ግሸን ማርያም

‹‹ግሸን ማርያም›› በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት፤ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ፣ በደላንታ፣ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ የምትገኝ አንድ መግቢያ በር ብቻ ያላት ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ናት፡፡ በበርዋ ከተገባ በኋላ ግቢዋ ከላይ ሜዳና መስቀለኛ ቦታ ነው፡፡

በ፲፩ኛው ክፍለ ዘመን ዐፄ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው ‹‹እግዚአብሔር አብ›› የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሠሩ ‹‹ደብረ እግዚአብሔር›› ተብላ ተሰየመች። ብዙም ሳይቆይ ‹‹ደብረ ነገሥት››ተባለች። ከዚያም የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ‹‹ደብረ ነጎድጓድ›› ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት በመሆኗ ‹‹ደብረ ነጎድጓድ›› ተብላለች፡፡

በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ‹‹ደብረ ከርቤ›› ተብላ ተሰየመች፡፡ ከዐፄ ድልናአድ ዘመን ፰፻፹፮ዓ.ም እስከ ፲፩ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ ‹‹ደብረ ከርቤ›› በመባል ትታወቅ ነበር። በዚህ ጊዜ የነበረው የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መምህረ እስራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር። በመጨረሻም ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም የሚል ስያሜ አገኘች፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ ‹‹ገሰ›› ወይም በአማርኛው ‹‹ገሰገሰ›› የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተዛወረ፤ አካባቢው በዚህ ስም ታወቀ።

በዚያችም አምባ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው ዘመኑም በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡

ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ንዋየ ቅዱሳት ጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳ፣ ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ፣ የቅዱስ ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል፣ ቅዱስ ሉቃስ የሳለው የእመቤታችን ስዕል፣ የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር፣ የዮርዳኖስ ውሃ እና በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ናቸው፡፡

የእነዚህን ንዋየ ቅዱሳት ዝርዝር ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሸን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩፻፬፻፵ ዓ.ም. በጽሑፍ በመዘርዘር ገለጹ፡፡

በዚያም ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ጳጳሳት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ከንጉሡ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጋር ሆነው የምሕረት ቃል ኪዳን ለመቀበል በዚህች በግሸን ደብር ሱባዔ ገቡ፡፡ በሱባዔአቸውም መጨረሻ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ‹‹ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን ትሁን፤ የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን ትሁን፤ የተቀበርኩባትንም ጎልጎታን ትሁን፤ በዚህች ቦታ እየመጣ የሚማፀነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች፤ ጠለ ምሕረቴም አይለይባትም›› አላቸው፡፡ በዚያ ለተገኙት ምእመናን ሁሉ በጽሑፍ ካሰሙ በኋላ ጠቅላላ የግማደ መስቀሉንና የሌሎቹን ታሪካውያን ንዋየ ቅዱሳትንም ዝርዝር ታሪክ የያዘውን መጽሐፈ ‹‹ጤፉት›› ብለው ሰይመው ድንጋጌውን ሁሉ በመዘርዘር ለ ‹‹ግሸን እግዚአብሔር አብ›› ሰጡ፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብም በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ እሌኒ የተሰኘችው ንግሥት በእመቤታችን ማርያም ስም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አዘው፤ የእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ አሳንጻ ጥር ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡ ይህችን ደብር ‹‹ደብረ ከርቤ›› ብለው በመሰየም ‹‹እንኳንስ ሰው የሠገረ ቆቅ፣ የበረረ ወፍ እንዳይገደል ዳሯ እሳት መሀሏ ገነት ትሁን›› ብለው ደንብና ሥርዓት በ ‹‹መጽሐፈ ጤፉት›› ውስጥ አጽፈዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በየጊዜው የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ ጳጳሳት፣ መሳፍንትና መኳንንት ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳትንና መጻሕፍትን፣ የወርቅንና የብር ጻሕል ጽዋን፣ መስቀልን እና የመሳሰሉትን ስጦታ አበርክተዋል።

ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ቢሆንም ኢትዮጵያ ‹‹ግሸን አምባ›› የገባበት፣ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በጽሑፍ በመዘርዘር የገለጹበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ ይህን ዕለትም በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፤ ምእመናንም በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሓ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ሁሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ‹‹ጤፉት›› በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ፣ የእመቤታችን አማላጅነት፣ የግማደ መስቀሉ፣ የአባቶቻችን ሊቃውንትና ነገሥታት በረከት አይለየን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፡- መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መጽሐፈ ጤፉት

ወስብሐት ለእግዚአብሔር