የስድስተኛው ፓትርያርክ ቅድመ ምርጫ ሂደቶች

የካቲት 20 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን ከምርጫው በፊት ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባራት በአስመራጭ ኮሚቴው እየተመራ ይገኛል፡፡ ሂደቱንም አስመራጭ ኮሚቴው ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አድባራትና ገዳማት፤ ከቤተ ክርስቲያናት፤ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች፤ ከምእመናን፤ እንዲሁም ከውጭ ሀገራት በመራጭነት የተወከሉ መራጮች ከየካቲት 18 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

 

የካቲት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ መራጮች ከየሀገረ ስብከታቸው በመራጭነት መወከላቸውን የሚገልጽ ማስረጃ በመያዝ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ የተገኙ ሲሆን በአስመራጭ ኮሚቴው በምርጫው ሂደት ላይ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡ መራጮችን በአግባቡ መመዝገብ እንዲቻል በምድብ እና በምድብ በመመደብ ምዝገባውን በማካሔድ የመራጭነት ካርዳቸውን ወስደዋል፡፡

የካቲት 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ሁሉም መራጮች ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት በጠቅላይ ቤተ ክህነት በመገኘት በምርጫው አካሔድ ላይ ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማስቻል በአስመራጭ ኮሚቴው ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡ ማብራሪያውን የሰጡት የአስመራጭ ኮሚቴው ጸሐፊ ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ እና የአስመራጭ ኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት አቶ ባያብል ሙላቴ ናቸው፡፡

 

ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ባስተላለፉት መልእክትም  “ቤተ ክርስቲያንን የሚመሩ አባት ለመምረጥና ምርጫውን ለማካሔድ አደራ ተሸክማችሁ የመጣችሁ በመሆኑ ምርጫውን በራሳችሁ ፈቃድ ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ ሆናችሁ ቤተ ክርስቲንን ሊመሩ ይችላሉ የምትሏቸውን አባት እንድትመርጡ” ብለዋል፡፡ ለመራጮቹም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ውሳኔ የሆነውንና ከአስመራጭ ኮሚቴው የቀረቡለትን አምስቱን ሊቃነ ጳጳሳት ተወያይቶ በእጩነት ለፓትርያርክነት  ለምርጫ ማቅረቡን የሚገልጸው ውሳኔ አንብበዋል፡፡

 

የአስመራጭ ኮሚቴው ሕዝብ ግንኙነት አቶ ባያብል ሙላቴ በሰጡት ሰፋ ያለ ማብራሪያም ”የምርጫውን ካርድ ካልያዛችሁ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት መግባት አትችሉም፡፡ ስለዚህ የምርጫ ካርዱን በጥንቃቄ መያዝ ይገባችኋል፡፡ ቢጠፋም ምትክ አንሰጥም” ያሉ ሲሆን የምርጫ ካርድ የያዙትም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ላይ ተጠቃለው ጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ በመገኘት እነሱን ለማስተናገድ በተመደቡ አገልጋዮች አማካይነት ካርዳቸውንና ማንነታቸውን ከተመዘገበው መዝገብ ላይ በማመሳከር የምርጫ ካርዱን በማስረከብ በተዘጋጀለት ሳጥን ውስጥ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ የምርጫ ወረቀቱን በመቀበል ወደ አዳራሽ ውስጥ እንዲገቡ እንደሚደረግ አብራርተዋል፡፡

 

አቶ ባያብል ሙላቴ ማብራሪያቸውን በመቀጠል “ከጧቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት ከአቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ጋር በመገኘት እንዲሁም ታዛቢዎች በተገኙበት በአቃቤ መንበረ ፓትርያርኩ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል አማካይነት መራጮች ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ” ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ቃለ መሐላው ከተፈጸመ በኋላ ለመምረጥ ለእያንዳንዱ ቃለ መሐላ ለማስገባት እንደማይቻል ያስገነዘቡ ሲሆን “ደክማችሁ እንዳትመለሱ በሰዓቱ እንድትገኙ” በማለት ገልጸዋል፡፡

 

የምርጫ ወረቀቱ ምን እንደሚመስል ለመራጮች በግልጽ በማሳየት አቶ ባያብል ሙላቴ በሰጡት ማብራሪያም የአምስቱም እጩ ፓትርያርኮች ፎቶ ግራፍና ስም ጵጵስና በተሾሙበት ጊዜ ቅደም ተከተል መቀመጡን፤ መራጮችም በሚፈልጉት  እጩ ፓትርያርክ ፊት ለፊት ከፎቶ ግራፋቸው ትይዩ  ባለው ሳጥን መሰል ቦታ ውሰጥ አንድ ጊዜ ብቻ የ ምልክት በማድረግ ወረቀቱን አራት ቦታ በማጠፍ በተዘጋጀው ባለ መስታወት የምርጫ ሳጥን ውስጥ እንዲከትቱ በማሳሰብ ከ ምልክቱ ውጪ የምርጫ ወረቀቱ ላይ ምንም አይነት ምልክት ወይም ጽሑፍ መጻፍ እንደማይፈቀድና ተጽፎ ቢገኝ የምርጫ ወረቀቱ እንደሚሰረዝ  አሳስበዋል፡፡

 

ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ብፁዐን ሊቃነ ጳጳሳት፤ የምርጫው ታዛቢዎችና መራጮች ባሉበት በይፋ ሳጥኑ ተከፍቶ ቆጠራ እንደሚካሔድና ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት አባት እዚያው አዳራሹ ውስጥ ሁሉም ባለበት ፓትርያርክ ሆነው መመረጣቸውን እንደሚያበስሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሁለት አባቶች ተመሳሳይ ድምጽ ቢያገኙ በዕጣ እንደሚለዩ ገልጸዋል፡፡