በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ -  ማኅበረ ቅዱሳን
  • ቀዳሚ ገጽ
  • ስለ ማኅበሩ
    • ማእከላት
      • ሰሜን አሜሪካ
      • አውሮፓ
      • ሩቅ ምሥራቅ
      • ደቡባዊ አፍሪካ
      • የካናዳ ማእከል
      • አዲስ አበባ ማእከል
        • የወርሃዊ አስተዋጽኦ መሰብሰቢያ
    • ኅትመት እና ሚዲያ
      • ሐመር እና ስምዐ ጽድቅ
      • ማኅበረ ቅዱሳን ቲቪ
      • የማኅበረ ቅዱሳን ዩቲዉብ
      • መጽሔተ ተልዕኮ
      • ማእከለ ሥዕላት
        • ካሜራው ምን ይላል
        • የቅዱሳት ሥዕላት ማኅደር
  • ትምህርቶች
    • የርቀት ትምህርት
    • ስብከት
    • መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች
  • ግቢ ጉባኤ
  • ሌሎች ድረ ገጾች
    • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ ልዩ ጽ/ቤት ድረ ገጽ
    • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ ገጽ
    • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ድረ ገጽ
  • ቋንቋ
    • አማርኛ
    • ትግርኛ
    • ወላይትኛ
    • ሲዳምኛ
    • Affan Oromo
    • English
  • ያግኙን
  • Click to open the search input field Click to open the search input field Search
  • Menu Menu

“ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን?”

You are here: Home1 / መግለጫ2 / “ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ? ሰላ...

“ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን?”

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በዓለ ልደትን አስመልክቶ ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ያስተላለፉት መልእክት።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ!

በፍጹም ፍቅሩ እኛን ወደ ሰላም ለማምጣት በእኛ ሰውነት በዚህ ዓለም የተወለደው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በደኅና አደረሳችሁ!

“ትእምርተ ሰላምነ ወልድ ተወልደ ለነ፤ የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነው ወልድ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ተወለደልን” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

ዓለም ሁሉ በተለይም የክርስቲያኑ ዓለም በትክክል እንደሚያውቀው ቅዱስ መጽሐፍ በሰዎች የቋንቋ ዘይቤ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ርእዮት ቋንቋ የመልእክት ማስተላለፊያና መግባቢ መሳሪያ እንደሆነ ይታወቃል፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ መልእክቱን በዚህ መንገድ ለሰዎች ሲያስተላል ኖሮአል፤ የሚያስተላልፈውም መልእክት እንዲሁ ተሰምቶ እንዲቀር ሳይሆን እንዲታወቅ፣ እንዲታመን እንዲተገበርና ሰዎች እንዲጠቀሙበት ነው፤ ከሚፈለገው ጥቅም ለመድረስም ሰዎች መልእክቱን በሚገባ መረዳት የግድ ይሆናል፤ ሰዎች እንዲረዱት ደግሞ በቋንቋቸውና በባህላቸው ዘይቤ ሊነገራቸው ይገባል፡፡

በመሆኑም እግዚአብሔር ቃሉን በሰዎች ቋንቋ ባህላዊ ዘይቤ መልእክቱን ለዓለም ሲያስተላልፍ ኖሮአል ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ የእግዚአብሔርን ቃል በሰው ቋንቋ ዘይቤ ታስተምራለች፤ ከዚህ አንጻር በሰው ልማዳዊ የዘይቤ ቋንቋ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የሰላም ሰንደቅ ዓላማ” የሚል ቅፅል ተሰጥቶታል፤ ምክንያቱም ንጉሥም ወታደርም ተራው ሕዝብም የሀገሩ ነጻነትና ክብር፣ አንድነትና ሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ተከትሎ ሥራ ይሠራል፤ ክብሩንም ይገልፃልና ነው፤ ተከተል አለቃህን ተመልከት ዓላማህን የሚለው ብሂልም ይህንን ያንጸባርቃል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

ምእመናንና ምእመናት!

ጌታችን በመድኅንነቱ የሁላችን የሰላም ሰንደቅ ዓላማ በመሆኑ መምህራችን ቅዱስ ያሬድ የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነ ልጅ ተወለደልን ብሎ ይገልጸዋል፤ ጌታችን በዛሬው ዕለት በቤተ ልሔም ሰውነታችንን ሰውነት አድርጎ መወለዱ ራሱ የሰላም ማሳያ ምልክት ነው፤ ምክንያቱም ሳይወደን አይቀርበንም፤ አይዋሐደንምና ነው፤ በልደቱ ዕለት “ለዕጓለ እመሕያው ሠምሮ የሰው ልጅን ወደደው” ተብሎ በቅዱሳን መላእክት የተዘመረበትም ምክንያት ይኸው ነው፤

እንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልጽ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነው፡ በዚህ ዓለም የኖረውም ከሚያሳድዱት፣ ከሚከሱት፣ ስሙን ከሚያጠፉና ሊገዱሉት ከሚከጅሉ ጋር እንጂ ከወዳጆቹ ጋር ብቻ አልነበረም፤ እርሱ ግን ሁሉንም በፍቅር ይቀበል ነበረ፤ ይፈውስና ያድን ነበረ፤ ያስተምርም ነበረ፤ ለሁሉም ሥርየተ ኃጢአትን ሰጠ፤ ለጠላቶቹም ጸለየ፤ ጌታችን በዚህ ሁሉ ለእኛ አርእያና የተግባር መምህር በመሆኑ የሰላም ሰንደቅ ዓላማችን ነው፡፡

ምእመናንና ምእመናት!

ዓለም በጌታችን ዕለተ ልደት የተዘመረውን ሰማያዊውን የሰላም መዝሙር መዘመር ከጀመረች እነሆ ዛሬ ድፍን ሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመት ሆነ፤ የሰላሙ መዝሙር ዛሬም በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ይዘመራል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም ሰላም ሰፍኖ እየታየ አይደለም፤ ይህ ለምን ሆነ ቢባል ደምበኛ መልስ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔርን አለማመንና አለመፍራት ያመጣው ችግር ነው የሚል ነው፤ ምክንያቱም ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለ ፍትሕ ይጐድላል፤ ፍትሕ ከጐደለ ብሶት ይፈጠራል፤ ብሶት ካለ ሰላም ሊኖር አይችልም።

በሁሉም የዓለማችን ክፍል ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚብሔር እየተዘነጋ በመሄዱ ቀውሱ ተባብሶ ይታያል፤ የሰው ልጅ ኑሮ በየትም ይሁን በየት በስጋት የተሞላ ሆኖአል፤ የሚወራው ሁሉ ስለ ግጭት ስለ አየር ብክለት ስለ ረኃብና እልቂት ሆኖአል፤ ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል፤ የዝቅተኛው ማኅበረሰብ ሰብአዊ መብት ተዘንግቶአል፣ ከዚህ አኳያ ዓለም በዚህ እስከ ቀጠለች ድረስ ሰላም የማግኘቷ ዕድል በጣም አጠራጣሪ ነው፤ የክርስቶስ ልደት ያስተማረን ግን እንደዚህ አልነበረም፡፡

ጌታችን የተወለደው በተዋበና ምቹ በሆነ የሀብታም ቤት ሳይሆን በከብቶች በረት ነበረ፤ የተገለጠውም ለባለ ሥልጣኖች ሳይሆን ዝቅተኞች ለሚባሉ እረኞች ነበረ፤ ልዑላኑ ሰማያውያንና ትሑታኑ ምድራውያን በአንድነት አገናኝቶ ስለ ሰላም በጋራ እንዲዘምሩ አደረገ፤ አሳዳጅ ሳይሆን ተሳዳጅ ሆኖ በግብጽ አገር በመንከራተት አደገ፤ ይህን ሁሉ ያደረገው እኛ እርሱን እያየን እንደ ሰንደቅ ዓላማ እንድንከተለው ነበር፤ ጌታችን ከባለ ሥልጣናቱና ከባለ ሀብቶቹ ይልቅ በድሆቹ ደረጃ የተወለደው ለድሆቹና ለዝቅተኞቹ ትኩረት እንድንሰጥ ለማስተማር ነው፤ የእኛ ድርጊት ግን ግልባጩ ሆኖ እየተስተዋለ ነው፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ክርስቲያን ነኝ ብሎ፤ በስመ እግዚአብሔር ተሰይሞ፤ መስቀልን በአንገቱ ተሸክሞ የእርሱ መሰል በሆነው ወይም መስቀል በተሸከመው ወንድሙ እና እኅቱ እንዲሁም በመሰል ፍጡር ላይ ያለ ርኅራኄ ሲጨክን መታየቱ ነው፤ እንዲህ እየሆነ እንዴት ሰላም ይምጣ? እግዚአብሔርስ እንዴት በረከቱ ይሰጣል? ይህ እጅግ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!

ምእመናንና ምእመናት!

እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ ዓይነቱ የሃይማኖትና የሞራል ዝቅጠት በአስቸኳይ መውጣት አለብን፤ ጠቡ፤ መለያየቱ፣ መጨካከኑ፤ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተናዊ ውድመት ብቻ ነው፤ ያስገኘልን ትርፍ ይህ መሆኑ እያወቅን በዚሁ ልንቀጥል አይገባም። ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን?

ሦስት ሺሕ ዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦች እንዴት ችግራቸውን በጠባይና በብልሐት ማስወገድ አቃታቸው? ይህ ከቶ ሊሆን አይገባም፤ ሁላችንም ሰክን ብለን እናስብ፤ ለሁሉም የማሰቢያና የመመካከሪያ ጊዜ ፈጥረን ችግሩን በስፍሐ አእምሮ እንፍታው፡ ችግርን በምክክርና በይቅርታ መፍታት አማራጭ የሌለው ጥበብ ነው፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ምሁራንና ልኂቃን በዚህ ተግተን ልንሰራ ይገባል፤ መንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ የበኩላቸውን ድጋፍ ያድርጉ፤ በዚህም ሰላማችንን እንመልስ፡፡

በመጨረሻም

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በተከሠተው የድርቅና የሰው ሰራሽ ምክንያት በችግር ላይ የወደቁ ወገኖች በርካታ ናቸው፤ በመሆኑም የወገን ደራሽ ወገን ነውና ሁሉም ካለው ብቻ ሳይሆን የቀን ቍርሱን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲለግስና በመተጋገዝ ረኃቡን እንድንከላከለው ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን!

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር! አሜን!!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም
ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ

በፌስቡክ የትስስር ገጽ ያግኙን

Search Search

አዳዲስ ጽሑፎች

  • ዘመነ ክረምት
  • “መሠረተ ሃይማኖት” የተባለ የልጆች መጽሐፍ የፊታችን እሑድ እንደሚመረቅ የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ገለጸ
  • ደብረ ማርቆስ ማእከል 252 የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን አስመረቀ።
  • በዘንድሮው ዓመት ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ካዘጋጃቸው 18 ሜዳሊያ ዋንጫውን ጨምሮ 14ቱ በግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የተወሰዱ መሆናቸው ተገለጸ
  • የግቢ ጉባኤ አባል (CGPA) 4.00 ነጥብ በማምጣት የዓመቱ የዋንጫ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሆነ።
  • ማኅበረ ቅዱሳን እያስገነባ የሚገኘውን የልህቀት ማእከል የመጀመሪያ ዙር የፊኒሺንግ ሥራ ለማከናወን የገንዘብና የዐይነት ድጋፍ ማሰባሰብ መጀመሩን አስታወቀ
  • እንኳን ለእናታችን ለእመቤታችን ለቅድስተ ቅዱሳን ለድንግል ማርያም ሰኔ ጐልጐታና ሕንጸተ ቤተ ክርስቲያን (ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያኗ ለታነጸበት) ክብረ በዓል በሰላምና በጤና አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
  • የእንጅባራ ማእከል ላለፉት 4 ዓመታት ሲያስተምራቸው የቆዩ 200 ተማሪዎችን  አስመረቀ
  • ማኅበረ ቅዱሳን በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች  አስቸኳይ የምግብ ግብዓቶች ድጋፍ አደረገ
  • የአዲስ አበባ ማእከል 500 የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች መመረቃቸውን ገለጸ።
  • የወላይታ ሶዶ ማእከል ለ8 ወራት ያስተማራቸውን 45 የበገና ዘማርያንን አስመረቀ።
  •    ‘’ከመላእክት አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ።’’ (ት.ዳን. ፲ ፥፱)
  • በዓለ ደብረ ምጥማቅ
  • የቅዱስ ያሬድን ትሩፋት በዓለም የዕውቀት መድረክ ላይ ለማስተዋወቅ የምርምር ማእከላትን የማቋቋምና የዲጂታል ቅርስ አያያዝ ዘዴዎችን የመተግበር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
  • አውስትራሊያ ማእከል ዝክረ ቅዱስ ያሬድ መርሐ ግብር አካሄደ

የጽሑፎች ማውጫ – በወራት

© Mahibere Kidusan - All Rights Reserved. Website by MK-IT
  • Link to Facebook
Link to: ወልድ ተወለደልን! Link to: ወልድ ተወለደልን! ወልድ ተወለደልን! Link to: ቁጣና መዘዙ Link to: ቁጣና መዘዙ ቁጣና መዘዙ
Scroll to top