በዝቋላ ገዳም የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት ተግባራዊ ሊደረግ ነው፡፡

ሐምሌ 24 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስ


ለዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት ለመተግበር ስምምነት ላይ መደረሱ ተገለጸ፡፡

 

በገዳሙ በቅርቡ ከፍተኛ የደን ቃጠሎ ተከስቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ገዳሙን ለመርዳት በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የሚገኙ ምእመናን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ምእመናንን በማስተባበር ከ600,000.00 ብር /ስድስት መቶ ሺህ ብር/ በላይ ለማሰባሰብ መቻሉን የማኅበሩ ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ አብዛኛው በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል አስተባባሪነት በአሜሪካ የሚገኙ የማኅበረ በዓለወልድ እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ያሰባሰቡት መሆኑ ታውቋል፡፡

የተገኘውን እርደታ ወደ ተግባር ለመለወጥ በታቀደው መሠረት “ለገዳሙ ቋሚ ፕሮጀክት እንደሚያስፈልገው ስለታመነበት ቦታው ድረስ ባሙያዎች በመላክ የዳሰሳ ጥት የተደረገ ሲሆን ከገዳሙ ሓላፊዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይቱም ለገዳሙ ትልቅ ጥቅም የሚሰጠው የትራክተር ግዢ ቢሆንም ለጊዜው የተሰበሰበው ገንዘብ ይህንን ለማስፈጸም የማይበቃ በመሆኑ ከዚህ በፊት ተጀምሮ የነበረው የወተት ላም እርባታ ፕሮጀክት እንዲተገበር ስምምነት ላይ ተደርሷል” በማለት የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡ በስምምነቱ መሠረት የማኅበሩ የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ፕሮጀክቱን እንደሚያስፈጽም ተናግረዋል፡፡

 

የገዳሙ ደን በተቃጠለበት ወቅት የቀለብ እጥረት በመከሰቱ ማኅበሩ ምእመናንን በማስተባበር 50 ኩንታል ስንዴ 20 ኩንታል ጤፍ፣ 40 ሺህ ብር የሚገመት መጠጥ ውኃ፣ በሶ፣ ስኳር፣ ዳቦ ድጋፍ ማድረጉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የወሰነው ውሳኔ ለማኅበሩ መድረሱ ተገለጸ

ሐምሌ 23ቀን 2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ


የ2004 ዓ.ም. የግንቦቱ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን የወሰነው ውሳኔ   በደብዳቤ የተገለጸ መሆኑን የማኅበሩ ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፤ የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት ለብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በጻፉት ደብዳቤ ማኅበሩ ለብፁዕነታቸው ተጠሪ እንዲሆን በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መወሰኑን ጠቅሰው ከማኅበሩ እድገት ጋር አብሮ ሊሄድ እንዲችል የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አስጠንተው ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል፡፡

 

ቅዱስነታቸው በቁጥር 451/275/2004 በቀን 13/11/2004 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ “ማኅበረ ቅዱሳን ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ተለይቶ የራሱ የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ተጠንቶ እስኪወጣለት ድረስ ተጠሪነቱ ለብፁዕነትዎ ሆኖ ሲሠራ እንዲቆይ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ተወስኗል፡፡” በማለት ያስታወሱት ቅዱስ ፓትርያርኩ መተዳደሪያ ደንቡን እንዲያጠኑ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ የተመረጡትን የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስም ዝርዝር ጠቅሰዋል፡፡በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፤ ጌዴኦና አማሮ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ገሪማ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ሓላፊ ፤የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት የክብር ፕሬዚዳንት ቢሮ ዋና ጸሐፊና የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ብፁዕ አቡነ ያሬድ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ የሰዋሰወ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ሓላፊ፤ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ ሐድያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት እና የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ፤ ከሕግ ባለሙያዎችና ከማኅበረ ቅዱሳን አባላት ጋር በመሆን መተዳደሪያ ደንቡን አስጠንተው ለጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲያቀርቡ ገልጸዋል፡፡

 

ማኅበረ ቅዱሳን ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ወጥቶ ለጠቅላይ  ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ  ተጠሪ እንዲሆን  በግንቦቱ ርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የተወሰነ ሲሆን በዚሁ ወቅት ቅዱስ ሲኖዶስ ስለማኅበሩ በሰጠው አስተያየት “ማኅበረ ቅዱሳን የመሥራት አቅሙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰና በቤተ ክርስቲያኒቱ እየሠራ ባለው ሥራ ሁሉ አብተ ክርስቲያናትንና ገዳማትን በስፋት እየጠቀመ ያለ በምሁራን የታቀፈ፤ ሁለንተናዊ ዝግጅት ያለው ማኅበር ስለሆነና ብዙ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ የሚገኝ በመሆኑ እራሱን የቻለ ድርጅታዊ መዋቅር ሊዘረጋለት ይገባል” ማለቱ ይታወሳል፡፡

1

“ዝክረ ቅዱስ ቂርቆስ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መንፈሳዊ መርሐ ግብር ተጠናቀቀ፡፡


ሐምሌ 17 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

1በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ያዘጋጀው መርሐ ግብር ከሐምሌ 12 እስከ ሐምሌ 15 ቀን ተካሄደ፡፡ ዝግጅቱ በሁለት ዐበይት ክፍሎች ተከፍሎ የተካሄደ ሲሆን፡- ይህም ከመክፈቻው ሐምሌ 12-14 በዐውደ ርዕይ፣ እንዲሁም ሐምሌ 15 ቀን 12 ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተሳተፉበት መንፈሳዊ መርሐ ግብር የቀረበበት መሆኑ ታውቋል፡፡

 

ለ3 ቀናት የቆየውን ዐውደ ርዕይ በጸሎት የከፈቱት የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን  አስተዳዳሪ መልአከ ገነት አባ ኀይለ ማርያም መንገሻ  ዐውደ ርዕዩን በጸሎት ከከፈቱ በኋላ በሰጡት አስተያየት በዕድሜ ሕፃናት የሆኑት ልጆች ባዘጋጁት መርሐ ግብር ከፍተኛ ደስታና ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸው፡- “የዛሬ አበባ የነገ ፍሬ የሆኑ ሕፃናት ልጆቻችንን በደንብ ልንንከባከባቸው ይገባናል፡፡ ይህንንም ካደረግን በመጪው ጊዜ ቤተ ክርስቲያንን የሚረከብ ትውልድ በብዛት ብቻ ሳይሆን በጥራትም እናፈራለን፤ ይህም ታላቅ ተስፋችን ነው፡፡” ብለዋል፡፡ መልአከ ገነት አባ ኀይለ ማርያም በማጠቃለያ መልእክታቸው “የአድባራት አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የምንገኝ መሪጌቶችና አገልጋዮች በሙሉ ለሰንበት ትምህርት ቤት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለብን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን የነገዋን ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ፈተና ውስጥ እንደሚገባ ልንረዳ ይገባናል” ብለዋል፡፡

 

5“ሰንበት ትምህርት ቤታችን ከዚህ ቀደም የተለያዩ ዐውደ ርዕዮችን ያዘጋጀ ሲሆን ሕፃናትን በተመለከተ ግን ይህ ዐውደ ርዕይ የመጀመሪያው ነው፡፡ ሕፃናትን የተመለከተ ዐውደ ርዕይ እንድናቀርብ የተፈለገበት ዋነኛው ምክንያት ተገቢውን ትኩረት ለሕፃናት እንዲሰጥ ለመቀስቀስ ነው፡፡” በማለት ዐውደ ርዕዩ በሕፃናት ዙሪያ እንዲከናወን ምክንያት ስለሆነው ሁኔታ ያስረዳው ወጣት ዮሐንስ መረቀኝ የደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤት ምክትል ሰብሳቢ ነው፡፡

 

“በቀደምት ኢትዮጵያውያን ወላጆቻችን ዘንድ እንደ ልምድ ተይዞ የነበረው ልጆችን በሕፃንነት እድሜአቸው ወደ አብነት ትምህርት ቤት የመላክ ሁኔታ አሁን አሁን እየተቀየረ÷ በዘመናዊ ትምህርት ብቻ እንዲማሩ ማድረግ  ‘ባሕል’ እየሆነ የመጣበት ጊዜ ላይ በደረስንበት በዚህ ወቅት ሕፃናት ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን፣ ትምህርተ ሃይማኖትን፣ ጸሎቱንና የመሳሰለውን እንዲማሩና እንዲያውቁ የማስቻል ሓላፊነት ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ወላጆች ልንወጣ ይገባናል፡፡በዐውደ ርዕዩ ላይ የተካተቱት ልዩ ልዩ ክፍሎች ሕፃናት በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ተስፋ ለማመላከት ታስበው የተዘጋጁ ናቸው” በማለት ወጣት ዮሐንስ አስረድቷል፡፡

 

25 የሚደርሱ ሕፃናት በገላጭነት የተሳተፉበት ዐውደ ርዕዩ በ8 ልዩ ልዩ ክፍሎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን በዋነኝነት ሕጻናት ሊቃውንት፣ ሕጻናት ሰማዕታት፣ ሕጻናት በመጽሐፍ ቅዱስ፣ ሕጻናትና ሥራዎቻቸው ፣ ሕጻናትና ጥፋታቸው፣ እንዲሁም ለወላጆች የሚሉና መሰል ሌሎች ክፍሎች የተካተቱበት ነበር፡፡

 

በመዝጊያ መርሐ ግብሩ ላይ በደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ሰንበት ትምህርት ቤት አማካኝነት “ቁጥሮች ለሕፃናት” እንዲሁም 12ቱም ሰንበት ትምህርት ቤቶች በጋራ የተሳተፉበት “ድምፀ ሕፃናት” በሚል ርዕስ የተዘጋጁ የኅትመት ውጤቶች ተመርቀው ለአንባብያን ቀርበዋል፡፡

ec_members

አውሮፓ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤውን አካሄደ

ሐምሌ 13 ቀን 2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዶ/ር መርሻ አለኸኝ


  • የማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት እና የአውሮፓ ማእከል 12ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል በስውድን ተከበረ።

በማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል ጠቅላላ ጉባኤውን ከሰኔ 29 እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም. በሀገረ ስዊድን ስቶክሆልም ከተማ አካሄደ። ከመላው አውሮፓ የተሰባሰቡ ec_membersየማኅበሩ አባላት፣ በስዊድን የተለያዩ ከተሞች የሚያገለግሉ ካህናትና ምእመናን በተሳተፉበት በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ የማእከሉ የ2004 ዓ.ም. የአገልግሎት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል። በውይይቱም ማእከሉ በአገልግሎት ዘመኑ አጠናክሮ የሰጣቸውን አገልግሎቶች በቀጣዩ ዓመትም አጠናክሮ እንዲቀጥልባቸው ሊፈጽማቸው ያቀዳቸው ነገር ግን በልዩ ልዩ ምክንያት መፈጸም ያልቻላቸውን ወይም ከታቀደው በታች ያከናወናቸውን አገልግሎቶች በሚቀጥለው ዓመት እንዲፈጽማቸው ውሳኔ አሳልፏል።

 

ማኅበረ ቅዱሳን በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ በተለይም በሬድዮ እየሰጠ ያለውን ሰፊ አገልግሎት ለመደገፍ ማእከሉ ባቋቋመው የሬድዮ ቤተሰብ አማካይነት እያደረገ ስላለው ድጋፍና ቀጣይ ሂደትም ተወያይቶ ጠቃሚ ውሳኔዎችን አሳልፏል። ከዚህም ጋር በዋናው ማእከል እየተተገበረ ያለው የስብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜና ዝርዝር ተግባራት መሠረት ይፈጽም ዘንድ ማእከሉ ባቋቋመው የድጋፍ ሰጪ አስተባባሪ ቡድን አማካይነት በመስጠት ላይ ስላለው ድጋፍ ሪፖርት ቀርቦ ጉባኤው ሰፊ ውይይት በማድረግ ልዩ ልዩ የማሻሻያ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

 

ጉባኤው ማኀበረ ቅዱሳን በቅዱሳት መካናትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ድጋፍ ገዳማት ከሚያመርቷቸው ምርቶች የአውሮፓmk_eu_12th_anniversary ምእመናን ተጠቃሚ በሚሆኑበት ሁኔታ ላይም ተወያይቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ለተፈጻሚነታቸው በማእከሉ ስር ላለው ቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷል። የጉባኤውን ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሌላው አጀንዳ “የአውሮፓ ማእከል አባላት የአገልግሎት ሱታፌ ከማኀበረ ቅዱሳን ተልእኮ አንጻር” በሚል ርእስ የቀረበው ጥናት ነበር። በማእከሉ ሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ በተቋቋመው ቡድን ተዘጋጅቶ የቀረበው ይህ ጥናት በሁሉም የአውሮፓ ሀገራት የሚገኙ አባላት በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ሥር ታቅፈው በመስጠት ላይ ያሉትን አገልግሎት የዳሰሰ፣ ጥንካሬዎችንና ድክመቶችን ነቅሶ ያወጣ፣ ወደፊት ሊደረግ የሚገባውን ያመላከተ ሰፊ ጥናት ነበር። ጉባኤው በጥናቱ ላይ ሰፊና ሞቅ ያለ ውይይት አድርጎ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

 

ጉባኤው ከዋናው ማእከል የተላከለትን ሪፖርትና መልእክት በተወካዩ አማካይነት በማድመጥ ውይይት አድርጓል። ጉባኤው የማኀበራችንን 20ኛ ዓመት እንዲሁም የአውሮፓ ማዕከልን 12ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ማእከሉ በተመሠረተበት ሀገር በስዊድን በደመቀ ሁኔታ አክብሯል።

 

ga_2004_participantsበመጨረሻም ጉባኤው በቀረበለት የቀጣዩ የ2005 ዓ.ም. የአገልግሎት ዘመን ዕቅድ ላይ ተወያይቶ የማሻሻያ ዐሳቦችን በመስጠት ካጸደቀ በኋላ ማእከሉን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚመራ አዲስ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤ መርጦ የጉባኤው ፍጻሜ ሆኗል። ማእከሉ ስምንት የግንኙነት ጣቢያዎች እና አምስት ቀጠና ማእከላት ያሉት ሲሆን በስዊድን ቀጠና ማእከል የተዘጋጀው የዘንድሮው ጉባኤ የተሳካ እንደነበር የጉባኤው ተሳታፊዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ቀጠና ማእከሉ ለጉባኤው መሳካት አስተዋጽዖ ያደረጉትን አባላትና ምእመናን እንዲሁም ተቋማት በተለይ ጉባኤው በተመቼ ሁኔታ ይካሄድ ዘንድ መሰብሰቢያ አዳራሽና የተሳታፊዎችን ማረፊያ ቤት ከሙሉ አገልግሎት ጋር በነጻ የሰጠውን በብሬድንግ የስዊድን ቤተ ክርስቲያን አመስግኗል።

 

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን።

hitsanat

ልዩ የሕፃናት መርሐ ግብር ተዘጋጀ

ሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም.

በፍጹም ዓለማየሁ

hitsanat

በ12 የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የጋራ ጥምረት እና በአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት አዘጋጅነት ለሕፃናት የሚሆን መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡ መርሐ ግብሩ ከሐምሌ 12-15/2004 ዓ.ም. ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በሦስቱ የመጀመሪያ ቀናት “ዝክረ ቅዱሳን ሕፃናት በልሣነ ሕፃናት” በሚል መሪ ቃል በአስተናጋጅ ሰንበት ትምህርት ቤት ሕፃናት የተዘጋጀ ዐውደ ርዕይ ይቀርባል፡፡ ከመርሐ ግብሩ አስተባባሪዎች እንደተረዳነው ሐሙስ ሐምሌ 12 ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት የሚከፈተው ይህ ዐውደ ርዕይ የሕፃናቱን የእደ ጥበብ ውጤቶች ጨምሮ 8 ክፍሎች ይኖሩታል፡፡

በተጨማሪም በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ሐምሌ 15 ዕለተ እሑድ ከቀኑ 6፡00 ጀምሮ በሚካሄደው “ዝክረ ቅዱስ ቂርቆስ ወሕፃናት” በተሰኘው የሕፃናት ጉባኤ፣ በመርሐ ግብሩ ተሳታፊ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሕፃናት የተዘጋጀ ወረብ፣ መንፈሳዊ ቅኔ፣ የኪነ ጥበብ ፍሬዎች በተጨማሪም በሕፃናቱ የተዘጋጀ ስለ ቅዱስ ቂርቆስ ተራኪ የሆነ ፊልም የሚቀርብ ሲሆን በሥዕል የተደገፈ የሕፃናት መጽሐፍ በዕለቱ ይመረቃል፡፡ በዕለቱም ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዕለቱም ሕፃናት ልጆችዎን ይዘው በመርሐ ግብሩ ላይ እንዲገኙ የመርሐ ግብሩ አስተባባሪዎች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

«ወደ እኔ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ማቴ. 11፥28

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

እግዚአብሔር ሁሉን አዘጋጅቶ በመጨረሻ ለፈጠረው ለሰው ልጅ ያላደረገለትና ያልሰጠው ነገር የለም፡፡ ሁሉን ከማከናወኑ ጋር የሰው ልጅ የሚያስፈልገውን ነገር በአባትነቱ ያውቃልና የሰው ልጅ በባሕርይው የሚያሻውን ነገር የሚያበጃጃት ገነት፣ የምትመቸውን ረዳት፣ የሚገዛቸውን ፍጥረታት ሁሉ ለሰው እንደሚገባ ሰጥቶታል፡፡ ከእነዚህ ተቆጥረው ከማያልቁ ሥጦታዎች አንዱ ደግሞ ዕረፍት ነው፡፡ «እግዚአብሔር የተናገረው ይህ ነው፤ ነገ ዕረፍት ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሰንበት ነው» ተብሎ እንደተጻፈ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ዕረፍት እንደሚያስፈልግ አውቆ የሰንበትን ቀን ሰጥቶአል /ዘጸ. 16.23/፡፡

«ሠርዐ ለነ ሰንበተ ለዕረፍተ ዚኣነ ፍስሓ ወሰላም ለእለ አመነ፤ ሰንበትን ለእኛ ዕረፍት ይሆን ዘንድ ሠራልን ደስታና ሰላም ለምናምን ሁሉ» እያልን በማለዳ ማመስገናችንም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡ በባሕርይው ድካም የሌለበትና ዕረፍት የማይሻው አምላክ «ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ሊያደርገው ከፈጠረው ሥራ ሁሉ ዐርፎአልና» ተብሎ የተነገረው ከትንቢታዊ ትርጓሜው ባሻገር ሰንበት እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ዕረፍት እንደሚያስፈልገው አውቆ ያዘጋጃት ማረፊያ መሆኗንና በተግባር «ዐረፈ» መባልን ፈጽሞ መስጠቱን ያስረዳል፡፡ ከሰውም አልፎ የምትታረስ መሬት እንኳን ዕረፍት እንድታደርግ ማዘዙም ለፍጥረቱ ዕረፍት የሚያስብ አምላክ ያሰኘዋል፡፡ እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል፡፡ ወደ ዕረፍቱ የገባ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እርሱ ደግሞ ከሥራው ዐርፎአልና /ዕብ. 4.9/፡፡

 

የዕረፍት ጽንሰ አሳብ ሥራን ሠርቶ ከማረፍ ጋር ብቻ የተያያዘ አለመሆኑ ግልጥ ነው፡፡ ሰው ሥጋዊ ብቻም ሳይሆን መንፈሳዊም ነው፡፡ ሰው የተሰኘውም በባሕርያተ ሥጋ ብቻ ሳይሆን በባሕርያተ ነፍስም ነው፤ ስለዚህ ዕረፍተ ሥጋ ብቻ ሳይሆን ዕረፍተ ነፍስም ያስፈልገዋል፡፡ ሥጋዊ ዕረፍት የሰው ልጅ ከሥጋ ድካሙ የሚያርፈው ሲሆን መንፈሳዊ ዕረፍት ደግሞ ከኅሊና ውጥረት፣ ከጭንቀት በኃጢአት ምክንያት ከሚመጣ መታወክ የሚታረፍና ውስጣዊ ሰላም የሚገኝበት ነው፡፡

ዕረፍት በመንፈሳዊ መነፅርና በሥጋዊ መነፅር ሲታይ የተለያየ ትርጉም አለው፡፡ እግዚአብሔርን ባለማወቅ ለሚኖሩ ሰዎች ዕረፍት መስሎ የሚታያቸው ለመንፈሳውያን ድካም ነው፡፡ ክርስቲያኖች ዕረፍት ነው የሚሉት ደግሞ ለሌሎች ድካም ሆኖ ይሰማቸዋል፡፡

አምላካችን «ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ብሎ ሲናገር የሚያሳርፈን ዕረፍት ሥጋዊ ዕረፍትን አይደለም፡፡ «ወደ እኔ ኑ» የሚለውን ጥሪ የተቀበሉና የተከተሉት ቅዱሳንም ከእርሱ ያገኙት መንፈሳዊ ዕረፍትን እንጂ ሥጋዊ ዕረፍትን አልነበረም፡፡ ስለዚህም «በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሥጋችን ዕረፍት አልነበረውም» በማለት ተናግረዋል /2ቆሮ. 7.5/፡፡ በእርግጥም እርሱን የተከተሉ ሁሉ ሥጋዊ ዕረፍትን አላገኙም፤ በነፍሳቸው ግን ፍፁም ዕረፍትን አግኝተዋል፡፡ በነፍሳቸው ያገኙት ዕረፍትም በሥጋ ማረፍን እንዳይፈልጉ አድርጓቸው «በመከራ፣ በችግር በጭንቀት፣ በመገረፍ በወኅኒ፣ በሁከት፣ በድካም፣ እንቅልፍ በማጣት፣ በመጦም» ውስጥ እየኖሩ ተጋድሎአቸውን ፈጽመዋል/2ቆሮ. 6.5/፡፡

እግዚአብሔር «አሳርፋችኋለሁ» ያለው ዕረፍት ሰነፉ ባለጠጋ ለነፍሱ ሊሰጣት የወደደውን ዕረፍትም አይደለም፡፡ ይህ ሰነፍ ሰው እርሻው ፍሬያማ ስትሆንለት ጎተራውን አፍርሶ ሌላ ጎተራ ሊሠራ አቀደ፤ ለነፍሱም እንዲህ ሊላት ወደደ፤ «አንቺ ነፍሴ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ ብዪ ጠጪ፡፡» ይሁንና እግዚአብሔር በዚያች ሌሊት ነፍሱ እንደምትወሰድ ነገረው /ሉቃ.12.16-20/፡፡ ይህ ሰው የተመኘው ዕረፍት ከመብል ከመጠጥ፣ ከተከማቸ ሀብት የሚገኝን ዕረፍት ነበር፡፡ ስለዚህም በድንገት ተወሰደ «ያርፍ ዘንድ ተስፋ ባደረገ ጊዜ እበላለሁ፣      እጠጣለሁ፣ ባለ ጊዜ እንግዲህስ ደስ ይለኛል ገንዘብም በቃኝ ባለ ጊዜ የሚሞትባትን ቀን አያውቅም ገንዘቡን ሁሉ ለባዕድ ትቶ እሱ ይሞታል» የተባለው በእርሱ ተፈጸመ /ሲራ.11.19/፡፡ መብል፣ መጠጥ፣ የተከማቸ ሀብት ፍጹም ዕረፍትን አይሰጥም፡፡ እንዲያው በተቃራኒው ዕረፍትን ሲነሣም እናገኘዋለን፡፡ ሀብትን፣ መብልና መጠጥን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ይዞት ለሚኖር ሰው ግን በጎ ሥራን ሠርቶበት ዕረፍትን ሊያገኝበት ይችላል፡፡

በሃይማኖት መንገድ የሚኖሩ ክርስቲያኖች በተገቢው አረማመድ እስከሄዱ ድረስ የነፍስን ዕረፍት ያገኛሉ፡፡ «እግዚአብሔር እንዲህ ይላል- በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርስዋም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፡፡» የሚለው የጥሪ ቃል እዚህ ላይ ሊነሣ ይችላል /ኤር.6.16/፡፡ የክርስትና ሃይማኖት መንገድም የነፍስ ዕረፍት የሚገኝባት መሆኗ ርትዕት /የቀናች/ መሆኗን ያስረዳል፡፡ በነፍስ ዕረፍትን በማግኘት ፈንታ ሥጋዊ ደስታ የሚገኝበት መንገድ የሃይማኖት መንገድ አይደለም፡፡ ሃይማኖት በሥጋ እየደከሙ በነፍስ የሚያርፉበት፤ መከራን እየታገሡ፣ ሥቃይን እየተቀበሉ የልብ ዕረፍትን የሚያገኙበት ነው፡፡ በመከራም እያሉ እንኳን «ወደ ወጥመድ አገባኸን፤ በጀርባችንም መከራን አኖርህ፤ በራሳችን ላይ ሰውን አስረገጥኸን፤ በእሳትና በውኃ መካከል አለፍን፤ ወደ ዕረፍትም አወጣኸን» እያሉ ከቅዱሳን ጋር በማመስገን ከመከራ ባሻገር ያለውን የነፍስ ዕረፍት የሚቀበሉበት ሕይወት ነው /መዝ.65.11-12/፡፡

ለሰው ልጅ በተለይም ለክርስቲያን በእግዚአብሔር ዘንድ ከሚያገኘው ዕረፍት የሚልቅ ዕረፍት የትም አይገኝለትም፡፡ ቅዱስ አውግስጢኖስ የተባለ አባት «በአንተ ዕረፍት እስካላገኙ ድረስ ልቦቻችን ዕረፍት አይኖራቸውም» ብሎ እንደተናገረው «ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ» ወደ ሚለን አምላክ እስካልተጠጋን ድረስ ልባችን ዕረፍትን አያገኝም፡፡ ይኸው አባት በሌላ ጊዜም «ጌታ ሆይ ለራስህ ብለህ ስለፈጠርኸን ልባችን በአንተ ላይ እስኪያርፍ ድረስ ይባክናል» ብሎ ተናግሯል፡፡ ይህንን ጥሪ መቀበልም ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መቅረብ፣ እንደ ሕጉ እንደ ትእዛዙ ለመኖር መፍቀድ ነው፡፡ «እኔም አሳርፋችኋለሁ» ያለ አምላክ የከበደ ሸክማችንን አውርዶ የሚያሸክመን ልዝብ ቀንበርና ቀሊል ሸክም ደገኛይቱ ሕገ ወንጌልን አዘጋጅቶልናል፡፡ ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን የራቀ፣ ከሥጋ ወደሙ ከደጀ ሰላሙ የተለየ ሰው በቤቱ የሚገኘውን ዕረፍት በየትም ሥፍራ ሊያገኘው አይቻለውም፡፡ በኖኅ መርከብ ውስጥ የነበረችው ርግብ ከመርከቡ ወጥታ ማረፊያ እንዳጣች ሁሉ እንደርግብ የዋኀን የሆኑ ምእመናንም ከመርከቢቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተለይተው ዕረፍት አይኖራቸውም፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመብላት፣ በመጠጣት፣ በመተኛት የማይገኝ በመራብ በመጠማት እንቅልፍ በማጣትና በመንገላታት የማይታጣ ፍጹም ዕረፍት አለ፡፡

«እኔም አሳርፋችኋለሁ!» የሚለው ቃል የሚነግረን ሌላው ዕረፍት ደግሞ ሁላችን የምንናፍቃትን ተስፋ የምናደርጋት ዘላለማዊት መንግሥቱን ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰማያዊት መንግሥቱን «ዕረፍት» ብሎ ይጠራታል፡፡ በቀደመው ዘመን እሥራኤል ከባርነት ወጥተው እንዲወርሱአት የተዘጋጀችው ከነዓን ዕረፍት ተብላ ትጠራ ነበር፡፡ የተፈታተኑኝ አባቶቻችሁ ፈተኑኝ፤ ሥራዬንም አዩ፤ ያቺን ትውልድ አርባ ዓመት ተቈጥቻት ነበር፤ ሁልጊዜ ልባቸው ይስ ታል፤ እነርሱም መንገዴን አላወቁም አልሁ፡፡ ወደ ዕረፍቴም እንዳይገቡ በቁጣዬ ማልሁ» በማለት እንደተናገረ /መዝ. 94.9-11/

እኛ ክርስቲያኖች የምንናፍቃት ከነዓን ደግሞ መንግሥተ ሰማያት ናት፡፡ እሥራኤል ፋሲካን አድርገው ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጥተው ባሕረ ኤርትራን ተሻግረው አርባ ዓመት ተጉዘው ከነዓንን /በቁጥር ጥቂቶች ቢሆኑም/ እንደወረሱ እኛም ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ ወጥተን ባሕረ  ኃጢአትን ዘመነ ፍዳን ተሻግረን «በፋሲካችን ክርስቶስ» መከራና ሞት ነጻ ወጥተን በዚህች ዓለም ተጉዘን የምንወርሳት ከነዓን ኢየሩሳሌም ሰማያዊት /መንግሥተ ሰማያት/ ናት፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን በላከው ክታቡ እሥራኤል ሕጉን በመተላለፋቸው ወደ ቀደመችዋ ዕረፍት ወደ ከነዓን ስላለመግባታቸው ከዘረዘረ በኋላ «እንግዲህ እንደዚያ እንደ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ፤ ወደዚያ ዕረፍት ለመግባት እንትጋ» በማለት አሳስ ቦናል /ዕብ.4.11/፡፡ በእርግጥም ዕረፍት መንግሥተ ሰማያትን ለማግኘት፣ «ወደ ዕረፍቱም አትገቡም» ከመባል ለመዳን መጠንቀቅና መትጋት ይገባናል፡፡ እሥራኤል ወደ ከነዓን ባይገቡ በሞተ ወልደ እግዚአብሔር ወደ ገነት ገብተዋል፤ እኛ ግን ወደ መንግሥተ ሰማያት ባንገባ ቆይተን የምንገባበት ሌላ ዕረፍት  የለምና  ወደ ዕረፍቱ ለመግባት እንትጋ!

ye_mekina_setota

ማኅበረ ቅዱሳን የመኪና ስጦታ ተበረከተለት

ሰኔ 20 ቀን 2004 ዓ.ም.

በእንዳለ ደጀኔ

ማኅበረ ቅዱሳን የጀመረውን ዓለም አቀፍ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት አጠናክሮ መቀጠል እንዲችል የሚያግዘው የመኪና ስጦታ ተበረከተለት፡፡


መኪናውን ለማኅበሩ ያበረከቱት ዶ/ር አንተነህ ወርቁና ዶ/ር ሰላማዊት እጅጉ ሲሆኑ ያዘጋጁትን ስጦታ በዶ/ር ሰላማዊት ወላጅ አባት በአቶ እጅጉ ኤሬሳ አማካኝነት አበርክተዋል፡፡


ye_mekina_setota

የመኪናውን ቁልፍ የተረከቡት የማኅበረ ቅዱሳን ም/ሰብሳቢ አቶ ታደሰ አሰፋ ‹‹ማኅበራችን ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ከዕለት ወደ ዕለት የሚያደር ግለት ነገሮች እየበዙ ነው፡፡ ይህን እንደምክንያት ልናየው እንችላለን ስለ ሁሉም ነገር ስጦታውን ያበረከቱትን ወንድምና እታችንን እናመሰግናለን ብለዋል፡፡›› አቶ ታደሰ አክለውም ‹‹የግንቦቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን ወሳኝ መሆኑን የተረጋገጠበት ነው፡፡ የጎደለንን ነገር ስለሞላችሁልን እግዚአብሔር ይስጥልን›› ብለዋል፡፡


አቶ እጅጉ ኤሬሳ ስጦታውን በሰጡበት ወቅት ‹ልጆቼ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ዛሬ አይደለም የጀመሩት ፡፡ የጀመሩትን አገልግሎት እስከ ፍጻሜ እግዚአብሔር እንዲያጸናቸው በጸሎታችሁ አትርሱብኝ፡፡›› በማለት አሳስበዋል፡፡


በማኅበሩ ጽ/ቤት በተካሔደው የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የማኅበሩ የሥራ አመራር ጉባኤ አባላት፣ የሥራ አስፈጻሚ ጉባኤና የዶ/ር አንተነህ እህት ወ/ሮ ዘላለም ወርቁ ተገኝተዋል፡፡ የማኅበሩን አገልግሎት ለማገዝ በርካታ በጎ አድራጊዎች በተለያየ ጊዜያት ስጦታ ያበረክቱ ሲሆን ከዚህ ቀደም የአቶ ግርማ ዋቄ ባለቤት ወ/ሮ ውብዓለም ገብሬ የቤት መኪናቸውን ማበርከታቸው የሚታወስ ነው፡፡


ዶ/ር አንተነህና ዶ/ር ሰላማዊት ከጎንደር ዩኒቨርስቲ ተመርቀው ኑሮአቸውን በማሊ ያደረጉ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳን በቅዱሳን ገዳማትና አድባራት በሚያበረክተው አገልግሎት በጥሩ አርአያነት እያገለገሉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

theology1

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ 397 ደቀ መዛሙርትን አስመረቀ


በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቀን በማታና በርቀት ትምህርት ያስተማራቸውን ደቀመዛሙርት እሑድ ሰኔ 10 ቀን 2004 ዓ.ም ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት አስመረቀ፡፡

theology1

ኮሌጁ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሆኖ ከተቋቋመበት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ ለቅድስት ቤተክስቲያንና ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አገልግሎት ያበረከቱ ደቀመዛሙርትን አሰልጥኖ ማውጣቱን የኮሌጁ ምክትል ዲን ዶክተር አባ ኃይለማርያም መለስ ለመካነድራችን ሪፖርተር በሰጡት መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ዶክተር አባ ኃይለማርያም በዚሁ መግለጫቸው፡-“የዘንድሮውን የምርቃት መርሐ ግብር ልዩ ከሚያደርጉት ነጥቦች አንዱ ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ መልኩ በቁጥር ከፍ ያሉ ሴት ተማሪዎች መመረቃቸው እና አብዛኛዎቹም የመአረግ ተመራቂዎች መሆናቸው ነው፡፡” ብለዋል፡፡

theologyከመንፈሳዊ ኮሌጁ የሬጅስትራር ጽ/ቤት ባገኘነው መረጃ በዚህ ዓመት በድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ (P.G.D) 16፣ በዲግሪ 95፣በዲፕሎማ 72፣ በግእዝ ቋንቋ 14፣ እንዲሁም 200 ተማሪዎች በሰርተፍኬት መርሐ ግብር ተመርቀዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚህ ዓመት በደቀ መዝሙር ኢያሱ ጥጋቡ የተመዘገበው 3.98 ነጥብ በኮሌጁ ታሪክ እስከአሁን ከተመዘገቡት ከፍተኛው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ አካባቢ ራሳቸውን “ጉባኤ አርድዕት” ብለው የሰየሙ ቡድኖች እየተፈጠሩ መሆናቸው ተገለፀ፡፡

ሰኔ 09 ቀን 2004 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ባለፉት ረጅም ዓመታት በርካታ ፈተናዎችን አልፋ የተጓዘች መሆኗ ይታወቃል፡፡ በተለይም ራሳቸውን ተሐድሶ ብለው የሰየሙ ቡድኖች ተመሳስለው ውስጧ በመግባት ውስጥ ለውስጥ ሲያደሟት ቆይተዋል፡፡

የእነዚህ ድብቅ ቡድኖች አካሄድ ለብዙ ጠንካራ ኦርቶዶክሳውያን ግልፅ የነበረ በመሆኑ ላለፉት ተከታታይ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤያት ማንነታቸው ተገልጾ ውግዘት የተላለፈባቸውና በሕግ የሚጠየቁትም በሕግ እንዲጠየቁ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ነገር ግን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተገልጾ ለምዕመናን እንዲደርስ ለማድረግ ሰፊ ሥራ እየተሠራ ባለበት በአሁኑ ወቅት በ25 አባላት መሰራችነት የሚመራ አዲስ ቡድን በመንበረ ፓትርያርክ አካባቢ ብቅ ማለት ጀምሯል፡፡

የቡድኑ ዋና አላማ ነው ተብሎ ከተገለፀው መካከል የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ሥራ ላይ እንዳይውል የሚያደርጉትን ጥፋት መደገፍና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የሆኑ ሊቃነ ጳጳሳትን ከማስፈራራት ጀምሮ ማንኛውንም ጫና በማድረግ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ማድረግ ነው ተብሏል፡፡

የጉባኤ አርድዕት መሪዎችና መስራቾች “ማኅበር ለቤተ ክርስቲያን አያስፈልግም” ብለው ሲሟገቱ የነበሩ ሲሆን ለእነርሱ እስከጠቀማቸው ድረስ “ጉባኤ አርድዕት” ወደ “ማኅበረ አርድዕት” ለመቀየር ሀሳብ ያላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡

ziway abune gorgorios1

ዝክረ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊካሄድ ነው

ሰኔ 09 ቀን 2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደም

የማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ማእከል የማኅበሩን 20ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ምክንያት በማድረግ “ዝክረ አቡነ ጎርጎርዮስ” በሚል ርእስziway abune gorgorios1 የጥናትና የውይይት መድረክ ሰኔ 16 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አዲሱ አዳራሽ አዘጋጅቷል፡፡

የጥናትና ምርምር ማእከሉ ም/ዳይሬክተር አቶ ሰይፉ አበበ መርሐ ግብሩን አስመልክቶ እንደገለጹት “የጥናት መድረኩ ዋና ዓላማ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በሕይወት ዘመናቸው ለቤተ ክርስቲያን ያበረከቱትን አገልግሎት፣ የሕይወት ልምዳቸውን፣ ወጣቱን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በአንድ ዓላማ ለማሰለፍ ያደረጉትን ተጋድሎ እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ እድገት የነበራቸውን ርዕይ የሚዘክር ይሆናል” ብለዋል፡፡

ziway abune gorgoriosበተጨማሪም ለማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት ጉልህ አስተዋጽኦ የነበራቸው አባት በመሆናቸው ማኅበሩ 20ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት ብፁዕነታቸውን መዘከር ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል ላይ ለሚገኙ አገልጋዮችና ደቀ መዛሙርቶቻቸው በተለይም ወጣቶችን የሚያተጋ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡

በጥናት መድረኩ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በዘርፉ የተሰማሩ ተመራማሪዎች፣ ደቀ መዛሙርቶቻቸው ፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላትና ምእመናን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡