‹‹ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ›› (ሉቃ. ፲፫፥፳፬)

ዲያቆን ዐቢይ ጌታሁን

ኅዳር ፴ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በምድራዊ ሕይወት ሰዎች የሥጋ ፈቃዳቸውን ብቻ መፈጸማቸው ለኃጢአታቸው መብዛት መንሥኤ ይሆናል፤ በጾም በጸሎት እንዲሁም በስግደት ስለማይተጉና በመከራ ስለማይፈተኑም እንደፈለጉ በመብላት በመጠጣት፣ ክፋት በመሥራት እንዲሁም ሰውን በመበደል በድሎት እንዲኖሩ ዓለም ምቹ ትሆንላቸዋለች፡፡ ዓለማዊነት መንገዱ ሰፊ በመሆኑ የሥጋ ፈቃዳችን የምንፈጽምበት መንገድም በዚያው ልክ ብዙ ነው፡፡

በክርስትና ሕይወት ውስጥ ግን ሰው በትጋቱ ልክ ፈተናውም የበዛ ነው፡፡ ክርስትና የራሱ መለኪያ ስላለውም በሕገ እግዚአብሔር በመኖር፣ ትእዛዛቱን በመፈጽም እና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በመጠበቅ ለመዳን መትጋት ያስፈልጋል እንጂ በስመ ክርስትና የይምሰል ኑሮ በመኖርና በጥፋት መንገድ በመጓዝ ላለመጥፋት ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡

በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በየከተማውና በየመንደሩ እየሄደ፥ በኢየሩሳሌምም እየተመላለሰ በሚያስተምርበት ወቅት አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ጠየቀው፡፡ ‹‹አቤቱ የሚድኑ ጥቂቶች ናቸውን?›› ጌታችንም እንዲህ ብሎ መለሰ፤ ‹‹ወደ ጠባቡ በር ትገቡ ዘንድ በርቱ፤ እላችኋለሁ፥ ሊገቡ የሚሹ ብዙዎች ናቸው፤ ግን አይችሉም፡፡›› (ሉቃ. ፲፫፥፳፪-፳፬)

ጠባብ በር የተባለውም የመንግሥተ ሰማያት በር ነው። ነገር ግን ጠባብ የሆነው በር በሥጋቸው ፈቃድ ኃጢአትን ለሚሠሩ እንጂ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ሰዎች ቤት ተለክቶ ጠባብ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ማቴዎስ ወንጌል ላይ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፤ ‹‹በጠባቢቱ በር ግቡ፤ ወደ ጥፋት የምትሰድ በር፤ ሰፊ መንገድም አለችና፤ ወደ እርስዋም የሚገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወደ ሕይወት የምትወስደው በር እጅግ ጠባብ፤ መንገድዋም ቀጭን ናትና፤ የሚገቡትም ጥቂቶች ናቸው፡፡›› (ማቴ.፯፥፲፫-፲፬)

የመንፈሳዊነት መለኪያው ክርስቲያን መምሰል ሳይሆን በማመን የተቀበልነውን ሕገ እግዚአብሔር (ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን) በተግባር እየገለጥን ምሥጢራትን መካፈልና ሆኖ መገኘት ነው፡፡ ስለጸለይን፣ ስላስቀደስን ወይንም ስለጾምን ብቻ መንፈሳዊ ሰው ነን ማለት አይቻልም፤ ከውስጥ ከመነጨ መንፈሳዊ ስሜት ክርስቲያናዊ ምግባርን መፈጸም ይኖርብናል፤ ይህም ማመንን በመታመን (በተግባር) መግለጽ ማለት ነው፡፡

አንድ ሰው ፈቃደ ሥጋውን ለፈቃደ ነፍሱ ማስገዛት የሚሳነው በዓለም ሲኖር መንፈሳዊ ሕይወትን ትቶ ለሕገ እግዚአብሔር ለመገዛት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር ነው፡፡ በዚህም ጊዜ የጽድቁ መንገድ ይጠፋበትና የመንግሥተ ሰማያትም በር መግቢያው ሁሉ እየጠበበት ይሄዳል፡፡ ብዙውን ጊዜ ከሃይማኖት እና ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የራቁ ሰዎች ለመጾም የሚከብዳቸው የሥጋቸውን ፈቃድ ብቻ ስለሚያዳምጡ የነፍሳቸውን ፈቃድ (ሕገ እግዚአብሔርን) መስማት ስለሚተዉ ነው። ነፍሳቸው ግን ለእሷ የሚያስፈልጋትን ምግብ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት፣ ንስሐ መግባት ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን መቀበል በአጠቃላይ ምሥጢራትን መካፈል ስላልቻለች ሁልጊዜም ጽድቅን በመራብ መንፈሳዊ ኃይሏን እያጣች በመሄድ ለፈቃደ ሥጋ ወደ መገዛት ትወርዳለች ያኔ የዚያ ነፍስና ሥጋ (ሰውነት) ባለቤት በጠባቡ በር መግባት ይሳነዋል፡፡

ፈቃደ ሥጋችን በእኛ ላይ በሚሰለጥንበት ጊዜ የነፍሳችንን ፈቃድ (መሻት) ማዳመጥም ያቅተናል። ስለዚህ የነፍስን ፈቃድ ከሥጋችን ፈቃድ ማስበለጥ (ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ) ማስገዛት ይኖርብናል፡፡ አንድ ወታደር ለትግሉ መሣሪያ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ነፍሳችንም ከእግዚአብሔር የሰማችውንና የምታምነውን የሕይወት ቃል በተግባር ለመፈጸም ሥጋችን ለፍሳችን የጽድቅ ሥራ መሥሪያ በመሆኑ ሥጋችን ለነፍስ ፈቃድ መገዛት መቻል አለበት፡፡

በሰውነታችን፣ በጊዜያችን እና በገንዘባችን ላይ መወሰን ስንችል የጽድቁ በር አይጠብብንም፤ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛትም እንችላለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ዓለማዊነትን መርጦ ከመንፈሳዊነት የራቀ ሰው ግን በሰፊው መንገድ ላይ እየተጓዘ በመሆኑ ወደ ጠባቡ በር መግባት ይሳነዋል፡፡

በዚህ ዘመን አብዛኛው ሰው ዓለማዊውን እና መንፈሳዊውን ሕይወት በመደባለቅ ለመኖር በመፈለጉ በትክክለኛው መንገድ መጓዝ ሲያቅተው እናያለን፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ሰርጉ ላይ እንዲዘመርለት እና እንዲሸበሸብለት፤ እንዲዘፈንለት እንዲሁም እንዲጨፈርለት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለ ውሳኔ ሊወስን የቻለው በዚያች ዕለት ምድራዊ ደስታን ለማግኘት በማሰብ እንጂ እውነትን በማወቁ ወይንም መዳን በመፈለጉ አይደለም፡፡ ፍላጉቱም ፈቃደ ሥጋን መፈጸም ብቻም ስለሆነ ትዳሩ አይባረክለትም፡፡

በተለይም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት የማይችሉት ወጣቶች መሆናቸውን አስተውለን ሊሆን ይችላል፡፡ እነርሱም ከልጅነታቸው ጀምሮ የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ያላደጉ፤ የራሳቸውን ሰውነት ለቃለ እግዚአብሔር በማዘጋጀት እና ቃለ እግዚአብሔርን ከዕውቀት በላይ በእምነት መኖር ያልቻሉ ወጣቶች ናቸው፡፡ ለዚህም ቤተሰብ ኀላፊነት አለባቸው፤ ልጆቻቸውን በሰንበት ትምህርት ቤት እንዲማሩ በማድረግ፣ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በማነጽ እና በማሳደግ ለክርስቲያናዊ ሕይወታቸው አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡፡ መምህራን ደግሞ ክፍተቶችን በመለየት እንደየፍላጎታቸውና አቅማቸው ቤተሰብን ለብቻ ልጆችን ለብቻ በተናጠል በማስተምር ኀላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ይህን ማድረግ ከተቻለ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ተግባብተው መኖር ይቻላቸዋል፡፡ ልጆችም ወላጆች የሚሏቸውን ሰምተው አድርጉ የሚባሉትን በማድረግ ጥሩ ልጆች የመሆን ዕድል ፈንታቸው የሰፋ ይሆናል፡፡ ‹‹አባትህንና እናትህን አክብር›› የሚለውን ሕግም እየተገበሩ ያድጋሉ፤ ልጆች ቤተሰቦቻቸውን በማክበር በሥጋም በነፍስም በረከት ያገኛሉ፡፡ ‹‹ልጆች ሆይ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ›› እንዲል፤ (ዘፀአት.፳፥፲፪፣ ኤፌ. ፮፥፩)

ሰው በዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለበት ለይቶ ሊያውቅ ይገባል፡፡ በተለይ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ዓለምን በመመርመር በጎውን መለየትና በጽድቁ ጎዳና መጓዝ እንዳለብን ቅዱስ ጳውሎስ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹መንፈሳዊ ሰው ግን ሁሉን ይመረምራል፤ ራሱ ግን በማንም አይመረመርም፡፡›› (፩ ቆሮ. ፪፥፲፭)

በአሁኑ ጊዜ ግን በብዙዎች የሥጋ ፈቃድና የነፍስ ፈቃድን ለይቶ የማወቅና የመተግበር ፍላጎት ባለመኖሩ ዓለማዊውና መንፈሳዊው እሳቤ ስለሚቀላቀልባቸው በሰፊ በር ውስጥም እንዳሉ መረዳት አልቻሉም፡፡

በዘመነ ሐዋርያት የሐዋርያትን ስብከት የሰሙ እና ክርስትና የተቀበሉ ክርስቲያኖች በቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ ሞት ምክንያት ቢበተኑም ለክርስትናው መስፋፋት ምክንያት መሆን የቻሉት ከፈቃደ ሥጋ ርቀው የተማሩትን ትምህርት በቃልም በሕይወትም መተግበር ስለቻሉ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለምእመናንና ለሌሎች ወገኖች ቃለ እግዚአብሔርን የማስተማር ኀላፊነት እንዳለባቸው እንረዳለን፡፡ ነገር ግን ትምህርተ ወንጌል በተገቢው መንገድ ተሰጥቶም በራስ ስንፍና መምህራንን እንዲሁም ሌሎች ካህናትና አገልጋዮችን በመውቀስ ከቤተ ክርስቲያን መራቅና ከመንፈሳዊ ሕይወት መውጣት እራስን እንጂ ሌላን አያስጠይቅም፤ ‹‹እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ›› እንዲል፡፡ (ማቴ. ፯፥፩)

ሁሉም እንደ ሥራው በዕለተ ምጽአት ዋጋውን ያገኛልና ለመዳን የራስ ጥረት ያስፈልጋል፤ ደኅንነትን መሻት እና በመዳኛው ጎዳና ለመጓዝ መበርታት እንዲሁም የራሱን ድርሻ መወጣት አለበት፡፡ ምንም እንኳን በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ኮትኩተው ሊያስድጉን የሚገባቸው ቤተሰቦች እና መምህራን ቢሆኑም በእምነትም ሆነ በሃይማኖት ጸንቶ መኖር ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሰባት ዓመት ከሆነው በኋላ በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መኖር እንዳለበት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ ይህም መጸለይ መጾም እና ክርስቲያናዊ ተግባራትን መፈጸም ስለሆነ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ሥር ያለን የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ይህን ዓለም ንቀንና ርቀን በጠባቡ በር እንድንገባ ሥጋችን አሸንፈን ለፈቃደ ነፍሳችን እንገዛ! ለዚህም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!