ytenaten 058

አምስቱ እጩ ፓትርያርኮች ታወቁ

የካቲት 19 ቀን 2005 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ


ስድስተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ÷ አስመራጭ ኮሚቴ ዛሬ የካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም በሰጠው መግለጫ÷ አምስቱ እጩ ፓትርያርኮችን ይፋ አደረገ፡፡

ytenaten  058ዛሬ ከስዓት በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት፣ እንዲሁም ከልዩ ልዩ የሚዲያ አካላት የተወከሉ ጋዜጠኞች በተገኙበት በተሰጠው መግለጫ ላይ፡-ብፁዕ አቡነ ማትያስ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ የምዕራብና ደቡብ አዲስ አበባ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ለፓትርያርክነት እጩ ሆነው መቅረባቸው ተገልጧል፡፡

 

በብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አማካኝነት የቀረበው መግለጫ “መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን በዕጩነት ከቀረቡት ብፁዓን አባቶች መካከል ለመንጋው እረኛ እግዚአብሔር አምላክ እንዲሰጠን ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ በጾምና በጸሎት ፈጣሪያቸውን እንዲጠይቁ” አሳስቧል፡፡ ከመግለጫው በኋላ ከጋዜጠኞች ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቷል፡፡