ቤተ ክርስቲያን

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት አላችሁ? የዓመቱ የማጠቃለያ ፈተና እንዴት ነበር? በየትምህርት ወቅት መምህራን ሲያስተምሯችሁ የነበረውን ዕውቀት በማስተዋል ሲከታተል የነበረ፣ ያልገባውን ጠይቆ የተረዳና በደንብ ያጠና ተማሪ በጥሩ ውጤተ ከክፍል ክፍል ይሸጋገራል፤ መቼም እናንተ ጎበዝ እንደሆናችሁ ተስፋችን እሙን ነው፤ መልካም!

ልጆች! ባለፈው ጊዜ ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትርጉም እንዲሁም የመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን በማን፣ መቼና የት ቦታ እንደታነጸች ተመልክተናል፤ ዛሬ ደግሞ በያዝነው ቀጠሮ መሠረት በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላሉት ሦስት ክፍላት ማለትም ስለቅኔ ማኅሌት፣ ቅድስት፣ መቅደስ አገልግሎትና ምሥጢራዊ ትርጉም እንማማራለን፤ መልካም ቆይታ!

ምስካዬ ኅዙናን መድኃኒዓለም ገዳም

ምስካዬ ኀዙናን መድኃኒዓለም በታሪካዊ ሂደቱና በአገልግሎቱ የተለያዩ ሥራዎችን በመጀመር ለሌሎች ቤተ ክርስቲያናት አርአያ የሆነ ገዳም ነው፡፡

ግሸን ማርያም

ወሎ፣ አምባሰል አውራጃ ውስጥ በደብር በሐይቅና በመቅደላ፣ በደላንታ፣ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ የምትገኝ አንድ መግቢያ በር ብቻ ያላት ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ትገኛለች፡፡ በበርዋ ራስ ላይም የመስቀል ምልክት ሲኖር አጥርዋን አልፈን ከገባን በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡

ደብርዋም በመጀመሪያ ደብረ እግዚአብሔር በሚለው ስያሜ ትታወቅ ነበር፡፡ በንጉሥ ቅዱስ ላሊበላ እጅ ከቋጥኝ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ቤተ መቅደስ በእግዚአብሔር አብ ስም ስለነበረ ደብረ እግዚአብሔር ተብሎ ተጠራ፡፡ ከዚያም የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ደብረ ነጎድጓድ ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት ስለሆነች ከደብረ እግዚአብሔር ደብረ ነጎድጓድ ተብላለች፡፡ ከዚያም በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዓፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ከደብረ ነጎድጓድ ደብረ ከርቤ ተብላለች፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪም መምህረ እሥራኤል ዘደብረ ከርቤ ትባል ነበር፤ ከደብረ ከርቤም ግሸን ማርያም ተብላለች፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

ቤተ ክርስቲያን ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደሙ ዋጅቶ የመሠረታት፣ በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን በሙሉ መሰብሰቢያችን የተቀደሰች ቤታችን ናት፡፡ ቤተ ክርስቲያን ስንልም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን፣ የክርስቲያን ወገን፣ የምእመናን አንድነት ወይንም ማኅበረ ምእመናን እንዲሁም እያንዳንዱ ምእመናን ማለታችን ነው፡፡…

የሻጮችና የለዋጮች ወንበር የሞላው ቤተ መቅደስ

ጥንቱን ለልማዱ የቤተ መቅደስ መሠራት ምክንያቱ ሰዎችን ለመቀደስ፣ ሕያዊት ነፍስ የተሰጠቸው ሥጋዊ ደማዊ ፍጥረት ሁሉ ጸሎቱን አድርሶ መሥዋዕቱን አቅርቦ ከእግዚአብሔር ምሕረት ሊቀበልበት አልነበረምን? ‹‹ለዘለዓለም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይህን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ ዓይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይኖራሉ›› ብሎ የመረጠው የነገሥታት ንጉሥ የእግዚአብሔር ልዩ ሥፍራ ነው ቤተ መቅደስ፡፡ መቅረዙና ጠረጴዛው የመሥዋዕቱም ኅብስት ነበረበት፤ የወርቁ ማዕጠንት፣ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ጽላት፣ በውስጧም መናን የተሸከመችው መሶበ ወርቅና ክህነት የጸናባት የአሮን በትር እንዲኖሩ ታዝዞ ነበር፡፡  በምድራውያን ሰዎች መካከል እንደ ምሰሶ የሚቆመው ካህን ገብቶ የሚያጥንበት ይህ ቤተ መቅደስ ምንኛ የከበረ ነው? ለሰዎች ሁሉ ራዕይን አይቶ የሚነግራቸው ባለ ራዕይ ነቢይ የማይታጣበት፣ ሊቀ ካህናቱ የሚደገፈው ያቁም፣ ንጉሡ የሚደገፈው በለዝ የሚባሉት ምሰሶዎች የሚገኙበትም ነው፡፡ ያዕቆብ እንዳለው ይህ ቤተ መቅደስ የሰማይ ደጅ ነው እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ (፩ ነገ. ፱÷፫፣ ዕብ. ፱÷፪፣ ዘፍ. ፳፰÷፲፯)

የቃል ኪዳኑ ታቦት

ነቢዩ ሙሴ ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጸልዮና ጹሞ ዐሥርቱ ቃላት የተጻፈበትን ጽላት ከእግዚአብሔር ከተሰጠው በኋላ የቃል ኪዳኑን ታቦት ‹ታቦተ ጽዮንን› እንደሠራት መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል፡፡ ታቦተ ጽዮን ከማይነቅዝ እንጨት የተሠራችበት ምክንያት የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ንጽሕና ለማመልከት ነው፡፡ በውስጥም በውጪም በጥሩ ወርቅ የተለበጠች መሆኗ ደግሞ የእመቤታችን ድንግል ማርያም ቅድስናዋንና በሁለት ወገን ድንግል የመሆኗ ምሳሌ ነው፡፡

ግሸን ማርያም

ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ቢሆንም ኢትዮጵያ ‹‹ግሸን አምባ›› የገባበት፣ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በጽሑፍ በመዘርዘር የገለጹበትም መስከረም ፳፩ ቀን በመሆኑ በድምቀት ይከበራል…

የጎንደር መካነ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን

 ነሐሴ 1 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

ክፍል ሦስት

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤ እንቅስቃሴ

በጎንደር በአራት ቦታዎች ላይ የትርጓሜ መጻሕፍት ጉባኤ ቤቶች ይገኛሉ፤ ትምህርትም በተጠናከረ ሁኔታ ይሰጥባቸዋል፡፡ ነገር ግን ለቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆኑት የመምህር ኤስድሮስ ወንበር በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ታጥፏል፡፡ ይህንን ገጽታ ለመቀየርና የመምህር ኤስድሮስን ወንበር ወደነበረበት ለመመለስ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ብፁዕ አቡነ እንድርያስ ጉባኤ ቤቶቹን ዳግም ወደነበሩበት ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ለፍጻሜ ሳይበቃ ወደ ደቡብ ጎንደር ተቀይረው ሄዱ፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ ተግባራዊ ባይሆንም በቅርቡ አንድ ውጤት ላይ ለመድረስ ጠንክረው እንደሚሰሩ አስተዳደሩና ሰበካ ጉባኤው ይገልጻሉ፡፡ ወደፊት ሊሰሩ ከታቀዱ ሥራዎች መካከል አንዱ የጉባኤ ቤቱን ጥንት ወደነበረበት መመለስ ይገኝበታል፡፡

ከታቀዱት የልማትና የአገልግሎት ሥራዎች መካከል ቅድሚያ የሚያደርጉት ቤተ ክርስቲያኗ ሙሉ አገልግሎት መስጠት የምትችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት በመሆኑ፤ ካህናቱ የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ በትምህርት ብቃታቸውን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሠራ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ብቃት ያላቸው መምህራንን በማዘጋጀት፤ ከማኅበረ ቅዱሳን ጎንደር ማእከል ጋር በመተባበር በወንጌል ትምህርት በቂ ልምድ እንዲኖራቸው በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡

“በልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ጥላ ዘቅዝቆ መለመን አይቻልም፡፡ ምእመናን ሳይሳቀቁ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው በነፃነት ጸሎት አድርሰው፤ ቡራኬ ተቀብለው እንዲሄዱ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረናል ለማለት እንችላለን፡፡ ምእመናንን በልመና ማሳቀቅ አይገባም፤ አስበውና ደስ ብሏቸው ነው መሥጠት የሚኖርባቸው” በማለት የሰበካ ጉባኤው ምክትል ሰብሳቢ ዲያቆን ሙሉቀን ብርሃኑ ይገልጻሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያኗ አገልገሎት አይቋረጥም፤ ሊቃውንቱም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ጠብቀው ያገለግላሉ፡፡ ለአብነት ተማሪዎች ቤት ተሰጥቷቸው፤ የመብራትና ውኃ ተከፍሎላቸው በመማር ላይ ይገኛሉ፡፡ በእንተ ስማ ለማርያም በሚሰማሩበትም ወቅት ምእመናን ስለሚያውቋቸው ያላቸውን ሰጥተው ይሸኗቸዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኗ ጽ/ቤት በእያንዳንዱ አገልጋይ ካህን ስም ፋይል ከፍቶ የንስሐ ልጆቻቸውን ስም ዝርዝር እንዲያስመዘግቡ ተደርጓል፡፡ እያንዳንዳቸው የንስሐ ልጆቻቸውን በአግባቡ በመያዝና በመምከር፤ ቢያንስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከንስሐ ልጆቻቸው ጋር እንዲገናኙ በማድረግ፤ በየቤታቸው እየተገኙ ጸሎት አድርስው፤ ጠበል ረጭተውና አስተምረው የመመለስ ግዴታ እንዳለባቸው በመረዳት ይህንኑ በተግባር ላይ እያዋሉት ይገኛሉ፡፡ አስተዳደሩም ይከታተላል፡፡ የንስሐ አባቶቻቸው የሚፈለግባቸውን ሓላፊነት ካልተወጡና የሥነ ምግባር ችግር እንዳለባቸው ካረጋገጡ ምእመናን ወደ ጽ/ቤት በመምጣት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ አስተዳደሩም ችግሩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ አንስቶ አስተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡

ምእመናን ሓላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በማድረግ ረገድ ለካህናት ብቻ የተተወ ባለመሆኑ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር መምህራንን በመመደብ፤ ትምህርተ ወንጌል የሚያገኙበትን ሁኔታ በማመቻቸት አንድ ክርስቲያን በክርስትና ሕይወት ውስጥ እስካለ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡ ምእመናን ሓላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታ ነው፡፡ አሥራት በኩራት ከማውጣት አንስቶ ንስሐ በመግባት ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን በመቀበል በሕይወታቸው ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ምእመናን ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው በመጨመር እየፈሩ ነው፡፡

የልማት እቀዶች፡-

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደር የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ በ400 ሺህ ብር የዳቦ መጋገሪያ ማሽን አስገብቷል፤ ሦስት ቋት ያለው ወፍጮና አንድ ማበጠሪያ በመትከል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ ዙሪያ ሰፊ ቦታ ስላለ ባለ አራት ፎቅ ሁለገብ ሕንፃ በመሥራትና በማከራየት ራሷን የምትችልበት ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያኗን በአዲስ መልክ በጥሩ ዲዛይን ለማነጽ በብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡ ለታቦቱ ማረፊያ የሚሆን ባለ አንድ ፎቅ ሕንፃም በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ምእመናን ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል፡፡ የጎንደር መምህራን ኮሌጅ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አዳራሽ ለመገንባት ለቤተ ክርስቲያኗ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ተፈቅዶላቸው ግንባታውን በማጠናቀቅ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡

የጠበሉ ቦታን በማስተካከል ምእመናን ሳይቸገሩ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ በማመቻቸት የግንባታ ሥራው ይከናወናል፡፡

የልደታ ለማርያም የጥምቀተ ባሕር ቦታ ለሙስሊሞች ተሰጥቶ ስለነበር ከፍተኛ ችግር ተከስቶ ቆይቷል፡፡ በተለይም በ2001 ዓ.ም. የተፈጠሩት ግጭቶች አስቸጋሪ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ የችግሩ አሳሳቢነት ቀጥሎም ጥምቀተ ባሕሩ ከሙስሊሞች ተወስዶ ለአንድ ጀርመናዊ ባለ ሀብት ተሰጠ፡፡ ነገር ግን በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ እና በከተማው ወጣቶችና ምእመናን ብርቱ ጥረት ሳይሳከላቸው ቀርቷል፡፡

ቦታው የቤተ ክርስቲያን ሃብት በመሆኑ የልማት ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ በማመን ፕሮፖዛል በማዘጋጀት ለአማራ ክልላዊ መንግሥት ኢንዱስትሪና ከተማ ልማት ቢሮ ቀርቦ ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ጎንደር ከተማ አስተዳደር አስተላልፎት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡

ቦታው 46 ሺህ ካሬ ሜትር የሚገመት ሲሆን፤ የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው ይህን ሥፍራ ለጥምቀተ ባሕርና ለልማት ለማዋል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ በቦታውም የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ቤት፤ ሁለገብ ሕንፃ፤ የአረንጓዴ መናፈሻ፤ የኪነ ጥበብ ማእከል፤ መዋኛ ገንዳ፤ ሁለገብ የመሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎችንም ያቀፈ እንዲሆን ተደርጎ ዲዛይኑን በማዘጋጀት ለከተማ አስተዳደሩ ገብቷል፡፡ የሚመለከተው አካል ያጸድቀዋል ተብሎም ይጠበቃል፡፡  

a gonder tabote 2006 02

የጎንደር መካነ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን

ሐምሌ 16 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

ክፍል ሁለት

ጥምቀት

በጎንደር ጥምቀትን አስመልክቶ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር የሚወርዱበትና የሚመለሱበት ሦስት ዓይነት ሥርዓት ይገኛሉ፡፡ እነዚህም እየተፈጸሙ እስከ ዛሬ ድረስ ደርሰዋል፡፡

a gonder tabote 2006 02በዐፄ ገብረ መስቀል የነበረው ሥርዓት ታቦታት ከመንበራቸው ይወጣሉ፤ ወደ ጥምቀተ ባሕር ወርደው ሕዝቡን ባርከው በእለቱ ተመልሰው ወደ መንበራቸው ይገባሉ፡፡ በንጉሥ ላሊበላ ዘመን ደግሞ ቀድሞ የነበረው ሥርዓት ተቀይሮ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ወንዝ በመውረድ አድረው በመጡበት መንገድ እንዲመለሱ ተደረገ፡፡ ሦስተኛው በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ በዋዜማው ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመውረድ ያድራሉ፡፡ አድረው ወደ መንበራቸው ሲመለሱ ግን ወደ ጥምቀተ ባሕር በወረዱበት ሳይሆን በሌላ መንገድ አገሩንና ሕዝቡን እየባረኩ እንዲመለሱ ተደረገ፡፡

ሦስቱንም ሥርዓት ዛሬ በጎንደር እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው እንደ ዐፄ ገብረ መስቀል ሥርዓት ከመንበሯ ወጥታ ሕዝቡን ባርካ በዕለቱ ወደ መንበሯ የምትመለሰው የጎንደር በዓታ ለማርያም ናት፡፡ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ቅዱስ ኡራኤል በ22 ወጥቶ በእለቱ ሕዝቡን ባርኮ ወደ መንበሩ በክብር ይገባል፡፡ እንደ ዐፄ ላሊበላ ታቦታት ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር በመውረድ አድረው በመጡበት መንገድ መመለስን 8ቱ ዐፄ ፋሲል ባሰራው ጥምቀተ ባሕር የሚወጡት ታቦታት ናቸው፡፡ እንደ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ሥርዓት ታቦታት ወደ ጥምቀተ ባሕር በወረዱበት ሳይሆን በሌላ መንገድ ወደ መንበሯ የምትመለሰው ታቦት በጎንደር ውስጥ ብቸኛዋ የልደታ ለማርያም ታቦት ናት፡፡

መምህር ኤስድሮስ፡-

asdrose 2006 04በቤተ ክርስቲያኗ ከአንድ መቶ ሃምሳ በላይ የአቋቋምና የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ነበሩባት፡፡ የአቋቋም መምህራንና ጉባኤው አሁንም ድረስ ሳይቋረጥ የቀጠለ ቢሆንም የትርጓሜ መጻሕፍት መምህራን ግን ድርቡሽ ቤተ ክርስቲያኗን ካወደመና ንዋያተ ቅድሳትን ዘርፎ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ከሔደ በኋላ ወንበሩ እንደታጠፈ ነው፡፡ የመምህር ኤስድሮስ የትርጓሜ ወንበር ታጥፎ ወደ ሠለስቱ ምዕት ቤተ ክርስቲያን ተወስዷል፡፡

የጎንደር ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ዐራት ዓይና የነበሩት መምህር ኤስድሮስ የትርጓሜ መጻሕፍትን ወንበር ዘርግተው በማስተማር ታላላቅ ሊቃውንትን ያፈሩባት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለውለታ የሆነች ናት፡፡

መምህር ኤስድሮስ በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የትርጓሜ መጻሕፍትን ጉባኤ ተክለው ወንበር ዘርግተው በማስተማር የተለያዩ የቤተ ክርስቲያንን መጽሕፍት እየመረመሩ ለተማሪዎቻቸው በቂ እውቀት እያስጨበጡ ተመርቀው ይወጣሉ፡፡ ከደቀመዛሙርቱም መካከል የቻለ ወንበር ዘርግቶ በማስተማር፤ ሌሎቹ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማገልገላቸውን ይቀጥላሉ፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ሁለት ዓይነት የአተረጓጎም ሥልቶች ይገኛሉ፡፡ እነሱም የላይ ቤትና የታች ቤት ትርጓሜ በመባል ይታወቃሉ፡፡ የትርጓሜ መጻሕፍትን በምሥጢር ካበለጸጓቸው መምህራን አንዱ መምህር ኤስድሮስ ሲሆኑ፤ የታች ቤት ትርጓሜ መሥራችም ናቸው፡፡

መምህር ኤስድሮስ መጸሕፍትን በመመርመር የሚታወቁ በመሆናው አንድ ወቅት ወደ ጣና ገዳማት ሔደው ከ300 በላይ መጻሕፍትን ለማንበብ ችለዋል፡፡ መጻሕፍቱን በማንበባቸው ቀድሞ በነበራቸው እውቀት ላይ በመጨመር እስከዚያ ጊዜ ድረስ ለተማሪዎቻቸው ያስተማሩት ትምህርት በቂ እንዳልነበር ተረዱ፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም አስተምረዋቸው፤ ለወጡ ደቀ መዛሙርቶቻቸው መልእክት በመላክ “የጎደለን ምሥጢር አለ” በማለት እንዲሰበሰቡ አደረጉ፡፡

በርካቶቹ የመምህራቸውን ጥሪ ተቀብለው ቢመጡም፤ ጌታ ዮናስ የተባሉት ደቀመዝሙራቸውና ሌሎች ግን እርስዎ ልዩ ትርጓሜ ከመጨመርዎ በፊት አስተምረውናል በማለት በመምህር ኤስድሮስ ተሻሻለ የተባለውን አንድምታ ትርጓሜ ለመማር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፡፡ እንደ ምክንያትነት ያስቀመጡት “ኢተወለድነ እምዝሙት፤ እኛ ከዝሙት አልተወለድንም፡፡ ከመጀመሪያው ጉባኤ ተምረን ተመርቀን ወጥተናልና አንመለስም” በማለታቸው ነው፡፡

ጥሪያቸውን ተቀብለው ለመጡት ደቀመዛሙርቶቻቸው ከጣና ገዳማት ከመጻሕፍት ያገኙትን እውቀት ሳይቆጥቡ ያላስተማሩትን እየጨመሩ ምሥጢሩን አስፋፍተው፤ ያጠረውን እያስረዘሙ፤ የረዘመውን እያሳጠሩ አስተማሯቸው፡፡

የመምህር ኤስድሮስን ጥሪ ተቀብለው በመምጣት እንደገና አስፋፍተው ያስተማሩትን “የታች ቤት ትርጓሜ” ሲባል፤ ጥሪያቸውን ሳይቀበሉ የቀሩትና እነ ጌታ ዮናስ በቀጣነት ያስተማሩት ጥንታዊው ትርጓሜ ደግሞ “የላይ ቤት ትርጓሜ” ተብሎ ለሁለት ተከፈለ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በጎንደር ተስፋፍቶ የሚሰጠው የታች ቤት ትርጓሜ ሲሆን፤ በጎጃምና አካባቢው ደግሞ የላይ ቤት ትርጓሜ በስፋት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ 2000 ዓ.ም. ገጽ194፤ ዝክረ ሊቃውንት፤ በመልአከ ምክር ከፍያለው መራሒ፤ 2003 ዓ.ም./

አለቃ ገብረ ሃና፡-

aleka g 2006 01ከልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ጋር ተያይዞ ስማቸው ከሚነሱ ሊቃውንት መካከል አለቃ ገብረ ሃና አንዱ ናቸው፡፡ በዓታ ለማርያም ወንበር ዘርግተው አቋቋም እያስተማሩ ወደ ልደታ ለማርያም እየመጡም ያገለግሉ ነበር፡፡ አለቃ ገብረ ሃና ለልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አንድ ከበሮ ራሳቸው አሰርተው በስጦታ አስገብተው ስለነበር ወደ ቤተ ክርስቲያኗ በሚመጡበት ወቅት አገልግሎት ይሰጡበታል፡፡ እስከ ዛሬም ድረስ በልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ ሲሆን፤ “የአለቃ ገብረ ሃና ከበሮ” እየተባለም ይጠራል፡፡ ከበሮው በቅርስነት የተያዘና በክብር እንዲቀመጥ በመደረጉ ለዓመታዊ ክብረ በዓል ካልሆነ በቀር ለአገልግሎት አይወጣም፡፡

የድርቡሽ ጦር ጠባሳ፡-

የድርቡሽ ጦር በተለይም በጎንደር በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ያደረሰው ከፍተኛ ውድመት በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የራሱን ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ አባቶች ታርደዋል፤ ተሰደዋል፤ ንዋያተ ቅድሳት ተዘርፈዋል፤ ተቃጥለዋል፡፡ ከፍተኛ ውድመት ከደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

ቤተ ክርስቲያኗን ድርቡሽ ከማፍረሱ በፊት ምን ትመስል እንደነበር መገመት ይከብዳል፡፡ ነገር ግን የንጉሥ ኢያሱ ዜና መዋዕል እንደሚነግረን “ዐፄ ዮስጦስ ልደታ ለማርያም የምትባል ረጅም ፤ ከፍ ያለች ፤ ከከፍታዋ የተነሳ ከርቀት የምትታይ ቤተ ክርስቲያን ሠሩ” እያለ ይነግረናል፡፡

ከልደታ ለማርም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጋር ስማቸው ከሚነሱ ነገሥታት መካከል ዐፄ ዮስጦስ፤ ንጉሥ ዐጽመ ጊዮርጊስ፤ ንጉስ ተክለ ሃይማኖትና ዐፄ በካፋ ይገኙበታል፡፡ ቤተ ክርስያኗን በተለያዩ ዘመናት በማሠራት ይታወቃሉ፡፡

የዐፄ ዮስጦስ የንግሥና ዘመን በአጭርነቱ ከሚጠቀሱት ውስጥ የሚደመር ሲሆን፤ ለአምስት ዓመታት በንግሥና በቆዩባቸው ዘመናት በርካታ ቤተ ክርስቲያንና አገርን የሚጠቅሙ ሥራዎች ለመሥራት ጥረዋል፡፡ ነገር ግን በዙሪያቸው የነበሩ ተቀናቃኞቻቸው ሊያጠፏቸው ሌት ተቀን ያደቡ ስለነበር አባ እንጦንስ ቤተ ክርስቲያን ሔደው አስቀድሰው እንደተመለሱ ከምግብ ጋር መርዝ ሰጥተዋቸው የካቲት 12 ቀን 1708 ዓ.ም. አርፈው በማግሥቱ የካቲት 13 ቀን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ መቃብራቸውም በልደታ ማርያም ቤተ ክርስቲያንና በቤተልሔሙ መካከል ከቤተ ክርስቲያኑ ተጠግቶ ይገኛል፡፡ የልደታ ቤተ ክርስቲያንን ቅጥርና ደጀ ሰላም በማሠራት ላይ እያሉ በመሞታቸውም ዐፄ በካፋ ቅጥሩን አሠርተው አጠናቀውታል፡፡

በድርቡሽ ወራራ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ንዋያተ ቅድሳት ወደ ጣና ደሴቶች እንደተወሰዱ የሚነገር ሲሆን፤ የት እንዳሉ ግን ማወቅ አልተቻለም፡፡ ሳይወሰዱ የተረፉትም እንደ ብራና፤ ተአምረ ኢየሱስ፤ የደብሩን ታሪክ በተለይም የንጉሱን ታሪክ የሚናገር ስንክሳር የመሳሰሉት መጻሕፍት ዛሬም ድረስ በቤተ ክርስቲያኗ ይገኛሉ፡፡

ድርቡሽ በጎንደር ውስጥ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን አፍርሷል፤አቃጥሏል፤ ንዋየ ቅድሳትን ዘርፏል፡፡ ነገር ግን የድርቡሽ ጦር የልደታ ለማርያምና የቁስቋም አብያተ ክርስቲያናት ደጀ ሰላምን ማፍረስ ግን አልተቻለውም፡፡

አሁን ያለው ቤተ ክርስቲያን እንዴት ታነጸ?

amde kome 2006 03የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን የቀድሞ ገጽታ ከፍርስራሹና ሙሉ ለሙሉ ካልወደቁት ቆመ ብእሲ በመነሳት መገመት አይቻልም፡፡ ድርቡሽ ቤተ ክርስቲያኗን ሲያወድም ቅጥሩን ግን ማፍረስ ሳይችል ቀርቶ እስከ ዛሬ ድረስ ከነደጀ ሰላሙ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለው ግድግዳ የጥንቱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗን ድርቡሽ ካፈረሰ በኋላ መቃረቢያ ተሰርቶላት ለረጅም ዘመናት በዚያ ሲቀደስ ነበር፡፡ ይህ አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለው ቤተ ክርስቲያን በ1970ዎቹ ውስጥ የታነጸ ነው፡፡

በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኗን ያሠሩት በዓታ ለማርያም ሲያገለግሉ የነበሩ ቄስ አቡሐይ የሚባሉ አባት ናቸው፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ ገጽታ እየፈረሰ መሆኑን በመረዳታቸው ምእመናንን ሰብስበው ላሰራው በማለት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ በወቅቱ የነበሩት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደርና ምእመናን ከለከሏቸው፡፤ እሳቸው ግን ተሰፋ ባለመቁረጥ አስተዳደሩንም ሆነ ምእመናንን ለማሳመን ባደረጉት ተከታታይ ጥረት ተፈቅዶላቸው አሳንጸዋል፡፡ በዚህ ወቅት በርካታ ፈተና ገጥሟቸዋል፤ ብዙም ደክመውበታል፡፡ የዓፄ ዮስጦስና የመምህር ኤስድሮስ ታላቅ ሥፍራ ፈርሶ መቅረት የለበትም በሚል በቁጭት ተነሣስተው ለፍጻሜ ለማብቃት ችለዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑን ማሠራት ብቻ ሳይሆን ለቤተ መቅደሱ ልዩ ድምቀት የሆኑትን ቅዱሳት ሥዕላትን በማሣል አስረክበዋል፡፡

 

የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን

ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

ክፍል አንድ፡-

በጎንደር ከተማ በርካታ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ሲሆን አብያተ ክርስቲያናቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ደንብ ጠብቀው፣ እንዲሁም በዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያዊያን የሥልጣኔ ደረጃ ከፍተኛ መሆንን የሚያመለክቱ አሻራዎች አርፎውባቸዋል፡፡ ይህንንም አሻራዎቻቸውን ይዘው ዛሬ ድረስ ዓለምን እያስደመሙ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም አድባራትና ገዳማት በነገሥታት፤ በባላባቶችና በሀገሬው ሰው የተተከሉ ሲሆኑ፤ በነገሥታቱ ከተተከሉት አድባራት ውስጥ በ1703 ዓ.ም በንጉሡ በዐፄ ዮስጦስ የተመሠረተችው የጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን አንዷ ናት፡፡

ደጀ ሰላሙ በድንጋይ ጥርብ እንደተካበ ጥንታዊነቱን ጠብቆ ግርማ ሞገሱን ተላብሶ ይታያል፤ የቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ በድንጋይ ካብ እንደታጠረ ከቅጥሩ ጋር ተያይዞ ነገሥታቱ ፀሎት ያደርጉባቸው የነበሩ በእንቁላል ቅርጽ የታነጹት ማማዎች ቁልቁል gonder ledetaአካባቢውን ለመቃኘት ያስችላሉ፡፡ ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ድርቡሽ ጥንታዊውን ቤተ ክርስቲያን ሲያፈርስ ለታሪክ ምሥክርነት የቀሩት የቤተ ክርስቲያኑ ዓምዶች አሁን ያለውን ቤተ ክርስቲያን ዙሪያውን ከበው ይታያሉ፡፡ በግቢውና ውጪ የሚታዩት እድሜ ጠገብ ዛፎች፤ ቤተልሔሙ፤ የዐፄ ዮስጦስ መቃብር . . . ለቤተ ክርስቲያኑ ጥንታዊነት ምሥክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡

ግቢውን እየቃኘን በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ለመሥራት ላሰብነው ዘገባ መረጃ ሊሰጡን በቀጠሯቸው ተገኝተው እኛን በመጠበቅ ላይ ወደ ነበሩት አባቶችና ወንድሞች አመራን፡፡ ከቤተ ክርስቲያኗ አገልጋይ አባቶችና ወንድሞች ጋር ቤተ ክርስቲያኗን በሚመለከት ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡

አመሠራረት

ዐፄ ዮስጦስ ንግሥናቸው በእናታቸው ወገን በመሆኑ በርካታ ተቀናቃኞች ነበሯቸው፡፡ ተቀናቃኞቻቸውም “ንግሥና በአባት ወገን እንጂ፤ እንዴት በእናት ወገን ይሆናል?” እያሉ በርካታ ሴራዎችን በማሴር ንግሥናቸውን ለመቀማት ጥረት አድርገውባቸው ነበር፡፡ ንጉሡ ግን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነበራቸው ፍቅር እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ ተቀናቃኞቻቸውን በጦርነት ብቻ ሳይሆን በጾምና በጸሎት ድል ያደርጓቸው ነበር፡፡

በአንድ የጾመ ፍልሰታ ለማርያም ወቅት ሱባኤ ላይ እያሉ ከተቀናቃኞቻቸው መካከል አንዱ መንግሥታቸውን ለመቀማት ጦር አዘመተባቸው፡፡ ወታደሮቻቸው በሁኔታው በመደናገጥ “ከሱባኤዎ ይውጡ፤ የመጣውን የጠላት ጦር መክተን እንመልስ ዘንድ ይምሩን፤ በጠላት ከመያዛችን በፊት ድረሱልን” በማለት አስጨነቋቸው፡፡

ዐፄ ዮስጦስ ግን አሻፈረኝ በማለት ከያዙት ሱባኤ እንደማይወጡ ለወታደሮቻቸው ይናገራሉ፡፡ ወታደሮቻቸውም ጥያቄያቸውን በመቀጠል “በሚቀጥለው ዓመት ሱባኤ ይገባሉ፤ ራስዎን፣ እኛንም ለጠላት አሳልፈው አይስጡን፤ እባክዎ ከሱባኤ ወጥተው ጠላቶቻችንን ድል እናድርግ” በማለት ተማጸኗቸው፡፡

የወታደሮቻቸው ጉትጎታ አላሳርፍ ያላቸው ንጉሡ “ጠላትን ድል አድርጌ በሰላም ከተመለስኩ በዚህ ቦታ ላይ የልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን እሠራለሁ” ሲሉ ስዕለት ተስለው ወታደሮቻቸውን እየመሩ ወደ ጦርነቱ ዘመቱ፡፡ በጦርነቱም ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግ ድል አድርገው ተመለሱ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባደረገችላቸው መልካም ነገር በመደሰት ቃላቸውን ጠብቀው የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያንን ሱባኤ ይዘውበት በነበረበት ቦታ ላይ በ1703 ዓ.ም. ተከሉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኗ በንጉሥ ዐፄ ዮስጦስ ስትመሠረት የነገሥታት ትክል በመሆኗ ብዙ ሰው በአጥቢያዋ አልነበረም፡፡ የምትተዳደረውም ሪም በሚባል ሥርዓት ነበር፡፡ /የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከአለቃው ጀምሮ እስከ ዲያቆናትና ዐቃቢት ድረስ በተዋረድ እንደ አገልግሎታቸው ከቤተ ክርስቲያኗ ጉልት እየተከፈለ መሬት ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ለአገልጋዮቹ የሚሰጣቸው መሬት ሪም በመባል ይታወቃል፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮችም ከተሰጣቸው ሪም ላይ ከሚኖሩ ዜጎች ዓመታዊ ምርት /እህል ብቻ/ ሢሶውን ለመተዳደሪያቸው ይቀበላሉ፡፡/ በጊዜው ቤተ ክርስቲያኗን ለሚያገለግሉ ከ150 በላይ ለሆኑ ሊቃውንት ደምቢያ ከሚባል አገር እህል ይጫንላቸው ነበር፡፡

አድርሺኝ

ከጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን መተከል ጋር በተያያዘ በጎንደር ከተማ ውስጥ የሚካሔድ አንድ ሥርዓት አለ፡፡ ይህም ሥርዓት አድርሺኝ በመባል ይጠራል፡፡ ሥርዓቱ የሚከናወነው በፍልሰታ ጾም ወቅት ነው፡፡

ስለ ሥርዓቱ አጀማመር አባቶች ሲናገሩ፣ ዐፄ ዮስጦስ ወደ ጦርነት ሲዘምቱ “ጦርነቱን በልደታ ለማርያም ምልጃ ተደግፌ አሸንፌ ከተመለስኩ በፍልሰታ ለማርያም ሱባኤ ማታ ማታ ካህናቱን፤ መኳንንቱንና ምእመናንን ሰብስቤ ግብዣ አደርጋለሁ” በማለት ብፅዐት ይገባሉ፡፡ እርሳቸውም ድል አድርገው ተመለሱ፤ በቃላቸውም መሠረት ግብዣ አደረጉ፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑም እርሳቸውን ተከትሎ በጾመ ፍልሰታ ወቅት ይህን ሥርዓት ይተገብሩት ጀመር፤ ስያሜውም “አድርሺኝ” ተባለ፡፡

አድርሺኝ በመላው ጎንደር እስከ ዛሬ ድረስ በየቤተ ክርስቲያኑና በየአካባቢው በፍልሰታ ጾም ወቅት ይከናወናል፡፡ ምእመናን ከቅዳሴ መልስ ሱባኤው እስኪያልቅ በመረጡት አንድ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ቆሎና ጠላ ተዘጋጅቶ በእመቤታችን ስም ጽዋ ይጠጣሉ። በተለይ መነኮሳያት እናቶች በሚታደሙበት ጽዋ ላይ “ኦ! ማርያም” የሚለውን የተማጽኖ መዝሙር ይዘምራሉ። ይህ መዝሙር በሚዘመርበት ጊዜ እመቤታችን ፊት ለፊት ስለምትቆም በፍፁም ተመስጦና መንበርከክ ያከናውኑታል።

በዋነኛነት የመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ይህንን የተቀደሰ ተግባር በማስተባበርና በማስፈጸም እንዲሁም ትውፊቱ እንደጠበቀ ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ እየሠራ ይገኛል፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምና ዐፄ ዮስጦስ

gonder ledeta 2 ዐፄ ዮስጦስ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የነበራቸው ፍቅር እጅግ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ በርካታ ታሪኮች እንዳሏቸው ይነገራል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የጥምቀትን በዓል ለማክበር ዐፄ ዮስጦስ ከካህናቱ፤ ከመኳንንቱና ከምእመናን ጋር በመሆን ታቦቱን አጅበው ቀሃ ዳር ወደሚገኘው ጥምቀተ ባሕር በመውረድ ላይ ሳሉ አንዲት ሴት ከታቦቱ አጠገብ ስትጓዝ ይመለከታሉ፡፡ “ከታቦቱ አጠገብ የምትጓዘውን ሴት ከሥፍራው አርቋት፤ ከታቦት አጠገብ እንዴት ብትዳፈር ነው የምትጓዘው?” በማለት ለወታደሮቻቸው ትእዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ ወታደሮቻቸው ግን ንጉሡ ያሏትን ሴት ማግኘት አልቻሉም፡፡ እሳቸውም ሠይፋቸውን መዝዘው ቢሔዱም ከታቦቱ አጠገብ ተሰወረችባቸው፡፡

“ይህ ምሥጢር ሳይገለጽልኝ ወደ ንግሥናዬና ወደ ቤተ መንግሥቴ አልመለስም” በማለት እዚያው ድንኳን አስተክለው ሱባኤ ይገባሉ፡፡ በሦስተኛው ቀን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ተገልጻ “ከታቦቱ አጠገብ ያየኸኝ እኔ ድንግል ማርያም ነኝ” በማለት ተናገረቻቸው፡፡ ጊዜ እረፍታቸውንም መች እንደሚሆን አስታውቃና ባርካ፤ በየዓመቱ ኅዳር 21 በአክሱም ጽዮን ማርያም፤ ለአስተርእዮ ማኅደረ ማርያም እንደምገኝ ሁሉ በጥምቀት በጎንደር መካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም እገኛለሁ በማለት ቃል ኪዳን ገብታላቸዋለች፡፡

ምእመናን በቤተ ክርስቲያኗ የጥምቀት ዕለት ገንዘብ አዋጥተው ዝክር መዘከር የጀመሩት ከዚህ ቃል ኪዳን ጋር በተገናኘ መሆኑን አረጋውያን ያስረዳሉ።

ለውኃ ለውኃ ምን አለኝ ቀሃ

የቀሃ ወንዝ በጎንደር ውስጥ የጎንደርን ከተማ ለሁለት ከፍሎ ይልፋል፡፡ ቀሃ በጎንደር ውስጥ ታዋቂ ከመሆኑ የተነሣም “ለውኃ ለውኃ ምን አለኝ ቀሃ” እየተባለም ይነገራል፡፡ የጥምቀት በዓል በሚከበርበት ወቅት የልደታ ለማርያም ታቦት በዚሁ አካባቢ ታርፋለች፡፡

gonder ledeta 3 አረጋዊ መንፈሳዊ ስለ እንጦንስ የትውልድ አካባቢ ሲናገር ቀሃ ወንዝን እንደምልክትነት ይጠቀመዋል፡፡ ወንዝ ዳር፤ ወንዝ አካባቢ እንደሆነ ይነግረንና ምን ትመስላለች የሚለውን ሲገልጽ “ቀሃ ዳር ልደታ ማርያም እንዳለች ሁሉ . . . ” እያለ ያብራራል፡፡
የልደታ ውኃበጎንደር ከተማው ውስጥ በዛ ያሉ የጸበል ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህ የጸበል ቦታዎች አንዱ በመካነ ስብሐት ልደታ ለማርያም ቤተ ክርስቲያን ይገኛል፡፡ የጸበል ቦታውም የልደታ ውኃ በመባል እየተባለ ይጠራል፡፡ በጸበሉ በርካታ ድውያን የሚፈወሱበት ሲሆን እንደ ግሸ አባይ ከምእራብ ወደ ምሥራቅ ይፈሳል፡፡

የልደታ ውኃ በተለያዩ የትርጓሜ መጻሕፍት ውስጥ ትገኛለች፡፡ መምህር ኤስድሮስ ውዳሴ ማርያምን ሲተረጉሙ “ዳዊት ዘነግሠ ለእሥራኤል አመ ይትነሥኡ ላዕሌሁ ዕልዋን ፈተወ ይስተይ ማየ እም ዓዘቅተ ቤተልሔም. . .፤ የሕይወት ውኃነት እንዳላት ከምእራብ ወደ ምሥራቅ እንደምትፈሰው እንደ ልደታ ውኃ” ይላል፡፡

በጸበሏ ዛሬም ድረስ በርካታ ሕሙማን እየተፈወሱ ይገኛሉ፡፡

ይቆየን