ወልድ ተወለደልን! 

ታኅሣሥ ፳፮፤፳፻፲፮ ዓመተ ምሕረት

በኃጢአት ባርነት ስኖር ታስሬ

በችግር በመከራ በጭንቅ ተወጥሬ

ለ፶፻፭፻ ዘመናት ከአምላኬ ያራቀኝ

ጥንተ ጠላቴ ዲያብሎስ ሲያውከኝ

ምድርም አሜኬላ አብቅላ ሐሣር ስታበላኝ

ወደ ፈጣሪዬ ጮኹ ፈጥሮ ለማይተወኝ

እርሱም አለኝ …

“ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ!

እኔም “አቤቱ አምላኬ በተስፋ እጠብቃለሁ!

ምሕረትህ የበዛ ሥራህም ድንቅ ነው”  አልሁ!

ብዙ ሺህ ዘመናትንም ታግሼ ኖርኩ

ልፈታ ከእስር ቃሉን ተስፋ አደረኩ

ጊዜው ደረሰ እና አምላክ ሰው ሊሆን

ተወለደ ከማርያም ከእመቤታችን!

ኧረ ይህች ቀን ምንኛ ድንቅ ናት!

በዓይን የማይታየው የተገለጠባት

የማይዳሰሰው በአካል የተገኘባት

አንድ አምላክ ፈጣሪ የተወለደባት

እርሱ ነው ተስፋችን የዓለም መድኃኒት

የሆነው ቤዛ ለሁሉ ፍጥረት!

ወልድ ተወለደልን መድኃኒዓለም

በከብቶች በረት በቤተ ልሔም!