kidus estifanos

ቅዱስ እሰጢፋኖስ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ አስተምህሮ

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ
ዳር 17/2004 ዓ.ም

ስለ ቅዱስ እስጢፋኖስ  ክፍል አንድ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

 

አይሁድን ቀርቦ ለመረመራቸውም አሕዛብ ከሆኑት ከፋርስ ወገን እንደሆኑ እንዲሁም አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ተአምራትን ሳይሻ ለእግዚአብሔር መከራዎቹን ሁሉ ታግሦና ተቋቁሞ የተመላለሰው እንደሆነ እግዚአብሔር ልጁ እንደሚያደርገው፣ እንዲሁም የሁሉ አባት አብርሃም እንዳደረገው የአባቶችን መቃብርና ያለንን ሁሉ በመተው ልንታዘዝ እንደሚገባንም ጠቁሞናል ፡፡

kidus estifanos

የአብርሃም አባትና ዘመዶቹ ምንም እንኳ ረጅም ጉዞ ከአብርሃም ጋር ቢጉዋዙም ከንዓንን ይወርሱ ዘንድ የተገባቸው ካልሆኑ ልጆቹስ ላይ እንዴት ይህ እጣ ፈንታ አይደርስባቸው ይሆን? “ነገር ግን ልጅ ሳይኖረው ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ ተስፋ ሰጠው፡፡” አለ፡፡ በዚህ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስጦታንና የአብርሃምን እምነት ታላቅነት እንመለከታለን፡፡ “ልጅ ሳይኖረው” የሚለው አገላለጽ የእርሱን በእምነት መታዘዝን የሚገልጥ ነው፡፡ “ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ ርስት አድርጎ ይሰጠው ዘንድ”የሚለው በድርጊት ከታየው ጋር ስናነጻጽር የተቃረነ መስሎ ይታየናል፡፡ ምክንያቱም አስቀድሞ “በዚችም የእግር ጫማ ስንኳ የሚያህል ርስት አልሰጠውም” እንዲሁም ልጅም አልነበረውም ይለናልና፡፡ እነዚህ ዐረፍተ ነገሮች አብርሃም በእምነቱ ከተሰጠው ጋር የሚጣጣሙ ላይመስሉን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሊሰጥ ያሰበውን ያንኑ ነው የሚሰጠው፡፡ በዚህ ቦታ ግን ቃሉና ድርጊቱ የተቃረኑ ይመስሉናል፡፡ ነገር ግን እንደ እኛ አስተምህሮ ፈጽሞ የሚጣረሱ አይደሉም፡፡ እንደውም ፈጽመው የሚጣጣሙ እንጂ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በዚህ እንደምንደክም ነገር ግን እረፍታችን በላይ በሰማይ እንደሆነ አስተምሮናል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ እስጢፋኖስ እንዲህ አለ፡፡

 

“ስለምን የተስፋው ቃል እንደተፈጸመ እናስባለን ? ስለምን ነገሮችን እናምታታቸዋለን? በዚህም ምድር መከራን ተቀበላችሁን? በድህነት ለመኖር ተገደዳችሁን? አዘናችሁን? በዚህ አትጨነቁ፡፡ ስለ ክርስቶስ ስትሉ በዚህ ምድር የምትቀበሉት መከራ በሚመጣው ዓለም ዕረፍት ያሰጣችኋል፡፡ የዚህ ምድር መከራችሁ ለዘለዓለማዊ ዕረፍታችሁ ምክንያት ነው፡፡ “ይህ ሕመም” ይልና “የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለእግዚአብሔር ክብር ነው ለሞት አይደለም”ይለናልና (ዮሐ.11፡ 4) በሚመጣው ዓለም የምንቀበል ከሆነ ፍርዱ ነው፤ ነገር ግን በዚህ ምድር የምንቀበለው መከራ የምንማርበትና የምንታረምበት መከራ ነው፡፡ ፍልሚያው በዚህ ምድር ነው ኃጢአትን ደምን እስከማፍሰስ ደርሶ መዋጋት የእኛ ድርሻ ነው፡፡ ጦርነቱ በዚህ በምድር እንጂ በሰማያት አይደለም፡፡ በውጊያ ላያ ያለ ወታደር ዕረፍትን ሊሻት አይገባም፡፡ በውጊያ ሰፈር እንደንጉሥ የቅምጥልንነት ሕይወትን ሊኖር አይገባውም፣ ሀብትን ለመሰብሰብ ወይም ስለቤተሰቡ በማሰብ ሊጨነቅ አይገባውም፡፡ አንድ ወታደር ውጊያው ላይ ብቻ ሊያተኩር ይገባዋል፡፡ እርሱም በጠላቴ ላይ እንዴት ድልን ልቀዳጅ እችላለሁ የሚለው ነው፡፡ በዚህ ምድር ስንኖር ስንቃችን ይህ ይሁን፡፡ እንዲህ ከሆነ በጠላት ተሸንፈን ከሆነ ተመልሰን ድል እንነሣዋለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ሁሉን የጦር ትጥቆች አስታጥቆናል፡፡ ጠላታችንን ዲያብሎስ እንዴት ድል መንሣት እንችላለን የሚለው ብቻ የእኛ ግብ ይሁን፡፡ እንዲህ የምናስብ ከሆነ ልምምዳችንም ይህ ይሆናል፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋም ይህን እንድናከናውን የድርሻውን ይወጣል፡፡ ስለዚህም እንዴት የሚረዳንንም የእግዚአብሔር ጸጋ ማቅረብ እንደምንችል እንወቅበት፡፡ እንዲህ ከሆነ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል” (ሮሜ.8፡31) አንድ ነገር ብቻ የእኛ ልምምድ ይሁን እርሱም እግዚአብሔር አምላክ የእኛ ጠላት በመሆን ፊቱን ከእኛ እንዳይመልስ ነው፡፡


መከራን በመቀበላችን ክፉ ደረሰብን ብለን አንመረር፤ ነገር ግን ኃጠአትን በፈጸምን ወቅት መከራ እንደመጣብን እንቁጠር፡፡ ይህ ነው መራሩ መከራ፡፡ እኛ ግን በዚህም ምድር ኑሮአችንን በቅንጦት እያሳለፍን የሚመጣውን ዓለም ሕይወት ለመስበክ አንሻም፡፡ እንዳውም በሚመጣው ዓለም የምንኖረው እንዲህ ዓይነት ሕይወት እንደሆነ እናስተምራለን፡፡ ሕሊናችን እንዴት በኃጢአት እንደተጨማለቀ እስቲ ቆም ብለን እናስብ ፡፡ ይህ ከሌሎች ቅጣቶች ይልቅ አጅግ ከባዱ ቅጣት አይደለምን?

 

በኃጢአት ሕይወት ለሚመላለሱ ወገኖች ምንም እንኳ የራሳቸውን ኃጢአት የማያስተውሉ፣ ስለጽድቅ መከራን ለመቀበል ለሚሰቀቁ ነገር ግን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ለሚኖሩ … አንድ ጥያቄ ላንሣ፡፡ በወዲያኛው ዓለም ዕረፍትን ማግኘት ትፈልጋላችሁን? በዚህ ምድር ስለክርስቶስ ስትሉ መከራን ተቀበሉ፡፡ ይህን የመሰለ ዕረፍት ፈጽሞ አታገኙም፡፡ ሐዋርያት ስለክርስቶስ ሲሉ በተቀበሉት መከራ ደስተኞች ነበሩ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን አስመልክቶ “በጌታ ደስ ይበላችሁ” (ፈልጵ.4፡4) አለ፡፡ እየታሰሩ እየተገረፉ በሸንጎ ፊት እየቀረቡ እንዴት ነው ደስ ሊላቸው የቻለው? ሁሉም ደስተኞች ነበሩ ይላልና፡፡ እንዴት እንዲህ ደስ ሊላቸው ቻለ ብለህ ጠይቅ፡፡ እንዴት ደስ ላይላቸው ይችላል፡፡ ሕሊናቸው እኮ ከኃጠአት ንጹሕ ነው፡፡ ስለዚህ እጅግ ልዩ በሆነ ደስታ ውስጥ ይዋኛሉ፡፡ መከራቸው በበዛ ቁጥር እንዲሁ ደስታቸውም ከመከራቸው እጥፍ ይጨምርላቸው ነበር፡፡

 

አንድ ወታደር በጦር ሜዳ ደጋግሞ ቢቆስልና ወደቤቱ በድል አድራጊነት ቢመለስ ደስታው ታላቅ አይሆንምን? በጦር ሜዳ ስለመዋሉ ቁስሉ በግልጥ አይናገርምን? ለትምክህቱስ ምስክር አይሆኑለትምን? አንተም ልክ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በደስታ “እኔ የኢየሱስን ማኅተም በሥጋዬ ተሸክሜአለሁ”(ገላ.6፡17) ለማለት የበቃህ እንድትሆን ዘንድ ስለክርስቶስ መከራን ለመቀበል አትሰቀቅ እንዲህ ያደረግህ ከሆነ ደስታህ እጅግ ታላቅ በክብር ያጌጠ ይሆናል፤ በአምላክም ዘንድ የታወቅህ ትሆናለህ፡፡

 

ለክብር የማያበቃህ መከራ የለም ስለዚህም አንድ ሰው በአንተ ላይ በጠላትነት ቢነሣብህ ክርስቶስን አስበህ ክፉ ቃል እንዳትናገር ፍራ፤ እናም የትዕቢትን አገዛዝ በጽናት ተቋቋመው፤ ቁጣንና ሴሰኝነትንም በጽናት ተቃወማቸው፡፡ እነዚህ ለአንተ እንደ ማኅተም ናቸው፡፡ እነዚህ ለአንተ እንደግርፋት ናቸው፡፡ አንድ ነገር ልጠይቃችሁ የትኛውን ነው የከፋው ግርፋት የምትሉት? ነፍስ በገሃነም እሳት የምትገረፉትን መገረፍ አይደለምን? በዚህ ምድር መከራ ብንቀበል በሥጋችን ነው፡፡ ነገር ግን በሚመጣው ነፍሳችንም ሥጋችንም ነው መከራ የሚቀበሉት፡፡

 

ሁሉም ክፋቶች ከነፍስ ይመነጫሉ፡፡ አንድ ሰው ቢቆጣ ቢቀና እኒህን የሚመሰሉ ክፋቶችን ቢፈጽም በነፍሱ ላይ ስቃይን እያመጣ ነው፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ክፋቶች ወደ ድርጊት የተመለሱ ባይሆኑም መቆጣትና ቅናት አንዲሁም እነዚህን የመሰሉ ሁሉ ኃጢአቶች ናቸው፡፡ በእርግጥም ቁጣና ቅናት ነፍስን የሚያቆስሉና የሚጎዱ መከራዎችም ናቸው፡፡ ስለዚህም ተቆጥተህ እንደሆነ በመከራው ውስጥ ራስህን እንደጣልህ ቁጠር፡፡ እንዲህ ከሆነ የማይቆጣ ሰው ራሱን መከራ ውስጥ አልጣለም ማለት ነው፡፡

 

የተሰደበ ሰው መከራን በነፍሱ እየተቀበለ ነው ብለህ ታስባለህን ? አይደለም ነገር ግን ከላይ እንዳስተማርኩት ተሳዳቢው በነፍሱ መከራን እየተቀበለ ነው፡፡ ስለዚህም እነዚህ ነገሮችን መፈጸም አንድ ሰውን ኃጠአተኛ የሚሰኙት ከሆነ መከራ አለበት ማለት ነው፡፡ ስለዚህም መከራ እየተቀበለ ያለው ተሰዳቢው ሳይሆን ተሳዳቢው መሆኑን መረዳት ይቻለናል፡፡

 

አንተ “እርሱን ልጄን ሞኝ ብሎ ተሳድቦአል” ልትል ትችላለህ፤ ነገር ግን አንተ ለስድቡ አጸፌታውን በመመለስ በበደል እርሱን አትምሰለው፡፡ አንድ ነገር እጠይቅሃለሁ ይህ ሰው መልካም ነገር አደረገን? አንተ እርሱ መልካም አድርጎአል አትልም፤ ስለዚህም እርሱ የፈጸመው መልካም ካልሆነ አንተ እርሱ የፈጸመውን ከማድረግ በመከልከል መልካምን አድርግ፡፡ ልጅህ በመሰደቡ ምን ያህል ቁጣ በውስጥህ እንደሚቀጣጠል እረዳለሁ፡፡ ነገር ግን አንተ “ እርሱ ልጄን የሰደበ ከሆነ እንዴት ነው ይህን ሰው እኔንም ከመሳደብ የሚመለሰው? ብለህ ትጠይቅ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያደረገውን ሰው በትሕትና ገሥጸው፣ ምከረው ብዬ እመክርሃለሁ፡፡ ትሕትና ቁጣ አንዱ ካንዱ የሚቃረኑ ጠባያት ነው፡፡ በትሕትና ቁጣን ማብረድ ይቻልሃል፡፡

 

በእኛ ላይ ክፉ ስለተፈጸመብን በምላሹ እኛም ክፉን ልንፈጽም አይገባንም ነገር ግን ስለሌሎች መዳን ስንል መልካምን ልናደርግ ይገባናል፡፡ ልጅህ በመሰደቡ ምክንያት ራስህም እንደተሰደብክ አድርገህ አትቁጠር፡፡ በእርሱ ምክንያት አንተ ልትቆጣ ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ላትሳደብም ትችላለህ፡፡ ልጅህ በመሰደቡ ምክንያት የአንተም ክብር እንደተነካ ልትቆጥር ትችላለህ፡፡ ነገር ግን ነገሩን ስናስተውለው ልጅህ የሰደበው እንጂ የሚጎዳው ልጅ ወይም አንተ አትጎዱም ክብርህም አይዋረድም፡፡

 

ስለዚህም እንደ ሰይፍ የሰላውን የቁጣ ሰይፍህን ከሰገባው ውስጥ መልሰው፡፡ ነገር ግን የቁጣ ሰይፋችንን ብንመዝና ያለጊዜዋ ብንጠቀምባት በእርሱ ተይዘን እኛም እንጠፋለን፡፡ ነገር ግን ቁጣችንን በውስጣችን ይዘን ትዕግሥትን የተላበስን ከሆነ ግን ቁጣው ይከስምልናል፡፡ ክርስቶስ በእርሱ ምክንያት ወደ ቁጣ እንዳንገባ አሳስቦናል፡፡ ጌታችን ለቅዱስ ጴጥሮስ ምን እንዳለው ስማ “ሰይፍ የሚያነሣ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋልና ሰይፍህን ወደ ስፍራው መልስ፡፡”(ማቴ.26፡52) አለ፡፡ አንተ ስለልጅህ መነቀፍ ትቆጣለህን? ስለዚህም ልጅህን ምክንያታዊ እንዲሆን አስተምረው፡፡ ስለእርሱ የደረሰብህን ሕማም ንገረው እንዲህ አድርገህ መምህር ክርስቶስን ምሰለው፡፡

 

እርሱ በደቀመዛሙርቱ ላይ መከራ ያጸኑባቸውን ወገኖች “እኔ እበቀላቸዋለሁ አላለም” ነገር ግን “በእኔ እንዳደረጉት በእናንተም ላይ ይፈጽማሉና በትዕግሥት ተቀበሉ፡፡ እናንተ ከእኔ አትበልጡምና” ነበር ያላቸው፡፡ አንተም ለልጅህ አንተ ከጌታችን አትበልጥም ብለህ ልትነግረው ይገባሃል፡፡

 

ይህ መንፈሳዊ ፍልስፍና የአሮጊቶች ተረት ሊመስለን ይችላል ፡፡ በቃል ሰዎችን ከጥፋት ከመመለስ ይልቅ በድርጊት ሰዎችን መመለስ እጅግ ታላቅ ጥበብ አይደለምን? አሁን አንተ በመሃል ቆመሃል፡፡ መከራ ከደረሰባቸው ወገን እንጂ መከራን ከሚያደርሱት ወገን አትሁን፡፡ መከራ ከሚደርስባቸው ወገን በተግባር ካልሆንክ እነርሱ ከሚያገኙት የድል አክሊል ውጪ ትሆናለህ፡፡

 

እግዚአብሔር አምላክህ ቃየንን ስለ ወንድሙ አቤል እንዴት ብሎ በትሕትና እንደጠየቀውና ቃየንም እግዚአብሔር አምላክህን እንዴት ብሎ በንቀት ቃል እንደተናገረው ተመልከት እርሱ “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው” ሲለው ቃየን ደግሞ በምላሹ “አላውቅም እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” ብሎ ነበር የመለሰው፡፡ (ዘፍ.4፡9)ከዚህ መልስ በላይ እጅግ ጸያፍ የሆነ መልስ ምን አለ? ከእናንተስ መካከል እንዲህ ዓይነት ጸያፍ የሆነ መልስን ልጁ ቢመልስለት የሚታገሥ አባት ማን ነው? ከወንድሙስ ቢሰማ እርሱን እንደ ሰደበው አይቆጥርበትምን ? ጌታችን ግን እንዲሀ አላደረገም ነገር ግን በትሕትና ቃል መልሶ ”ምን አደረግህ? የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል፡፡” ብሎ ጠየቀው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ከቁጣ በላይ ነው ልትል ትችላለህ፡፡ ትክክል ብለሃል ነገር ግን እንደ ችሎታህ መጠን በጸጋ አምላክ ትሆን ዘንድ ስለአንተ ሲል የእግዚአብሔር ልጅ ሰው ሆኖአል፡፡

 

ነገር ግን ከእናንተ መካከል አንዱ “እኔ ሰው ነኝ አንዴት አምላክ ልሆን እችላለሁ ?ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ደህና! ምሳሌ የሚሆኑህን ሰዎች ልጥቀስልህ ስለ ጳውሎስ ወይም ስለ ጴጥሮስ የምናገር አድርገህ አታስብ፡፡ ከእነርሱ በእጅጉ ያነሰውን ሰው እንደምሳሌ አንሥቼ ላስረዳህ ካህኑ ኤሊ የሳሙኤልን እናት ሃናን “ስካርሽ እስከመቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው፡፡” (1ሳሙ.1፡14) ብሎአት ነበር፡፡ ከዚህ የከፋ የነቀፋ ቃል ምን አለ? ነገር ግን እርሱዋ ምን ብላ መለሰች “ጌታዬ ሆይ አይደለም፣ ጌታ ሆይ እኔ ልቡዋ ያዘነባት ሴት ነኝ” ብላ መለሰችለት በእርግጥ በእርሱዋ ላይ የተሰነዘረው የነቀፋ ቃል እርሱዋ ከምትጓጓለት ጋር የሚሰተካከል አልነበረም፡፡ እርሱዋ ለእውነተኛው መንፈሳዊ ፍልስፍና እናቱ ነበረች፡፡ እቺ ሴት ጣውንት ነበረቻት ነገር ግን እርሱዋን አንድም ቀን ተናግራት አታውቅም ነበር፡፡ ነገር ግን ወደ እግዚአብሔር ተጠጋች፡፡ በፀሎቱዋ ስሙዋን እያነሣች ስለስድቡዋ እግዚአብሔር ይቀጣላት ዘንድ አለመነችውም፡፡ እቺ ሴት አጅግ ድንቅ የሆነች ሴት ነበረች፡፡ እርሰዋን ተመልክተን ወገኖቻችንን በእግዚአብሔር ፊት የምንካሰስ እንፈር፡፡ እንደ ቅናት ብርቱ የሆነ ነገር እንደሌለም አንተ ታውቃለህ ነገር ግን እርሱዋ ቅናት ድል ነስቶአት በጣውንቷ ላይ በጠላትነት አልተነሣችም ነበር፡፡

 

ቀራጩ በፈሪሳዊው ሰው ሲንጓጠጥ እየሰማ እርሱም በምላሹ የስድብን ቃል አልተናገረውም፡፡ እንዲህ ማድረግ አቅቶት ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ልክ እንደ ጥበበኛ ሰው በምስጋና በመቀበል ስለራሱ ግን “አምላክ ሆይ እኔ ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር፡፡” ለመነ (ሉቃ.18፡13) ሜምፊቦስቴ ምንም ክስና ውንጀላ በባሪያው ቢቀርብበትም በባሪያው ላይ ምንም ክፉ ነገር ወይም ቃል ሊናገርው አልፈቀደም ነበር፡፡ በንጉሥ ዳዊት ፊት እንኳ ሊወቅሰው አልፈቀደም፡፡ (2ሳሙ.19፡26)

 

ድንቅ የሆነ ፍልስፍናን ስለተላበሰችው ስለዘማዊቱዋ ሴት ደግሞ ልንገርህን? ክርስቶስ እግሮቹን በእንባዋ አርሳ በጠጉሮቹዋ ስለአበሰችው ሴት ምን ብሎ አስተማረ “እውነት እላችኋለሁ ቀራጮችና ጋለሞቶች ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በመግባት ይቀድሙአቸዋል” (ማቴ.21፡31)ብሎ አላስተማረምን? እርሱዋ የቆመችበትን ቦታ፣ ጽናቱዋን እንዲሁም ኃጢአቱዋን እንዴት አጥባ እንዳስወገደች አታስተውልምን? በፈሪሳዊው ስምዖን እንዴት ተብላ ስትነቀፍ እንደነበር አስተውል፤ ስምዖን “ይህስ ነቢይ ቢሆን ይህች የምትዳስሰው ሴት ማን አንደሆነች እንዴትስ እንደነበረች ባወቀ ነበር፡፡”(ሉቃ.7፡39) ሲላት “ አንተስ ማነህና አንተ ከኃጢአት ንጹሕ ነህን ? ብላ መልስ አልሰጠችውም፡፡ ነገር ግን ራሱዋን በጌታዋ ፊት ይበልጥ አዋርዳ አብዝታ አለቀሰች ትኩስ የሆነው እንባዋንም በጌታዋ እግር ላይ እንዲፈስ ፈቀደች፡፡

 

ሴቶች፣ ቀራጮች፣ አመንዝሮች ጥምቀት ሳትሠራ በፊት እንኳ መንፈሳውያን ፈላስፎች ሆነው ከሆኑ፤ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋዎች የተሰጣችሁ እናንተ እርስ በእርሳችሁ ከአራዊት በከፋ መልኩ እርስ በእርሳችሁ በመፋጀታችሁ፣ አንዱ አንዱን በማሳዘኑና በመምታቱ እንዴት የባሰ ፍርድ አይጠብቃችሁ ይሆን? ከቁጣ በላይ የሚከፋ፣ የሚያዋርድ፣ የሚያስፈራ፣ የሚያሳዝን፣ የሚጎዳም ምንም የለም፡፡

 

ይህን በውጭ ላሉ ሰዎች የምናሳየው ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ሚስታችን ተናገሪ ከሆነች ለእርሱዋም ይህን ትዕግሥት ልናሳያት ይገባናል፡፡ ሚስትህ ለአንተ ቁጣን ከሰውነትህ የምታስወግድባት ትምህርት ቤትህ ትሁን፡፡ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ታጋሽ ሁን ሥጋን ብቻ ለሚጠቅም ነገር ታጋሾች ለመሆን ልምምዶችንና ጽኑ የሆኑ መከራዎችን የምንቀበል ስንሆን ነገር ግን ይህን ትዕግሥት በቤታችን የማንፈጸመው ከሆነ ማን ነው የድሉን አክሊል በራሳችን ላይ ሊደፋልን የሚችለው? ሚስትህ ትሰድብሃለችን? እርሱዋን መልሰህ በመሳደብ አንተው እርሱዋን አትምሰላት፡፡ ራስን ከክብር ማሳነሥ የነፍስ ደዌ ነው፡፡ ሚስት ስትሰድብህ አንተ እርሱዋን መልሰህ መሳደብ የተገባ እንዳልሆነ ልብ በል፡፡ በተቃራኒው አንተ እርሱዋን አየተሳደብኽ እርሱዋ የታገሰች ከሆነም ከዚህ የሚበልጥ ውርደት የለም፡፡ እናም እርሷ አንተን በመስደቡዋ የማይገባና የሚያዋርድ ነገርን በመናገርህ በራስህ ላይ የባስ ፍርድን ታመጣለህን፡፡ እርሷ ስትሳደብ ብትታገሣት ግን ያንተን ጽናት ታላቅነት ማረጋገጥ ትችላለህ፡፡ እንዲህ ስል ግን ሚስቶች ተሳዳቢዎች ይሁኑ ማለቴ ግን አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ይህን ማለትን ከእኔ ያርቅ፡፡ ነገር ግን በሰይጣን ግፊት ይህ ተፈጽሞ እንደሆነ እንዲህ አድርጉ ማለቴ ነው፡፡ የሚስትን ድክመት መሸከም የባል ድርሻ ነው፡፡

 

ሠራተኛህ ከአንተ ጋር ቢጋጭ በጥበብ ታገሠው፡፡ ለእርሱ ማድረግ የሚገባህን ወይም መናገር የሚገባህን አትናገር ማለቴ ግን አይደለም፡፡ ነገር ግን ከአንደበትህ በእርሱ ላይ የነቀፋ ቃል አይውጣ፡፡ ሴትን ልጅ የሚያዋርድ ንግግርን አትናገራት፡፡ አገልጋይ ሠራተኛህን በንቀት ቃል አትጥራው፡፡ እንዲህ ብታደርግ ግን እርሱን እያዋረድካት አይደለህም ራስህን እንጂ፡፡

 

ቁጡ ሰው ሆኖ ራስን ገዝቶ መኖር አይቻልም፡፡ ከተራራ ላይ ቁልቁል እየተምዘገዘገ እንደሚወርድ ውኃ ምንም የጠራ ቢሆን ተንደርድሮ አፈሩን ሲመታው ውኃው ደፍርሶ ከጭቃው ጋር ይቀየጥና የማይጠጣና ቆሻሻ ውኃ እንዲሆን የቁጡ ሰውም እጣ ፈንታ እንዲሁ ነው፡፡ ወዳጅህን በቁጣ ገንፍለህ ልትመታው ኮቱንም ልትቀድበት ትችላለህ፤ ነገር ግን የከፋውን ቅጣት የምትጠጣው አንተው ትሆናለህ፡፡ ያንተ ቡጢ በእርሱ ሥጋ ላይ፣ ቁጣህም በእርሱ ልብስ ላይ አርፎ ይሆናል፤ ነገር ግን በአንተ ነፍስ ላይ ቅጣቱ እንዲሁ ይሆንብሃል፡፡ ከሁለት የምትተረትራት የራስህን ነፍስ ነው፡፡ ስቃይህም በውስጥ ሰውነትህ ውስጥ ይሆናል፡፡

 

አንተ የሰረገላው መሪ ከወንበሩ ላይ ፈንግለህ ጥለኸዋል፡፡ ሰረገላህም ነፍስህን ከምድር ላይ ጥሎ እየጎተታት ነው፡፡ በቁጣ ሰረገላውን የሚመራ ሰው እጣ ፈንታው ነፍሱ ተዋርዳ በመሬት ላይ መጎተት ይሆናል፡፡ ልትገሥጽ ፡ ልትመክር ሌላም ልታደርግ ብትፈልግ ሁሉን ያለቁጣ ከስሜታዊነት ወጥተህ ፈጽም፡፡ለራሱ ሐኪም እያስፈለገው ሌላውን ሊፈውስ እንዴት ይቻለዋል፡፡ ራሱን አቁስሎ ሳለ የሌላውን ቁስል ሊፈውስ የሚጥር ይህ ሰው ራሱን የሚያድነው መቼ ነው? አንድ ሐኪም ሌላውን ለማዳን በሚሄድበት ጊዜ የራሱን እጅ ያቆስላልን? አስቀድሞ የራሱን ዐይን አሳውሮ የሌላውን ዐይን ለማዳን የሚሄድ ሐኪም አለን? እንዲህ ከማድርግ እግዚአብሔር ይጠብቀን፡፡ ቢሆንም ሌላውን ከመገሠጽህና ከመምከርህ በፊት የራስህ ዐይኖች አጥርተው የሚያዩና ንጹሐን ይሁኑ፡፡

 

እእምሮህን ከጭቃው ጋር አትደባልቀው እንዲህ አድርገህ እንደሆነ እንዴት ተብሎ ነው አንተን መፈወስ የሚቻለው?ቁጡና ከቁጣ ንጹሕ መሆን ልዩነታቸው በጭራሽ የሚነጻጸሩ አይደሉም፡፡ ያንተን ጌታ አስቀድመህ ከዙፋኑ ላይ ጥለህና ከጭቃው ጋር ለውሰህ ስታበቃ እንዴት ብለህ ነው ከእርሱ እርዳታን የምትሻው? ዳኞች የዳኝነት ካባቸውን ደርበው ከፍርድ ዙፋናቸው ላይ ከመቀመጥ ይልቅ በአፈር ላይ ይቀመጣሉን? አንተም ነፍስህን የዳኝነት ልብስን አልብሰሃት በተገቢው ቦታዋ ልታስቀምጣት ይገባሃል፡፡ እርሱም የማስተዋል ልብስ ነው፡፡ ነገር ግን “እንዲህ ባደርግ ሠራተኛዬ እኔን ሊፈራኝ አይችልም ትለኝ” ይሆናል፡፡ ይበልጥ ይፈራሃል፡፡ አንተ ሠራተኛህን ለምን እንዲህ እንዲህ አላደረግህ በቀጥታ ብትናገረው ባንተ ላይ ሊቆጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን በትሕትና የተናገርኸው ከሆነ በስህተቱ ራሱን ይወቅሳል፡፡ እንዲህ በማደርግህ የመጀመሪያህ ጥቅምህ ምንድን ነው? እግዚአብሔር አንተን ያከብርሃል ከዘለዓለማዊውም በረከቶቹ ተሳታፊ ያደርግሃል፡፡ በጌታችን በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ለእግዚአብሔር አብና ለእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ክብር ምስጋና አገዛዝ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ ይሁን አሜን፡፡

የቅዱስ ኤፍሬም ቅኔያዊ መዝሙራት /ክፍል ሁለት/

ዳር 14/2004 ዓ.ም

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

“እግዚአብሔር በሰው አምሳል የመታየቱ ምሥጢር”

በዚህ ርእስ ግሩም የሆነውን የቅዱስ ኤፍሬም መጽሐፍ ቅዱስን የመረዳት ጸጋውን እንመለከታለን፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ለሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ በኩል ሲናገር  የሰውን የአካል ክፍል እና ጠባይ ለራሱ በመጠቀም ነው፡፡ ይህ መዝሙር እንዴት የሰው ልጅ በእርሱና በእግዚአብሔር መካከል ያለውን ታላቅ የሆነውን ልዩነት አልፎ  ስለእግዚአብሔር ባሕርያት ማወቅ ይችላል? ብሎ ይጠይቃል፡፡ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን ልዩነት ቅዱስ ኤፍሬም ታላቅ ገደል ወይም ቅዱሱ ጸጥታ ብሎ ይጠራዋል፡፡ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም አስተምህሮ ለሰው የሚሰጠውን መጠሪያና ተፈጥሮ ለራሱ በመጠቀም  በእርሱና በሰው መካከል ያለውን ሰፊ የሆነ ልዩነት ያጠበበው እግዚአብሔር ራሱ ነው፡፡ እንዲህ ማደርጉ ክብር ይግባውና ለሰው ልጆች ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ለሰው የሚሰጠውን መጠሪያና ጠባይ ለራሱ ተጠቅሞበት እናገኛለን፤ እንደ ቅዱስ ኤፍሬም ትምህርት ደግሞ እንደ ልብስ ለብሶአቸው እናገኛቸዋለን፡፡

አስተምህሮውን ከዚህ ቅኔያዊ መዝመር ያገኙታል፡፡
1.በእኛ ምሳሌ በመገኘት ራሱን የገለጠልን እግዚአብሔር አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤

መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር እንደሚሰማን ለማስረዳት ሲል ስለጆሮዎቹ ጻፈልን፤ /መዝ. 33፥15/
እኛን ስለመመልከቱ ሊያስተምረንም ስለ ዐይኖቹ ተረከልን፤ /መዝ. 33፥15/
በዚህ መልክ በምሳሌአችን ተገልጦ ለእኛ ታየን፡፡
እርሱ በባሕርይው ቁጣና ጸጸት የሌለበት አምላክ ሲሆን፤ ዘፍ.6፥6
ስለእኛ ደካማነት እነዚህንም ስሞች ለራሱ በመስጠት ተጠቀመባቸው ፡፡ /1ሳሙ.15፥29/

2.እርሱ በእኛ ምሳሌ ተገኝቶ ባያስተምረን እርሱን ባላወቅነው ነበር፤

በምሳሌአችን ተገልጦ ወደኛ ቀረበ እኛም ወደ እርሱ ቀረብን፡፡  
አባት ከልጁ ጋር ሲነጋገር በልጁ ማስተዋል መጠን እንዲናገር፣
እንዲሁ እግዚአብሔር በእኛ ማስተዋል መጠን ስለፈቃዱ አስተማረን፡፡

3. እንደመረዳታችን መጠን አስተማረን ስንል እርሱ እንደእኛ ነው ማለታችን ግን አይደለም፤

እርሱ በእኛ ምሳሌ ተገለጠ ወይም አልተገለጠ እርሱ እርሱ ነው፤ አይለወጥም፡፡
ሲያስፈልግ እኛን ለማስተማር በአንዱ ጠባያችን  ተገልጦ ይታየናል፤
ሌላ ጊዜ ደግሞ አስቀድሞ የተላበሰውን ምሳሌአችንን እንደልብስ አውልቆ ሌላውን ለብሶ ይገለጥልናል፤
እርሱ በምሳሌአችን ተገኝቶ ለእኛ በመናገሩ እርሱ እንዲህ ነው ማለት ግን አይደለም፤
ነገር ግን ባሕርይው የማይመረመር ነውና በምንረዳው በእኛ ምሳሌ ተገኝቶ ፈቃዱን ገለጠልን፡፡

4.በአንድ ቦታ እርሱ በዘመን ርዝማኔ የሸመገለ አረጋዊ መስሎ ሲታየን፤ /ዳን.7፥9/

በሌላ ስፍራ ደግሞ እጅግ ብርቱ የሆነ ተዋጊ ሆኖ ይገለጥልናል፡፡ /ዘፀ.15፥3/
በሽማግሌ አምሳል መታየቱ ፍትሐዊ መሆኑን ለማስተማር ነው፤
ብርቱ ጦረኛ ሆኖ መታየቱ የእርሱን ኃያልነት ለማስረዳት ነው፤
በአንድ ቦታ እንደሚዘገይ በሌላ ቦታ የሚቀድመው የሌለ ፈጣን እንደሆነ መጻፉ፤
በአንድ ቦታ እንዳዘነ በሌላ ቦታ ደግሞ እንዳንቀላፋ ሰፍሮ መገኘቱ፤ኢሳ./7፥13፣ መዝ.43፥23፣ 78፥66/
በአንድ ቦታም  ሁሉን እንዳጣ ምስኪን ሆኖ ስለእርሱ መተረኩ፤
ስለእኛ ጥቅም እንጂ እርሱ ሁሉ የእርሱ የሆነ ባለጠጋ ነው፤
በእውኑ በእኛ ላይ የሚታዩት ጠባያት በእርሱ ላይ አሉን? የሉም፡፡

5.ቸር የሆነው ፈጣሪ አንዳች ሳይቸገር፣ ያለፈቃዳችን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራን እንድንፈጽም ማስገደድ ይቻለዋል፤

ከዚህ ይልቅ ግን በፈቃዳችን እርሱን ደስ የሚያሰኝ ሥራን እንድንሠራ ይሻል፤
ስለዚህ እርሱ የሚወደውን የጽድቅ ሥራ እንድንሠራና በጽድቅ ተውበን እንድንገኝ በእኛ አምሳል ተገለጠልን፡፡
አንድ ሠዓሊ የሣለውን ሥዕል በቀለማት እንዲያስውበው፤
አምላካችንም በአምሳላችን ለእኛ በመገለጥ በጽድቅ ሕይወት አስጌጠን፡፡

6.አንድ ሰው በቀቀንን ንግግር ለማስተማር ቢፈልግ ራሱን በመስታወት ጀርባ ይሰውራል፤

በቀቀኑዋን ግን ከመስታወቱ ፊት በማድረግ የሰውን ቋንቋ ያሰማታል፤
በቀቀኑዋም ድምፁን ወደሰማችበት አቅጣጫ ስትዞር የራሱዋን ምስል በመስታወት ውስጥ ታገኛለች፤
ምስሏን ስትመለከት ሌላ በቀቀን እርሱዋን እያነጋገረቻት ይመስላታል፤ስለዚህም አጸፌታውን ትመልሳለች፤
በዚህ መልክ ሰውየው በበቀቀን አምሳል በመገኘት ለበቀቀኑዋ ንግግርን ያስተምራታል፡፡

7.ይቺ በቀቀን ከሰው ጋር ተግባብታ የምትኖር ፍጥረት ነች፤

ነገር ግን እንዲህ እንድትግባባ ከእርሱዋ ተፈጥሮ ውጪ የሆነው ሰው ሊያስተምራት ተገባ፤
እንዲሁ ከሁሉ በላይ እጅግ ከፍ ከፍ ያለው መለኮት፤
ስለፍቅር ከላይ ከከፍታው ራሱን ዝቅ በማድረግ በእኛ ምሳሌና ልማድ ተገኝቶ ፈቃዱን ያስተማረን፤
ሁላችንን  ወደ ጽድቅ ሕይወት ለመምራት በደካማው በሰው አምሳል ለእኛ ተገለጠልን፡፡


8.እርሱ አንድ ጊዜ በእድሜ ርዝማኔ ያረጀ ሽማግሌ መስሎ ሲታይ ሌላ ጊዜ በተዋጊ ተመስሎ ይገለጥልናል፤

በአንድ ቦታ የማያቀላፋ ትጉህ እረኛ ሆኖ ሲታይ፤ በሌላ ስፍራ ደግሞ እንዳንቀላፋ ሆኖ ይገለጥልናል፤/መዝ.12ዐ፥3-4/
በአንድ ቦታ እንደሚጸጸት ሆኖ ሲገለጥልን፤ በሌላ ስፍራ ደግሞ ጸጸት የሌለበት ጌታ እንደሆነ ያስተምረናል፤/ኢሳ.40፥28/
በፈቃዳችን ራሳችንን ለማስተማር እንድንበቃ  እርሱ በሚወሰንና በማይወሰን አምሳል ለእኛ ተገለጠልን፡፡
በአንድ ስፍራ ብሩህ በሆነ የሰንፔር ድንጋይ በሚመስል ወለል ቦታ እንደቆመ ሆኖ ሲታየን፤ /ዘፀ.4፥10/
በሌላ ቦታ ደግሞ ሰማይንና ምድርን የሞላ ፤ ፍጥረት ሁሉ በመሃል እጁ የተያዘች እንደሆነች ይነግረናል፡፡ /ኢሳ.40፥12/

9.ሲፈልግ በተወሰነ ቦታ ለእኛ ሲገለጥ፤

ሲፈልግ ደግሞ በሁሉ ስፍራ ይገልጥልናል፤
በአንድ ስፍራ በአምሳላችን ሲገለጥ በቦታ የተወሰነ ይመስለናል፤  እርሱ ግን በሁሉ ስፍራ ነው፡፡
በሌላ ስፍራ እኛን በቅድስና ሕይወት የበቃን ያደርገን ዘንድ ታናሽ መስሎ ለእኛ ይገለጥልናል፤
በተቃራኒው ደግሞ እኛን እጅግ ባለጠጎች ያደርገን ዘንድ በታላቅነቱ ያታየናል፤
እኛን በክብር ለማላቅ ሲል አንዴ ታናሽ ሌላ ጊዜ ታላቅ ሆኖ ይገለጥልናል፤
እርሱ ታናሽ ሆኖ ብቻ እንጂ ታላቅ ሆኖ ባይገለጥልን፤
ደካማ መስሎን ስለእርሱ ግንዛቤ የተዛባ ይሆን ነበር፡፡
እንዲህ እንዳይሆንም አንዴ ታናሽ ሌላ ጊዜ ታላቅ ሆኖ ይታየናል፡፡


10.ኑ  የእኛን ታናሽ የሆነን ተፈጥሮ ለማላቅ ሲል ታናሽ መስሎ የተገለጠውን አምላክ እናድንቅ፤

ለእኛ ታናሽ መስሎ እንደተገለጠ ሁሉ በታላቅነቱ ለእኛ ባይገልጥልን፤
እርሱን ደካማ አድርገን ስለምንቆጥር ስለእርሱ ያለን ግንዛቤ ያነሰ ይሆን ነበር፡፡
አይደለም በታላቅነቱ በእኛ አምሳል ተገልጦልን እንኳ ስለእርሱ መለኮታዊ ባሕርይ መረዳት አልተቻለንም፤
ስለእርሱ ታላቅነት በተመራመርን ቁጥር እጅግ እየረቀቅን በእውቀትም እየመጠቅን እንሄዳለን፤
እርሱን የመረዳት አቅማችን እየጫጨ ሲመጣ ፣ ለእኛ አምሳል በመታየት ወደ እርሱ ፈቃድ ይመራናል፡፡

11.እግዚአብሔር በእኛ አምሳል መገለጡ ሁለት ዓበይት ቁምነገሮችን ሊያስተምረን በመሻቱ ነው፤ /ዮሐ.1፥11/

አንደኛው አምላክ ሰው መሆኑን ሁለተኛው ሰው መሆኑ አምላክነቱን እንዳላሳጣው ሲያስተምረን ነው፡፡
ለእኛ ለባሮቹ ካለው ፍቅር የተነሣ በሚታይ አካል ለእኛ ተገለጠ፤
ነገር ግን በሰው አምሳል በመገለጡ እርሱን በማሳነስ እንዳንጎዳ፣
አንዴ በአንዱ አምሳል ሌላ ጊዜ በሌላ አምሳል ለእኛ ይገለጥልናል፤
በዚህም እርሱን የሚመስለው እንደሌለ አስተማረን፤
እርሱ በሰው አምሳል መታየቱን ሳይተው ለእኛ መገለጡ፤
እርሱን በተለያየ አምሳል እንዳይገለጥ አይከለከለውም፡፡

ክፍል ሦስት ይቀጥላል…….

ጾመ ነቢያት

በዲ/ን አሻግሬ አምጤ
ቀን: ህዳር 14/2004ዓ.ም.

ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር በጸጋ እንደተወለዱ በማመን ለእግዚአብሔር ያላቸውን ፍቅር ከሚገልጡባቸው ነገሮች አንዱ ጾም ነው፡፡ ጾም ፍቅረ መብዓ ከመሆኑ በተጨማሪ ታዛዥነትንና የገቡትን ቃል ኪዳን ጠባቂነትንም ማሳያ ነው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አርአያ ተፈጥሯአል፡፡ ኃጢአት ሠርቶ የእግዚአብሔር አርአያነቱን ቢያጠፋውም እግዚአብሔር ግን በአርአያው ሲፈጥረው ምን ያህል እንደሚወደው ማረጋገጫ ስለነበር በኃጢአት ሲወድቅም እንደወጣ ይቅር ሳይል ሊፈልገው መጣ፡፡ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሊፈልግ የመምጣቱ ተስፋ የተነገረበትንና ሱባኤ የተቆጠረበትን ዕለት ለማየት በመናፈቅ ከቀረበው መሥዋዕት አንዱ ጾም ነበር፡፡

 

ሰው በኃጢአት ቢወድቅም ፈጣሪው ሊያነሳው፤ ቢጠፋ ሊፈልገው እንደሚመጣ በተስፋ ሲጠብቀው ወልደ አምላክ ሰው መሆኑ የተረጋገጠ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ አዳም የልደቱን ነገር በትንቢት መነፅርነት ሲመለከተው /በነቢያቱ ትምህርትና ስብከት/፣ በሚኖርበት ዓመተ ፍዳ የምሥጢረ ሥጋዌ  ብርሃን ከሩቅ ሲመለከተው ኖረ፡፡ ምሥጢረ ሥጋዌን በትንቢት መነፅርነት ማየቱም መከራውን እንዲቋቋመው የተስፋ ስንቅ ሆነው፡፡

 

ጾም ሰው ለእግዚአብሔር ያለውን ፍቅር እና ታዛዥነት መግለጫና ማረጋገጫ ብቻ አይደለም፤ አልነበረም፡፡ ሲወድቁ መነሻ ከብልየት መታደሻ፥ ከኃጢአት ቆሻሻ መታጠቢያ /ከንስሓ ጋር አብሮ ሲፈጸም/ ሳሙናም ነው፡፡ ሊቀ ነቢያት ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እግዚአብሔር ወደ ነበረበት ጨለማ የገባው፣ አስፈሪውን መብረቅና ነጐድጓድ የተቋቁመው፣ ጨለማውን አልፎ የሰው ልጅ ያልሠራትን ሰማያዊ መቅደስ የተመለከተውና ወደ ዓለቱ ድንጋይ የቀረበው ራሱን ለእግዚአብሔር በጾም በመቀደስ ጭምር ነው፡፡ /የወገን ፍቅርና ለእግዚአብሔር ታዛዥነቱ እንዳለ ሆኖ/፡፡ ጾም እነዚህንና መሰል መንፈሳዊ በረከትን ስለሚያስገኝ ክርስቲያኖች ይመጣላቸው ዘንድ ይናፍቁታል፡፡ ከእነዚህ የሚናፈቁ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ጾመ ነቢያት የሚባለው ጾመ ገና፣ ጾመ ማርያም፣ ጾመ አዳም፣ ጾመ ፊልጶስ ተብሎ እንደሚጠራ መምህር ቃኘው ወልዴ ጾምና ምጽዋት በተሰኘው መጽሐፋቸው ገልጠውታል፡፡

 

ጾመ ነቢያትም ሆነ ሌሎች አጽዋማት ሲደርሱ ክርስቲያኖች የሚደሰቱት ጾም የሥጋ ፈቃድ እንዳይሰለጥንባቸው፣ ቁስለ ሥጋን በማከም፣ ቁስለ ነፍስን ስለሚፈውስላቸው ነው፡፡  ጾም የቁስል መፈወሻ ኃይለ መዊዕም ይሆናል፡፡ ከሥጋም ከመንፈስም ተቆራኝቶ ሰውን ወደ ጥፋት የሚወስድን ክፉ መንፈስ ለማራቅም ይጠቅማል፡፡ ጾም የሥጋን ምኞት እስከመሻቱ ቆርጦ የሚጥል፣ ለመንፈስ ልዕልና የሚያበቃውን መሳሪያ የሚያስታጥቅ ነው፡፡ ክርስቲያን ይህን መሰል መንፈሳዊ የጦር እቃ እንዳይለየው አጥብቆ ይለምናል፡፡ የጦር ልምድ እንደሌለው ወታደር ጠላቱን የሚቋቋምበት የጦር ትጥቅ ሳይዝ አውላላ ሜዳ ላይ  ባዶውን አይቆምም፡፡ መንፈሳዊ ውጊያን በሥጋዊ ጥበብ ማሸነፍ ስለማንችል ነው አበው ፍቅረ አጽዋማትን በአስተምህሮአቸውና በሕይወታቸው የሰበኩልን፡፡

 

የጾመ ነቢያት መግቢያ በሊቃውንቱም ሆነ የጠለቀ እውቀት በሌለው ምእመን አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ችግሩን ለመፍታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ፕትርክና ጾመ ነቢያት ኅዳር አስራ አምስት እንዲጀመር ተወስኗል፡፡ ክርስቲያኖችም የአባቶችን ውሳኔ መሠረት በማድረግ እየጾሙት ይገኛሉ፡፡

 

ጾመ ነቢያት ለአዳም የተነገረው ትንቢት፣ የሚጠበቀው ሱባኤ እንደደረሰ የሚያበስር በመሆኑ ጾመ አዳም ይባላል፡፡ አዳም ቢበድልም ንስሐ ገብቶ በማልቀሱ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሀለሁ ብሎ የተነገረው ተስፋ መድረሱን፣ ምሥጢረ ሥጋዌ እውን ሊሆን መቃረቡን የሚያስረዳ ጾም ነው፡፡ ነቢያትም የምሥጢረ ሥጋዌ ነገር ተገለጦ ስለታያቸው፣ ክርስቶስ ለሰው ልጅ የሚከፍለውን የፍቅር ዋጋ በትንቢት ተመልክተው ጾመውታልና ጾመ ነቢያት ይባላል፡፡ ይህ ጾም የራቀውን አቅርቦ፣ የረቀቀውን አጉልቶ ስላሳያቸው እስከሞት ድረስ ቢደበደቡም፣ ከመከራው ጽንአት የተነሣ ዋሻ ለዋሻ፣ ፍርኩታ ለፍርኩታ ቢንከራተቱም፣ የፍየል ሌጦ ለብሰው ቢዞሩም የተስፋው ቃል ሁሉን አስረስቶአቸው ከትንቢቱ ባለቤት ጋር በመንፈስ ተዋሕደው አልፈዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሐዋርያት ምን ሠርተን የክርስቶስን ልደት እንቀበለው ብለው ስለጾሙት ጾመ ሐዋርያት ተብሎ ይጠራል፡፡

 

ጾመ ነቢያት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ወልደ አብን ፀንሼ ምን ሠርቼ እወልደዋለሁ በማለት ጾማዋለችና ጾመ ማርያም ይባላል፡፡ ይህን ያለችው በመደነቅ፣ አንድም በትሕትና አንድም ቀደምት አባቶቿ ነቢያት ሲጾሙት አይታ ጾማዋለች፡፡ እንዴት ፀንሼ እወልደዋለሁ ማለት ጥርጥር ሳይሆን ተደሞ፣ መደነቅ የነገረ ልደቱን አይመረመሬነት ይገልጻል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትሕትና ነው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ቅድስናዋን አይቶ በብስራተ መልአክ አማካኝነት ክርስቶስን እንደምትወልድ ቢነግራትም የትሕትና እናት ናትና ምን ሠርቼ የሰማይና ምድርን ፈጣሪ እችለዋለሁ ስትል ጾማዋለች፡፡ ይህ ጾም ጾመ ፊልጶስም ይባላል፡፡ ሐዋርያው ፊልጶስ በአረማውያን ዘንድ ገብቶ ሲያስተምር በሰማዕትነት ሲሞት አስከሬኑ ከደቀመዛሙርቱ ስለተሰወረ እግዚአብሔር የተሰወረውን የመምህራቸውን አስከሬን እንዲገልጽላቸው ከኅዳር አስራ ስድስት ጀምረው ሲጾሙ በሦስተኛው ቀን የመምህራቸው አስከሬን ቢመልስላቸውም ጾሙን ግን እስከ ልደት ቀጥለዋል፡፡ የጾመ ነቢያት መግቢያው ኅዳር አስራ አምስት ቢሆንም ማብቂያው ልደት ነው፡፡ ጾምን ትእዛዝ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የፍቅርና የበረከት ምንጭ በመሆኑ ጭምር ደስ እያለን ብንጾመው የቅዱሳኑ በረከት ያድርብናል፡፡

ይቆየን…..

ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ወሰላም በምድር ስምረቱ ለሰብ

የአትናቴዎስ ትምህርት ስለ መንፈስ ቅዱስ

የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ
አባ ጎርጎርዮስ የሸዋ ሊቀ ጳጳስ /M.A/

አትናቴዎስ ስለ መንፈስ ቅዱስም በተናገረበት ባስተማረበት አንቀጽ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብ እንደ ወልድ ከአብ ከወልድ ጋር ፍጹም አካል መኾኑን፣ በባሕርይ በህልውና አንድ መኾኑን ይናገራል፡፡ ከቅድስት ሥላሴ ሦስተኛው አካል መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ   ፍጡር አይደለም፡፡ በብሉይ ኪዳን፣ በሐዲስ ኪዳን እንደ አብና እንደ ወልድ አምላካዊ ክብሩ ተነግሮለታልና፡፡ እነ አርዮስ እንደሚሉት መንፈስ ቅዱስ ፍጡር ቢኾን ኑሮ  የፍጡራን ሕይወት ባልኾነም ነበር፤ እንዴትስ የእግዚአብሔርን ምሥጢር ለማወቅ ቻለ? /1ኛቆሮ.2÷10/ ወልድ ከአብ ጋር አንድ ባሕርይ እንደሆነ መንፈስ ቅዱስም ከአብና ከወልድ ጋር አንድ ባሕርይ ነው፡፡ ሦስቱ አካላት /ገጻት/ ባንድ ባሕርይ ባንድ ህላዌ ይኖራሉ፤ አብ በወልድ ቃልነት ዓለምን ፈጠረ፡፡ ሦስቱ አካላት አንድ አምላክ ነው፡፡ በምሥጢረ ሥላሴ ወይም በሦስቱ መካከል ባዕድ ባሕርይ የለምና፡፡

ወልድ ከአብ እንደ ተወለደ መንፈስ ቅዱስም ከአብ የሠረጸ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ምሥጢር ገልጧል፤ ቋንቋ አናግሯል፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ከበዓለ ጰንጠቆስጤ ጀምሮ የሚመራ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ በአትናቴዎስ ትምህርት የባሕርይና የህላዌ እንዲሁም የአካላት ልዩነት፣ በምሥጢረ ሥላሴ የሚነገሩ ባሕርይ፣ ህላዌ፣ ከዊን  በእስክንድርያ ትምህርት ቤት ከአትናቴዎስ በኋላ ትክክለኛ ፍቻቸው እንደሚከተለው ነው፡፡ /ኡሲያ/ ህላዌ የሚለው ቃል በእስክንድርያ ትምህርት ቤት በነበረው የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት አካል ከባሕርይ ሳይለይ አንዱ ከሌላው ተለይቶ የሚታወቅበት ከዊን ማለት ነው፡፡ በአንጾኪያ ግን ይልቁንም ጳውሎስ ሳምሳጢና ተከታዮቹ «ህላዌ» የሚለውን ቃል በተሳሳተ አተረጓጐም በመተርጎም፤ ብዙዎቹን አሳስተዋል፡፡

ለምሳሌ «ዋሕደ ህላዌ» ማለት ሦስቱ አካላት አንዱ በአንዱ አድሮ የሚኖር ማለት ነው፤ ብለው ያስተምራሉ፡፡ እዚህ ላይ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አካላዊና በከዊን የተለየ ህላዌ አልነበራቸውም ለማለት ጳውሎስ ሳምሳጢ ይመቸዋል፡፡ በሱ አስተሳሰብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በአብ ህልዋን ኹነው የሚያገለግሉ ዝርዋን እንጂ አካላውያን አይደሉምና፡፡ ስለዚህም በ260 ዓ.ም እሱን ለማውገዝ የተሰበሰቡ ሊቃውንት «ዋሕደ ህላዌ ምስለ አብ» ብሎ አትናቴዎስ ረትቶበታል፡፡ /አሞኡሲዮን ቶ፣ -ትረ/ ይህም የአትናቴዎስ አባባል ከጳውሎስ ሳምሳጢ ጋር ዝምድና የለውም፡፡ «ዋሕደ ባሕርይ» በማለት የባሕርዩን አንድነት «ምስለ አብ» አብ ማለት የአካልን ልዩነት ያሳያልና «ዋሕደ ህላዌ ምስለ አብ» በአንቀጸ ሃይማኖት «ዘዕሩይ ምስለ አብ በመለኮቱ» የምንለው ነው፡፡ እንግዲህ ህላዌ የሚለው ቃል፤ በምሥጢረ ሥላሴ አንዱ አካል በሌላው አድሮ ወይም ጥገኛ ኹኖ የማይኖር፣ ከሥላሴ አንዱም አንዱ፣ እያንዳንዱ አካል በአካሉ፣ በመልኩ፣ በገጹ ፍጹም መኾኑን ያሳያል፣ ያመለክታል፡፡ «ህቡረ ህላዌ ምስለ አበመለኮቱ፣ ኅቡረ ህላዌ ምስሌነ በትስብእቱ» /ተረፈ ቄርሎስ/
በሌላም ቦታ «ህላዌ» ከግብርና ከአካል ስም ጋር ተጣምሮ ይገኛል፤ ለአብ የወላዲነት ለወልድ የተወላዲነት፣ ለመንፈስ ቅዱስ የሠራጺነት ስሙ ነው፡፡ «እስመ አበዊነ ስመይዎን በዝንቱ ገጸ መካን ለህላዌያት አካላተ፤ አትናቴዎስኒ ረሰየ ህላዌ አሐደ አካለ ዘእግዚአብሔር ቃል ዘተሠገወ» እንዲል፡፡
ዳግመኛም ህላዌ አካልና ባሕርይ አንድ ኹነው የቆሙበት አስተጋባኢ ስም ስለሆነ ለአካልም ለባሕርይም ይነገራል፡፡ በአንቀጸ ተዋሕዶ ማለት የሦስቱን አንድነት በምንናገርበት ጊዜ አሐዱ ህላዌ እንላለን፡፡ መውለድና ማሥረጽ፣ መወለድና መሥረጽ በዚያው ባንድ ባሕርይ ውስጥ ነውና፡፡

 

ስለዚህ በምሥጢረ ሥላሴ ባሕርይ አይከፈልም፡፡ አካል አይቀላቀልምና፡፡ ህላዌ ግን ለአካልም ለባሕርይም መነገሩን ገልጠናል፡፡ ባሕርይ ምንጊዜም ቢኾን ለአካል አይነገርም፤ አካልም ለባሕርይ ስም አይኾነውም፣ አለዚያ ግን ባሕርይን መክፈል ስምና ግብርን ማፋለስ ይኾናል፡፡ ወላዲ ባሕርይ፣ ተወላዲ ባሕርይ፣ ሠራጺ ባሕርይ የማይባለውም ስለዚህ ነው፡፡ ከተባለ ግን ሦስት መለኮት፣ ዘጠኝ አካላት ወደ ማለት ይሸነሸናል፤ የምሥጢረ ሥላሴው የግብር ስም ለምሥጢረ ተዋሕዶው የባሕርይ ስም አይሰጥም፡፡ የሦስቱም አካላት መለኮት ወይም ባሕርይ አንድ ነው፡፡ «ሠለስቱ ገጻተ አሐዱ አምላክ» ብሎ ለማመንና ለማሳመን ይህን ኹሉ ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ በላይ እንዳየነው በእስክንድርያ የትርጓሜ ትምህርት ቤት እነ አትናቴዎስ «ህላዌን» /ኡሲያን/ ለአካልም ለባሕርይም ሰጥተው ይናገራል፡፡ /ኩነት/ ከዊን ግን ለአካል ብቻ ነው /ኢስታሲስ/ በአንጾኪያ ግን «ህላዌን» /አሲያን/ ለባሕርይ ብቻ /ኩነትን/ ከዊንን /ኢስታሲስን/ ለአካል ብቻ ሰጥተው ይናገራሉ፤ በዚህኛው ልዩነት የለም፡፡

«ጾምን ቀድሱ» /ኢዮ.2-15/

ጾም


የሰውን ልጆች የሚወደውና ስለ እነርሱም ብሎ በገነት ያሉትን ዛፎች ሁሉ የፈጠረው እግዚአብሔር በገነት ካሉት ዛፎች መካከል አንዲቱን እንዳይበላ አዳምን አዘዘው፡፡ ይኽ አዳምን ለመጫን፣ ኃይሉን በእርሱ ላይ ለማሳየት ሳይሆን ሰው በመጾም /ባለመብላት/ እና በመታዘዝ ለሚወደው አምላኩ ፍቅሩን ይገልጽ ዘንድ ነው፡፡

 

ከአዳም ድቀት በኋላም በየዘመናቱ የተነሡ መንፈሳውያን ሰዎች እና ሕዝቦች በየግላቸው እንዲሁም በአንድነት /በጋራ/ ሲጾሙ፣ በጾማቸውም ሲጠቀሙ ኖረዋል /ሕዝበ እስራኤል ሙሴ፣ ኤልያስ፣ የነነዌ ሰዎች. . ./፡፡

 

ጌታችንም፣ በእደ ዮሐንስ ከተጠመቀ በኋላ፤ የማስተማር አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ጾሟል፡፡ ከዚህ ክርስቲያናዊ ትውፊት በመነሣትም ሐዋርያትና ደቀመዛሙርቱም እንዲሁ አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው በፊትና በአገልግሎታቸው ወቅት ይጾሙ ነበር፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርቲያናችን በትውፊት ያገኘነውን፣ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተማሩንን ጠቃሚ ሥርዓቶችን አውርሳናለች፡፡ ከነዚህ የከበሩ ሀብታት መካከል ሥርዓተ ጾም አንዱ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የአዋጅ እና የግል /የፈቃድ/ አጽዋማት አሉን፡፡ ቤተክርስቲያናችን መንፈሳዊት ዓለም እንደመሆኗም የጾም አስተምህሮዋ «ለጾም አድሉ» የሚል ነው፡፡ ምእመናንም የዓመቱ ብዙውን ቀናት በዚህ በተቀደሰ መንፈሳዊ ምግባር ያሳልፋሉ፡፡

የጾም ጽንሰ ሐሳብ

1. መጾም ማለት በፈቃድ ለተወሰነ ጊዜ ከምግብ መከልከልና መራብ ማለት ነው፡፡ ጌታችን በጾመ ጊዜ ተርቧል /ማቴ.4-2/፡፡ ሐዋርያትም በጾማቸው ጊዜ ተርበዋል /ሐዋ.10-1/፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተወሰነ ጊዜ /ሰዓታትን፣ ቀናትን. . . / ካሳለፍን በኋላም ቢሆን ሥጋን የሚያለመልሙ ምግቦች አንመገብም፡፡ ከአባቶቻችን እንደተማርነው ከእንስሳትና ከእንሰሳት ውጤቶች፣ እንዲሁም ከሌሎች ለሥጋ እጅግ ከሚመቹ ምግቦች እንርቃለን እንጂ፤

ዳንኤል:-«በዚያም ወራት እኔ ዳንኤል ሦስት ሳምንት ሳዝን ነበርሁ፡፡ ማለፊያ እንጀራ አልበላሁም፣ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፡፡ ሦስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም»/ዳን.10-3/፡፡

ዳዊት:- «ሥጋዬ ቅባት በማጣት ከሳ፣ ጉልበቶቼም በጾም ደከሙ»/መዝ.108-24/፡፡

ይኽ እንዳለ ሆኖ ጾም ማለት ከምግብ፣ ከመጠጥና ከምቾት መታቀብ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ የግዴታ አንድያ ልጁን ለእኛ እንዲሞት ለሰጠው ለእምላካችን ያለንን ፍቅር የምንገልጥበት መንገድ መሆንም አለበት፡፡ ስለዚህ የጾም ወቅት የበለጠ ስለ እግዚአብሔር የሚያስቡበትና በፍቅሩ የሚመሩበት፤ ወደ እርሱ የሚቀርቡበት ወቅት መሆን አለበት፡፡ የምንጾመው «ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኔ ሞቶልኛል፤ እኔም ቀኑን ሙሉ ፈቃዴን ለእርሱ እገድላለሁ» በሚል አሳብ ነው፡፡

ከዚህም በላይ ጾም ከኃጢአት መራቅን ስለ ቀደሙ በደሎች ንስሓ መግባትን እና በመንፈሳዊነት ማደግን ያካተተ መሆን አለበት፡፡

2. እግዚአብሔር እኛን የፈጠረን ሥጋችንና ነፍሳችን መንፈሳዊ ሆነው በአንድነት ለእርሱ እንዲገዙና ፈቃዱን እንዲፈጽሙ ነው፡፡ መንፈሳዊ መሆን ማለት በመንፈስ ቅዱስ መመራት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የሥጋችንን ፈቃድ በናረ ጊዜ ነፍሳችን ለመንፈስ ቅዱስ /ለእግዚአብሔር/ ፈቃድ ሳይሆን ለሥጋ ፈቃድ ትገዛለች፡፡ እንደ ሥጋውያን መመላለስ ኃጢአት መሥራት እንጀምራለን፡፡ ጾም ይህንን ለማስቀረት ሥጋችንን የምናደክምበትና ፈቃድ እንዳያይል የምናደርግበት መንገድ ነው፡፡

3. የጾም ወቅት የንስሓ እና የሐዘን ወቅት ብቻ ሳይሆን የደስታ ወቅትም ነው፡፡ ምክንያቱም የጾም ወቅት ነፍስን ከሚያስጨንቅ የሥጋ ፈቃድ የምንላቀቅበትና መንፈሳዊ ድል የምናገኝበት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ፍቅር የምናጣጥምበት ወቅት ነው፡፡

በነቢዩ ኢዩኤል «የተቀደሰ ጾም» ተብሎ የተገለጠው እንዲህ ያለው ጾም ነው፡፡ /ኢዩ.2.15/፡፡

ሥርዓተ ጾም

ይኽንን በመረዳት ሁላችንም አዘውትረን መጾም አለብን፡፡ በእርግጥም ብዙ ክርስቲያኖች የዓመቱን አብዛኛውን ጊዜ በጾም ያሳልፋሉ፡፡ እናት ቤተክርስቲያንም በመንፈሳዊ ዝለት ይኽንን በሚገባ ሳናደርገው እንዳንቀር በዓመቱ ውስጥ በዐዋጅ የሚጾሙ አጽዋማትን አዘጋጅታለች፡፡ እነዚህም ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ጋድ፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ድኀነት /ረቡዕና አርብ/፣ጾመ ሐዋርያት፣ጾመ ፍልሰታ ናቸው፡፡

በእነዚህ የአዋጅ አጽዋማት ወቅት በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን የተደረጉ የተለያዩ ነገሮች ስለሚታሰቡባቸው ይኽም ለመንፈሳዊ ተመስጦ ስለሚጠቅም ጥቅማቸው እጥፍ ድርብ ይሆናል፡፡

ጾመ ነቢያት

ከላይ በተናገርነው መሠረት ከምንጾማቸው የአዋጅ አጽዋማት አንዱ በየዓመቱ ከኅዳር 15 እስከ ታኅሣሥ 28 /በዘመነ ዮሐንስ እስከ ታኅሣሥ 27/ ድረስ የምንጾመው ጾመ ነቢያት ነው፡፡ ይኽን ጾም የምንጾመው ነቢያት በየዘመናቸው ስለ መሲህ መመጣት በናፍቆት ይጾሙ ይጸልዩ ስለነበር የእነርሱን አርአያ ተከትለን ነው፡፡ የክርስቶስን ልደት ከማክበራችን ቀደም ብለን ይኽን ጾም እንድንጾምም ቅድስት ቤተክርስቲያን ወስናለች፡፡ የተቀደሰ ጾም ለመጾም፣ ጾመንም ልደተ እግዚእን ለማክበር እንትጋ፡፡

አምላከ ነቢያት አይለየን፡

ዘመነ አስተምህሮ

ኅዳር 6/2004 ዓ.ም

በቤተ ክርስተያናችን የዘመን አቆጣጠር /አከፋፈል/ መሠረት ከኀዳር 6 ጀምሮ እስከ ታኀሣሥ 13 ድረስ ያለው ወቅት ዘመነ አስተምህሮ ይባላል፡፡

መሀረ ማለት ይቅር አለ ማለት ሲሆን፤ ዘመነ አስተምህሮ ማለት ይቅርታ የመጠየቅ /የምልጃ/ ዘመን ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ቤተ ክርስቲያን ስለ ልጆቿ ይቅርታ የምትጠይቅበት፤ ምዕመናንንም ስለ በደላቸው ይቅርታ የሚጠይቁበት፤ ስለዚህም በስፋት ትምህርት የሚሰጥበት ዘመን ነው፡፡

በዚህ ዘመን ያሉት አምስት እሑዶችና በእነዚህ እሑዶች የሚጀምሩት ሳምንታት አስተምህሮ፣ ቅድስት፣ ምኩራብ፣ መጻጉዕ፣ እና ደብረ ዘይት በመባል ይጠራሉ በየሳምንቱ ቤተ ክርስቲያን የምታቀርበውን ትምህርት በየጊዜው እናከብራለን የመጀመሪያውን ሳምንት /የአስተምህሮ/ ትምህርት እነሆ: –

እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል፤ በደላችንን ይቅር በለን /ማቴ.6-12/

ይህ ቃል የተወሰደው ጌታችን በደቀ መዛሙርቱ በኩል እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ለሚኖሩ /ዛሬም ላለን/ ክርስቲያኖች እንዲህ ብላችሁ ጸልዩ ብሎ ካስተማረው ፀሎት ነው፤

በሰማይ የምትኖር አባታችን ሆይ ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን፤ የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን፤ እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን፤ ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለም አሜን/ ማቴ.6. 9-14/

ይህ ጸሎት በጥንታውያን የቤተ ክርስቲያን አባቶች እና ሊቀውንት «የጌታ ጸሎት» ተብሎ ይጠራል፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የጸሎቱን የመጀመሪያ ሐረግ በመያዝ «አባታችን ሆይ» ወይም በግእዝ «አቡነ ዘበሰማያት» እንለዋለን፡፡

ይህ ጸሎት ጌታችን ራሱ ያስተማረው በመሆኑ በቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ የሌሎች ጸሎታት ሁሉ ማሰሪያ /ማሳረጊያ/ ሆኖም ያገለግላል፡፡ በውስጡም «አባታችን ሆይ» ከምትለው ከመጀመሪያዋ ሀረግ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ እጅግ ጥልቅ የሆኑና ነፍስን የሚያጠግቡ ወደ ሰማይ ከፍ የሚያደርጉ መንፈሳዊና ነገረ መለኮታዊ መልእክቶችን ያዘለ ነው፡፡

ይህ የዘመነ አስተምህሮ የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ይቅርታ የሚሰበክበት ነውና በጸሎቱ ውስጥ ስለዚህ የሚናገረውን አንቀጽ መሠረት አድርገን እንማራለን፤

«እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን» ከዚህ ቃል በርካታ ነገሮችን እንማራለን፤

1. እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን እንደሚወድ

አምላካችን ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ባይወድ ኖሮ ይቅርታን እንድንጠይቅ አይነግረንም ነበር፡፡ አዎ እኛ ከተመለስን ምንም ያህል በደለኛ ብንሆን ይቅር ሊለን፤ ምንም ያህል ብንቆሽሸ ሊያድነን ዝግጁ ነው፡፡ እንዲህ እያለ ይጠራናል፤ «እናንተ ሸክማችሁ የከበዳችሁ፤ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ»፡፡ ስለዚህ በዚሀ ጸሎትም ላይ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጠይቀው አስተማረን፤ ይቅር ይለን ዘንድ፡፡

2. ይቅር ለመባል ምን ማድረግ እንዳለብን፤

ይቅር ሊለን ስለ ወደደም ይቅርታን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በዚሁ ቃል ነግሮናል፤ ማድረግ ያለብን ምንድን ነው?

– ኀጢአታችንን ማወቅ፣ ማመን፣ ማስታወስ

– የበደሉንን ይቅር ማለት

– ይቅርታን መለመን

ኅጢአታችንን ማወቅ /ማመን/

ጌታ «በደላችንን ይቅር በለን» ብለን እንድንጸልይ ሲነግረን በመጀመሪያ ደረጃ በደለኛ እንደሆንን እያስታወስን /እንድናስታውስ እያደረገን/ ነው፡፡

ሁልጊዜም በማሰብ፣ በመናገርና በማድረግ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ የሆነውን ልባችንን /ኅሊናችንን/ እና ሰውነታችንን እናቆሽሻለን፤ መድኃኔዓለም ክርስቶስ የሞተለትን ማንነታችንን እናጎድፋለን፡፡ ይህም የሰው ልጆች በቅድስና እርሱን መስለን እንድንኖር በኋላም የተዘጋጀልንን የዘለዓለም መንግሥት እንድወርስ ብቻ ፈቃዱ የሆነውን እግዚአብሔርን ያሳዝናል፤ በአርአያውና በአምሳሉ ለክብር የፈጠረው ሰውነታችን መጉደፍ ያስቆጣዋል፤ ንጹሐ ባሕርይ የሆነ እርሱ ኀጢአት አይስማማውምና፡፡

እንግዲህ ይቅር ለመባል በመጀመሪያ እንዲህ ኀጢአት እየሠራን መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልገናል፡፡ ወደዚህ ዕውቀት ለመድረስም የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል መማር የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ ምክንያቱም ስህተት የሚታወቀው ያለውን ሁኔታ /ድርጊታችንን ንግግራችንን፣ ሀሳባችንን.. / መሆን ከነበረበት /ከትክክለኛው/ ጋር በማነጻጸር በሚዛን ላይ በማስቀመጥ ነው፡፡ የማነጻጻሪያ ሚዛኖቻችን ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉ ሕግጋትና ትዕዛዛት ናቸው፡፡ እነዚህን ስናውቅ ጉድለቶቻችን፣ ድካሞቻችን ፍንተው ብሎ ይታዩናል፡፡ አሊያ ግን እየበደለን ያልበደልን ሊመስለን ይችላል፡፡

የበደሉንን ይቅር ማለት

ጌታ በዚህ ጸሎት ይቅርታ እንድንጠይቀው በማስተማር ይቅር ሊለን እንደሚወድ ዝግጁም እንደሆነ ቢነግረንም ይቅር ለመባል ግን እኛ የበደሉንን ይቅር ማለታችን የግድ እንደሆነ በግልጽ አስቀምጦልናል፤

«በደላችንን ይቅር በለን» ከማለታችን በፊት «እኛ የበደሉንን ይቅር እንደምንል» እንድንል ያዘዘን እኛ ይቅርታ የምናገኘው ሌሎችን ይቅር ስንል ብቻ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡

ጌታችን ይህንን ጉዳይ በሌሎች የተለያዩ ቦታዎችም በተደጋጋሚ አስተምህሮናል፤ በዚሁ በተራራው ስብከት ይኸው ጉዳይ ሁለት ጊዜ በጌታችን ትምህርት ተሰጥቶበታል፡፡


«እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና በምትሰፍሩበትም መስፈሪያ ይሰፈርባችኋል፡፡ » /ማቴ.7-2/

በሌላ ቦታም እንዲህ ሲል ይህንኑ ጉዳይ በምሳሌ አስተምሯል፤

መንግስተ ሰማያት ባሮቹን ለመቆጣጠር የወደደን ንጉሥ ትመስላለች መቆጣጠርም በጀመረ ጊዜ እልፍ መክሊት ዕዳ ያለበትን አንድ ሰው ወደ እርሱ አመጡ፡፡ ባለ እዳው ሰው የሚከፍለው ስላጣ እርሱና ሚስቱ ልጆቹም ያለውም ሁሉ እንዲሸጥና ዕዳው እንዲከፈል ንጉሡ አዘዘ፡፡ በዚህም ጊዜ ባርያው ወድቆ ሰገደለትና ጌታ ሆይ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ አለው፡፡ የዚያም ባርያ ጌታ አዘነለትና ለቀቀው፡፡ ይህ ባርያ ግን ወጥቶ ከባልጀሮቹ /እንደርሱ ባርያ ከሆኑት/ መቶ ዲናር ዕዳ ያለበትን አንዱን አገኘና ዕዳህን ክፈለኝ ብሎ ያዘና አነቀው፡፡ ባልንጀራው ባርያም ወድቆ ታገሰኝ፤ ሁሉንም እከፍልሃለሁ፤ ብሎ ለመነው፡፡ እርሱ ግን ሊተወው አልወደደም፡፡ ዕዳውን እስኪከፍልም በወኅኒ አኖረው፡፡ ይህንን ያዩ ሰዎችም አዘኑ፤ ሄደውም የሆነውን ሁሉ ለንጉሡ ተናገሩ፡፡


«ከዚህ ወዲያ ንጉሡ ጠርቶ፣ አንተ ክፉ ባርያ ስለ ለመንከኝ ያን ዕዳ ሁሉ ተውሁልህ፤ እኔ እንደ ማርሁህ ባልንጀራህን የሆነውን ባርያ ልትምረው ለአንተስ አይገባህምን አለው፡፡ ጌታውም ተቆጣና ዕዳውን ሁሉ እስኪከፍለው ድረስ ለሚያሰቃዩት አሳልፎ ሰጠው፡፡»

ጌታ ይህንን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ የምሳሌውን ትርጉም እንዲህ ሲል ገልጦታል፤ ብሏል፤ «ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል»/ማቴ.18. 23- 35/

በአጠቃላይ ይቅር ለመባል ይቅር ማለት የግድ ነው፡፡ በእኛ ላይ የሚፈረድብን ፍርድ በእኛው እጅ ላይ ነው፡፡ ጌታችን በእነዚህ ትምህርቶች እንዲህ እያለን ነው «እኔ እናንተ ላይ የምፈርደው እናንተ በራሳችሁ ላይ በፈረዳችሁበት መንገድ /መልኩ ነው/»፡፡

ይቅርታ መጠየቅ

ኀጢአታችንን ካወቅንና ካመንን፣ የበደሉንንም ከልብ ይቅር ካልን በኋላ ይቅር እንድንባል መጠየቅ /መለመን/ አለብን ፡፡

«ይቅር በለን» ብላችሁ ጸልዩ ብሎ በማስተማሩ ይህንን እንረዳለን፡፡ ወደ ንስሐ አባት መሄድና ኀጢአትን ተናዞ ቀኖና መቀበል የሚገባው መጀመሪያ በዚህ መልኩ ስለ ኀጢአት ካለቀሱ በኋላ ነው፡፡ ከዚያም ቀኖና ተቀብለን ስንፈጽምም ሆነ ከዚያ በኋላ ይኸው ስለ ኀጢአት ይቅርታ መጠየቁ ይቀጥላል፡፡

በእርግጥም ይቅርታ የምንጠይቀው አዳዲስ ስለ ሠራናቸውና ንስሐ ገና ስላልገባንባቸው ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይሆን ንስሐ ስለ ገባንባቸው ስለ ቀደሙት በደሎቻችንም ጭምር ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ዳዊት «የቀደመ በደላችንን አታስብብን ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን» /መዝ.78-8/ እያልን ሰለ ቀደሙ በደሎቻችንንም እያሰብን በሕይወታችን ዘመን ሁሉ መጠየቅ አለብን፡፡

ይቅርታ የምንጠይቀው ስለምናውቃቸው /ስለምናስተውላቸው/ ኀጢአቶቻችን ብቻ ሳይሆን ስለ ማናስተውላቸውም መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ «ይቅር ብለን» ስንል እኛ ካስተዋልናቸው መንገዶች ውጪ በብዙ መልኩ እርሱን እንደምንበድል አስበን ተማጽኗችን ስለነዚህም መሆን አለበት፡፡

ስለዚህ ለጸሎት ከመቆማችንና የጌታን ጸሎት ከመጸለያችን በፊት የበደሉንን ይቅር እንዳልን እርግጠኛ መሆን አለብን እኛ የበደሉንን ይቅር እንዳልን ልንል ነውና፡፡

«እኛንም በደላችንን ይቅር በለን» ስንልም ከላይ ያየናቸውን ነገሮች ሁሉ እያሰብን፤ ይቅር ሊለን የወደደ አምላካችንንም እያመሰገንን መሆን አለበት፡፡ በእውነት ይህንን ጸሎት የምንጸልየው በዚህ መልኩ ነውን? ካልሆነ ልምምዱን ዛሬውኑ እንጀምረው፡፡ ይህንን ማድረግ እንችል ዘንደ የእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Gubae_Qana

እነሆ እኔ በእናንተ ደስ ይለኛል፡፡ ፊል. 2፡17

ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ አንሥቶ የቀና እውነተኛና መልካም ጉዞዋን የሚፈታተኑ በዙሪያዋ ጠፍተው አያውቁም፡፡ ከሰው መፈጠር በፊት በመላእክት ዘንድ የነበረችው የመላእክት ማኅበር በክፉው መልአክ /በዲያብሎስ/ እና እርሱን በመሰሉ ጭፍራዎቹ መካከል Gubae_Qanaያለ ነውርና ነቀፋ በመገኘቷ የተመረጠች ነበረች፡፡

 

በጥንተ አበው ታሪክም የምናየው ይህንኑ ነው፡፡ ከአቤል ጀምሮ እስከ ዮሴፍ ያሉ አበው በክፉዎች ብዙ መከራ የደረሰባቸው፣ በዚህች ምድር ላይ እንግዶችና መጻተኞች ሆነው የኖሩ ናቸው፡፡ጌታችን ወደዚህ ምድር በሥጋ እስከመጣበት ድረስ የነበሩት የእስራኤል ልጆች ታሪክም በክፉና መልካም ነገሮች ከሚጎረብጠው ትውልድ መካከል የነበረ ውጣ ውረድ የበዛበት ነው፡፡

የአበው ተስፋ ተፈጽሞ ጌታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ መወለዱን፤ በሞቱና በትንሣኤው ዓለምን ማዳኑን የምሥራች አምነው፤ በሐዋርያት ስብከት የተሰበሰቡ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝባቸው ማኅበረ ምእመናንም በዚሁ ታሪክ እንደኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመጀመሪያዎቹ ክፍለ ዘመናት ብዙ መከራ ስትቀበል ነውርና ነቀፋ የሌለባቸውንም ብዙ ቅዱሳን አፍርታለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሰማዕታት ዘመን ክርስቶስን እንዲክዱ ከክፉና ጠማማው ትውልድ ብዙ መከራ ደርሶባቸው በእምነታቸው በመጽናት ያለነቀፋና ነውር ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ያቀረቡ “እነሆ በእናንተ ደስ ይለኛል” ፈል.፪፥፲፯ ብሎ እግዚአብሔር የተናገረላቸው አሁን የምንዘክራቸው ብዙ ቅዱሳን ሰማዕታትን አግኝታለች፡፡

የመከራው ዘመን ለጊዜውም ቢሆን ሲያልፍ የቀጠለው መናፍቃን በቤተ ክርስቲያን ላይ ያመጡት መከራ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንን እስከ መከፋፈል የደረሱ ሰዎች በአሕዛብ መንደር የሊቃቀሙትን የሐሰት ትምህርት ከቤተ ክርስቲያን ንጹሕ አስተምህሮ ጋር ለማቀያየጥ በሞከሩ ጊዜ በትምህርታቸው ነውርና ነቀፋ የሌለባቸው ሊቃውንት አበው ብዙ መከራ ተቀብለው እውነተኛውን አስተምህሮ አጽንተዋል፡፡
ከዚያም በኋላ እስካሁን የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ለመበረዝ አልፎም ለማጥፋት የሚታትር ትውልድ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ያለንበትም ዘመን ከምንጊዜውም የበለጠ ለቤተ ክርስቲያን አስቸጋሪ ዘመን መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ክፉ አሳቢነት በአብዛኛው ተንሰራፍቶ እና ተደላድሎ የሚታይበት ዘመን ነው፡፡

 

ዘመኑ የክርስቲያኖችን ልቦና ለመክፈል በሚችሉ አያሌ እንግዳ እና አደገኛ አስተሳሰቦች በተለይ በወጣቱ ዘንድ የተናኙበት ዘመን ነው፡፡ በነዚህ ሁሉ ከክርስትና ጋር የማይስማሙ የእንግዳ አስተሳሰቦች ማዕበል መካከል ደግሞ ከኃጢአት ርቆ ለመኖር የሚታገሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆችን የሚፈታተን ልቅ ዓለማዊነት በስፋት የሚሰበክ የዓለም ሥርዓት መሆን ጀምሯል፡፡

 

በዚህ ሁሉ መካከል የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስን ምክር ሁል ጊዜም በልቦናችን መያዝ እና ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጎራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ፤ በእነርሱም መካከል የሕይወትን ቃል እየሰበካችሁ እንደብርሃን ትታያላችሁ” /ፊል.፪፥፲፬-፲፮/፡፡ ምንም እንኳ ክፉና ጠማማ ትውልድ መኖሩ የማይፈለግ ቢሆንም ከኖረ ዘንድ ግን ክፉን ለመልካም ማዋል የሚችል እግዚአብሔር ብዙ ቅዱሳን የሚገኙበት፣ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ እንደማለዳ ፀሐይ እየደመቀ እንዲሔድ ማድረጊያ መንገድ አድርጎታል፡፡ በእኛ ዘመንም እግዚአብሔርን ይህን ከማድረግ የሚከለክለው የለም፤ የሚፈለገው “በክፉና በጠማማ ትውልድ” መካከል ሆኖ እንደ ቤተ ክርስቲያን ትእዛዝ ለመኖር መጣር እና መጋደል ነው፡፡

 

ውድ ወንድሞችና እኅቶች ቤተ ክርስቲያን በብዙ ፈተና በተከበበችበት ዘመን ያለ ነቀፋ በየዋህነትና ያለ ነውር” ለመኖር እና ልዑል እግዚአብሔር በእኛ ደስ እንዲለው ክፋትን በመልካምነት ለማሸነፍ ልንጋደል ይገባል፡፡ ሁላችንም ከቤተሰቦቻችን ርቀን በዓለማዊ የትምህርት አዝመራ ፍሬአማ ለመሆን በምንጥርበት ወቅት ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጪ መንፈሳዊ ዕሴቶቻችንን ሊፍቁ ከሚሯሯጡ ቀሳጢዎች እራሳችንን መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሆኖ ለመገኘት መትጋትን የዕለት ተዕለት ጥረታችን ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህም የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱሳን ጸሎትና ረዳትነት አይለየን፡፡አሜን፡፡

 

ምንጭ፡ 4ኛ ዓመት ቁጥር 1 ጉባኤ ቃና ጥቅምት 2004 ዓ.ም

weddingpic

ሰርግ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ትምህርት

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

ኅዳር 06/2004 ዓ.ም.

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ቅዱስ ጳውሎስ ለቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክት ም.፬፥፲፪ ላይ ያለውን ኃይለ ቃል በተረጎመበት ፲፪ኛው ድርሳኑ በዘመኑ የሚፈጸመውን የሰርግ ሥርዐት መሠረት በማድረግ ሰርግን አስመልክቶ ሰፋ ያለ ትምህርትን ሰጥቶአል ፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በሰርግ ምክንያት የሚወጡትን ወጪዎችና ግርግርና ሁካታ አጥብቆ የሚቃወም አባት ነው ፡፡ በዚህም ጽሑፍ ይህን ወደማስተዋል ልንመጣም እንችላልን ፡፡ መልካም ንባብ

ስለዚህ እንዲህ ብሎ ያስተምራል ፡- ትዳር ምንድን ነው? ትዕይንት(ትያትር) ነውን ? አይደለም፡፡  ምንም እንኳ እናንተ ለትዳርና ለምሳሌውweddingpic አክብሮት ባይኖራችሁ ትዳር ግሩም ምሥጢርና የታላቅ መንፈሳዊ ምሥጢር ምሳሌ ነው ፡፡ ቅዱስ    ጳውሎስ ስለዚህ ሲያስተምር “ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው”   ይልና ጨምሮ “እኔ ግን ስለ ክርስቶስና    ስለ  ቤተ ክርስቲያን እላለሁ” ይላል   ፡፡(ኤፌ.፭፥፴፪) ጋብቻ የቤተ ክርስቲያንና   የክርስቶስ ምሳሌ ነው ፤  እንዲህ በከበረ    ምሥጢር ላይ ዳንኪረኞችን በመጋበዝ   ዝሙትን ታስተዋውቁበታላችሁን ? ነገር   ግን  ከእናንተ መካከል አንዱ እኔን፡- እንዲህ ስትል ደናግል ወይም ያገቡት አይጨፍሩ እያልክ ነው ፤  እንግዲያ እነርሱ በዚህ ሰርግ ላይ ካልጨፈሩ ማን ሊጨፍር ነው ? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል ፡፡ ማንም  አይጨፍር ነው መልሴ ፡፡

በአሕዛብ ዘንድ ይህን በመሰሉ ሥርዐቶቻቸው ዳንኪረኞች ዳንኪራቸውን ያቀርባሉ፡፡ በእኛ ግን ማንኛውም ምሥጢራት ሲከናወኑ በጸጥታ፣ በትሕትናና  በጥሩ ሥነምግባር እንዲሁም በመልካም ሥርዐት ነው፡፡ ይህ የጋብቻ ሥርዐት አመንዝሮች ከተጠሩበት እግዚብሔርን የማይፈሩ ከተጋበዙበት እንዴት ብለን ነው መንፈሳዊ ጋብቻ ብለን ልንጠራው የምንችለው ? እንዲህ ከሆነ እንዴት ተብሎ ነው ሁለቱ አካላት አንድ ሆነዋል ልንል የምንችለው ?

ክርስቶስ በተገኘበት ጋብቻ ግን ዳንኪራ የለም የእምቢልታም ድምፅ አይሰማበትም፡፡ ነገር ግን ግሩም የሆነ ጸጥታ የሰፈነበት፣ በታላቅ መንፈሳዊ ሥርዐት የሚከናወን ነው፡፡ በዚህ ሥርዐት  አንድ አካል ወደመሆን ሲመጡ አንድነታቸው ሕይወት አልባ ፍጥረታት እንደሚኖራቸው አንድነት ወይም በዚህ ምድር የሚታየውን ዓይነት አንድነት አይደለም፡፡ ነገር ግን የእግዚአብሔር አርዓያና አምሳል ሆነው አንድ ይሆናሉ፡፡ ይህ ታላቅ የሆነ ምሥጢር በሚከናወንበት ሥፍራ እንደ አራዊት ታላቅ ሁካታና ረብሻ እንዲሁም ነፍስን የሚያሳድፉ ታላቅ የሆነ በደል ይፈጸማልን ?

ሁለቱ አንድ አካል በመሆናቸው በዚህ ያለውን የፍቅርን ምሥጢር አስተውል ፡፡ እነዚህ ሁለት አካላት ሁለትነታቸውን ይዘው የሚቀጥሉ ከሆነ ብዙ ሊሆኑ አይችሉም ፡፡ ነገር ግን አንድ ወደመሆን ሲመጡ ብዙዎች ይሆናሉ ፡፡ ከዚህ ምን እንማራለን ? የትዳርን ታላቅነት አይደለምን ? ሥላሴ ሁለት የሆነው አካል አንድ አድርጎ ፈጠረው ስሙንም ሰው አለው፡፡ ይህን አንድ የሆነው አካልንም ሁለት በማድረግ ገለጠው ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ አካላት ሁለት ቢሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ  ግን አንድ ይሆኑ ዘንድ ነበር ፡፡

በዚህም ምክንያት አንዱ አምሳሉን ለመውለድ ብቻውን ብቁ እንዲሆን አላደረገውም ፡፡ ስለዚህ ከተቃራኒው አካል ጋር አንድነትን ላልመሠረተ ሰው አንድ አካል የሚባለው ስያሜው አይሰጠውም ነገር ግን የሌላኛው ግማሽ አካል ይባላል ፡፡ ለዚህም ምስክሩ ልጅን መውለድ አለመቻሉ ነው ፡፡ ይህ እግዚአብሔር አስቀድሞ የሠራው ሥርዐት ነው፡፡ የጋብቻን ምሥጢር አስተዋላችሁን ? አስቀድሞ አንድ አድርጎ ፈጠራቸው በኋላም ነጣጠላቸው ፤ እንደገና ሁለት የነበሩትን እነዚህን ወገኖች ወደ አንድነት አመጣቸው ፡፡ እንዲህም አድርጎ ስለሠራው ሰው በትዳር አንድ ከሆኑ ወገኖች እንዲፈጠር ሆነ ፡፡

ባልና ሚስት ሁለት አካላት አይደሉም ነገር ግን አንድ አካል ናቸው ፡፡…. ይህን “ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር …ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው” (ዘፍ.1፡27) በሚለው ቃል ማረጋገጥ ይቻላል  ፡፡ ባል ራስ ነው ፤ ሚስት ደግሞ ቀሪው አካል ናት ፡፡ ስለዚህ አንዱ የደቀመዝሙርነት ማዕረግ ሲኖረው አንዱ የመምህርነት ቦታ ይይዛል አንዱ መሪ ሲሆን ሌላው ደግሞ ታዛዥ አደረገው ፡፡ ሔዋን ከአዳም ጎን ትገኝ እንጂ ወደ ኋላ መለስ ብለን የእርሱዋን ልደት ስንመረምረው አንድ አካል እንደነበሩ ማስተዋል እንችላለን  ፡፡በዚህ ምክንያት አንድ አካል እንደሆኑ ለማስረዳት ሲል እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን ረዳት አላት፡፡ (ዘፍ.2፡18) በአንድነት ከመኖራቸውና አባትና እናት ከመሆን ባለፈ አንድ አካል በማድረግ አከበራቸው፡፡ (ዘፍ.2፡24)

በሌላ መልኩ ደግሞ አባት ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ የራሳቸውን አካል አግኝተው በመጣመራቸው እጅግ ደስ ይሰኛል፡፡ አባት ምንም ሀብት የተረፈው ባለጠጋ ቢሆን ወንድ ልጁ ወይም ሴት ልጁ ያላገቡ  ከሆኑ ውስጡ ምንም ዓይነት መረጋጋት አይኖረውም፡፡ ይህን ታግሶ መኖርም አይቻለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምንም ልጅ ከእናቱ አካል ተከፍሎ የተወለደ ቢሆን በዚህ ምድር ዘሩ እንዲቀጥል ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ስለዚህም በራሱ ሙሉ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ሚልክያስ “እግዚአብሔር የሕይወትን መንፈስ አንድ አድርጎ ጠብቆልን የለምን? እርሱም የሚፈልገው ምንድን ነው? ዘር አይደለምን? (ሚል.፪፥፲፭) ይለናል፡፡

እንዴት ነው ታዲያ አንድ ሥጋ ወደ መሆን የሚመጡት ? እጅግ ንጹሕ የሆነን ወርቅን ማግኘት ከፈለግህ ወርቅህን ከሌላ ወርቅ ጋር ትቀይጠዋለህ፤ ከእነዚህም አንድነት ልዩ የሆነ ወርቅ ይገኛል፡፡ በዚሁ መልክ እናት በደስታ ዘርን ተቀብላ ከራሱዋ ጋር በማዋሐድ፣ ፅንሱን በመመገብና እንክብካቤ በማድረግ ሰው ሆኖ ወደዚህ ዓለም እንዲመጣ የራሱዋን ድርሻ ትወጣለች፡፡ልጅ እንደ ድልድይ ነው ፡፡ በእርሱም ምክንያት ሦስቱ አንድ ሥጋ ይባላሉ ፡፡ ልጅ ሁለቱ አካላት ፍጹም አንድ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል ፡፡ በመካከላቸው ባለው ታላቅ ወንዝ ምክንያት የተለያዩ ከተሞች በወንዙ ላይ በሚሠራው ድልድይ ምክንያት ሁለት መሆናቸው ቀርቶ አንድ እንዲሆኑ እንዲሁም ልጅም እንዲህ ነው ፡፡

ልጅ በፊት በባልና በሚስት መካከል የተፈጠረውን አንድነት ይበልጥ ያጠናክረዋል ፡፡ ለባልና ሚስት ድልድይ የሆነው ልጅ የሁለቱ ተዋሕዶ ውጤት ነውና ፡፡ ራስና ቀሪው አካል በአንገት አንድ እንዲሆን ፣ እንዲሁ ልጅም በባልና በሚስት መካከል ሆኖ በእነርሱ መካከል ያለውን አንድነት ይበልጥ ያጠብቀዋል ፡፡ ከልዩነታቸው ይልቅ አንድነታቸውን በልጅ ምክንያት ይበልጥ እየጠበቀ ይመጣል ፡፡

እንዲሁም ዘማርያን በአንድነት ሲዘምሩ ዝማሬው አንድ ሆኖ ይወጣል ፡፡ ወይም ሁለት ወገኖች እጃቸውን እርስ በእርሳቸው ቢያቆላልፉ ከእንግዲህ አንድ እንጂ ሁለት አይደለንም ማለታቸው እንደሆነ እንዲሁ ባልና ሚስትም በአንድነታቸው በሚፈጠሩት በልጅ በኩል ፍጹም የሆነ አንድነትን ይመሠርታሉ ፡፡ ስለዚህ ጌታችን ግሩም በሆነ ቃሉ “ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ አለ” በተለይ በልጆቻቸው ፡፡ እንዲህ ሲባል ባልና ሚስት ልጅ ካልወለዱ ሁለት እንደሆኑ አይቀጥሉም ማለት ነውን ? በፍጹም አይደለም ፤ ሁለቱ በሥጋ ሲተባበሩ አንድ አካል ወደ መሆን ይመጣሉ ፡፡ የሽቶ ዘይትን ከሌላ የሽቶ ዘይት ጋር ሲደባልቁት አንድ እንዲሆኑ ከተቀየጡም በኋላ አንድ የሽቶ ዘይት እንዲሆኑ እንዲሁ በዚህም እንዲሁ ነው ፡፡

እኔ አሁን እንዲህ በግልጽ ስለዚህ ጉዳይ በመናገሬ አንዳንዶች ነውር ነው በማለት ትምህርቴን እንደሚጠየፉት እረዳለሁ ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው ? ይህን አሁን የምናገረውን እንደ ብልግና ንግግር ስለሚቆጥሩት ነው ፡፡እነዚህ ወገኖች በትዳር ውስጥ የሚፈጠረውን እንደዚህ ላለው አንድነት ልዩ የነቀፋ ስም ይሰጡታል (ብልግና ይሉታል) ፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ “መጋባት በሁሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን”(ዕብ.፲፫፥፬) ብሎ አስተምሮናል ፡፡

ስለምን እናንተ ክቡር የሆነውን እንደ ነውር ፣ ንጹሕ የሆነውን እንደ ርኩስ ትቆጥሩታላችሁ ? ይህ ጋብቻን እንደ ርኩሰት የሚቆጥሩትና በራሳቸው አካል ላይ ዝሙትን የሚፈጽሙ የከሃድያን አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም ነው ይህን ክፉ አስተሳሰብ ለማጥራትና ወደ ቀድሞው ክብሩ ለመመለስ ስል በዚህ መልክ ያስተማርኩት፡፡ በዚህም እስተምህሮ የከሃድያን አፍ ይዘጋል፡፡

እነርሱ የእግዚአብሔርን ድንቅ ስጦታንና የልደታችን መሠረት የሆነውን ተራክቦን ሲነቅፉት ይሰማሉ፡፡

ይህን የመገኛችን ምንጭ የሆነውን ተራክቦ እንደ ቆሻሻና እንደማይጠቅም ረብ የለሽ ከንቱ ነገር አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ስለዚህ እኛ ይህን አስተምህሮ ከዚህ ዓይነት አመለካከት ንጹሕ ልናደርገው ይገባናል፡፡ተወዳጆች ሆይ ይህ ጉዳይ ሲነሣ እንደሚጠየፉት ከሃዲያን እንድንሆን አልሻም፤ ይልቁንስ ከእነርሱ አጸያፊ ሥራ ትሸሹ ዘንድ እመክራችኋለሁ፡፡ ነገር ግን በዚህ እነርሱን የምትመስሉዋቸው ከሆነ በቀጥታ እግዚአብሔርን እየተሳደባችሁ ነው፡፡

ትዳር ለቤተ ክርስቲያን የተፈጸመላት ምሥጢር ምሳሌ እንደሆነ ላስረዳችሁን? ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን የራሱ ሲያደርጋትና በመንፈሳዊ ተዋሕዶ ከእርሱዋ ጋር አንድ ሲሆን ቅዱስ ጳውሎስ “እንደ ንጽሕት ድንግል” ይልና “እናንተን ለክርስቶስ ላቀርብ ለአንድ ወንድ አጭቻችኋለውና” ይለናል፡፡ (፪ቆሮ.፲፪፥፪) ታዲያ እኛ ምን ሆንን ? የእርሱ የአካል ሕዋሳቶችና “ሥጋው” ሆንን፡፡ ይህን ሁሉ በማስተዋል ታላቅ ምሥጢር የሆነውን ትዳርን ከማቃለል እንቆጠብ፡፡ ሰርግ ማለት የክርስቶስ በሰዎች መካከል ሰለመገኘቱ የሚመሰልበት ታላቅ ምሥጢር ነው፡፡ ታላቅ የሆነው ይህ ምሥጢር በሚፈጸምበት ቦታ ስካር የሚገባ ነውን? ንገረኝ  የንጉሥ ምስል በቆመበት ስፍራ ሆነህ እርሱን ማዋረድ ትጀምራለህን? ይህን ፈጽሞ አታደርገውም፡፡

አሁን ግን ሰርግ ሲሲረግ  ሰርጉ ለተመሰለበት ምሳሌ ተገቢውን አክብሮት ከመስጠት ይልቅ ቦታውን የኃጢአት መፍለቂያ ምንጭ አድርገነዋል፡፡ ሥርዐቱ ሙሉ ለሙሉ ተለውጦ ሕገወጥ ሥራዎች የሚፈጸሙት ሥርዐት ሆኗል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸው” አላለንምን? እንዲሁም “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ፡፡” (ኤፌ.፭፥፬፤፬፥፳፱) ብሎ አላስተማረንምን? አሁን ግን በዚህ ታላቅ በሆነ ምሥጢር ላይ የስንፍና ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛ ነገሮች፣ ፌዝና ቀልዶች ሞልተውበታል፡፡

እነዚህ ከንቱ ነገሮች በቀላሉ የሚቀርቡም አይደሉም  እኮ እነዚህ ከንቱ ነገሮች እንደ ጥበብ ተቆጥረው በአቅራቢዎቻቸው ተቀናብረው በሰርጉ ለታደሙት ይቀርባሉ፡፡ ይህንንም ለሚያቀርቡ ሰዎችም ታላቅ ክብርና  ምስጋና ይሰጣቸዋል፡፡ ይገርማል  ኃጢአት እንደ ጥበብ ተቆጠረ፡፡ ከዚህም በላይ ኃጢአትን ለእኛ የሚያስተዋውቁንን ወገኖች ትዕይንት የምንከታተለው  ትኩረት ሰጥተንና በጸጥታ ነው፤ ከአንደበታቸው የሚያወጡትንም ቃል በአጽንዖት በመስማት ጭምር እንጂ እንዲያው በከንቱ አናዳምጣቸውም፡፡ ስለዚህ ዲያብሎስ በዚህ የሰርግ ቤት ለእርሱ ወታደሮች ይሆኑ ዘንድ ሠራዊቶችን ይመለምላል፡፡ ስካር ባለበት ቦታ ዝሙት አለ፡፡ ከንቱ ንግግር ባለበት ቦታ ሰይጣን የራሱን አስተዋጽኦ ለማድረግ ይመቸዋል፡፡ እስቲ ንገረኝ እንዲህ በሆነ ቦታ ሰይጣን እንዲገኝ እየጋበዝህ ክርስቶስ የሚገኝበትን ምሥጢር እየፈጸምኩ ነው ትላለህን?

አንተ እኔን ለዚህ ነገር ጠንካራ ተቃዋሚ እንደሆንኩ አድርገህ ትቆጥረኛለህ ፡፡ ከዚህ ጥመትህ ትድን ዘንድ አንተን በጽኑ የሚገሥጽህንም ሰው እንዲህ እንድትመለከተው አውቃለሁ ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ አንተን “የምትበሉም የምትጠጡም ብትሆኑ ወይም ማናቸውም ተግባር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት”(፩ቆሮ.፲፥፴፩) አላለህምን ? አንተ ግን ሥራዎችህን ሁሉን ራስህን ለማዋረድና የሰውን ልጅ ለሚጎዱ ነገሮች ታውላዋለህ ፡፡ ነቢዩስ “ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ በረዓድም ደስ ይበላችሁ”(መዝ.፪፥፲፩) አላለህምን ? አንተ ግን ሥርዐት አልባ ሆነህ ትመላለሳለህ ፡፡

በአንድ ጊዜ ደስታውንና ጥንቃቄውንም ማስኬድ ትፈልጋላችሁን? አጥንትን የሚያለመልም መዝሙርን መስማትስ ትሻላችሁን? በእርግጥ ከመዝሙሮች ሁሉ የሚልቅ መዝሙርን ልትሰሙ ትችላላችሁ፡፡ እናንተ ግን አትፈቅዱም፤ ብትፈቅዱ ግን  ሰይጣናዊ ዘፈኖች ከመስማት ይልቅ መንፈሳዊ ዝማሬን ለመስማት ትበቃላችሁ፡፡ የመዘምራንን ግሩም የሆነ መጓደድ መመልከት ትሻላችሁ? እነሆ የመላእክት ዝማሬና መጓደድ፡፡ እንዴት ሆኖ ነው የእነርሱን ዝማሬን መስማት በልዑል ፊት መጓደዳቸው መመልከት የሚቻለው ብሎ የሚጠይቀኝ ካለ “እነዚህን ግሳንግሶችን ከነአካቴው ከተውክና በሰርግህ ክርስቶስ እንዲገኝ ከፈቀድክ ይህ ይሆናል፡፡  ክርስቶስ በሰርግህ የታደመ ከሆነ መላእክትም ከእርሱ ጋር በሰርግህ ይገኙልሃል፡፡

ከአንተ ዘንድ ፈቃዱ ካለ እርሱ በአንተ ሰርግ መገኘት ብቻ አይደለም  ውኃውን ወደ ወይን ጠጅነት በመቀየርም ሰርግህን ያደምቅልሃል፡፡ እንደ ውኃ ቀዝቃዛና ወራጅ የሆነውን የዚህን ዓለም ደስታና ፈንጠዝያ አጥፍቶ መንፈሳዊ ደስታን ከሚያጎናጽፈው ከዚህ ተአምር በላይ ምን ድንቅ ተአምር አለ!! ይህ ነው ውኃውን ወደ ወይንነት የመቀየሩ ትርጉም፡፡ እንቢልታ ነፊዎች ባሉበት ክርስቶስ ፈጽሞ አይገኝም፡፡ እርሱ በዚህ ሰርግ ቢገኝ እንኳ መጀመሪያ ይህንን አስወግዶ ነው፡፡ ከዚያም የራሱን ተአምርን ይፈጽማል፡፡ ከዚህ የሰይጣን መሳሪያ ከሆነ እቢልታ በላይ ምን የሚጠላ ነገር አለ? ሁሉ በሥርዐት ካልሆነ ምንም ነገር ያለጥቅም ይሆናል፡፡ ድካማችን ሁሉ ያለፍሬ ይቀራል እኛንም ወደ ውርደት ይጥለናል፡፡

ከመልካም ሥነምግባር የበለጠ አስደሳች ነገር የለም፣ ሥርዐት ወዳድ ከመሆን የበለጠ ጣፋጭ የሆነ ነገር የለም፣ ጽድቅ ለመፈጸም ቆራጥ ከመሆን የበለጠ ተወዳጅ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ሥርዐቶቻችን ልክ እኔ ስለጋብቻ ሥነ ሥርዐት ባስተማርኩት መልክ ይሁኑ፡፡ እንዲህ ከሆነ ደስተኛ ልንሆን እንችላለን፡፡

ነገር ግን ጋብቻን ሊያደርግ የሚሻ ሰው ከማን ጋር ጋብቻውን መፈጸም እንዳለበት ይጠንቀቅ፡፡ ሴት ልጅ ያለችው ሰው   አስቀድሞ እውነተኛና እርሱዋን ሊንከባከባት የሚችል ባልን ሊፈልግላት ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ወንድ ለአካል ራስ እንዲሆን ሊመረጥ ይገባዋል፡፡ ለእርሱ ስትሰጥም እንደ ባሪያ አድርጎ ሊይዛት ሳይሆን እንደ ልጁ ሊያያት ሊሆን ይገባል፡፡

ሀብት ስላለው ወይም ከከበረ ቤተሰብ በመሆኑ ወይም ሰፊ ግዛት ስላለው እርሱን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ አትምረጡ፡፡ ነገር ግን በነፍሱ ትሑት፣ አስተዋይ፣ ቅንነት ያለውና እግዚአብሔርን የሚፈራ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ምረጡ፡፡ እንዲህ ከሆነ የምታፈቅሩዋት ልጃችሁ በደስታ ልትኖር ትችላለች፡፡ ባለጠጋ ሆኖ በምግባሩ ግን ብልሹ የሆነን ሰው ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ያጫችሁት ከሆነ እርሱዋን አለመጥቀማችሁ ብቻ ሳይሆን እርሱዋን ነጻ ሰው ከማድረግ ይልቅ የእርሱ ባሪያ በማድረግ ትጎዱአታላችሁ፡፡ ልጃችሁ የእርሱ ሚስት በመሆኑዋ ምክንያት በምታገኛቸው ሀብት ደስ ከመሰኘት ይልቅ እርሱዋን እንደ ባሪያ ቆጥሮ በእርሱዋ ላይ የሚያደርስባት በደል የከፋ ይሆናል፡፡

እንዲህ ዓይነት ድርጊትን ከመፈጸም ትቆጠቡ ዘንድ እለምናችኋለሁ ፡፡  ነገር ግን ከእርሱዋ ጋር ተቀራራቢ ኑሮ ያለውን ለልጃችሁ ባል ይሆን ዘንድ ታጩ ዘንድ እመክራችኋለሁ ፡፡ ይህ ባይሆን ምንም ሀብት ለሌለው ነገር ግን በጎ ሕሊና ላለው ሰው ትድሩዋት ዘንድ አሳስባችኋለሁ ፡፡ እንዲህ በማድረጋችሁ ልጃችሁን ሌላው ቢቀር ለአንድ ጌታ ልጃችሁን እንደባሪያ ከመሸጥ ተቆጥባችሁ በትክክለኛው ትርጉም እንደ ባል ሊሆናት ለሚችል ሰው መስጠት ይቻላችኋል ፡፡

ለልጅህ ባል የሚሆናትን ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰውን ሰው በጥንቃቄ መርምረህ በማግኘት  ልትድራት ስትዘጋጅ ክርስቶስ ኢየሱስ በጋብቻው ሥነ ሥርዐት ላይ  እንዲገኝልህ ጥራው፡፡  በዚህ የደስታ ቀንህ እርሱን በእንግድነት እንዲገኝ  ስለጋበዝከው ቅር አይሰኝም፡፡ ምክንያቱም እርሱ የሚገኝበት ምሥጢር ነውና፡፡ አዎን ከዚሀ ይልቅ ግን አስቀድመህ ለልጅህ ባል አድርገህ ያጨኸውን ሰው  እርሱ እግዚአብሔር ተወዳጅ ባል ያደርገው ዘንድ ለምነው፡፡

የአብርሃም ባሪያ እንኳ ያላደረገውን አስከፊ ድርጊት ከማድረግ ግን ራስህን ጠብቅ፡፡ እርሱ በጌታው በአብርሃም በተላከ ጊዜ እግዚአብሔርን መንገዱን ያቀናለት ዘንድ ለምኖት ነበር፡፡ እንዲህ በማድረጉም ሁሉን ነገር ሰመረለት፡፡ እንዲሁ አንተም ለልጅህ ባልን በመፈለግ አእምሮ ቢባክን ወደ እግዚአብሔር  “ጌታ ሆይ አንተ የፈቀድከውን አድርግ”  ብለህ ጸልይ፡፡ ለእርሱን እንዲህ በማለት ፈቃድህን አሳልፈህ ስጠው፡፡ በዚህ መልክ ለእርሱ ክብርን ስጥ፤ እርሱም በምላሹ ፈቃድህን በመፈጸም ያከብርሃል፡፡ በእርግጥ አንተን ሁለት ሥራዎች ይጠብቁሃል፡፡ እነርሱም ፈቃድህን ለእርሱ ሙሉ ለሙሉ መስጠትና፣  እርሱ የመሰከረለትን በጥሩ ሥነ ምግባር የታነጸውን ሰው መሻት ናቸው፡፡

የልጅህን ሰርግ ለመሰረግ በምትዘጋጅበትም ጊዜ እቃዎችንና ልብሶችን ለመዋስ ስትል ቤት ለቤት አትዙር፡፡ ምክንያቱም ሰርጉ የሚፈጸመው ትዕይንትን ልታቀርብ ወይም የልጅህን ቁንጅና ልታሳይበት አይደለምና፡፡ በመሆኑም ሰርግህን ልትፈጽም በምትዘጋጅበት ጊዜ ባለህ ነገር ብቻ ቤትህ ለማስዋብ ሞክር፡፡ በመቀጠል ጎረቤቶችህን ወዳጆችህንና የቅርብ ዘመዶችህን ጥራ፡፡ እንዲሁም ጥሩ ባሕርይ አላቸው የምትላቸውን ሰዎች በሰርጉ እንዲታደሙልህ ጋብዝ፡፡ ሙዚቀኞችን ግን ፈጽመህ አትጥራ ለእነርሱ የምታወጣው ወጪ በራሱ ከፍተኛና ሊሆን የማይገባ ነው፡፡

ከእነዚህ ሁሉ አስቀድሞ ግን ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ ጋብዘው፡፡ እርሱን እንዴት አድርገህ እንደምትጋብዘው ታውቃለህን ? “ንጉሡም መልሶ፡- እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት ይላቸዋል”(ማቴ.፳፭፥፵) እንዲል ድሆችን በሰርግ እንዲገኙ በማድረግ ክርስቶስን በሰርግህ እንዲገኝ ማደረግ ይቻልሃል፡፡ ስለክርስቶስ ብለህ ድሆች በሰርግህ እንዲገኙ ስላደረግህ ሰርግህ የተበላሸ አድርገህ አትቁጠር፤ ነገር ግን ሴሰኞችን በሰርግህ ብትጋብዝ ሰርግህ በእርግጥ የረከሰ ይሆናል፡፡ ድሆችን ወደ ሰርግህ መጥራትህ ሀብት ወደ ቤትህ እንዲገባ መጥራትህ ነው፡፡ ቅምጥሎችን ከሰርጉ እንዲታደሙ የጠራህ እንደሆነ ግን ውርደትን እየጠራህ ነው፡፡

ሙሽሪትን በወርቅ ጌጣ ጌጦች አታስጊጣት ነገር ግን በጥሩ ሥነ ምግባርና በጭምትነት አስጊጣት እነዚያን ነገሮች ፈጽመህ አትፈልጋቸው፡፡ ግርግርና ሁካት በሰርግህ ፈጽሞ አይኑር፡፡ ሙሽራውን ጥራና ሚስቱን ይዞ ወደ ቤቱ ይግባ፡፡ በምሳና በራት ግብዣህ ላይ አስካሪ  መጠጦች አይገኙ፡፡ ነገር ግን ሰርግህ በደስታ የሞላበት ይሁን፡፡

እንዲህ አድርገህ ሰርግህን በመከወንህ ምን ያህል ተጠቃሚ እንደሆንክ ለማስተዋል እንድትችል በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚቆጠሩት ጋር ያንተን የሰርግ ሥነ ሥርዐት አስተያይ፡፡ ሌላው ይቅርና ያንተን ሰርግ የተመለከተ ሰው ሁሉ የቁንጅና ውድድር ሳይሆን በእውነተኛ ትርጉም ሰርግን እንዳየ ምስክርነትን ይሰጥሃል፡፡ በዘመኑ ሰርግ ተብለው ከሚጠሩት ውስጥ ግን እጅግ የበዙ ክፋቶች ታጭቀው ይገኙበታል፡፡ በአዳራሽ የሚፈጸመው ሰርግ በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት ከሚደረገው ጋር ሲነጻጸሩ በቶሎ የሚጠናቀቁ ሰርጎች አይደሉም ፡፡ ከዚህም ባለፈ በውሰት የመጡት እቃዎች ሊጠፉም ስለሚችሉ ፍጻሜው ከደስታ ይልቅ ሊቋቋሙ ከማይችሉት ከባድ ሃዘን ውስጥ ሊጥል ይችላል ፡፡ ይህ የከበደ ሃዘን በአማች ላይ የሚታይ ነው ፡፡ ነገር ግን ሙሽሪትም ከዚህ ሃዘን ነጻ ልትሆን አትችልም ፡፡ በሰርጉም ፍጻሜም የቤቱ ውበቱ ጠፍቶ በሃዘን ታወሮ ይታያል ፡፡

በጥንቃቄና እግዚአብሔርን በመፍራት በሚከናወነው ሰርግና በአሕዛብ ልማድ በሚፈጸመው ሰርግ መካከል ሰፊ የሆነ ልዩነት አለ፡፡ በዚህ ክርስቶስ ሲገኝ በዚያ ግን ሰይጣን ነግሦ ይታይበታል ፡፡ በዚህ ፍጽም የሆነ ፍስሐ ሲታይ በዚያ ደግሞ ጥቅ ያጣ አለባበስ ይተዋወቅበታል ፡፡ በዚህ ፍጹም ደስታ ሲኖር በዚያ ግን ሕማምና ሰቆቃ ይተርፈዋል ፡፡ በዚያ የወጣው ወጪ ታላቅ ሲሆን በዚህ ግን እዚህ ግባ የማይባል ወጪ ብቻ ያስተናግዳል ፡፡ በዚያ ግርግርና ሁካታ ሲታይ በዚህ ግን ግብረ ገብነት ጎልቶ ይንጸባረቅበታል፡፡ በዚያ ኃጢአት ሠልጥና ስትታይ በዚህ ግን ኃጢአት ፈጽማ አትኖርም ፡፡ በዚያ ስካሮች ሲኖሩባት በዚህ ግን ሰላም ወዳዶች ይታዩባታል ፡፡ በዚያ ሁካታና ጠብ ሲኖር በዚህ ግን እርጋትና ሰላም ሰፍነው ይታዩበታል ፡፡

እነዚህን ሁሉ ልብ በሉ ፡፡ እግዚአብሔርን ደስ በማሰኘት እርሱን ለሚያፈቅሩት ካዘጋጀው ከመንግሥቱ ተካፋዮች እንድንሆን ከዚህ ቀን ጀምረን ይህን ክፉ ልማድ ከራሳችን አርቀነው እናስወግደው ፡፡ የሰውን ልጅ ከመውደዱ የተነሣ ሰው በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር አብ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋር ክብር ምስጋና ዛሬም ዘወትርም እስከዘለዓለሙ ይሁን አሜን !!

የቅዱስ ኤፍሬም ቅኔያዊ መዝሙራት

ጥቅምት 30/2004 ዓ.ም

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

መግቢያ

የሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም አጭር የሕይወት ታሪክ

ቅዱስ ኤፍሬም 299 ዓ.ም ገደማ ንጽቢን በምትባለው ታላቅ ከተማ ተወለደ፡፡ ንጽቢን በጥንታዊቱ የሮም ግዛት በምሥራቅ የምትገኝ ከተማ ነበረች፡፡ አብዛኞቹ የታሪክ ጸሐፍት እንደሚስማሙበት ቅዱስ ኤፍሬም ከክርስቲያን ቤተሰብ የተገኘ ሲሆን በተወለደባት ከተማ በድቁና ሲያገለግል ረጅም የእድሜ ዘመኑን ያሳለፈ ቅዱስ ነው፡፡ አንዳንድ የታሪክ ጸሐፍት ግን የቅስና ማዕረግ አንዳለውም ይተርካሉ፡፡ ነገር ግን በአብዛኛዎቹ የሶርያ የታሪክ ጸሐፊያን ዘንድ ቅዱስ ኤፍሬም ዲያቆን እንደነበረ ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ስለዚህም እስካሁን ድረስ በሶርያውያን ክርስቲያኖች ዘንድ የድቁና ማዕረግ በቅዱስ ኤፍሬም ምክንያት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ማዕረግ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ቅዱስ ኤፍሬም በንጽቢን ከተማ ሳለ በቤተ ክርስቲያን በሴቶች ዘማሪያን የሚቀርቡ ብዙ የመዝሙር ድርሰቶችን ደርሶአል፡፡ ቢሆንም በ363 ዓ.ም የሮም መንግሥት በመዳከሙ ምክንያት የፋርስ ንጉሥ ንጽቢን ለእርሱ ተላልፋ እንድትሰጥና በውስጡዋም የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከከተማዋ ለቀው እንዲወጡ ባቀረበው የመደራደሪያ ነጥብ የተነሣ ንጽቢን ለፋርስ መንግሥት ተሰጠች፤ ክርስቲያኖችም ከከተማዋ ወጥተው ተሰደዱ፡፡ ቅዱስ ኤፍሬምና ደቀመዛሙርቱም ወደ ዑር ወይም ኤዲሳ ወደምትባለው ከተማ አመሩ፡፡ በዚያም የእድሜውን ዐሰርት ዓመታት አሳለፈ፡፡ ዑር የምትባለው ከተማ በአሁኑ ጊዜ ኡርፋ በመባል የምትታወቀው በደቡባዊ ቱርክ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ በዚህም ሳለ በከተማይቱ የተነሡትን ከሃዲያንን በመቃወም ታላላቅ ሥራዎችን ሠርቶ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሚገርም ሁኔታ የግሪካውያንን ፍልስፍና ጠንቅቆ የሚያውቅ ስለመሆኑ ከጽሑፎቹ መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ድርሰቶቹን ሲደርስ ሴማዊውን የአጻጻፍ ስልት ሳይለቅ ነበር፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በሕይወቱ ክርስቶስን መስሎ ሲያገልግል ሳለ በተወለደ በ67 ዓመቱ ገደማ (በኤዲሳ) ዑር ተቀስቅሶ በነበረው ወረርሽኝ የተጎዱትን ሕመምተኞችን ሲረዳ ቆይቶ በመልካም ሽምግልና ግንቦት 29 በ366 ዐረፈ፡፡ (ዘመን አቆጣጠሩ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ነው)

 

ቅዱስ ኤፍሬም  ከጻፋቸው የመዝሙር ድርሰቶች መካከል

1.ስለክርስቶስ ሥጋዌ 59 መዝሙራት
2.ጾምን አስመልከቶ 67 መዝሙራት
3.ንጽቢንን አስመልክቶ 77 መዝሙራት
4.ስለክርስቶስ ሙሽራ አይሁድን በመቃወም የጻፈው 66 መዝሙራት
5.ስለቤተ ክርስቲያን 52 መዝሙራት እንዲሁም ሌላ ስለ ቤተ ክርስቲያን የሚያወሳ 52 መዝሙራት
6.ስለእምነት 87 መዝሙራት
7.አሮኒየስ ለሚባለው ከሃዲ የሰጠው መልስና ስለ ገነት 56 እና 15 መዝሙራት
8.ንስሐ ስለሚገቡ ክርስቲያኖችና በሞት ለተለዩ የሚቀርቡ መዝሙራትን አዘጋጅቶአል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ  ዘፍጥረትን፣ ዘጸአትን፣ ዐራቱ ወንጌላትን፣ የጳውሎስ መልእክታትን ተርጉሟል፡፡ የቅዱስ ኤፍሬም ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ላይ ይደርብንና ከዚህ በማስከተል ከመዝሙር ድርሰቶቹ መካከል አንዳንዶቹን እንመለከታለን፡፡
ስለገነት የደረሰው መዝሙር

በዚህ መዝሙር ቅዱስ ኤፍሬም እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን ዓለት በመጥቀስ እግዚአብሔር ፍጥረታትን እንዴት እንደፈጠራቸውና ሌሎችም ስለገነት ያለውን አስተምህሮዎቹን እናገኝበታለን፡፡

1. እስራኤላውያንን በምድረ በዳ ይከተላቸው የነበረውን አለትን አስታውሼ፤

ዓለማትን የፈጠረውን የእግዚአብሔርን ቃል ልብ አልኩ፤
እንደ ታላቅ ወንዝ ለእነርሱ ከአለቱ ውስጥ የፈለቀው ውኃ፤
በውስጡ ካለው የውኃ ቋት የተገኘ አልነበረም፤
በአለቱ ውስጥ አንድም ጠብታ ውኃ የለም፤
ነገር ግን ልክ የእግዚአብሔር ቃል ፍጥረትን ከምንም እንዳስገኛቸው፤
አንዲሁ ታላቅ የውኃ ጅረት ከደረቅ ድንጋይ ውስጥ ፈለቀ፡፡

2.ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ተፈጥሮ ገልጦ ጽፎልናል፤

ስለዚህም ተፈጥሮና መጽሐፍ ቅዱስ ስለፈጣሪ ምስክሮች ሆኑ፤
የሰው ልጅ ተፈጥሮን ለራሱ ጥቅም ሲገለገልባት እንደሚያውቃት፤
እንዲሁ መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ በውስጡ የያዘውን መረዳት ይቻለናል፤
እነዚህን ሁለቱን ምስክሮች በሁሉ ስፍራ እናገኛቸዋለን፡፡
እግዚአብሔር የለም የሚሉትን ኢአማንያንን ለማሳፈር፣
እነዚህ ሁለቱ በሁሉም ጊዜና ሰዓት የሚገኙ የእግዚአብሔርን መኖር አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው፡፡

3.ጌታ ሆይ የመጽሐፍህን መግቢያ ባነበብኩ ጊዜ ልቤ በሃሴት ተሞላ፤

የምንባቡ ቁጥሮችና ኃይለ ቃላት እኔን ለመቀበል እጆቻቸውን ዘረጉ፤
ይዘውኝም በፍቅር አቀፉኝ ሳሙኝም ወደ ወዳጃቸውን መርተው አደረሱኝ፡፡
የገነት ታሪኩዋ እኔን ወደ ላይ ወደ ሰማይ እንድነጠቅና ወደ ውስጥ እንድገባ አሸጋገረኝ፤
ከመጽሐፉ እቅፍ ወደ ገነት እቅፍ ተሸጋገርኩ፡፡

4.ዐይኔና ልቤ ቃሎቹ በሰፈሩበት መስመር ላይ ተጓዙ፤

በድልድይ እንደሚሸጋገር ሰው በገነት ታሪክ ወደ ላይ ተነጠቅሁ፡፡
ዐይኖቼ  ምንባቡን  ሲያነቡ አእምሮዬ ያርፍ ነበር፤  
አእምሮዬ በምሥጢር ሲነጠቅ ዐይኔ ደግሞ በተራው ከማንበብ ያርፋል፤
ከንባብ በኋላ ዐይኖቼ ሲያርፉ አእምሮዬ ምሥጢራትን በመመርመር ተጠመደ፡፡

5.ወደ ገነት መሸጋገሪያ ድልድዩንና መግቢያ በሩን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አገኘሁት፤

ስለዚህም በድልድዩ ተሸጋግሬ በበሩ በኩል ወደ ውስጥ ዘልቄ ገባሁ፤  
በእርግጥ ዐይኖቼ በውጭ ነበሩ አእምሮዬ ግን ወደ ውስጥ ዘልቆ ገብቶአል፤
በቃላት ሊገለጡ በማይችሉት መካከል ቆሜ መደነቅ ሞላብኝ፤
ስፍራው ታላቅ፣ ፀጥታ የሰፈነበት፣ ፍጹም ንጹሕና በክብር ከፍ ከፍ ያለ ግሩም ነበር፡፡
በረከቶች ሁሉ የሚገኝበትን ይህን ስፍራ መጽሐፍ ቅዱስ ኤደን ብሎ ሰየመው፡፡

 

6.    በዚያም ለቅዱሳን የሆነ አጸድና የተንጣለለ ለምለም መስክ አየሁ፤

በላዩም መዓዛው እጅግ ማራኪ የሆነ ሽቱ ተርከፍክፎበታል፤
አጸዱም በፍራፍሬዎች የተጌጠ፣ የፈኩ አበቦቹም አክሊሎች የሆኑለት ነው፤
መስኩ ርስት ሆኖ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን የሚሰጥ ሲሆን፤  
በጽድቅ ሕይወት ላልተጋው ውበቱ ማራኪ ያልሆነ ያልተጌጠ መስክ ይሰጠዋል፤  
ለተጋው ግን ውበቱ ዐይንን አፍዝዞ የሚያስቀር እጅግ ማራኪ የሆነ መስክ ያገኛል፡፡

7.    በአጸድ ውስጥም ሳለሁ ገነት ለቅዱሳን ማረፊያነት ትበቃቸዋለችን? ብዬ ጠየቅሁ፤

መሠረቴን መጽሐፍ ቅዱስ አድርጌ በመጽሐፍ ውስጥ ያልሰፈሩትን ለመመርመር ሞከርኹ፡፡
ሌጌዎን የተባለው የአጋንንት ሠራዊት በአንድ ሰው ሰውነት ውስጥ ሰፍሮ እንደነበር አስተዋልሁ፤(ማር.5፡9-10)
በቁጥራቸው እጅግ የበዙ ቢሆንም ከርቀታቸው(ከጥቃቅንነታቸው) የተነሣ እንደ አንዲት ነፍስ እንኳ ጎልተው መታየት አልተቻላቸውም፡፡

8.     በአንድ አካል ውስጥ የአጋንንት ሠራዊት ከትሞ እንዳለ ነገር ግን እጅግ ረቂቃን እንደሆኑ፤

እንዲሁ በትንሣኤ የተነሡ ቅዱሳን በገነት ውስጥ መቶ ሺኽ እጥፍ ረቀው ይኖሩባታል፡፡   
ገነት በአእምሮ ፣ ቅዱሳንም በአእምሮ የማሰብ አቅም ይመሰላሉ ፤
አንድ ሰው እንደ ፈቃዱ በአሳቡ እጅግ ሊራቀቅና ሊመጥቅ ይችላል፤
ቢፈልግ አመለካከለቱን በአንድ ነገር ላይ ብቻ ሊወስነው ይችላል፡፡
አንድ ሰው አመለካከቱን በቦታ ሊወሰን ወይም በቦታ ላይወስነው ይችላል፤

9.     መብራት ሲበራ እጅግ የብዙ ብዙ ሺኽ ጨረሮች በአንድ ቤት እንዲኖሩ ፤


ከብዛታቸው የተነሣ ቤቱ እንደማይጠባቸው፣  ከአንድ ከፈካ አበባ የሚወጣው መዓዛ አካባቢውን እንዲያውደው ነገር ግን በቦታ እንዲወሰን እንዲሁ በገነትም የሚኖሩ፤ ቅዱሳንም እንደ ብርሃኑ ጨረሮችና እንደ አበባው መዓዛ ናቸው ፡፡

ምንም እንኳ የብርሃኑ ጨረሮችና የአበባው መዓዛ በጠባብ ቦታ ላይ የተወሰኑ ቢሆንም፣
የስፍራው ውሱንነት ግን እንደልባቸው እንዲዋኙ እንዳይከለክላቸው ፤ ገነትም እንዲሁ ለቅዱሳን ናት ፡፡
ስለዚህም ገነት በውስጡዋ በመንፈሳዊ ፍጥረታት የተሞላች ብትሆንም፤
ወደ እርሱ የፈለሱትን ለማኖር ከበቂ በላይ የሆነ ሥፍራ አላት፡፡

10.     በቁጥር እጅግ የበዙ አሳቦች በመጠን ካነሱት የሰውነት ክፍሎቻችን አንዷ በሆነችው በልባችን ውስጥ ይኖራሉ ፤

የአካሉዋ ማነስ አንዱ በአንዱ እንዲወሰን ወይም አሳቦቻችንን እንደልባቸው እንዳንሸራሽር አይከለክለንም፤
ይህ እንዲህ ከሆነ እንዴት ገነት በመጠናቸው እጅግ ረቂቃን ለሆኑት ቅዱሳን ሰውነት የበቃች አትሆን !!
የቅዱሳንን ነፍሳት ርቀትን(ረቂቅነትን)ፈጽሞ በአእምሮአችን ተመራምረን የምንደርስበት አይደለም ፡፡

11.    በገነት መካከል ሆኜ እንደ ችሎታዬ መጠን ምስጋናዬን ለአምላኬ ላቀርብ ሞከርኩ፤

ድንገትም በገነት ውስጥ እንደ ነጎድጓድ የመሰለ ጥሙም የምስጋና ድምፅ ተሠማ ፤
ድምፁም ልክ በአንድ የጦር ሰፈር እንደሚነፋ መለከት ድምፅ ዓይነት ነበር፤
ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሚል የምስጋና ዝማሬ ሦስት ጊዜ ተደጋግሞ ተሰማ፤
ይህን ስሰማ አምላክ ከቅዱሳኑ ምስጋናን ለእርሱ እየቀረበለት መሆኑን ተረዳሁ ፡፡
እስከዛ ጊዜ ድረስ ግን ገነት ባዶ መስላኝ ነበር፤
ነገር ግን እንደ ነጎድጓድ የሆነውን ይህን ድምፅ ስሰማ ቅዱሳን በዚያ ከትመው እንዳሉ ተማርኹ፡፡

12.    ስለዚህም ገነት በጸጥታዋና በውበቱዋ እጅግ ማረከችኝ ደስም አሰኘችኝ፤

በውስጡዋ ያለው  አጸድ ውበት አንዳች እንከን የለበትም፤  
በውስጡዋ ከሰፈነው ጸጥታ የተነሣ አንዳች ፍርሃት የለም፡፡
ገነትን ለመውረስ የተገባው ቅዱስ እንዴት ብፁዕ ሰው ነው፤
ይህችን ስፍራ እንደ ቅድስናችን መጠን ሳይሆን እንደ እርሱ ጸጋ፤
እንደ እኛ ድካም ሳይሆን እንደ እርሱ ቸርነት የምንወርሳት ናት፡፡

13.     የገነትን ድንበሮችን አልፌ ወደ ውስጡዋ ስገባ በውበቱዋ እጅግ ተደመምኩ፤

በዙሪያው ያሉትን ወዳጆቼን ወደኋላ ትቼ በደኅንነት ወደሚኖሩባት ገነት ዘለቅሁ፤
ነገር ግን ከእርሱዋ ተመልሼ የሾኽና የአሜካላ እናት ወደሆነችው ምድር ስመለስ፤
ልዩ ልየ ዓይነት ሕማማትንና  ስቃዮችን ተቀበልኩ፤
ስለዚህም ገነትን ከምድር ጋር ሳነጻጽራት ልክ እንደወ¬ህኒ ቤት ሆና አገኘኋት፤
ነገር ግን በውስጡዋ ያሉ እስረኞች እርሱዋን ትተው ሲለዩዋት ያነባሉ፡፡ (ይህ ደግሞ የሚደንቅ ነው)

14.    ሕፃናት ከእናታቸው ማኅፀን ሲወጡ ማልቀሳቸው ይገርመኝ ነበር ፤

እኚህ ሕፃናት የሚያነቡት ከጨለማ ወደ ብርሃን በመውጣታቸው ነበር ፤
ከተጨናነቀው ሥፍራ ወደ ሰፊይቱ ዓለም በመምጣቸው ነበር የሚያለቅሱት፡፡
ልክ ከእናታችን ማኅፀን ስንወጣ እንደሚሆነው በሞት ከዚህ ዓለም ስንለይም እንዲሁ እናነባለን፤
ነገር ግን ሰዎች የሚያነቡት የስቃይ እናት ከሆነችው ከዚህች ዓለም ተወልደው እጅግ ግሩም ወደ ሆነችው ገነት ሲገቡ መሆኑ ይደንቃል፡፡

15.    የገነት ጌታዋ የሆንኽ ቸሩ ፈጣሪዬ ሆይ ለእኔ ራራኝ፤

ወደ ገነት ለመግባት ምናልባት እንኳ የበቃሁ ባልሆን፤
ከአንተ ጋር ያሉ ቅዱሳን ከገነት ፍሬዎች ተመግበው ሲጠግቡ፤   
በአንተ ቸርነት ከፍርፋሬአቸው ተመግበን ሕያዋን እንድንሆን፤
በገነት  ባለው አጸድ ዙሪያ እንድንሰፍር ፍቀድልን፡፡

ይቀጥላል ….

«ወአድኀነ ሕዝቦ በመስቀሉ»

ክፍል ሁለት

 

3. ክብረ መስቀል

እኛ ኦርቶዶክሳውያን የመስቀልን መንፈሳዊ ትርጉም ከመረዳትና በልባችን ከመያዝ በተጨማሪ ለመስቀል ያለንን ክብር እና ፍቅር ለመግለፅ የምናደርጋቸው በርካታ ነገሮች አሉ፤ ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹን እንጠቁማለን፡-

3.1 መስቀልን በቤተ ክርስቲያን፣ በንዋያተ ቅዱሳት፣ በሰውነት ላይ ማድረግ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ የመስቀልን በዓል አስመልክተው ባስተማሩት ትምህርት ላይ እንዲህ ይላሉ፤

«መስቀል ባሉት መንፈሳዊና ትምህርተ ሃይማኖታዊ ትርጉሞች ምክንያት ክርስቲያኖች ሁሉ የሙጥኝ ብለን እንይዘዋለን፡፡ በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እናደርገዋለን፤ በተለያየ መስክ እንቀርፀዋለን፤ በደረታችን ላይ እናንጠለጥለዋለን፣ በምልክቱ እናማትባለን፤ ፀሎታችንን እንጀምርበታለን፤ ካህናትም በእጃቸው ይይዙታል፣ ሰዎችንም ይባርኩበታል፣ የሐዲስ ኪዳን በረከቶች ሁሉ ምንጭ መስቀል እንዲሆን በማመን መስቀል በሁሉም ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያን አፈጻጸም ላይ እንጠቀምበታለን፤ በካህናቱ ልብሶች ላይ እናደርገዋለን ይኸውም ለጌጥ ሳይሆን ስለ ኃይሉ እና ስለ ቡራኬው ነው፡፡»

3.2. መስቀልን በመሳለም መባረክ

በጥንት ጊዜ መስቀል የመርገም ምልክት ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታችን በመስቀል ላይ መርገማችንን ሁሉ ተሸክሞ ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅንና የአዲስ ሕይወትን በረከት ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም የሐዲስ ኪዳን ታላላቅ ነገሮች ሁሉ የተገኙት ከመስቀል ነው፡፡

ስለዚህ ካህናት ቡራኬን ለመስጠት መስቀልን ይጠቀማሉ፤ ይህም በረከቱ የሚመጣው /የሚመነጨው/ ከራሳቸው ሳይሆን በረከትን እንዲሰጡበት የሰጣቸው ጌታችን ከተሰቀለበት መስቀል መሆኑን እና በሐዲስ ኪዳን ያሉ በረከቶች ሁሉ ምንጭ መስቀል መሆኑን ላይ ለማመልከት ነው፡፡

እግዚአብሔር የማይታዩ ፀጋዎችን ለሰዎች የሚሰጠው በሚታዩ አገልግሎቶች ነው፡፡ ይኸውም ነገሮችን ለሰው ልጅ ህሊና በሚረዳ መልኩ ለማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ከተወለደ ጀምሮ ዓይን ያልነበረውን ዓይን የፈጠረለት በሚታይ መልኩ በምድር አፈርና በምራቁ ጭቃ ሰርቶ ነው፡፡ ጥምቀትንም በውሃ ውስጥ በመነከር አድርጎታል፡፡ በዚሁ መሰረት በመስቀልን በመባረክ የማይታዩ በረከቶች እና ፀጋዎችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ በረከቶችም ደስታ፣ የመስቀሉ ፍቅር፣ ጥብአት /ድፍረት/ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

3.3. ማማተብ

አተበ ማለተ አመለከተ ማለት ነው፡፡ ማማተብ ማለት ደግሞ ማመልከት ማለት ነው፡፡ ማማተብ ማለት ከአውራ ጣት ቀጥሎ ባለው ጣትና በቀሪዎቹ ሦስት ጣቶች የመስቀል ምልክት ሰርቶ እጅን ከግንባር ጀምሮ ከላይ ወደ ታች ከዚያም ከግራ ወደ ቀኝ «በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ» እያሉ ስመ ሥላሴን እየጠሩ ሰውነትን ማመልከት ማለት ነው፡፡

እጃችንን ከላይ ወደታች ማውረዳችን እግዚአብሔር ወልድ ከሰማየ ሰማያት ወረዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ሰው መሆኑን እንዲያሳስበን ነው፡፡

ከግራ ወደ ቀኝ ማድረጋችን በመከራውና በሞቱ ከግራ /ከሞት/ ወደ ቀኝ / ወደ ሕይወት / እንዳሸጋገረን እንዲያሳስበን ነው፡፡ የመስቀል ቅርጹ ደግሞ መከራ መስቀሉን ያሳስበናል፡፡

ስናማትብ ራሳችንን እንባርካን፣ አጋንንት እኩያት መናፍስት ይርቁልናል፣ መከራ መስቀሉንም እናስባለን፤ መስቀሉን እንሸከማለን፡፡ ስለዚህ ጠዋት ስንነሳ፣ በፀሎታችን ወቅት፣ ክፉ ሀሳብ ሲመጣብን፣ የማያስፈራ ነገር ሲገጥመን፣ ደስ ሲለን፣…. እናማትባን፡፡

3.4. ለመስቀል መስገድና መገዛት

እኛ ኦርቶዶክሳውያን በመስቀል ፊት እንሰግዳለን፡፡ በመስቀል ፊት የምንሰግደው ስግደት ከሁለቱ የመስቀል ትርጉሞች አንጻር ሁለት ዓይነት መልኮች አሉት

ሀ. መስቀል የክርስቶስ መከራ ስቅለት እና ሞት የሚወክል አርማ እንደመሆኑ መጠን በመስቀለ ፊት ስንሰግድ ጌታችንን እያሰብን ለአምላክ ብቻ የሚገባውን የአምልኮ ስግደት ለአምላካችን እንሰግዳለን፤ ይህም ልክ በጌታችን ስዕለ አድኅኖ ፊት እንደመስገድ ያለ ነው፡፡

ለ. መስቀል የተከበረ ንዋይ ስለሆነ ለመስቀሉ ያለንን ፍቅር እና አክብሮት ለመግለጽ የፀጋ የአክብሮት ስግደት እንሰግድለታን፡፡ እንገዛለታን /እናከብረዋለን/ ቅዱስ ያሬድ ይህንን ሁለተኛውን ስግደት አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡፡ «ሀለው እለ ይቤሉ ለዕፅኑ ታመልኩ፣ ለለዕፅኑ ትገብሩ በዓለ፣ አቀደሶኑ በደሙ ክቡር ለዕፀ መስቀሉ፣ ወእንተዝ ንሕነ ናመልኮ» «የምታመልኩት ዕፅን/ የምትገዙት ለዕፅ/ ነውን? በዓልስ የምታደርጉት ለዕንጨት ነውን? የሚሉ አሉ፡፡ በክቡር ደሙ መስቀሉን ቀድሶት የለምን? ስለዚህ እኛ እናመልከዋለን /እንገዛለታለን/»

መለከ ማለት ገዛ ማለት ነው፡፡ ናመልከ ማለት እንገዛለታለን፤ እናከብረዋለን፣ ከፊቱ ራሳችንን ዝቅ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ ክቡር መስቀል ክርስቶስ ማዳኑን የፈፀበት፣ በደሙ ያከበረው ንዋይ ቅዱስ ስለሆነ የፀጋ ስግደት እንሰግድለታለን፡፡ እንገዛለታለንም፡፡

ከዚህም በተጨሪ በመስቀል ስም ታቦታትን በመቅረጽና አብያተ ክርስቲያናትን በማነጽ፣ የመስቀልን በዓላት በማክበር፣ ስመ ክርስትናን ወልደ መስቀል፣ ወለተ መስቀል፣ ገብረ መስቀል እያልን በመሰየም ለመስቀሉ ያለንን ክብር እና ፍቅር እንገልጣለን፡፡

እነዚህን ነገሮች ከማድረግም በተጨማሪ መስቀልን እንዲህ እያልን በቅዱስ ያሬድ ድርሰቶች እናመሰግነዋለን፡-

– «መስቀል ኃይልነ ወፀወንነ መድኃኒተ ነፍስነ ፍጽምን ወከዋላን ምጽንአተ ቅጽርነ መስቀል ቤዛነ ኃይልነ ወፀወንነ ዮም ፍስሓ ለነ» «መስቀል ኃይላችን፣ መመኪያችን፣ የነፍሳችን መድኃኒት ነው፡፡ የአጥራችን መጽኛ፣ ቤዛችን ነው፡፡ ዛሬ ለእኛ ደስታ ሆነ»

– «ወሀለወት አሐቲ ሀገር ብርሐት ከመ ፀሐይ ሕንፄነ ወሱራሬሃ አዳም የዓውደ ሐጹር በትእምርተ መስቀል» «አንዲት እንደ ፀሐይ የምታበራና ህንጻዋና አስራሯ ያማረ ሀገር አለች /ቤተ ክርስቲያንን ነው/፡፡ በመስቀል ምልክት የሆነ አጥር ይከባታል»

– «መስቀልከ ተስፋ ቅቡጻን መስቀልከ ልብስ ለዕሩቃን አንቅዕት ለፅሙዓን መርሶ መድኃኒቶሙ ለአሕዛብ» «መስቀልህ ተስፋ ለቆረጡ ተስፋ፣ ለተራቆቱ ልብስ፣ ለተጠሙ ምንጭ፣ ለአህዛብ ደግሞ የመድኃኒታቸው ወደብ /መጠጊያ/ ነው»

– «መስቀል ዘኀኑ ለባሕር፣ መርሶሙ ለአሕማር መስቀል ብርሃን ወሃቤ ሰላም ብርሃነ ዓለም» «መስቀል የባሕር ፀጥታ፣ የመርከቦች ወደብ፣ የዓለም ብርሃን እና ሰላምን ሰጪ ነው፡፡»  

4. የመስቀሉ ኃይል

ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶሳውያን በላከው የመጀመሪያ መልዕክቱ እንዲህ ይላል፡- «የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት ነው፤ ለእኛ ለምንድነው ግን የእግዚአብሔር ኀይል ነው፡፡» /1ኛ ቆሮ.1-18/

መስቀል ከሁለቱ ትርጉሞቹ /መልዕክቶቹ/ አንጻር ኃይልነቱም በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል፤

ሀ/ መስቀል ኀጢአታችንንና በኀጢአታችን ምክንያት የደረሰብንን ሞት፣ የጌታችንን ሕማማት፣ መስቀል እና ሞት፣ ትንሳኤውንና ዳግም ምፅአቱንና እኛም ከሞት ተነስተን ለፍርድ የምንቆም መሆናችንንና ሌሎች ተያያዥ ነገሮችን የሚወክልና የሚያስታውሰን ምልክት ነው፡፡

እነዚህን ነገሮች ማሰባችንና ማስታወሳችን ሁል ጊዜ በመንፈሳዊ ሃሳብ ውስጥ እንድንሆንና ዓለምንና የዓለም የሆነውን በሚያስንቅ የክርስቶስ ፍቅር፣ እንድንሞላ ስለሚያደርገን መስቀል ኃይላችን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስለ ሚደርስብን ፈተና እና ስለ እግዚአብሔር ብለን ስለምንተወው ነገር ሁሉ የምንቀበለውን አክሊልም እያስታወሰ ብርታት ስለሚሆነን መስቀል ኀይላችን ነው፡፡

ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ይህንን ሁለተኛውን የመስቀል ኀይልነት ሰያብራሩ እንዲህ ይላሉ፣ «የመስቀል ምልክት ሰይጣናት ሁሉ የሚፈሩት ኀይል እንደሆነ እናያለን፤ ሰይጣን የሰው ልጆችን ለማጥፋት ያደረገው ጥረትና የደከመው ድካም የከሸፈው በመስቀል ላይ በተደረገው ነጻ ማውጣት ነው፡፡ ስለዚህ ሰይጣን የመስቀልን ምልክት ይፈራል፤ ስለዚህ በእምነት ከተደረገ በመስቀልና በመስቀል ምልክት እጋንንትን ማራቅ፣ ማውጣትና ማሳደድ ይቻላል፡፡ እኛም የእግዚአብሔር ልጆች የድል ምልክት አድርገን እንይዘዋለን፤ አጋንንትን ድል ለማድረግ እንጠቀምበታለን፡፡

ስለዚህ በዘወትር ጸሎታችን «መስቀል ኃይላችን ነው» እንላለን፤ ስለ መስቀሉና ስለ አምላካችን ውለታና ስለ ዘለዓለማዊ ህይወታችን በማሰብ ክፉ ሃሳብና ፍትወታትን ድል እናደርግበታለን፤ በመስቀል ምልክት በማማተብና በዕፀ መስቀል በመባረክ /ባ ይጠብቀል/ እና በመባረክ /ለካህናት/ አጋንንትን እናርቃለን፤ ከሰዎችም እናስወጣለን፡፡

5. ጌታችን የተሰቀለበት ዕፅ መስቀል መገኘት

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ተአምራትን ማድረግ ሙታንን ማስነሣት፣ በሽተኞችን መፈወስ፣ አጋንንትን ማውጣት ስለጀመረ በቅንአታቸውና ባለማወቃቸው ጌታን የሰቀሉት አይሁድ መስቀሉ በኢየሩሳሌም አካባቢ ባለው የቀራንዮ ተራራ ላይ ቀብረው ቦታውን የቆሻሻ መጣያ አደረጉት፡፡ ሁሉም የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ቆሻሻቸውን በዚያ መጣል ጀመሩ፡፡ በጊዜ ብዛትም የቆሻሻው ክምር አድጎ ትልቅ ኮረብታ አከለ፡፡

ክርስቲያኖች መስቀሉ ያለበትን ቦታ ቢያውቁም ሊያወጡት ግን አልቻሉም ነበር፡፡ ነገር ግን በ70 ዓ.ም የሮማው የጦር ጀነራል /በኋላ ንጉሠ ነገሥት/ ቬስፓስያንና ልጁ ጥጦስ ኢየሩሳሌምን ሊያጠፋ ጥቂት ጊዜ ሲቀራቸው ክርስቲያኖች ከተማውን ለቀው ስለወጡና የነበሩት አይሁድ ስለተገደሉ፣ የቀሩትም ስለሸሹና ከተማዋ ባዶ ስለሆነችና ከዚያ በኋላ የነበረውም ዘመን ለክርስቲያኖች የሰማእትነት፣ የስደትና የመከራ ዘመን ስለነበር መስቀሉን ማውጣት አልተቻለም ነበር፡፡ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ሳይቀር ተረሳ /ጠፋ/፡፡

ከ300 ዓመታት ያህል በኋላ እግዚአብሔር ንጉሥ ቆስጠንጢኖስን አስነሣ፡፡ ቆስጠንጢኖስ መክስምያኖስ ከሚባል ጠላቱ ጋር አስጨናቂ የሆነ ጦርነት ላይ በነበረበት ወቅት በሰማይ ላይ ብርሃናዊ የመስቀል ምልክት ታየው፤ «ከዚያም በዚህ ምልክት ጠላትህን ታሸንፋለህ፡፡» የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰማ፡፡ /ይህ የሆነው ቆስጠንጢኖስ ለብቻው ሁኖ በተመስጦ እያሰበ ሳለ ነው፡፡/ ወዲያውም የክርስትናን እምነት ተቀበለ፡፡ /የተጠመቀው ግን ሊሞት ጥቂት ሲቀረው ነው፡፡ መስቀልን የመንግሥቱና የሠራዊቱ አርማ አደረገ፡፡ በሠራዊቱ ልብሶች፣ የጦር ዕቃዎች፣ ፈረሶች ሁሉ ላይ የመስቀልን ምልክት አድርጎ ጠላቱን በመዋጋት ድል አደረገ፤ ለክርስቲያኖች ነጻነትን ሰጠ የዘመነ ሰማዕታት ፍጻሜ ሆነ፤ ክርስቲያናዊ መንግሥት መሠረተ፡፡

የቆስጠንጢኖስ እናት ቅድስት እሌኒ ትባላለች፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ስለ ቅድስት እሌኒ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል፡- «ልጇ ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ንግሥት በማድረግ አከበራት፤ በቤተ መንግሥቱ ንዋይም ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጣት፤ እርሷም ይህንን ገንዘብ በደግነት በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ሠራችበት፤ ድሆችንና የተቸገሩትንም ረዳችበት፡፡ ከቦታ ቦታ ስትዘዋወርም ሰዎችን ትረዳና ከባርነት ነጻ ታወጣ ነበር፡፡

«በጣም ሃይማኖተኛም ነበረች፡፡ ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትሔደው ንግሥት ብትሆንም እንኳን ቀላል እና ተራ ልብሶችን ለብሳ ነበር፡፡ ጸሎቷን ያለ ማስታጐል /ያለማቋረጥ/ ትጸልይ ነበር፡፡ ከመንፈሳዊ መርሐ ግብሮችንም አትቀርም ነበር፡፡ እንደ ንግሥት ከኖረችው በላይ እንደ አማኝ ኖራለች፡፡ ቅዱሳት መካናትን ትጎበኝና በእርጅናዋ ወራት የረጅም ጉዞን ድካም ትቀበል ነበር፡፡ ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ወደ ኢየሩሳሌም ሔዳ መስቀሉን እንድታወጣ በራእይ ነገራት፡፡ እሌኒም የታዘዘችውን ለመፈጸም ወደ ኢየሩሳሌም ብትሔድም መስቀሉን ግን ማግኘት አልቻለችም፡፡ በኢየሩሳሌም የሆነውን ነገር ቅዱስ ያሬድ በድጓው ጽፎታል፤

«ሖረት ዕሌኒ በሰላም ከመ ትኀስስ ዕፅ መስቀል ወረከበት መሐይምናነ እምዘመደ ዕብራውያን ወትቤሎሙ በአይቴ ሰቀሉ ወልደ ዋህደ ወይቤልዋ በቀራንዮ በበህየ ሰቀልዎ፤ ዕሌኒ መስቀሉን ትፈልግ ዘንድ በሰላም ሔደች፤ ከዕብራውያን ወገኖች መካከል ምዕመናንን አገኘችና ጌታን የሰቀሉት የት ነው ብላ ጠየቀቻቸው፤ እነርሱም በቀራንዮ ነው የሰቀሉት አሏት፡፡» ከጠየቀቻቸው ሰዎች መካከልም ኪራኮስ አሚኖስ የሚባሉ ሰዎች እንዳሉበት ቅዱስ ያሬድ እንዲህ እያለ ይነግረናል፡፡

«ትቤሎ ዕሌኒ ለኪራኮስ ምዕመን ንግረኒ አፍጥን ኀበ ሀሎ መስቀሎ ለኢየሱስ ክርስቶስ፤ ዕሌኒ ኪራኮስን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የት እንዳለ ቶሎ ብለህ ንገረኝ አለችው፡፡»

ትቤሎሙ ዕሌኒ ለኪራኮስ ወለ አሚኖሰ ንግሩኒ ኀበ ሰቀሉ ወልደ ዋህደ፤ ዕሌኒ ኪራከስንና አሚኖስን አይሁድ ጌታን የት እንደሰቀሉት ንገሩኝ አለቻቸው፡፡»

ኪራኮስም እንዲህ አላት፡- እኔ ዘመኑ ሩቅ ስለሆነ አላውቀውም፤ አባቴ ግን የቦታው ስም ቀራንዮ መሆኑን ነግሮኛል፡፡»

ይሁን እንጂ በቀራንዮ ተራራ ላይ ቁፋሮ ቢጀመርም መስቀሉ ሊገኝ አልቻለም፡፡ በኋላ አባ መቃርስ የተባለው የኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ አይሁድ መስቀሉን አስቀብረው ቦታውን የቆሻሻ መጣያ እንዳደረጉትና ቦታውም በተራራው ላይ ባሉት ኮረብታ መሰል ክምሮች አንዱ እንደሆነ ነገራት፡፡ ይሁን እንጂ በቀራንዮ ተራራ ላይ በርካታ ትናንሽ ኮረብታዎች ክምሮችን በመኖራቸው መስቀሉ ያለበት ሊታወቅ አልቻለም፡፡

ከዚህ በኋላ «ወትቤ ዕሌኒ አንሰ ኢይለብስ አልበሰ መንግሥትየ ለእመ ኢተረክበ ዕፅ መስቀል ወፀርሐት ኀበ እግዚአብሔር በዐቢይ ቃል፤ ዕሌኒም ዕፅ መስቀሉ ካልተገኘ የመንግሥቴን ልብስ አልለብስም አለች፤ በታላቅ ቃልም ወደ እግዚአብሔር ጮኸች» እንዳለው ዕሌኒ ሱባኤ ገብታ ጸሎት ማድረግ ጀመረች፡፡ በሱባኤዋም ወቅት መልአክ ተገልጦ ደመራ አስደምራ ዕጣን ብትጨምርበት ጢሱ መስቀሉ ያለበትን እንደሚያመለክታት ነገራት፡፡

በዚህም መሠረት መስከረም 16 ቀን ታላቅ ደመራ አስደምራ እሳት አስለኩሳ በጣም ብዙ ዕጣን ጨመረችበት የዕጣኑ ጢስም ወደ ሰማይ ወጥቶ ተመልሶ መስቀሉ ወዳለበት ኮረብታ ተመለሰና መስቀሉ ያለበትን አመለከተ፡፡ ቅዱስ ያሬድ ይህንን አስደናቂ ክስተት «ዘዕጣን አንዳረ ሰገደ ጢስ»፣ «ዕጣኑ መስቀሉ ያለበትን አመለከተ፣ ጡሱም ለመስቀል ሰገደ» በማለት ገልጾታል፡፡

ወዲያውም ቁፋሮ ተጀመረ፡፡ ከስድስት ወራት በኋላም በመጋቢት 1ዐ ቀን ስንክሳር እንደተገለጠው ሦስት መስቀሎች /የጌታችንና አብረውት የተሰቀሉት ሁለት ወንበዴዎች/ ተገኙ፡፡ የጌታችን መስቀል ሙት በማስነሣቱና ድውያንን በመፈወሱ ተለይቶ ታውቋል፡፡ ከመስቀሉ ጋርም አክሊለ ሶኩና ጌታችን የተቸነከረባቸው ችንካሮች እንደተገኙ መጽሐፈ ስንክሳርና መጽሐፈ ድጓ ይናገራሉ፡፡

ዕሌኒም በጣም ተደሰተችና በቀራንዮ ተራራ ላይ በመስቀል ስም ቤተ ክርስቲያን አሠራች፡፡ ቤተ ክርስቲያኑም መስከረም 16 ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከብሮ መስከረም 17 ቀን ተቀደሰበት፡፡ የጌታችን መስቀልም በወርቅ ሳጥን ውስጥ በዚያው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀመጠ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በዚህ ምክንያት የመስቀሉን በዓል ቅዳሴ ቤቱ በተከበረበት መስከረም 16 ቀን ዳመራ ደምራ ታከብራለች፡፡ መጋቢት 1ዐ ቀንም መስቀሉ የተገኘበትን ዕለት ታስባለች፡፡

የመስቀሉ በረከት ይደርብን፤ አሜን፡፡