል መጽሐፋቸው ግስን እንደሚከተለው ገልጸውት እናገኛለን።

ግስ ድርጊትንና ሁኔታን የሚገልጽ የቋንቋ መዝገበ ቃል የምሥጢር መፍቻ ቁልፍ ነው። (አስበ ድንግል፣ገጽ፴፭)

ሌላው መምህር ዕንባቆም ገብረ ጻድቅ የግእዝ ቋንቋ የሰዋስው መጽሐፍ በሚል መጽሐፋቸው እንዲህ ገልጸውት እናገኛለን።

ግስ ማለት ጌሰ፤ ገሰገሰ፤ ተራመደ፤ ተስፋፋ፣ ከሚለው ግስ የተገኘ ዘመድ ዘር ሲሆን የአንድ ዐረፍተ ነገር (ኃይለ ቃል) ማሰሪያ አንቀጽ በመሆን ዐረፍተ ነገሩ ትርጉም እንዲኖረው የሚያደርግ ነው።

ግስ ማለት፡- ገሰሰ ዳሰሰ ከሚለው ግስ የወጣ ዘመድ ዘር ሲሆን የቃላት መራቢያ፣ ገስጋሽ፣ ተመላላሽና ተወራራሽ ቃል ነው። (ዕንባቆም፣፴፭)

ከመምህር ዕንባቆም አገላለጽም የምንረዳው ከላይ በተመለከትነው መሠረት ግስ የዐረፍተ ነገር ማሰሪያ አንቀጽ በመሆን የሚያገልግል፣ የሐሳብ መቋጫ የሚሆን፣ በብዙ መንገድ የሚረባ የቃላት ሁሉ መነሻ ማለት እንደሆነ ነው።

በሌላ መልኩ አንዳንድ መምህራን ግስን አንቀጽ በሚል ስያሜ ይጠሩታል።

አንቀጽ፡- የአድራጊ፣ የድርጊትና የሁኔታ፣ አንድና ብዙ ቍጥርን፣ ቅርብና ሩቅ መደብን፣ ተባዕታይና አንስታይ ጾታን፣ ሐላፊ፣ አሁንታና ትንቢት ጊዜያትን፣ ወዘተ የሚያስረዳ ቃል አንቀጽ ይባላል። አንቀጽ ማለት መግቢያ፣ መውጫ፣ መመላለሻ በር ማለት ነው።

አንቀጽ የተባለበት ምክንያትም፡- ይህ ዓይነት ቃል “አንቀጽ” ተብሎ የተሰየመበት ምክንያት በበር እንደሚገባበት፣ እንደሚወጣበት፣ እንደሚመላለሱበት፣ አእምሮ (ዕውቀት) የጠለቀ ምሥጢርን፣ የረቀቀ ጥበብን፣ ለመረዳት አንቀጽን እየመረመረ በምርምራዊ ሐሳብ ስለሚወጣበት፣ ስለሚገባበት፣ ስለሚመላለስበት ነው።

ጠቅለል ሲደረግ ግስ ድርጊት አመልካች የሆነ፣ በዐሥሩም መራሕያን እየረባ ለብዙ ቃላት መመሥረት መነሻ የሚሆን፣ መደብን ፣ ቍጥርን፣ ጾታን የሚያመለክቱ ምዕላዶችን እየጨመረ በልዩ ልዩ መልኩ የሚረባ ቃል ማለት ነው። አንቀጽ መባሉ አንቀጽ መግቢያ በር ማለት ሲሆን ግስም ቃላትን ለመመሥረት መነሻና መጀመሪያ በመሆን ስለሚያገለግል ነው።

የግስ ዓይነት፡-

የግስ ዓይነት ሲባል በልዩ ልዩ መልኩ ልንመለከተው እንችላለን።  ይህም ከአርእስት አንጻር፣ ከመሳብና ካለመሳብ አንጻር፣ ልንመለከተው እንችላለን።

ከአርእስት አንጻር ስንመለከተው ስምንት ናቸው። ከመሳብና ካለመሳብ አንጻር ስንመለከተው ደግሞ ሁለት ናቸው ። እነርሱም ገቢርና ተገብሮ ይባላሉ። እንዲሁም ዘር አንቀጽና  ነባር አናቅጽ ተብለውም በሁለት ይከፈላሉ። እያንዳንዱን ከምሳሌ ጋር እንመለከተዋለን።

ገቢርና ተገብሮ ግስ

ገቢር ግስ፡- ይህ ማለት ባለቤት አድራጊ የሆነበትና ግሱ ተሳቢ የሚፈልግ ማለት ነው። ለምሳሌ፡- ዳዊት ቀተለ ጎልያድሀ ቢል ዳዊት ጎልያድን ገደለ ማለት ነው። በዚህ ዐረፍተ ነገር ባለቤቱ ዳዊት ነው አድራጊ ነው። ግሱ ቀተለ ነው ተሳቢ ጎልያድን የሚፈልግ ወይም የሚሻ ማለት ነው።

ተገብሮ ግስ፡- ባለቤቱ ድርጊቱ የሚፈጸምበትና ግሱ ሌላ ተሳቢ የማይፈልግ ማለት ነው። ለምሳሌ ጎልያድ ተቀትለ ቢል ጎልያድ ተገደለ ማለት ሲሆን ባለቤቱ ራሱ ጎልያድና ድርጊት የሚፈጸምበትም ራሱ ነው ስለዚህ ግሱም ሌላ ተሳቢ አያስፈለገውም።

ዘር አንቀጽና ነባር አናቅጽ

ዘር አንቀጽ ፡-ይህ ማለት  መነሻ አንቀጽ ያለው የሚረባ፣ የሚገሰስ ማለት ነው። ለምሳሌ ቀደሰ፣ ቀተለ፣ ተንበለ፣ ወዘተ. ሲሆን ዘር አንቀጽ በራሱ ዐበይትና ንኡሳን አናቅጽ ተብለው በሁለት ይከፈላሉ። ዐበይት የሚባሉት ራሳቸውን ችለው ማሰር የሚችሉ ናቸው። ለምሳሌ ቀዳማይ አንቀጽ፣ ካልዓይ አንቀጽ፣ ሣልሳይ አንቀጽ ናቸው። ንኡሳን አናቅጽ የሚባሉት ግን የግስ ዘር ሁነው ግን ራሳቸውን ችለው ማሠር የማይችሉት ናቸው። ለምሳሌ ዘንድ አንቀጽ፣ ውስጠ ዘ፣ ሳቢዘር ወዘተ.

ነባር አንቀጽ፡- ይህ ማለት ደግሞ የሚረባ ግስ የሌለው በራሱ ማሰሪያ አንቀጽ የሚሆን ማለት ነው። ለምሳሌ ውእቱ፣ አልቦ፣ አኮ፣ ቦ ወዘተ

ውድ አንባብያን እያንዳንዱን በሰፊው በሚቀጥለው ክፍል እንመለስበታለን ለአሁኑ ግን እዚህ ላይ ይቆየን።