‹‹አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› (መዝ. ፻፴፩፥፰)

በመምህር ሳሙኤል ተስፋዬ

ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹አምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ሲፈጸም ከልጅ ልጅህ ተወልጄ ስደትህን በስደቴ፣ ሞትህን በሞቴ አጥፍቼ፤ የቀደመ ክብርህን መልሼ ያጣኸውን ርስት፣ ገነትን (መንግሥተ ሰማያትን) አወርስሃለሁ›› በማለት ለአባታችን አዳም የገባው ቃል ኪዳን ፍጻሜው በደረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ወልድ ማደሪያነት የተመረጠች፣ ለአዳም እና ለዘሩ መዳን ምክንያት የኾነች ‹‹የልጅ ልጅ›› የተባለችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዳ ፲፭ ዓመት ሲኾናት በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት የእግዚአብሔር ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ማደሪያ ኾነች (ገላ. ፬፥፬)፡፡ ልጇን በወለደች ወቅት ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ወዴት አለ?›› የሚለውን የሰብአ ሰገልን ዜና የሰማው ሄሮድስ ሕፃኑን ለመግደል ፈለገ፡፡ እመቤታችንም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማዳን ወደ ግብጽ ይዛው ተሰደደች (ማቴ. ፪፥፲፪)፡፡ የስደቱ ዘመን አልቆ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ በኋላም ኢየሱስ ክርስቶስ ፴ ዓመት ሲኾነው ስለ መንግሥተ ሰማያትና ስለ ሰው ልጆች ነጻነት ይሰብክ ጀመር፡፡ ከዚህ በኋላ የአዳምና የዘሩን ሞት ለማጥፋት በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሞተ፤ በሦስተኛው ቀን ተነሥቶ፣ ባርነትን አስወግዶ ለሰው ልጅ ነጻነትን ዐወጀ፡፡

በዚህ ዅሉ የድኅነት ጉዞ ውስጥ ያልተለየችና ምክንያተ ድኂን የኾነችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደች በ፷፬ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች፡፡ ይህን የእመቤታችን ሞት የሚያስደንቅ መኾኑን ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድ «ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ሞት ለማናቸውም ሰው የተገባ ነው፡፡ የማርያም ሞት ግን ዅሉን ያስደንቃል» በማለት ገልጾታል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት የእመቤታችንን የከበረ ሥጋዋን ገንዘውና ከፍነው ለማሳረፍ ወደ ጌቴሴማኒ መካነ ዕረፍት (የመቃብር ቦታ) ይዘው ሲሔዱ አይሁድ በቅናት መንፈስ ተነሣሥተው «ቀድሞ ልጇንበሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፤ በዐርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡ እንደገናም ተመልሶ ይህን ዓለም ለማሳለፍ ይመጣልእያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ፡፡ አሁን ደግሞ እርሷንምእንደ ልጇ ተነሣች፣ ዐረገችእያሉ ሲያውኩን ሊኖሩ አይደለምን? ! ተሰብሰቡና በእሳት እናቃጥላት» ብለው ተማከሩ፡፡

ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊም የከበረ ሥጋዋን የተሸከሙበትን አጎበር (የአልጋ ሸንኮር) በድፍረት ያዘ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ በእሳት ሰይፍ ሁለት እጆቹን ቆረጣቸው፡፡ እጆቹ ተንጠልጥለው ከቆዩ በኋላ ‹‹በእውነት የአምላክ እናት ናት›› ብሎ ስለ አመነ እጆቹ ተመልሰው እንደ ነበሩ ኾነዉለታል፡፡ ከዚህ በኋላ መልአከ እግዚአብሔር የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ  ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር ነጥቆ ወስዶ በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አስቀመጠው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ከጥቂት ወደ ሐዋርያት በተመለሰ ጊዜም የእመቤታችን የከበረ ሥጋ በገነት መኖሩን ነገራቸው፡፡ ሐዋርያትም የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አግኝተው  ለመቅበር በነበራቸው ምኞትና ጉጉት ‹‹ዮሐንስ አይቶ እኛ እንዴት ሳናይ እንቀራለን? ብንጠየቅስ ምን እንመልሳለን?›› በማለት በነሐሴ አንድ ቀን ሱባኤ ጀምረው ሲጾሙና ሲጸልዩ ከሰነበቱ በኋላ በሁለተኛው ሱባዔ መጨረሻ (ነሐሴ ፲፬ ቀን) ጌታችን የእመቤታችንን ትኩስ የከበረ ሥጋ አምጥቶ ሰጥቷቸው በታላቅ ዝማሬና ውዳሴ በጌቴሴማኒ ቀብረውታል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ የእመቤታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት ሲፈጸም አልነበረምና ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጣ እመቤታችን በተቀበረች በሦስተኛው ቀን  እንደ ልጇ ተነሥታ ስታርግ አገኛት፡፡ በዚህ ጊዜ ‹‹ቀድሞ የልጅሽን፣ አሁን ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ›› ብሎ ቢያዝን እመቤታችን ከእርሱ በቀር ሌሎች ሐዋርያት ትንሣኤዋን እንዳላዩ ነግራ አጽናናችው፡፡ ወደ ምድር ወርዶ የኾነውን ዅሉ ለሐዋርያት እንዲነግራቸው አዝዛው፣ ለምልክት ይኾነው ዘንድም የተገነዘችበትን ሰበኗን ሰጥታው ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡ ቅዱስ ቶማስም ሐዋርያት ወደ አሉበት ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ «የእመቤታችን ነገር እነዴት ኾነ  ብሎ ቢጠይቃቸው፤ «እመቤታችንን እኮ ቀበርናት» ብለው ነገሩት፡፡

እርሱም ምሥጢሩን ደብቆ «አይደረግም! ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር  እንደምን ይኾናል አላቸው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹አንተ መጠራጠር ልማድህ ነው፡፡ ቀድሞ የጌታን ትንሣኤ ተጠራጠርክ አሁንም አታምንም?›› ብሎ የእመቤታችን መካነ መቃብር ሊያሳዩት ይዘውት ሔዱ፡፡ መቃብሩን ቢከፍቱ የእመቤታችንን የከበረ ሥጋ አጡት፤ ደነገጡም፡፡ በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ «አታምኑኝም ብዬ ነው እንጂ እመቤታችንስ ተነሥታ ዐርጋለች» ብሎ  የኾነውን ዅሉ ተረከላቸውና የሰጠችውን ሰበኗን አሳያቸው፡፡ እነርሱም ማረጓን አምነው ሰበኗን ለበረከት ተከፋፍለው ወደየአህጉረ ስብከታቸው ሔዱ፡፡ በዚያም ሕሙማንን ሲፈውሱበትና ገቢረ ተአምር ሲያደርጉበት ኖረዋል፡፡

በዓመቱ ‹‹ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እንዴት እኛ ይቅርብን?›› ብለው ከነሐሴ ፩ ቀን ጀምሮ ሱባዔ ገብተው ነሐሴ ፲፮ ቀን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ልመናቸውን ተቀብሎ እመቤታችንን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ንፍቅ (ረዳት) ቄስ፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ገባሬ ሠናይ (ዋና) ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ አቍርቧቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችንን ሐዋርያት በግልጽ እያዩዋት ከጌታችን ጋር በክብር በይባቤና በዝማሬ ወደ ሰማይ ዐርጋለች፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ትንሣኤ ጊዜያዊና ዘለዓለማዊ በመባል ይታወቃል፡፡ ጊዜያዊ ትንሣኤ የሚባለው የእግዚአብሔር ከሃሊነት የሚገለጽበት ተአምራዊ ሥራ ኾኖ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የሚፈጸምና ዳግም ሞትን የሚያስከትል ነው፡፡ ለምሳሌ ኤልያስ ያስነሣውን ወልደ መበለት (፩ኛነገ. ፲፯፥፰-፳፬)፤ ዐፅመ ኤልሳዕ ያስነሣውን ሰው (፪ኛነገ. ፲፫፥፳-፳፩)፤ ወለተ ኢያኢሮስን (ማቴ. ፱፥፰-፳፮)፤ በዕለተ ስቅለት ከመቃብር ወጥተው በቅድስት ከተማ የታዩ ሙታንን (ማቴ. ፳፯፥፶፪-፶፫)፤ በቅዱስ ጴጥሮስ ጸሎትና ምልጃ የተነሣችዋን ጣቢታን (ሐዋ. ፱፥፴፮-፵፩)፤ እንደዚሁም ትንሣኤ አልዓዛርን መጥቀስ ይቻላል (ዮሐ. ፲፩፥፵፫-፵፬)፡፡ እነዚህ ዅሉ ለጊዜው ከሞት ቢነሡም ተመልሰው ዐርፈዋል፡፡ ወደፊትም ትንሣኤ ዘጉባኤ ይጠብቃቸዋል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በትንቢቱ «ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅድስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም» (መዝ. ፻፴፩፥፰) በማለት አስቀድሞ የክርስቶስን ትንሣኤ ከገለጸ በኋላ ቀጥሎ የመቅደሱ ታቦት እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከሞት እንደምትነሣ ተናግሯል (ማቴ. ፭፥፴፭፤ ገላ. ፬፥፳፮፤ ዕብ. ፲፪፥፳፪፤ ራእ.፫፥፲፪)፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ የክብርና የሕይወት ትንሣኤ ሲኾን ሁለተኛ ሞትን አያስከትልም፤ ትንሣኤ ዘጉባኤንም አይጠብቅም፡፡ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤያችን በኵር ኾኖ በሞተ በሦስተኛው  ቀን ተነሥቷል፡፡ እመቤታችንም በልጇ ሥልጣን፤  እንደ ልጇ ትንሣኤ በሦስተኛው ቀን ተነሥታ ትንሣኤ ዘጉባኤን ሳትጠብቅ በክብር ዐርጋለች፡፡

እንደዚህ ያለውን ትንሣኤ ከእርሷ በቀር ሌሎች ቅዱሳን ወይም ነቢያትና ሐዋርያት አላገኙትም፡፡ በዚህም ኹኔታ የቅድስት ድንግል ማርያም ትንሣኤ ከማናቸውም ትንሣኤ ልዩ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ትንሣኤ ዘለዓለማዊ፣ ከዳግም ሞተ ሥጋ ነጻ የኾነ ትንሣኤ ነው፡፡ ዕርገቷም በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ከእነ ሄኖክና ኤልያስ ዕርገት የተለየ ነው፡፡ «ሄኖክ ሞትን እንዳያይ በእምነት ተወሰደ፤ እግዚአብሔርም ስለ ወሰደው አልተገኘም» ተብሎ እንደ ተጸፈ (ዕብ. ፲፩፥፭)፣ ሄኖክ ወደ ሰማይ ያረገው በምድር ሳለ እግዚአብሔርን በእምነቱና በመልካም ሥራው ስላስደስተና በሥራውም ቅዱስ ኾኖ ስለ ተገኘ ነው፡፡ ኾኖም ግን ወደፊትም ገና ሞት ይጠብቀዋል፤ ሞቶም ትንሣኤ ዘጉባኤ ያስፈልገዋል፡፡ ነቢዩ ኤልያስም በእሳት ሠረገላም ቢነጠቅም (፪ኛ ነገ. ፪፥፲) ወደፊት ሞት ይጠብቀዋል፤ ትንሣኤ ዘጉባኤም ያስፈልገዋል፡፡ የእመቤታችን ትንሣኤ ግን ሞት የሌለበት ዘለዓለማዊ ትንሣኤ ነው፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በድርሰቱ ‹‹በቃልዋ የታመነች፣ በሥራዋም የተወደደች ቅድስት ድንግል ማርያምን መላእክት እያመሰገኗትና በመንፈሳዊ ደስታ እያጀቧት ወደ ሰማይ አሳረጓት›› ሲል እንደ ገለጸው፣ በመጽሐፈ ስንክሳርም እንደ ተመዘገበው ቅዱስ ዳዊት ‹‹በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋ፣ ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች›› (መዝ. ፵፬፥፱) በማለት የተናገረው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ አባቷ ዳዊት በበገና፣ ነቢዩ ዕዝራ በመሰንቆው እያመሰገኗት፤ በቅዱሳን መላእክት፣ በቅዱሳን ነቢያትና ጻድቃን ዝማሬ በብሩህ ደመና ወደ ሰማይ ዐርጋ በክብር ተቀምጣለች፡፡ «እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ዐረገች፤ በሰማይም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች» እንዳለ ቅዱስ ያሬድ በመዝሙሩ፡፡ በዚያም ሥፍራ ሁለተኛ ሞት ወይም ኀዘን፣ ጩኸትና፣ ስቃይ የለም፡፡ የቀደመው ሥርዐት አልፏልና (ራእ. ፳፩፥፬-፭)፡፡

ስለዚህም የእመቤታችን ዕረፍቷ፣ ትንሣኤዋና ዕርገቷ በሚታሰብበት በጾመ ፍልሰታ ሳምንታት ምእመናንን ከአካባቢያቸው ራቅ ብለው በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመሔድ አለዚያም በየአጥቢያቸው በመሰባሰብ እመቤታችን በተለያዩ ጊዜያት ሞቷንና ትንሣኤዋን ለሐዋርያት የገለጸችበትን ኹኔታ ያስባሉ፡፡ በጾም በጸሎት ተወስነው የልጇን ቸርነት የድንግልን አማላጅነት በእምነት ኾነው ይማጸናሉ፡፡ እንደዚሁም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነሐሴ ፲፮ ቀን እናቱን መንበር፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ተራዳዒ ካህን፣ ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ ቀድሶ ሐዋርያትንም እመቤታችንንም ማቍረቡን በማሰብና ድኅት ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ለማግኘት ቅዱስ ሥጋውን፣ ክቡር ደሙን ይቀበላሉ፡፡ ሱባዔው ሲፈጸምም «በእውነት ተነሥታለች» እያሉ በደስታ የጾሙን ወቅት ይፈጽማሉ፡፡ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የትንሣኤያችን በኵር የኾነው የአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት ከዅላችን ጋር ይኹን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡