የአሰቦት ገዳምን ለመርዳት ጉባኤ ሊካሄድ ነው፡፡

ግንቦት 8/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

የአሰቦት ደብረ ወገግ ቅድስት ሥላሴና አቡነ ሳሙኤል ገዳምን ለመርዳት ታላቅ መንፈሳዊ ጉባኤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሸ ሰኔ 3 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል፡፡ ከ800 ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው ገዳም በፃድቁ አቡነ ሳሙኤል ዘደብረ ወገግ የተመሠረተ ሲሆን በቅርቡ የገዳሙ ደን  ተቃጥሎ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑ ይታወሳል፡፡

ገዳሙ ከከተማው 18 ኪ. ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ለመድረስ 6 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለውን ተራራ በእግር መውጣት ይጠበቃል፡፡ የመንገዱ አስቸጋሪነት ገዳሙን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ያላስቻለው ሲሆን መንገዱን ለመሥራት ኮሚቴ በማዋቀር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ምዕመናን ይህንን ጥንታዊና ታሪካዊ ገዳምን ለመርዳት ትኬቱን በመግዛት ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ የገዳሙ አስተዳደር ጥሪውን ያቀርባል፡፡

maderaja memreya letter

በሕገወጦች በጨለማ የተዘጋጀው ደብዳቤ ተበተነ፡፡

ግንቦት 7/2004 ዓ.ም.

ከጥቂት ቀናት በፊት ማኅበረ ቅዱሳን ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ማእከላዊ አስተዳደር ተገዥ ካለመሆን አልፎ የተቋሙን ሕልውና ወደ መፈታተን እንደ ደረሰ በማተት የሚከስ ደብዳቤ ለሕግ ተገዢ ባልሆኑ ግለሰቦች በጨለማ ተረቅቆ በመምሪያው ሓላፊ እንዲፈረም ተደርጎ ሊወጣ እንደ ነበር፤ ነገር ግን በመምሪያው ሓላፊው በቆሞስ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ መታገዱን ገልጸን ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ አሁን ምክንያቱ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ “ፍጹም ሕገ ወጥ ድርጊት በሕጋዊዋና በእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መፈጸም የለበትም፤ ይቁም” ያሉትን የመመሪያ ሓላፊ አስተዳደሩ ከቦታቸው አንሥቷል፡፡ በምትካቸውም ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ደብዳቤውን በወቅቱ በተገለጠው ሁኔታ በማርቀቅ፣ እንዲፈረምና እንዲሠራጭ የሞት ሽረት ትግል ሲያደርጉ ከነበሩት ግለሰቦች አንዱ የሆኑትን መምህር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተን ሾሟል፡፡

ቆሞስ አባ ኅሩይ በመምሪያ ሓላፊነት ተመድበው ቦታውን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በማኅበሩ መስተካከል አለባቸው በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ሁሉ የማኅበሩን አመራር አካላት እየሰበሰቡ መመሪያ ሲሰጡ፣ ማኅበሩም መመሪያዎችን እየተቀበለ ወደ ተግባር ሲለውጥ ቆይቷል፡፡ ቆሞስ አባ ኅሩይ ደብዳቤ በማርቀቅ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ልዩ ልዩ ክፍሎች አልፎ እስከ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በሚደርስ ሁኔታ በማብረር የማያምኑ ውይይት ተኮር ዘመናዊ የአመራር ዘዴን የሚከተሉ በመሆናቸው ማኅበሩ መመሪያቸውን ሁሉ እየተቀበለ በማገልገል ላይ ነበር፡፡ ማኅበሩ የሚፈልገው በመጠነ ሰፊ ችግሮች ውስጥ ባለች ቤተ ክርስቲያን ሠርቶ የሚያሠራው ነውና፡፡

የመምሪያ ሓላፊው ቆሞስ አባ ኅሩይ ባላጠፉት ጥፋት ተከሰው ከቦታው መነሣታቸውን በመቃወም ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጥ ማኅበሩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ጉዳዩም በቅዱስ ሲኖዶስ በአጀንዳነት ተይዟል፡፡

maderaja memreya letter

ማኅበሩ ለጻፈው ደብዳቤ ምላሽ በሚጠብቅበት በአሁኑ ወቅት፤ በመምሪያ ሓላፊነት የተመደቡት መምህር ዕንቊ ባሕርይ ተከሥተ ለረጅም ዓመታት የታገሉለትን ማኅበሩን የማደናቀፍ እኲይ ተግባር የሚያረጋግጡላቸውን ደብዳቤዎች ማብረር ጀምረዋል፡፡ በትላንትናው ዕለት ካበረሯቸው ደብዳቤዎች አንዱ ለቆሞስ አባ ኅሩይ መነሣት ምክንያት የሆነውንና ራሳቸው መምህር ዕንቊ ባሕርይ ከመሰል ግብረ አበሮቻቸው ጋር ሆነው አርቅቀው እንዲፈረምና እንዲበር የተሯሯጡለት ደብዳቤ ነው፡፡

 

የማኅበሩ አመራር በደብዳቤው ይዘትና በመምሪያችን እየተፈጠረ ስላለው የተጠናና ቤተ ክርስቲያኗን የማዳከም እንቅስቃሴ ላይ ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ ለቅዱስ ሲኖዶስ ያቀረበውን አቤቱታ መልስ ይጠብቃል፡፡ በሒደቱ የሚፈጠሩትን ማናቸውንም ክስተቶች እየተከታተለ ለምእመናን ይፋ ያደርጋል፡፡

mk letter to synodos

የማኅበሩ አባላትም ሆኑ ምእመናን ዛሬ በማኅበራችን ላይ እየደረሰ ያለው ችግር በእናት ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ካለው ጋር ሲነጻጸር እዚህ ግባ የማይባል በመሆኑ አገልግሎታችንን በተለመደው ሁኔታ አጠናክረን እንድንቀጥል እናሳስባለን፡፡

DSC02522

ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል ስለምትገኝበት ሁኔታ ዐውደ ጥናት ተካሄደ

ግንቦት 7/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

DSC02522የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኦሮሚያ ክልል የምትገኝበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት ቅዳሜ ግንቦት 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ተካሔደ፡፡ አውደ ጥናቱ በማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል አስተባባሪነት የተዘጋጀ ሲሆን በዋና ክፍሉ ስር ከሚገኙት ዴስኮች መካከል የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ አማካይነት ቀርቧል፡፡

የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ በመደበኛና በኢመደበኛ አባላት የተጠናከረ ክፍል እንደመሆኑ በኦሮሚያ ክልል ቤተ ክርስቲያናችን ምን ላይ እንደምትገኝ የሚያሳይ ጥናት ይዞ እንዲቀርብ በተሰጠው ሓላፊነት መሠረት ጥናቱን ይዞ መቅረቡን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል ሓላፊ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ገልጸዋል፡፡ የጥናቱ ዋነኛ ዓላማን አስመልክተው ቤተ ክርስቲያናችን በኦሮሚያ ክልል ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ መዳሰስ፤ ችግሮቹን ለመፍታት ምን መደረግ እንደሚገባና ምዕመናን በአንዳንድ እምነቶች እንዳይወሰዱ በመረጃ የተደገፈ ምላሾችን መስጠት የሚያስችል ጥናት እንደሆነ ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኦሮምኛ ትርጉም ዴስክ ሓላፊ የሆኑት ቀሲስ ምስጋናው አገሳ እንደገለጹት ዴስኩ የትርጉም ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ፣ በተለይም ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ወንድሞችና እኅቶችን በማሰባሰብ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከአማርኛ ወደ ኦሮምኛ በመተርጎም ላይ እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ በዚህ ዓመትም 5 መፃሕፍትን ተርጉመው ለምእመናን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝና ይህ ጥናት በእነዚሁ አባላት አማካይነት የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥናት አቅራቢዎቹ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ችግሮች ያሏቸውን የሚያሳይ የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን ክልሉ ሰፊ እንደመሆኑ ችግሮቹም ስፋት ያላቸው ስለሆነ ተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ያሏቸውንም በሁለት በመክፈል ውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ችግሮች በማለት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ናቸው ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ ምዕመናን ከኦሮምኛ ቋንቋ በቀር መስማትና መናገር ባለመቻላቸው በቋንቋቸው የሚገባውን አገልግሎት መስጠትና ማግኘት ያለመቻሉ፤ ንስሐ ለመግባት በአስተርጓሚ እስከማከናወን መድረሱ፣ በቋንቋው የተዘጋጁ የቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍትና የቋንቋው ተናጋሪ አገልጋይ ያለመኖር፣ የምዕመናን ባህልና አኗኗር ማዕከል ያደረገ ሐዋርያዊ አገልግሎት መስጠት ያለመቻሉ፤ በተለያዩ እምነቶችና ባዕድ አምልኮዎች መጠመዱ…. የመሳሰሉት እንደሆኑ በጥናት አቅራቢዎቹ ተዳስሰዋል፡፡

DSC02521ከተለያዩ ዋና ዋና ክፍሎች የተገኙት የማኅበሩ አባላት በጥናቱ ላይ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን እንዲሁም የመፍትሔ ዐሳቦችን አቅርበዋል፡፡ ከጥናቱ አቅራቢዎችም ምላሾች ተሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም መፍትሔዎቹን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም  መካከል በክልሉ ምዕመናን በቋንቋቸው የሚገለገሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በተወላጆቹ /በቋንቋው ተናጋሪ አገልጋዮች/ አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻል፣ በኦሮምኛ ቋንቋ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማዘጋጀትና ማሰራጨት፣ አገልጋዮችን ለማፍራት ማሠልጠኛ ተቋም  መክፈት፣ በግቢ ጉባኤያት ለሚገኙ ተማሪዎች የአብነት ትምህርት መስጠት፣ ተጨባጭ ጥናቶችን በተጠናከረ ሁኔታ ማካሔድ…… የመሳሰሉትን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የተገለጹት ችግሮችና ከአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች የቀረቡ ጥያቄዎችና የመፍትሔ ዐሳቦችን በማጠናከር ከማኅበረ ቅዱሳን ሥራ አስፈጻሚ ጋር ተነጋግሮና አጽድቆ በአፋጣኝ ወደ ትግበራ እንደሚሸጋገር ዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ የገለጹ ሲሆን ጥናት አቅራቢዎቹንና የየክፍሉ ተወካዩችን በአውደ ጥናቱ በመገኘታቸው አመስግነዋል፡፡

የመጻሕትና የድምጽ ወምስል የምረቃ መርሐ ግብር ተካሔደ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋማት አስተዳደር ያሳተማቸውን መጻሕፍትና የድምጽ ወምስል የምረቃ መርሐ ግብር ሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም. በብሔራዊ ሙዚየም ትልቁ አዳራሽ አስመረቀ፡፡ ከተመረቁት መጻሕፍትና የድምጽ ወምስል ሥራዎች መካከል ዐስሩ የትርጉምና ወጥ መጻሕፍት ሲሆኑ በቪሲዲ እና በሲዲ የተዘጋጁ የአማርኛና የሞሮምኛ ስብከቶች ዘጋቢ ፊልሞች፣ ትርጉም ፊልሞችና መዝሙራት ይገኙበታል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም መርሐ ግብሩን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር በምረቃው ላይ የተገኙትን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችን በማመስገን ማኅበረ ቅዱሳን ከተሠረተ 20 ዓመታት አንስቶ ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ከተጠቀመባቸው መንገዶች ዋነኛው መንፈሳዊ ጋዜጣ መጽሔትና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን የተጻፉ መጻሕፍትንና የድምጽ ወምስል ውጤቶችን እያሳተመ ይገኛል፡፡ ከ1992 ዓ.ም. ጀምሮ የልማት ተቋማት አስተዳደርን በሥሩ በመመሥሪት ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ ለማድረግ የኅትመት ውጤቶችን በማሳተምና በማሰራጨት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ከኅትመት ከበቁት የድምጽ ወመስል ሥራወች መካከል ከእያንዳንዱ የተቀነጨቡ ክፍሎች የቀረቡ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲያንና ተርጓሚያን ከመጻሕፍቱ አንድ አንድ አንቀጽ አንብበዋል፡፡ በዲ/ን ታደለ ፈንታው በኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል አስተባባሪና በአቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ የልማት ተቋማት አስትዳደር ዳይሬክተር የመጻሕፍት ዝግጅት ክፍል እንቅስቃሴና የልማት ተቋማት አስተዳደር ልዩ ልዩ ክፍሎች ያከናወኗቸውን ተግባራት አጠር ያለ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

“የንስሓ ሸንጎ” የተሰኘ ወጥ መንፈሳዊ ልቦለድ የድርሰት ሥራቸውን ያቀረቡት ደራሲት ፀሐየ መላኩ ስለ ጥረታቸውና ሥራዎቻቸው ሲገልጹ አለማዊ ሕይወት መሠረቱና ማቃኛው መንፈሳዊ ሕይወት ነው ሁለቱንም ለማገናዘብ አጋጣሚው ነበረኝ ይላሉ፡፡ በተለይም አባታቸው ካህን ስለ ነበሩ ከለጅነት ጀምሮ መንፈሳዊ እውቀትን ለመቅሰም እድሉን አግኝተዋል፡፡ የኅብረተሰቡን ሕይወትና ፍላጎት፣ እምነት፣ ትዝብትና ገመና ላይ ያተኮሩ መጻሕፍትን ወደ ኅብረተሰቡ አድርሰዋል፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ አለማዊውን ሕይወት ማስተካከልና የተሟላ ስብእና ማግኘት እንደሚቻል ማስተማር ስለፈለግሁ “የንስሓ ሸንጎ” የተሰኘውን ወጥ መንፈሳዊ ድርሰት አቅርቤያለሁ ብለዋል፡፡ ሙሉ ጊዜያቸውን ለሥነ ጽሑፍ እንደሚሰጡና የኢትዮጵያዊው ታላቁ የሃይማኖት አርበኛ የሆኑት የቅዱስ ጴጥሮስን ታሪክ ለመጻፍ ጥረት በማድረግ  ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ሕልውና እንዳይቋረጥ አጋዥነቱን እያሳየ ስለሆነ ይህንን የጀመረውን ጉዞ ሌሎችንም ጸሐፍት የሚያበረታታ ስለሆነ ቢቀጥልበት በማለት አሳስበዋል፡፡ ደራሲት፣ ገጣሚት፣ ሰዓሊት ፀሐይ መላኩ “እመምኔት” የተሰኘ መንፈሳዊ ልቦለድ መጽሐፍ ከዚህ በፊት ከጻፏቸው መጻሕፍት መካከል አንዱ ሲሆን አሁን ደግሞ “የንስሓ ሸንጎ”ን ይዘው ቀርበዋል፡፡ በመጽሐፉ ዙሪያ በዲ/ን ታደለ ፈንታው መጽሐፍ ያተኮረባቸው መሠረታዊ ነጥቦት ላይ ትንታኔ ተሰጥቷል፡፡

ለምረቃ ከበቁት መጻሕፍት 3ቱን የጻፉት ዲ/ን ታደለ ፈንኀታው ስለ መጻሕፍቱ እንደገለጹት መጻሕፍቱ ነገረ ቅዱሳንን የሚያወሱ ናቸው፡፡ አስቀድሞ የነበሩ አባቶቻችን አሁን ያለው ትውልድ እየተፈተነበት ያለውን ሕይወት እግዚአብሔርን በመያዝ በመንፈሳዊ ሕይወት እንዴት እንደተመላለሱ ስለሚያሳይ ትውልዱ ራሱን እንዲጠብቅ ታላቅ መልእክት ያስተላልፋሉ ብዬ ስለማስብ ትኩረቴ ነገረ ቅዱሳን ላይ አድርጌአለሁ” ብለዋል፡፡

በመጻሕፍቱና በድምጽ ወምስል ሥራዎቹ ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በተለይም ማኅበረ ቅዱሳን ማተማያ ቤት ቢኖረው በኅትመትና ሥርጭት ረገድ አገልግሎቱን ማስፋፋት ይችል እንደነበር ተገልጿል፡፡ በተሰጡ አስተያየቶች ዙሪያ በማኅበረ ቅዱሳን የልማት ተቋመት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ደራሲያን የማተሚያ ቤት ሓላፊዎች ከተለያዩ ደራሲያን ማኅበራትና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡ የማኅበረ ቅዱሳን መዘምራንም ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበዋል፡፡

Tserha Tsion Sebakian wongel

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ሰባኪያነ ወንጌልን አስመረቀ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር በ14ኛው ዙር ለ3 ወራት ያሰለጠናቸውን 47 ሰባኪያነ ወንጌልን ሚያዚያ 21 ቀን 2004 ዓ.ም. አስመረቀ፡፡ በማኅበሩ የተመሠረተው የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የስብከተ ወንጌልTserha Tsion Sebakian wongel ማሰልጠኛ ተቋም በ12 የትምህርት ዓይነቶች ከጥር 21 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ ከ16 ሀገረ ስብከቶች በተለይም ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተውጣጥተው የተመረጡና እያንዳንዳቸው ከሁለት እስከ ሦስት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ሰባኪያነ ወንጌልን ቡራዩ አካባቢ በሚገኘው በተቋሙ ግቢ ውስጥ በደመቀ መንፈሳዊ መርሐ ግብር አስመርቋል፡፡ ከተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል መነኮሳት፣ ካህናት፣ መሪጌቶች፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አባላት ያካተተ ሲሆን ‹‹ለቤተ ክርስቲያናችን እጣን፣ ጧፍና ንዋያተ ቅድሳት ብቻ ሳይሆን ሰውም እንስጥ›› የሚል መመሪያ ይዞ በመነሣት በተለይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የመምህራን እጥረት ለመቅረፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ማናዬ አባተ የማኅበሩ መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እንዲሁም ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ የሊቃውንት ጉባኤ አባል ተገኝተዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ‹‹ማኅበሩ እያደረገ ያለውን ጥረት ለሌሎች አርአያ የሚሆንና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ደጋፊ አገኘች የምንልበት ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡ ለተመራቂ ደቀBitsu Abune Epiphanios መዛሙርትም “ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር እናንተን በወንጌሉ ቃል እንዳስታጠቃችሁ በሔዳችሁበትና በደረሳችሁበት ስፍራ ሁሉ የጠፉትን ወገኖቻችን የተበተኑትን አንድ በማድረግ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውለታ ለትመልሱ ይገባል” በማለት አደራቸውን አስተላልፈዋል፡፡ ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ተመራቂ ደቀ መዛሙርቱን ካስተማሩ አባቶች መካከል አንዱ ሲሆኑ ባስተላለፉት መልእክት “ግራኝ መሐመድ እንደተሸነፈ ልክ እንደዛሬው ማኅበረ ቅዱሳንና ማኅበረ ጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ ኖረው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ አፍሪካን ታጠምቅ ነበር፡፡” በማለት የማኅበሩን ጥረት አበረታተዋል፡፡

የማኅበሩ አባላት ልጆቻቸው ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ በማድረግ ረገድ በየሰንበት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት ላይ የሚሳተፉ ሲሆን በዕለቱ በመድረክ ላይ ያሬዳዊ ዝማሬን አቅርበዋል፡፡ ተመራቂ ደቀ መዛሙርትም አስር በሚደርሱ ቋንቋዎች ያሬዳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን የተማሩትን ትምህርት በተግባር ላይ እያዋሉ ስለመሆናቸው ምስክር ይሆን ዘንድ በአንድ ተመራቂ ደቀ መዝሙር ትምህርተ ወንጌል ተሰጠቷል፡፡

የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ከሰንበት ትምህርት ቤቶች የተወጣጡና በአንድነት በመኖር ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፊት ጽኑ አላማ ባላቸው ምእመናን የካቲት 23 ቀን 1980 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤትና ቀደም ሲል ከፍትህ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ ከፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኝ መንፈሳዊ ማኅበር ነው፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ የመለከት መጽሔትን በማሣተምና በማሰራጨት፤ በአካባቢው ለሚገኙ ረዳት ለሌላቸው አረጋውያንና ወላጅ አልባ ለሆኑ ሕፃናት የዕለት ምግብ በመስጠት፤ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስና የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ በማድረግ ፤አቅም ለሌላቸው በማኅበሩ ዘመናዊ ት/ቤት በአነስተኛ ክፍያ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

በጎ አድራጊ ምዕመናንን በማስተባበር ባለ ሁለት ፎቅ ዘመናዊ ሕንፃ በማጠናቀቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚካሔደውን የሰባኪያነ ወንጌል ሥልጠናን በአንደኛው ፎቅ ላይ በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ አስር የማደሪያ ክፍሎች ሲኖሩት በአንድ ዓመት በ2 ዙር እስከ 120 ደቀ መዛሙርትን ማሰልጠን ያስችላል፡፡ የመጸዳጃ ቤት፣ የገላ መታጠቢያ፣ የምግብ ማብሰያና በአንድ ጊዜ ከ500 ሰው በላይ ማስተናገድ የሚያስችል አዳራሽ የያዘ ነው፡፡ ስልጣገኞቹ ሙሉ የሕክምና ወጪ፤ የትምህርት መሣሪያዎች ድጋፍ በቀን 3 ጊዜያት የሚመገቡት ምግብ በማኅበሩ ይሸፈናል፡፡ ሕንፃው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ የቅዱስ ተክለ ሃይማኖት የሰባኪነ ወንጌል ማሰልጠኛ ተቋም በዓመት በ3 ዙር የሰባኪያነ ወንጌል ሥልጠና ለመስጠት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝና ማኅበሩ እስከ አሁን ድረስ በ14 ዙር ሥልጠናዎች 612 ሰባኪያነ ወንጌል ማሰልጠኑን መንፈሳዊ አገልግሎት መምሪያ ሓላፊው አቶ ማናዬ አባተ በሪፖርታቸው ገልጸዋል፡፡ ሠልጣናቹ የዘመናዊ ትምህርት ተማሪ ከሆኑ 10ኛ ክፍልና ከዚያ በላይ፣ የአብነት ተማሪ ከሆኑ በዘመናዊው ትምህርት ስድስተኛ ክፍልና ከዚያ በላይ የሆኑትን ከየሀገረ ስብከቱ የሚመረጡበት መስፈርት ሲሆን በተጨማሪም ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የወሰኑና የአካባቢውን ቋንቋ መስማትና መናገር የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡

ከደቡብ ኦሞ ጂንካ ሀገረ ስብከት አንቀጸ ብጹአን አቡነ ተክለ ሃይማሃት ቤተ ክርስቲያን የመጡት አባ ኃ/ሚካኤል በድሉ ከተመራቂ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ናቸው፡፡ “አካባቢያችን በመናፍቃን የተከበበ ነው፡፡ ምዕመናንም ሆኑ ካህናት ብዙ እውቀት የለንም፡፡ መናፍቃንን የምናሸንፍበት ትምህርት አጥተን ብዙዎች ተወስደውብናል፡፡ በሥልጠናው በነፃ የተቀበልነውን እውቀት በነፃ ለወገኖቻችን እናስተምራለን” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከምዕመናን መካከል ከጉጂ ቦረናና ሊበን ሀገረ ስብከት ሜጋ ቅዱስ ሚካኤል ሰበካ ጉባኤ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ተሰማ ርቀት ሳይገድባቸው እዚህ ድረስ የመጡት ከሚያገለግሉበት ቤተ ክርስቲያን ተመርጠው ለሰልጠናው የመጡትን ተመራቂ ደቀ መዛሙርትን ለመቀበል እንደሆነና አካባቢያቸውን አስመልክተው ባደረጉት ገለፃ “ያለንበት አካባቢ እጅግ ኋላ ቀር ነው፡፡ ኬንያ ድንበር ላይ ነው የምንገኘው፡፡ የአገልጋዮች እጥረት ያለበትና ቦታውም አመቺ ያልሆነ ነው፡፡ የጽርሐ ጽዮን ዘተዋሕዶ የአንድነት ኑሮ ማኅበር ደርሶልን ከጭንቅ እየገላገለን ነው፡፡ ወደፊትም ትብብራችሁ እንዳይለየን” በማለት ተማጽነዋል፡፡

ተመራቂ ደቀ መዛሙርት ከብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ እጅ የምስክር ወረቀትና መጽሐፍ ቅዱስ ተቀብለዋል፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ የደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ምክሐ ደናግል ማርያም ሰንበት ትምህርት ቤት በስጦታ የተገኘ ስለመሆኑ ከሓላፊዎቹ የተገለጸ ሲሆን  ደቀ መዛሙርቱን ለማፍራት በተደረገ ጥረት ውስጥ ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ሥልጠናውን ለሰጡ አካላት ማኅበሩ ምስጋናውን በእግዚአብሔር ስም አቅርቧል፡፡

የእግር ጉዞው መርሐ ግብር ተራዘመ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ  የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት ምስረታን ምክንት በማድረግ ለሚያዚያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም ተዘጋጅቶ የነበረው የእግር ጉዞ መርሐ ግብር ወደ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ተራዘመ፡፡ የመርሐ ግበሩ አስተባባሪ ሰብሳቢ ዲ/ን ዋሲሁን በላይ ቀኑ የተቀየረበትን ምክንያት እንደገለጹት የእግር ጉዞው በታቀደለት ጊዜ ለማካሔድ ከፍተኛ ጥረቶች መደረጋቸውን፤ በርካታ ቲኬቶችና ካናቴራዎችን ማሰራጨታቸውን፤ ነገር ግን ከምእመናን በተደጋጋሚ በቀረቡ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎች አንደኛ ከሰሙነ ሕማማት ጀምሮ በትንሳኤ በአል ምክንያት ምእመናን የተለያዩ ወጪዎችን ማውጣታቸውንና በጉዞው ላይ ለመሳተፍ ትኬቱን መግዛት ያለመቻላቸው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከትንሳኤ በአል በኋላ የቀኑ ማጠር፤ እንዲሁም በበአለ ሃምሳ ምክንያት የተለያ የማኅበራዊ ሕይወት ተሳትፎ ጎልቶ የሚታበት ወቅት በመሆኑ ቀኑ እንዲቀየርላቸው ከፍተኛ ግፊት በማድረጋቸው  ጥያቄያቸውን ተቀብለን የእግር ጉዞው መርሐ ግብር ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. እንዲሆን ተወስኗል ብለዋል፡፡ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም የተመረጠበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ምእመናን ከትንሣኤ በአል ጋር ተያይዞ ከማኅበራዊ ሕይወት ፋታ ያገኙበታል ተብሎ መታሰቡና ቅድስት ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው በዓላት አንዱ የጰራቅሊጦስ ዕለት በመሆኑ ቀኑን በአንድነት ሆነን እግዚአብሔርን እያመሰገንን እንድንውል በማሰብ ነው ብለዋል፡፡

ለምእመናን ባስተላለፉት መልእክት ዋናው የጉዞው ዓላማ የማኅበራችን 20ኛ ዓመት ምሥረታ ነው፡፡ በ20 ዓመታት ውስጥ ማኅበረ ቅዱሳን ብቻውን ያደረገው ምንም ነገር የለም፡፡ ከቅዱስ ፓትርርኩ ጀምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ ከቤተ ክርስቲያኒቱ የተለያዩ አካላትና ጽ/ቤቶች፤ ከሠራተኛ ጉባኤያት፤ ከሰ/ት/ቤቶች፤ በተለይም ከምእመናን ጋር በኅብረት ሰርተናል፡፡ አብረን ከተጓዝናቸው እሰካሁንም ደከመን ሰለቸን ሳይሉ በምክራቸው፤ በጸሎታቸው፤ በእውቀታቸው፤ በገንዘባቸውና በጉልበታቸው እያገለገሉ ካሉ አካላትና ምእመናን ጋር በኅብረት እግዚአብሔርን የምናመሰግንበት ቀን ነው፡፡ ቀጣይ ጊዜያችን ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ጠንክረን አብረን ተያይዘን ቅድስት ቤተክርስቲያናችን ከእኛ የምትፈልገውን አገልግሎት የምንፈጽምበት እንዲሆን ቃል የምንገባበት ዕለት ስለሆነ ምእመናን የተዘጋጀውን ቲኬት በመግዛት በእግር ጉዞው እንዲሳተፉና የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

 

በእግር ጉዞው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የመምሪያ ሓላፊዎች፤ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፤ ሰበካ ጉባኤያት፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ምእመናን ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ መንፈሳዊና ምእመናንን ሊያስተምሩ የሚችሉ መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተዋል፡፡

 

ጉዞው የሚደረገው፤ ወደ መንበረ ክብር ደብረ ታቦር ቅዱስ ሚካኤልና አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም ነው፡፡ የጉዞው መነሻ ቦታዎች፤ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፤ ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማዕከል /አምስት ኪሎ/ እና ሰሜን ማዘጋጃ ቶታል ናቸው፡፡

 

የጉዞው መነሻ ስዓት፤ ከጠዋቱ 1፡00 ስዓት ሲሆን ከምእመናን የሚጠበቁ ጉዳዮች በተመለከተ ለመንፈሳዊ ቦታዎች የሚመች አለባበስ መልበስ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የሩስያው ፕሬዝዳንት ለሀገራቸው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምስጋና አቀረቡ

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በስንሻው ወንድሙ

የሩስያ ፕሬዝዳንት ዴሚትሪ ሜድቬዴቭ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ ዜጎች ዘንድ መንፈሳዊ ሥርዐት እንዲጐለብት ለምታደርገው እንቅስቃሴ ከሁለት ሳምንት በፊት ምስጋና ማቅረባቸውን ዘ-ጋርዲያን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡

 

የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ 7 ባደረጉት ንግግራቸው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሕዝቦች ባሕልና ወጋቸውን ከሃይማኖት ሥርዐት ጋር ጠብቀው እንዲቆዩ ለአደረገችው አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውን ዘገባው አመልክቶ ፕሬዝዳንቱ «ይህን የሐሴት ቀን ከእናንተ ጋር በማሳለፌ ደስታ ተሰምቶኛል፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሃይማኖታዊ ሥርዐት እንዲሰፍን ለምታደርጉት እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ ሰላም እንዲሰፍንና መጪውን ትውልድ በበጐ ሥነ ምግባር ለመቅረጽ ለምታካሂዱት እንቅስቃሴ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እወዳለሁ» ሲሉ መናገራቸውንም ዘግቧል፡፡

 

ፕሬዝዳንቱ አክለው የበዓሉ መከበርና ሥርዐቱን የጠበቀ መሆን ለሰላምና ለመቻቻል እንዲሁም መንፈሳዊ እሴቶችን ከማጎልበት አንፃር አርአያ የሚሆን ተግባር ነው ማለታቸውን የዘገበው ጋዜጣ የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ ሕዝቦች ጠባቂ ናት ያሉት ፕሬዝዳንቱ ላለፉት በርካታ መቶ ዓመታት ጠብቃ ያቆየችውን የሀገር አንድነትን የመጠበቅ ሓላፊነት አሁንም አጠናክራ እንድትቀጥል መጠየቃቸውን ዘገባው አስፍሯል፡፡ በጉዳዩ ላይ ከቤተ ክርስቲያኗ የተሰጠ ምላሽ አልተካተተም፡፡

ለሩስያና ቡልጋርያ ግንኙነት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የበኩሏን እንድትወጣ ተጠየቀ፡፡

ግንቦት 3/2004 ዓ.ም.

በስንሻው ወንድሙ

ሩስያ ከቡልጋርያ ጋር ያላትን ዘርፈ ብዙ ግንኙነቶች በኦርቶዶክስ እምነት አባቶች በኩል ለማጠንከር የሀገሪቱ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ በቡልጋርያ ለሁለት ቀናት ጉብኝት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡

 

እንደ ዘጋርድያን ጋዜጣ ዘገባ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ክሪል ከቡልጋርያው አቻቸው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማክሲም ጋር ተገናኘተው ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ያላቸውን መልካም ግንኙነት በማጠንከር በሁለቱ ሀገራት መካከል የተፈጠረውን የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በድልድይነት በሚያገለግሉበት ላይ ውይይት አካሂደዋል፡፡

ፓትርያርክ ክሪል የቡልጋርያ ሁለተኛ ታላቅ ከተማ ፕሎቭዲቭ ሲደርሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምእመናን የተቀበሏቸው ሲሆን ከሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮዜን ፕሌቭንሊቭና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦይብ በሪስቭን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ ፓትርያርኩ በከተማዋ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ባደረጉት ንግግር «ከቡልጋርያ ቤተ ክርስቲያን መልእክተኞች ጋር ተገናኝተናል፡፡ ቀደም ሲል የኛ መልእክተኞችን ቡልጋርያ ለመላክ ችለናል፡፡ በዚህ የጠበቀ ኦርቶዶክሳዊ ወንድማማችነት በመፍጠር ችግሮችን ለማስወገድ ጥረት ላይ ነን» ሲሉ ፓትርያርክ ክሪል መናገራቸው ተጠቁሟል፡፡

 

በጉብኝታቸውም በደቡብ ቡልጋርያ የሚገኘውንና እ.ኤ.አ ከ1877-1878 በሩስያ ቱርክ ጦርነት እንዲሁም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለሀገራቸው የተሰውትን ሩስያውያን መካነ መቃብርን ጎብኝተዋል፡፡ ፓትርያርክ ክሪል በቡልጋርያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው ጉብኝታቸውን አስመልክቶና የሀገሪቱ ግንኙነት በሚጠናከርበት ላይ የሁለቱ ሃይማኖት አባቶች ሊያደርጉቸው የሚገቡ መሠረታዊ ነጥቦችን መጥቀሳቸውን ዘገባው ማስፈሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 

የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሀገሪቱ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የምታደርገውን እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ የሩስያ ኦርቶዶክስ በዓለም መድረክ ሊኖራት የሚገባውን ሥፍራ ለማጠንከርና የእምነቱ ተከታዮችን ለማጽናት ትልቅ እንቅስቃሴ ታደርጋለች፡፡ ቀደም ሲል ከሩስያው ፕሬዝዳንት ዴሞትሪ ሜድቬዴቭ ጋር በመሆን በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የሩስያ ቤተ ክርስቲያን ይዞታ በመጎብኘት ቅርሳቸውን በሚጠብቁበት ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

የእመቤታችን በዓለ ልደት ተከበረ፡፡

ግንቦት 2/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኖአምላክ

በየዓመቱ ግንቦት አንድ ቀን በልዩ መንፈሳዊ ድምቀት የሚከበረው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የልደት በዓል ትናንት በመላው ዓለም በሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት ተከብሮ ዋለ፡፡

 

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል አስተባባሪነት በማኅበሩ ሕንፃ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ አዳራሽ በተከናወነው የእመቤታችን የልደት በዓል መርሐ ግብር ከስድስት መቶ በላይ የሚሆኑ የማኅበሩ አባላትና ሌሎች ተጋባዥ ምእመናንም ተገኝተዋል፡፡ የእመቤታችንን በዓል ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀውን መልእክት የአዲስ አበባ ማዕከል ሰብሳቢ ዲ/ን አንዱ ዓለም ኀይሉ አቅርበዋል፡፡

“የእመቤታችንን በዓል መንፈሳዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በማክበር ከእመቤታችን በረከተ ረድኤትን ለማግኘት፣ ለመማማር ለመመካከርና አገልግሎታችንም የተቃና እንዲሆን በጸሎት ለማሳሰብ እንዲረዳን ጭምር ነው፡- በዓለ ልደታን እንዲህ ባለ መልኩ ያከበርነው” ሲሉ የገለጹት የአዲስ አበባ ማዕከል ጸሓፊ አቶ ካሳሁን ኀይሌ ናቸው፡፡

 

በጸሎተ ኪዳንና በመዝሙረ ዳዊት በተከፈተው ጉባኤ ላይ ትምህርት፣ የግንቦት ልደታን እንዴት እናክብር? በሚል ምክርና ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከአገልግሎት ባልተለዩ  አባላት አማካኝነት የሕይወት ተሞክሮ የቀረበ ሲሆን በዓሉን ምክንያት በማድረግ በእመቤታችን ስም የተዘከረ ጸበል ጸዲቅ ቀርቧል፡፡

 

የማኅበረ ቅዱሳንን ሃያኛ ዓመት ምሥረታና የእመቤታችንን በዓል በጋራ እያከበርን በምንገኝበት በዚህ ወቅት ለአባላት የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድር ነው? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ካሳሁን፡- የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና መንፈሳዊ ይዘቱን የጠበቀ የበዓል አከባበር እሴታችንን በመጠበቅ ወደፊትም ማዕከሉ ተመሳሳይ መርሐ ግብራትን እንደሚያዘጋጅ ገልጸው፥ ምእመናንም በያሉበት ይህንኑ በጎ ትውፊት እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡

001

የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ጉባኤ ተካሄደ

ግንቦት 2/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኩኖአምላክ

001በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደቡብ ክ/ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ዓመታዊ ጉባኤውን ሚያዚያ 23 ቀን 2004 ዓ.ም. አካሂዷል፡፡ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተከናወነው በዚሁ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ላይ፡- በክፍለ ከተማው የሚገኙ 32 ሰንበት ትምህርት ቤቶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በጉባኤው ላይ ተገኝተው ትምህርተ ወንጌል የሰጡት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ ክቡር ቆሞስ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው ናቸው፡፡

የመምሪያ ሓላፊው “ልጄ ሆይ ሰው ሁን” በሚል ርዕስ ባስተማሩት ትምህርት ላይ “ የሰንበት ትምህርት ቤቶች የአንድነት ጉባኤ በየዓመቱ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ ይህንን ጉባኤ ማካሄዳችን በየሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን ያሉብንን ችግሮች ለማስወገድና በቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴ የበኩላችንን እገዛ ልናደርግ እድል ይፈጥርልናል፡፡ በየሰንበት ት/ቤቱ የሚገኙ ልጆቻችንም ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከብፁአን አባቶቻችን ቡራኬና ትምህርት የሚቀበሉበት መርሐ ግብር ይሆናል በአጠቃላይም ይህን ጉብኤ ለማዘጋጀት የማደራጃ መምሪያው ድጋፍ አይለየውም” ብለዋል፡፡

 

የክፍለ ከተማው ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምክትል ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ዘሪሁን መኮንን በጉባኤው ላይ ባቀረበው ሪፖርት ሰንበት002 ትምህርት ቤቶቻችን በየዓመቱ የደመራ በዓልን ለማክበር በአደባባይ ከመሰባሰብ ውጪ መንፈሳዊ አንድነት ፈጥረው እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነት ሊያበረክቱት የሚገባቸውን ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከት ሳይቻላቸው በርካታ ጊዜያት ማለፋቸውን አስታውሶ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ግን የተጠናከረና ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በእኩል ሊያሳትፍ የሚችል መተዳደሪያ ደንብ መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡

 

ከዚህ በተጨማሪ በክፍለ ከተማው የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ኅብረታቸውን በመጠበቅ የጋራ ዕቅዳቸውን ለማሳካት አገልግሎታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጿአል፡፡ ም/ሰብሳቢው በክፍለ ከተማው የተሠሩ ሥራዎችን ሳያብራራ፡- በሁሉም ሰንበት ትምህርት ቤቶች ያሬዳዊ ዝማሬን ለማስጠናት የሚችሉ የአሰልጣኞች ሥልጠና ለሦስት ዓመታት ተካሂዷል” ብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መምህራንን በማፍራቱና በማሰልጠን ረገድ በ3 ጊዜያት ቁጥራቸው ከ146 በላይ አባላትን ማስተማሩንና በተመሳሳይ መልኩ ከልዩ ልዩ አድባራት የተውጣጡ መምህራን የሰጡትን የአብነት ትምህርት በሚገባ የተከተሉ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ሥልጣነ-ክህነት እንዲቀበሉ ማድረጉን አስረድቷል፡፡ የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን አንድነት ለመመሥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ የሚገኘው ክፍለ ከተማው የተሃድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴን የመከታተል ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ፣ እንዲሁም ለሰንበት ትምህርት ቤቶች የአስተዳደርና ሒሳብ አያያዝ ሥልጠና መስጠቱን ገልጿል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ “ድንግል ሆይ ብረሳሽ” የተሰኘ መነባንብ፣ እንዲሁም “ሰንበት ት/ቤት” የሚል ግጥም ቀርቧል፡፡

 

ከጉባኤው በኋላ የክፍለ ከተማው ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሰብሳቢ የሆነው ወጣት ሳሙኤል እሸቴን “የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማኅበር አወቃቀሩ ምን ይመስላል?” ስንል ላቀረብንለት ጥያቄ ምላሽ ሲጠጥ “….በሥራ አስፈፃሚ ደረጃ የተዋቀረ ተጠሪነቱም ለአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት የሆነ የአገልግሎት ክፍል አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዘጠኝ የአገልግሎት ክፍሎች አሉ፡፡ እነኚህን ለማገዝ በክፍለ ከተማችን የሚገኙ 32 ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በ4 ምድብ በመክፈል እየተናበቡ ተግባራትን እንዲያስፈጽሙ እያደረግን እንገኛለን፡፡ ይህንንም ለማገዝ በማደራጃ መምሪያው መልካም ፈቃድና እገዛ በመካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን አንድ ቢሮ ተሰጥቶናል” ብሎናል፡፡

 

003ወጣት ሳሙኤል ከዚሁ ጋር አያይዞ ሚያዝያ 23 ቀን 2004 ዓ.ም. ስለተከናወነው መርሐ ግብር በተመለከተ ሲናገር “የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቀን በሚል ርእስ በየዓመቱ የሚከናወነው መርሐ ግብር ዘንድሮ ለ4ኛ ጊዜ የተከናወነ ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች በአንድነት በአንድ ጉባኤ ተሰብስበው የመማራቸው ፋይዳው፡-

 

የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ለእናት ቤተ ክርስቲያን ሊያበረክቱ የሚገባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል፤ በቅርቡም በዝቋላ የአቡነ ገ/መንፈስ ቅዱስ ገዳም ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ለማጥፋት እርስ በርስ ተጠራርተው መሄዳቸውና ያንን የመሰለ አስደናቂ ተግባር ፈጽመው መመለሳቸው የመገናኘቱ ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል የማደራጃ መምሪያችን ሓላፊ ቆሞስ አባ ኅሩይ ወንድ ይፍራው በጉባኤያችን ላይ ተገኝተው በየክፍለ ከተማው የሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ቢያንስ  በዓመት ሁለት ጊዜ ትምህርትና ቡራኬን ከብፁዓን አባቶች መቀበል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ በሰላሳ ሁለቱ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ምን ያህል አባላት አሉ? የሚል ጥያቄ ያቀረብንለት ወጣት ሳሙኤል “በግምት ከ20 እስከ 30ሺ የሚደርሱ አባላት አሉን፡፡ በቅርቡ ግን በእያንዳንዱ ሰንበት ትምህርት ቤት ምን ያህል አባላት እንደሚገኙ በዕድሜአቸው በትምህርታቸው /በሙያቸው/ እንዲሁም በሌላ አስፈላጊ መረጃዎች የተጠናከረ መረጃ /ዳታ/ የማሰባሰብ ሥራ እንጀምራለን፡፡ ይህም ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል ያልተነካ የሰው ኃይል በሰንበት ትምህርት ቤቶቿ እንዳላት መረጃ ይሰጣልና፡፡”

 

በስተመጨረሻ የደቡብ ክፍለ ከተማ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በመወከል ማስተላለፍ የምትፈልገው ነገር ካለህ? ተብሎ የተጠየቀው ወጣት ሳሙኤል፡፡

 

“የሰንበት ትምህርት ቤቶቻችን በአብነት ትምህርት ላይ ትኩረት አድርገው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአብነት ትምህርት ጉዳይ ለነገ የሚባል ሳይሆን ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የነገ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ ትውልድ የሚፈሩባቸው ከመሆናቸው አንፃር በትክክል የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርት ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተናጠል ከመሥራት ወጥተን /የአንዲት ርትዕት ቅድስት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በመሆናችን/ በአንድነት የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማፋጠን መሥራት ይኖርብናል፡፡ በመጨረሻ በሰንበት ትምህርት ቤቶች የምንገኝ ወጣቶች ሁላችን ሀገራዊ ራእይ ሃይማኖታዊ አቋምን አጠናክረን ልንይዝ ይገባናል” ብሏል፡፡