ማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎቱን በይፋ መጀመሩን አበሰረ
ግንቦት 16 ቀን 2005 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲየን ማኀበረ ቅዱሳን ላለፉት ሃያ ዓመታት በመንፈሳዊ መገናኛ ብዙኃን ሲሰጥ የቆየውን አገልግሎት በማስፋት የቴሌቪዥን ሥርጭት በኦፊሴል መጀመሩን ለምእመናን የሚያበስርበት ጉባኤ ቅዳሜ ግንቦት 17 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል እንደሚያካሂድ ተገለጸ፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በሚሳተፉበት በዚህ ጉባኤ ማኅበሩ ዐቢይ ተልዕኮ አድርጎ ይዞት የተነሣውን የስብከተ ወንጌል አገልሎት ለማሳካት መንፈሳዊ መገናኛ ብዙኃንን እንዴት ሲጠቀም እንደቆየና በዘርፉ አገልግሎቱን ለማጠናከር ያለው ዕቅድ በብሮድ ካስት መገናኛ ብዙኃን የቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎትን ለምን እንደጀመረ፣ ወደፊትም አጠናክሮ ለመቀጠል ያለውን ዕቅድና በአገልግሎቱ ምእመናን ሊኖራቸው ስለሚገባው ተሳትፎ መነሻ የሚሆኑ አሳቦች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተጠቁሟል፡፡
ማኅበሩ ከየካቲት 16 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን ሥርጭት ጣቢያ በየሳምንቱ እሑድ ከረፋዱ 5፡30 እስከ 6፡00 እና ሐሙስ ከጠዋቱ 1 ሰዓት እስከ 1፡30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነትና ትውፊት የሚያስተላልፉ ዝግጅቶችን እንደሚያቀርብ ይታወቃል፡፡
የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት መታሰቢያ በድምቀት ተከበረ
ግንቦት 13 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል “ሕያው ዜማከ ወሕያው ድርሳንከ” በሚል መሪ ቃል ስድስት ኪሎ በሚገኘው የኢትዮጵያ ስብሰባ ማእከል አዳራሽ ግንቦት 11 ቀን 2005 ዓ. ም. በድምቀት ተከብሯል፡፡
ከየአድባራቱና ገዳማት የመጡ ታላላቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ምእመናን የተገኙ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር በሆኑት ዶክተር ውዱ ጣፈጠ በቅዱስ ያሬድ ሕይወት ታሪክና ሥራዎቹ ላይ ያተኮረ ጥናት አቅርበዋል፡፡ ከሊቃውንቱ መካከልም በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኀኔዓለም የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪና የአራቱ ጉባኤያት የመጻሕፍት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ አዲስ የወንጌል ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ ከሊቃውንቱ መካከል የቤተልሔም፤ የቆሜና የአጫበር ዜማዎችን በየተራ ያቀረቡ ሲሆን የመርሐ ግብሩ ልዩ ድምቀት ነበር፡፡
በራስ ዳሸን ተራራ ላይ በችግር ውስጥ የሚገኘው የቅዱስ ያሬድ ገዳምን ለመርዳት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር የተደረገ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ክፍል እጅግ አስቸጋሪና የአንድ ቀን ሙሉ የእግር ጉዞ በማድረግ የሚደረስበትን በበረዶ የተከበበው ገዳም ድረስ በመሄድ ገዳሙ ያለበትን ችግር ለማጥናት ጥረት ማደረጉ ተገልጻል፡፡
በገዳሙ ከ70 በላይ መነኮሳትና መናንያን የሚገኙ ሲሆን ከቦታው ተራራማነት የተነሳ ምእመናን የማይደርስበት ቦታ በመሆኑ ገዳማውያኑ የሚረዳቸው በማጣት የአልባሳት፤ የምግብና የመጠለያ ችግር እንዳጋጠማቸው ተጠቅሷል፡፡ በዚህም መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን ከገዳሙ አቅራቢያ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ደባርቅ ከተማ ላይ ለገዳሙ አገልግሎት የሚውል የአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ከከተማው አስተዳደር በመረከብ ሕንፃ ለመገንባት ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በመጀመሪያው ዙርም 1.5 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ በመገለጹ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ተካሂዷል፡፡
በዕለቱ ከተገኙ ምእመናንም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ቃል የተገባ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል ለሕንፃጻው ማሠሪያ የሚውል ገንዘብ ለመላክ ቃል ገብቷል፡፡ማኅበረ ቅዱሳን ለአክሱም ጽዮን ማርያም ገዳም የብር መቋሚያና ጸናጽል በስጦታ ያበረከተ ሲሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በ2004 ዓ.ም. የተመረቀውና የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚው ዶክተር አምኃ መሸሻ ለቅዱስ ያሬድ ገዳም ሜዳልያውን አበርክቷል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በሰጡት ቃለምእዳን “ከየገዳማቱና አድባራቱ በዓሉን ለማክበር በመካከላችን የተገኙት ሊቃውንት አባቶቻችን የቅዱስ ያሬድን ፈለግ በመከተል ቤተ ክርስቲያን ያለተተኪ እንዳትቀር አገልጋዮችን በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አባቶቻችን የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ ፋብሪካዎች ናቸው” ብለዋል፡፡
በመርሐ ግብሩ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን መዝሙር ክፍል አባላት የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኙ ቀዳሚ ዜማ ዘያሬድ የሊቃውንት ማኅበር ያሬዳዊ ዝማሜና ወረብ አቅርበዋል፡፡
የቅዱስ ያሬድ ሥራዎችን በዩኔስኮ ማስመዝገብ እንደሚገባ ተገለጸ
የቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን አስመልክቶ ማኀበረ ቅዱሳን በግዮን ሆቴል ባዘጋጀውና ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በተገኙበት አውደ ጥናት ላይ የቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ሥራዎቹ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት /UNESCO/ ለማስመዝገብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለጸ፡፡
ቅዳሜ ግንቦት 10 ሙሉ ቀን በተደረገው በዚህ ዐውደ ጥናት ላይ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡባዊ ትግራይ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ ከየአድባባራቱና ገዳማት ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቃለምዕዳን ዐውደ ጥናቱ ተከፍቷል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ በሠጡት ቃለ ምዕዳን ማኅበሩ የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ መታሰቢያ በዓልን ማዘጋጀት በመቻሉ አመስግነው በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ያሬድ የዜማ ትምህርት ከፍተኛ እውቀት ያላቸው አባቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ መምጣቱንና በሀገረ ስብከታቸው ከሚገኙ 1000 ገዳማትና አድባራት ውስጥ በጣም ጥቂት የድጓ መምህራን ብቻ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህም አሳሳቢነቱን ከፍ ስለሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት መደረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ ተወካይ የሆኑት አቶ ወርቅነህ አክሊሉ ባቀረቡት ንግግር “ቅዱስ ያሬድ ወደር ያልተገኘለትና ዓለምን ያስደመመ የዜማ ጥበብ ባለቤት እንደመሆኑ የሥራ ውጤቶቹ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው እሰካለንበት ዘመን ከነውበታቸውና ከነክብራቸው ሊደርሱ ችለዋል፡፡ ተሸናፊነትን ያሸነፈ የትእግስት ተምሳሌት በመሆን አንድን ስጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ተግባር ከዳር ለማድረስ ያለመታከት መሥራትን በማሳየት ለተስፋ ቆራጭ ትውልድ የሕሊና ትንሳኤ አብነት ተደርጎ ሊቆጠር የሚችልና የሚገባውም ታላቅ ሊቅ ነው” በማለት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ድንበር ተሸጋሪነት ሲገልጹ “ቅዱስ ያሬድን ባሰብን ጊዜ የዘመን ውሽንፍር ያልገደባቸው ድርሰቶቹን እንደናስብ ስለሚያደርገን ዛሬም ድረስ በዚህ ሊቅ የሥራ ውጤቶች እንደ ኢትዮጵያዊነታችን እንኮራበታለን፡፡ የሌሎች ሀገሮች ህዝቦችም እንዲያውቁትና ይህ ጥበብ ድንበር ተሻጋሪ እንዲሆን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንሰራለን” ብለዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ አምስት ያህል ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን የቅዱስ ያሬድ ልደቱ፤ እድገቱ፤ የማኅሌታዊና የምናኔ ሕይወቱ በሚል ርዕስ ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡
ዲያቆን ሰሎሞን ወንድሙ በበኩላቸው የቅዱስ ያሬድ ዜና ሕይወቱ በተለያዩ ጸሐፍት ሥራዎች ሲዳሰስ በሚል ርዕስ ባቀረቡት ጥናትም በተለያዩ ጸሐፊያን የልደት ቀኑ፤ የእናትና አባቱ ስም፤ በስጋ ማረፉን ወይም መሰወሩን፤ የመምህራኖቹ ስም፤ . . . ወዘተ የመሳሰሉት ጉዳዮች ወጥነት ኖሯቸው መስተካከል እንደሚገባቸው መረጃ በማጣቀስ አቅርበዋል፡፡
ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ኦርቶዶክሳዊ ስብከት ከቅዱስ ያሬድ ድርሳናት አንጻር በተሰኘው ጥናታቸውም አንድ ኦርቶዶክሳዊ ስብከት ሊያሟላቸው ከሚገባቸው መሠረታዊ ነጥቦች አንጻር የቅዱስ ያሬድን ድርሰቶች በመመዘን አቅርበዋል፡፡
ሊቀ ጠበብት ተክሌ ሲራክ ባቀረቡት ጥናትም አራቱ የዜማ ዐበይት መንገዶች በሚል አጠር ያለ ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡ የቤተልሔም፤ የቆሜ፤ የአጫበርና የተጉለት ዜማዎችን በትውልድ ቅብብሎሽ በመከፋፈል ለማሳየት ጥረት አድርገዋል፡፡ በተለይ የተጉለት ዜማ በመጥፋት ላይ እንደሚኝና በአሁኑ ወቅት አንድ አባት ብቻ እንደቀሩና ለትውልድ ለማሸጋገር ብዙ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የመጨረሻው ጥናት በሙዚቃው ዘርፍ ባለሙያ የሆነውና በቅዱስ ያሬድ ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ምርምር እያደረገ የሚገኘው ሠርፀ ፍሬ ስብሐት የቅዱስ ያሬድ ዜማ በባሕላዊውና በዘመናዊው ሙዚቃ ያለው ተጽእኖ በማስመልከት አጠር ያለ ጥናታዊ ዳሰሳ አድርገዋል፡፡
በቀረቡት አምስት ያህል ጥናቶች መነሻነት የጉባኤው ተሳታፊ በሆኑት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተስተናግደዋል፡፡
የውይይቱ መቋጫ የሆነውም የቅዱስ ያሬድ ታሪክና ሥራዎች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባሕል ድርጅት /UNESCO/ ለማስመዝገብና ለዓለም ለማስተዋወቅ ጥናቶች እንዲጠኑ በማድረግና በማስተባበር አንድ እልባት ላይ መድረስ እንዲቻል ከጠቅላይ ቤተ ክህነት፤ ከሊቃውንት ጉባኤ፤ ከሊቃውንት አባቶች፤ ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከሙዚቃ ባለሙያዎች እንዲሁም ከማኅበረ ቅዱሳን የተውጣጣ 17 አባላትን ያቀፈ ኮሚቴ እንዲዋቀር በማድረግ ዐውደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡
የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ የልደት በዓል አስመልክቶ የተዘጋጀ ዐውደ ጥናት ተከፈተ
ዲ/ን መርሻ አለኸኝ(ዶ/ር)
የቅዱስ ያሬድን 1500ኛ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ በማኅበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የተዘጋጀ ዐውደ ጥናት በግዮን ሆቴል ሳባ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከፈተ፡፡ በዐውደ ጥናቱ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የልዩ ልዩ መምሪያዎች ሓላፊዎች፣ በዋና ዋና አብነት ት/ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራንና የመንግሥትና ልዩ ልዩ ተቋማት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው ሊቃውንት ተገኝተዋል፡፡
ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ማኅበሩ ቅዱሳት መካናት ራሳቸውን ችለው የሚተዳደሩባቸውን ዘላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግበር ለአብነት መምህራንና ተማሪዎች ድጋፍ በማድረግ ከፍተኛ ሥራ አየሠራ እንደኾነ ከገለጹ በኋላ፤ ሊቁ ለሀገራችን ከሰጠው አበርክቶ አንጻር ማኅበሩ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን የቅዱስ ያሬድን የ1500ኛ ዓመት የልደት በዓል በሰፊ ዝግጅት ለማክበር እንደወሰነ ገልጸዋል፡፡
አቶ ተስፋዬ ውብሸት የጠቅላይ ቤተ ክህነት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዐውደ ጥናቱን በንግግር ከፍተዋል፡፡ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ቅዱስ ያሬድ ለሀገራችን ካበረከተው አስተዋጽዖ አንጻር የልደት በዓሉ በዚህ መልኩ መከበሩ በእጅጉ ተገቢ እንደኾነ በመጥቀስ፤ ያዘጋጀውን ማኅበረ ቅዱሳንን ካመሰገኑ በኋላ ማኅበሩ በተለይ ቅዱሳት መካናትንና አድባራትን በመርዳት በኩል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲያግዝ ጥሪ አድርገዋል፡፡
በመቀጠልም አቶ ወርቅነህ አክሊሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ተወካይ የቅዱስ ያሬድ የዜማ ሀብት ከቤተ ክርስቲያኗ አልፎ የሀገር ሀብት በመኾኑ ሁሉም እንክብካቤ እና ጥበቃ እንዲያደርግለት፣ በሕይወት ያሉትን የዜማውን ሊቃውንት ከመንከባከብ ባሻገር መዳከም የሚታይበትን የዜማውን ሽግግር ለማንቃት ተረካቢዎችን ማፍራት እንደሚገባ በመግለጽ የጉባኤውን ታዳሚ ቀልብ የገዛ ንግግር አድርገዋል፡፡
ከዐውደ ጥናቱ መርሐ ግብር ለመረዳት እንደሚቻለው በቅዱስ ያሬድ ሕይወትና ዜማዎቹ ዙሪያ በዘርፉ ሊቃውንትና ተመራማሪዎች አምስት ያህል ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ነገ እሑድ ግንቦት 10 ቀን 2005 ዓ፡ም ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩን ጨምሮ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንትና ምእመናን በተገኙበት በሰፊው እንደሚዘከር ታውቋል፡፡
ጠቅላይ ቤተ ክህነት ደብሩ በ‹‹አጥማቂው›› ላይ የጣለውን እገዳ አጸና
በምሥራቅ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ሰላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያን ቅጽር ግቢ ‹‹ሲያጠምቅ›› በነበረው ግለሰብ ላይ ያሳለፈውን የእግድ ውሳኔ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አጸናው፡፡ ከደብሩ ሰበካ ጉባኤ ያገኘውን የእግድ ደብዳቤ መሠረት በማድረግ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በቁጥር 9474/756/2005 በቀን 08/09/05 ያወጣው ደብዳቤ ‹‹መ/ር ግርማ ወንድሙ ሰባኬ ወንጌልና አጥማቂ ነኝ፤ የማዳን ፈውስ አለኝ በማለት በሕገ ወጥ መንገድ እስከ አሁን ድረስ በደብሩ እያጠመቀ›› እንደሚገኝ ይገልጻል፡፡
በማከልም ቅዱስ ሲኖዶስ በሕገ ወጥ መንገድ የማዳን ፈውስ አለኝ በማለት በየደብሩ ቅጥር ግቢ በማሰባሰብ የሚያጠምቁትን በተመለከተ ያሳለፈውን የእግድ ውሳኔ በመጥቀስ፤ ‹‹መምህር ግርማ ወንድሙ በደብረ ሰላም ቅዱስ እሰጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚፈጽሙት የማጥመቅ ሥርዓትና የወንጌል አገልግሎት ሕገ ወጥ መኾኑን›› በአጽንዖት በመግለጽ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት በግለሰቡ ላይ ያሳለፈውን ውሳኔ እንዳጸናው ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም ከእግዱ ጋር በተያያዘ ሕዝበ ክርስቲያኑ የፀጥታ ችግር እንዳይገጥመው የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት ጥብቅ ክትትል በማድረግ ውሳኔውን ተግባራዊ እንዲያደርግ አሳስቧል፡፡ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ ለውሳኔው ተግባራዊነት አስፈላጊ ትብብር እንዲያደርጉ ለሚመለከታቸው የመንግሥት የፀጥታ አካላት ጥሪ አድርጓል፡፡ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እና የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት እግዱን ያስተላለፈበት ደብዳቤዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
ማእከላት ለኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጡ ተጠየቀ
ሚያዚያ 22 ቀን 2005 ዓ.ም.
በእንዳለ ደጀኔ
የማኅበረ ቅዱሳን ኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት ክፍል ማእከላት ለኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጡ የክፍሉ ሓላፊ አቶ የሸዋስ ማሞ አስታወቁ፡፡
በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ለሀገር ውስጥ ማእከላት ስለ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎትና አሠራር ዙሪያ ሚያዝያ 12 እና 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በተሰጠበት ወቅት ነበር ማእከላት አገልግሎቱን አጠናክረው መቀጠል የሚገባቸው መሆኑን የተገለጸው፡፡
ማእከላት የሒሳብ ክፍል አሠራራቸውንና የኦዲትና ኢንስፔክሽን ክፍሎቻቸውን ይበልጥ አጠናክረውና በሰው ኃይል አደራጅተው አገልግሎታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው በሥልጠናው ላይ ተገልጿል፡፡
ለማእከላት በርካታ ሥልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን የማእከላቱ የግንዛቤ መጠን መጠነኛ ለውጦችን ማምጣት መቻሉን አቶ የሸዋስ ገልጸው ማእከላቱ ለኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጡና ክፍሉንም በባለሙያ እንዲያጠናክሩ ጥሪያቸውን ያቀረቡት፡፡ የአገልግሎት ክፍሉ እና የሒሳብ ክፍሉ መጠናከር የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውና ለማእከላት ወጥ የሆነ የሒሳብ አያያዝ ሥርዓትም አዎንታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡
የአገልግሎት ክፍሉ የማኅበሩን ስልታዊ ዕቅድ ከማስፈጸም አኳያ የተለያዩ ድጋፎችን ለማእከላት የሚያደርግ መሆኑና በዕቅዱም ዘመን የራሱን የአገልግሎት ስልት ዘርግቶ እንደሚሠራ ነው ከሓላፊው ገለጻ የተረዳነው፡፡ ሚያዝያ 12 እና 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በተሰጠው ሥልጠና በሀገር ውስጥ ከሚገኙ ማእከላት ተወካዮች በሥልጠናው መሳተፋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ አባላት መንፈሳዋ ጉዞ አካሄዱ
ሚያዚያ 21 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዳዊት ደስታ
የማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል “መራሔ ፍኖት” በሚል መሪ ቃል በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተማሩ ላሉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መንፈሳዊ ጉዞ ወደ ሱሉልታ ደብረ ምሕረት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሚያዚያ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. አካሄደ፡፡
የጉዞውን ዓላማ አስመልክቶ አስተባባሪ የሆነው ሸዋለም ተክሉ ከዚህ ቀደም በግቢ ሲማሩ የነበሩ ተሞክሮአቸውን የሚያካፍሉበት፣ ተማሪዎች መንፈሳዊም ሆነ በሚማሩት ትምህርታቸው ያለባቸውን ጥያቄ የሚመለስበትና የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ሆነው ወደ ግቢ የማይመጡትን ተማሪዎችን በግቢ እየመጡ እንዲማሩ ለማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም ይህ የግቢ ጉባኤ አንድነት መርሐ ግብር ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ከጉዞው የሚጠበቀው ውጤት በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የዛሉ የመንፈስ ብርታት የሚያገኙበት፣ የግቢያት የአባላት ቁጥር ወደተሻለ እድገት እንዲመጣ ለማድረግ ነው ሲሉ አስተባባሪው ተናገረዋል፡፡
በዕለቱ በግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና በዘማርያም መዝሙር ቀርቢል፣ ትምህርተ ወንጌል የተሰጠ ሲሆን ግቢያቱ በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ የተጠየቁ ጥያቄች ምላሽ ተሰጥተውባቸዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ሲሳተፉ ያገኘናቸው ወጣት ዮዲት ተገኔ የሮያል ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተማሪ ስትሆን በዚህ ጉዞ ለመጀመሪያ ጊዜዬ ነው የተጓዝኩት፡፡ ጉዞው ትልቅ ነገር አስተምሮኛል፡፡ የሌሎችን ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ጋር አስተዋውቆኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እየተሠራ ያለውን ተግባር እንዳይ አድርጎኛል በማለት ገልጻለች፡፡
ሌላው የ5 ኪሎ ግቢ ጉባኤ ተማሪ የሆነው ናትናኤል ስዮም በጉዞው በመሳተፌ በውስጤ ይመላለስ የነበሩብኝ ጥያቄዎች ተመልሰውልኛል፡፡ እንደዚህ አይነት መርሐ ግብሮች ወጣቱን የሚያንፁ ስለሆነ ማኅበሩ አጠናክሮ ሊሠራበት የሚገባ ተግባር ነው፡፡ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ በጉዞው ላይ ከ60 በላይ ከሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የመጡ ከሁለት ሺህ በላይ ተጓዦች ተሳትፈዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጋር ልዩ ቃለ መጠይቅ አደረጉ
ሚያዚያ 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጋር በዓለ ትንሣኤን ምክንያት በማድረግ ልዩ ቃለ መጠይቅ አደረጉ፡፡ በዚህ አንድ ሰዓት የፈጀ ቃለ መጠይቅ ላይ ቅዱስነታቸው ስለ ልጅነት ጊዜያቸው ፣ በትምህርት ቤት ሳሉ ስለነበሯቸው ገጠመኞች ፣ ስለ ምንኩስና ሕይወት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስላሉ ልዩ ልዩ አስተዳደራዊና ችግሮች እና በተሠጣቸው ሓላፊነት ምን ሊሠሩ እንዳሰቡ ፣ ስለ ቅድስት ሀገር የርስት ጉዳይ ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመሥራት ስለታሰበው መፍትሔ እና ስለ ዕርቀ ሰላሙ ጉዳይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሠጡ ሲሆን ሙሉ ቃለ መጠይቁ በማኅበሩ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ከበዓለ ትንሣኤ ጀምሮ እንደሚቀርብ የማኅበሩ ሬድዮና ቴሌቪዥን ክፍል አስተባባሪ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ ገልጸዋል፡፡
የማኅበረ ቅዱሳን በኢቢኤስ ቴሌቪዥን መርሐ ግብር ከተጀመረበት የካቲት ፲፮ ፳፻፭ ጀምሮ እስከ በዓለ ትንሣኤ ድረስ ዐሥር ልዩ ልዩ መርሐ ግብራትን ያስተላለፈ ሲሆን የተጀመረበትን ሰዓት በማስተካከልም መርሐ ግብሩ ዘወትር እሑድ ከ5፡30 – 6፡00 ሰዓት ድረስ ሆኗል፡፡ የተላለፉ ዝግጅቶችም በኢንተርኔት http:// eotc.tv ላይ በማንኛውም ሰዓት መከታተል ይቻላል፡፡ ዝግጅቶቹን በመመልከት በስልክና በኢንተርኔት አድራሻዎቻችን ገንቢ አስተያየቶቻችሁን የሠጣችሁን ምዕመናንን እያመሰገንን ለበለጠ ሥራ ረድኤተ እግዚአብሔር እንዳይለየን ጸልዩልን ሲሉ የክፍሉ አስተባባሪ ገልጸዋል፡፡