“ኅርየተ ፓትርያርክ በቤተ ክርስቲያን ዘግብጽ ኦርቶዶክሳዊት፤ የፓትርያርክ ምርጫ ታሪክና አፈጻጸም በኮፕት ቤተ ክርስቲያን”

ነሐሴ 23 ቀን 2004 ዓ.ም.

ወልደ ማርያም

የዚህ አጭር ጽሑፍ ዋና ዓላማ በትምህርተ ሃይማኖትና ከሞላ ጎደል በሥርዓተ እምነት ከሚመስሉን አኀት አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ የሆነችው የኮፕት ቤተ ክርስቲያን በ2000 ዘመን ታሪኳ የሚመሯትን ፓትርያርኮች እየመረጠች የሄደችበትን ቀኖና ታሪክና ሥልት ጠቅለል ባለ መልኩ ማቅረብ ነው፡፡ ከሌሎቹ አኀት አብያተ ክርስቲያናት የኮፕት ቤተ ክርስቲያንን የምርጫ ቀኖናና ሂደት ዳስሰን ለማቅረብ የፈለግንበት ምክንያት የቤተ ክርስቲያኗ መንበረ ፕትርክና ለ1600 ዘመናት የቤተ ክርስያናችንም መንበረ ፕትርክና ሆኖ የቆየ ከመሆኑ አንጻር በጽሑፉ የሚወሳው ታሪክ የሚቀርበን በመሆኑ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኗ መንበረ ፕትርክናዋ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ወንጌላዊው ማርቆስ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በድምሩ 117 ፓትርያርኮችን እየመረጠች አስቀምጣለች፡፡ ፓትርያርኮቹም የተቀበሉትን ሰማያዊ ሓላፊነት በመያዝ ቤተ ክርስቲያኗ ክፉውንና ደጉን ዘመን አልፋ ዛሬ ካለችበት ደረጃ እንድትደርስ አድርገዋታል፡፡ አሁን ባለችበት ሁኔታ ቤተ ክርስቲያኗ በግብጽና በመላው ዓለም ከ15 እስከ 18 ሚልዮን የሚደርሱ ምእመናን ያሏት ሲሆን እነዚህንም ምእመናን በእረኝነት የሚጠብቁ ከ150 በላይ ሊቃነ ጳጳሳት አሏት፡፡ እነዚህ ሊቃነ ጳጳሳት በመንበረ ፕትርክናው ማእከላዊ አስተዳደር በሚመሩ 54 ያኽል አኅጉረ ስብከት በሊቃነ ጳጳስነት ተመድበው ያገለግላሉ፡፡ ከእነዚህ አኅጉረ ስብከት 15 የሚሆኑት ከግብጽ ውጪ በተለያዩ ክፍላተ ዓለም ተቋቁመው በማገልገል ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡

 

ቤተ ክርስቲያኗ በአሁኑ ወቅት ከ41 ዓመታት የፕትርክና አገልግሎት በኋላ መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. /በዚህ ጽሑፍ የተሰጡት የቀናትና የዓመታት ቁጥር በሙሉ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነው/ ከዚህ ዓለም የተለዩትን 117ኛውን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ሲኖዳ 3ኛን ለመተካት በከፍተኛ ዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኗ እ.ኤ.አ. ከ1975 ዓ.ም. ጀምሮ ባላት ቀዋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ደንብ መሠረት ሦስት ዕጩዎች ተለይተው አንዱ በዕጣ የሚመረጥበት የመጨረሻ ሥነ ሥርዓት ለመስከረም ቀጠሮ ተይዟል፡፡ ለመሆኑ ይህ ቀዋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ደንብ ተረቆ በመጽደቅ ሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት ያገለገሉት ፓትርያርኮች እንዴት ተመረጡ? የአመራረጣቸው ሂደትና ቀኖናስ ምን ይመስል ነበር? እያንዳንዱ ሂደትና ቀኖና ተመሳሳይ ነበር ወይስ ልዩነት ነበረው? ይህ ጽሑፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል፡፡

 

በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ የፓትርያርኮች ምርጫ ምንም እንኳን በመሠረታዊ የተመራጮቹ መመዘኛዎች በአብዛኛው ልዩነት ባይኖርም፤ የምርጫ አፈጻጸም ቀኖናዎች ላይ የሚስተዋሉ ልዩነቶች ነበሩ፡፡ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጥናቶችንና የፓትርያርኮቹን የሕይወት ታሪክ በማጥናት በቤተ ክርስቲያኗ የ2000 ዘመናት ታሪክ ዘጠኝ ዓይነት የምርጫ ቀኖናዊ ሥልቆች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህን ሥልቶች ከነ አፈጻጸማቸውና ከተመረጡባቸው ፓትርያርኮች ዝርዝር ጋር እንደ ሚከተለው እንመለከታለን፡፡

 

1.    የካህናት ብቻ ምርጫ /Election by Presbyterians of Alexandria/

ይህ ቀኖና ፓትርያርክ የመምረጡን ሓላፊነትና መብት ለካህናት ብቻ የሰጠ ቀኖና ነው፡፡ በተለይ በቤተ ክርስቲያኗ የመጀመሪያዎቹ ዘመናት ያገለገለው ይህ የምርጫ ቀኖና መሠረት ያደረገው በወቅቱ ቤተ ክርስቲያኗ የነበራትን አስተዳደራዊ መዋቅር ነበር፡፡ በተለያዩ መዛግብት ተገልጾ እንደሚገኘው በመጀመሪያዎቹ የአገልግሎት ዘመናቷ ቤተ ክርስቲያኗ ስትመራ የነበረው አባላቱ 12 በሆነ የካህናት ጉባኤ /Presbyterian Council/ አማካይነት ነበር፡፡ በ12ቱ ሐዋርያት ምሳሌነት በቅድስናቸውና በአገልግሎት ልምዳቸው ከማኅበረ ካህናቱ ተመርጠው የሚሾሙት እነዚህ 12 ካህናት ከመካከላቸው የበለጠ የተሻለ ነው ያሉትን አንድ አባት መርጠው በአስራ አንዱ አንበሮተ እድ ሊቀ ጳጳስ አድርገው ይሾሙታል፡፡ ይህ ሊቀ ጳጳስ ጉባኤውን በበላይነት ይመራል፤ ካህናትን ይሾማል፤ አንድ ፓትርያርክ ያለውን ሓላፊነት ሁሉ ይፈጽማል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ምርጫ እስከ 12ኛው ፓትርያርክ ዲሜጥሮስ ቀዳማዊ /189-231 ዓ.ም./ ድረስ ቤተ ክርስቲያኗ አንድ ጳጳስ ብቻ ነበራት፡፡

 

በዚህ የምርጫ ሥልት የተመረጠው ሊቀ ጳጳስ በእርግናም ይሁን በጤና መታወክ የተነሣ ኅልፈተ ሕይወቱ በደረሰ ጊዜ ከአስራ አንዱ ውስጥ ብቃት አለው ያለውን መርጦ ያለፈበት አካሄድ ነበር፡፡ ምርጫውንም የሚያውጀው ካህናትና ምእመናን በተሰበሰቡት ጉባኤ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳን ይሁን ብሎ መርጦት ቢሄድ ተመራጩ በመንብረ ፕትርክናው የሚቀመጠው በካህናት ጉባኤው ታምኖበት ሲጸድቅና በአንብሮተ እዳቸው ሲሾም ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ስድስተኛው ፓትርያርክ በቴኦናስ /282-300 ዓ.ም./ እና ሰባተኛው የግብጽ ፓትርያርክ ጴጥሮስ ቀዳማዊ /300-311 ዓ.ም./ ተመርጠው አገልግለው አልፈዋል፡፡

 

ይህ ፓትርያርኮችን የመምረጡ ሥልጣንና ሓላፊነት ካህናት ብቻ የሆነበት ቀኖና እስከ 19ኛው ፓትርያርክ አባ እስክንድር /312-326 ዓ.ም./ ድረስ ሲያገለግል ቆይቶ መንበረ ፓትርያርኩ ከአሌክሳንድርያ ተነሥቶ ወደ ካይሮ ከመዛወሩ ጋር ተያይዞ ተግባራዊነቱ እየቀነሰ መጥቶ በሌላ ቀኖና ተተክቷል፡፡

 

2.    የምእመናን ብቻ ምርጫ / Election by Laity Acting Alone/

ይህ የምርጫ ሥልት በተለይ ቤተ ክርስቲያኗ በእስልምና ወረራ የተነሣ ካህናቷን አጥታ በነበረችበት ዘመን ይፈጸም የነበረ ሲሆን፤ የፓትርያርክ ምርጫ መብት የምእመናን ብቻ የነበረበት ሥልት ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ሥልት ከተመረጡት አምስት ፓትርያርኮች ምእመናንና ዲያቆናት የነበሩ ይገኙባቸዋል፡፡

 

3.    የኤጲስ ቆጶሳት ብቻ ምርጫ /Election by Bishops Acting Alone/

በአፈጻጸሙ ከሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተመሳሳይነት ያለው ይህ ሥልት በፓትርያርኮች ምርጫ ምእመናንና ካህናት ቦታ ሳይኖራቸው በኤጲስ ቆጶሳት ብቻ የሚከናወን ነበር፡፡

 

በዚህ ሥልት በድምሩ አራት ፓትርያርኮች ብቻ የተመረጡ ሲሆን እነሱም 19ኛው ፓትሪያርክ አባ እስክድር /312-326 ዓ.ም./፣ 35ኛው ፓትርያርክ አባ ዳምያን /569-605 ዓ.ም./፣ 52ኛው ፓትርያርክ አባ ዮሳብ /830-849 ዓ.ም./ እና 112ኛው ፓትርያርክ አባ ቄርሎስ 5ኛ /1874-1927 ዓ.ም./ ናቸው፡፡

 

4.    በጠቅላላ ስምምነት /Election by General Consensus/

ይህ የምርጫ ቀኖና አፈጻጸሙ ከሊቃነ ጳጳሳት፣ ከካህናት ተወካዮችና ከሌሎች መሪዎች የተውጣጡ መራጮች ካሉት ሊቃነ ጳጳሳት አንዱን በሙሉ ስምምነት መርጠው የሚሾሙበት ቀኖና ነበር፡፡ በዚህ ቀኖና ሠላሳ አምስት ፓትርያርኮች ተመርጠው አገልግለው አልፈዋል፡፡ የፓትሪያርኮችን ዝርዝር ከጽሑፉ መጨረሻ ከሚቀርበው ሠንጠረዥ ይመለከቷል፡፡

 

5.    በሓላፊው ፓትርያርክ ምርጫ /Election through the Appointment of the Predecessor/

በዚህ የምርጫ ቀኖና በዕድሜ መግፋትም ይሁን በጤና መታወክ የተነሣ ኅልፈተ ሕይወቱን በሚጠባበቅበት አልጋ ላይ /Death bed/ ሆኖ የሚጠብቀው ፓትርያርክ ካሉት ጻጳሳት ወይም መነኮሳት ውስጥ የበለጠ ይመጥናል ያለውን መርጦ የሚያስቀምጥበት ቀኖና ነው፡፡ ይህንን ቀኖናዊ የምርጫ ሥልት ቤተ ክርስቲያኗን ያጠኑ ሊቃውንት የፓትሪያርክ የመጨረሻ ምኞት /patriarchal Death bed wish/ ይሉታል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት ትረካ የዚህ ቀኖና መሠረቱ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያኗ መሥራችና ፓትርያርክ ቅዱስ ማርቆስ በእሱ መንበር ተቀምጦ ቤተ ክርስቲያኗን ይመራ ዘንድ ሁለተኛውን ፓትርያርክ አባ አንያኖስን /68-85 ዓ.ም./ መርጦ ያለፈበት ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ቀኖናዊ የምርጫ ሥልት በድምሩ ሰባት ፓትርያርኮች ተመርጠዋል፡፡ ይህ ሥልት በብቃት ሳይሆን ለፓትርያርኩ ካላቸው ቅርበት የተነሣ እንዲመረጡ ያደረጋቸው አንዳንድ አባቶች እንዳሉ በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ ይወሳል፡፡ በዚህ ረገድ በምሳሌነት የሚጠቀሰው ሠላሳ ስምንተኛው ፓትርያርክ አባ ቢንያም ቀዳማዊ /622-661 ዓ.ም./ ነው፡፡ ይህ ፓትርያርክ ሲመረጥ በቅድስናም ይሁን በአገልግሎት ልምድ ከእነሱ የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በዘመነ ፕትርክናው ያገለግለው የነበረው ሓላፊ ፓትርያርክ ስለመረጠው እንደተሾመ ተጽፏል፡፡

 

6.    መለኮታዊ ምርጫ ወይም ራእይ /Election by Divine Appointment or vision/

እንደ ቤተ ክርስቲያኗ ሊቃውንት አስተምህሮ ይህ ሥልት የተወሰደው የመጀመሪያው ፓትሪያርክ ቅዱስ ማርቆስ ወንጌላዊ በመለኮታዊ ጥበብ ከተሾመበት አካሄድ ነው፡፡ ይህ ሥልት በተለይ በሓላፊው ፓትርያርክ ወይም ለእሱ ለሚቀርቡና በፓትርያርክ ምርጫው ተሳትፊ በሆኑ አካላት በሚታይ ራእይ ተመሥርቶ ፓትርያርክ የሚመረጥበት ዘዴ ነበር፡፡ ለምሳሌ በእርግና አልጋው ላይ የነበረው 11ኛው ፓትርያርክ አባ ዩልየስ /189-231 ዓ.ም./ መልአኩ ተገልጦ “ነገ ወደ መንበረ ፕትርክናው መጥቶ ዕቅፍ ወይን የሚያበረክትልህ እሱ በመንበርህ ይተካል” እንዳለውና በወቅቱ በግብርና የገዳም ማኅበሩን ሲያገለግል የነበረው ዲሜጥሮስ ባልተለመደ ሁኔታ ማሳው ላይ የወይን ተክል በማግኘቱ “ይህስ ለቅዱስ ፓትርያርክ ይገባል” ብሎ ቆርጦ በዕቅፉ ወስዶ ስላበረከተለት መንበረ ፓትርያርኩን ተረክቦ ቤተ ክርስቲያኗን ለ42 ዓመታት /189-231 ዓ.ም./ እንዳገለገለ መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ በተመሳሳይም 46ኛውን ፓትርያርክ ለመምረጥ ኤጲስ ቆጶሳት ካህናትና ምእመናን ተሰብስበው ሦስት ዕጩዎችን ቢያቀርቡም በመራጮቹ መካከል ከፍተኛ ልዩነትና ጭቅጭቅ በተነሣ ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ የሆነው ሊቀ ዲያቆን፤ አባ ኽኢል የተባለው ሰው ለመንበሩ ብቃት እንዳለው ራእይ በማየቱ በእሱ ሕልም ተመርተው በሙሉ ስምምነት እንደሾሙት ተጽፏል፡፡

 

7.    ዕጣ የማውጣት ምርጫ /Election through Casting of Lots/

ይህ ቀኖና አስራ አንዱ ሐዋርያት በይሁዳ ምትክ ከእነሱ ጋር ይደመር ዘንድ ማትያስን የመረጡበትን አካሄድ በሞዴልነት በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ ዘመናት እንደታየው ይህ ዘዴ ተግባር ላይ ሲውል የነበረው በዕጩዎች መካከል እኩል ተቀባይነትና ቅድስና ኖሮ አንዱን ከሌላው ለመለየት አስቸጋሪ ሲሆን ወይም ዕጩዎች ያገኙት ድምጽ አንድ ዓይነት ሲሆንና /ምሳሌ ሰባ አንደኛው ፓትርያርክ አባ ሚካኤል /1145-1146 ዓ.ም/ እና በዕጩዎቹ ደጋፊዎች መካከል ከፍተኛ ሽኩቻና ጸብ ሲኖር /ምሳሌ 48ኛው ፓትርያርክ ዮሐንስ አራተኛ /775-799 ዓ.ም./ ነው፡፡ የዕጣ አወጣጥ ሥርዓቱም በሰንበት ቀን የዕጩዎቹ ስም በታሸገ ኢንቨሎፕ ከመንበሩ ላይ ይቀመጥና ጸሎተ ቅዳሴ እንዲሁም ቀኖና የሚያዝዘው ጸሎት ሁሉ ተደርጎ ሲያበቃ አንድ ሕጻን ከአስቀዳሾች መካከል ቀርቦ ዓይኑን በጨርቅ ከታሰረ በኋላ አንዱን ያወጣል፡፡ ስሙ የወጣውም ቀጣዩ የቤተ ክርስቲያኗ ፓትርያርክ ሆኖ ይሾማል፡፡ በዚህ ቀኖናዊ ሥልት በአጠቃላይ አሥር ያህል ፓትርያርኮች ተመርጠው አገልግለው አልፈዋል፡፡

 

ከዚህ በታች የምናያቸው ሁለት የምርጫ ሂደቶች በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ በቀኖናዊ ሥልትነት የተመዘገቡ ሳይሆኑ፤ ፓትርያርኮች ተመርጠው ያለፉባቸው አካሄዶች ናቸው፡፡

 

8.    የመንግሥት ጣልቃ ገብነት /Strong Intervention by Government/

የኮፕት ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ድረስ ዘልቀው ከሚያስቸግሯት ፈተናዎች አንዱ በሀገሪቱ መንግሥት ያለባት ጫና ነው፡፡ ይህ የገዥዎች ቀንበር በቤተ ክርስቲያኗ ጫንቃ ላይ የወደቀው ሀገሪቱ በአረብ እስላሞች እጅ ከወደቀችበት 640 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ሀገሪቱን የሚመራው ኢስላማዊ መንግሥት በቤተ ክርስቲያኗ ላይ ከሚያሳድረው ተጽዕኖ መገለጫዎች አንዱ በቤተ ክርስቲያኗ የፓትርያርክ ምርጫ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖና የወሳኝነት ሚና ነበር፡፡ እሱም ቢሆን ከመንግሥቱ ጣልቃ ገብነት ሳይወጣ፤ ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ አካሄድ ይሆነኛል ያለችውን ብትመርጥም ተመራጩ አባት ፓትርያርክ ሆኖ የሚሠየመው ስሙ ወደ ሀገሩ ገዥ ተልኮ ሲጸድቅ ብቻ ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት በቤተ ክርስቲያኗ ታሪክ ስድስት ያህል ፓትርያርኮች ተመርጠው አገልግለው አልፈዋል፡፡ በእርግጥ ቤተ ክርስቲያኗ በፓትርያርክ ምርጫ ከፍተኛ የመንግሥት ተጽዕኖ ነበረባት ቢባልም፤ በወቅቱ የነበሩት አባቶችና ምእመናን ተጽዕኖውን በመቋቋም የቤተ ክርስቲያናቸውን ክብር ለማስጠበቅ ሞክረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከሊቃነ ጳጳሳቱ፣ ማኅበረ ካህናቱና ምእመናኑ ፈቃድና ይሁንታ ውጭ በወቅቱ ለነበሩት ገዥዎች በነበረው ቀረቤታና አገልግሎት በመንግሥት ቀጥተኛ ምርጫና ትእዛዝ እንዲመረጥ የቀረበውን ሰባ አምስተኛውን ፓትርያርክ አባ ቄርሎስ 3ኛ /1235-1243 ዓ.ም./ እንዳይመረጥ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ በዚህ የተነሣም ምንም እንኳን የኋላ ኋላ መንግሥት አሸንፎ አባ ቄርሎስ ፓትርያርክ ሆኖ ቢመረጥም፤ ለ19 ዓመታት መንበሩ ባዶ ሆኖ ታግለዋል፡፡

 

9.    በአጋጣሚ /Election by Coincidence or Chance/

ይህ የምርጫ ሂደት መራጮቹም ይሁኑ ተመራጩ ባላሰበበት ሁኔታ በአጋጣሚ ያልታሰቡ መነኮሳት ተመርጠው ለከፍተኛው ሥልጣን የበቁበት ሂደት ነው፡፡ ለዚህ ሂደት በምሳሌነት በተደጋጋሚ ተጠቅሶ የሚገኘው የ64ኛው ፓትርያርክ አመራረጥ ሂደት ነው፡፡ 63ኛው ፓትሪያርክ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለየ ሲሰማ፤ አንድ ባዕለ ጸጋ በዘመኑ ለነበረው ኸሊፋ /የግብጽ ገዥ/ ብዙ ገንዘብ ከሰጠው በኋላ ባለፈው ፓትርያርክ መንበር እንዲሾመው ይጠይቀዋል፡፡ ኸሊፋውም የባዕለ ጸጋውን ገንዘብና ጥያቄ ተቀብሎ በካይሮ ያሉት አባቶች ትእዛዙን ይፈጽሙ ዘንድ ደብዳቤ አስይዞ ይልከዋል፡፡ በዚህ ተጨንቀው የተቀመጡ አባቶችም ነጋዴውን በመጠባበቅ ላይ ሳሉ አንድ በቅድስናውና በአገልግሎት ትጋቱ የታወቀ መነኩሴ የሸክላ ድስት ይዞ አባቶች ተሰባስበው ወደ ተቀመጡበት አዳራሽ ይገባና እየጮኸ ድስቱን ከደረጃ ላይ በኀይል ይጥለዋል፡፡ ደጋግሞም እያነሳ ይጥለዋል፡፡ ነገር ግን ባልተለመደ ሁኔታ ድስቱ ሳይሰበር ቀረ፡፡ ይህንን ያዩና በጭንቀት ውስጥ የነበሩ አባቶች ባዕለ ጸጋው ከመድረሱ በፊት ቶሎ ብለው አባ ዘካርያስ /1004-1032/ ብለው መነኩሴውን እንደ ሾሙት በቤተ ክርስቲያኗ የታሪክ መዛግብት ሰፍሮ ይገኛል፡፡

 

ከላይ ባየናቸው ቀኖናዊ የምርጫ ማስፈጸሚያ ሥልቶችና ሂደቶች በእያንዳንዱ የተመረጡትን አባቶች ዝርዝር በሚከተለው ሠንጠረዥ ማየት ይቻላል፡፡

 

ተ.ቁ

ቀኖናዊ የምርጫ ሥልት

ወይም ሂደት

በሥልቱ ወይም በሂደቱ የተመረጡ አባቶች ብዛት

የተመረጡት ፓትሪያርኮች

ተራ ቁጥር

1

የካህናት ብቻ ምርጫ

16

4፣5፣6፣7፣8፣9፣10፣11፣12፣13፣14፣

15፣16፣17፣18፣

2

የምእመናን ብቻ ምርጫ

5

44፣70፣74፣77፣101

3

የኤጲስ ቆጶሳት ብቻ ምርጫ

4

19፣35፣52፣112

4

በጠቅላላ ስምምነት

35

20፣22፣24፣28፣36፣37፣43፣45፣

47፣51፣53፣54፣55፣61፣62፣67፣

68፣69፣72፣73፣76፣80፣81፣83፣

87፣95፣100፣106፣107፣109፣

110፣111፣113፣114፣115

5

በሓላፊው ፓትርያርክ ምርጫ

7

2፣21፣38፣39፣49፣50፣88

6

መለኮታዊ ምርጫ ወይም ራእይ

4

1፣12፣46፣82

7

ዕጣ የማውጣት ምርጫ

10

3፣48፣71፣102፣103፣104፣

105፣108፣116፣117

8

የመንግሥት ጣልቃ ገብነት

6

27፣31፣33፣41፣75፣78

9

በአጋጣሚ

3

42፣63፣64

 

በየትኛው ሥልት ወይም ሂደት እንደተመረጡ የማይታወቁ

27

 

 

ድምር

117

 

 

የፓትርያርክ ምርጫ ሥርዓትና አፈጻጸም በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ

ከላይ ባየናቸው ሥልቶች ፓትርያርኮቿን እየመረጠች 2000 ዓመታት የተጓዘችዋ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በቅርቡ ያለፉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሲኖዳ 3ኛና እሳቸው የተኳቸው አባ ቄርሎስ ምርጫ ወቅት ሥራ ላይ ውሎ የተፈተነ ቀዋሚ የፓትርያርክ ምርጫ ደንብ አላት፡፡ የዚህን ደንብ ትርጉም ተግባር ላይ ከመዋሉ በፊትና ከዋለ በኋላ ያጋጠሙትንና እያጋጠሙት ካሉት ተግዳሮቶች ጋር በሚቀጥለው አቀርባለሁ፡፡

 

ምንጭ:-

Atiya, Aziz S.ed., The Coptic Encyclopedia.8 vols. New York:macmillan,1991.

E l- Masri, Iris Habib. The Story of the Copts: The true Story of Christian in Egypt. Cairo: Coptic Bishopric of African Affairs.1987.

Evetts. B. ed “History of the patriarchs of the Coptic Church of Alexandria” Patrologia Orientalis I.4, Paris,1984

Meinardus, O.F.A. Christian Egypt: Faith and Life. Cairo: American University in Cairo Press, 1970.

Saad Michael Saad and Nardine Miranda Saad. “Electing Coptic Patriarchs: A Diversity of Tradition”

Bulletin of St. Shenouda the Archimanrite Coptic Society 6,1999-2000, pp.20-32.