የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአታችን ሁሉ ያነጻናል፡፡ (፩ኛ ዮሐ.፩፥፯)

ክብር ምስጋና ይድረሰውና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ሁኖ ያፈሰሰው ክቡር ደሙ እኛን ከኀጢአታችን ሁሉ እንደሚያነጻን ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በሚገባ ይነግረናል፡፡ ‹‹ወደሙ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያነጽሐነ እምኵሉ ኀጣውኢነ፤ የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከኀጢአታችን ሁሉ ያነጻናል›› እንዲል በቀራንዮ የተቆረሰው ቅዱስ ሥጋ የፈሰሰው ክቡር ደም ዛሬም በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከኃጢአታችን እንነጻበት ዘንድ እንቀበለዋለን፡፡ (፩ኛ ዮሐ.፩፥፯)

እንዲህ ማለት ግን ሰው ሁሉ ወደ ንስሓ አባቱ ሳይቀርብ ንስሓ ሳይገባ በንስሓ ሳሙና ሳይታጠብ ከነኀጢአቱ  ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ቢቀበል ከኀጢአቱ ይነጻል ማለት አይደለም ሊሆንም አይችልም፡፡ የሰው ልጅ ከጥምቀት በፊት የሠራው ኀጢአት በጥምቀት የሚሰረይለት ሲሆን ከጥምቀት በኋላ የሚሠራው ኀጢአት ደግሞ የሚሰረየው  ንሰሓ ገብቶ በቅዱስ ሥጋውንና በክቡር ደሙን ሲቀበል ነው፡፡ ኀጢአት ዘእምቅድመ ጥምቀት ይሰረይ በጥምቀት ኀጢአት ዘእምድኅረ ጥምቀት ይሰረይ በሥጋሁ ወደሙ፤ ከጥምቀት በፊት  ያለ ኀጢአት በጥምቀት ይሰረያል ከጥምቀት በኋላ ያለ ኀጢአት በሥጋ ወደሙ ይሰረያል፡፡ ከጥምቀት በኋላ ያለ ኀጢያት በሥጋ ወደሙ ይሰረያል ማለት ከተጠመቀ በኋላ ኀጢአት መሥራት የሚገባው ሁኖ አይደለም፡፡ እንጨት ሁኖ የማይጤስ ሰው ሁኖ የማይበድል የለምና የሰው ልጅ በስሕተትም በድፍረትም በልዩ ልዩ መንገድ ኀጢአት ሊሠራ ይችላል፡፡ ይህን የሠራውን ኀጢአቱን ወደ ካህን ቀርቦ ሲናዘዝ ሰይጣን ክፉ ነውና ለካህኑ እንዳይናገር ከልቡናው የሰወረበትንና ጥቃቅኑን ኀጢአት ንስሓውን ጨርሶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ሲቀበል እግዚአብሔር በቸርነቱ ይቅር ይለዋል፡፡ በዚህ መሠረት የምንቀበለውንም ማወቅ ይገባናልና ይህ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የማን ነው? ጥቅሙ ምንድነው? እንዴት እንቀበለው? የሚለውን ከዚህ ቀጥለን እንመልከት፡፡

የምንቀበለው ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የማን ነው?

ይህ መለኮት የተዋሐደው ነፍስ የተለየው ትኩስ ሥጋና ክቡር ደም ከመድኃኔዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ የተሰጠን፣ ከሲኦል የዳንበት ከባርነት ነፃ የወጣንበት ከኀጢአታችን የነጻንበት ገነት የተከፈተበት የሰው ልጅ ሁሉ ደስታን ያገኘበት ነው፡፡ ታድያ ይህን ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ዛሬም ቢሆን ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመቅረብ በንጽሕና ስንቀበለው ከኀጢአታችን እንነጻለን፡፡  ይህ ሕይወተ ሥጋ ሕይወተ ነፍስ መድኃኒተ ሥጋ መድኃኒተ ነፍስ የሆነ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም የፈጣሪ እንጂ የፍጡር አይደለምና፡፡ የፍጡር ደም ቢጠጡት ይመራል ሥጋውንም ቢበሉት በሽታ ይሆናል፡፡ ይህን ግን ከኀጢአት ነጽተው  ቢቀበሉት በልሳነ ነፍስ የሚያናግር ምሥጢር የሚያስተረጉም ነው፡፡ እንዳለ ሊቁ አባ ሕርያቆስ፡፡ (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ)

ኢትዮጵያዊው  ቅዱስ ያሬድ የምንቀበለው ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ ከኀጢአታችን ሊያነጻን ወደ እርሱ ሊያቀርበን ያደለን እንዲሁም ከፍጡራን ደም የተለየ መሆኑን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ይህ ደም ወንድሙ በቅንዐት እንደገደለው እንደ አቤል ደም አይደለም፤ ይህ ደም አባቷ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርጎ እንዳቀረባት እንደ ዮፍታሔ ልጅ ደም አይደለም፤  ይህ ደም በእንጨት መጋዝ እንደተረተሩት እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ደም አይደለም፤ ይህ ደም በደንጋይ እንደ ወገሩት እንደ ኤርምያስ ደም አይደለም፤ ይህ ደም በምድረ ምድያም እንደ ገደሉት እንደ ሕዝቅኤል ደም አይደለም፤ ይህ ደም ስለ ወይኑ ርስት እንደገደሉት እንደ እስራኤላዊ ናቡቴ ደም አይደለም፤ ይህ ደም በቤተ መቅደስ እንደገደሉት እንደ ዘካርያስ ደም አይደለም፤ ይህ ደም ስለ ወንድሙ ሚስት ሄሮድስ እንደገደለው እንደ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስ ደም አይደለም፤ ይህ ደም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይገድለው ዘንድ ሲፈልገው ሄሮድስ እንደ ገደላቸው እንደ ሕፃናት ደም አይደልም፤ ይህ ደም ኀጢአትን ይቅር ለማለት የፈሰሰ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው፤ይህ ደም ዓለምን ሁሉ ያዳነ ደም ነው፤ ይህ ደም አዳምንና ልጆቹን ከሲኦል ያዳነ ደም ነው… ይህ ደም ለዓለሙ ሁሉ ቤዛ የሆነ ደም ነው፤ አሁንም ቅዱስ ወደሆነ መሥዋዕቱ እንቅረብ ለስርየተ ኀጢአት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንቀበል፡፡›› (ዝማሬ ምሥጢር ክፍል)

በትምህርተ ጥቅስ ያየነው ቅዱስ ያሬድ ያስቀመጠልን መልእክት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከፍጡራን ደም የተለየ መሆኑን ነው የሚያስረዳን፡፡ በግፍ የሞተ አቤል ደም፣ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሁና የቀረበች የዮፍታሔ ልጅ ደም፣ ይወርዳል ይወለዳል ዓለምን ያድናል ብለው ትንቢት የተናገሩ በዚህም ምክንያት ደማቸው የፈሰሰ የነቢያት (ኢሳያይስ፣ ኤርምያስ፣ ሕዝቅኤል) ደም፤ እንዲሁም በቤተ መቅደስ የተገደለ የካህኑ ዘካርያስ ደም፤ የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ደም፤ ዕዳ በደል የሌለባቸው የንጹሓን ሕፃናት ደም ሁሉ የፍጡራን ደም ስለሆነ ሰዎችን ከኀጢአት አላነጻም ዓለምንም አላዳነም፡፡ ዓለምን ማዳን ይቅርና ራሳቸውን እንኳ ከሥጋ ሞት ከነፍስም ሞት ማዳን አለቻልም፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ይቅር ማለት ኀጢአትን ማንጻት ሲኦልን መክፈት በከበረ ደሙ ፈሳሽነት በዓለመ ሥጋና በዓለመ ነፍስ ያሉትን ማዳን የሚችል የመድኃኔ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ደም ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ታድያ ይህ የፈጣሪ ደም እንደመሆኑ መጠን ለመቀበል በመንዘጋጅበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈለጋልና በድፍረት ሳይሆን በፍርሃት በኀጢአት ሳይሆን በንጽሕና ሁነን ልንቀበለው ይገባል፡፡ 

የቅዱስ ሥጋና የክቡር ደሙ ጥቅም ምንድን ነው?

ሕይወትን ይሰጣል፡- ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደሙን የሚቀበሉ ሰዎች ዘለዓለማዊ ሕይወትን ያገኛሉ፡፡ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይታበል ቃሉ እንደተናገረው ‹‹ዘበልዐ ሥጋየ ወሰትየ ደምየ ቦ ሕይወት ዘለዓለም፤ ሥጋየን የበላ ደሜን የጠጣ የዘለዓም ሕይወት አለው፡፡›› (ዮሐ.፮፥፶፬) የሰው ልጅ ሥጋ ወደሙን ካልተቀበለ ሕይወትን ማግኘት አይችልም ወደ ገነትም ለመግባት እድሉ አይኖረውም፡፡ ማንኛውም ሰው ሃይማኖት አለኝ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ክርስቲያን ነኝ ለማለት ከጥምቀት ቀጥሎ በሜሮን መታተም ሥጋ ወደሙን መቀበል አለበት፡፡ ይህ ሲሆን ነው ሕይወትን ማግኘት በሕይወት መኖር የምንችለው፡፡ ያለሥጋ ወደሙ ረጅም ጾምና ጸሎት ብቻውን አይጠቅምም ይህንንም ለመረዳት የላመ የጣመ ከመቅመስ የሞቀ የደመቀ ከመልበስ ተቆጥበው ዓለምን ንቀው ለብዙ ዘመናት ለረጅም ወራት በዱር በገደል ወድቀው ጤዛ ልሰው ደንጊያ ተንተርሰው በጾም በጸሎት ተወስነው የሚኖሩት አባቶቻችንን መላእክት እየመጡ ሥጋ ወደሙን ካልተቀበላችሁ ድካማችሁ ከንቱ ነውና ቤተ ክርስቲያን ወዳለበት ሂዳችሁ ሥጋ ወደሙን ተቀበሉ እያሉ እንደሚነግሯቸው እነሱም ከበአታቸው ወጥተው ሥጋ ወደሙን ተቀብለው ወደ በአታቸው እንደሚመለሱ ከቅዱሳን የታሪክ መዛግብት እንረዳለን፡፡ ‹‹አንድ ባሕታዊ ከሰው ተለይቶ ከበአት ተከቶ ከበርሃ ወድቆ ይኖር ነበር በ፵ ዘመኑ መልአኩ መጥቶ ሥጋ ወደሙን ካልተቀበልክ አይረባህም አይጠቅምህምና ከቤተ እግዚአብሔር ሂደህ ሥጋ ወደሙን ተቀበል አለው ቢሄድ ቄሱ ቅድሳት ለቅዱሳን (ከኀጢአት ንጹሕ የሆነ ሥጋ ወደሙን ይቀበል) እያለ ሲያውጅ ሰማው ለዚህስ አልበቃሁም ብሎ ተመልሶ ሄደ ደግሞ በ፵ ዘመኑ ሂደህ ተቀበል አለው ቢሄድ እንደዚያው ቅድሳት ለቅዱሳን እያለ ሲያውጅ ሰማው ለዚህስ አልበቃሁም ብሎ ተመልሶ ሂዷል በ፫ኛው መልአኩ አሁንስ በቅተሃል ተቀበል ብሎት ተቀብሏል፡፡›› (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ)

የሰው ልጅ ንስሓ ገብቶ ከኀጢአት ነጽቶ ቅዱስ ቊርባንን የሚቀበል ከሆነ ዳግም ሞት የለበትም፡፡ በፍጻሜ ዘመኑ ከዚህ ዓለም ተለይቶ ወደ ወዲያኛው ዓለም በሚሸጋገርበት ጊዜም ወደ ገነት እንጅ ወደ ሲኦል አይወርድም፡፡ ወደ ሲኦል ቢሄድም እንኳ ልትቀበለው አትችልም፤ ምክንያቱም በሕይወተ ሥጋ ሳለ በደመ ክርስቶስ ታትሟልና፡፡ ለዚህም ማስረጃ ይሆነን ዘንድ በርቱዐ ሃይማኖት የተጻፈውን እንመልከት፤ ‹‹ሄርማ እንዲህ አለ ሁለንተናዋ ደረቅ የሆነ በላይዋ ልምላሜ የሌላት እንጨት ለእሳት የተዘጋጀች ናት (በእሳት ትነዳለች) ቅጠል ያለውን ግን ወደ እሳት ቢጨምሩት አይቃጠልም እሳቱ ይጠፋል እንጂ፡፡ እንደዚህም ከተጠመቀ በኋላ ጥምቀቱን ጠብቆ በቅዱስ ሥጋው እና በክቡር ደሙ ጸንቶ የሚኖር ክርስቲያን ቢሞትም ዕዳ የለበትም፡፡ መልካምም ክፉም ያላደረገ ከቅዱሳን መካከል አንድ ሰው ነበር ነገር ግን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሥጋ ወደሙን ይቀበላል ሳይቆርብ አንድ ቀን እንኳ አያሳልፍም በሞተ ጊዜም መላእክተ ብርሃንና መላእክተ ጽልመት የእኛ ነው በማለት ይከራከሩ ጀመር ይህንን ነገርም ወደ እግዚአብሔር አደረሱት እግዚአብሔርም ወደ ሲኦል ሂዱና ተፋረዱ አላቸው ወደ ሲኦል በአደረሷት ጊዜም ሲኦል ይህችን ነፍስ ወደ እኔ አታቅርቧት ሁለንተናዋ በክርስቶስ ሥጋና ደም ታትሟልና አለች እኔ እሷ ማቃጠል የምችል አይደለሁም እርሷ ታቃጥለኛለች እንጅ የመለኮት ኀይል በእርሷ ላይ አድሯልና፡፡ መላእክተ ጽልመት ይህን በሰሙ ጊዜ ሸሹ መላእክተ ብርሃንም ሰውን ለወደደ እግዚአብሔር ምስጋና ይገባዋል እያሉ እያመሰገኑ ይህችን ነፍስ ወደ ገነት ወሰድዋት (አስገቧት)፡፡ በንጽሐ ሥጋ በንጽሐ ነፍስ ሁኖ ሥጋ ወደሙን የሚቀበል ክርስቲያን ብፁዕ ነው፡፡›› (ርቱዐ ሃይማኖት) ልብ ብለን ካስተዋልነው ሄርማ ሥጋ ወደሙን ስለሚቀበል ሰው የተናገረው ቃል ፍጻሜው በሕይወት መኖር እንደሚችል ነው፡፡ ስለዚህ በንጽሐ ሥጋ በንጽሐ ነፍስ በንጽሐ ልቡና ሁነን በሚገባ ተዘጋጅተን የዘለዓለም ሕይወትን ወደምናገኝበት ነፍሳዊ ምግብ በፍጹም ትሕትና ልንቀርብ ይገባናል እንጅ ልንርቅ አይገባንም፡፡ አንዳንዶች ለምን ሥጋ ወደሙን አትቀበሉም ሲሏቸው እኔ ገና ወጣት ነኝ ኀጠአት ልሠራ እችላለሁ ዕድሜየም ለሥጋ ወደሙ አልደረሰም ዛሬ ተቀብየ ነገ ባቋርጠውስ በትዳሬ ባልጸናስ እያሉ ያለሆነ  ምክንያት ሲያቀረቡ ይደመጣሉ፡፡ ሌሎችም ሥጋ ወደሙ ከተቀበልን ዐይናችን ይፈዛል እጅና እግራችን ይተሳሰራል ጉልበታችን ይደክማል እርጅና ይመጣል ጆሯችን ይደነግዛል የሚል ከየት እንደሰሙት የት እንዳመጡት የማይታወቅ ዲያብሎስ ከዚህ ቅዱስ ማዕድ ለይቶ ከመንግሥተ ሰማያት ለማውጣት ስለሚፈልግ በጆሯቸው ሹክ ያለቸው ይመስል እንዲህ ዐይነት ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ያሳዝናል እጅግ ያሳዝናል፤ ያሳዝናል የሚለው ቃል ራሱ አይገልጸውም ምክንያቱም በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን ከተባለ ክርስቲያን  እንዲህ አይነት የወረደ ቃል ሲሰማ ያሳዝናል፡፡ ደግሞም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም ዐይነ ሥጋን የሚያፈዝ ሳይሆን ዐይነ ልቡናንም ጭምር የሚያበራ ለደካሞች ብርታትን ለበሽተኞች ፍጹም ጤናን ለኀዘንተኞች መጽናናትን ለኃጢአተኞች እና ምሕረትን እና ይቅርታን የዘላለም ሕይወትን የሚሰጥ መሆኑን ማንም ሰው መዘንጋት ይለበትም፡፡

  እንዴት እንቀበለው?

ንስሓ በመግባት፡- ንስሓ ማለት መጸጸት በሠሩት ኀጢአት ማዘን ወደ እግዚአብሔር መመለስ ይሠሩት የነበረውን ኀጢአት እርግፍ አድርጎ ትቶ ሐዲስ የጽድቅ መንገድ የቅድስና ኑሮ የንጽሕና ሕይወት መጀመር ያለፈውን ኀጢአት ላለመድገም በቁርጥ ኅሊና አምኖ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር መወሰን ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለመኖር የወሰነ ሰው ደግሞ ምሥጢራትን መካፈል የግድ ያሻዋልና በንጽሕና ሁኖ ሥጋ ወደሙን ሊቀበል ይገባዋል፡፡ ይህ ቅዱስ ቊርባን ንስሓ ገብተው ለሚቀበሉት ሰዎች የሚያድናቸው ሲሆን በኀጢአት ውስጥ ሁነው የሚቀበሉትን ደግሞ ያጠፋቸዋል ለዚህም የብሕንሳ ኤጲስ ቆጶስ አባ ሕርያቆስ ምስክራችን ነው፡፡ ‹‹እሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ፤ ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሰዎች የሚያድን እሳት ነው፤ እሳት በመጠን የሞቁት እንደሆን ውርጭ ያርቃል የበሉትን የጠጡትን ከሰውነት ያስማማል፤ ሥጋ ወደሙም ከኀጢኣት ነጽተው  ቢቀበሉት ሕይወተ ሥጋ ሕይወተ ነፍስ ይሆናልና፡፡ እሳት በላዒ ለዐማፅያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ፤ ስመ አምላክነቱን ለሚክዱ ሰዎች የሚያቃጥል እሳት ነው… ስመ አምላነቱንስ ይሁን ስመ ቊርባንነቱን ከካዱማ ምን ይረባናል ምን ይጠቅመናል ብለው ይቀበሉታል ቢሉ በግብር መካድ አለና ሥጋ  ወደሙም ከኀጢአት ሳይነጹ ሳይበቁ ቢቀበሉት በፍዳ ላይ ፍዳ ያመጣልና እንዲል፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ወይእዜኒ ዘበልዖ ለዝንቱ ኅብስት ወዘሰትዮ ለዝንቱ ጽዋዕ እንዘ ኢይደልዎ ደይኖ ወመቅሠፍቶ በልዐ ለርእሱ፤ አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ ይህንንም ጽዋዕ የጠጣ ለራሱ ፍርዱንና መቅሠፍቱን ይበላል፡፡ እንዳለ ሳይገባን ተቀብለን ፍዳንና መቅሠፍትን በራሳችን ላይ እንዳናመጣ አስቀድመን ሰውነታችንን መርምረን እንወቅ፡፡ (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ፩ኛቆሮ.፲፩፥፳፯)

ይህንንም አባቶቻችን ሥጋውን በእሳተ ባቢሎን ደሙን በማየ ግብፅ መስለው፤ እሳተ ባቢሎን ሠለስቱ ደቂቅን ሳይነካ በአፍኣ ያሉትን እንዳቃጠላቸው ማየ ግብፅም እስራኤላውያንን ሳይነካ ግብጻውያንን እንዳሰጠማቸው ሁሉ፤ ሥጋ ወደሙም ከኀጢአት ለነጹ ጻድቃን ዕሤትን (ዋጋን) የሚያሰጥ ሲሆን በኀጢአት ላሉ ኃጥኣን ደግሞ መቅሠፍትን የሚያመጣ መሆኑን ምሳሌ መስለው አስረድተውናል፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ዛሬም ቄሱ በቅዳሴ ጊዜ ‹‹የወሰዳችሁትን ሳትመልሱ የበደላችሁትን ሳትክሱ ንስሓ ሳትገቡ ከኀጢአት ሳትነጹ ብትቀበሉት ሥጋው እሳት ሁኖ ያቃጥላችኋል ደሙ ባሕር ሁኖ ያሰጥማችኋል›› እያለ ለሁሉም አዋጅ የሚነግረው፡፡ በተጨማሪም አባ ሕርያቅስ ከነኀጢአታችን ወደ ቅዱስ ቊርባን መቅረብ እንደማይገባን ይነግረናል፡፡ ‹‹ከኀጢአት ንጹሕ ያልሆነ ሰው ቢኖር ሥጋ ወደሙን ከመቀበል ይራቅ በኀጢአት የተሰነካከለ ሰው ቢኖር ኀጢአቱን አይዘንጋ ኀጢአት ሠርተው ሊዘነጉት አይገባምና፡፡ ይህን ሥጋ ወደሙን የሚያቃልል ሰው ቢኖር አይቅረብ (አይቊረብ) ይከልከል እንጂ›› በማለት ይነግረናልና ለኀጢአታችን ምክንያት እየደረደርን ከሥጋ ወደሙ መራቅ ሳይሆን የበደልነውን በደል ያጠፋነውን ጥፋት የፈጸምነውን ግፍ ለመምህረ ንስሓችን ተናዘን መምህረ ንስሓ የሚያዘውን ቀኖና ፈጽመን አምላካችን ሆይ እንደ ቸርነትህ ይቅር በለን እያልን ለዚህ ዘለዓለማዊ የሕይወት ምግብ ብቁ ሁነን መንግሥቱን ለመውረስ ስሙን ለመቀደስ እንድንበቃ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት የሁሉም ቅዱሳኑ ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡