በዓለ ደብረ ቁስቋም  

ከሦስት የስደት እና መከራ ዓመታት በኋላ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ይዛ አረጋዊ ዮሴፍንና ሰሎሜን አስከትላ ወደ ግብፅ ስትሰደድ በስተደቡብ የምትገኘው ደብረ ቊስቋም ላይ ያረፉበችበት ኅዳር ፮ ቀን ይከበራል፡፡

የቁስቋም ተራራ ጌታችን ኢየሱስን ለመግደል ከሚፈልጉት ሸሽተው መጠጊያ ያገኙበት እንዲሁም ቅዱስ ገብርኤል ንጉሥ ሄሮድስ መሞቱን ለቅዱስ ዮሴፍ በሕልሙ የገለጸበት ስፍራም ጭምር ነው፡፡ ‹‹የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሞተዋልና፥ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ›› እንዲል። (ማቴ.፪፥፲፱-፳)

ቁስቋም ተራራ ጌታችን ብዙ ተዓምራት የፈጸመበት በመሆኑ ተባርኳል፤ ተቀድሷልም፡፡ ይህ ተራራ የተቀደሰ ስለመሆኑ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ታኦፊሎጎስ በድርሳነ ማርያም እንዲህ ብሏል፤ ‹‹ይህም ከሀገሮቹ ሁሉ ተራሮች የሚበልጥ (የተለየ) ከፍ ያለ ተራራ ነው፡፡ በውስጡ ቅዱስ አግዚአብሔር ያድራል፡፡ ይህንን ተራራ የእግዚአብሔር ልጅ ወዶታል፤ አክብሮታልምና፤ ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ከተቀደሰች እናቱ ጋር አድሮባታልና፡፡ ከመላእክት ቤት ያድር ዘንድ አልወደደም፤ ቢታንያንም አልመረጠም፤ ከተራራው ላይ ባለች ገዳም ቤት ውስጥ አደረ እንጂ፤ ነቢዩ ዳዊት፤ የጽዮንን ተራራ ወደደ፤ በአርያምም መቅደሱን ሠራ እንዳለ፡፡››

ሊቁም በመቀጠል ሙገሳውን እንዲህ ሲል ገልጿል፤ ‹‹አንተ ተራራ ሆይ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆንህ ጊዜ በኪሩቤልና በሱራፌል መካከል ፍጹም ደስታ ተደረገ፡፡ የመላእክት ሠራዊት ቅዱስ የሆነ ፈጣሪያቸውንና ጌታቸውን ይታዘዙ (ያገለግሉ) ነበር፡፡ አንተ ተራራ ሆይ ያደረብህ ጌታችን ስለሆነ ከተራሮች ሁሉ ከደብረ ሲናም ይልቅ ከፍ ከፍ አልህ፤ ጌታችን በደብረ ሲና ባረፈ ጊዜ ፍጹም ደስታ፣ ታላቅ ብርሃንም በሆነ ጊዜ መቅረብና መመልከት ከሙሴ በቀር የቻለ የለም፡፡ እርሱም ቢሆን ፊቱን ማየት አልቻለም፡፡ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እርሱን ዐይቶ በሕይወት መኖር የሚቻለው የለምና፡፡ እኛ ግን አየን፤ ከዚህ ማደሩንም ተረዳን፤ ዳግመኛም ንጽሕት በሆነች በማርያም ዘንድ አየነው፡፡ ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ማርያም ዘንድ በቤተልሔም ስለ እኛ በተዋሐደው ሥጋ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ያለን እኛን ከቸርነቱና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ መጥቶ አዳነን፤ ከዓለም ሁሉ ይልቅ ጣዖትን በማምለክ ሲበድሉም ወደ ግብፅ  ሀገር ወርዶ በእነርሱ ላይ የመለኮትነት ብርሃኑን በማብራት ታላቅ የሆነ ክብሩን ገለጠ››፡፡ እመቤታችን ቅድስት ማርያምም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር በዚህም ተራራ ስድስት ወራት ዐርፈዋል፡፡ (ድርሳነ ማርያም)

በየዓመቱ ኅዳር ፮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የእነርሱን ስደትና ወደ ሀገራቸው እስራኤል መመለሳቸውን በማስታወስ ታከብራለች፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ሄሮድስ ጌታችን ኢየሱስን ለመግደል በፈለገ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ዮሴፍ በሕልሙ ‹‹ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ›› ባለው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫-፲፭)

እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር ከመሰደዷ አስቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብፅ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደ ግብፅ ይወርዳል›› ተብሎም በተናገረው መሠረት ትንቢቱ ተፈጽሟል፡፡ (ኢሳ. ፲፱፥፩)

ኅዳር ፮ ቀን የሚነበበው የመጽሐፈ ስንክሳር ክፍል ጌታችን ኢየሱስ ዳግመኛም በኋላ ዘመን ሐዋርያትን በደብረ ቁስቋም ሰብስቦ፤ ታቦትንና ቤተ ክርስቲያኑን አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን እንደ ሰጣቸው፤ ጌታችንም ካረገ ከብዙ ዘመናት በኋላ በኅዳር ፮ ቀን ‹‹አስተጋብኦሙ እግዚእነ ለሐዋርያቲሁ ቅዱሳን ውስተ ዝንቱ ደብረ ቊስቋም ወቀደሰ ታቦተ ወቤተ ክርስቲያን ወሠርዐ ቊርባነ ወመጠዎሙ ሥጋሁ ቅዱሰ
ወደሞ ክቡረ፤ በዚህ በደብረ ቊስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰበሰባቸው፤
ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ
ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል›› ይላል፡፡ (ስንክሳር ኅዳር ፮)

እኛንም ለዚህ ክብር የበቃን እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ ድርሳነ ማርያም መጽሐፍ ትርጉም በመምህር ተስፋ ሚካኤል፤ ፳፻፫ ዓ.ም፣ ስንክሳር ኅዳር ፮