Debre_Tabor

ደብረ ታቦር

ሐሴ 13 ቀን 2004 ዓ.ም.

በመ/ር ምሥጢረ ሥላሴ ማናየ

“ወኮነት ደብረ ታቦር አምሳለ ቤተ ክርስቲያን እስመ አስተጋብአት እም ብሉይ ወሐዲስ”

 

ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ነች፤ ከብሉይና ከሐዲስ ሰብስባለችና፡፡ ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ሙሴና ኤልያስን ከሐዲስ ኪዳን ሐዋርያት ጴጥሮስን ያዕቆብን፣ ዮሐንስን ከመምህራቸው ከክርስቶስ ጋር ሰብስባለችና፡፡ ቤተ ክርስቲያን በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ተመሥርታለች “እስመ ተሐነጽክሙ ዲበ መሠረተ ነቢያት ወሐዋርያት እንዘ ክርስቶስ ርዕሰ ማዕዘንተ ሕንጻ”  “በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ ታንጻችኋል፤ የማዕዘኑም ራስ ደንጋይ ክርስቶስ ነው” እንዲል፡፡ኤፌ. 2፥20

የታቦር ተራራ

፩. የቤተ ክርስቲያን

፪. የወንጌል

፫. የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡

 

አንደኛውን ምሳሌ ከላይ የተመለከትን ሲሆን ሁለተኛው ምሳሌ አበው መተርጉማን በትርጓሜአቸው እንዲህ አብራርተውታል፡፡ ተራራ ሲወጡት አድካሚ ነው ከወጡት በኋላ ግን ሁሉንም ቁልጭ አድርጎ ሲያሳይ ደስ ያሰኛል፤ ወንጌልም ሲማሯት፤ ሲያስተምሯት ታደክማለች፤ ከተማሯት በኋላ ግን ጽድቅና ኀጢአትን ፤እውነትንና ሐሰትን ለይታ ስታሳውቅ ደስ ታሰኛለችና”፡፡ “በሌላ መልኩ ከተራራ ላይ ያለ ሰው ጠላቱን በቀላሉ በአፈር በጠጠር ድል መንሣት፣ ፍትወታት እኩያትን ማሸነፍ ይችላል፡፡ ከተራራ ላይ ያለ ልሰወር ቢል እንዳይችል በወንጌል ያመነ ሰውም ተሰውሮ አይቀርም በመልካም ሥራው ለሁሉም ይገለጣል፡፡ በሦስተኛውም ተራራው የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው፡፡ ከነቢያት ሁለቱ ከሐዋርያት ሦስቱ በተራራው ላይ መገኘታቸው መንግሥተ ሰማያት ነቢያትም ሐዋርያትም አንድ ሆነው የሚወርሷት መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከደናግ ኤልያስዮሐንስ ከመአስባን (በሕግ ጋብቻ ኖረው ሚስቶቻቸው የሞቱባቸው ወይም ትዳራቸውን የተው) ሙሴ ጴጥሮስ በተራራው ላይ መገኘታቸውም መንግሥተ ሰማያት ደናግም መአስባንም መልካም ሥራ ሠርተው በአንድነት የሚወርሷት እንደሆነ ይገልጻል፡፡

እንዲሁም ተራራ ሲወጡት አድካሚ ነው መንግሥተ ሰማያት በብዙ ድካም ትወረሳለችና “እስመ በብዙህ ጻማ ሐለወነ ንበአ ውስተ መንግሥተ እግዚአብሔር” ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ አለን” እንዲል ሐዋ.14፥23 ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር የገለጸበት ምክንያት ምሥጢር በብዙ ድካም እንጂ ምንም ሳይደክሙ እንደማይገኝ ሲገልጽ ነው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ ብዙዎቹን ምሥጢራት የገለጠላቸው ከከተማ ውጭ ነው፡፡ ቀደም ሲልም ለሙሴ የቃል ኪዳኑን ጽላት ሲሰጠው ወደ ሲና ተራራ በመጥራት ነበር፡፡ ነገረ ሥጋዌውንም በነበልባልና በእሳት አምሳል የገለጠለት በኮሬብ ተራራ በጎቹን አሰማርቶ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ መጻሕፍት ይመሰክራሉ ዘፀ.3፥1 ምሥጢር ይገለጽልን ባላችሁ ጊዜ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገስግሱ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ ጽኑ ለማለት ነው፡፡ ወደ ተራራውም ሲወጣ ስምንቱን ደቀ መዛሙርቱን ከይሁዳ ጋር ከተራራ እግር ስር ትቶ ሦስቱን አስከትሎ ወጥቷል፡፡ ለሦስቱ በተራራው ላይ የተገለጠው ድንቅ ምሥጢርም ከእግረ ደብር ላሉት በሳምንቱ ተገልጿል፤ ከይሁዳ በቀር፡፡ ለዚህ ምሥጢር ብቁ ያልነበረው ይሁዳ ብቻ ነው፡፡ ይህም የሚያስተምረን ተገቢውን ምሥጢር ለተገቢው ሰው መንገር እና ለማይገባው ከመንገር መቆጠብ ተገቢ መሆኑን ነው፡፡ “እመኒ ክዱን ትምዓርትነ ክዱን ውእቱ ለህርቱማን ወለንፉቃን” ወንጌላችን የተሰወረ ቢሆንም እንኳን ፥ የተሰወረባቸው ለሚጠፉት ነው፡፡ እግዚአብሔርን የሚመስለው የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው የዚህ ዓለም አምላክ ልባቸውን አሳውሯልና፡፡ 2ቆሮ.4፥3-5 ያለው የሐዋርያው ትምህርት ይህን መሰል ምሥጢር ለሚገባው እንጂ ለማይገባው መግለጽ ተገቢ አለመሆኑን ነው፡፡

 

በዓለ ደብረ ታቦር

እንደሚታወቀው በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዘጠኙ ዐበይት /ታላላቅ/ በዓላት አንዱ በዓለ ደብረ ታቦር ነው፡፡ ከዐበይት በዓላት የተመደበበትም ምክንያት በደብረ ታቦር የተገለጸው ምሥጢር ድንቅ በመሆኑ ነው፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ አንድ አንድ ጊዜ ለሁሉም፤ አንድ አንድ ጊዜ ደግሞ በከፊል ምሥጢራትን ገልጾላቸዋል፡፡ ከእነዚህም ምሥጢራት የሚከተሉት ተጠቃሾች ናቸው ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንን በቤተ አልዓዛርና በቤተ ኢያኤሮስ፣ ምሥጢረ ቊርባንን እንዲሁ በአልዓዛር ቤት፣ ነገረ ምጽአትን በደብረ ዘይት ገልጿል፡፡ ማቴ.9፥23፣ 26፥26፣24፥3፣ ዮሐ.11፥43 ከእነዚህ ከላይ ከተዘረዘሩት ምሥጢራት ምሥጢረ ትንሣኤ ሙታንና ምሥጢረ ቊርባንን ሁሉም ደቀ መዛሙርት ያዩ ሲሆን ነገረ ምጽአትን ግን በከፊል ከደቀ መዛሙርቱ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ አራተኛ እንድርያስን ጨምረው ተረድተዋል፡፡ ደብረ ታቦርን ከዚህ ልዩ የሚያደርገው ከሐዋርያት ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ያዕቆብ ያሉ ሲሆን ከነቢያት ሙሴና ኤልያስ መጨመራቸው ነው፡፡ ከጌታችን ዘጠኝ በዓላት አንድ አንዶቹ በተፈጸመው ድርጊት የተሰየሙ ሲሆን ከፊሎቹ ድርጊቱ በተፈጸመባቸው ቦታዎች ተሰይመዋል፡፡ በድርጊቱ የተሰየሙት ጽንሰት፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገት ሲሆኑ ሁለቱ ሆሳዕናና  ጰራቅሊጦስ ደግሞ ድርጊቱንና ስምን አስተባብረው የያዙ ሲሆን ከእነዚሁ ሁሉ ተለይቶ ደብረ ታቦር ድርጊቱ በተፈጸመበትDebre_Tabor ቦታ ተሰይሟል፡፡

 

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉም ምሥጢራት ነገረ ምጽአቱንና ምሥጢረ መንግሥቱን በተራራ ላይ ገልጿል፡፡ ነገረ ምጽአትን በደብረ ዘይት የገለጸበትን ምክንያት ጠቢቡ ስሎሞን ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለ ለጊዜው ትተነው ወደ ደብረ ታቦር እንመለስ ፡፡ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ነቢያት ሊያዩት የተመኙትን ያዩበት ነቢያትና ሐዋርያት በአንድነት የተገናኙበት፣ ተገናኝተው እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆነው የክርስቶስን የባህርይ አምላክነት የመሰከሩበት፤ እግዚአብሔር ወልድ በክበበ ትስብዕትና በግርማ መለኮት የተገለጠበት፣ እግዚአብሔር አብ በደመና የምወደው ለተዋሕዶ የመረጥኩት በዕርሱ ህልው ሆኜ የምመለክበት ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሎ የመሰከረበት፣ መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ የወረደበት፣ እግዚአብሔር አንድነቱን ሦስትነቱን የገለጠበት እነ ቅዱስ ጴጥሮስ ለመኖር የተመኙት ደብረ ታቦር ነው፡፡ በዓሉ የጌታችን ሲሆን በስሙ ደብረ ታቦር ተብሏል፡፡ ይህን በዓል ስናከብር ያን ጊዜ ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን አስከትሎ ወደ ተራራው ሲወጣ በተራራው ራስ ላይ ምሥጢሩን ሲገልጥላቸው አእምሮአቸውን ሲከፍትላቸው ከግርማው የተነሣ ፈርተው ሲወድቁ ሲያነሣቸው በዐይነ ሕሊና የምንመለከትበት ነው፡፡

 

ለዚህ ምሥጢር ደብረ ታቦር ለምን ተመረጠ?

1.    ደብረ ታቦር የድል ተራራ ነው፡፡

የእስራኤል ነቢይት ዲቦራ ለባርቅ የእስራኤል ጠላት የነበረው የኢያቢስን የሠራዊት አለቃ ሲሣራን ለመውጋት ወደ ደብረ ታቦር አስር ሺ ሰዎችን አስከትሎ እንዲወጣ ነግራዋለች፤ “የአቢኒኤምን ልጅ ባርቅ ጠርታ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሔደህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን ልጆች አስር ሺ ሰዎች ውሰድ” መሳ.4፥6፡፡ በዚህ መልኩ ባርቅ አስር ሺ ሰዎችን አሰልፎ ዲቦራን አስከትሎ በደብረ ታቦር ሰፍሮ የነበረውን የሲሣራን ሠራዊት ድል ነሥቶበታል፡፡ ሲሣራ ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገላ እንዲሁ ብዙ ሠራዊትም በታቦር ያሰለፈ ቢሆንም ድል ግን ረድኤተ እግዚብሔርን ጥግ ላደረገ ለባርቅ ሆነ፤ በዚህ ጊዜ ዲቦራ በታቦር ተራራ የሙሴ እኅት ማርያም በኤርትራ ባሕር የዘመረችውን መዝሙር የመሠለ ምስጋና አቅርባለች፡፡ ሁሉም እስራኤላውያን የድል መዝሙር ዘምረውበታል ፈጣሪአቸውን አመስግነውበታል፡፡ ጌታችንም የባሕርይ አምላክነቱን ገልጾ ከደቀ መዛሙርቱ ልቡና አጋንንትን የሚያባርርበት ዲያብሎስን ድል የሚነሳበት ስለሆነ ከሌሎች ተራሮች ተመርጧል፡፡

 

2.    ትንቢት ተነግሮለታል

“ታቦር ወአርሞንዔም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ወይሴብሑ ለስምከ” መዝ. 88፥12 ታቦርና አርሞንዔም በስምህ ደስ ይላቸዋል” ብሎ ቅዱስ ዳዊት ከክርስቶስ ሰው ሆኖ መገለጥ በፊት አምላካችን ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በደብረ ታቦር እንደሚገልጽ ብርሃኑ ከደብረ ታቦር እስከ አርሞንዔም ድረስ እንደሚታይ ይህም መለኮታዊ ብርሃን በታቦርና በአርሞንዔም ዙሪያ ለነበሩ ሕዝቦች ደስታ እንደሚሆን ተናግሯል፡፡ እንደሚታወቀው ታቦር የተባለው ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራብ በኩል 10 ኪ. ሜትር ርቆ የሚገኝ ተራራ ሲሆን ተራራው እስከ 572 ሜትር ከባሕር ጠለል/ወለል ከፍ ይላል፡፡ ቀደም ሲል እንደገለጽነው ባርቅ ሲሣራን ድል ነሥቶበታል፤ የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳዖል በሳሙኤል እጅ ተቀብቶ ሲመለስ ሦስት ሰዎች ታገኛለህ አንዱ ሦስት የድል ጠቦቶች ሁለተኛው ሦስት ዳቦ ይዟል፤ ሦስተኛውም የወይን ጠጅ አቆማዳ ይዟል፡፡ ሠላምታ ይሰጡሀል ብሎ ሳሙኤል ነግሮት ነበር፡፡ በነገረው መሠረት ሦስት ሰዎችን አግኝቶበታል፡፡ “ከዚያም ደግሞ ወደፊት ትሔዳለህ ወደታቦር ወደትልቁ ዛፍ ትደርሳለህ” 1ሳሙ.10፥3-5፡፡

 

ስለዚህ ተራራ ቅዱስ ዳዊት በድጋሜ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሮለታል፡፡ “የእግዚአብሔር ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፡፡ የጸና ተራራ የለመለመ ተራራ ነው፡፡ እግዚአብሔር ይህን ተራራ ያድርበት ዘንድ ወደደው” መዝ.67፥15 ብሎ እግዚብሔር ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጥበት ዘምሮአል፡፡ በእነዚህ ከላይ በአየናቸው ሁለት ምክንያት ደብረ ታቦር ለዚህ ተመርጧል፡፡ወንጌላዊያኑ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ማርቆስ ጌታችን ወደ ደብረ ታቦር የወጣው ደቀ መዛሙርቱን በቂሣርያ “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል” ብሎ በጠየቃቸው በሰባተኛው ቀን ነው ብለው በቅዱስ ወንጌል የጻፉ ሲሆን ቅዱስ ሉቃስ በስምንተኛው ቀን ነው ይላል፡፡ ማቴ.17፥1-8፣ ማር.9፥2-8፣ ሉቃ.9፥28 ነገሩ እንዴት ነው? “እምድኅረ ሰዱስ መዋዕል ነሥኦሙ እግዚእ ኢየሱስ ለጴጥሮስ ወለ ያዕቆብ ወለ ዮሐንስ ዕሁሁ ወአፅረጎሙ ደብረ ነዋኅ እንተ ባህቲቶሙ” ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው” ማቴ. 17፥1፣ ማር.9፥2፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ነገሩ እንደ ማቴዎስ ነው ብለው በሰባተኛው ቀን መሆኑን በትርጓሜያቸው አስቀምጠዋል፡፡ ታዲያ ስለምን ስምንት አለ? የሚለውን ሲያትቱ /ሲያብራሩ/ ስምንት ያለው ሰባት ሲል ነው ብለው ተርጉመውታል ምክንያቱም አንድ ሳምንት የሚባለው ሰባት ቀን ነው፡፡ ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ዕለተ ሰንበት ሲናገር ኦ ቅድስት ንዒ ኀቤነ ለለሰሙኑ ከመንትፈሣህ ብኪ ለዓለመ ዓለም” ቅድስት ሆይ በየሳምንቱ ወደኛ ነዪ በአንቺ ደስ ይለን ዘንድ ለዘለዓለሙ”  በማለት ሰሙን ማለት ስምንት ማለት ቢሆንም ሊቁ ግን ሳምንት ብሎት ይገኛል፤ ሳምንት ማለት ደግሞ ሰባት ቀን ነው ከዚህ የተነሣ ሉቃስ በሰባተኛው ቀን ያለው በሰባተኛው ሲል ነው፡፡ በሌላ መልኩ ማቴዎስ በሰባተኛው ቀን ሲል ሉቃስ በስምንተኛው ቀን ማለቱ የወጡበትንና የተመለሱበትን ቆጥሮ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ መጽሐፍ የጎደለውን ሞልቶ የሞላውን አትርፎ መናገር ልማዱ ነው ይህንም በሚከተሉት ማየት እንችላለን፡፡

 

ሰሎሞን “ወነበርኩ ውስተ ከርሰ ዕምየ አሠርተ አውርሀ ርጉኦ በደም” ጥበ.7፥2 “በእናቴ ማኅፀን በደም ረግቼ አሥር ወር ነበርኩ ብሏል ይህን ያክል ረጅም ቀን የመጨመር ልማድ ያለው መጽሐፍ በስምንተኛ ቀን ቢል ብዙ የሚደንቅ አይደለም የሚጣረስም አይደለም፡፡ የሚጣረሰው ወይም የሚጋጨው የእኛ አእምሮ ነው ከዕውቀት ማነስ ስለሆነ፡፡

 

ወበጽሐ ወርሀ ለኤልሳቤጥ” የኤልሳቤጥም የመውለጃዋ ወራት ደረሰ ሲል ቀን አልዘረዘረም ሰው የሚወለድበት ቀኑ የታወቀ ስለሆነ ነው፡፡ ሉቃ.1፥57 ስለ እመቤታችንም ሲናገር “በዚያ ሳሉም የመውለጃዋ ወራት ደረሰ የበኩር ልጅዋንም ወለደች” ሉቃ.2፥6 ወራት ሲል ከአንድ በላይ ሁለትም ሦስትም ወራት ይባላሉ አሁን ከዚህ የምናየው መጽሐፍ ጠቅልሎ ሲፈልግ ዘርዝሮ አስፈላጊ ሲሆን በአኀዝ ወስኖ ሲልም ጎድሎ አስፈላጊ ሲሆን ሞልቶ ሊናገር እንደሚችል ያስረዳናል፡፡ “ተፀውረ በከርሣ ፱ተ አውራሀ” ዘጠኝ ወር በማኅፀኗ አደረ” ወደ ማርያም በማኅፀኗ ያደረው ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ሲሆን አምስት ቀን አጉድሎ ሲናገር እናገኘዋለን ከዚህ አንጻር ሉቃስም አንድ ጨምሮ ነው ስምንት ያለው መጨመር ማጉደል የመጻሕፍት ልማድ ነውና፡፡

 

ጌታችን በደብረ ታቦር ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠው እንዴት ነው?

ይህንን ከማየት አስቀድሞ መገለጡ በምን ምክንያት ነው የሚለውን ማየቱ የተሻለ ነው፡፡ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠው በሦስት ምክንያቶች ነው ነሐሴ ሰባት ቀን በቂሳርያ ደቀ መዛሙርቱን “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን ይሉታል? ” ብሎ በጠየቃቸው ጊዜ ኤርምያስ ነው፣ ኤልያስ ነው፣ ዮሐንስ መጥምቅ ነው፣ ከነቢያት አንዱ ነው፣ ይሉሀል የሚል የተለያየ መልስ ተሰጥቶት “እናንተስ ማን ትሉኛላችሁ?” ባላቸው ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መስክሯል፡፡

 

  1. በፍጡር ቃል የተመሰከረውን በባሕርይ አባቱ ለማስመስከር

  2. ከነቢያት አንዱ ነው ብለውት ነበርና እግዚአ ነቢያት /የነቢያት ጌታ/ እንደሆነ ለማስረዳት

  3. እሞታለሁ እሰቀላለሁ ሲል ጴጥሮስ “ሀሰ ለከ” ልትሞት አይገባህም ብሎት ነበርና እርሱን ስሙት ለማለት፡፡

 

በፍጡር በጴጥሮስ የተመሠከረውን ምስክርነት የባሕርይ አባቱ “ይህ የምወደው ልጄ ነው እርሱን ስሙት” ማለት እሞታለሁ እሰቀላለሁ ቢላችሁ አይገባህም አትበሉት ዓለም የሚድነው በእርሱ ሞት ነውና ተቀበሉት ለማለት ነው፡፡  ለጴጥሮስ መልስ እንዲሆን ይህ ሊሆንብህ አይገባም ብሎት ነበርና ያዕቆብና ዮሐንስም አንዳችን በቀኝህ አንዳችን በግራህ እንሾም ብለው ነበርና ፍቅረ ሲመትን ሊያርቅላቸው የእርሱን የባሕርይ ክብሩን አይተው የመጣለት ዓላማ ልዩ መሆኑን እንዲረዱ እነዚህን ሦስቱን ይዞ ወደ ተራራው ወጥቷል፡፡ ከነቢያት አንዱ ነው ብለውት ነበርና ከነቢያት ሙሴንና ኤልያስን በተራራው ተገኝተው እንዲመሰክሩ አድርጓል፡፡ ሙሴ ምነው የኔን የሙሴን አምላክ÷ አምላከ ሙሴ፣ እግዚአ ሙሴ ይበሉህ እንጂ ማነው ሙሴ የሚልህ፤ ኤልያስም የኔን የኤልያስን አምላክ÷ ኤልያስ የሚልህ ማነው? አምላከ ኤልያስ፣ እግዚአ ኤልያስ ይበሉህ እንጂ በማለት መስክረውለታል እንዴት ነው ምሥጢረ መለኮቱን የገለጠው የሚለውን ለማብራራትም ሆነ ለመተንተን ዕውቀትም ቃላትም ያጥረናል፡፡ ወንጌላውያን መግለጥ በሚችሉት መጠን ከገለጹት ያለፈ ልናብራራው የምንችለው አይደለም፡፡ ማቴዎስ እንዲህ ይገልጸዋል “ወተወለጠ ራዕዩ በቅድሜሆሙ ወአብርሀ ገጹ ከመ ፀሐይ ወአልባሲሆኒ ኮነ ፀአዳ ከመ በረድ” “በፊታቸውም ተለወጠ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ” ማቴ.17፥2 ብሎ ወንጌላዊው በዚህ ዓይነት ገለጾ የተናገረው ምሳሌ ስለ አጣለት ነው፡፡ ማርቆስም ይህንኑ ተጋርቶ “ልብሱን አንፀባረቀ አጣቢም በምድር ላይ እንደዚያ ሊያነጣው እስከማይችል በጣም ነጭ ሆነ” ማር.9፥2-4 “የፊቱ መልክ ተለወጠ ልብሱም ተብለጭልጮ ነጭ ሆነ” ሉቃ.9፥29-30፡፡ ከዚህ ወንጌላውያን ከገለጹበት የሚሻል ምሳሌ አናገኝለትም፡፡ በደብረ ታቦር ሐዋርያት ካዩት በተጨማሪ አብ በደመና ሆኖ የምወደው ልጄ ነው እርሱን ስሙት ሲል ተሰምቷል መንፈስ ቅዱስም በአምሳለ ርግብ ታይቶ አንድነት ሦስትነት ተገልጿል፡፡

 

ይህንን ኢትዮጵያዊቷ የቅኔ መምህርት እማሆይ ገላነሽ እንዲህ በማለት በቅኔአቸው ገልጸውታል፡፡

“በታቦርሂ አመቀነፀ መለኮትከ ፈረስ

ኢክህሉ ስሂቦቶ ሙሴ ወኤልያስ”

መለኮት ፈረስ በደብረ ታቦር በዘለለ ጊዜ ሙሴና ኤልያስ ሊስቡት አልቻሉም”

ብለው በምን አይነት ግርማ እንደተገለጸ ተቀኝተዋል፡፡

የደብረ ታቦር ባሕላዊ አመጣጥና ከመንፈሳዊው ሥርዓት ጋር ያለው ተዛምዶ፡-

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፣ “የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው የደብረ ታቦር በዓል አከባበርን አስመልክቶ በሀገራችን ያለውን ሥርዓትና የትመጣነት እንደሚከተለው ጽፈውታል፡-

አስቀድመን እንደተመለከትነው ጌታችን በዚህ ዓለም እየተመላለሰ በሚያስተምርበት ጊዜ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን መግለጡን በማሰብ በየዓመቱ ነሐሴ 13 ቀን በዓሉ ይከበራል፡፡ ይህ በዓል በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለይም በምእመናን ዘንድ የተለየ ስም አለው፤ ይኸውም “ቡሄ” የሚለው መጠሪያ ስም ነው፡፡ ቡሄ ማለት /መላጣ ፣ ገላጣ/ ማለት ነው፡፡ በሀገራችን ክረምቱ፣ አፈናው ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታይበት በዚሁ በዓል አካባቢ ስለሆነ “ቡሄ” ያሉት ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ድርጊቱ በተፈጸመበት በፍልስጥኤም ግን የደመና መልክ የማይታይበት ፍጹም የበጋ ወራት ነው፡፡ በሀገራችን ሕፃናቱ ይህ በዓል ከመድረሱ በፊት ቀደም አድርገው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮሁ /ሲያኖጉ/ ይሰነብታሉ፡፡ እናቶችም ለዚህ በዓል የሚሆን ዳቦ ለመጋገር /የሚከበረው በዓል ነውና/ ስንዴያቸውን ሲያጥቡ፣ ሲፈትጉ ይሰነብታሉ፡፡ በዓሉ እንደነገ ሊሆን እንደ ዛሬ በዋዜማው /ነሐሴ 12/ የሠፈር ሕፃናት በየቤቱ እየዞሩ “ቡሄ ቡሄ” እያሉ ይጨፍራሉ፡፡ የሚገጥሙትም ግጥም አላቸው፡፡ “ቡሄ ና ቡሄ በሉ፤ ቡሄ መጣ፣ ያመላጣ ቅቤ ቀቡት እንዳይነጣ” እዚህ ላይ ቡሄ ያሉት ዳቦውን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ እናቶች ካዘጋጁት ዳቦ እያነሱ ይሰጧቸዋል፡፡ ሄደው ዳቧቸውን እየገመጡ ሲጋረፉ ይውላሉ፡፡ ለግርፊያው ተምሳሌት ባይገኝለትም የጅራፉ መጮህ የድምፀ መለኮት ፣ጅራፉ ሲጮህ ማስደንገጡ የሐዋርያትን /የጴጥሮስን፣ የያዕቆብንና የዮሐንስን/ በድምፀ መለኮት መደንገጣቸውንና መውደቃቸውን ያስተውላል፡፡

በአንዳንድ ቀበሌዎች የቡሄ ዕለት ማታ ችቦ ያበራሉ፡፡ በደብረ ታቦር ለታየው ብርሃነ መለኮት ምሳሌ ነው፡፡ በዚያውም ላይ በኢትዮጵያችን የፀዓተ ክረምት ዋዜማ ስለሆነ ቡሄን ብርሃን ቢሉት ይስማማዋል፡፡ “ቡሄ ከዋለ የለም ክረምት ዶሮ ከጮኸ የለም ሌሊት” እንዲሉ፡፡ የቡሄ ዕለት ለዘመድ ለአዝማድ ለእያንዳንዱ ቤተሰብ በልጆቹ ልክ ዳቦ ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ለክርስትና ልጅ፣ ለአማች ለምራት፣ የቅርብ ዕውቂያ ላለውም ሁሉ የቡሄ ዳቦ ይሰጣል፡፡ በተማሪ ቤት ደግሞ ተማሪዎች ቀደም አድርገው “ስለደብረ ታቦር” እያሉ እህሉን፣ ጌሾውን ብቅሉን ይለምናሉ፤ ሕዝቡም ባሕሉን ስለሚያውቅ በገፍ ይሰጣቸዋል፡፡ የደብረ ታቦር ዕለት ጠላውን ጠምቀው ቆሎውን ቆልተው ዳቦውን ጋግረው ሊያስቀድሱ የመጡትን ምእመናን ሁሉ ከቅዳሴ በኋላ ይጋብዛሉ፡፡ ይህ እስከ አሁን በትምህርት ቤቶች የሚሠራበት ነባር ትውፊት ነው፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር