abuneteklhymanote

ሐዲስ ሐዋርያ ተክለ ሃይማኖት

ነሐሴ 23 ቀን 2004 ዓ.ም.


abuneteklhymanoteጻድቃንን ማሰብ ሥራቸውን መዘከር ክርስቲያናዊ ሕይወታችንን ያጐለምሳል፡፡ የበረከታቸው ተሳታፊ በማድረግ በነፍስ በሥጋ የሚታደገንን የሚረባን፤ የሚጠቅመን ይሆናል፡፡ ስለጻድቁ አባታችን ስለ ቅዱስ ተክለ ሃይማኖትም የምናስበው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በመንፈሳዊ አርአያነታቸው፣ በጸሎታቸውና በትምህርታቸው ከከበቡን የነፍስ ጠላቶች፤ ከርኲሳን መናፍስትና ከጨለማው ልጆች፣ ከክፉ ሰዎች ሽንገላና ተንኰል ለመሰወርና ለመጠበቅ ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ሥልጣን ምን ጊዜም ይሠራል፡፡ በጻድቃን መኖር ሀገር ከጥፋት ትድናለች፡፡ የጻድቃንን ስም ጠርቶ እግዚአብሔርን በመለመን በረከትና ረድኤት ይገኛል፡፡ ስለጻድቃን ብሎ እግዚአብሔርም ምሕረቱን ያድላል፡፡ ስለዚህ ነው ቤተ ክርስቲያናችን ጻድቃንን እንድናስባቸው፣ በስማቸውም ለድሆችና ለጦም አዳሮች እንድንመጸውት መታሰቢያቸውን እንድናደርግ የምትመክረን፤ የምታስተምረን፡ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖትንም የምናስባቸው ከዚሁ የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በመነሣት ነው፡፡ ማቴ.10፥41-42 ጻድቃንን በሕይወተ ሥጋ ሳሉም ቢሆን፤ ከሞቱም በኋላ በአጸደ ነፍስ በጸሎታቸው ለሚታመኑ፣ በቃል ኪዳናቸው ለሚማጸኑ፣ የድኅነተ ሥጋ፣ የድኅነት ነፍስ ምክንያት ናቸው፡፡

በዚህ መሠረት ከቅዱሳን አባቶች መካከል ለኢትዮጵያ ሐዲስ ሐዋርያ ሆነው የተመረጡና ከጻድቃን መካከል የሆኑትን የቅዱስ ተክለሃይማኖት በዓለ ዕረፍትን መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ ዜና ሕይወታቸውን ከዚህ እንደሚከተለው በአጭሩ እናቀርባለን፡፡

 

ጻድቁ አባታችን ተክለ ሃይማኖት በአምላክ ፈቃድ፣ በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት፤ ከአባታቸው ከካህኑ ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኀረያ ታኅሣም 24 ቀን 1212 ዓ.ም.  ተወለዱ፡፡ ወላጆቻቸው ስማቸውን ፍሥሐ ጽዮን በማለት አወጡላቸው፡፡ በተወለዱ በሦስተኛውም ቀን እሑድ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው “አሐዱ አብ ቅዱስ፤ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፤ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፡- አንዱ አብ ቅዱስ ነው፤ አንዱ ወልድ ቅዱስ ነው፤ አንዱ መንፈስ ቅዱስ ቅዱስ ነው፡፡” በማለት የሥላሴን ስም ጠርተው አመስግነዋል፡፡ በተወለዱ በ15 ዓመት ዕድሜያቸው ዲቊናን፣ በ22 ዓመታቸው ቅስናን ከግብፃዊው ጳጳስ ከአባ ጌርሎስ /ቄርሎስ/ ተቀብለዋል፡፡

 

ከዕለታት በአንዱ ቀን አባታችን ወደ ጫካ ለአደን ሄደው ሳለ፤ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ግሩም ድንቅ የሆነ ልብስ ለብሶ ታያቸው፡፡ አባታችንም እንደዚህ ባለ ገናንነት የማይህ ጌታዬ ማነህ?” አሉት፡፡ ቅዱስ ሚካኤልም “ዘወትር የምጠብቅህ ካንተ የማልለይ እናትህንና አባትህንም ስላንተ ከውኃ ስጥመትና ከምርኮ ያዳንኳቸው እኔ ሚካኤል ነኝ፡፡ እንግዲህ አውሬ አዳኝ አትሁን፤ ሰውን ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ሰውን በትምህርት የምታድን ሁን እንጂ፡፡ እነሆ እግዚአብሔር ጽኑዕ ሥልጣን ሰጥቶሀልና፤ ሙት ታስነሣለህ፤ ድውያንን ትፈውሳለህ፤ አጋንንትም አንተን በመፍራት ይሸሻሉ፡፡ ስምህ ፍሥሐ ጽዮን አይሁን፤ ተክለ ሃይማኖት ይሁን እንጂ፡፡ ትርጓሜውም ተክለ አብ፥ ተክለ ወልድ፥ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት ነው፡፡” አላቸው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ይህን ሲያነጋግራቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር እንደነበር ሆኖ መልከ መልካም ጎልማሳ መስሎ ታያቸው፡፡ ጌታችንም “ወዳጄ እንዴት ሰነበትክ! ቸር አለህን፤” አላቸው፡፡ ብፁዕ ተክለ ሃይማኖትም “ጌታዬ ሆይ አንተ ማነህ? ብለው ጠየቁ፡፡ ጌታም “እኔ የዓለም መድኀኒት ኢየሱስ ነኝ፤ በናትህ ማኅፀን ፈጥሬህ ያከበርኩህ እኔ ነኝ፡፡ በተወለድክ በሦስተኛው ቀን አሐዱ አብ ቅዱስ፥ አሐዱ ወልድ ቅዱስ፥አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ፥ብለህ ታመሰግነኝ ዘንድ የምስጋና ሀብት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ በረሃብ ዘመን በቤት የሚያሻው ምግብ ሁሉ ቅቤው፣ የስንዴው ዶቄት በእናት በአባትህ ቤት ይመላ ዘንድ በእጅህ ሀብተ በረከት ያሳደርኩብህ እኔ ነኝ፡፡ ያንን ሰው አንተን በተጣላ ጊዜ በነፋስ አውታር የሰቀለኩት በመዓት ጨንገር የገረፍኩት እኔ ነኝ፡፡ ውኃ ጠምቶህ በለመንከኝ ጊዜ ከደረቅ መሬት የጣፈጠ ውኃ ያመነጨሁልህ አኔ ነኝ፡፡ ከልጅነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ብዙ ተአምራት እያደረግሁ በአንተ እጅ የታመሙትን ያዳንኳቸው እኔ ነኝ፡፡ ወደ ፊትም አደርግልሃለሁ፡፡ ይህንን ብሎ ንጹሓት ክቡራት በሆኑ እጆቹ ባረካቸው “ንሣእ መንፈስ ቅዱስ” ብሎ የሹመትን ሀብት አሳደረባቸው፡፡ በምድር ያሰርከው በሰማይ የታሰረ ይሁን፡፡ በምድርም የፈታኸው በሰማይ የተፈታ ይሁን፤ አንተን የሰማ እኔን መስማቱ ነው፤ የላከኝ አባቴንም መስማቱ ነው፡፡ አንተን እንቢ ያለ እኔን እንቢ ማለቱ ነው፡፡ የላከኝ አባቴንም እንቢ ማለቱ ነው፡፡ ይህን ሥልጣን ቀድሞ ለሐዋርያት ሰጥቻቸው ነበር፡፡ ከሐዋርያትም ሹመትን የተቀበለ ጳጳሱ ትሾምና ትሽር ትተክልና ትነቅል ዘንድ ሥልጣንን ሰጠህ፡፡ ይህንንም ያደረኩልህ የጳጳሱን ቃል በመናቅ አይደለም፡፡ የፍቅሬን ጽናት ባንተ እገልጽ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ሐዋርያት ወደአልደረሱበት ሕዝብ በመምህርነት እልክህ ዘንድ በሚካኤል ቃል አዲስ ስም አወጣሁልህ፡፡ አንተም በማናቸውም ሥራ ከነሱ አታንስም፡፡ ሐዲስ ሐዋርያ አድርጌሃለሁና፡፡ ሰውን ሁሉ በእኔ ስም እያስተማርክ ታሳምን ዘንድ፤ ሚካኤልም ባሰብከው ሥራ ሁሉ ረዳት ይሁንልህ፡፡ ሁል ጊዜ ካንተ አይለይም፡፡ በምትሄድበትም ጎዳና ሁሉ እርሱ መሪ ይሁንህ፡፡ እኔም ባለ ዘመንህ ሁሉ አልለይህም” ብሎ ሰላምታ ሰጥቷቸው ዐረገ፡፡ ብፁዕ አባታችንም እጅ ነስተው “ለእኔ ለኀጥኡ የማይገባኝ ሲሆን ይህን ሁሉ ጸጋ የጠኸኝ ስምህ በሰማይ በምድር የተመሰገነ ይሁን” አሉ፡፡ ከዚያች ቀን ጀምሮ ሀብተ ኀይልን የተመሉ ሆኑ፡፡ ከዚያም ወደቤታቸው ተመልሰው ያላቸውን ንብረት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው ጨረሱ፡፡ ከዚያም “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደተከፈተ ተውኩልህ” ብለው ቤታቸውን እንደተከፈተ ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡ /ገድለ ተክለሃይማኖት ዘሠሉስ ምዕ.28 ገጽ 116/

 

ከ1219-1222 ዓ.ም. በከተታ ሦስት ዓመት፣ ወንጌልን አስተማሩ፡፡ ቀጥለውም ዘጠኝ ወር በዊፋት አገልግሎታቸውን ፈጽመዋል፡፡ ከ1223-1234 ዓ.ም. ዳሞት በተባለው ስፍራ ወይም በወላይታ ሀገር ለ12 ዓመታት ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ትምህርት በመስጠት ተአምራት አድርገው፤ መልሰዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንንም አንፀዋል፡፡ በዚህ ሀገር ዲያብሎስ በዛፍ ላይ አድሮ አምላክ ነኝ እያለ ለረጅም ዘመናት ሕዝቡን በማሳት የሚጠቀምበትን ዛፍ በተአምራት ከሦሩ ነቅለው አፍልሰዋል፡፡

 

በዚህ ተግባራቸው ጌታችን በቅዱስ ወንጌል “የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፤ ይሄንን ሾላ ተነቅለህ ወደ ባሕር ተተከል ብትሉት ይታዘዝላችኋል፡፡” ሉቃ.17፥6 ያለውን አምላካዊ ቃል በተግባር አስመስክረዋል፡፡ ከዚህም በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድና ትእዛዝ ወደ አማራ ሳይንት ወሎ በመሄድ ሥርዓተ ምንኲስናን ከአባ በጸሎተ ሚካኤል ገዳም ገብተው ከ1234-1244 ዓ.ም. ለዓሥር ዓመታት የእርድና ሥራ በመሥራትና ገቢረ ታምራትን በማሳየት ጌታ በቅዱስ ወንጌል “ማንም ከእናንተ ታላቅ ሊሆን የሚወድ ለእናንተ አገልጋይ ይሁን፤ ከእናንተ ማንም ፊተኛ ሊሆን የሚወድ የእናንተ ባሪያ ይሁን፡፡ እንዲሁም የሰው ልጅ /ወልደ እጓለ እመሕያው ክርስቶስ/ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም፡፡ ማቴ.20፥26-28 ያለውን መለኮታዊ ትእዛዝ በተግባር አሳይቷል፡፡ ከ1244-1254 ዓ.ም. አባ ኢየሱስ ሞዓ ወደሚገኙበት ገዳም ሐይቅ እስጢፋኖስ በቅዱስ ሚካኤል መሪነት ሐይቁን በእግራቸው እንደ ደረቅ መሬት በመርገጥ ወደ ደሴቲቱ በመግባት የምንኲስናን ተግባራቸውን በመቀጠል በግብረ ሐዋርያትና በወንጌል የተነገረውን የእርድናን ተግባር ፤የአገልግሎትና ትሩፋት/ሥራ ከፍጻሜ አድርሰዋል፡፡ በአባ ኢየሱስ ሞዓ እጅም የንጽሕና ምልክት የሆነውን የምንኲስናን ቀሚስ ተቀብለዋል፡፡

 

ከ1254-1266 ዓ.ም. ለዐሥራ ሁለት ዓመታት አቡነ አረጋዊ ወዳቀኑት ገዳም በትግራይ ሀገረ ስብከት ወደሚገኘው ደብረ ዳሞ ገዳም በመግባትDebre libanos Monastary. በጊዜው ከነበሩት አበምኔት ከአባ ዮሐኒ ቆብና አስኬማ ተቀብለው በገድል በትሩፋት መንፈሳዊ ተጋድሎአቸውን ቀጠሉ፡፡ ከደብረ ዳሞ ገዳም ወደሌላ ለመሄድ ሲነሡ፤ ክቡር አባታችን ተክለሃይማኖት አበምኔቱና መነኰሳቱ ሲሸኟቸው ሳለ፤ አርባ ክንድ ርዝመት ባለው ገመድ ገደሉን ለመውረድ እንደጀመሩ፤ ገመዱ ከካስማው ሥራ በመቆረጡ እንዳይወድቁ በተሰጣቸው ስድስት የብርሃን ክንፎች እየበረሩ፤ ክንፎቻቸውን እያማቱ ሦስት ምዕራፍ ሄደው ዐርፈዋል፡፡ ከዚያም ወደ ገዳመ ዋሊ ገብተዋል፡፡ በዚህም ጊዜ ነቢዩ ኢሳይያስ የተናገረው ትንቢት “ለደካማ ኀይልን ይሰጣል፤ ጉልበት ለሌለው ብርታትን ይጨምራል፡፡ ብላቴኖች ይደክማሉ፤ ይታክቱማል፡፡ ጐበዛዝትም ፈጽመው ይወድቃሉ፡፡ እግዚአብሔርን በመተማመን የሚጠብቁ ግን ኀይላቸውን ያድሳሉ፤ እንደ ንስርም በክንፍ ይወጣሉ፤ ይሮጣሉ፤ አይታክቱም፡፡ “ኢሳይያስ 40፥29-31 ያለው ቃል በጻድቁ በቅዱስ ተክለ ሃይማኖት ሕይወት ሊተረጐም ችሏል፡፡ ከ1266-1267 ዓ.ም. አንድ ዓመት ሙሉ ገዳማተ ትግራይን በመጐብኘት ኢየሩሳሌምንና ግብፅ ያሉ ቅዱሳት መካናትን ሲጎበኙ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ አንድ ወር ሙሉ “ዳዳ” በተባለ ስፍራ ይመለክ የነበረውን 75 ክንድ ዘንዶ በጸሎት ኀይል በተአምራት ገድለውታል፡፡ አርባዓቱ እንስሳ /በኪሩቤልና በሱራፌል/ ስም ቤተ ክርስቲያን አንፀው፤ ታቦተ ሕግ /ጽላተ ሕግ/ አስገብተዋል፡፡ ከሴቶችና ከልጆች ሌላ፤ ሦስት ሺህ በጣዖት የሚያመልኩ ወንዶችን መልሰው፤ አጥምቀው አቊርበዋል፡፡ በዚህም ተግባራቸው መድኀኒታችን “እነሆ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ በጠላትም ኀይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጎዳችሁም ምንም የለም” ሉቃስ 10፥19 ያለው ቃል ተፈጽሞላቸዋል፡፡ ክቡር ዳዊት በመዝሙር 90፥13-14 “በተኲላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውና ዘንዶውን ትረግጣለህ፡፡ በእኔ ተማምኗልና አስጥለዋለሁ፤ ስሜንም ዐውቋልና እጋርደዋለሁ፡፡” የተባለው ትንቢት ተፈጽሞላቸዋል፡፡ ከ1267-1289 ዓ.ም. በደብረ ሊባኖስ ካለችው ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባት፤ ስምንት ጦሮችን /ሁለቱን በፊት፣ ሁለቱን በኋላ ሁለቱን በቀኝ፣ ሁለቱን በግራ አስተክለው  እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማምና ሞት፣ ነገረ መስቀልን በማሰብ በተመስጦ ሌትና ቀን ያለማቋረጥ በጾምና በጸሎት በአርምሞ ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከቊመት ብዛት የተነሣ ጥር 4 ቀን 1289 ዓ.ም. አንዲቱ የእግራቸው አገዳ ተሰብራለች፡፡ ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን ስባረ ዐፅም አክብረው በሥርዓት አኑረውታል፡፡ እግራቸው እስኪሰበር የቆዩባቸው ዓመታት በቊጥር ሃያ ሁለት ናቸው፡፡ በመዓልትና በሌሊት በትጋትና በቊመት በተጋድሎ ብዛት፤ አንዲት የአገዳ እግራቸው ስትሰበር፤ ዕድሜያቸው 92 ዓመት ሆኗቸው ነበር፡፡

 

ከ1289-1296 ዓ.ም. ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው በመቆም ያለምግብና ያለውኃ በትኅርምት ሌትና ቀን እንቅልፍ በዓይናቸው ሳይዞር እንደ ምሰሶ ጸንተው፤ በተመስጦ በትጋት ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነትን ሲለምኑ ኖረዋል፡፡ ከሰባቱ ዓመታት ውስጥ ጥቂት ውኃ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ ነበር፡፡ ማቴ.4፥4 የሐ.14፥22፣ 2ቆሮ.11፥26፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ጌታችን ተገልጾ፤ “በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ” በማለት የመለኮትን ነገር የሚናገር የእሳት አንደበት ያላቸው የመንግሥት ልብስ አልብሷቸዋል፡፡ በመስቀል ምልክት የተጌጡት ሰባት የሕይወት አክሊላት “ስለ ቀናች ሃይማኖትህ፤ ሃይማኖትን ለማስተማር መላዋን ኢትዮጵያን ስለመዞርህ፤ ከአረማውያን ሕዝብ ጋር በሃይማኖት ስትታገል ደምህን ስለማፍሰስህ፤ ወደ ኢየሩሳሌም ወርደህ ልዩ ልዩ የቅዱሳን ቦታዎች ስለመሳለምህ፤ በሰባት ዓመታት ቊመት የአንዱ አገዳ እግርህ ስለመሰበሩ፤ ስለብዙ ጾም ጸሎትህ ስግደትህ፤ ስለልብህ ንጽሕናና ቅድስና” ብሎ አቀዳጅቷቸዋል፡፡ ዝክራቸውን በማዘከር መታሰቢያቸውን የሚያደርጉ ሁሉ በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ፍጹም ዋጋና ፍጹም ክብር እንደሚሰጣቸው ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል፡፡ ያዕ.1፥12፣ ራእ.14፥1213፣ 2ጢሞ.4፥6-8 በመጨረሻም ለዐሥር ቀናት በሕመም ቆይተው፤ ፈጣሪያቸው የገባላቸውን ቃል ኪዳን ለመነኰሳት መንፈሳውያን ልጆቻቸውና ለደቀ መዛሙርቶቻቸው ከነገሩ በኋላ ነሐሴ 24 ቀን በክብር ዐርፈዋል፡፡ በከበረች ዕረፍታቸው ከዚህ የሚከተለውን የሃይማኖት ኑዛዜ አውርሰውናል፡፡

 

“ልጆቼ! አታልቅሱ፤ ነገር ግን የሽማግሌውን የአባታችሁን ቃል ስሙ፡፡ መጀመሪያ እምነታችሁ በእግዚአብሔር ላይ ይሁን፡፡ በዚህ ዓለም እንደተያዙ እንደ ዓለም ሰዎች ስለ ልብስና ስለምግብ አሳብ አታብዙ፡፡ በየጊዜው ሁሉ መጸለይን አታቋርጡ ለቤተ ክርስቲያንም ሌትና ቀን አገልግሉ፡፡ እግዚአብሔር በሚወደው ገንዘብ ንጽሐ ሥጋንና ጾምን ውደዱ፡፡ ውዳሴ ከንቱም የሚቀረውንም የዚህን ዓለም ክብር አትውደዱት፤ እናንተስ የቀደሙትን አባቶች በመከራና በድካም ብዛት ከዓለም የወጡትን በመጋደላቸውም ክፉውን ዐሳብ ድል የነሡትን ምሰሏቸው፡፡

 

ፍለጋቸውንም ካልተከተላችሁ፤ ልጆቻቸው አትባሉምና፤ በመከራቸው ካልመሰላችኋቸው በደስታቸው አትመስሏቸውም፤ በድካማቸውም ካልተባበራችሁ ወደ ቤታቸው አትገቡም.. እነሱን መስላችሁ ኀጢአተኛ አባታችሁን እኔን ደግሞ ምሰሉ፤ ስለትኅርምቱም በመብል በመጠጥ ልባችሁ እንዳይከብድ፣ ሥጋ ከመብላትና ጠጅ ከመጠጣት ተጠበቁ፡፡ ለመመካትም በዓለማዊ ልብስ አታጊጡ፡፡ የመላእክት አስኬማ ከዓለማዊ ሥራ ጋር አይስማማምና፤ ዓለምንም በዓለም ላይ ያለውን ሁሉ አትውደዱ፡፡ ዓለሙም ፈቃዱም ሓላፊ ነውና፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘለዓለም ይኖራል፡፡

 

ልጆቼ ሆይ! ትሩፋትን ሁሉ በችኮላ ሠርታችሁ በጎይቱን ሃይማኖታችሁን አስከትሏት፡፡ ለነፍሳችሁ እንጂ ለሆዳችሁ አትገዙ፡፡ ሁላችሁ ወንድማማች ሁኑ፡፡ እርስ በርሳችሁም ተፋቀሩ፤ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ፍቅር ኀጢአትን ያጠፋልና፤ የነፍስና የሥጋን ርኲሰት ያነጻልና፡፡ ይህንንም ብትጠብቁ በእውነት ልጆቼ ናችሁ፡፡ የሕይወትንም ፍሬ የምታፈሩ ትሆናላችሁ፡፡ ወደ እግዚአብሔር ፊት በክብር ትደርሳላችሁ፤…

 

ልጆቼ ሆይ! ሰላም ለእናንተ ይሁን፡፡ እንግዲህ ወዲህ ተሰናበትኳችሁ የእግዚአብሔር ፍቅሩ የክብሩም ባለሟልነት፣ የረዳትነቱም ሀብት ዘወትር ከእኔና ከሁላችሁ ጋር ይኑር ለዘላለም በእውነት ይኑር፡፡” /ገድለ ተክለ ሃይማኖት ዘቀዳሚት ምዕ.54/

 

ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል፡፡ ማንም ከእነዚህ ከተናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ብቻ በደቀ መዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋው አይጠፋበትም፡፡” /ማቴ.10፥40-42/ ብሎ የተናገረውን መለኮታዊ ቃል ኪዳን ኦርቶዶክሳዊ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተቀብላ፤ መጋቢት 24 ፅንሰታቸውን፣ ታኅሣስ 24 ቀን ልደታቸውን፣ ጥር 24ን ሰባረ ዐፅማቸውን /የዕረፍታቸውን ቀን ይዞ በዚሁ ወር 24 ይከበራል ሰባረ ዐፅማቸው ከላይ እንደተገለጸው በጥር 4 ነው፡፡/ በግንቦት 12 ቀን ፍልሰተ ዐፅማቸውን ነሐሴ 24 ቀን ዕረፍታቸውን በትላቅ ደስታ ታከብራለች፡፡ ጸሎታቸውና በረከታቸው ረድኤታቸውና ምልጃቸው በመላው ሕዝበ ክርስቲያንና በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ሁሉ አድሮ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

 

አርኬ፡-

ሰላም እብል እንበለ አርምሞ በጽዋዔ፡፡ ኪያከ አበ ወኪያከ ረዳኤ፡፡ ተክለ ሃይማኖት መዋዒ እንዘ ትጸንሕ ተስፋ ትንሣኤ፡፡ አጽናዕከ ለቀዊም አእጋረ ክልኤ፡፡ ወእምስቴ ማይ አሕረምከ ጒርዔ፡፡


አሸናፊ የሆንህ ተክለ ሃይማኖት! አባት አንተን ረዳት፥ አንተን ያለዝምታ በጥሪ ሰላም እላለሁ፡፡ የትንሣኤ ተስፋን ስትጠብቅ፤ ሁለት እግሮችን ለቊመት አጸናህ፤ ጒሮሮህንም ውኃ ከመጠጣት አረምኽ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- መለከት መጽሔት 18ኛ ዓመት ቁጥር 9