ዘመነ ስብከት

ዲያቆን ፍቅረሚካኤል ዘየደ

ታኅሣሥ ፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የዘመን አከፋፈል መሰረት ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በፊት ከታኅሣሥ ፯ ጀምሮ እስከ ፳፱ ያለው ወቅት ዘመነ ስብከት ይባላል፡፡ እያንዳንዱ ሳምንታትም ስብከት፣ ብርሃን እና ኖላዊ በሚል ስያሜ ይታወቃሉ፡፡ በዚህም ወቅት ስለ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር መምጣት መወለድ ነቢያት የተናገሩት ትንቢት በስፋት ይነገርበታል፡፡

ነቢያት ጌታ ይወርዳል ይወለዳል ብለው በኦሪተ ሙሴ በነቢያትና በመዝሙራት መጻሕፍት ላይ አስቀድመው ትንቢት እንደተናገሩ የምሕረት አምላክ ጌታችንም ለአዳም ቃል የገባውን ሊፈጽም ሥጋ ማርያምን ለብሶ ከነበረብን ዕዳ በደል ሊያነጻን አምላክ ወሰብእ ሆነ፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህን በማሰብ ከልደተ አብርሀም እስከ ልደተ ዳዊት ባለው ትውልድ ውስጥ ስለ ክርስቶስ ሰው መሆን የተሰበከውን በወንጌሉ፣ በምስባኩና በመዝሙሩ ትሰብከዋለች፡፡

ስብከት (ከታኀሣሥ ፯ እስከ ታኅሣሥ ፲፫)

በስብከት ሰንበት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሙሴ በሕግ ነቢያትም በትንቢት እንደጻፉለት የሚናገረው ወንጌል ይነበባል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም ‹‹ፈኑ እዴከ እምአርያም አድኅነኒ ወባልሃኒ እማይ ብዙኅ፤ እጅህን ከአርያም ላክ ከብዙ ውኃም አድነኝም›› ብሏል፡፡ ዳግመኛም ከዓበይት ነቢያት አንዱ የሆነው ኢሳይያስም ‹‹ሰማዮችን ቀደህ ምነው ብትወርድ፤ ተራሮችም ምነው ቢናወጡ›› ብሎ ስለ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት መውረድ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መወለድ የተናረውን ትንቢት ቤተ ክርስቲያን ትሰብካለች፡፡ ቅዱስ ያሬድም በመዝሙሩ ከዓለም በፊት የነበረውንና መድኃኒት የሆነውን ወልድን እንሰብካለን በማለቱ ወቅቱ ስብከት ተብሏል፡፡ (መዝ. ፻፵፫፥፯፣ ኢሳ. ፷፬፥፩፣ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

ብርሃን (ከታኅሣሥ ፲፬ እስከ ታኅሣሥ ፳)

የዘመነ ስብከት ሁለተኛው ሰንበት ብርሃን ይባላል፡፡ ይህም ነቢያት የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል ብለው ስለመስበካቸው እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለማስተማራቸው የሚታሰብበት ሲሆን በዚሁ ኢየሱስ ክርስቶስ አማናዊ ብርሃን መሆኑ ይሰበክበታል፤ ይዘመርበታል፡፡

በዘመነ ብሉይ መከራ ሥጋ መከራ ነፍስ የጸናበት የሰው ልጅ ብርሃን ከሆነው አምላክ ጋር የተራራቀበት በመሆኑ ነቢያት ያንን ጊዜ የጨለማ ወቅት ብለው በመግለጽ የነፍሳችን ብርሃን ይወለዳል፤ እውነተኛ ብርሃን ይመጣል ብለው ስለመስበካቸው የሚታሰብበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት ከልደተ ዳዊት እስከ ፍልሰተ ባቢሎን የነበረው ፲፬ ትውልድ ይታሰብበታል፡፡
ልበ አምላክ ዳዊት በመዝሙሩ አምላክ ወልደ አምላክ ብርሃን ስለመሆኑ ‹‹ብርሃንህን እና ጽድቅህን ላክ›› በማለት ይናገራል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ወደ ዓለም መጣ ብሎ እንደመሰከረው እውነተኛ ብርሃን ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃንነት የሚሰበክበት ሰንበት ነው፡፡ (መዝ. ፵፪፥፫)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በመዋዕለ ስብከቱ ‹‹የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ፤ የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ያገኛል እንጂ በጨለማ አይመላለስም›› ብሎ እንዳስተማረው በዚህ ሰንበት ስለ እርሱ ብርሃንነትና ክርስቲያኖችም እርሱን ብርሃናቸው እንዲያደርጉት ይሰበካል፡፡ (ዮሐ. ፰፥፲፪)

እኛም አባቶቻችንን አብነት አድርገን ቅዱስ ኤፍሬም በዕለተ ሠኑይ ውዳሴ ማርያም ላይ እንዳስተማረን ‹‹በዚህ ዓለም ለሚኖሩ ሰዎች ሁሉ የምታበራ እውነተኛ ብርሃን ስለ ሰው ፍቅር ወደ ዓለም የመጣህ ፍጥረት ሁሉ በመምጣትህ ደስ አለው፡፡ አዳምን ከስሕተቱ አድነኸዋልና፡፡ ሔዋንንም ከሞት ፃዕረኝነት ነጻ አድርጎኦታልና፡፡ የምንወለድበትን መንፈስ ሰጠኸን፡፡ ከመላዕክት ጋርም አመሰገንህ›› በማለት የሕይወታችን ብርሃን የሆነውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እናመሰግናለን፤ ሳምንቱንም ብርሃን በማለት እንቀበለዋለን፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘሠኑይ)

ኖላዊ (ከታኅሣሥ ፳፩ እስከ ታኅሣሥ ፳፰)

የዘመነ ስብከት ሦስተኛው ሰንበት ኖላዊ ይባላል፡፡ ኖላዊ ማለት እረኛ ወይም ጠባቂ ማለት ነው፤ በዚህ ዕለት ነቢያት የእግዚአብሔር ልጅ እውነተኛ ጠባቂ መሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እያሰበች የምትዘምርበት እና የምትቀድስበት ዕለት ነው፡፡

ነቢያት ራሳቸውን እና ሕዝበ እስራኤልን ብሎም ዓለምን እረኛቸው እንደተዋቸው በጎች በመቁጠር ስለእውነተኛው እረኛ መምጣት ትንቢት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሰንበት ከፍልሰተ ባቢሎን እስከ ልደተ ሰንበት ድረስ ያለው ዐሥራ አራት ትውልድ የነበረው ይታሰባል፡፡ በዚህ ሰንበት ቤተ ክርስቲያናችን እረኛ የሌለው በግ፣ ተኩላ፣ ነጣቂ እንዲበረታበት በበደሉ ምክንያት ከትጉህ እረኛ የተለየው የሰው ልጅም ሰብሳቢና የሚያሰማራ ጠባቂ እንዲኖረው ነቢያት ‹‹ዮሴፍን እንደ መንጋ የምትመራ፥ የእስራኤል ጠባቂ ሆይ አድምጥ፤ በኪሩቤል ላይ የምትቀመጥ፥ ተገለጥ›› (መዝ ፸፱፥፩) በማለት ይማጸኑ እንደነበር ታስተምራለች፡፡

ቸር ጠባቂ ጌታችንም የትንቢቱ ፍጻሜ ሲደርስ ‹‹መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ መልካም እረኛ ነፍሱን ስለበጎቹ ይሰጣል›› በማለት እውነተኛ አረኛ እርሱ መሆኑን መልስ ተናግሯል፡፡ (ዮሐ. ፲፥፲፩)

በመጨረሻም ጾሙን ጨርሰን የአምላክን መወለድ በማሰብ የምናከብረው በዓለ ልደት ወይም በተለምዶ ገና የምንለው በዓል እናከብራለን፡፡ ትክክለኛ ስያሜውም ጌና ነው፤ ጌና የክርስቶስ ልደት በዓል መሆኑን መጽሐፈ ስንክሳር ይጠቅሳል፡፡ (ስንክሳር ታኅሣሥ ፳፱)

አምላካችን እግዚአብሔር ጾሙን በሰላም አስጨርሶ ለበዓለ ልደቱ ያደርሰን ዘንድ ፍቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ዋቢ ጽሑፍ፡- ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ፣ ውዳሴ ማርያም ዘሠኑይ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘታኅሣሥ