የድንግል ማርያም ክብሯ፣ ዕረፍቷ እና ትንሣኤዋ

 

በዲያቆን ታደለ ፈንታው

ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ክብሯ

እግዚአብሔር ዘላለማዊ ኀይሉንና አምላክነቱን ለዓለም ከገለጸበት ታላቅ ሥራ መካከል በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም የገለጸው ድንቅ ሥራው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ይህንን ኹኔታ ድንግል ማርያም ‹‹ብርቱ የኾነ እርሱ ታላቅ ሥራን በእኔ አድርጓል፤ ስለዚህም ፍጥረት ዅሉ ያመሰግኑኛል›› በማለት ገልጻዋለች (ሉቃ. ፩፥፵፱)፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ከሴቶች መካከል ተለይተሽ የተባረክሽ ነሽ›› ብሏታል (ሉቃ. ፩፥፳፰)፡፡ ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹የጌታዬ እናት›› ብላታለች (ሉቃ. ፩፥፵፫)፡፡ ቅዱስ ዳዊት ደግሞ ‹‹ልጄ›› ይላታል (መዝ. ፵፬፥፱)፡፡ ሰሎሞንም ‹‹እኅቴ›› ብሎ ጠርቷታል (መኃ. ፭፥፩)፡፡ ለወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ የተሰጠችውም እናት ኾና ነው (ዮሐ. ፲፱፥፳፮)፡፡

ቅዱስ እግዚአብሔር ፍጥረቱንና ዓለሙን ለማዳን የወሰነው ጊዜ ሲደርስ የተወለደው ከድንግል ማርያም ነው፡፡ አስቀድሞ በመልአኩ አፍ እንዳናገረ ክብሩ በእርሷ ላይ ታየ (ኢሳ. ፷፥፪)፡፡ ማኅፀኗን ከተማ አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርስዋ አደረ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በእመቤታችን ላይ የማደሩ ምሥጢር ያነጻቸው፤ ይቀድሳቸው፤ በሥጋም በነፍስም መርቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያገባቸው ዘንድ በነቢያት፣ በሐዋርያት ላይ እንዳደረው ዓይነት አይደለም፡፡ ከሦስቱ አካል አንዱ አካል እግዚአብሔር ወልድ (ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍስዋ ነፍስን ነስቶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ ኾነ እንጂ፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ይህን ዘለዓለማዊ እውነት ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፤ የልዑል ኃይልም ይጸልልሻል፡፡ ስለዚህ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል›› በማለት ገልጾታል (ሉቃ. ፩፥፵፭)፡፡

‹‹በእግዚአብሔር፣ በመላእክትና በሰው ፊት የከበረ ሰው መታሰቢያው ለዘለዓለም ነው፡፡ በቤቱ በቅጥሩ የማይጠፋ የዘለዓለም ስምን ይቀበላልና›› ተብሎ በትንቢተ ኢሳይያስ እንደ ተገለጸው (ኢሳ. ፶፭፥፫) ይህን ታላቅ በረከት እንደሚሰጣቸው የተናገረው የማይዋሸው ቅዱስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ወልድ እናት ከድንግል ማርያም የበለጠ በሰውና በእግዚአብሔር ዘንድ የከበረ ማንን ልንጠራ እንችላለን? እንደ እርሷስ ሊታሰብ፣ ሊከበርም የሚችል በቅድስና ሕይወት ያለፈ ማን ይኖራል? እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ስለ ድንግል ማርያም ያልተናገረበት ጊዜ፤ ያላናገረው ቅዱስም የለም፡፡

ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች በጻፈው መልእክቱ እንደ ተናገረው ‹‹የቅድስት ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና፤ አማኑኤልን መውለዷና የማይሞተው ጌታ መሞቱ›› እነዚህ ሦስቱ ከዚህ ዓለም ጥበበኞችና ገዢዎች የተሰወሩ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቅዱስ አግናጥዮስ ‹‹እነዚህ ድንቅ ምሥጢራት በራሳቸው ከንግግርና ከቋንቋዎች በላይ ኾነው የሚነገሩ በእግዚአብሔር የዝምታ መጐናጸፊያ የተጠቀለሉ ድብቅና ጣፋጭ ምሥጢሮች ናቸው›› ይላል፡፡ የእመቤታችን ክብር ውስንና ደካማ የኾነ አእምሮ ሊገነዘበው ከሚችለው በላይ ነውና፡፡ የእመቤታችን ምስጋናዋ የበዛለት ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊም ‹‹አቤቱ መሰንቆ ልቡናዬን አነቃቃ፤ የልቤንም እንዚራ፡፡ ድምፁን ከፍ አድርጎ የዳዊት ልጅ የኾነችውን፣ የጌታውን እናት ድንግል ማርያምን ያመሰግናት ዘንድ፤ ለዓለም ሕይወት የሚሰጠውን የወለደች እናቱ የኾነች እርሷን ከፍ ከፍ ያደርጋት ዘንድ›› ብሏል፡፡ በሌላም አንቀጽ ደግሞ ‹‹ከሕሊናት ዅሉ በላይ ለኾነ ለዚህ ነገር አንክሮ ይገባል፡፡ ምድራዊት ሴት ፈጣሪዋን ወለደችው፤ እርሱም እናቱን ፈጠረ›› በማለት የእመቤታችንን ወላዲተ አምላክነት ያደንቃል፡፡

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ደራሲና ገጣሚ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም እንዲህ ሲል ክብሯን ገልጾታል፤ ‹‹የእስራኤል ንጉሥ በእስራኤል ልጅ አደረ፤ የዳዊት አምላክ ከዳዊት ልጅ ሥጋን ለበሰ፡፡ የዕብራውያን ጌታ በዕብራውያን ልጅ ማኅፀን ተወሰነ፡፡ ለአብርሃም የዕብራይስጥ ልሳን ያስተማረው ከቀድሞም ያልሰማውን ልሳን እንዲናገር አፉን ጆሮውን የከፈተለት ከዕብራዊት ድንግል ተወለደ፤ በድንግልና ወተት ጥቂት ጥቂት እያለ አደገ፡፡ የሕፃናትን ሥርዓት እንዳያጎድል አፉን የሚፈታባት ዘመን እስኪፈጸም ጥቂት ጥቂት እያለ በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ለሙሴ በዕብራይስጥ ልሳን በጣቶቹ የተጻፉትን ዐሠርቱ ቃላትን የሰጠ የዕብራይስጥ ፊደል ለመማር ከመምህር እግር በታች ተቀመጠ፡፡ የባቢሎን አውራጃ በምትኾን ሰናዖርም የፍጥረትን ሁሉ ቋንቋ የበተነ እርሱ የአሕዛብን ቋንቋ እንደማያውቅ እናቱ አፍ በፈታችበት ልሳን በዕብራይስጥ ልሳን ሲናገር ኖረ፡፡ ጆሮ ይህንን ነገር ከመስማት የተነሣ የሚለመልምበት ይህ ነገር ዕፁብ ድንቅ ነው፡፡ ለዚህ አንክሮ ይገባል፡፡›› ይህ በሰው ጥበብ በብራናና በቀለም የተጻፈ እውነት ሳይኾን ለድኅነት በተጠሩ ሰዎች ዅሉ ልቡና በአምላክ ጥበብ የተጻፈ እውነት ነው፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ በማኅፀን የተጀመረው የማዳን ሥራ፤ ፍጻሜውን ያገኘው በቀራንዮ ነው፡፡ የጌታ ልደቱና ጥምቀቱ፣ ሞቱ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግመኛ መምጣቱ በነገረ ድኅነት ትምህርታችን እጅግ ጠቃሚ የኾኑ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቤተልሔም የሥጋዌውን ምሥጢር ሲያሳይ ዮርዳኖስ ቀዳማዊ ልደቱን ያሳያል፡፡ የመጀመርያው የእኛ ባሕርይ ሲኾን ሁለተኛ የጌታ የራሱ የባሕርይ ገንዘቡ የኾነ ነው፡፡ እርሱ የሰው ልጅ ኾነ፤ እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ኾንን፡፡ ይህ ዅሉ የተደረገው አምላካችን ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ ነው፡፡ እርሱ የእኛን ተፈጥሮ ገንዘቡ ስላደረገ እኛ ደግሞ የእርሱን ቅድስና ገንዘብ በማድረግ የመንግሥቱ ተካፋዮች ኾንን፡፡ የእኛ የኾነው ዅሉ የእርሱ፤ የእርሱ የኾነውም የእኛ ኾነ፡፡ የእኛ መንፈሳዊ ልደት የተገኘው ጌታ በሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው ልደት ነው፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አምላክና የሰው ልጆች የተገናኙበት፤ አምላክና ሰው የተዋሐዱበት መካነ ምሕረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዙፋኑን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት የዘረጋበት መካነ ሰላም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዙፋን ፍጹም በማይናወጥና ጸጥታ በነገሠበት ሥፍራ የሚዘረጋ የክብር ዙፋን ነው፡፡ ይህም ዙፋን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ነው፡፡ ለዚህ ክብር በቅታ ያከበረችንን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያዛመደችንን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እንደምን አናከብራትም?

ዕረፍቷ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ ከልጇ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወራት፤ ከጌታ ስቅለት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመታት ኖራለች፡፡ ጌታን የፀነሰችበትን ወራት ስንጨምር እመቤታችን በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይኾናል፡፡ ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ያረፈችውም በጥር ሃያ አንድ ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጽሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ‹‹ከሚያሰጥመው ባሕር ሞገድ የተነሣ የማትነቀነቅ፤ መልሕቆቿም በሦስቱ ሥላሴ ገመድ የተሸረቡ ናቸው፡፡ ይህቺ ደግሞ ከነፋሳት ኀይል የተነሣ የማትናወጥ፤ በጭንጫ ላይ ያለች የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ ናት፡፡ እርሷን የተጠጋ መውደቅ መሰናከል የለበትም›› የሚላት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞት አይቀርምና እርሷም እንደሰው የምትሞትበት ጊዜ ደረሰ፡፡ እግዚአብሔር አያዳላምና (ሮሜ. ፪፥፲፩)፡፡

የቤተ ክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደ ኾነ ያስረዳል፤ የመጀመሪያው፡- ‹‹ለመለኮት ማደርያ ለመኾን የበቃችው ኀይል አርያማዊት ብትኾን ነው እንጂ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን ልትሸከመው ይቻላታል?›› የሚሉ ወገኖች ነበሩና በእርግጥም እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ እንጂ የመላእክትን አለመኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ጌታችን የሱራፌልን፣ የኪሩቤልን ባሕርይ ባሕርዩ አላደረገም፡፡ የመላእክትንም ባሕርይ እንደዚሁ፡፡ የእርሷን አካል ባሕርዩ አደረገ እንጂ፡፡ ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ ‹‹… የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም›› አለ (ዕብ. ፪፥፲፬-፲፭)፡፡ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መኾኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛው፡- ቅዱስ ያሬድ እንደ ተናገረው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት አምላክ መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ዅሉ በለበሰው ሥጋ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡

በቅዱሳት መጻሕፍት ሞትን እንዳያዩ የተወሰዱ ቅዱሳን ሄኖክ፣ ኤልያስ፣ ሌሎችም እንዳሉ ተጠቅሷል፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም የኀያሉ እግዚአብሔር እናቱ፣ መቅደሱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ኾና እያለ ሞትን መቅመሷ የሚያስገርም ምሥጢር ነው፡፡ ይህ ከሕሊናት ዅሉ በላይ የኾነው ምሥጢር ርቀቱ (ረቂቅነቱ) በሊቃውንት እንዲህ ተገልጿል፤ ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ኀይለኛ በኀይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላዳላም፤ ሞትስ ለሟች ይገባዋል የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው፡፡››

ትንሣኤዋ

ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ከሞት ወጥመድ በላይ እንኳን የኾነ ሌላ ኀይል አለ፤ ይኼውም ሞት ፈጽሞ ሊያሸንፈውና ሊገዳደረው የማይችል የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኀይል ነው፡፡ በሰይጣን ዘንድ ያለው የሞት ኀይል ነው፡፡ ሕያው እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነውና ሞት ሊያሸንፈው ሊደርስበትም የማይችለውን ሕይወት ይሰጣል፡፡ ይህንን እግዚአብሔር የሚሰጠውን ሕይወት ሰይጣን በእጁ ሊነካው ከቶውንም አይችልም፡፡ እግዚአብሔር ለሙታን ሕይወትን ይሰጣል፡፡ የሞትም የሕይወትም ባለቤት እርሱ ነውና፡፡ ከሞት ኀይል በላይ የኾነው ይኸው የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን የድንግል ማርያምን ሥጋ መልካምም ኾነ ክፉ ለሠሩ ሰዎች ዋጋ ይከፍል ዘንድ ለፍርድ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ፈርሶና በስብሶ በምድር ላይ እንዲቀር አላደረገም፡፡ ከሙታን መካከል ተለይታ ተነሥታለች፡፡ ሊቁ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፤ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና›› በማለት ያቀረበው ምስጋናም ትንሣኤዋን የሚገልጽ ነው፡፡

መንፈስ ቅዱስ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን በትንቢት እንዳናገረ ትንሣኤዋንም በትንቢት ሲያናግር ኑሯል፡፡ ይህን ታላቅ ምሥጢር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› ብሎ ገልጾታል (መዝ. ፻፴፩፥፰)፡፡ ነቢዩ የትንቢት ክፍል ትንሣኤዋን አስረድቷል፡፡ ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው፡፡ በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፈው ሕጉ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ያከበረው ነገር ኾኖ ሊመጣ ላለው ነገር ማሳያ ነው፡፡ እውነተኛዋ ታቦት ድንግል ማርያም ናት፡፡ ሙሴ በተቀበለው ታቦት ውስጥ ያለው ጽላት በውስጡ የያዘው ሕጉን ነው፤ በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን የሕጉ ባለቤት ነውና፡፡

እመቤታችን ከጌታችን ፅንሰት ጀምሮ እስከ ቀራንዮ አደባባይ ድረስ፤ ሐዋርያት ጉባኤያትን ሲያካሒዱ አብራ ነበረች፡፡ ይህ ዅሉ ታላቅ ሥራ ከተፈጸመ በኋላ ዓረፍተ ዘመን ገታት፡፡ በሥጋ ዐረፈች፡፡ ሐዋርያት ሊቀብሯት ሲሹም ከአይሁድ ክፋት የተነሣ ልጇ ሌላ ክብርን ደረበላት፡፡ ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይቷል፡፡ ልጇ ወዳጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ የልጇ መለኮታዊ ኀይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አደረጋት፤ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለ ትንሣኤዋ የተናገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ጠቢቡ ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቁርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› (መኃ. ፪፥፲-፲፬) በማለት የተናገረው ትንቢት የዚህ ዓለም ድካሟ ዅሉ መፈጸሙን ያስረዳል፡፡

እመቤታችን ልጇን ይዛ ከአገር አገር በረሀብና ጥም የተንከራተተችበት ጊዜ አሁን አለፈ፡፡ ታናሽ ብላቴና ሳለች ልጇን አዝላ በግብጽ በረኀ የተቀበለችው መከራ ዅሉ ፍጻሜ አገኘ፡፡ ከእግረ መስቀል ሥር ወድቃ የልጇን የቆሰለ ገላ እየተመለከተች የደረሰባት ልብ የሚሰነጥቅ ሐዘን ወደ ደስታ ተለወጠ፡፡ ‹‹በነፍሷ ሰይፍ ያልፋል›› ተብሎ የተነገረው ልብ የሚሰነጥቅ መከራ እንደ ነቢዩ ቃለ ትንቢት የሚቀጥልበት ጊዜ ተፈጸመ፡፡ እርሷ ባለችበት ሥፍራ የሕይወት ትንሣኤ ያላቸው ሰዎች ይኾኑ ዘንድ አስቀድማ ከሙታን ተለይታ በመነሣት የተጠበቀልን ተስፋ ማሳያ ኾነችን፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ስደት፣ መከራ፣ ሐዘን፣ ሰቆቃ የለም፤ መገፋት መግፋትም የለም፡፡ ከእንግዲህ ወዲያ ልጇ ሲንገላታ፣ ሲሰደድ ሲገረፍ፣ ሲሰቀል፣ ሲቸነከር ያየችበት ዓለም አለፈ፡፡ አሁን የልጇን ልዕልና ከሚያደንቁ ጋር ታደንቃለች፤ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት ጋር ታከብረዋለች፡፡ ይኸውም ከገቡ የማይወጡበት፤ ሐዘን፣ መከራ፣ ችግር የሌለበት ሰማያዊት አገር ነው፡፡ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው የድል አክሊልን የሚቀዳጁበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚያም ከፍጡራን ዅሉ ከፍ ባለ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘላለም ትኖራለች፡፡

ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ፍቅሯ፣ አማላጅነቷ፣ የልጇም ቸርነት በዅላችንም ላይ አድሮ ይኑር፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡