መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

  • ብፁዕ አቡነ ያሬድ

የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃምና የአርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኃላፊ፤

  • ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ

የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሲዳማ፣ የጌድኦ፣ የአማሮና ጉርጂ  አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤

  • ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
  • በአጠቃላይ በዚህ ታላቅ ቅዱስ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፦

በዓለም ውስጥ የሰላምና የአንድነት ማእከል ሆና ታገለግል ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን በክቡር ደሙ ቀድሶ የሰጠን ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሽህ ዐሥራ ዐራት ዓ.ም የረክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ አደረሳችሁ!!!

‹‹ወሩፁ ኀበ ሰላም ምስለ ኵሉ፤ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም  ሩጡ›› (ዕብ.፲፪፥፲፬)፤

ሁላችንም እንደ ምንገነዘበው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም መመሥረት ዋና ዓላማ ሕዝብንና አሕዛብን በክርስቶስ ትምህርተ ሰላም አገናኝታ፣ አቀራርባና አንድ አድርጋ በሃይማኖት ለእግዚአብሔር መንግሥት ንጹሕ ወገንን ማቅረብ ነው፡፡ ለዚህ ለተቀደሰ መለኮታዊ ዓላማ እውን መሆን ሲባል ከራሱ ከባለቤቱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አንሥቶ  ብዙ ቅዱሳን አበው የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ክቡር ደም አማካኝነት ድል በድል እየተሻገረችና እየተራመደች እስካሁን ደርሳለች፤ ዛሬ በክብር የተቀመጥንበት ወንበርም የዚህ ደም ውጤት እንደ ሆነ አሳምረን እናውቃለን፡፡

በየጊዜው በኃላፊነት የተቀመጡ ቅዱሳን አበው መከራ መስቀሉን ፈርተውና ተሰቅቀው ቢያፈገፍጉ ኖሮ ይህ እኛ ዛሬ የተሰየምንበት ክብረ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚገኝ አልነበረም፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጉዞ አንድ ተብሎ ሲጀመር በፍኖተ መስቀል ስለሆነ  ፍኖተ መስቀሉ ተቋርጦ አያውቅም፤ ለወደፊትም ይቋረጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በዚህ ፍኖት የሚጓዙ ቅዱሳንም አይታጡም ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፤ ፍኖተ መስቀል በልዩ ልዩ ዕንቅፋቶችና መሰናክሎች የተሞላ፣ አባጣ ጐርባጣ፣ ወጣ ገባ ቢሆንም መጨረሻው ስኬትና ድል ነውና ለፍጹም ዘለዓለማዊ ሰላምና አንድነት ሲባል የሚጓዙበት መንገድ ነው፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡-

የዘመናችን ፍኖተ መስቀልም መሰናክሉንና ዕንቅፋቱን በሀገራችን፣ በቤተ ክርስቲያናችንና በምእመናን ልጆቻችን  ጫናው እያበረታ እንደ ሆነ መጠራጠር ያለብን አይመስለንም፡፡

የምእመናን፣ የካህናትና የአብያተ ክርስቲያናት ጉዳት አሁንም ገዝፎና ሰፍቶ እየቀጠለ ነው፡፡ ስጋትና ጭንቀት፣ አለመተማመንና ቀቢፀ ተስፋ ተንሰራፍቶአል፤ አብሮ ተከባብሮ ከመኖር ይልቅ  ሌላውን ጥሎ ኮርቻ ላይ ለመውጣት የሚደረገው እሽቅድምድም በሰፊው እየተሠራበት እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡ይህንን አደገኛ አካሄድ ለማሳካት ሲባል የሚደረገው ያልነበረ ልማድም ቤተ ክርስቲያናችንን እየተጋፋ ነው፤ ምእመናንንም እያሳዘነ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በሃይማኖት ነጻነት መከበር ችግር ባይኖርባትም በአጉል ፉክክር የሚደረጉ፣ ካሁን በፊት ያልነበሩ የሥርዓተ ሃይማኖታችን ዐደባባዮችን ለመቀራመት የሚደረገው  አካሄድ  ተገቢ ነው አንልም፡፡ ይህ ሁኔታ ለሁሉም በሚበጅና ሁሉም በየራሱ የሚስተናገድበት የየራሱ የሆነ ክቡር ስፍራ አግኝቶ ሊስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረ ጥሩ ሊሆን አይችልም፤ ችግሩም በግልፅ እየታየ ስለሆነ የሚመለከተው አካል ፈጣን መፍትሔ ሊያበጅበት ይገባል፡፡

ከታሪክ፣ ከነባር ባህል ጥበቃ፣ ከሃይማኖት ክብርና መብት ባሻገር በአንድ ስፍራ ሁለት የተለያዩ ሃይማኖታውያን እንዲገለገሉ የሚደረግ ከሆነ ሁለት የተለያየ እምነት ያላቸው ሃይማኖታውያን በዓላቸው በአንድ ቀን ቢውል ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡

ሃይማኖታውያንም ለራሳቸው ሲሉ ይህንን ችግር ራሳቸው የመፍትሔ አካል መሆን የኖርባቸዋል፤ የሰላም ጠበቆች መሆናቸውንም  በዚህ ሊያሳዩ ይገባል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!!

የሰላም አስፈላጊነት በየቀኑ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዷ ሰኮንድ ለሃይማኖታችን መጠበቅና ለሕዝባችን ደኅንነት መረጋገጥ  ትልቅ  ዋጋ  አላት፡፡

ሰላም በደፈረሰ ቍጥር  የምናጣው  ብዙ ነው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው ሁሉ ከማንም ተግባር በፊት ሰላምን መጠበቅ ላይ ቢሠራና ሰላምን ገንዘብ አድርጎ ቢመላለስ በሁሉም ነገር ስኬታማ መሆን ይችላል፡፡

በተለይም ሕዝብን በኃላፊነት በመምራት የምንገኘው ዓለማውያንም ሆን ሃይማኖታውያን  ከማናቸውም ተግባር በፊት ሰላምን ማረጋገጥ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፤ ምክንያቱም ሃይማኖታዊም ሆነ ሀገራዊ ጥቅም ያለ ሰላም በምንም ተአምር ሊመጣ አይችልምና ነው፡፡

ሰላም ከሞላ ጐደል ፍጥረት ሁሉ  የሚፈልጋት ውድ ነገር ብትሆንም መገኛዋን በተመለከተ ግን ብዙ አናውቀውም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰላም በጕልበት አትገኝም፤ በሀብትም አትገኝም፤ በሥልጣንም ሆነ በነጠላ ዕውቀትም አትገኝም፡፡

እውነተኛዋና ዘላቂነት ያላት ሰላም የምትገኘው ‹‹ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ›› በሚለው ትምህርተ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ሰው ሌላውን ቸል ብሎ ራሱን ሲያስቀድም የሰላም ፀር ይሆናል፤ ራሱን ሳይሆን ሌላውን ሲያስቀድም ግን የሰላም ጠበቃ ይሆናል፡፡

በሀገራችን ተከሥቶ ሕዝባችንን እያንገላታ የሚታየው ክሥተት ይህ ራስን ማብለጥ ሌላውን ማንጓጠጥ ነው፤ ይህንን በአግባቡ አርመን አንተ ትበልጣለህ፤ አንተ ትሻላለህ፤ ወደ ሚል  ትሕትና ካልተመለስንና ነገሮችን በፍቅር ለመለወጥ ካልጣርን የሕዝባችንን መከራ ማሳጠር አንችልም፡፡ ‹‹ዕርቅ ደም ያደርቅ›› እንዲሉ የዕርቅን ጥቅም በመቀበል ወደ ተሻለ ነገር መራመድ ጊዜው የሚጠይቀን ተግባር ነው፡፡ ይህንን በማስተማርና በመምከር ሕዝቡን ወደ ዕርቅና ወደ ይቅርታ ማምጣት ደግሞ የኛው የሃይማኖት አባቶች ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፤ ምክንያቱም ‹‹ወደ ሰላም ሩጡ›› ተብለናልና!