በአታ ለማርያም

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

ታኅሣሥ ፪ ቀን ፳፻፲፫ .

ጥንትም ስትታሰብ በአምላክ ኅሊና

ትታወቅ ነበረ በሥሉስ ልቡና

በአቷን አደረገች የአርያም መቅደስ

የዓለሙን ፈጣሪ ዘወትር ለማወደስ

አዳም ተፈርዶበት የሞት ሞት ውሳኔ

ምንም አጋዥ ቢያጣ የሚለው ወገኔ

ሔዋን ብትማቅቅም ከሲኦል ደይን ወድቃ

አስታራቂ ባይኖር ቢጠፋ ጠበቃ

ይግባኝ አለ አዳም ቸርነቱን አውቆ

 ከፈጣሪው ዙፋን ከችሎቱ ወድቆ

የአዳምን ልመና አምላክ ተቀበለ

ሐዘን ጩኸትህን ሰምቼአለሁ አለ

ከልጅ ልጅህ አንዷን እናቴ አድርጌ

እመጣለሁ ካንተ ዝምድና ፈልጌ

በቀነ ቀጠሮ አዳም ተሰናብቶ

ተስፋውን ሰንቆ ወጣ እጅ ነሥቶ

ይህም የተስፋ ቃል በሰማይ ተሰማ

በኢዮር፣ በኤረር እንዲሁም በራማ

ምስጋናቸው ናኘ ዓለም ሁሉ ሰማ

ወደ የት ነው በአቷ?

ማን ትሆን እያሉ በተስፋ ዓለሙ

ተልእኮውን ሽተው በተጠንቀቅ ቆሙ

ዐበይት ደቂቃኑ ነቢያቱ ጓጉ

በአታቸው ጸንተው በአትሽን ፈለጉ

ሕዝቅኤልም አለ በምሥራቅ አየኋት

የተዘጋች መቅደስ ማንም ያልገባባት

ኢሳይያስም ጮኸ በታላቅ ደስታ

ወንድ ልጅ ተሰጠን የሚሆን መከታ

ዳንኤልም አያት ከተራራው ላይ ጫፍ

አንቀጸ ብርሃን የሰማይ ደጃፍ

አምስት ሺህ ዘመን ከአምስት መቶ ዓመት

ሲታሰስ ሲፈለግ የማርያም መምጣት

ሊባኖስ ላይ ታየች እንደ ፀሐይ ደምቃ

በኢያቄም ሐና ቤት ፍጹም አሸብርቃ

ሰማያዊው ጽላት ከወዴት ይቀመጥ

የሊባኖስ ዝግባ ጥድ ዋርካ ይቆረጥ

ለፈጣሪ ዙፋን ይታነጽ መቅደሱ

የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ተቀኘ ንጉሡ

እቴ ሙሽራዬ እያለ ቢዘምር

መዓዛዋ አወደው ከሊባኖስ ምድር

ለጽላት ማደሪያ ለታቦቱ ዙፋን

ሠርቶ አጠናቀቀ ጠቢቡ ሰሎሞን

የኢያቄም ፍሬ የሐና እሸት

ለአምላክ ማደሪያ አፈራች እናት

በታቦት ላይ ታቦት በመቅደስ ላይ መቅደስ

በአታ ለማርያም ተገኘ ታኅሣሥ

ከአእላፍ አንዱ ከፈጣሪው ታዞ

ወረደ ፋኑኤል ኅብስት ጽዋ ይዞ

ቅዳሴያቸው ናፍቋት የእልፍ አእላፉ

በክብር ቤት ገባች ሸፍኗት በክንፉ