በዓለ ቅዱስ ያሬድ

ግንቦት ፲ ቀን፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

ኢትዮጵያዊው ሊቅ የዜማ ደራሲ ቅዱስ ያሬድ ወደ ብሔረ ሕያዋን የተሠወረበት ቀን ግንቦት ፲፩ የከበረ በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታከብረዋለች። ይህ ቅዱስ ከአባ ጌዴዎን ዘመዶች ወገን ነው። እርሱም በኢትዮጵያ ሀገር ከታነጹት አብያተ ክርስቲያናት ለምትቀድም ከአክሱም ካህናት ውስጥ ነው፡፡ እርሷም አስቀድሞ የክብር ባለቤት የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖት በውስጥዋ የተከበበና አምላክን በወለደች በእመቤታችን በከበረች ድንግል ማርያም ስም የከበረች ናት::

ይህም አባት አባ ጌዴዎን ትምህርትን ሊያስተምረው በጀመረ ግዜ መቀበልም ማጥናትም ተሳነው፡፡ ከዕለታት አንድ ቀንም መምህሩም በእርሱ ተበሳጭቶ መትቶ ባሳመመውም ጊዜ ከአባቶቹ ቤት ሸሽቶ ጫካ ገባ፤ ከአንዲትም ዛፍ አጠገብ ሲደርሰ ከዚያ ዐረፈ፤ ወደ ዛፉ ላይም ትል ሲወጣ አየ፤ እርሱም ከዛፉ ጫፍ ላይ ያለን ፍሬ መብላት እየጣረ ነበር። ወደ ዛፊቱም እኩሌታ ደርሶ ወደ ምድር ይወድቃል፤ ሁለተኛም ተመልሶ ወደ ላይ ይወጣል፤ መጀመርያ ወደ ደረሰበት ሲደርስ ይወድቃል፤ ሲወጣ ሲወድቅ ብዙ ጊዜ ያደርጋል። ከዚህም በኋላ በብዙ ጭንቅ ከዛፉ ላይ ወጣ፤ ከዚያም ፍሬዋን በላ፡፡

ቅዱስ ያሬድም የትሉን ትጋት ባየ ጊዜ ወደ መምህሩ ጌዲዮን ተመልሶ ‹‹አባቴ ሆይ ይቅርታ አድርግልኝና እንደ ወደድክ አድረገኝ›› አለው፤መምህሩም ተበለው፤ አብዝቶ በማልቀስ እግዚአብሔርን ለመነ፤ አምላክም ጸሎቱን ሰምቶ ልቡናውን አበራለት፤ በአጭር ጊዜም የብሉይና የሐዲስ መጻሕፍትን ተማረ፤ ከዚህም በኋላ ዲቂና ተሾመ፡፡

በዚያም ወራት በትሑት እንጂ እንደዛሬ በከፍተኛ ቃል የመዝሙር ማኅሌት የለም ነበር፤ እግዚአብሔርም መታሰቢያ ሊያቆምለት በወደደ ጊዜ ከኤዶም ገነት ሦስት አዕዋፍን ላከለት፤ እነርሱም በሰው አንደበት ተናግረውት ወደ እየሩሳሌም ሰማያዊት ከእነሱ ጋር አወጡት፤ በዚያም ፳፬ (ሃያ ዐራቱ)  ካህናተ ሰማይ የሚያመሰግኑበትን ማኅሌት ተማረ::

ወደ አነዋወሩ ወደ ምድርም በተመለሰ ጊዜ በአክሱም ዳር ወደ ከበረች ቤተ ክርስቲያን በሦስት  ሰዓት ገባ፤ በታላቅም ቃል ‹‹ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ የጽዮንም ደገኛዋ ሰማይን ፈጠረ፤ ዳግመኛም እንዴት እንደሚሠራት የድንኳንን አሠራር ለሙሴ አሳየው አስተማረው›› አለ:: ይህቺንም ምስጋና አርያምብሎ ጠራት፤ የቃሉንም ድምጽ በሰሙ ጊዜ ንጉሡም፣ ንግሥቲቱም፣ ጳጳሱም፣ ከካህናቱ ሁሉ ጋር የመንግሥት ታላላቆችና ሕዝቡ ሁሉ ወደ እርሱ ሮጡ፤ ሲሰሙትም ዋሉ፡፡

ከዚህም በኋላ ከዓመት እስከ ዓመት በየክፍለ ዘመኑ በክረምትና በበጋ፣ በመጸውና በጸደይ በአጽዋማትና በበዓላት፣ በሰንበታትም እንዲሁም በመላእክት በዓል በነቢያትና በሐዋርያት፣ በጻድቃንና በሰማዕታት በደናግልም በዓል የሚሆን አድርጎ በሦስቱ ዜማው ሠራ፤ ይኸውም ግዕዝ፣ ዕዝል፣ አራራይ ነው:: የሰው ንግግር የአዕዋፍ የእንሳትና የአራዊት ጩኸት ከእነዚህ ከሦስቱ ዜማ አይወጣም፡፡

በአንዲት ዕለትም ቅዱስ ያሬድ ከንጉሥ ገብረ መስቀል እግር በታች ቆሞ ሲዘምር ንጉሡም የያሬድን ድምጽ እያዳመጠ ልቡ ተመስጦ የብረት ዘንጉን ወይም መቋምያውን በያሬድ እግር ላይ ተከለው፤ ከእርሱም ደምና ውኃ ፈሰሰ፤ ያሬድም መኅሌቱን እስከሚፈጽም አልተሰማውም ነበር፤ ንጉሡም አይቶ ደነገጠ፤ በትሩንም ከእግሩ ላይ ነቀለ፤ ‹‹ስለፈሰሰው የደምህ ዋጋ የፈለከውን ለምነኝ›› ብሎ ለያሬድ ተናገረው፤ ያሬድም ‹‹ላትከለክለኝ ማልልኝ›› አለው፤ ንጉሡም በማለለት ጊዜ ‹‹ወደ ገዳም ሄጄ እመነኩስ ዘንድ አሰናብተኝ›› አለው፤ ንጉሡም ሰምቶ ከመኳንንቱ ጋር እጅግ አዘነ፤ ተከዘም፤ እንዳይከለክለውም መሐላውን አሰበ፤ እያዘነም አሰናበተው፡፡

ከዚህም በኋላም ቅዱስ ያሬድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ በታቦተ ጽዮን ፊት ቆሞ ‹‹ፈጽሞ የከበርሽ እና የተመሰገንሽ ከፍ ከፍ ያልሽ የብርሃን መውጫ የሕይወት ማዕረግ የሆንሽ›› የሚለውን ምስጋና (አንቀጸ ብርሃን) እስከመጨረሻ በተናገረ ጊዜ ክንድ ያህል ከምድር ከፍ ከፍ አለ::

ከዚህ በኋላ ወደ ሰሜን ሀገር ሄዶ፣ በጾም በጸሎት ተወስኖ፣ ሥጋውን እጅግ እያደከመ ኖሮ ገድሉን በዚያ ፈጸመ፤ እግዚአብሔር ስሙን ለሚጠራ መታሰቢያውን ለሚያደርግ ቃል ኪዳን ሰጠው፤

አምላካችን እግዚአብሔር ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ የአባታችን የአምሳለ ሱራፌል የሊቁ ማኅሌታይ የቅዱስ ያሬድ ጸሎቱ በረከቱ ረድኤቱ በኛ ላይ ይደርብን፤ አሜን!

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት