ዓርብ ስቅለት (የድኅነት ቀን)

ሊቀ ማእምራን ብርሃነ መስቀል አጠና 

ዓርብ ስቅለት የዕዳ ደብዳቤያችን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለመጨረሻ ጊዜ የተደመሰሰበት፤ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ የወጣንበት ዕለት ስለኾነ ‹የድኅነት ቀን› ይባላል፡፡ ጌታችን ከተያዘባት ሰዓት አንሥቶ አይሁድ ከቀያፋ ወደ ሐና፣ ከሐና ወደ ቀያፋ ሲያመላልሱት አደሩ፡፡ ሲነጋ ከቀያፋ ወደ ጲላጦስ አደባባይ አስረው ወሰዱት (ማቴ. ፳፯፥፩-፶፯)፡፡ አይሁድ ይህን አጥፍቶአል የሚሉት ነጥብ ሳይኖራቸው ነውና ጌታችንን ለፍርድ ያቀረቡት ጲላጦሰ እነርሱ ወደ ተሰባሰቡበት ቦታ ወጥቶ ‹‹ይህን ሰው ወደ እኔ ያመጣችሁበት በደል ምንድን ነው?›› ሲል በጠየቃቸው ጊዜ በቂ ምላሽ አላቀረቡም፡፡ ‹‹ክፉ  የሠራ  ባይኾንስ  ወደ  አንተ  ባላመጣነውም  ነበር›› በሚል የሸፍጥ ቃል ሲያጕረመርሙ ጲላጦስ መልሶ  ‹‹እኔ  ምንም  ጥፋት  አላገኘሁበትም፤  እናንተወስዳችሁ  እንደ  ሕጋችሁ  ፍረዱበት፤›› አላቸው፡፡ አይሁድም ኦሪት ‹‹ኢትቅትል  ብእሴ  ጻድቀ  ወኀጥአ  ኢታኅዩ፤  ጻድቅን  ሰው  አትግደል፤  ኀጥኡንም  ከፍርድ አታድን፤›› ትላለችና ‹‹እኛስ ማንንም ልንገድል አልተፈቀደልንም፤››  ብለዋል (ዮሐ. ፲፰፥፳፰-፴፩)፡፡

ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ‹‹በሕጋችን  ጻድቀ  ባሕርይ ክርስቶስን  መግደል  አይገባንም  ሙሉ በሙሉ ጥፋተኞች ነን፤›› ሲያሰኛቸው ነው፡፡ በኋላም እርሱ ሞቶ ዓለም ይድን ዘንድ ወደ ምድር መጥቷልና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ ጥፋቱ ሞት ተፈረደበት፡፡ ስለዚህም ገርፈው ሰቀሉት፡፡

ጌታችን ሲሰቅልም የሚከተሉት ሰባት ተአምራት ተፈጽመዋል፤

፩. ፀሐይ ጨለመ፤

፪. ጨረቃ ደም ኾነ፤

፫. ከዋክብት ረገፉ፤

፬. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ተቀደደ፤

፭. አለቶች ተፈረካከሱ፤

፮. መቃብራት ተከፈቱ፤

፯. ሙታን ተነሡ (ማቴ. ፳፯፥፶፩-፶፬)፡፡

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ የሚከተሉትን ሰባት ዐበይት ቃላት አሰምቶ ተናግሯል፤

፩. ‹‹ኤሎሄ ኤሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አምላኪየ አምላኪየ ለምን ተውኸኝ?)››፤

፪. ‹‹እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ››፤

፫. ‹‹አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁትምና ይቅር በላቸው››፤

፬.እመቤታችንን ‹‹ሴትዮ ሆይ፣ እነሆ ልጅሽ››፤ ደቀ መዝሙሩንም‹‹እናትህ እነኋት› በማለት የቃል ኪዳን እናትነትና ልጅነት ማከናወኑ፤

፭. ‹‹አባት ሆይ በአንተ እጅ ነፍሴን አደራ እሰጣለሁ››

፮. ‹‹ተጠማሁ››፤

፯. ‹ዅሉ ተፈጸመ› (ማቴ. ፳፯፥፵፭-፵፮፤ ሉቃ. ፳፫፥፵፫-፵፮፤ ዮሐ. ፲፱፥፲-፴)፡፡

ከስድስት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ጨለማ ኾኖ ከቈየ በኋላ ከዘጠኝ እስከ ማታ እንደ ተለመደው ብርሃን ኾኖአል፡፡ ‹ወፍና ሠርክ ይበርህ ብርሃነ ፀሐይ›› እንዲል (ዘካ. ፲፬፥፯)፡፡ በዚህ ዕለት ሰባት መስተፃርራን (ጠበኞች) ታረቁ፤ ተስማሙ፡፡ እነዚህም፡- ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሕዝብና አሕዛብ፣ ነፍስና ሥጋ ናቸው (ኤፌ. ፪፥፲፤ ቈላ. ፩፥፳)፡፡ ጌታችን ጠዋት በሦስት ሰዓት ተገረፈ፤ በስድስት ሰዓት ተሰቀለ (ማቴ. ፳፯፥፩-፴፯፤ ሉቃ. ፳፫፥፩-፵፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፩)፡፡

በዘጠኝ ሰዓት ጌታችን በውኃው ተጠምቀን፣ ደሙን ተቀብለን የእግዚአብሔር ልጆች እንኾን ዘንድ ከቀኝ ጎድኑ ጥሩ ውኃ፣ ትኩስ ደም አፈሰሰልን (ዮሐ. ፲፱፥፴፬)፡፡ በዐሥራ አንድ ሰዓት ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ከመስቀል አውርደው ሽቶ እየረበረቡ በድርብ በፍታ ገንዘው ቀበሩት (ሉቃ. ፳፫፥፶-፶፬፤ ዮሐ. ፲፱፥፴፰-፵፪)፡፡ ቅድስት ነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዳ ነፍሳትን ነጻ አወጣች (፩ኛ ጴጥ. ፫፥፲፱)፡፡ በዚህ ጊዜ በርሃነ መለኮቱ በሲኦል ተገለጠ፡፡ ስለዚህም ‹‹ንሴብሖ ለእግዚአብሔር›› እየተባለ ይዘመራል፡፡ ከሆሣዕና አንሥቶ ተከልክሎ የነበረው ኑዛዜ ይናዘዛል፤ ጸሎተ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር